በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወጣቶች፣ ፈጣሪያችሁ ደስተኛ እንድትሆኑ ይፈልጋል

ወጣቶች፣ ፈጣሪያችሁ ደስተኛ እንድትሆኑ ይፈልጋል

“በሕይወት ዘመንሽ ሁሉ መልካም ነገሮች ያጠግብሻል።”—መዝ. 103:5

መዝሙሮች፦ 135, 39

1, 2. በሕይወታችሁ ውስጥ የምታወጧቸውን ግቦች ስትወስኑ ፈጣሪያችሁ የሚለውን መስማታችሁ ጥበብ የሆነው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያሉትን ፎቶግራፎች ተመልከት።)

ወጣቶች ከሆናችሁ የወደፊት ሕይወታችሁን በተመለከተ ብዙ ምክር ይሰጣችሁ ይሆናል። አስተማሪዎች፣ የትምህርት ቤት አማካሪዎች ወይም ሌሎች ሰዎች ከፍተኛ ትምህርት እንድትከታተሉ እንዲሁም ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ እንድትይዙ ሊያበረታቷችሁ ይችላሉ። ይሖዋ ግን ከዚህ የተለየ አካሄድ እንድትከተሉ ይመክራችኋል። እርግጥ ነው፣ ትምህርት ከጨረሳችሁ በኋላ ራሳችሁን ማስተዳደር እንድትችሉ ተማሪ ሳላችሁ ጠንክራችሁ እንድትሠሩ ይጠብቅባችኋል። (ቆላ. 3:23) ሆኖም በሕይወታችሁ ውስጥ ቅድሚያ የምትሰጧቸውን ነገሮች ስትወስኑ እሱ ባወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድትመሩ ይፈልጋል፤ እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች አምላክ በመጨረሻው ዘመን ለምንኖረው ለእኛ ያለውን ዓላማና ፈቃድ ግንዛቤ ውስጥ ያስገቡ ናቸው።—ማቴ. 24:14

2 በተጨማሪም ይሖዋ ሁሉን ነገር እንደሚያውቅ አስታውሱ፤ አምላክ ያለንበት ዓለም ከፊት ለፊቱ ምን እንደሚጠብቀውና መጥፊያው ምን ያህል እንደቀረበ ያውቃል። (ኢሳ. 46:10፤ ማቴ. 24:3, 36) ስለ እኛም ቢሆን የተሟላ እውቀት አለው፤ እውነተኛ እርካታና ደስታ የሚሰጠን እንዲሁም ለሐዘንና ለብስጭት የሚዳርገን ምን እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል። በመሆኑም ሰዎች የሚሰጡት ምክር ምንም ያህል ምክንያታዊ ቢመስል በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እስካልሆነ ድረስ ምክሩ ጥበብ የተንጸባረቀበት ነው ሊባል አይችልም።—ምሳሌ 19:21

“ይሖዋን የሚጻረር ጥበብ . . . ከንቱ ነው”

3, 4. አዳምና ሔዋን እንዲሁም ዘሮቻቸው መጥፎ ምክር መስማታቸው ምን ውጤት አስከትሏል?

3 በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መጥፎ ምክር የሰጠው አካል ሰይጣን ነው። ሰይጣን በእብሪተኝነት ተነሳስቶ ራሱን አማካሪ አድርጎ በመሾም ለሔዋን አንድ ምክር ሰጣት፤ እሷና ባሏ ሕይወታቸውን በራሳቸው መንገድ ቢመሩ ይበልጥ ደስተኞች እንደሚሆኑ ነገራት። (ዘፍ. 3:1-6) እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሰይጣን ይህን ምክር የሰጣት በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ ነው። አዳምና ሔዋን እንዲሁም ወደፊት የሚወልዷቸው ልጆች ከይሖዋ ይልቅ እሱን እንዲያመልኩትና ለእሱ እንዲገዙለት ፈልጎ ነበር። ለመሆኑ ሰይጣን ለእነዚህ ባልና ሚስት ምን አድርጎላቸው ያውቃል? ያላቸውን ነገር ሁሉ የሰጣቸው ይሖዋ ነው፤ ይሖዋ የትዳር አጋር፣ ውብ የሆነ መኖሪያና ለዘላለም ሊኖር የሚችል ፍጹም አካል ሰጥቷቸዋል።

