በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 49

ለሥራም ሆነ ለእረፍት “ጊዜ አለው”

ለሥራም ሆነ ለእረፍት “ጊዜ አለው”

“ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ትንሽ አረፍ በሉ።”—ማር. 6:31

መዝሙር 143 ነቅተን በተስፋ እንጠብቃለን

ማስተዋወቂያ *

1. ብዙ ሰዎች ለሥራ ምን አመለካከት አላቸው?

በምትኖርበት አካባቢ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች ለሥራ ምን አመለካከት አላቸው? በብዙ አገሮች ውስጥ ሰዎች ከበፊቱ የበለጠ ለረጅም ሰዓት አድካሚ የሆነ ሥራ ይሠራሉ። ከመጠን በላይ የሚሠሩ ሰዎች ደግሞ ለእረፍት፣ ከቤተሰባቸው ጋር አብሮ ለመሆን ወይም መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚሆን ጊዜ ለማግኘት ይቸገራሉ። (መክ. 2:23) በሌላ በኩል ግን ሥራ ጨርሶ የማይወዱና ላለመሥራት ሰበብ የሚፈላልጉ ሰዎችም አሉ።—ምሳሌ 26:13, 14

2-3. ይሖዋ እና ኢየሱስ ከሥራ ጋር በተያያዘ ምን ምሳሌ ትተውልናል?

2 ዓለም ለሥራ ካለው ሚዛናዊ ያልሆነ አመለካከት በተቃራኒ ይሖዋ እና ኢየሱስ ለሥራ ምን አመለካከት እንዳላቸው እስቲ እንመልከት። ይሖዋ ሥራ እንደሚወድ ምንም ጥያቄ የለውም። ኢየሱስ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም እሠራለሁ” በማለት ይህን እውነታ አረጋግጧል። (ዮሐ. 5:17) አምላክ እጅግ በጣም ብዙ መንፈሳዊ ፍጥረታትንና ግዙፉን ጽንፈ ዓለም ሲፈጥር ምን ያህል ሥራ እንዳከናወነ ለማሰብ እንሞክር። በምንኖርባት ውብ ምድር ላይም የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች እናገኛለን። በእርግጥም መዝሙራዊው “ይሖዋ ሆይ፣ ሥራህ ምንኛ ብዙ ነው! ሁሉንም በጥበብ ሠራህ። ምድር በፈጠርካቸው ነገሮች ተሞልታለች” ማለቱ የተገባ ነው።—መዝ. 104:24

3 ኢየሱስ የአባቱን ምሳሌ ተከትሏል። በጥበብ የተመሰለው ወልድ፣ አምላክ “ሰማያትን ባዘጋጀ ጊዜ” በሥራው ተካፍሏል። “የተዋጣለት ሠራተኛ” ሆኖ ከይሖዋ ጋር ይሠራ ነበር። (ምሳሌ 8:27-31) ይህ ከሆነ ከበርካታ ዘመናት በኋላ ደግሞ ኢየሱስ ወደ ምድር መጥቶ አስደናቂ ሥራ አከናውኗል። ይሖዋ የሰጠው ይህ ሥራ ለኢየሱስ እንደ ምግብ ሆኖለታል፤ ያከናወናቸው ሥራዎችም እሱን የላከው አምላክ እንደሆነ አረጋግጠዋል።—ዮሐ. 4:34፤ 5:36፤ 14:10

4. እረፍት ማድረግን በተመለከተ ከይሖዋ እና ከኢየሱስ ምን እንማራለን?

4 ይሖዋ እና ኢየሱስ ተግቶ በመሥራት ረገድ የተዉት ምሳሌ እረፍት ማድረግ እንደማያስፈልገን የሚያሳይ ነው? በፍጹም። ይሖዋ ፈጽሞ ስለማይደክመው እረፍት ማድረግ አያስፈልገውም። በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ሰማያትንና ምድርን ከፈጠረ በኋላ ‘ሥራውን እንዳቆመና እንዳረፈ’ ይናገራል። (ዘፀ. 31:17) ሆኖም ይህ ሐሳብ ይሖዋ ሥራውን ቆም አድርጎ፣ ያከናወነውን ነገር በመመልከት በሥራው እንደተደሰተ የሚጠቁም ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስም ቢሆን ምድር ላይ ሳለ ተግቶ ቢሠራም እረፍት ለማድረግና ከወዳጆቹ ጋር ለመመገብ የሚሆን ጊዜ ለማግኘት ይጥር ነበር።—ማቴ. 14:13፤ ሉቃስ 7:34

5. ብዙዎች ምን ማድረግ ያስቸግራቸዋል?

