በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ገነት ውስጥ እንገናኝ!”

“ገነት ውስጥ እንገናኝ!”

“ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ።”—ሉቃስ 23:43

መዝሙሮች፦ 145, 139

1, 2. ሰዎች ስለ ገነት ምን የተለያየ አመለካከት አላቸው?

በስፍራው የሚታየው ነገር ልብ የሚነካ ነበር። በሶል፣ ኮሪያ በተደረገ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከውጭ አገር የመጡት ልዑካን ስብሰባው ካበቃ በኋላ ስታዲየሙን ለቀው ሲወጡ በዚያ አገር የሚኖሩት ወንድሞች ከበቧቸው። አብዛኞቹ እጃቸውን እያውለበለቡ “ገነት ውስጥ እንገናኝ!” ይሏቸው ነበር። ለመሆኑ እነዚህ ወንድሞች እየተናገሩ የነበረው ስለ የትኛው ገነት ነው?

2 በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች ስለ ገነት የተለያየ አመለካከት አላቸው። አንዳንዶቹ ገነት በምናብ ዓለም ያለ ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ ደስታና እርካታ የሚያገኙበት ቦታ ሁሉ ገነት እንደሆነ ይናገራሉ። በድግስ ቦታ ላይ የተገኘ አንድ በጣም የተራበ ሰው የቀረበውን ምግብ ሲያይ ገነት ውስጥ እንደገባ ሊሰማው ይችላል። በ19ኛው መቶ ዘመን አንዲት ጎብኚ በዱር አበቦች የተሞላ ሸለቆ ስታይ “ይሄማ ገነት ነው!” በማለት ተናግራለች። ያ ስፍራ በየዓመቱ ከ15 ሜትር በላይ በረዶ የሚጥልበት ቢሆንም እስካሁን ድረስ ፓራዳይዝ (ገነት) ተብሎ ይጠራል። አንተስ ገነት የሚለውን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? በዚያ ለመኖር ትጓጓለህ?

3. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ገነት የሚናገር ሐሳብ የምናገኘው የት ነው?

3 መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በፊት ስለነበረውም ሆነ ወደፊት ስለሚመጣው ገነት ይናገራል። እንዲያውም ስለ ገነት የሚናገር ሐሳብ የምናገኘው ገና በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ነው። ከላቲን የተተረጎመው የካቶሊክ ዱዌይ ቨርዥን ዘፍጥረት 2:8 ላይ እንዲህ ይላል፦ “በመጀመሪያ ጌታ አምላክ የደስታ ገነትን ተከለ፤ የሠራውንም [አዳም] በዚያ አስቀመጠው።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) የዕብራይስጡ ጽሑፍ ‘የኤደን የአትክልት ስፍራ’ ይላል። ኤደን የሚለው ቃል “ደስታ” የሚል ትርጉም አለው፤ በእርግጥም ያ የአትክልት ስፍራ በጣም አስደሳች ነበር። የተትረፈረፈ ምግብና ውብ መልክዓ ምድር ያለው ሲሆን ሰዎች ከእንስሳት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ነበራቸው።—ዘፍ. 1:29-31

4. የኤደን የአትክልት ስፍራን ገነት ብለን ልንጠራው የምንችለው ለምንድን ነው?

4 “የአትክልት ስፍራ” ተብሎ ለተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል አቻ ሆኖ የገባው የግሪክኛ ቃል ፓራዲሶስ የሚለው ነው። በማክሊንቶክና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ የግሪክኛውን ፓራዲሶስ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “አንድ ግሪካዊ ተጓዥ ይህን ቃል ሲሰማ በአእምሮው ውስጥ የሚስለው እንደሚከተለው ያለውን ቦታ ነበር፦ ጉዳት እንዳይደርስበት የታጠረ ሰፊና የተንጣለለ መናፈሻ፣ ምንም ያልተነካ የተፈጥሮ ውበት ያለው፣ ግርማ ሞገስ የተላበሱና ፍሬያማ የሆኑ ዛፎች የሞሉበት፣ ኩልል ያሉ ወንዞች የሚያጠጡት እንዲሁም በወንዞቹ ዳርቻ የድኩላ ወይም የበግ መንጋ የተሰማራበት ስፍራ።”—ከዘፍጥረት 2:15, 16 ጋር አወዳድር።

5, 6. የሰው ልጅ በገነት ውስጥ የመኖር መብቱን ያጣው ለምንድን ነው? ይህስ ምን ጥያቄ ያስነሳል?

