በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ሐዋርያው ጳውሎስ “ወደ ሦስተኛው ሰማይ” እንዲሁም “ወደ ገነት [የተነጠቀው]” በምን መንገድ ነው?—2 ቆሮ. 12:2-4

በ2 ቆሮንቶስ 12:2, 3 ላይ ጳውሎስ “ወደ ሦስተኛው ሰማይ [ስለተነጠቀ]” ሰው ተናግሯል። ይህ ሰው ማን ነው? ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ አምላክ እሱን ሐዋርያ አድርጎ እየተጠቀመበት እንዳለ በአጽንዖት ገልጿል። (2 ቆሮ. 11:5, 23) ከዚያም ‘ከጌታ ስለተቀበላቸው ተአምራዊ ራእዮችና ጌታ ስለገለጠለት መልእክቶች’ ተናግሯል። ጳውሎስ ከዚህ ራእይ ጋር በተያያዘ ሌሎች ወንድሞችን አልጠቀሰም። በመሆኑም ራእዮችና መልእክቶች እንደተቀበለ ሰው አድርጎ የተናገረው ስለ ራሱ ነው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው።—2 ቆሮ. 12:1, 5

ስለዚህ “ወደ ሦስተኛው ሰማይ” እንዲሁም “ወደ ገነት [የተነጠቀው]” ሰው ጳውሎስ ነው። (2 ቆሮ. 12:2-4) ጳውሎስ ‘የተገለጡልኝ መልእክቶች’ የሚለውን አገላለጽ መጠቀሙ የተመለከታቸው ነገሮች ወደፊት የሚፈጸሙ መሆናቸውን ያመለክታል።

ጳውሎስ “ሦስተኛው ሰማይ” በማለት የገለጸው ነገር ምንድን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሰማይ” የሚለው ቃል ግዑዙን ሰማይ ሊያመለክት ይችላል። (ዘፍ. 11:4፤ 27:28፤ ማቴ. 6:26) ይሁን እንጂ “ሰማይ” ሌሎች ነገሮችን ለማመልከትም ተሠርቶበታል። አንዳንድ ጊዜ ሰብዓዊ አገዛዝን ያመለክታል። (ዳን. 4:20-22) አሊያም ደግሞ እንደ አምላክ መንግሥት ያለውን መለኮታዊ አገዛዝ ሊያመለክት ይችላል።—ራእይ 21:1

ጳውሎስ ‘ሦስተኛውን ሰማይ’ እንዳየ ተናግሯል። ይህ ምን ያመለክታል? አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ሐሳብ ለማጉላት፣ አጽንዖት ለመስጠት ወይም ክብደት ለመጨመር ያንን ሐሳብ ሦስት ጊዜ ይደጋግመዋል። (ኢሳ. 6:3፤ ሕዝ. 21:27፤ ራእይ 4:8) ከዚህ አንጻር ጳውሎስ ስለ “ሦስተኛው ሰማይ” ሲናገር ከፍ ያለ ወይም የላቀ አገዛዝን ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስና በ144,000 ተባባሪ ገዢዎች የሚመራውን መሲሐዊ መንግሥት ማመልከቱ ሳይሆን አይቀርም። (የጥቅምት 15, 2004 መጠበቂያ ግንብ፣ ገጽ 8 አን. 5⁠ን ተመልከት።) ሐዋርያው ጴጥሮስ አምላክ በገባው ቃል መሠረት “አዲስ ሰማያት” እንደምንጠባበቅ ሲገልጽ ስለ መሲሐዊው መንግሥት እየተናገረ ነበር።—2 ጴጥ. 3:13

ጳውሎስ የጠቀሰው “ገነት” ምን ያመለክታል?

“ገነት” የሚለው ቃልም ቢሆን የተለያዩ ነገሮችን ሊያመለክት ይችላል፦ (1) ገነት የሰው ልጆች የመጀመሪያ መኖሪያ ከመሆኗ አንጻር “ገነት” የሚለው ቃል ወደፊት የሚኖረውን ምድራዊ ገነት ሊያመለክት ይችላል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። (2) የአምላክ ሕዝቦች በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖራቸውን መንፈሳዊ ሁኔታ ሊያመለክት ይችላል። (3) በራእይ 2:7 ላይ ‘የአምላክ ገነት’ ተብሎ የተገለጸውን በሰማይ ያለ አስደሳች ሁኔታ ሊያመለክት ይችላል።—የሐምሌ 15, 2015 መጠበቂያ ግንብ፣ ገጽ 8 አን. 8⁠ን ተመልከት።

በ2 ቆሮንቶስ 12:4 ላይ ጳውሎስ በራእይ የተመለከተውን ነገር ሲገልጽ እነዚህን ሦስት የተለያዩ ገጽታዎች እያመለከተ ሊሆን ይችላል።

ለማጠቃለል ያህል፦

በ2 ቆሮንቶስ 12:2 ላይ የተጠቀሰው “ሦስተኛው ሰማይ” የሚያመለክተው “አዲስ ሰማያት” ተብለው የተገለጹት ኢየሱስ ክርስቶስና 144,000ዎቹ የሚያስተዳድሩትን መሲሐዊ መንግሥት ሳይሆን አይቀርም።—2 ጴጥ. 3:13

“ሦስተኛው ሰማይ” የተባለው ይህ መንግሥት ከፍ ያለ ወይም የላቀ አገዛዝ ስለሆነ ነው።

ጳውሎስ በራእይ “ተነጥቆ” የተወሰደበት “ገነት” (1) ወደፊት ቃል በቃል በምድር ላይ የሚኖረውን ገነት፣ (2) ምድር ገነት በምትሆንበት ጊዜ የሚኖረውንና አሁን ካለው መንፈሳዊ ገነት እጅግ የላቀ የሚሆነውን መንፈሳዊ ገነት እንዲሁም (3) በሰማይ ያለውን “የአምላክ ገነት” የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። ወደፊት በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ሦስቱም በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ይኖራሉ።

በመሆኑም አዲሱ ዓለም አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን አካትቶ የያዘ ይሆናል። ይህ አዲስ ዝግጅት በሰማይ ያለውን የአምላክ መንግሥት አስተዳደርና ገነት በሆነች ምድር ላይ ይሖዋን የሚያገለግሉ የሰው ልጆችን ያቀፈ ነው።