በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 52

ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወዱ አሠልጥኗቸው

ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወዱ አሠልጥኗቸው

“ልጆች ከይሖዋ የተገኙ ውርሻ ናቸው።”—መዝ. 127:3

መዝሙር 134 ልጆች ከአምላክ በአደራ የተሰጡ ናቸው

ማስተዋወቂያ *

1. ይሖዋ ለወላጆች የትኛውን ኃላፊነት በአደራ ሰጥቷቸዋል?

ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት የፈጠራቸው ልጅ የመውለድ ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርጎ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ልጆች ከይሖዋ የተገኙ ውርሻ ናቸው” የሚለው ለዚህ ነው። (መዝ. 127:3) ይህ ምን ማለት ነው? አንድ የቅርብ ወዳጃችሁ በርከት ያለ ገንዘብ እንድታስቀምጡለት በአደራ ሰጣችሁ እንበል። ምን ይሰማችኋል? ይህ ወዳጃችሁ እምነት ስለጣለባችሁ ደስ እንደሚላችሁ የታወቀ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በአደራ የተሰጣችሁን ገንዘብ አስተማማኝ ቦታ ላይ የማስቀመጡ ጉዳይ ያሳስባችሁ ይሆናል። ከማንም በላይ የቅርብ ወዳጃችን የሆነው ይሖዋ ከገንዘብ የላቀ ዋጋ ያለውን ሀብት ለወላጆች በአደራ ሰጥቷቸዋል፤ ይህ አደራ፣ ልጆችን የመንከባከብና ደስተኛ እንዲሆኑ አድርጎ የማሳደግ ኃላፊነት ነው።

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 ‘ልጅ እንውለድ ወይስ አንውለድ? የምንወልድ ከሆነስ መቼ?’ የሚለውን ጉዳይ መወሰን ያለበት ማን ነው? ወላጆች፣ ልጆቻቸው ደስተኛ እንዲሆኑ ለመርዳት ምን ማድረግ ይችላሉ? ክርስቲያን ባለትዳሮች በዚህ ረገድ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ማድረግ እንዲችሉ የሚረዷቸውን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እስቲ እንመልከት።

የባለትዳሮችን ውሳኔ ማክበር

3. (ሀ) ባለትዳሮች ልጅ መውለድ ይኖርባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ያለበት ማን ነው? (ለ) የአንድ ባልና ሚስት ጓደኞችና ቤተሰቦች የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ማስታወስ ይኖርባቸዋል?

3 በአንዳንድ ባሕሎች፣ አንድ ወንድና ሴት ከተጋቡ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ልጅ እንዲወልዱ ይጠበቅባቸዋል። ባልና ሚስቱ፣ የቤተሰባቸው አባላት ወይም ሌሎች ሰዎች ይህን ባሕል እንዲከተሉ ጫና እንዳደረጉባቸው ይሰማቸው ይሆናል። ጄትሮ የተባለ በእስያ የሚኖር አንድ ወንድም “በጉባኤያችን ውስጥ የሚገኙ ልጅ ያላቸው አንዳንድ ባለትዳሮች፣ ልጅ የሌላቸውን ባልና ሚስት እንዲወልዱ ይገፋፏቸዋል” ሲል ተናግሯል። ጄፍሪ የተባለ በእስያ የሚገኝ ሌላ ወንድም ደግሞ ያስተዋለውን ሲናገር “አንዳንዶች ልጅ ላልወለዱ ባለትዳሮች፣ ሲያረጁ የሚጦራቸው እንደሌለ ይነግሯቸዋል” ብሏል። ያም ሆኖ ልጅ መውለድ ይኖርባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ያለባቸው ባለትዳሮቹ ራሳቸው ናቸው። አዎ፣ ይህን ውሳኔ ማድረግ የእነሱ ኃላፊነት ነው። (ገላ. 6:5) እርግጥ ነው፣ የአዲስ ተጋቢዎቹ ጓደኞችና ቤተሰቦች ባለትዳሮቹ ደስተኛ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። ሆኖም እነዚህ ሰዎች፣ ልጅ መውለድን ወይም አለመውለድን በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ ያለባቸው ራሳቸው ጥንዶቹ እንደሆኑ ማስታወስ አለባቸው።—1 ተሰ. 4:11

4-5. ልጅ ከመውለድ ጋር በተያያዘ በየትኞቹ ሁለት ጉዳዮች ላይ መወያየት ያስፈልጋል? ይህን ውይይት ለማድረግ የተሻለው ጊዜስ መቼ ነው? አብራራ።

4 ልጅ ለመውለድ የወሰኑ ባልና ሚስት፣ ‘መውለድ ያለብን መቼ ነው? እንዲኖረን የምንፈልገውስ ስንት ልጅ ነው?’ በሚሉት ሁለት አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ጥሩ ይሆናል። ታዲያ እንዲህ ያለውን ውይይት ለማድረግ የተሻለው ጊዜ መቼ ነው? እነዚህ ሁለት ጉዳዮች ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል የምንለውስ ለምንድን ነው?