5 መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮችን ሥራ እንዲወዱ ያበረታታል። የአምላክ አገልጋዮች፣ ታታሪ ሠራተኞች እንጂ ሰነፎች መሆን የለባቸውም። (ምሳሌ 15:19) አንተም ቤተሰብህን ለማስተዳደር ሰብዓዊ ሥራ ትሠራ ይሆናል። በተጨማሪም ሁሉም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ የመካፈል ኃላፊነት አለባቸው። ያም ቢሆን በቂ እረፍት ማድረግ ያስፈልግሃል። ታዲያ ለሰብዓዊ ሥራ፣ ለአገልግሎት እና ለእረፍት የሚሆን ጊዜ በመመደብ ረገድ ሚዛናዊ መሆን ያስቸግርሃል? ደግሞስ ለሥራ እና ለእረፍት ምን ያህል ጊዜ መመደብ እንዳለብህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

ሚዛናዊ መሆን

6. ማርቆስ 6:30-34 ኢየሱስ ለሥራም ሆነ ለእረፍት ሚዛናዊ አመለካከት እንደነበረው የሚያሳየው እንዴት ነው?

6 ከሥራ ጋር በተያያዘ ሚዛናዊ መሆን አስፈላጊ ነው። ንጉሥ ሰለሞን “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው” ሲል በመንፈስ መሪነት ጽፏል። ሰለሞን ከጠቀሳቸው ነገሮች መካከል መትከል፣ መገንባት፣ ማልቀስ፣ መሳቅና ጭፈራ ይገኙበታል። (መክ. 3:1-8) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሥራ እና እረፍት፣ በሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው ነገሮች ናቸው። ኢየሱስ ለሥራም ሆነ ለእረፍት ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው። በአንድ ወቅት ሐዋርያቱ ከስብከት ጉዞ ከተመለሱ በኋላ የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሐዋርያቱ በሥራ በጣም ከመጠመዳቸው የተነሳ “ምግብ ለመብላት እንኳ ፋታ አላገኙም” ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ “ለብቻችን ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ትንሽ አረፍ በሉ” አላቸው። (ማርቆስ 6:30-34ን አንብብ።) ኢየሱስ እና ደቀ መዛሙርቱ የሚፈልጉትን ያህል ማረፍ የቻሉት ሁልጊዜ ባይሆንም ኢየሱስ እረፍት እንደሚያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር።

7. ስለ ሰንበት ሕግ መመርመራችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

7 አንዳንድ ጊዜ፣ ማረፍ ወይም ከተለመደው ፕሮግራማችን ለየት ያለ ነገር ማድረግ ያስፈልገናል። አምላክ ለጥንት ሕዝቦቹ ያደረገው አንድ ዝግጅት ይኸውም ሳምንታዊው የሰንበት እረፍት ለዚህ ማስረጃ ይሆነናል። ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባንሆንም እንኳ ስለ ሰንበት የሚገልጸውን ዘገባ መመርመራችን ይጠቅመናል። ከዚህ ዘገባ የምናገኘው ትምህርት ለሥራ እና ለእረፍት ያለንን አመለካከት ለመገምገም ይረዳናል።

ሰንበት—ለእረፍትና ለአምልኮ የተመደበ ጊዜ

8. በዘፀአት 31:12-15 መሠረት ሰንበት ምን የሚደረግበት ቀን ነበር?

8 ይሖዋ ከስድስት የፍጥረት ቀናት በኋላ፣ በምድር ላይ ከሚያከናውነው የፍጥረት ሥራ አረፍ እንዳለ የአምላክ ቃል ይናገራል። (ዘፍ. 2:2) ይሁንና ይሖዋ ሥራ ስለሚወድ ከሌሎች ነገሮች ጋር በተያያዘ ‘እስካሁንም እየሠራ ነው።’ (ዮሐ. 5:17) በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ስድስት ቀን ሠርቶ በሰባተኛው ቀን አርፏል፤ ሳምንታዊው የሰንበት ዝግጅትም ይህን አካሄድ የሚከተል ነው። አምላክ፣ ሰንበት በእሱና በእስራኤላውያን መካከል ያለ ምልክት እንደሆነ ተናግሯል። ሰንበት “ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት . . . ለይሖዋ የተቀደሰ [ቀን] ነው።” (ዘፀአት 31:12-15ን አንብብ።) በዚህ ዕለት ልጆችንና ባሪያዎችን ጨምሮ ማንኛውም ሰው ሥራ እንዳይሠራ ሕጉ ያዝዝ ነበር፤ ሌላው ቀርቶ የቤት እንስሳት እንኳ ሥራ መሥራት አልነበረባቸውም። (ዘፀ. 20:10) ይህ ዝግጅት እስራኤላውያን ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጡ ያስችላቸው ነበር።

9. በኢየሱስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ሰንበትን በተመለከተ ምን የተዛባ አመለካከት ነበራቸው?