5 አምላክ አዳምና ሔዋንን እንዲህ ባለ ገነት ውስጥ እንዲኖሩ አድርጓቸው ነበር፤ ሆኖም ቆይታቸው ብዙ አልዘለቀም። ለምን? የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ በዚያ ለመኖር የሚያስችላቸውን ብቃት አጓደሉ። በመሆኑም እነሱም ሆኑ ዘሮቻቸው በገነት ውስጥ የመኖር መብታቸውን አጡ። (ዘፍ. 3:23, 24) የአትክልት ስፍራው ከዚያ በኋላ ማንም ሰው ባይኖርበትም እስከ ኖኅ የጥፋት ውኃ ድረስ የቆየ ይመስላል።

6 አንዳንዶች ‘የሰው ልጅ ገነት በሆነች ምድር ላይ ዳግመኛ የመኖር አጋጣሚ ያገኝ ይሆን?’ የሚል ጥያቄ ይፈጠርባቸው ይሆናል። ማስረጃዎች ምን ያሳያሉ? ከምትወዷቸው ሰዎች ጋር በገነት ውስጥ እንደምትኖሩ የሚያረጋግጥ ምን አሳማኝ ማስረጃ አለ? ወደፊት ምድር ገነት እንደምትሆን እርግጠኛ የሆናችሁበትን ምክንያት ማስረዳት ትችላላችሁ?

ምድር ገነት እንደምትሆን የሚያሳዩ ማስረጃዎች

7, 8. (ሀ) አምላክ ለአብርሃም ምን ቃል ገብቶለታል? (ለ) አምላክ የገባው ቃል አብርሃምን ምን ብሎ እንዲያስብ አድርጎት ሊሆን ይችላል?

7 የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የመጀመሪያውን ገነት የፈጠረው አምላክ፣ በመንፈሱ መሪነት ያጻፈውን መጽሐፍ መመርመራችን ምክንያታዊ ነው። ለምሳሌ አምላክ ለወዳጁ ለአብርሃም የነገረውን ሐሳብ እንመልከት። አምላክ የአብርሃምን ዘር “በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ” እንደሚያበዛው ተናግሮ ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ ለአብርሃም የሚከተለውን ትልቅ ትርጉም ያዘለ ተስፋ ሰጥቶት ነበር፦ “ቃሌን ስለሰማህ የምድር ብሔራት ሁሉ በዘርህ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ።” (ዘፍ. 22:17, 18) አምላክ ለአብርሃም ልጅና የልጅ ልጅም ይህንኑ ተስፋ ሰጥቷቸዋል።—ዘፍጥረት 26:4⁠ን እና 28:14ን አንብብ።

8 አብርሃም የሰው ልጆች የመጨረሻ ሽልማታቸውን የሚያገኙት ሰማይ ላይ ባለ ገነት ውስጥ ነው ብሎ ተስፋ ያደርግ እንደነበር የሚጠቁም ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። በመሆኑም አብርሃም “የምድር ብሔራት ሁሉ” እንደሚባረኩ ሲነገረው እነዚህ ብሔራት በረከቱን የሚያገኙት ምድር ላይ ነው ብሎ አስቦ መሆን አለበት። በተጨማሪም ይህን ቃል የገባው አምላክ ስለሆነ አብርሃም “የምድር ብሔራት ሁሉ” ወደፊት የተሻለ ሕይወት ይኖራቸዋል ብሎ ለመጠበቅ የሚያስችል በቂ ምክንያት ነበረው። ምድር ገነት እንደምትሆን የሚያሳዩ ሌሎች ማስረጃዎችስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይኖሩ ይሆን?

9, 10. ወደፊት ምድር ገነት እንደምትሆን የሚጠቁሙት የትኞቹ ከጊዜ በኋላ የተሰጡ ተስፋዎች ናቸው?