5 አብዛኛውን ጊዜ ‘ልጅ እንውለድ ወይስ አንውለድ’ የሚለው ጉዳይ መወሰን ያለበት ትዳር ከመመሥረቱ በፊት ነው። ይህ ጊዜ ለውሳኔ የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት፣ ተጋቢዎቹ በዚህ ረገድ ተመሳሳይ አቋም መያዛቸው በጣም አስፈላጊ መሆኑ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ይህን ኃላፊነት ለመሸከም ዝግጁ መሆን አለመሆናቸውን መወያየት ያስፈልጋቸዋል። አንዳንዶች ከተጋቡ በኋላ ልጅ ሳይወልዱ ቢያንስ ለአንድ ወይም ለሁለት ዓመት ለመቆየት ወስነዋል፤ ምክንያቱም ልጆችን መንከባከብ ብዙ ጊዜና ጉልበት ይጠይቃል። ስለዚህ ልጅ ሳይወልዱ ለተወሰነ ጊዜ መቆየታቸው የትዳር ሕይወት ከሚያስከትለው ለውጥ ጋር ለመላመድና እርስ በርስ ይበልጥ ለመቀራረብ እንደሚያስችላቸው ይሰማቸዋል።—ኤፌ. 5:33

6. አንዳንድ ባለትዳሮች ያለንበትን ዘመን ግምት ውስጥ በማስገባት ምን ውሳኔ አድርገዋል?

6 ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ የኖኅ ሦስት ልጆችና ሚስቶቻቸው የተዉትን ምሳሌ ለመከተል መርጠዋል። እነዚያ ሦስት ጥንዶች እንደተጋቡ ወዲያውኑ ልጅ አልወለዱም። (ዘፍ. 6:18፤ 9:18, 19፤ 10:1፤ 2 ጴጥ. 2:5) ኢየሱስ ያለንበትን ጊዜ ‘ከኖኅ ዘመን’ ጋር አመሳስሎታል፤ ደግሞም የምንኖረው ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን’ ውስጥ ነው። (ማቴ. 24:37፤ 2 ጢሞ. 3:1) አንዳንድ ባለትዳሮች ይህን እውነታ ግምት ውስጥ በማስገባት ልጅ ሳይወልዱ ለመቆየት መርጠዋል፤ ይህም በክርስቲያናዊ አገልግሎት ሰፋ ያለ ጊዜ ለማሳለፍ አስችሏቸዋል።

ጥበበኛ የሆኑ ባልና ሚስት ልጅ ለመውለድ ወይም ላለመውለድ እንዲሁም ስንት ልጅ እንደሚወልዱ ሲወስኑ ‘ወጪያቸውን ያሰላሉ’ (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት) *

7. ባለትዳሮች በሉቃስ 14:28, 29 እንዲሁም በምሳሌ 21:5 ላይ ከሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

7 ጥበበኛ የሆኑ ባለትዳሮች ልጅ መውለድ ይኖርባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ እንዲሁም ስንት ልጅ መውለድ እንደሚፈልጉ ከመወሰናቸው በፊት ‘ወጪያቸውን ያሰላሉ።’ (ሉቃስ 14:28, 29ን አንብብ።) ብዙ ወላጆች፣ ልጅ ማሳደግ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ጊዜና ጉልበትም እንደሚጠይቅ ያውቃሉ። ስለዚህ አንድ ባልና ሚስት እንደሚከተሉት ባሉ ጥያቄዎች ላይ መወያየታቸው አስፈላጊ ነው፦ ‘የቤተሰቡን መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ሁለታችንም መሥራት ይጠበቅብናል? መሠረታዊ ፍላጎት የምንላቸው ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ተስማምተናል? ሁለታችንም መሥራት ካለብን ልጆቻችንን የሚንከባከበው ማን ነው? የልጆቻችንን አስተሳሰብና ድርጊት የሚቀርጸው ማን ይሆናል?’ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ በቁም ነገር የሚወያዩ ባልና ሚስት በምሳሌ 21:5 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ያደርጋሉ።—ጥቅሱን አንብብ።

አፍቃሪ የሆነ ባል ሚስቱን ለማገዝ የሚችለውን ያደርጋል (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት)

8. ክርስቲያን ባለትዳሮች የትኞቹ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሟቸው መጠበቅ ይኖርባቸዋል? አንድ አፍቃሪ ባል ምን ማድረግ ይችላል?

