በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በ2019 መጠበቂያ ግንብ ላይ የተመሠረቱትን እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ትችላለህ?

አምላክ “አንቺን ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል” በማለት የገባው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? (ኢሳ. 54:17)

አንድ ግንብ፣ አውዳሚ ከሆነ ውሽንፍር እንደሚከልል ሁሉ ይሖዋም ‘ከጨቋኞች ቁጣ’ እንደሚከልለን መተማመን እንችላለን። (ኢሳ. 25:4, 5) ጠላቶቻችን በእኛ ላይ ዘላቂ ጉዳት ማድረስ አይችሉም።—w19.01 ከገጽ 6-7

አምላክ በከነአናውያንና በዓመፀኛ እስራኤላውያን ላይ የወሰደው እርምጃ ፍትሑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

አምላክ፣ አስጸያፊ የሆነ የፆታ ብልግና በሚፈጽሙ ወይም በሴቶችና በልጆች ላይ ጥቃት በሚያደርሱ ሰዎች ላይ የፍርድ እርምጃ ወስዷል። ሕዝቡ ለእሱ ታዛዥ ሲሆኑና ሌሎችን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሲይዙ ይባርካቸው ነበር።—w19.02 ከገጽ 22-23

አንድ የማያምን ሰው ሲጸልይ በስፍራው ተገኝተን ቢሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

አክብሮት ልናሳይ የሚገባ ቢሆንም ምንም ነገር ከመናገር እንቆጠባለን። ለጸሎቱ “አሜን” በማለት ምላሽ አንሰጥም፤ እንዲሁም በቦታው ከተገኙ ሌሎች ሰዎች ጋር እጅ ለእጅ አንያያዝም። በልባችን የራሳችንን ጸሎት መጸለይ እንችላለን።—w19.03 ገጽ 31

በልጆች ላይ የሚፈጸመው ፆታዊ ጥቃት ምን ያህል ከባድ ኃጢአት ነው?

በልጆች ላይ የሚፈጸመው ፆታዊ ጥቃት በልጁ፣ በጉባኤው፣ በሰብዓዊ ባለሥልጣናትና በአምላክ ላይ የሚፈጸም ኃጢአት ነው። ሽማግሌዎች፣ ሕፃናትን ከማስነወር ጋር የተያያዙ ክሶች ሪፖርት እንዲደረጉ የሚጠይቁ ሰብዓዊ ሕጎችን ይታዘዛሉ።—w19.05 ከገጽ 9-10

አእምሯችንን የሚያሠራውን ኃይል መለወጥ ወይም ማስተካከል የምንችለው እንዴት ነው?

ለዚህ የሚረዱን ወሳኝ እርምጃዎች ይሖዋን በጸሎት ማነጋገር፣ ራሳችንን ለመገምገም በሚያስችሉን ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰል እና ጓደኞቻችንን በጥበብ መምረጥ ናቸው።—w19.06 ገጽ 11

ለስደት ለመዘጋጀት ከአሁኑ ምን ማድረግ እንችላለን?

ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ማጠናከር ይኖርብናል። ይሖዋ እንደሚወደንና ፈጽሞ እንደማይተወን እርግጠኞች እንሁን። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ እናንብብ እንዲሁም ዘወትር እንጸልይ። የአምላክ መንግሥት እንደሚያመጣቸው ቃል የተገባልን በረከቶች እንደሚፈጸሙ እንተማመን። የምንወዳቸውን ጥቅሶችና የውዳሴ መዝሙሮችን በቃላችን ለመያዝ ጥረት እናድርግ።—w19.07 ከገጽ 2-4

የቤተሰባችን አባላት መዳን እንዲያገኙ ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን?

ስሜታቸውን ለመረዳት ጥረት ማድረጋችን፣ በምግባራችን ምሥክርነት መስጠታችን እንዲሁም ትዕግሥተኛና ዘዴኛ መሆናችን አስፈላጊ ነው።—w19.08 ከገጽ 15-17

ኢየሱስ በማቴዎስ 11:28 ላይ ቃል በገባው መሠረት እረፍት የምናገኘው እንዴት ነው?

አፍቃሪ የሆኑ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችና ከሁሉ የተሻሉ የሥራ ባልደረቦች ያሉን ከመሆኑም ሌላ ከሁሉ የተሻለ ሥራ ተሰጥቶናል።—w19.09 ገጽ 23

አምላክ የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስችል ፍላጎትና ኃይል የሚሰጠን እንዴት ነው? (ፊልጵ. 2:13)

የአምላክን ቃል ስናነብና ባነበብነው ነገር ላይ ስናሰላስል፣ አምላክ የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስችል ፍላጎትና ኃይል በመስጠት ለተግባር እንድንነሳሳ ያደርጋል። መንፈሱን በመስጠት ችሎታዎቻችንን እንድናሻሽል ሊረዳን ይችላል።—w19.10 ገጽ 21

ከባድ ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት የትኞቹን እርምጃዎች መውሰዳችን ይጠቅመናል?

ልንወስዳቸው የምንችላቸው አምስት እርምጃዎች፦ የተሟላ መረጃ ለማግኘት ጥረት ማድረግ፣ ጥበብ ለማግኘት መጸለይ፣ የተነሳሳንበትን ዓላማ መገምገም፣ በግልጽ የተቀመጠ ግብ መያዝ እና ምክንያታዊ መሆን ናቸው።—w19.11 ከገጽ 27-29

ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት ሰይጣን በኤደን ለሔዋን ከነገራት ነገር የመነጨ ነው?

አይመስልም። ሰይጣን ለሔዋን የነገራት እንደማትሞት እንጂ በሥጋ የሞተች ቢመስልም ከእሷ የሚወጣ አንድ የማይታይ ነገር በሌላ ቦታ መኖሩን እንደሚቀጥል አይደለም። የተሳሳተ ሃይማኖታዊ ትምህርት የሚያስተምሩ ሰዎች ከጥፋት ውኃ አላለፉም። የማትሞት ነፍስ እንዳለች የሚገልጸው እምነት የመጣው፣ አምላክ የባቤልን ግንብ ይሠሩ የነበሩት ሰዎች በመላው ምድር ላይ እንዲበተኑ ከማድረጉ በፊት ሳይሆን አይቀርም።—w19.12 ገጽ 15