9 የአብርሃም ዘር የሆነው ዳዊት ወደፊት “ክፉ አድራጊዎች” የሚጠፉበትና ‘ክፉዎች የማይኖሩበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ተናግሯል። (መዝ. 37:1, 2, 10) “የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።” በተጨማሪም ዳዊት በመንፈስ መሪነት “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” የሚል ትንቢት ተናግሯል። (መዝ. 37:11, 29፤ 2 ሳሙ. 23:2) እነዚህ ተስፋዎች የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ በሚፈልጉ ሰዎች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳደሩባቸው ይመስልሃል? የአምላክ አገልጋዮች፣ ጻድቃን ብቻ በምድር ላይ የሚኖሩ ከሆነ በኤደን የአትክልት ስፍራ የነበረው ዓይነት ገነት መልሶ ይቋቋማል ብለው ተስፋ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ምክንያት ነበራቸው።

10 ሆኖም ይሖዋን እንደሚያገለግሉ ይናገሩ የነበሩት አብዛኞቹ እስራኤላውያን በጊዜ ሂደት ለይሖዋና ለእውነተኛው አምልኮ ጀርባቸውን መስጠት ጀመሩ። በመሆኑም አምላክ ባቢሎናውያን ሕዝቡን እንዲወሩ፣ ምድሪቷን እንዲያጠፉና ብዙዎቹን በግዞት እንዲወስዱ አደረገ። (2 ዜና 36:15-21፤ ኤር. 4:22-27) በዚያ ጊዜም እንኳ የአምላክ ነቢያት፣ ከ70 ዓመታት በኋላ ሕዝቡ ወደ ትውልድ አገሩ እንደሚመለስ ተንብየው ነበር። እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ሆኖም በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛም ትልቅ ትርጉም አላቸው። ከእነዚህ ትንቢቶች መካከል አንዳንዶቹን ስንመረምር ምድር ገነት እንደምትሆን በሚያሳዩ ማስረጃዎች ላይ ትኩረት ለማድረግ ሞክሩ።

11. ኢሳይያስ 11:6-9 የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ሆኖም ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን ጥያቄ ይነሳል?

11 ኢሳይያስ 11:6-9ን አንብብ። አምላክ ሕዝቦቹ ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ከባድና አደገኛ ሁኔታዎች እንደማያጋጥሟቸው እንዲሁም አራዊት ወይም የአውሬነት ባሕርይ ያላቸው ሰዎች ጥቃት ይሰነዝሩብኛል የሚል ስጋት ሊያድርባቸው እንደማይገባ በኢሳይያስ በኩል አስቀድሞ ነግሯቸው ነበር። ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች የሚያሰጋቸው ምንም ነገር አይኖርም። ይህ ትንቢት በኤደን ገነት ውስጥ የነበረውን ሁኔታ አያስታውሰንም? (ኢሳ. 51:3) በተጨማሪም አምላክ በኢሳይያስ በኩል የተናገረው ትንቢት “ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን ምድርም በይሖዋ እውቀት ትሞላለች” ይላል፤ በይሖዋ እውቀት የሚሞላው የእስራኤል ብሔር ብቻ ሳይሆን መላዋ ምድር እንደሆነች ልብ በል። ይህ የሚሆነው መቼ ነው?

12. (ሀ) ከባቢሎን ምርኮ የተመለሱት ሰዎች ምን በረከቶች አግኝተዋል? (ለ) ኢሳይያስ 35:5-10 ሌላ ፍጻሜ እንዳለው የሚጠቁመው ምንድን ነው?

12 ኢሳይያስ 35:5-10ን አንብብ። ኢሳይያስ ከግዞት የተመለሱት ሰዎች ከእንስሳትም ሆነ ከሰዎች ጥቃት እንደማይሰነዘርባቸው በድጋሚ ተናግሯል። የሚኖሩበት ምድር ልክ እንደ ኤደን ገነት በቂ ውኃ ስለሚያገኝ የተትረፈረፈ ምርት ይሰጣል። (ዘፍ. 2:10-14፤ ኤር. 31:12) ሆኖም የዚህ ትንቢት ፍጻሜ ይህ ብቻ ነው? ከግዞት የተመለሱት ሰዎች ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከሕመማቸው እንደተፈወሱ የሚያሳይ ማስረጃ የለም። ለምሳሌ ዓይነ ስውራን ዓይናቸው አልበራም። በመሆኑም አምላክ ይህን ተስፋ የሰጠው የታመሙ ሰዎችን ቃል በቃል የሚፈውስበት ጊዜ እንደሚመጣ ለመጠቆም ነበር።