8 ልጆችን መንከባከብ ብዙ ጊዜና ጉልበት ይጠይቃል፤ ደግሞም ወላጆች ለልጆቻቸው እንዲህ ማድረጋቸው ተገቢ ነው። ስለዚህ ባለትዳሮች በላይ በላዩ የሚወልዱ ከሆነ ለእያንዳንዱ ልጅ የሚያስፈልገውን ትኩረት ለመስጠት ሊቸገሩ ይችላሉ። አከታትለው ልጆች የወለዱ አንዳንድ ባለትዳሮች ነገሮች ከአቅማቸው በላይ ሆነውባቸው እንደነበር ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። አንዲት እናት ኃይሏ እንደተሟጠጠና እንደዛለች ሊሰማት ይችላል። ይህ ደግሞ አዘውትራ ለማጥናት፣ ለመጸለይና በአገልግሎት ለመካፈል የሚያስችል ብርታት እንዳይኖራት ሊያደርግ ይችላል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥመው ሌላው ተፈታታኝ ነገር ደግሞ በስብሰባዎች ላይ በትኩረት ማዳመጥ አለመቻል ነው። እርግጥ ነው፣ አፍቃሪ የሆነ አንድ ባል በስብሰባ ላይም ሆነ ቤት ውስጥ ልጆቻቸውን በመንከባከብ ረገድ ሚስቱን ለማገዝ የሚችለውን ያደርጋል። ለምሳሌ፣ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት ሚስቱን ሊረዳት ይችላል። ሁሉንም ሊጠቅም የሚችል ቋሚ የሆነ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም እንዲኖር ለማድረግ ጠንክሮ ይሠራል። በተጨማሪም ክርስቲያን አባቶች ከቤተሰባቸው አባላት ጋር አዘውትረው በአገልግሎት ይካፈላሉ።

ልጆች ይሖዋን እንዲወዱ ማስተማር

9-10. ልጆቻቸውን መርዳት የሚፈልጉ ወላጆች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

9 ወላጆች፣ ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱ ለማስተማር ማድረግ የሚችሏቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ልጆቻቸውን ከመጥፎ ተጽዕኖ መጠበቅ የሚችሉትስ እንዴት ነው? ወላጆች ሊያደርጓቸው የሚችሉ አንዳንድ ነገሮችን እስቲ እንመልከት።

10 የይሖዋን እርዳታ በጸሎት ጠይቁ። የሳምሶን ወላጆች የሆኑት ማኑሄና ሚስቱ የተዉትን ምሳሌ ለማስተዋል ሞክሩ። ማኑሄ እሱና ሚስቱ ልጅ ሊያገኙ እንደሆነ ሲያውቅ፣ ልጁን እንዴት ማሳደግ እንዳለባቸው የሚገልጽ መመሪያ ለማግኘት ይሖዋን ተማጽኗል።

11. ወላጆች በመሳፍንት 13:8 ላይ የተገለጸውን የማኑሄን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

11 በቦስኒያ እና ሄርዘጎቪና የሚኖሩት ኒሆድና ኦልሞ፣ የማኑሄን ምሳሌ ተከትለዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “ጥሩ ወላጆች መሆን ስለምንችልበት መንገድ መመሪያ እንዲሰጠን ልክ እንደ ማኑሄ ይሖዋን ተማጸንነው። ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በጽሑፎቻችን እንዲሁም በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች አማካኝነት ለጸሎታችን መልስ ሰጥቶናል።”መሳፍንት 13:8ን አንብብ።

12. ዮሴፍና ማርያም ለልጆቻቸው ምን ምሳሌ ትተዋል?