9 ሰንበት የአምላክን ሕዝብ የሚጠቅም ዝግጅት ነበር፤ ይሁን እንጂ በኢየሱስ ዘመን የነበሩ በርካታ የሃይማኖት መሪዎች ይህ ዝግጅት ከልክ በላይ ጥብቅ እና ጫና የሚፈጥር እንዲሆን አድርገው ነበር። በሰንበት ቀን እሸት መቅጠፍ ወይም የታመመን ሰው መፈወስ እንኳ ሕጉን መጣስ እንደሆነ ይናገሩ ነበር። (ማር. 2:23-27፤ 3:2-5) እንዲህ ያለው አመለካከት የአምላክን አስተሳሰብ አያንጸባርቅም፤ ኢየሱስም ለአድማጮቹ ይህን ግልጽ አድርጎላቸዋል።

የኢየሱስ ቤተሰብ በሰንበት ዕለት በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ያደርግ ነበር (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት) *

10. ኢየሱስ ስለ ሰንበት የነበረውን አመለካከት በተመለከተ በማቴዎስ 12:9-12 ላይ ከሚገኘው ዘገባ ምን እንማራለን?

10 ኢየሱስና አይሁዳውያን ተከታዮቹ፣ በሙሴ ሕግ ሥር ስለነበሩ ሰንበትን ያከብሩ ነበር። * ያም ቢሆን ኢየሱስ የሰንበትን ሕግ ከማክበር ጋር በተያያዘ ምክንያታዊ መሆን እንደሚያስፈልግ እንዲሁም በዚህ ዕለት ደግነት ማሳየትና መልካም ማድረግ እንደሚፈቀድ ተናግሯል፤ በድርጊቱም ቢሆን ይህን አሳይቷል። “በሰንበት መልካም ነገር ማድረግ ተፈቅዷል” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ማቴዎስ 12:9-12ን አንብብ።) በሰንበት ዕለት ደግነት ማሳየትና መልካም ማድረግ ከሕጉ ጋር እንደሚጋጭ አልተሰማውም። ኢየሱስ ያደረገው ነገርም የሰንበት ሕግ የተሰጠበትን ዋነኛ ምክንያት እንደተገነዘበ የሚያጎላ ነው። በዚህ ቀን የአምላክ አገልጋዮች ከዕለት ተዕለት ሥራቸው ስለሚያርፉ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ይችላሉ። ኢየሱስ ያደገው የሰንበት ቀንን ለመንፈሳዊ ነገሮች በሚያውል ቤተሰብ ውስጥ ነው። ኢየሱስ ወዳደገበት ወደ ናዝሬት ከተማ በሄደበት ወቅት ያደረገው ነገር ይህን ያሳያል፤ ዘገባው “እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኩራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነስቶ ቆመ” ይላል።—ሉቃስ 4:15-19

ለሥራ ምን አመለካከት አለህ?

11. ኢየሱስ ከሥራ ጋር በተያያዘ የማንን ምሳሌ መከተል ይችል ነበር?

11 የኢየሱስ አሳዳጊ አባት የሆነው ዮሴፍ ልጁን ኢየሱስን አናጺ እንዲሆን ሲያሠለጥነው፣ አምላክ ለሥራ ያለውን አመለካከት እንዳስተማረው ጥያቄ የለውም። (ማቴ. 13:55, 56) ኢየሱስም ቢሆን ዮሴፍ ትልቅ የሆነውን ቤተሰቡን ለማስተዳደር በየዕለቱ ጠንክሮ ሲሠራ ተመልክቶ መሆን አለበት። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ‘ለሠራተኛ ደሞዙ ይገባዋል’ ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ መናገሩ አያስገርምም። (ሉቃስ 10:7) በእርግጥም ኢየሱስ ተግቶ ስለ መሥራት ያውቅ ነበር።

12. ጳውሎስ ተግቶ ስለ መሥራት ያለውን አመለካከት የሚያሳዩት የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?

