በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 50

ይሖዋ ነፃ የምንወጣበት ዝግጅት አድርጎልናል

ይሖዋ ነፃ የምንወጣበት ዝግጅት አድርጎልናል

“በምድሪቱም ለሚኖሩ ሁሉ ነፃነት አውጁ።”—ዘሌ. 25:10

መዝሙር 22 በሰማይ የተቋቋመው መንግሥት ይምጣልን!

ማስተዋወቂያ *

1-2. (ሀ) ኢዮቤልዩ ምንድን ነው? (“ ኢዮቤልዩ ምን ዓይነት በዓል ነበር?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) በሉቃስ 4:16-18 ላይ ኢየሱስ ስለ ምን ተናግሯል?

በአንዳንድ አገሮች፣ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ክንውኖች 50ኛ ዓመት ማክበር የተለመደ ነው፤ ይህ በዓል ኢዮቤልዩ ተብሎ ይጠራል። ክብረ በዓሉ ለአንድ ቀን፣ ለሳምንት ወይም ከዚያ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆይ ይችላል፤ ሆኖም የሚያበቃበት ጊዜ አለው፤ በዓሉ የሚያስገኘው ደስታም ቢሆን ብዙም ሳይቆይ ይረሳል።

2 በዚህ ርዕስ ውስጥ ከዚህ ስለሚልቅ ኢዮቤልዩ እንመረምራለን፤ ይህ ኢዮቤልዩ በጥንቷ እስራኤል ውስጥ በየ50 ዓመቱ ይከበር ከነበረውና ለአንድ ዓመት ከሚቆየው ኢዮቤልዩም የላቀ ነው። በጥንቷ እስራኤል ይከበር የነበረው ኢዮቤልዩ ለሕዝቡ ነፃነት ያስገኝ ነበር። ይሁንና ስለዚህ ኢዮቤልዩ ማወቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? የእስራኤላውያን ኢዮቤልዩ፣ ይሖዋ ዘላቂ ነፃነት እንድናገኝ ሲል ያደረገውንና አሁንም እየጠቀመን ያለውን አስደናቂ ዝግጅት ስለሚያስታውሰን ነው፤ ኢየሱስም ስለዚህ ነፃነት ተናግሯል።ሉቃስ 4:16-18ን አንብብ።

የእስራኤላውያን ኢዮቤልዩ፣ ባሪያዎች ወደ ቤተሰባቸውና ወደ ርስታቸው የሚመለሱበት አስደሳች ወቅት ነበር (አንቀጽ 3⁠ን ተመልከት) *

3. በዘሌዋውያን 25:8-12 ላይ እንደተገለጸው ኢዮቤልዩ ለእስራኤላውያን ምን ጥቅም ያስገኝ ነበር?

3 ኢየሱስ ነፃ ስለ መውጣት ሲናገር ምን ማለቱ እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንልን፣ በመጀመሪያ አምላክ ለጥንት ሕዝቦቹ ስላደረገው የኢዮቤልዩ ዝግጅት እንመርምር። ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ሃምሳኛውን ዓመት ቀድሱ፤ በምድሪቱም ለሚኖሩ ሁሉ ነፃነት አውጁ። ለእናንተ ኢዮቤልዩ ይሆንላችኋል፤ ከእናንተ እያንዳንዱ ወደየርስቱ ይመለሳል፤ ከእናንተም እያንዳንዱ ወደየቤተሰቡ ይመለስ።” (ዘሌዋውያን 25:8-12ን አንብብ።) ሳምንታዊው ሰንበት እስራኤላውያንን እንዴት እንደጠቀማቸው ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ተመልክተናል። ኢዮቤልዩስ እስራኤላውያንን የጠቀማቸው እንዴት ነበር? ዕዳ ውስጥ የገባን አንድ እስራኤላዊ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህ ሰው ዕዳውን ለመክፈል ሲል መሬቱን ለመሸጥ ተገደደ። በኢዮቤልዩ ዓመት ይህ ሰው መሬቱ ይመለስለታል። በመሆኑም ሰውየው ‘ወደ ርስቱ ይመለሳል’፤ ለልጆቹ የሚያወርሰው ርስትም ይኖረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ እስራኤላዊ ያለበትን ዕዳ ለመክፈል ሲል ከልጆቹ አንዱን ወይም ራሱን ለባርነት ይሸጥ ይሆናል። በኢዮቤልዩ ዓመት ግን ባሪያ ሆኖ የተሸጠው ሰው ‘ወደ ቤተሰቡ ይመለሳል።’ በመሆኑም ነፃ የመውጣት አጋጣሚ ሳይኖረው ለዘላለም ባሪያ ሆኖ የሚቀር ሰው አይኖርም! ይሖዋ እንዴት ያለ አሳቢ አምላክ ነው!