13, 14. ከግዞት የተመለሱት እስራኤላውያን በኢሳይያስ 65:21-23 ላይ የሚገኘው ትንቢት ሲፈጸም የተመለከቱት እንዴት ነው? ሆኖም ገና ፍጻሜውን ያላገኘው የዚህ ትንቢት የትኛው ክፍል ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

13 ኢሳይያስ 65:21-23ን አንብብ። አይሁዳውያኑ ከግዞት ሲመለሱ ምቹ መኖሪያ ቤት፣ የለማ መሬት ወይም የወይን እርሻ አልጠበቃቸውም። ሆኖም አምላክ ስለባረካቸው ከጊዜ በኋላ ሁኔታቸው ተለውጧል። በሠሯቸው ቤቶች ውስጥ መኖር ሲጀምሩ ምን ያህል እንደተደሰቱ መገመት እንችላለን! እህል ማምረትና የተትረፈረፈ ምርት መሰብሰብ ይችሉ ነበር።

14 በዚህ ትንቢት ውስጥ የሚገኝ አንድ አስፈላጊ ነጥብ እንመልከት። ትንቢቱ ዕድሜያችን “እንደ ዛፍ ዕድሜ” የሚሆንበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። ታዲያ እንዲህ ያለ ጊዜ ይመጣ ይሆን? አንዳንድ ዛፎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ይኖራሉ። የሰው ልጆች እንዲህ ያለ ዕድሜ እንዲኖራቸው ጤነኞች ሊሆኑ ይገባል። ኢሳይያስ በትንቢቱ ላይ የገለጸው ዓይነት ሕይወት መኖር ከቻሉ ሕይወታቸው እጅግ አስደሳች ይሆናል! ደግሞስ ገነት ማለት ይህ አይደል? በዚያን ጊዜ ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኛል!

ኢየሱስ ስለ ገነት የሰጠው ተስፋ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው? (አንቀጽ 15, 16⁠ን ተመልከት)

15. በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ የተጠቀሱትን አስደሳች ተስፋዎች ጠቅለል አድርገህ ግለጽ።

15 እስካሁን የተመለከትናቸው ትንቢቶች ወደፊት ምድር ገነት እንደምትሆን የሚጠቁሙት እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክሩ፦ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በአምላክ የተባረኩ ይሆናሉ። ማንም ከአውሬዎች ወይም የአውሬ ባሕርይ ካላቸው ሰዎች ጥቃት ይሰነዘርብኛል ብሎ አይሰጋም። ዓይነ ስውራን፣ መስማት የተሳናቸውና አንካሶች ይፈወሳሉ። ሰዎች የራሳቸውን ቤት የሚሠሩ ከመሆኑም ሌላ እህል ማምረትና የተትረፈረፈ ምርት መሰብሰብ ይችላሉ። ዕድሜያቸው ከዛፍ ዕድሜ የበለጠ ይሆናል። አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ጊዜ እንደሚመጣ ይጠቁማል። ሆኖም አንዳንዶች እነዚህን ትንቢቶች በዚህ መልኩ ለመረዳት የሚያስችል በቂ ማስረጃ እንደሌለ ይሰማቸዋል። እንዲህ ለሚሉ ሰዎች ምን ብለህ ትመልሳለህ? ምድር ገነት እንደምትሆን ተስፋ ለማድረግ የሚያስችል ምን አሳማኝ ማስረጃ አለህ? በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቁ ሰው አስተማማኝ ማስረጃ ሰጥቶናል።

በገነት ትሆናለህ!

16, 17. ኢየሱስ ስለ ገነት የተናገረው በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነበር?

16 ኢየሱስ ያለጥፋቱ ተከሶ እንጨት ላይ በተሰቀለበት ጊዜ፣ ሁለት አይሁዳዊ ወንጀለኞች በቀኙና በግራው ተሰቅለው ነበር። አንደኛው ወንጀለኛ ኢየሱስ ንጉሥ መሆኑን በመገንዘብ ከመሞቱ በፊት “ኢየሱስ ሆይ፣ ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” የሚል ጥያቄ አቀረበ። (ሉቃስ 23:39-42) በሉቃስ 23:43 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የሰጠው ምላሽ የእኛንም የወደፊት ሕይወት የሚመለከት ነው። በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ምሁራን ይህን ጥቅስ “እውነት እልሃለሁ፣ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት ተርጉመውታል። በዚህ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ነጠላ ሰረዙ መግባት ያለበት “ዛሬ” ከሚለው ቃል በፊት ነው ወይስ በኋላ የሚለውን በተመለከተ ተርጓሚዎች የተለያየ አመለካከት አላቸው። ለመሆኑ ኢየሱስ “ዛሬ” የሚለውን ቃል የተጠቀመበት እንዴት ነው?

