በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ለሁሉም ነገር አመስግኑ”

“ለሁሉም ነገር አመስግኑ”

አመስጋኝ ሰው እንደሆንክ ይሰማሃል? ይህ እያንዳንዳችን ልናስብበት የሚገባ ጥያቄ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ብዙ ሰዎች “የማያመሰግኑ” እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞ. 3:2) አንተም ማንኛውንም ነገር ማግኘት እንደሚገባቸው ወይም ሰዎች ለእነሱ አንድ ነገር የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው የሚሰማቸው ሰዎች አጋጥመውህ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ላገኟቸው ነገሮች አመስጋኝ መሆን እንዳለባቸው የሚሰማቸው አይመስልም። እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር መሆን አያስደስትም ቢባል አትስማማም?

ከዚህ በተቃራኒ የይሖዋ አገልጋዮች “አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ” እንዲሁም “ለሁሉም ነገር አመስግኑ” ተብለዋል። (ቆላ. 3:15፤ 1 ተሰ. 5:18) ደግሞም አመስጋኝ መሆን እኛንም ይጠቅመናል። እንዲህ የምንልባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ።

አመስጋኝ መሆን ለራሳችን ጥሩ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል

የአመስጋኝነት መንፈስ ለማዳበር የሚያነሳሳን አንዱ ምክንያት አመስጋኝነት ለራሳችን ጥሩ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዳን መሆኑ ነው። ለተደረገለት ነገር አመስጋኝ የሆነ ሰው ብዙ ጊዜ ለራሱ ጥሩ አመለካከት ይኖረዋል፤ የሚመሰገነው ሰውም ቢሆን ደስ ይለዋል። አመስጋኝነት ሁለቱንም ወገኖች የሚያስደስተው እንዴት ነው? እስቲ ይህን ለማሰብ ሞክር፦ ሰዎች ለአንተ አንድ ነገር ለማድረግ መፈለጋቸው፣ ጥሩ ነገር ሊደረግልህ እንደሚገባ የሚሰማቸው መሆኑን ያሳያል። እንዲህ የሚያደርጉት ስለሚያስቡልህ ነው። ይህን ማስተዋልህ ደግሞ ለራስህ ጥሩ አመለካከት እንዲኖርህ ያደርጋል። ሩት ያጋጠማት ሁኔታ ይህን ያረጋግጣል። ቦዔዝ ለሩት ደግነት አሳይቷታል። ሩት የሚያስብላት ሰው እንዳለ ማወቋ በጣም እንዳስደሰታት ጥርጥር የለውም።—ሩት 2:10-13

በተለይ ደግሞ አምላክን ማመስገናችን ተገቢ ነው። ይሖዋ በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ እስከ ዛሬ ስላደረጋቸውና ወደፊት ስለሚያደርጋቸው ብዙ መልካም ነገሮች አልፎ አልፎ ማሰብህ አይቀርም። (ዘዳ. 8:17, 18፤ ሥራ 14:17) ሆኖም ስለ አምላክ ጥሩነት ለአፍታ ያህል ከማሰብ ባለፈ አምላክ ለአንተም ሆነ ለቤተሰብህ ስለሰጠህ የተትረፈረፈ በረከት ለማሰላሰል ለምን ጊዜ አትመድብም? ፈጣሪህ ባሳየህ ልግስና ላይ ማሰላሰልህ ለእሱ ያለህ አድናቆት እንዲጨምር እንዲሁም ምን ያህል እንደሚወድህና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከትህ ይበልጥ እንድትገነዘብ ያደርጋል።—1 ዮሐ. 4:9

ይሁንና ስለ አምላክ ልግስና እንዲሁም ስለሰጠህ በረከቶች በማሰብ ብቻ አትወሰን፤ ይሖዋን ለጥሩነቱ አመስግነው። (መዝ. 100:4, 5) ደግሞም አንዳንዶች እንደሚናገሩት “ምስጋናን መግለጽ ለሰው ልጆች ደስታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል።”

አመስጋኝ መሆን ወዳጅነትን ያጠናክራል

አመስጋኝነት ይጠቅመናል የምንልበት ሌላው ምክንያት ወዳጅነትን የሚያጠናክር መሆኑ ነው። ማናችንም ብንሆን የሌሎች ምስጋና ያስፈልገናል። አንድን ሰው ላደረገልህ መልካም ነገር ከልብህ ስታመሰግነው ከግለሰቡ ጋር ይበልጥ ትቀራረባላችሁ። (ሮም 16:3, 4) ከዚህም በተጨማሪ አመስጋኝ የሆኑ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ ናቸው። ሌሎች የሚያሳዩአቸውን ደግነት ስለሚያስተውሉ እነሱም በምላሹ ደግነት ለማሳየት ይነሳሳሉ። ደግሞም ሌሎችን መርዳት የሚያስደስት ነገር ነው። ኢየሱስ እንዳለው “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—ሥራ 20:35

በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ አመስጋኝነትን በተመለከተ የተደረገ አንድ ጥናት ተባባሪ ዳይሬክተር የሆኑት ሮበርት ኤመንስ እንዲህ ብለዋል፦ “አመስጋኝ መሆን እንድንችል፣ አንዳችን የሌላው እርዳታ እንደሚያስፈልገን ይኸውም ሰጪ የምንሆንበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ ተቀባይ የምንሆንበት ጊዜም እንዳለ መገንዘብ ይኖርብናል።” እንደ እውነቱ ከሆነ በሕይወት መቀጠልም ሆነ ደስተኛ ሆነን መኖር እንድንችል በብዙ መንገዶች የሌሎች እርዳታ ያስፈልገናል። ለምሳሌ ያህል፣ የምንበላው ነገር ወይም ሕክምና ለማግኘት የሌሎች እርዳታ ሊያስፈልገን ይችላል። (1 ቆሮ. 12:21) አመስጋኝ የሆነ ሰው ሌሎች ለሚያደርጉለት ነገር አድናቆት እንዳለው ግልጽ ነው። ታዲያ አንተስ ሌሎች ላደረጉልህ ነገር ምስጋናህን የመግለጽ ልማድ አለህ?