4 የሚያሳዝነው ግን አዳምና ሔዋን አምላክን ባለመታዘዛቸው ራሳቸውን ከእሱ ጋር አቆራረጡ። እንደምናውቀው ይህ ውሳኔያቸው አሳዛኝ ውጤት አስከትሏል። ከዋናው ግንድ ላይ እንደተቆረጠ አበባ ቀስ በቀስ እየጠወለጉ መሄድና ወደ ሞት ማዝገም ጀመሩ። ልጆቻቸውም የኃጢአትና ኃጢአት የሚያስከትለው ውጤት ሰለባ ሆኑ። (ሮም 5:12) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ሰዎች ልክ እንደ አዳምና ሔዋን ለአምላክ ለመገዛት አሻፈረኝ ብለዋል። ሕይወታቸውን በራሳቸው መንገድ መምራት ይፈልጋሉ። (ኤፌ. 2:1-3) ይህ አካሄዳቸው ያስከተለው ውጤት “ይሖዋን የሚጻረር ጥበብ . . . ከንቱ” እንደሆነ በግልጽ ያሳያል።—ምሳሌ 21:30

5. አምላክ ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነው? እንዲህ ያለ እምነት መጣሉስ ተገቢ ነው?

5 ይሁን እንጂ ይሖዋ ከሰው ልጆች መካከል እሱን ለማወቅ ጥረት የሚያደርጉና የሚያገለግሉት ሰዎች እንደሚኖሩ ያውቃል፤ ከእነዚህ መካከል ደግሞ በርካታ ወጣቶች ይገኙበታል። (መዝ. 103:17, 18፤ 110:3) እነዚህ ወጣቶች በይሖዋ ፊት እጅግ ውድ ናቸው! አንተስ ከእነሱ መካከል አንዱ ነህ? ከሆነ ለደስታህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ በርካታ ‘መልካም ነገሮችን’ ከአምላክ እያገኘህ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝሙር 103:5ን አንብብ፤ ምሳሌ 10:22) ከዚህ ቀጥሎ እንደምንመለከተው እነዚህ “መልካም ነገሮች” የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብን፣ ከሁሉ የተሻሉ ጓደኞችን፣ ጠቃሚ ግቦችንና እውነተኛ ነፃነትን ያካትታሉ።

ይሖዋ መንፈሳዊ ፍላጎታችሁን ያሟላላችኋል

6. ለመንፈሳዊ ፍላጎታችሁ ትኩረት መስጠት ያለባችሁ ለምንድን ነው? ይሖዋ መንፈሳዊ ፍላጎታችሁን የሚያሟላላችሁ እንዴት ነው?

6 የሰው ልጆች ከእንስሳት በተለየ መልኩ መንፈሳዊ ፍላጎት አላቸው፤ ይህን ፍላጎታቸውን ሊያሟላላቸው የሚችለው ደግሞ ፈጣሪ ብቻ ነው። (ማቴ. 4:4) ይሖዋ የሚላችሁን የምትሰሙ ከሆነ ማስተዋል፣ ጥበብና ደስታ ታገኛላችሁ። ኢየሱስ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴ. 5:3) አምላክ በቃሉ እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያቀርበው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አማካኝነት መንፈሳዊ ፍላጎታችሁን ያሟላላችኋል። (ማቴ. 24:45) ደግሞም ይህ መንፈሳዊ ምግብ ገንቢና ፈጽሞ የማይሰለች ነው!—ኢሳ. 65:13, 14

7. አምላክ የሚያቀርብላችሁን መንፈሳዊ ምግብ መመገባችሁ ምን ጥቅም ያስገኝላችኋል?

7 አምላክ የሚያቀርብላችሁ መንፈሳዊ ምግብ ጥበብና የማመዛዘን ችሎታ እንድታዳብሩ ይረዳችኋል፤ እነዚህ ባሕርያት ደግሞ በብዙ መንገድ ጥበቃ ያስገኙላችኋል። (ምሳሌ 2:10-14ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ ጥበብና የማመዛዘን ችሎታ ‘ፈጣሪ የለም’ እንደሚሉት ያሉ የሐሰት ትምህርቶችን መለየት እንድትችሉ ዓይናችሁን ያበሩላችኋል። ‘ደስተኛ ለመሆን ቁልፉ ገንዘብና ቁሳዊ ንብረት ማካበት ነው’ ከሚለው የተሳሳተ አመለካከትም ይጠብቋችኋል። በተጨማሪም መጥፎ ምኞቶችንና ጎጂ ልማዶችን ለይታችሁ ማወቅና መከላከል እንድትችሉ ይረዷችኋል። እንግዲያው አምላካዊ ጥበብንና የማመዛዘን ችሎታን መፈለጋችሁን እንዲሁም እንደ ውድ ሀብት መመልከታችሁን ቀጥሉ! እነዚህን ውድ ባሕርያት እያዳበራችሁ ስትሄዱ፣ ይሖዋ እንደሚወዳችሁና ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንድታገኙ እንደሚፈልግ በራሳችሁ ሕይወት መመልከት ትችላላችሁ።—መዝ. 34:8፤ ኢሳ. 48:17, 18