12 ሐዋርያው ጳውሎስም ታታሪ ሠራተኛ ነበር። ዋነኛ ሥራው ስለ ኢየሱስ ስም መመሥከርና የእሱን መልእክት ማወጅ ነበር። ያም ቢሆን ጳውሎስ ራሱን ለማስተዳደር ይሠራ ነበር። የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች፣ ጳውሎስ ማንንም “ብዙ ወጪ በማስወጣት . . . ሸክም ላለመሆን” ሲል “ሌት ተቀን በመሥራት” ይደክምና ይለፋ እንደነበር ያውቃሉ። (2 ተሰ. 3:8፤ ሥራ 20:34, 35) ጳውሎስ ይህን ሲል ድንኳን በመስፋት ስለሚያከናውነው ሥራ እየጠቀሰ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ፣ በቆሮንቶስ በነበረበት ወቅት አቂላ እና ጵርስቅላ ቤት አርፎ “አብሯቸው ይሠራ ነበር፤ ሙያቸውም ድንኳን መሥራት ነበር።” በእርግጥ ጳውሎስ “ሌት ተቀን” እንደሠራ ሲናገር ያለእረፍት እንደሠራ መግለጹ አልነበረም። በሰንበት ቀን እና በሌሎች ጊዜያት ከሥራው ያርፍ ነበር። በዚያ ዕለት እረፍት ማድረጉ፣ እንደ እሱ በሰንበት ከሥራቸው ለሚያርፉት አይሁዳውያን ለመመሥከር አጋጣሚ ሰጥቶታል።—ሥራ 13:14-16, 42-44፤ 16:13፤ 18:1-4

13. ጳውሎስ ከተወው ምሳሌ ምን እንማራለን?

13 ሐዋርያው ጳውሎስ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ሰብዓዊ ሥራ መሥራት የነበረበት ቢሆንም “የአምላክን ምሥራች በማወጁ ቅዱስ ሥራ” አዘውትሮ ይካፈል ነበር። (ሮም 15:16፤ 2 ቆሮ. 11:23) ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ አበረታቷል። አቂላና ጵርስቅላ ‘በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውት የሚሠሩ’ የሥራ ባልደረቦቹ ነበሩ። (ሮም 12:11፤ 16:3) ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን “የጌታ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ” በማለት አሳስቧቸዋል። (1 ቆሮ. 15:58፤ 2 ቆሮ. 9:8) እንዲያውም “መሥራት የማይፈልግ ሁሉ አይብላ” በማለት በይሖዋ መንፈስ መሪነት ጽፏል።—2 ተሰ. 3:10

14. ኢየሱስ በዮሐንስ 14:12 ላይ ያለውን ሐሳብ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?

14 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ሥራ ምሥራቹን መስበክና ደቀ መዛሙርት ማድረግ ነው። እንዲያውም ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ከእሱ የበለጡ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ አስቀድሞ ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:12ን አንብብ።) ኢየሱስ ይህን ሲል እንደ እሱ ተአምራት እንደምንፈጽም መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ተከታዮቹ የሚሸፍኑት የአገልግሎት ክልል ስፋት፣ የሚሰብኩላቸውና የሚያስተምሯቸው ሰዎች ብዛት እንዲሁም ይህን ሥራ የሚያከናውኑበት ጊዜ ከእሱ እንደሚበልጥ መናገሩ ነበር።

15. ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል? ለምንስ?

15 ሰብዓዊ ሥራ የምትሠራ ከሆነ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በሥራ ቦታዬ የምታወቀው ታታሪ ሠራተኛ በመሆኔ ነው? ሥራዬን በሰዓቱ ለመጨረስና አቅሜ በፈቀደው መጠን ጥሩ አድርጌ ለመሥራት እጥራለሁ?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች ‘አዎ’ የሚል መልስ ከሰጠህ የአሠሪህን አመኔታ ታተርፋለህ። በተጨማሪም አንተን የሚመለከቱ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ለማዳመጥ ሊነሳሱ ይችላሉ። ከስብከቱና ከማስተማሩ ሥራ ጋር በተያያዘ ደግሞ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራስህን ጠይቅ፦ ‘ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ የምታወቀው ትጉ በመሆኔ ነው? ለሰዎች ምሥራቹን ለመመሥከር በሚገባ እዘጋጃለሁ? ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ሳልዘገይ ተመላልሶ መጠየቅ አደርጋለሁ? በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች አዘውትሬ እካፈላለሁ?’ መልስህ ‘አዎ’ ከሆነ በሥራህ ደስታ ታገኛለህ።

ለእረፍት ምን አመለካከት አለህ?

16. ኢየሱስና ሐዋርያቱ ስለ እረፍት የነበራቸው አመለካከት በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ካላቸው አመለካከት የሚለየው እንዴት ነው?