4-5. በጥንት ጊዜ ስለነበረው የኢዮቤልዩ ዝግጅት መመርመር ያለብን ለምንድን ነው?

4 ኢዮቤልዩ የሚያስገኘው ሌላ ጥቅም ምን ነበር? ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርገህ እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር ላይ ይሖዋ ስለሚባርክህ ከእናንተ መካከል ማንም ድሃ አይሆንም።” (ዘዳ. 15:4) ይህ ሁኔታ፣ በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው ልዩነት በጣም እየሰፋ በሚሄድበት በዚህ ዓለም ላይ ከሚታየው ነገር ምንኛ የተለየ ነው!

5 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በሙሴ ሕግ ሥር አይደለንም። በመሆኑም ባሪያዎች ነፃ እንዲወጡ፣ ዕዳ እንዲሰረዝና ርስት ለባለቤቱ እንዲመለስ የሚያደርገውን የጥንቱን የኢዮቤልዩ ዝግጅት አንከተልም። (ሮም 7:4፤ 10:4፤ ኤፌ. 2:15) ያም ቢሆን ስለዚህ ዝግጅት መመርመራችን ይጠቅመናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ይሖዋ እኛም ነፃነት የምናገኝበት ዝግጅት ስላደረገልን ነው፤ ይህ ዝግጅት ይሖዋ ለጥንት እስራኤላውያን ያቋቋመውን የኢዮቤልዩ በዓል ያስታውሰናል።

ኢየሱስ ነፃነትን አውጇል

6. የሰው ዘር ከየትኛው ባርነት ነፃ መውጣት ያስፈልገዋል?

6 ሁላችንም ከሁሉ በከፋው ባርነት ይኸውም በኃጢአት ባርነት ሥር ስለሆንን ነፃ መውጣት ያስፈልገናል። ኃጢአተኞች በመሆናችን እናረጃለን፣ እንታመማለን እንዲሁም እንሞታለን። ብዙዎች በመስታወት መልካቸውን ሲመለከቱ ወይም ሐኪም ጋ ሲሄዱ ይህ እውነታ ቁልጭ ብሎ ይታያቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ኃጢአት የምንሠራ መሆናችን ተስፋ እንድንቆርጥ ያደርገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “[በሰውነቱ] ውስጥ ላለው የኃጢአት ሕግ ምርኮኛ” እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። አክሎም “እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! እንዲህ ወዳለው ሞት ከሚመራኝ ሰውነት ማን ይታደገኛል?” ብሏል።—ሮም 7:23, 24

7. ኢሳይያስ ነፃነትን በተመለከተ ምን ትንቢት ተናግሮ ነበር?

7 ደስ የሚለው ነገር አምላክ ከኃጢአት ነፃ የምንወጣበት ዝግጅት አድርጎልናል። ይህን ነፃነት እንድናገኝ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው ኢየሱስ ነው። በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነቢዩ ኢሳይያስ ወደፊት ስለሚኖር ታላቅ ነፃነት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር፤ ይህ ታላቅ ነፃነት የእስራኤላውያን የኢዮቤልዩ ዓመት ከሚያስገኘው ነፃነት እጅግ የላቀ ነው። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የሉዓላዊው ጌታ የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋ የዋህ ለሆኑ ሰዎች ምሥራች እንድናገር ቀብቶኛል። ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣ ለተማረኩት ነፃነትን እንዳውጅ . . . ልኮኛል።” (ኢሳ. 61:1) ይህ ትንቢት የሚናገረው ስለ ማን ነው?

8. ኢሳይያስ ስለ ነፃነት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በማን ላይ ነው?