8. አሁን ወደ አምላክ መቅረባችሁ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረጋችሁ ለወደፊቱ ጊዜ የሚጠቅማችሁስ እንዴት ነው?

8 በቅርቡ የሰይጣን ዓለም ድምጥማጡ ይጠፋል፤ በዚያን ጊዜ አስተማማኝ ጥበቃ ሊያደርግልን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። ሌላው ቀርቶ የዕለት ጉርሳችንን ለማግኘት እንኳ የእሱን እጅ መጠባበቅ ሊያስፈልገን ይችላል! (ዕን. 3:2, 12-19) ወጣቶች፣ በሰማይ ወዳለው አባታችሁ የምትቀርቡበትና በእሱ ላይ ያላችሁን እምነት የምታጠናክሩበት ጊዜ አሁን ነው። (2 ጴጥ. 2:9) እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ በዙሪያችሁ ምንም ነገር ቢከሰት “ይሖዋን ሁልጊዜ በፊቴ አደርገዋለሁ። እሱ በቀኜ ስላለ ፈጽሞ አልናወጥም” በማለት የጻፈውን የመዝሙራዊው ዳዊትን ስሜት ልትጋሩ ትችላላችሁ።—መዝ. 16:8

ይሖዋ ከሁሉ የተሻሉ ጓደኞች እንድታገኙ ይረዳችኋል

9. (ሀ) በዮሐንስ 6:44 መሠረት ይሖዋ ምን ያደርጋል? (ለ) ከአንድ ሰው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስንገናኝ ግለሰቡ የይሖዋ ምሥክር መሆኑና አለመሆኑ ምን ለውጥ ያመጣል?

9 ይሖዋ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች በደግነት ወደ እውነተኛው አምልኮ በመሳብ የመንፈሳዊ ቤተሰቡ አባላት እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። (ዮሐንስ 6:44ን አንብብ።) የይሖዋ ምሥክር ያልሆነን አንድ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ስታገኙት ስለዚያ ሰው ምን የምታውቁት ነገር ይኖራል? ከስሙና ከውጫዊ ገጽታው ባለፈ ያን ያህል መረጃ ላይኖራችሁ ይችላል። ይሖዋን የሚያውቅንና የሚወድን ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ስታገኙ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። ግለሰቡ ከእናንተ የተለየ አስተዳደግ፣ ባሕል ወይም ጎሳ ቢኖረው አሊያም ከሌላ አገር የመጣ ቢሆን እንኳ ስለ እሱ ብዙ መረጃ ይኖራችኋል! እሱም ቢሆን ስለ እናንተ ብዙ ነገር ያውቃል።

ይሖዋ ከሁሉ የተሻሉ ጓደኞች እንድናገኝና መንፈሳዊ ግቦች እንድናወጣ ይፈልጋል (አንቀጽ 9-12⁠ን ተመልከት)

10, 11. የይሖዋ ሕዝቦች ምን የጋራ ነገር አላቸው? ይህስ ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል?

10 ለምሳሌ ያህል፣ ቋንቋችሁ የተለያየ ቢሆንም ሁለታችሁም የእውነትን “ንጹሕ ቋንቋ” ትናገራላችሁ። (ሶፎ. 3:9) በመሆኑም ስለ አምላክ፣ ስለምትመሩባቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜና ስለ ሌሎች ጉዳዮች ያላችሁ እምነት ተመሳሳይ ነው። ደግሞም እነዚህ መረጃዎች በአንድ ግለሰብ ላይ እምነት እንድንጥል የሚያደርጉን በጣም አስፈላጊ መረጃዎች ናቸው። በተጨማሪም ከሰዎች ጋር ጤናማና ዘላቂ ወዳጅነት ለመፍጠር የሚያስችሉ መሠረት ናቸው።

11 የይሖዋ አገልጋዮች መሆናችሁ ከሁሉ የተሻሉ ጓደኞችን እንድታገኙ አድርጓችኋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከአብዛኞቹ ጋር ገና ተገናኝታችሁ ባታውቁም በዓለም ዙሪያ እጅግ ብዙ ወዳጆች አሏችሁ! ከይሖዋ ሕዝቦች ውጭ እንዲህ ያለውን ውድ ስጦታ ያገኘ ማን አለ?