12 ምሳሌ በመሆን አስተምሯቸው። ወላጆች በአንደበታችሁ ለልጃችሁ ብዙ ትምህርት መስጠት ትችላላችሁ፤ ሆኖም በልጃችሁ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ተግባራችሁ ነው። ዮሴፍና ማርያም፣ ኢየሱስን ጨምሮ ለሁሉም ልጆቻቸው ግሩም ምሳሌ እንደነበሩ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ዮሴፍ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ለማቅረብ ተግቶ ይሠራ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ቤተሰቡ ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት እንዲኖረው ለማድረግ ይጥር ነበር። (ዘዳ. 4:9, 10) በሙሴ ሕግ መሠረት፣ ዮሴፍ “በየዓመቱ” በሚከበረው የፋሲካ በዓል ላይ ለመገኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ መላ ቤተሰቡን ይዞ መጓዝ አይጠበቅበትም፤ እሱ ግን እንዲህ ያደርግ ነበር። (ሉቃስ 2:41, 42) በዚያ ጊዜ የነበሩ አንዳንድ አባቶች መላውን ቤተሰብ ይዞ እንዲህ ያለ ጉዞ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ፣ ጊዜ የሚፈጅና ብዙ ገንዘብ የሚያስወጣ እንደሆነ ተሰምቷቸው ይሆናል። ዮሴፍ ግን ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት ነበረው፤ ልጆቹም እንዲህ እንዲያደርጉ ያስተምራቸው ነበር። ማርያምም ብትሆን ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ ታውቅ ነበር። ልጆቿ የአምላክን ቃል እንዲወዱ በቃልም ሆነ በተግባር እንዳስተማረቻቸው ምንም ጥርጥር የለውም።

13. አንድ ባልና ሚስት፣ የዮሴፍንና የማርያምን ምሳሌ የተከተሉት እንዴት ነው?

13 ቀደም ሲል የተጠቀሱት ኒሆድና ኦልሞ፣ ዮሴፍና ማርያም የተዉትን ምሳሌ ለመከተል ጥረት አድርገዋል። ታዲያ ይህ ጥረታቸው ልጃቸው ይሖዋን እንዲወድና እሱን የማገልገል ፍላጎት እንዲያድርበት በማድረግ ረገድ የረዳቸው እንዴት ነው? እንዲህ ብለዋል፦ “ከይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምቶ መኖር ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ በአኗኗራችን ለማሳየት ጥረት አድርገናል።” ኒሆድ አክሎ “እናንተ ራሳችሁ፣ ልጃችሁ እንዲሆን የምትፈልጉትን ዓይነት ሰው ሁኑ” ብሏል።

14. ወላጆች ልጆቻቸው ከእነማን ጋር እንደሚቀራረቡ ማወቅ ያለባቸው ለምንድን ነው?

14 ልጆቻችሁ ጥሩ ጓደኞች እንዲመርጡ እርዷቸው። እናቶችም ሆኑ አባቶች፣ ልጆቻቸው ከእነማን ጋር እንደሚቀራረቡና ከእነሱ ጋር ሲሆኑ ምን እንደሚያደርጉ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ይህም ልጆቻቸው በማኅበራዊ ድረ ገጾችና በሞባይል ስልኮቻቸው አማካኝነት ከእነማን ጋር እንደሚገናኙ ማወቅን ይጨምራል። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በልጆቹ አስተሳሰብና ድርጊት ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም።—1 ቆሮ. 15:33

15. ወላጆች ጄሲ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

15 ወላጆች ስለ ኮምፒውተር ወይም ስለ ሞባይል ስልክ ያላቸው እውቀት ውስን ከሆነ ምን ማድረግ ይችላሉ? በፊሊፒንስ የሚኖር ጄሲ የተባለ አባት እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ቴክኖሎጂ ያን ያህል እውቀት የለንም። ይህ ግን የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን መጠቀም ሊኖረው ስለሚችለው አደጋ ልጆቻችን እንዲያውቁ ከመርዳት አላገደንም።” ጄሲ ስለ ቴክኖሎጂ ያለው እውቀት ውስን ስለሆነ ብቻ ልጆቹን በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች እንዳይጠቀሙ አልከለከላቸውም። ጄሲ “ልጆቼ በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻቸው ተጠቅመው አዲስ ቋንቋ እንዲማሩ፣ ለስብሰባ እንዲዘጋጁ እንዲሁም በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነብቡ አበረታታቸው ነበር” በማለት ተናግሯል። እናንት ወላጆች፣ የጽሑፍ መልእክት መላላክን ወይም ኢንተርኔት ላይ ፎቶዎችን ማውጣትን በተመለከተ በjw.org® ላይ “ለወጣቶች” በሚለው ርዕስ ሥር የሚገኘውን ሚዛናዊ የሆነ ሐሳብ ከልጆቻችሁ ጋር አንብባችሁ ተወያይታችሁበታል? በተጨማሪም የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ሕይወትህን እየተቆጣጠሩት ነው? እና ማኅበራዊ ድረ ገጾችን ስትጠቀም አስተዋይ ሁን የሚሉትን ቪዲዮዎች ከልጆቻችሁ ጋር አይታችሁ ለመወያየት ሞክሯችኋል? እነዚህ ነገሮች ልጆቻችሁ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በጥበብ እንዲጠቀሙ በምታስተምሩበት ጊዜ ትልቅ እገዛ ያደርጉላችኋል። *ምሳሌ 13:20

