በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ጻድቅ ሰው በይሖዋ ሐሴት ያደርጋል”

“ጻድቅ ሰው በይሖዋ ሐሴት ያደርጋል”

ዲያና የተባሉት እህት ዕድሜያቸው ከ80 ዓመት በላይ ነው። ባለቤታቸው የአልዛይመር በሽታ ስለነበረባቸው ከመሞታቸው በፊት ያሉትን የተወሰኑ ዓመታት ያሳለፉት በአረጋውያን መጦሪያ ተቋም ውስጥ ነው። በተጨማሪም እህት ዲያና ሁለት ወንዶች ልጆቻቸውን በሞት ያጡ ከመሆኑም ሌላ በጡት ካንሰር ይሠቃዩ ነበር። ሆኖም የጉባኤያቸው አባላት በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ወይም አገልግሎት ላይ ሲያዩዋቸው ሁሌም ደስተኛ ናቸው።

ጆን የተባሉት ወንድም ደግሞ ከ43 ለሚበልጡ ዓመታት በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት አገልግለዋል። ይህን የአገልግሎት ዘርፍ በጣም ይወዱት የነበረ ሲሆን ከዚህ አገልግሎት ውጭ ምንም ሕይወት አይታያቸውም ነበር! ሆኖም የታመመ ዘመዳቸውን ለመንከባከብ ሲሉ የተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራቸውን አቋርጠው በአካባቢያቸው ባለ ጉባኤ ውስጥ ማገልገል ጀመሩ። ከዚህ በፊት የሚያውቋቸው ሰዎች ወንድም ጆንን በወረዳ ወይም በክልል ስብሰባ ላይ ሲያገኟቸው ልክ እንደ ድሮው ፊታቸው በደስታ እንደሚያበራ ይናገራሉ።

እህት ዲያናና ወንድም ጆን እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ሥር እያሉም እንኳ ደስተኛ ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው? ስሜታዊም ሆነ አካላዊ ሥቃይ እየደረሰበት ያለ ወይም ከፍ አድርጎ የሚመለከተውን የአገልግሎት መብት ያጣ ሰው ደስተኛ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቅ ሰው በይሖዋ ሐሴት ያደርጋል” በማለት ምክንያቱን ግልጽ ያደርግልናል። (መዝ. 64:10) ዘላቂ ደስታ የሚያስገኙና የማያስገኙ ነገሮችን ለይተን ማወቃችን ይህን አስፈላጊ እውነት በሚገባ ለመረዳት ያስችለናል።

ጊዜያዊ ደስታ

በጥቅሉ ሲታይ ምንጊዜም ቢሆን ደስታ የሚያስገኙ አንዳንድ ነገሮች አሉ። ከሚወዱት ሰው ጋር ትዳር መመሥረት፣ ልጅ መውለድ ወይም አንድ ዓይነት ቲኦክራሲያዊ መብት ማግኘት ያስደስታል። እነዚህን ነገሮች ያገኘነው ከይሖዋ ስለሆነ እንዲህ የሚሰማን መሆኑ ተገቢ ነው። ጋብቻን ያቋቋመው፣ ልጅ የመውለድ ችሎታ የሰጠንም ሆነ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የተለያዩ መብቶች እንዲኖሩ ያደረገው ይሖዋ ነው።—ዘፍ. 2:18, 22፤ መዝ. 127:3፤ 1 ጢሞ. 3:1

ይሁን እንጂ ደስታ የሚያስገኙልን አንዳንድ ነገሮች ጊዜያዊ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ አንድ የትዳር ጓደኛ ታማኝነቱን ሊያጓድል ወይም ሊሞት ይችላል። (ሕዝ. 24:18፤ ሆሴዕ 3:1) አንዳንድ ልጆች ወላጆቻቸውንም ሆነ አምላክን የማይታዘዙ ሊሆኑ አልፎ ተርፎም ከክርስቲያን ጉባኤ ሊወገዱ ይችላሉ። የሳሙኤል ልጆች ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ አላገለገሉም፤ ዳዊት የፈጸመው መጥፎ ድርጊትም ከገዛ ቤቱ መከራ እንዲመጣበት አድርጓል። (1 ሳሙ. 8:1-3፤ 2 ሳሙ. 12:11) እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ለሐዘንና ለጭንቀት መንስኤ እንደሚሆኑና ደስታ እንደሚያሳጡ የተረጋገጠ ነው።

በተመሳሳይም አንድ የአምላክ አገልጋይ በጤና መጓደል፣ በቤተሰብ ኃላፊነት አሊያም በድርጅታዊ ማስተካከያዎች የተነሳ ከዚህ በፊት የነበረውን የአገልግሎት መብት ሊያጣ ይችላል። እንዲህ ባለው ለውጥ ምክንያት የአገልግሎት መብታቸውን ያጡ በርካታ ክርስቲያኖች፣ ቀደም ሲል የነበራቸው ሕይወት እንደሚናፍቃቸው ተናግረዋል።