8 ስለ ነፃነት የሚናገረው ይህ አስፈላጊ ትንቢት ፍጻሜውን ማግኘት የጀመረው ኢየሱስ አገልግሎቱን ከጀመረ በኋላ ነው። ኢየሱስ ባደገበት በናዝሬት ከተማ ወደሚገኝ አንድ ምኩራብ በገባበት ወቅት በዚያ ለተሰበሰቡት አይሁዳውያን ይህን የኢሳይያስ ትንቢት አንብቦላቸው ነበር። ትንቢቱን ካነበበ በኋላም ትንቢቱ በእሱ ላይ ፍጻሜውን እንዳገኘ ገለጸ፦ “የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ምክንያቱም ለድሆች ምሥራች እንድናገር ቀብቶኛል። ለተማረኩት ነፃነትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቆኑትን ነፃ እንዳወጣ እንዲሁም የይሖዋን ሞገስ ስለሚያገኙበት ዓመት እንድሰብክ ልኮኛል።” (ሉቃስ 4:16-19) ታዲያ ኢየሱስ ይህ ትንቢት እንዲፈጸም ያደረገው እንዴት ነው?

በመጀመሪያ ነፃ የወጡት እነማን ናቸው?

ኢየሱስ በናዝሬት በሚገኘው ምኩራብ ነፃነት አውጇል (ከአንቀጽ 8-9⁠ን ተመልከት)

9. በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ብዙ ሰዎች ምን ዓይነት ነፃነት ለማግኘት ይጓጉ ነበር?

9 ኢሳይያስ አስቀድሞ የተናገረለትና ኢየሱስ ያነበበው ስለ ነፃነት የሚገልጸው ትንቢት ፍጻሜውን ማግኘት የጀመረው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ነው። ኢየሱስ “ይህ አሁን የሰማችሁት የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል ዛሬ ተፈጸመ” ብሎ መናገሩ ይህን ያረጋግጣል። (ሉቃስ 4:21) ኢየሱስ ትንቢቱን ሲያነብብ ካዳመጡት ሰዎች ብዙዎቹ፣ ፖለቲካዊ ለውጥ እንደሚመጣ ይኸውም ከሮም አገዛዝ ነፃ እንደሚወጡ ይጠብቁ የነበረ ይመስላል። “እኛ ግን ይህ ሰው እስራኤልን ነፃ ያወጣል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር” ብለው እንደተናገሩት ሁለት ሰዎች ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። (ሉቃስ 24:13, 21) ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ ተከታዮቹን እንደ ቀንበር በተጫናቸው የሮም አገዛዝ ላይ እንዲያምፁ አላበረታታቸውም። ከዚህ በተቃራኒ “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር” እንዲከፍሉ አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 22:21) ታዲያ ኢየሱስ በዚያ ወቅት ነፃነት ያመጣው እንዴት ነው?

10. ኢየሱስ ከምን ዓይነት ባርነት ነፃ መውጣት የሚቻልበትን መንገድ ከፍቷል?

10 የአምላክ ልጅ የመጣው ሰዎች ከሁለት ነገሮች ነፃ እንዲወጡ ለመርዳት ነው። አንደኛ፣ የሃይማኖት መሪዎቹ ከሚያስተምሯቸው በሕዝቡ ላይ ጫና የሚያሳድሩ ትምህርቶች ነፃ መውጣት የሚቻልበትን መንገድ ከፍቷል። በዚያ ዘመን የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን በተለያዩ ወጎችና በተሳሳቱ እምነቶች ባርነት ሥር ነበሩ። (ማቴ. 5:31-37፤ 15:1-11) መንፈሳዊ መመሪያ እንዲሰጡ የሚጠበቅባቸው ሰዎች ደግሞ ታውረው ነበር ማለት ይቻላል። መሲሑንና እሱ ያስገኘውን መንፈሳዊ ብርሃን ለመቀበል ፈቃደኞች ባለመሆናቸው በጨለማ ውስጥ እንዲሁም በኃጢአት ባርነት ሥር ለመኖር መርጠዋል። (ዮሐ. 9:1, 14-16, 35-41) ኢየሱስ ግን ትክክለኛ ትምህርቶችን በማስተማርና ጥሩ ምሳሌ በመተው፣ መንፈሳዊ ነፃነት የሚገኝበትን መንገድ ለቅኖች አሳውቋል።—ማር. 1:22፤ 2:23 እስከ 3:5

11. ኢየሱስ የሰው ዘርን ነፃ ያወጣበት ሁለተኛው መንገድ ምንድን ነው?