16. ብዙ ወላጆች ምን አድርገዋል? ምን ውጤትስ አግኝተዋል?

16 ብዙ ወላጆች፣ ልጆቻቸው አምላክን በማገልገል ረገድ ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኑ ክርስቲያኖች ጋር መቀራረብ የሚችሉበትን አጋጣሚ ለመፍጠር ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በኮት ዲቩዋር የሚኖሩት ነደኒ እና ቦሚን የተባሉ ባልና ሚስት፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ብዙ ጊዜ ቤታቸው እንዲያርፍ ያደርጉ ነበር። ነደኒ “ይህ በልጃችን ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ከጊዜ በኋላ ልጃችን አቅኚነት ጀመረ፤ አሁን ደግሞ ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ እያገለገለ ነው” ሲል ተናግሯል። እናንተስ ልጆቻችሁ ጥሩ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ትችሉ ይሆን?

17-18. ወላጆች ለልጆቻቸው የሚሰጡትን ሥልጠና መጀመር ያለባቸው መቼ ነው?

17 ሥልጠናውን ገና ከልጅነታቸው ጀምሩ። ወላጆች ልጆቻቸውን ገና ከሕፃንነታቸው ማሠልጠን መጀመራቸው የተሻለ ነው። (ምሳሌ 22:6) ከጊዜ በኋላ የሐዋርያው ጳውሎስ የጉዞ አጋር የሆነውን የጢሞቴዎስን ሁኔታ ለማሰብ ሞክሩ። እናቱ ኤውንቄ እና አያቱ ሎይድ ጢሞቴዎስን ‘ከጨቅላነቱ’ ጀምሮ አሠልጥነውታል።—2 ጢሞ. 1:5፤ 3:15

18 በኮት ዲቩዋር የሚኖሩት ዦን ክሎድ እና ፒስ የተባሉ ሌላ ባልና ሚስት ደግሞ ስድስቱም ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱና እሱን የማገልገል ፍላጎት እንዲያድርባቸው አድርገው ማሳደግ ችለዋል። ስኬታማ እንዲሆኑ የረዳቸው ምንድን ነው? የኤውንቄንና የሎይድን ምሳሌ መከተላቸው ነው። እነዚህ ባልና ሚስት “የአምላክን ቃል በልጆቻችን ልብ ውስጥ መቅረጽ የጀመርነው ከጨቅላነታቸው አንስቶ ማለትም ከተወለዱ ብዙም ሳይቆይ ነበር” ብለዋል።—ዘዳ. 6:6, 7

19. የአምላክን ቃል በልጆቻችሁ ውስጥ መቅረጽ ሲባል ምን ማለት ነው?

19 የይሖዋን ቃል በልጆቻችሁ ውስጥ ‘መቅረጽ’ ሲባል ምን ማለት ነው? ‘መቅረጽ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ደግሞ ደጋግሞ በመናገር ማስተማርና ማስገንዘብ” የሚል መልእክት አለው። ይህን ለማድረግ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አዘውትረው ጊዜ ማሳለፍ አለባቸው። መመሪያዎችን ለልጆች ደጋግሞ መናገር አንዳንድ ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ወላጆች፣ ልጆቻቸው የአምላክን ቃል እንዲያስተውሉና ተግባራዊ እንዲያደርጉ መርዳት የሚችሉት በዚህ መንገድ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርባቸዋል።

ወላጆች እያንዳንዱ ልጅ ምን ዓይነት ሥልጠና እንደሚያስፈልገው መለየት ይኖርባቸዋል (አንቀጽ 20⁠ን ተመልከት) *

20. በመዝሙር 127:4 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ልጆችን ከማሳደግ ጋር በተያያዘ የሚሠራው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