17 በዘመናችን ያሉ በርካታ ቋንቋዎች የአንድን ዓረፍተ ነገር ትክክለኛ ትርጉም ለማስተላለፍ ወይም መልእክቱን ግልጽ ለማድረግ ነጠላ ሰረዝ ይጠቀማሉ። ጥንታዊ የሚባሉት በእጅ የተገለበጡ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ግን ሥርዓተ ነጥቦችን ወጥ በሆነ መንገድ አይጠቀሙም። ይህም የሚከተለውን ጥያቄ ያስነሳል፦ ኢየሱስ ያለው “እውነት እልሃለሁ፣ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ነው ወይስ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ”? ተርጓሚዎች ነጠላ ሰረዙን የሚያስገቡት ኢየሱስ የተናገረውን ነገር በተረዱበት መንገድ ላይ ተመሥርተው ሲሆን ሁለቱም አቀማመጦች በዛሬው ጊዜ በስፋት በተሰራጩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ይገኛሉ።

18, 19. ኢየሱስ ምን ማለቱ እንደነበር ለማወቅ የሚረዳን ምንድን ነው?

18 ሆኖም ኢየሱስ ቀደም ሲል ተከታዮቹን “የሰው ልጅ . . . በምድር ልብ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይቆያል” እንዳላቸው ማስተዋል ያስፈልጋል። በተጨማሪም “የሰውን ልጅ ለሰዎች አሳልፈው ይሰጡታል፤ እነሱም ይገድሉታል፤ እሱም በሦስተኛው ቀን ይነሳል” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 12:40፤ 16:21፤ 17:22, 23፤ ማር. 10:34) ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህ እንደተፈጸመ ገልጿል። (ሥራ 10:39, 40) በመሆኑም ኢየሱስ በሞተበት ዕለት ወደ ገነት አልገባም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ከሞት እስኪያስነሳው ድረስ “በመቃብር [ወይም “በሐዲስ”]” ውስጥ ነበር።—ሥራ 2:31, 32 ግርጌ *

19 በመሆኑም ኢየሱስ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ” የሚሉትን ቃላት የተጠቀመባቸው ለወንጀለኛው የሚሰጠውን ተስፋ ከመናገሩ በፊት እንደ መንደርደሪያ አድርጎ እንደሆነ መረዳት እንችላለን። እንዲህ ዓይነቱ አገላለጽ በሙሴ ዘመንም እንኳ የተለመደ ነበር። ለምሳሌ ሙሴ “እኔ ዛሬ የማዝህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ” በማለት ተናግሯል።—ዘዳ. 6:6፤ 7:11፤ 8:1, 19፤ 30:15

20. ኢየሱስ የሰጠውን መልስ የምንረዳበትን መንገድ የሚደግፍ ምን ማስረጃ አለ?

20 በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖር አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ ኢየሱስ የሰጠውን ምላሽ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “እዚህ ላይ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ቃል ‘ዛሬ’ የሚለው ሲሆን ጥቅሱ መነበብ ያለበት ‘እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ’ ተብሎ ነው። ይህ ቃል የተገባው በዚያ ዕለት ነው፤ ፍጻሜውን የሚያገኘው ደግሞ ወደፊት ነው። ይህ በምሥራቃውያን ዘንድ የተለመደ የአነጋገር ዘይቤ ሲሆን ቃል የተገባው በዚያ ዕለት እንደሆነና የተሰጠው ተስፋ መፈጸሙ እንደማይቀር ለመጠቆም የሚያገለግል ነው።” ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ በአምስተኛው መቶ ዘመን የተዘጋጀ የሲሪያክ ትርጉም ኢየሱስ የሰጠውን መልስ “አሜን፣ ዛሬ እንደምልህ አንተ ከእኔ ጋር በኤደን የአትክልት ስፍራ ትሆናለህ” በማለት ተርጉሞታል። ይህ ተስፋ ሁላችንንም የሚያበረታታ ነው።

21. ወንጀለኛው ምን አጋጣሚ አላገኘም? ለምንስ?