11 ሁለተኛ፣ ኢየሱስ የሰው ልጆች ከአዳም የወረሱት ኃጢአት ካስከተለባቸው ባርነት ነፃ መውጣት የሚችሉበትን መንገድ ከፍቷል። የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ስለተከፈለ አምላክ፣ እምነት ያላቸውንና እሱ ያዘጋጀውን ቤዛ የሚቀበሉ ሰዎችን ኃጢአት ይቅር ማለት ይችላል። (ዕብ. 10:12-18) ኢየሱስ “ወልድ ነፃ ካወጣችሁ፣ በእርግጥ ነፃ ትሆናላችሁ” ብሏል። (ዮሐ. 8:36) ይህ ነፃነት በእስራኤል ይከበር የነበረው የኢዮቤልዩ ዓመት ከሚያስገኘው ነፃነት እጅግ የላቀ እንደሆነ ጥርጥር የለውም! አንድ ምሳሌ እንውሰድ፦ በኢዮቤልዩ አማካኝነት ከባርነት ነፃ የወጣ ሰው መልሶ ባሪያ ሊሆን ይችላል፤ ደግሞም ይህ ሰው ከሞት ባርነት ማምለጥ አይችልም።

12. ኢየሱስ ካወጀው ነፃነት የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚዎች እነማን ናቸው?

12 በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት፣ ይሖዋ ሐዋርያትን እንዲሁም ሌሎች ታማኝ ወንዶችንና ሴቶችን በመንፈስ ቅዱስ ቀባቸው። ልጆቹ አድርጎ የተቀበላቸው ሲሆን ይህም ከጊዜ በኋላ ትንሣኤ አግኝተው በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ለመግዛት ያስችላቸዋል። (ሮም 8:2, 15-17) እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ በናዝሬት በሚገኘው ምኩራብ ካወጀው ነፃነት የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚዎች ናቸው። እነዚያ ወንዶችና ሴቶች፣ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ከሚያስተምሯቸው የሐሰት ትምህርቶችና ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ወጎች ባርነት ነፃ ወጥተዋል። በተጨማሪም አምላክ፣ እነዚህን ሰዎች ወደ ሞት ከሚመራው የኃጢአት ባርነት ነፃ እንደወጡ አድርጎ ቆጥሯቸዋል። ምሳሌያዊው ኢዮቤልዩ የጀመረው በ33 ዓ.ም. የክርስቶስ ተከታዮች በመንፈስ ቅዱስ ሲቀቡ ሲሆን በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ ያበቃል። ለመሆኑ ይህ ዝግጅት የሰው ልጆች የትኞቹን በረከቶች እንዲያገኙ ያደርጋል?

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎችም ነፃ ይወጣሉ

13-14. ኢየሱስ ያወጀውን ነፃነት ከቅቡዓን ክርስቲያኖች በተጨማሪ እነማንም ማግኘት ይችላሉ?

13 በዘመናችን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸውና ከብሔራት ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል ናቸው። (ዮሐ. 10:16) አምላክ እነዚህን ሰዎች በሰማይ ከኢየሱስ ጋር እንዲገዙ አልመረጣቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዳላቸው ይናገራል።

14 የአንተም ተስፋ ይህ ከሆነ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ክፍል የሚሆኑ ሰዎች የሚያገኟቸውን አንዳንድ በረከቶች በአሁኑ ወቅትም እያገኘህ ነው። በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ እምነት በማሳደር ይሖዋ ኃጢአትህን ይቅር እንዲልልህ መጠየቅ ትችላለህ። ይህም በአምላክ ፊት ጥሩ አቋም እንዲኖርህና ንጹሕ ሕሊና እንድታገኝ ይረዳሃል። (ኤፌ. 1:7፤ ራእይ 7:14, 15) ከዚህ ቀደም ታምንባቸው ከነበሩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ትምህርቶች ባርነት ነፃ መውጣትህ ስላስገኘልህ በረከቶችም ለማሰብ ሞክር። ኢየሱስ “እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ብሏል። (ዮሐ. 8:32) እንዲህ ያለ ነፃነት ማግኘት ምንኛ አስደሳች ነው!