16 ኢየሱስ፣ እሱና ሐዋርያቱ አልፎ አልፎ እረፍት እንደሚያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር። በዚያ ዘመንም ሆነ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ያላቸው አመለካከት ግን ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ ከተጠቀሰው ሀብታም ሰው ጋር የሚመሳሰል ነው። ይህ ሰው፣ ነፍሱን “ዘና በይ፣ ብዪ፣ ጠጪ፣ ደስም ይበልሽ” ብሏታል። (ሉቃስ 12:19፤ 2 ጢሞ. 3:4) ይህ ሰው ትኩረት ያደረገው በእረፍትና በተድላ ላይ ነበር። ከዚህ በተቃራኒ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ራሳቸውን በማስደሰት ላይ ያተኮረ ሕይወት አልመሩም።

ለሥራ እና ለእረፍት ሚዛናዊ አመለካከት መያዛችን፣ አስደሳች በሆኑ መልካም ሥራዎች ላይ ትኩረት እንድናደርግ አጋጣሚ ይሰጠናል (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት) *

17. ከሰብዓዊ ሥራችን ነፃ የምንሆንበትን ጊዜ የምንጠቀምበት እንዴት ነው?

17 በዛሬው ጊዜ ያለን ክርስቲያኖች፣ ከሥራ ነፃ የምንሆንበትን ጊዜ ለማረፍ ብቻ ሳይሆን ለሰዎች ለመመሥከርና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት በማዋል የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል እንጥራለን። እንዲያውም ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ እና ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ከፍ አድርገን ስለምንመለከታቸው በእነዚህ ቅዱስ ሥራዎች አዘውትረን ለመካፈል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። (ዕብ. 10:24, 25) ለእረፍት ወደ ሌላ አካባቢ በምንጓዝበት ጊዜም እንኳ በሄድንበት ቦታ ስብሰባ ላይ በመገኘት እንዲሁም ለምናገኛቸው ሰዎች ምሥራቹን መናገር የምንችልበት አጋጣሚ በመፈለግ መንፈሳዊ ልማዶቻችንን እንቀጥላለን።—2 ጢሞ. 4:2

18. ንጉሣችን ክርስቶስ ኢየሱስ ምን እንድናደርግ ይፈልጋል?

18 ንጉሣችን ክርስቶስ ኢየሱስ ምክንያታዊ ከመሆኑም ሌላ እንዲሁም ለሥራ እና ለእረፍት ሚዛናዊ አመለካከት እንድናዳብር ስለሚረዳን በጣም አመስጋኞች ነን! (ዕብ. 4:15) ኢየሱስ፣ የሚያስፈልገንን እረፍት እንድናገኝ ይፈልጋል። በሌላ በኩል ደግሞ ለሕይወት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላት ጠንክረን እንድንሠራ እንዲሁም አስደሳች በሆነው ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ እንድንካፈል ይፈልጋል። በቀጣዩ ርዕስ ላይ ኢየሱስ፣ እኛን ከከፋ ባርነት ነፃ ለማውጣት ስለሚጫወተው ሚና እንመለከታለን።

መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል

^ አን.5 ቅዱሳን መጻሕፍት ከሥራ እና ከእረፍት ጋር በተያያዘ ሚዛናዊ አመለካከት እንድናዳብር ያስተምሩናል። ይህ ርዕስ፣ ለእስራኤላውያን የተሰጠውን ሳምንታዊውን የሰንበት ዝግጅት እንደ ምሳሌ በመጠቀም ስለ ሥራ እና ስለ እረፍት ያለንን አመለካከት እንድንገመግም ይረዳናል።

^ አን.10 ደቀ መዛሙርቱ ለሰንበት ሕግ ከፍተኛ አክብሮት ስለነበራቸው፣ የሰንበት ቀን እስኪያበቃ ድረስ ከኢየሱስ አስከሬን ጋር በተያያዘ የሚያደርጉትን ዝግጅት አቁመው ነበር።—ሉቃስ 23:55, 56

^ አን.55 የሥዕሉ መግለጫ፦ በሰንበት ቀን ዮሴፍ ቤተሰቡን ወደ ምኩራብ ሲወስድ።

^ አን.57 የሥዕሉ መግለጫ፦ ቤተሰቡን ለማስተዳደር የሚሠራ አንድ አባት ከሥራ ነፃ በሚሆንበት ጊዜ ሌላው ቀርቶ ከቤተሰቡ ጋር ለሽርሽር ወጣ ሲሉም ጭምር በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ይካፈላል።