ይሖዋ ጠቃሚ ግቦችን እንድታወጡ ይረዳችኋል

12. ምን ዓይነት መንፈሳዊ ግቦች ልታወጡ ትችላላችሁ?

12 መክብብ 11:9–12:1ን አንብብ። ልትደርሱባቸው የምትጣጣሯቸው መንፈሳዊ ግቦች አሏችሁ? ለምሳሌ በየዕለቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሰነ ክፍል የማንበብ ግብ ይኖራችሁ ይሆናል። አሊያም ደግሞ የንግግርና የማስተማር ችሎታችሁን ለማሻሻል ጥረት እያደረጋችሁ ሊሆን ይችላል። ያወጣችሁት ግብ ምንም ይሁን ምን፣ ጥሩ ውጤት ስታገኙ ወይም ሌሎች የምታደርጉትን ጥረት አይተው ሲያመሰግኗችሁ ምን ይሰማችኋል? ደስታና እርካታ እንደሚሰማችሁ ምንም ጥርጥር የለውም። ደግሞም እንዲህ የሚሰማችሁ መሆኑ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ይህ፣ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ከራሳችሁ ፈቃድ ይልቅ የአምላክን ፈቃድ እያስቀደማችሁ እንዳላችሁ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።—መዝ. 40:8፤ ምሳሌ 27:11

13. ዓለማዊ ግቦችን ከማሳደድ ይልቅ አምላክን ማገልገል የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?

13 መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ መጣጣራችሁ እውነተኛ እርካታ ያስገኝላችኋል የምንልበት ሌላው ምክንያት ደግሞ የምታከናውኑት ሥራ በምንም ዓይነት ከንቱ አለመሆኑ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ጸንታችሁ ቁሙ፤ አትነቃነቁ፤ እንዲሁም ከጌታ ጋር በተያያዘ በትጋት የምታከናውኑት ሥራ ከንቱ አለመሆኑን አውቃችሁ ምንጊዜም የጌታ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ።” (1 ቆሮ. 15:58) በአንጻሩ ግን ዓለማዊ ግቦችን በመከታተልና ትልቅ ቦታ ላይ ለመድረስ በመጣጣር ላይ ያተኮረ ሕይወት ስኬታማ ሊመስል ቢችልም የኋላ ኋላ ከንቱ መሆኑ አይቀርም። (ሉቃስ 9:25) የንጉሥ ሰለሞን ሕይወት በዚህ ረገድ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆነናል።—ሮም 15:4

14. ሰለሞን ደስታ የሚሰጡ ነገሮችን ፈትኖ ለማየት ካደረገው ጥረት ምን ትምህርት ታገኛላችሁ?

14 እጅግ በጣም ሀብታምና ኃያል የነበረው ንጉሥ ሰለሞን ‘ደስታን ለመፈተንና ምን መልካም ነገር እንደሚገኝ ለማየት’ ቆርጦ ተነስቶ ነበር። (መክ. 2:1-10) በመሆኑም ቤቶችን ገነባ፣ የአትክልት ቦታዎችንና መናፈሻዎችን አዘጋጀ እንዲሁም የተመኘውን ሁሉ አደረገ። ከዚያስ ምን ተሰማው? ያከናወናቸው ነገሮች ደስታና እርካታ አስገኝተውለት ይሆን? ሰለሞን ራሱ መልሱን ሰጥቶናል። ‘እጆቼ የሠሩትን ሥራ ሁሉ መለስ ብዬ ሳስብ፣ ሁሉ ነገር ከንቱ መሆኑን አስተዋልኩ፤ እውነተኛ ፋይዳ ያለው አንዳች ነገር አልነበረም’ በማለት ጽፏል። (መክ. 2:11) ይህ እንዴት ያለ ትልቅ ትምህርት ነው! እናንተስ ከሰለሞን ታሪክ በመማር ጥበበኛ እንደሆናችሁ ታሳያላችሁ?

15. እምነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? መዝሙር 32:8 ላይ እንደተገለጸው እምነታችሁን መገንባታችሁ ምን ጥቅም ያስገኝላችኋል?

15 ይሖዋ፣ ከሚደርስባችሁ መከራ እንድትማሩ አይፈልግም። እርግጥ ነው፣ አምላክን ለመታዘዝና በሕይወታችሁ ውስጥ የእሱን ፈቃድ ለማስቀደም እምነት ያስፈልጋችኋል። እንዲህ ያለው እምነት በዋጋ ሊተመን የማይችልና ፈጽሞ ለቁጭት የማይዳርግ ነው። አዎ፣ ይሖዋ “ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር” ፈጽሞ አይረሳም። (ዕብ. 6:10) እንግዲያው ጠንካራ እምነት ለመገንባት ብርቱ ጥረት አድርጉ፤ እንዲህ ማድረጋችሁ በሰማይ ያለው አባታችሁ ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንድታገኙ እንደሚፈልግ በገዛ ሕይወታችሁ ለመመልከት ያስችላችኋል።—መዝሙር 32:8ን አንብብ።

አምላክ እውነተኛ ነፃነት እንድታገኙ ይረዳችኋል

16. ነፃነታችንን ከፍ አድርገን ልንመለከተውና በጥበብ ልንጠቀምበት የሚገባን ለምንድን ነው?

16 ጳውሎስ “የይሖዋ መንፈስ ባለበት . . . ነፃነት አለ” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮ. 3:17) አዎ፣ ይሖዋ ነፃነትን ይወዳል፤ እናንተንም የፈጠራችሁ ነፃነትን እንድትወዱ አድርጎ ነው። ያም ቢሆን ነፃነታችሁን ኃላፊነት እንደሚሰማችሁ በሚያሳይ መንገድ እንድትጠቀሙበት ይፈልጋል፤ ይህ ደግሞ ለእናንተም ጥበቃ ያስገኝላችኋል። የብልግና ምስሎችን የሚመለከቱ፣ የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ፣ አደገኛ በሆኑ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የሚካፈሉ ወይም አደንዛዥ ዕፆችንና የአልኮል መጠጦችን አላግባብ የሚጠቀሙ ወጣቶችን ታውቁ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ወጣቶች ለአጭር ጊዜ ያህል ደስታ ሊያገኙ ይችላሉ። ሆኖም በዚህ መልኩ የሚገኘው ደስታ አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላቸዋል፤ ለበሽታ፣ ለሱስ አልፎ ተርፎም ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ። (ገላ. 6:7, 8) እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህ ሰዎች ነፃነት ያገኙ ይምሰላቸው እንጂ ራሳቸውን እያታለሉ ነው።—ቲቶ 3:3

17, 18. (ሀ) አምላክን መታዘዝ ነፃነት የሚሰጠው እንዴት ነው? (ለ) አዳምና ሔዋን መጀመሪያ ላይ የነበራቸው ነፃነት በዛሬው ጊዜ የሰው ልጆች ካላቸው ነፃነት ጋር ሲወዳደር ምን ይመስላል?

17 በአንጻሩ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ለመመራት ጥረት በማድረጋቸው ምክንያት የታመሙ ምን ያህል ሰዎች ታውቃላችሁ? ይሖዋን መታዘዝ ጤናማ ሕይወት ለመምራትና ነፃነት ለማግኘት እንደሚያስችል ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝ. 19:7-11) በተጨማሪም ነፃነታችሁን በጥበብ ስትጠቀሙበት ማለትም ፍጹም በሆኑት የአምላክ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ስትመሩ እምነት የሚጣልባችሁ ሰዎች እንደሆናችሁ እንዲሁም ተጨማሪ ነፃነት ሊሰጣችሁ እንደሚችል ለአምላክም ሆነ ለወላጆቻችሁ ታሳያላችሁ። እንዲያውም የአምላክ ዓላማ ለታማኝ አገልጋዮቹ በሙሉ ፍጹም ነፃነት መስጠት ነው፤ ይህ ነፃነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት” ተብሎ ተገልጿል።—ሮም 8:21