20 አስተዋይ ሁኑ። መዝሙር 127 ልጆችን ከፍላጻዎች ጋር ያመሳስላቸዋል። (መዝሙር 127:4ን አንብብ።) ፍላጻዎች የሚሠሩበት ነገርም ሆነ መጠናቸው እንደሚለያይ ሁሉ ሁለት ልጆችም ፍጹም አንድ ዓይነት ሊሆኑ አይችሉም። ስለዚህ ወላጆች እያንዳንዱ ልጅ ምን ዓይነት ሥልጠና እንደሚያስፈልገው መለየት አለባቸው። የይሖዋ አገልጋዮች የሆኑ ሁለት ልጆች ያሏቸው በእስራኤል የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት ጠቃሚ ሆኖ ያገኙትን ነገር ሲናገሩ “እያንዳንዱን ልጅ በተናጠል መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠናለን” ብለዋል። እርግጥ ነው፣ በዚህ መንገድ ልጆችን ማስጠናት አስፈላጊና የሚቻል ነገር መሆን አለመሆኑን መወሰን የእያንዳንዱ የቤተሰብ ራስ ኃላፊነት ነው።

ይሖዋ ይረዳችኋል

21. ይሖዋ ወላጆችን ለመርዳት የትኞቹን ዝግጅቶች አድርጓል?

21 አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸውን ማስተማር ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ሆኖም ልጆችን ስጦታ አድርጎ ለወላጆች የሰጠው ይሖዋ ስለሆነ እነሱን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ ነው። ይሖዋ ወላጆች የሚያቀርቡትን ጸሎት ለማዳመጥ ፈቃደኛ ነው። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በጽሑፎቻችን እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ በመንፈሳዊ የጎለመሱና ምሳሌ የሚሆኑ ሌሎች ወላጆች በሚሰጡት ምክር አማካኝነት ጸሎታቸውን ይመልስላቸዋል።

22. ወላጆች ለልጆቻቸው መስጠት ከሚችሏቸው ውድ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

22 ‘ልጅ ማሳደግ የ20 ዓመት ፕሮጀክት ነው’ ሲባል እንሰማለን፤ ሆኖም ወላጅ ምንጊዜም ወላጅ ነው። ወላጆች ለልጆቻቸው መስጠት ከሚችሏቸው ውድ ነገሮች መካከል ፍቅር፣ ጊዜና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ሥልጠና ይገኙበታል። እያንዳንዱ ልጅ ለሥልጠናው የሚሰጠው ምላሽ ይለያያል። ሆኖም ይሖዋን የሚወዱ ወላጆች ያሳደጓቸው በርካታ ልጆች በእስያ እንደምትኖረው እንደ ጆአኖ ማ ይሰማቸዋል፤ እንዲህ ብላለች፦ “ከወላጆቼ ስላገኘሁት ሥልጠና መለስ ብዬ ሳስብ በጣም አመስጋኝ ነኝ፤ ወላጆቼ ተግሣጽ ሰጥተውኛል፤ ይሖዋን እንድወደው አስተምረውኛል። ስለወለዱኝ ብቻ ሳይሆን ትርጉም ያለው ሕይወት እንድመራ ስለረዱኝም አመስጋኝ ነኝ።” (ምሳሌ 23:24, 25) በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ክርስቲያኖችም የእሷን ስሜት ይጋራሉ።

መዝሙር 59 ያህን አብረን እናወድስ

^ አን.5 ባለትዳሮች ልጅ መውለድ ያስፈልጋቸዋል? ለመውለድ ከወሰኑ ስንት ልጅ ሊኖራቸው ይገባል? ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱትና እሱን እንዲያገለግሉት ማሠልጠን የሚችሉትስ እንዴት ነው? ይህ ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችንና በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ ወላጆች የሰጡትን ሐሳብ ይዟል።

^ አን.15 በተጨማሪም ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1 ምዕ. 36⁠ን እና ጥራዝ 2 ምዕ. 11⁠ን ተመልከት።

^ አን.60 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ባልና ሚስት ‘ልጅ እንውለድ?’ በሚለው ጉዳይ ላይ እየተወያዩ ነው፤ ልጅ መውለድ የሚያስገኘውን ደስታና የሚያስከትለውን ኃላፊነት ከግምት አስገብተዋል

^ አን.64 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ባልና ሚስት የልጆቻቸውን ዕድሜና ችሎታ ግምት ውስጥ በማስገባት በተናጠል ሲያስጠኗቸው።