21 ሞት አፋፍ ላይ የነበረው ያ ወንጀለኛ ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ በመንግሥተ ሰማያት ከእሱ ጋር አብረው እንደሚሆኑ የገባላቸውን ቃል እንደማያውቅ ግልጽ ነው። (ሉቃስ 22:29) ከዚህም በላይ ይህ ወንጀለኛ ገና ለመጠመቅ እንኳ አልበቃም ነበር። (ዮሐ. 3:3-6, 12) በመሆኑም ኢየሱስ ቃል የገባለት ስለ ምድራዊ ገነት እንደሆነ መረዳት እንችላለን። ከዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ወደ ገነት ስለተነጠቀ’ ሰው በራእይ እንዳየ ተናግሮ ነበር። (2 ቆሮ. 12:1-4) ከዚያ ወንጀለኛ በተለየ ሐዋርያው ጳውሎስና ሌሎች ታማኝ ሐዋርያት ወደ ሰማይ ሄደው ከኢየሱስ ጋር በመንግሥቱ እንዲገዙ ተመርጠዋል። ሆኖም ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው ወደፊት ስለሚመጣ “ገነት” ነው። * ለመሆኑ ይህ ገነት የሚመጣው ምድር ላይ ነው? አንተስ እዚያ የመኖር አጋጣሚ ታገኝ ይሆን?

ምን ተስፋ ማድረግ ትችላለህ?

22, 23. የትኛውን ተስፋ በጉጉት መጠባበቅ ትችላለህ?

22 ዳዊት “ጻድቃን ምድርን [የሚወርሱበት]” ጊዜ እንደሚመጣ አስቀድሞ እንደተናገረ ልብ በል። (መዝ. 37:29፤ 2 ጴጥ. 3:13) ዳዊት ምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር አስማምተው ስለሚመሩበት ጊዜ መናገሩ ነበር። በኢሳይያስ 65:22 ላይ ያለው ትንቢት “የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናል” ይላል። ይህም ሰዎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት እንደሚኖሩ ያመለክታል። እንዲህ ያለ ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ማድረግ ትችላለህ? እንዴታ! ምክንያቱም በራእይ 21:1-4 መሠረት አምላክ ትኩረቱን ወደ ሰዎች ያዞራል፤ በተጨማሪም አምላክ ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለሚኖሩ አገልጋዮቹ ከሰጣቸው ተስፋዎች መካከል አንዱ “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም” የሚለው ነው።

23 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገነት የሚያስተምረው ትምህርት ግልጽ ነው። አዳምና ሔዋን በኤደን ገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር መብታቸውን ቢያጡም ምድር ዳግመኛ ገነት ትሆናለች። አምላክ ቃል በገባው መሠረት ወደፊት የምድር ሕዝቦች ይባረካሉ። ዳዊት የዋሆችና ጻድቃን ምድርን እንደሚወርሱና በእሷም ለዘላለም እንደሚኖሩ በመንፈስ መሪነት ተናግሯል። በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ትንቢቶች በገነት ውስጥ የሚኖረውን አስደሳች ሁኔታ በጉጉት እንድንጠባበቅ ያደርጉናል። ሆኖም ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ኢየሱስ ለአይሁዳዊው ወንጀለኛ የሰጠው ተስፋ በሚፈጸምበት ጊዜ ነው። አንተም በዚያ ጊዜ መኖር ትችላለህ። ያኔ የኮሪያ ወንድሞቻችን በስብሰባው ላይ ለተገኙት ልዑካን “ገነት ውስጥ እንገናኝ!” በማለት የገለጹት ምኞት ፍጻሜውን ያገኛል።

^ አን.18 ፕሮፌሰር ማርቪን ፔት እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል፦ “ብዙዎች ‘ዛሬ’ የሚለው ቃል የገባው የ24 ሰዓት ርዝማኔ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚከናወንን ነገር ለማመልከት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሆኖም ይህ አመለካከት ኢየሱስ ከሞተ በኋላ በመጀመሪያ ወደ ሐዲስ ‘እንደወረደ’ (ማቴ. 12:40፤ ሥራ 2:31፤ ሮም 10:7) ከዚያም ወደ ሰማይ እንደወጣ ከሚጠቁሙት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር ይጋጫል።”

^ አን.21 በዚህ እትም ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።