አመስጋኝ መሆን ለሕይወት ባለህ አመለካከት ላይ ለውጥ ያመጣል

አመስጋኝ እንድንሆን የሚያነሳሳን ሌላው ምክንያት ደግሞ አመስጋኝነት ከአሉታዊ ነገሮች ይልቅ በአዎንታዊ ነገሮች ላይ እንድናተኩር የሚረዳን መሆኑ ነው። አእምሯችን፣ በተወሰኑ ነገሮች ላይ እንድናተኩር በማድረግ የማይፈለጉትን ነገሮች አጣርቶ የማስቀረት ችሎታ አለው። አመስጋኝ የሆነ ሰው ትኩረት የሚያደርገው አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንጂ በችግሮች ላይ አይደለም። አመስጋኝ በሆንክ መጠን፣ ይበልጥ አዎንታዊ ትሆናለህ፤ ይህ ደግሞ ይበልጥ አመስጋኝ እንድትሆን ያደርግሃል። አመስጋኝ እንድትሆን በሚያደርጉህ ነገሮች ላይ የምታተኩር ከሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ” በማለት የሰጠውን ማበረታቻ ተግባራዊ ማድረግ ትችላለህ።—ፊልጵ. 4:4

አመስጋኝነት፣ አሉታዊ ስለሆኑ ነገሮች እንዳታስብ ይረዳሃል። አመስጋኝ ከሆንን እንደ ቅናት፣ ሐዘን ወይም ምሬት ያሉትን ስሜቶች ማስተናገድ ከባድ ነው። በተጨማሪም አመስጋኝ የሆኑ ሰዎች በአብዛኛው የቁሳዊ ነገሮች ፍቅር አያድርባቸውም። ላሏቸው ነገሮች አመስጋኝ ስለሆኑ ተጨማሪ ነገር ስለ ማግኘት ነጋ ጠባ አይጨነቁም።—ፊልጵ. 4:12

በረከቶችህን አስብ!

በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በሚገጥሙን መከራዎች ተስፋ ስንቆርጥ ከማየት የበለጠ ሰይጣንን የሚያስደስተው ነገር የለም። አሉታዊ አመለካከት ብንይዝና አጉረምራሚዎች ብንሆን በጣም ደስ ይለዋል። እንዲህ ያለው መንፈስ ምሥራቹን ለመስበክ በምታደርገው ጥረት ውጤታማ እንዳትሆን ሊያደርግህ ይችላል። አመስጋኝነት የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ ከሆኑ ባሕርያት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፤ ለምሳሌ አመስጋኝ ሰው አምላክ ባደረገለት ጥሩ ነገር ይደሰታል እንዲሁም እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ሁሉ ላይ እምነት ያሳድራል።—ገላ. 5:22, 23

የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆንህ መጠን በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ አመስጋኝነት በተጠቀሱት ሐሳቦች እንደምትስማማ የታወቀ ነው። ያም ቢሆን አመስጋኝና አዎንታዊ መሆን ሁልጊዜ ቀላል እንዳልሆነ ይሰማህ ይሆናል። ይህ ግን ተስፋ ሊያስቆርጥህ አይገባም። አመስጋኝነትን ማዳበርና ይህን አመለካከት ይዘህ መቀጠል ትችላለህ። እንዴት? በእያንዳንዱ ቀን በሕይወትህ ውስጥ ስላጋጠሙህ አመስጋኝ እንድትሆን የሚያነሳሱ ነገሮች ለማሰብ ጊዜ መድብ። እንዲህ ያለ ልማድ ባዳበርክ መጠን አመስጋኝ መሆን ይበልጥ ቀላል እየሆነልህ ይሄዳል። ይህም ችግር ላይ ማተኮር ከሚቀናቸው ሰዎች በተቃራኒ በሕይወትህ ደስተኛ እንድትሆን ያደርግሃል። አምላክና ሰዎች አንተን ለማበረታታትና ለማስደሰት ሲሉ ባደረጉልህ ነገሮች ላይ አውጠንጥን። እንዲያውም እነዚህን ነገሮች በጽሑፍ የምታሰፍርበት ማስታወሻ ማዘጋጀት ትችላለህ። በማስታወሻው ላይ በዕለቱ ያጋጠሙህን አመስጋኝ እንድትሆን የሚያደርጉ ሁለት ወይም ሦስት ነገሮች ጻፍ።

በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ያደረጉ አንዳንዶች እንደሚገልጹት “አመስጋኝ መሆንን ልማድ ካደረግን የአንጎላችን ሴሎች ይበልጥ አዎንታዊ እንድንሆን በሚያደርግ መንገድ መሥራት ይጀምራሉ።” አመስጋኝ የሆነ ሰው ይበልጥ ደስተኛ ነው። እንግዲያው ስላገኘሃቸው በረከቶች አስብ፤ በሕይወትህ ውስጥ ስላጋጠሙህ መልካም ነገሮች ቆም ብለህ አሰላስል እንዲሁም ምንጊዜም አመስጋኝ ሁን! ያገኘሃቸውን መልካም ነገሮች አቅልለህ አትመልከት፤ ከዚህ ይልቅ “ይሖዋ ጥሩ ስለሆነ ምስጋና [አቅርብለት]።” አዎን ‘ለሁሉም ነገር አመስግን።’—1 ዜና 16:34፤ 1 ተሰ. 5:18