እንዲህ ያሉት ደስታ የሚያስገኙ ነገሮች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አንጻራዊ ወይም ጊዜያዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ እንመለከታለን። ታዲያ ሁኔታዎች እንደተጠበቀው በማይሆኑበት ጊዜም እንኳ የማይጠፋ ደስታ ይኖር ይሆን? ‘አዎ’ ብለን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን፤ ምክንያቱም ሳሙኤል፣ ዳዊትና ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች መከራ ቢደርስባቸውም በተወሰነ መጠን ደስታቸውን ጠብቀው መኖር ችለዋል።

ዘላቂ ደስታ

ኢየሱስ እውነተኛ ደስታ የሚባለው ምን እንደሆነ ያውቅ ነበር። ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ እያለ ማለትም ሁኔታዎች የተመቻቹ በነበሩበት ጊዜ ‘በይሖዋ ፊት ሁልጊዜ ሐሴት ያደርግ ነበር።’ (ምሳሌ 8:30) ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ግን አንዳንድ ጊዜ ከባድ ችግሮች ያጋጥሙት ነበር። ያም ቢሆን ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ በመፈጸም ደስታ ያገኝ ነበር። (ዮሐ. 4:34) ኢየሱስ በሕይወቱ መጨረሻ ላይ ከባድ ሥቃይ በደረሰበት ጊዜስ ደስታውን መጠበቅ ችሎ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ “ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል . . . በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ጸንቷል” ይላል። (ዕብ. 12:2) በመሆኑም ኢየሱስ እውነተኛ ደስታን አስመልክቶ ብዙ ትምህርት ሊሰጠን ይችላል። እስቲ ስለዚህ ጉዳይ የተናገራቸውን ሁለት ነገሮች እንመልከት።

በአንድ ወቅት፣ ኢየሱስ እንዲሰብኩ የላካቸው 70 የሚያህሉ ደቀ መዛሙርት ሥራቸውን አጠናቀው ወደ እሱ ተመለሱ። እነሱም አጋንንትን ማስወጣትን ጨምሮ የተለያዩ ተአምራት መፈጸም በመቻላቸው ተደስተው ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “መናፍስት ስለተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፤ ከዚህ ይልቅ ስማችሁ በሰማያት ስለተጻፈ ደስ ይበላችሁ” አላቸው። (ሉቃስ 10:1-9, 17, 20) በእርግጥም ለየት ያለ የአገልግሎት መብት ከማግኘት ይልቅ እጅግ ከፍ ተደርጎ ሊታይ የሚገባው የይሖዋን ሞገስ ማግኘት ነው። ይሖዋ እነዚያ ታማኝ ደቀ መዛሙርት ሞገሱን እንዲያገኙ አድርጓል፤ ከዚህ የላቀ ደስታ የሚያስገኝላቸው ምንም ነገር የለም።

በሌላ ወቅት ደግሞ ኢየሱስ በርካታ ሰዎችን እያስተማረ ነበር። በዚህ ጊዜ አንዲት አይሁዳዊት ሴት ግሩም የማስተማር ችሎታ ያለውን ኢየሱስን የወለደች እናት ደስተኛ እንደሆነች ተናገረች። ኢየሱስ ግን “ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው!” በማለት ሴትየዋን አረማት። (ሉቃስ 11:27, 28) የሚያኮራ ልጅ መውለድ አስደሳች ነገር ነው፤ ከሁሉ የላቀ ደስታ የሚያስገኘው ግን ይሖዋን በመታዘዝ ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት ነው።

በእርግጥም የይሖዋን ሞገስ እንዳገኘን ማወቃችን እውነተኛ ደስታ ለማግኘት የሚያስችለን ወሳኝ ነገር ነው። የሚያጋጥሙን መከራዎች በራሳቸው አስደሳች ባይሆኑም ደስታችንን ሊነጥቁን አይችሉም። እንዲያውም የሚደርስብንን መከራ ተቋቁመን በታማኝነት መጽናታችን ይበልጥ ደስተኛ እንድንሆን ያደርገናል። (ሮም 5:3-5) በተጨማሪም ይሖዋ በእሱ ለሚታመኑ ሰዎች መንፈሱን ይሰጣል፤ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ አንዱ ገጽታ ደግሞ ደስታ ነው። (ገላ. 5:22) ይህም መዝሙር 64:10 “ጻድቅ ሰው በይሖዋ ሐሴት ያደርጋል” የሚለው ለምን እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ ያደርግልናል።

ወንድም ጆን ደስታቸውን ጠብቀው መኖር የቻሉት እንዴት ነው?

