‘ምድርን ለመውረስ’ ዝግጁ ነህ?
ሁላችንም ኢየሱስ “ገሮች ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” በማለት የገባው ቃል የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። (ማቴ. 5:5) ቅቡዓኑ በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ነገሥታት ሆነው በመግዛት ምድርን ይወርሳሉ። (ራእይ 5:10፤ 20:6) በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ እውነተኛ ክርስቲያኖች ደግሞ በምድር ላይ ለዘላለም በመኖር ምድርን ለመውረስ ተስፋ ያደርጋሉ። በዚያ ጊዜ ፍጹማን ይሆናሉ፤ እንዲሁም ሰላምና ደስታ ይኖራቸዋል። ሆኖም እነዚህ ሰዎች፣ ከዚህ ተስፋ ፍጻሜ ጋር በተያያዘ ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል። እስቲ ሦስቱን እንመልከት፦ ምድርን መግዛት፣ ከሞት የተነሱት ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማሟላት እንዲሁም ትንሣኤ ያገኙ ሰዎችን ማስተማር። በተጨማሪም በእነዚህ ሥራዎች መካፈል እንደምትፈልግ ከአሁኑ ማሳየት የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
ምድርን ለመግዛት መዘጋጀት
ይሖዋ ለሰዎች ‘ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም’ የሚል ትእዛዝ ሲሰጣቸው ውሎ አድሮ መላዋ ምድር ገነት እንደምትሆን መጠቆሙ ነበር። (ዘፍ. 1:28) ምድርን የሚወርሱ ሰዎች ይህን ትእዛዝ መፈጸም ይጠበቅባቸዋል። ሆኖም እንደ መነሻ የሚሆን ገነት አይኖራቸውም፤ ምክንያቱም የኤደን ገነት አሁን የለም። ከመነሻው አንስቶ ብዙ ሥራ ይኖራል፤ የተበላሹ ቦታዎችን ማጽዳት ያስፈልጋል። ይህ ከባድ ሥራ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም!
ይህ ሁኔታ፣ እስራኤላውያን ከባቢሎን ሲመለሱ የጠበቃቸውን ሥራ ያስታውሰናል። ምድራቸው ለ70 ዓመታት ባድማ ሆና ቆይታ ነበር። ሆኖም ኢሳይያስ፣ በይሖዋ በረከት ምድሪቱን ወደ ቀድሞ ይዞታዋ መመለስ እንደሚችሉ ትንቢት ተናግሯል። ትንቢቱ እንዲህ ይላል፦ “ምድረ በዳዋንም እንደ ኤደን፣ በረሃማ ሜዳዋንም እንደ ይሖዋ የአትክልት ስፍራ ያደርጋል።” (ኢሳ. 51:3) እስራኤላውያን ተሳክቶላቸዋል። በተመሳሳይም፣ ምድርን የሚወርሱት ሰዎች በይሖዋ በረከት ምድርን ገነት ማድረግ ይችላሉ። አንተም በዚህ ሥራ መካፈል እንደምትፈልግ ከአሁኑ ማሳየት ትችላለህ።
አንዱ መንገድ፣ ቤትህንና አካባቢህን ንጹሕና ሥርዓታማ
ለማድረግ የተቻለህን ጥረት ማድረግ ነው። ጎረቤቶችህ ምንም ያድርጉ ምን፣ አንተ የቤትህንና የአካባቢህን ንጽሕና መጠበቅ ትችላለህ። በተጨማሪም የጉባኤ ስብሰባ አዳራሹንና የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሹን በማጽዳቱና በመጠገኑ ሥራ መካፈል ትችላለህ። ሁኔታህ የሚፈቅድልህ ከሆነ፣ በአደጋ ጊዜ እርዳታ ሥራ ለመካፈል ማመልከቻ መሙላት ትችል ይሆናል። እንዲህ በማድረግ፣ ወንድሞችህንና እህቶችህን ለመርዳት ዝግጁ መሆንህን ታሳያለህ። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ምድርን የመውረስ መብት ባገኝ ልጠቀምባቸው የምችላቸውን ክህሎቶች ማዳበር እችል ይሆን?’ከሞት የተነሱት ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት መዘጋጀት
ኢየሱስ የኢያኢሮስን ልጅ ከሞት ካስነሳት በኋላ ለልጅቷ የሚበላ ነገር እንዲሰጧት ለቤተሰቦቿ ነግሯቸዋል። (ማር. 5:42, 43) ያቺ የ12 ዓመት ልጅ የሚያስፈልጋትን ነገር ማሟላት ያን ያህል ከባድ ላይሆን ይችላል። ይሁንና ኢየሱስ ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን ሰምተው እንደሚወጡ’ የገባው ቃል ሲፈጸም ሁኔታው ምን ሊመስል እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። (ዮሐ. 5:28, 29) መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ዝርዝር መረጃ ባይሰጠንም ትንሣኤ ያገኙት ሰዎች ምግብ፣ መጠለያና ልብስ ለማግኘት እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መጠበቅ እንችላለን። እነሱን ለመርዳት ዝግጁ መሆን እንደምትፈልግ ከአሁኑ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው።
ምድርን ለመውረስ ዝግጁ መሆንህን ለማሳየት ከአሁኑ ምን ማድረግ ትችላለህ?
የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤያችሁን እንደሚጎበኝ ማስታወቂያ ሲነገር እሱን ምግብ ለመጋበዝ ራስህን ታቀርባለህ? የልዩ ሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ከቤቴል ወጥተው በመስኩ ላይ እንዲያገለግሉ ሲመደቡ ወይም የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የጉብኝት ሥራቸውን ሲያቆሙ ቤት እንዲያገኙ ልትረዳቸው ትችላለህ? በአካባቢህ የክልል ስብሰባ ወይም ልዩ የክልል ስብሰባ ሲካሄድ ከስብሰባው በፊት ወይም በኋላ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነህ ለማገልገል ወይም ልዑካንን ለመቀበል ራስህን ማቅረብ ትችል ይሆን?
ትንሣኤ ያገኙትን ሰዎች ለማስተማር መዘጋጀት
በሐዋርያት ሥራ 24:15 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ አንጻር፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት እንደሚነሱ እንጠብቃለን። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ፣ ከመሞታቸው በፊት ይሖዋን የማወቅ አጋጣሚ አላገኙም። ከሞት ከተነሱ በኋላ ይህ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። a ተሞክሮ ያላቸው ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በዚህ የማስተማር ሥራ ይካፈላሉ። (ኢሳ. 11:9) በአውሮፓ፣ በደቡብ አሜሪካና በአፍሪካ ያገለገለችው ሻርሎት በዚህ ሥራ ለመካፈል ትጓጓለች። እንዲህ በማለት በደስታ ተናግራለች፦ “በትንሣኤ ወቅት ሰዎችን ለማስተማር እጓጓለሁ። ከዚህ በፊት በሕይወት ስለኖረ ሰው ሳነብ ‘ይህ ሰው ይሖዋን አውቆ ቢሆን ኖሮ እኮ ሕይወቱ በጣም የተለየ ይሆን ነበር’ ብዬ አስባለሁ። ትንሣኤ ላገኙት ሰዎች፣ ያኔ ያላወቋቸውን ነገሮች ልነግራቸው በጣም እናፍቃለሁ።”
ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የኖሩ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችም እንኳ ብዙ ነገር መማር ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ዳንኤል፣ የጻፋቸውን የአንዳንዶቹን ትንቢቶች ትርጉም አልተረዳም ነበር፤ የእነዚህን ትንቢቶች ፍጻሜ ለእሱ ማስረዳት እንዴት ያለ አስደሳች መብት እንደሆነ እስቲ አስበው። (ዳን. 12:8) ወይም ደግሞ ለሩትና ለናኦሚ ቤተሰባቸው በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ እንደተካተተ ስንነግራቸው ይታይህ። ይህ ክፉ ዓለም ከሚያሳድረው ጫናና ትኩረት ከሚከፋፍሉ ነገሮች ነፃ ሆኖ በዚህ ዓለም አቀፋዊ የትምህርት መርሐ ግብር መካፈል ምንኛ አስደሳች ይሆናል!
በዚህ ሥራ ለመካፈል ዝግጁ መሆን እንደምትፈልግ ከአሁኑ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ የማስተማር ክህሎትህን ማሻሻልና በአሁኑ ጊዜ እየተከናወነ ባለው ዓለም አቀፋዊ የስብከት ሥራ አዘውትረህ መካፈል እንደሆነ ግልጽ ነው። (ማቴ. 24:14) ዕድሜህ ወይም ያለህበት ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ በአገልግሎት የምታደርገውን ተሳትፎ ቢገድብብህም እንኳ ምርጥህን መስጠትህ፣ ትንሣኤ ያገኙትን ሰዎች ለማስተማር ዝግጁ እንደሆንክ ያሳያል።
በእርግጥም የሚከተሉትን ወሳኝ ጥያቄዎች ልናስብባቸው ይገባል፦ ምድርን ለመውረስ በእርግጥ ትጓጓለህ? ምድርን ለመግዛት እንዲሁም ከሞት የተነሱት ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላትና እነሱን ለማስተማር ትናፍቃለህ? በአሁኑ ጊዜ ያገኘኸውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመህ፣ ወደፊት ምድርን ስትወርስ ከሚጠብቁህ ሥራዎች ጋር ተመሳሳይ በሆኑ ሥራዎች በመካፈል ለዚያ ጊዜ ዝግጁ መሆንህን ማሳየት ትችላለህ!
a በመስከረም 2022 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የጽድቅን ጎዳና እንዲከተሉ ብዙ ሰዎችን መርዳት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።