18 አዳምና ሔዋን እንዲህ ያለ ነፃነት ነበራቸው። በኤደን ገነት ውስጥ ሳሉ አምላክ አንድ ገደብ ብቻ ጥሎባቸው ነበር። አምላክ የከለከላቸው የአንድን ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ ብቻ ነበር። (ዘፍ. 2:9, 17) ይህ ገደብ ጥብቅና መፈናፈኛ የሚያሳጣ ነበር? በፍጹም! ይህን ለመረዳት አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ፣ የሰው ልጆች እንዲያውቁና እንዲታዘዙ ከሚጠበቁባቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰብዓዊ ሕጎች ጋር ማወዳደር ብቻ በቂ ነው።

19. ነፃ ሰዎች እንድንሆን እየተማርን ያለነው እንዴት ነው?

19 ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚይዛቸው ጥበብ በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው። ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕጎች ከመስጠት ይልቅ በፍቅር ሕግ እንድንመራ በትዕግሥት ያስተምረናል። እሱ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድንከተልና ክፉ የሆነውን እንድንጠላ ይፈልጋል። (ሮም 12:9) ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ የሰጠው ትምህርት ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው፤ የተራራው ስብከት ያተኮረው መጥፎ ድርጊቶችን እንድንፈጽም በሚያነሳሳን ውስጣዊ ግፊት ላይ ነው። (ማቴ. 5:27, 28) የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ክርስቶስ፣ ከጽድቅና ከዓመፅ ጋር በተያያዘ የእሱን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ማንጸባረቅ እንድንችል በአዲሱ ዓለም ውስጥም እኛን ማስተማሩን ይቀጥላል። (ዕብ. 1:9) በተጨማሪም አካላዊና አእምሯዊ ፍጽምና ላይ እንድንደርስ ይረዳናል። እስቲ አስቡት! በዚያን ጊዜ ወደ ኃጢአት እንድናዘነብል ከሚያደርገን ግፊትም ሆነ ኃጢአት ካስከተለብን አስከፊ መዘዝ ሙሉ በሙሉ ነፃ እንወጣለን። በመጨረሻም ይሖዋ ቃል የገባልንን “ክብራማ ነፃነት” ማጣጣም እንችላለን።

20. (ሀ) ይሖዋ ነፃነቱን የሚጠቀምበት እንዴት ነው? (ለ) አምላክ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

20 እርግጥ ነው፣ ነፃነታችን ምንጊዜም ቢሆን ገደብ ይኖረዋል። ነፃነታችንን ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ እንድንጠቀምበት ይጠበቅብናል። ይሖዋ በዚህ ረገድ እሱን እንድንመስለው ይፈልጋል። እሱ ገደብ የለሽ ነፃነት አለው፤ ሆኖም የማሰብ ችሎታ ካላቸው ፍጥረታቱ ጋር በተያያዘ ማንኛውንም ነገር ሲያደርግ በፍቅር ለመመራት መርጧል። (1 ዮሐ. 4:7, 8) ከዚህ እንደምንረዳው ነፃነታችንን ሙሉ በሙሉ ተጠቅመንበታል ሊባል የሚችለው በአምላካዊ ፍቅር የምንመራ ከሆነ ብቻ ነው።

21. (ሀ) ዳዊት ስለ ይሖዋ ምን ተሰምቶታል? (ለ) በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

21 ይሖዋ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ፣ ጥሩ ጓደኞች፣ ጠቃሚ ግቦችና እውነተኛ ነፃነት የማግኘት ተስፋ ሰጥቷችኋል። ታዲያ ይሖዋ ለሰጣችሁ በርካታ “መልካም ነገሮች” አድናቆት አላችሁ? (መዝ. 103:5) ከሆነ መዝሙራዊው በመዝሙር 16:11 ላይ ያቀረበውን ጸሎት እንደምትጋሩ ምንም ጥርጥር የለውም፤ መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል፦ “የሕይወትን መንገድ አሳወቅከኝ። በፊትህ ብዙ ደስታ አለ፤ በቀኝህ ለዘላለም ደስታ አለ።” በቀጣዩ ርዕስ ላይ በመዝሙር 16 ውስጥ የሚገኙ ሌሎች መንፈሳዊ ዕንቁዎችን እንመረምራለን። ይህም እውነተኛ እርካታ የሚያስገኝ ሕይወት መምራት ስለሚቻልበት መንገድ ተጨማሪ ግንዛቤ እንድታገኙ ይረዳችኋል።