የአንባቢያን ጥያቄዎች
ሔዋን ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ ብትበላ እንደማትሞት ሰይጣን ሲነግራት በዛሬው ጊዜ በስፋት የሚታመንበትን ነፍስ አትሞትም የሚለውን ትምህርት እያስተዋወቀ ነበር?
አይመስልም። ዲያብሎስ፣ አምላክ የከለከላትን ፍሬ ብትበላ እንደማትሞት ለሔዋን ሲነግራት በሥጋ የሞተች ቢመስልም ከእሷ የሚወጣ አንድ የማይታይ ነገር (በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች የማይሞት ነፍስ ብለው የሚጠሩት ነገር) በሌላ ቦታ መኖሩን እንደሚቀጥል መግለጹ አልነበረም። ሰይጣን በእባብ አማካኝነት ለሔዋን የነገራት ከዛፉ ፍሬ ከበላች ‘ፈጽሞ እንደማትሞት’ ነው። ሰይጣን ይህን ሲል ሔዋን በሕይወት መኖሯን እንደምትቀጥል እንዲሁም ከአምላክ አመራር ውጭ ሆና በምድር ላይ አስደሳች ሕይወት እንደሚኖራት መጠቆሙ ነበር።—ዘፍ. 2:17፤ 3:3-5
ታዲያ ነፍስ እንደማትሞት የሚገልጸው የሐሰት ትምህርት የመነጨው በኤደን ካልሆነ ይህ ትምህርት የተጠነሰሰው መቼ ነው? በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ሆኖም የሐሰት አምልኮ በሙሉ በኖኅ ዘመን በደረሰው የጥፋት ውኃ እንደጠፋ እናውቃለን። ከጥፋቱ የተረፉት እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች የሆኑት ኖኅና ቤተሰቡ ብቻ ስለሆኑ የተሳሳተ ሃይማኖታዊ ትምህርት የሚያስተምሩ ሰዎች ከጥፋቱ አላለፉም።
እንግዲያው በዛሬው ጊዜ ያለው፣ የሰው ነፍስ እንደማትሞት የሚገልጸው ትምህርት የመነጨው ከጥፋት ውኃ በኋላ መሆን አለበት። አምላክ በባቤል የሰዎችን ቋንቋ ባዘበራረቀበት ወቅት ሰዎቹ “በመላው ምድር ላይ እንዲበተኑ አድርጓል”፤ እነዚህ ሰዎች የማትሞት ነፍስ እንዳለች የሚገልጸውን ትምህርት ወደተበተኑባቸው አካባቢዎች ይዘው ሄደው መሆን አለበት። (ዘፍ. 11:8, 9) ይህ የሐሰት ትምህርት የተጠነሰሰው መቼም ይሁን መቼ ትምህርቱን ያስጀመረው “የውሸት አባት” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነና ይህ ትምህርት ሲስፋፋ በማየት እንደተደሰተ ጥርጥር የለውም።—ዮሐ. 8:44