በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በደንብ አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

አምላክ ሥቃያችን እንደሚሰማው የሚያሳይ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አለ?

አምላክ የጥንቶቹ እስራኤላውያን በግብፅ ባርነት ውስጥ ሳሉ የሚደርስባቸውን ሥቃይ ያውቅ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ጭንቀታቸው ይሰማው ነበር። (ዘፀ. 3:7፤ ኢሳ. 63:9) እኛ የሌሎችን ችግር እንደ ራሳችን አድርገን የመመልከት ችሎታ የኖረን በአምላክ መልክ ስለተፈጠርን ነው። አምላክ ሊወደን የሚገባ ሰዎች እንዳልሆንን በሚሰማን ጊዜም እንኳ እሱ ስሜታችንን ይረዳልናል።—wp18.3 ከገጽ 8-9

ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች ሰዎች ጭፍን ጥላቻን እንዲያስወግዱ የረዱት እንዴት ነው?

በኢየሱስ ዘመን የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን ጭፍን ጥላቻ ነበራቸው። ክርስቶስ ትሑት የመሆንን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ተናግሯል፤ እንዲሁም በዘር መኩራት ተገቢ እንዳልሆነ አስተምሯል። ተከታዮቹ አንዳቸው ሌላውን እንደ ወንድም ሊያዩ እንደሚገባ አሳስቧል።—w18.06 ከገጽ 9-10

አምላክ ሙሴን ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ከከለከለበት ምክንያት ምን ትምህርት እናገኛለን?

ሙሴ ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና ነበረው። (ዘዳ. 34:10) እስራኤላውያን ለ40 ዓመታት ያህል በምድረ በዳ ያደረጉትን ጉዞ ሊያጠናቅቁ በተቃረቡበት ወቅት ውኃ በማጣታቸው ምክንያት ለሁለተኛ ጊዜ አጉረመረሙ። በመሆኑም አምላክ ዓለቱን እንዲናገረው ሙሴን አዘዘው። ሙሴ ግን ዓለቱን ከመናገር ይልቅ መታው። በዚህ ጊዜ ይሖዋ በጣም ተቆጣ። ይሖዋ የተቆጣው ሙሴ የተሰጠውን መመሪያ ስላልተከተለ ወይም ተአምሩን ለፈጸመው አምላክ ክብር ስላልሰጠ ሊሆን ይችላል። (ዘኁ. 20:6-12) ይህ ታሪክ ይሖዋን መታዘዝና ለእሱ ክብር መስጠት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስተምረናል።—w18.07 ከገጽ 13-14

የሰዎችን ውጫዊ ገጽታ አይተን ከፈረድን በቀላሉ ልንሳሳት የምንችለው ለምንድን ነው?

ስለ ሌሎች ባለን አመለካከት ላይ ብዙውን ጊዜ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እነሱም የሰዎች ዘር ወይም ብሔር፣ የኑሮ ደረጃ እንዲሁም ዕድሜ ናቸው። በዚህ ረገድ ከአድልዎ ነፃ የሆነውን አምላካችንን ለመምሰል መሞከራችን አስፈላጊ ነው! (ሥራ 10:34, 35)—w18.08 ከገጽ 8-12

አረጋውያን ክርስቲያኖች ሌሎችን መርዳት የሚችሉባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

ቀደም ሲል የነበራቸውን ኃላፊነት ያጡ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች አሁንም በአምላክ ዓይን ውድ ናቸው፤ ደግሞም ሌሎችን ለመርዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ። የማያምኑ የትዳር ጓደኞችን ሊረዱ፣ የቀዘቀዙ ክርስቲያኖችን ሊያበረታቱ፣ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ሊያስጠኑና አገልግሎታቸውን ሊያሰፉ ይችላሉ።—w18.09 ከገጽ 8-11

“በማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን” ውስጥ የትኞቹ መሣሪያዎች ተካተዋል?

ከማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን መካከል የአድራሻ ካርዶችና መጋበዣዎች ይገኙበታል። በተጨማሪም ማራኪ በሆነ መንገድ የተዘጋጁ ስምንት ትራክቶች እንዲሁም መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ይገኛሉ። የተወሰኑ ብሮሹሮች፣ ሁለት ዋና ዋና የማስጠኛ መጽሐፎችና አራት ቪዲዮዎችም አሉ፤ ከቪዲዮዎቹ መካከል መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የሚለው ይገኝበታል።—w18.10 ገጽ 16

ምሳሌ 23:23 በሚለው መሠረት አንድ ክርስቲያን ‘እውነትን መግዛት’ የሚችለው እንዴት ነው?

እውነትን ለመግዛት ገንዘብ መክፈል አያስፈልገንም። ሆኖም እውነትን ለማግኘት ጊዜያችንን መሠዋትና ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።—w18.11 ገጽ 4

ሆሴዕ ሚስቱን ጎሜርን ከያዘበት መንገድ ምን እንማራለን?

ጎሜር በተደጋጋሚ ምንዝር ብትፈጽምበትም ሆሴዕ ይቅርታ ያደረገላት ከመሆኑም ሌላ ጋብቻቸውን አላፈረሰም። አንድ ባለትዳር የፆታ ብልግና ቢፈጽም ታማኝ የሆነው ወገን ይቅርታ ለማድረግ ሊወስን ይችላል። ታማኝ የሆነው የትዳር ጓደኛ ከበደለኛው ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸሙን ከቀጠለ ቅዱስ ጽሑፋዊ ፍቺ ለመፈጸም መሠረት የሆነው ነገር ይወገዳል።—w18.12 ገጽ 13