የአንባቢያን ጥያቄዎች
መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ጉዳይ ለማረጋገጥ ቢያንስ ሁለት ምሥክሮች እንደሚያስፈልጉ ይናገራል። (ዘኁ. 35:30፤ ዘዳ. 17:6፤ 19:15፤ ማቴ. 18:16፤ 1 ጢሞ. 5:19) ይሁንና አንድ ሰው አንዲትን የታጨች ልጃገረድ “ሜዳ ላይ” አግኝቶ ቢደፍራት፣ ልጅቷ ከጮኸች እሷ ነፃ እንደምትሆን ሰውየው ግን በምንዝር ወንጀል እንደሚጠየቅ የሙሴ ሕግ ይገልጻል። ወንጀል መፈጸሙን ሊመሠክሩ የሚችሉ ሌሎች ሰዎች ባይኖሩም እሷ ነፃ የምትወጣው፣ እሱ ግን ጥፋተኛ የሚሆነው ለምንድን ነው?
በዘዳግም 22:25-27 ላይ የሚገኘው ዘገባ በዋነኝነት የሚያወሳው ሰውየው ጥፋተኛ መሆኑን ስለ ማረጋገጥ አይደለም፤ ምክንያቱም ግለሰቡ ጥፋተኛ መሆኑ የተረጋገጠ ነገር ነው። ይህ ሕግ ያተኮረው ልጅቷ ጥፋተኛ አለመሆኗን በማረጋገጥ ላይ ነው። እስቲ በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ እንመልከት።
ከዚህ በፊት ያሉት ቁጥሮች የሚገልጹት አንድ ሰው ከታጨች ሴት ጋር “ከተማ ውስጥ” የፆታ ግንኙነት ቢፈጽም ስለሚደረገው ነገር ነው። ግለሰቡ ይህን ድርጊት በመፈጸሙ በምንዝር ኃጢአት ይጠየቃል፤ ምክንያቱም የታጨች ሴት እንዳገባች ትቆጠር ነበር። ስለ ሴትየዋስ ምን ማለት ይቻላል? ጥቅሱ “በከተማው ውስጥ ስላልጮኸች” ይላል። ሴትየዋ ጮኻ ቢሆን ኖሮ ሌሎች ሰምተው ሊደርሱላት ይችሉ ነበር። እሷ ግን አልጮኸችም። በመሆኑም እሷም ምንዝር ፈጽማለች፤ ስለዚህ ሁለቱም ጥፋተኛ ተብለው ይፈረድባቸው ነበር።—ዘዳ. 22:23, 24
ቀጥሎ ያለው ሕግ ደግሞ ስለ ሌላ ሁኔታ የሚያብራራ ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ይሁንና ሰውየው የታጨችውን ልጃገረድ ያገኛት ሜዳ ላይ ቢሆንና በጉልበት አስገድዶ አብሯት ቢተኛ እሱ ብቻ ይገደል፤ በልጅቷ ላይ ምንም አታድርግ። ልጅቷ ሞት የሚገባው ኃጢአት አልሠራችም። ይህ ጉዳይ በባልንጀራው ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ከሚገድል ሰው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። ምክንያቱም ሰውየው ልጅቷን ያገኛት ሜዳ ላይ ሲሆን የታጨችው ልጅ ብትጮኽም እንኳ ማንም አልደረሰላትም።”—ዘዳ. 22:25-27
በዚህኛው ሁኔታ ላይ ዳኞቹ ልጅቷን እንዲያምኗት ይጠበቅባቸዋል። ለምን? ልጅቷ “ብትጮኽም እንኳ ማንም አልደረሰላትም” ተብሎ ስለሚታሰብ ነው። ስለዚህ ምንዝር እንደፈጸመች ተደርጋ አትቆጠርም። ሰውየው ግን አስገድዶ በመድፈርና በምንዝር ወንጀል ይጠየቃል፤ ምክንያቱም ጥቅሱ እንደሚናገረው የታጨችውን ልጅ “በጉልበት አስገድዶ አብሯት [ተኝቷል]።”
ይህ ሕግ ያተኮረው ልጅቷ ጥፋተኛ አለመሆኗን በማረጋገጥ ላይ ቢሆንም ሰውየው አስገድዶ በመድፈርና በምንዝር ተጠያቂ እንደሆነ መግለጹ ተገቢ ነው። ዳኞቹ ‘ጉዳዩን በጥልቀት ይመረምሩ’ እንዲሁም ይሖዋ በግልጽና በተደጋጋሚ ካስቀመጠው መሥፈርት ጋር የሚስማማ ውሳኔ ያደርጉ እንደነበር መተማመን እንችላለን።—ዘዳ. 13:14፤ 17:4፤ ዘፀ. 20:14