ቀደም ሲል የተጠቀሱት እህት ዲያናና ወንድም ጆን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ደስታቸውን ጠብቀው መኖር የቻሉት ለዚህ ነው። እህት ዲያና “አንድ ልጅ ወላጆቹን መጠጊያ እንደሚያደርግ ሁሉ እኔም ይሖዋን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ” በማለት ተናግረዋል። እህት ዲያና የይሖዋን ሞገስ እንዳገኙ እንዲሰማቸው ያደረገው ምንድን ነው? እንዲህ ብለዋል፦ “ይሖዋ ዘወትር ደስተኛ ሆኜ መስበኬን እንድቀጥል የሚያስችል ኃይል በመስጠት እንደባረከኝ ይሰማኛል።” ከፍ አድርገው የሚመለከቱትን የተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ካቆሙ በኋላም በአገልግሎት ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉት ወንድም ጆን ምን እንደረዳቸው ሲናገሩ “በ1998 የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት አስተማሪ ሆኜ ማገልገል ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ ከወትሮው በተለየ ጥልቀት ያለው የግል ጥናት አደርግ ነበር” ብለዋል። ራሳቸውንና ባለቤታቸውን አስመልክቶ ደግሞ እንዲህ ብለዋል፦ “በይሖዋ አገልግሎት ባሳለፍናቸው ዓመታት ሁሉ በተመደብንበት በማንኛውም ቦታ እሱን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ አድርገን ነበር፤ ስለዚህ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ይህን ለውጥ መቀበል ያን ያህል አልከበደንም። እንዲህ ያለ ውሳኔ በማድረጋችን ፈጽሞ አንቆጭም።”

ሌሎች በርካታ የአምላክ አገልጋዮችም በመዝሙር 64:10 ላይ ያለው ሐሳብ እውነት መሆኑን በገዛ ሕይወታቸው ተመልክተዋል። ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል ውስጥ ያገለገሉ አንድ ባልና ሚስትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ከጊዜ በኋላ ልዩ አቅኚ ሆነው በመስኩ ላይ እንዲያገለግሉ ተመደቡ። እነዚህ ባልና ሚስት “የሚወዱትን ነገር ማጣት ሐዘን እንደሚያስከትል ምንም ጥርጥር የለውም” በማለት የተሰማቸውን በሐቀኝነት ተናግረዋል። አክለውም “በሐዘን ተቆራምደን እንኖራለን ማለት ግን አይደለም” ብለዋል። በመሆኑም ወዲያውኑ ከጉባኤው ጋር በማገልገል በስብከቱ ሥራ ራሳቸውን አስጠመዱ። በተጨማሪም እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “አንዳንድ ነገሮችን ለይተን በመጥቀስ ጸልየናል። ጸሎታችን እንደተመለሰልን ማየታችን ብርታትና ደስታ ሰጥቶናል። ወደ ጉባኤው ከመጣን ብዙም ሳይቆይ ሌሎች የጉባኤው አባላትም በአቅኚነት ማገልገል ጀመሩ፤ እኛም እድገት የሚያደርጉ ሁለት ጥናቶች በማግኘት ተባርከናል።”

“ለዘላለም ደስ ይበላችሁ”

እርግጥ ሁልጊዜ ደስተኛ መሆን ቀላል አይደለም፤ አንዳንድ ጊዜ የሚያሳዝኑ ነገሮች ያጋጥሙናል። ሆኖም ይሖዋ በመዝሙር 64:10 ላይ የሚገኙትን የሚያጽናኑ ቃላት በመንፈሱ መሪነት አጽፎልናል። ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜም እንኳ በማንኛውም ሁኔታ ሥር ታማኝ ሆነን በመኖር ‘ጻድቅ’ መሆናችንን እስካስመሠከርን ድረስ ‘በይሖዋ ሐሴት ማድረግ’ እንደምንችል እርግጠኞች ነን። ከዚህም በላይ ይሖዋ “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር” እንደሚያመጣ የሰጠው ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። ያኔ አለፍጽምና ሙሉ በሙሉ ይወገዳል። ሁሉም የአምላክ ሕዝቦች አምላክ በሚፈጥራቸውና በሚሰጣቸው ነገሮች ‘ለዘላለም ደስ ይላቸዋል፤ ሐሴትም ያደርጋሉ።’—ኢሳ. 65:17, 18

ይህ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስበው፦ ፍጹም ጤንነት የሚኖረን ከመሆኑም ሌላ በእያንዳንዱ ቀን ኃይላችን ታድሶ እንነሳለን። ከዚህ በፊት የደረሰብን ስሜታዊ ቁስል ምንም ያህል ከባድ ቢሆን ይህ መጥፎ ትዝታ ወደ አእምሯችን እየመጣ አይረብሸንም። አምላክ “የቀድሞዎቹ ነገሮች አይታሰቡም፤ ወደ ልብም አይገቡም” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። ሞት የለያያቸው የቤተሰብ አባላት በትንሣኤ አማካኝነት እንደገና ይገናኛሉ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የ12 ዓመት ሴት ልጃቸውን ኢየሱስ እንዳስነሳላቸው ወላጆች “እጅግ ከመደሰታቸው የተነሳ የሚሆኑት [ይጠፋቸዋል]።” (ማር. 5:42) በጊዜ ሂደት በምድር ላይ የሚኖረው እያንዳንዱ ሰው ሙሉ በሙሉ “ጻድቅ” ይሆናል፤ እንዲሁም ለዘላለም “በይሖዋ ሐሴት ያደርጋል።”