15. ወደፊት ምን ዓይነት ነፃነትና በረከት እንደምናገኝ እንጠብቃለን?

15 ወደፊት ደግሞ ከዚህ የላቀ ነፃነት እንደምታገኝ መጠበቅ ትችላለህ። በቅርቡ ኢየሱስ የሐሰት ሃይማኖትንና ብልሹ የሆነውን ሰብዓዊ አገዛዝ ለማጥፋት እርምጃ ይወስዳል። አምላክ አገልጋዮቹ የሆኑትን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ከጥፋቱ የሚያድናቸው ሲሆን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ብዙ በረከቶችን እንዲያገኙ ያደርጋል። (ራእይ 7:9, 14) በዚያ ጊዜ ትንሣኤ የሚያገኙት በጣም ብዙ ሰዎች የአዳም ኃጢአት ካስከተላቸው ጉዳቶች ሁሉ ነፃ የመውጣት አጋጣሚ ያገኛሉ።—ሥራ 24:15

16. የሰው ልጆች ምን ታላቅ ነፃነት ያገኛሉ?

16 ኢየሱስና ተባባሪ ገዢዎቹ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት፣ የሰው ልጆች በአካላዊ ሁኔታ ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ እና የአምላክ ልጆች መሆን እንዲችሉ ያደርጋሉ። ይህ የተሃድሶና የነፃነት ጊዜ በእስራኤል ይከበር እንደነበረው ኢዮቤልዩ ይሆናል። በዚያ ወቅት፣ ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ፍጹም ይኸውም ከኃጢአት ሙሉ በሙሉ ነፃ ይሆናሉ።

በአዲሱ ዓለም ውስጥ ጠቃሚና እርካታ የሚያስገኝ ሥራ እናከናውናለን (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)

17. ኢሳይያስ 65:21-23 የአምላክን ሕዝብ በተመለከተ ምን ትንቢት ይዟል? (ሽፋኑን ተመልከት።)

17 በዚያን ጊዜ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖራቸው በኢሳይያስ 65:21-23 ላይ የሚገኘው ትንቢት ይገልጻል። (ጥቅሱን አንብብ።) ያ ዘመን ምንም ነገር ሳንሠራ እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥበት ጊዜ አይደለም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ጠቃሚና አርኪ የሆነ ሥራ እናከናውናለን። ይህ ጊዜ ሲያበቃ “ፍጥረት ራሱ . . . ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት” እንደሚያገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሮም 8:21

18. ወደፊት አስደሳች ጊዜ እንደሚጠብቀን እርግጠኞች የምንሆነው ለምንድን ነው?

18 ይሖዋ ለጥንት እስራኤላውያን እንዳደረገው ሁሉ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅትም ሕዝቦቹ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንዲሠሩና እንዲያርፉ ዝግጅት ያደርጋል። ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የሚመደብ ጊዜ እንደሚኖር ጥርጥር የለውም። አምላክን ማምለክ ለደስታችን የግድ አስፈላጊ ነው፤ በአዲሱ ዓለምም ቢሆን ይህ እውነታ አይቀየርም። በእርግጥም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት በምናከናውናቸው መልካም ሥራዎችና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንደምንደሰት አንጠራጠርም።

መዝሙር 142 ተስፋችንን አጥብቀን እንያዝ

^ አን.5 ይሖዋ በጥንቷ እስራኤል ነፃነት የሚታወጅበት ልዩ ዝግጅት አድርጎ ነበር። ይህ ዝግጅት ኢዮቤልዩ በመባል ይታወቃል። ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባንሆንም ከኢዮቤልዩ ዝግጅት የምናገኘው ትምህርት አለ። በጥንት ዘመን የነበረው ኢዮቤልዩ፣ ይሖዋ ለእኛ ያደረገውን ዝግጅት የሚያስታውሰን እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ከዚህ ዝግጅት ምን ጥቅም እንደምናገኝ በዚህ ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

^ አን.61 የሥዕሉ መግለጫ፦ ባሪያ የነበሩ ሰዎች በኢዮቤልዩ ወቅት ነፃ ስለሚወጡ ወደ ቤተሰባቸውና ወደ ርስታቸው መመለስ ይችላሉ።