በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 51

በመከራ ወቅት ሰላም ማግኘት ትችላላችሁ

በመከራ ወቅት ሰላም ማግኘት ትችላላችሁ

“ልባችሁ አይረበሽ፤ በፍርሃትም አይዋጥ።”—ዮሐ. 14:27

መዝሙር 112 ይሖዋ የሰላም አምላክ ነው

ማስተዋወቂያ a

1. “የአምላክ ሰላም” ምንድን ነው? ይህን ሰላም ማግኘታችን የሚጠቅመንስ እንዴት ነው? (ፊልጵስዩስ 4:6, 7)

 ዓለም ጨርሶ የማያውቀው የሰላም ዓይነት አለ። እሱም “የአምላክ ሰላም” ይኸውም ከሰማዩ አባታችን ጋር ውድ ዝምድና በመመሥረት የሚገኝ የመረጋጋት ስሜት ነው። የአምላክ ሰላም ሲኖረን የደህንነት ስሜት ይሰማናል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብብ።) እሱን ከሚወዱ ሰዎች ጋር የቅርብ ወዳጅነት ይኖረናል። እንዲሁም ‘ከሰላም አምላክ’ ጋር የቅርብ ዝምድና እንመሠርታለን። (1 ተሰ. 5:23) አባታችንን የምናውቀው፣ የምንታመንበትና የምንታዘዘው ከሆነ፣ መከራ ሲያጋጥመን የአምላክ ሰላም የተጨነቀውን ልባችንን ያረጋጋልናል።

2. የአምላክን ሰላም ማግኘት እንደሚቻል እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

2 እንደ ወረርሽኝ፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ ሕዝባዊ ዓመፅ ወይም ስደት ያለ መከራ ሲያጋጥመን በእርግጥ የአምላክን ሰላም ማግኘት እንችላለን? እነዚህ ችግሮች በፍርሃት እንድንዋጥ ሊያደርጉን ይችላሉ። ያም ቢሆን ኢየሱስ “ልባችሁ አይረበሽ፤ በፍርሃትም አይዋጥ” በማለት ተከታዮቹን መክሯቸዋል። (ዮሐ. 14:27) ደስ የሚለው፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የኢየሱስን ምክር ተግባራዊ አድርገዋል። ከባድ መከራ ቢያጋጥማቸውም በይሖዋ እርዳታ ሰላም ማግኘት ችለዋል።

በወረርሽኝ ወቅት ሰላም ማግኘት

3. ወረርሽኝ ሰላማችንን ሊያደፈርሰው የሚችለው እንዴት ነው?

3 ወረርሽኝ ሲከሰት ሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች በድንገት ሊቀየሩ ይችላሉ። ለምሳሌ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በብዙዎች ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ለማሰብ ሞክር። አንድ ጥናት እንደገለጸው፣ በጥናቱ ከተሳተፉት ሰዎች ግማሽ ያህሉ በወረርሽኙ ወቅት የእንቅልፍ ችግር አጋጥሟቸው እንደነበር ተናግረዋል። በወረርሽኙ ወቅት ጭንቀት፣ ድብርት፣ የአልኮልና የዕፅ ሱስ፣ የቤት ውስጥ ጥቃት እንዲሁም ራስን የማጥፋት ሙከራ በእጅጉ ጨምሮ ነበር። አንተስ በምትኖርበት አካባቢ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጭንቀትህን መቆጣጠርና የአምላክን ሰላም ማጣጣም የምትችለው እንዴት ነው?

4. ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት የተናገረውን ትንቢት ማወቃችን ሰላም የሚሰጠን እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት “በተለያየ ስፍራ” ቸነፈር ወይም ወረርሽኝ እንደሚከሰት ትንቢት ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) ይህን ማወቃችን ሰላም የሚሰጠን እንዴት ነው? ወረርሽኝ መከሰቱ አያስደነግጠንም። ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት እየተፈጸመ እንዳለ እንገነዘባለን። በመሆኑም ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን ለሚኖሩት ሰዎች “እንዳትደናገጡ ተጠንቀቁ” በማለት የሰጠውን ምክር እንከተላለን።—ማቴ. 24:6

በድምፅ የተቀዳውን መጽሐፍ ቅዱስ ማዳመጥህ በወረርሽኝ ወቅት የአእምሮ ሰላም እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት)

5. (ሀ) በፊልጵስዩስ 4:8, 9 መሠረት ወረርሽኝ ሲያጋጥመን ምን ብለን መጸለይ ይኖርብናል? (ለ) አንዲት እህት በድምፅ የተቀዳውን መጽሐፍ ቅዱስ ማዳመጧ የጠቀማት እንዴት ነው? እኛስ ከእሷ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

5 ወረርሽኝ ሲከሰት ጭንቀትና ፍርሃት ሊያድርብን ይችላል። ዴዚ b የተባለች እህት እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟት ነበር። አጎቷ፣ የአጎቷ ልጅ እንዲሁም ሐኪሟ በኮቪድ-19 ከሞቱ በኋላ እሷም በሽታው እንዳይዛትና ለአረጋዊት እናቷ እንዳታጋባ ፈርታ ነበር። በወረርሽኙ የተነሳ ሥራዋን ልታጣ እንደምትችልም ሰግታ ነበር። በመሆኑም ለምግብና ለቤት ኪራይ የሚሆን ገንዘብ ከየት እንደምታገኝ አሳሰባት። እነዚህ ነገሮች በጣም ስላስጨነቋት ሌሊት እንቅልፍ መተኛት አቃታት። ሆኖም ዴዚ ሰላሟን መልሳ ማግኘት ችላለች። እንዴት? ይሖዋ እንድትረጋጋና አዎንታዊ ነገሮችን እንድታስብ እንዲረዳት ጸለየች። (ፊልጵስዩስ 4:8, 9ን አንብብ።) በድምፅ የተቀዳውን መጽሐፍ ቅዱስ በመስማት ይሖዋ “ሲያነጋግራት” አዳመጠች። እንዲህ ብላለች፦ “የአንባቢዎቹ የሚያረጋጋ ድምፅ ጭንቀቴ ቀለል እንዲለኝ አደረገ፤ እንዲሁም ይሖዋ እንደሚያስብልኝ አስታወሰኝ።”—መዝ. 94:19

6. የግል ጥናትና የጉባኤ ስብሰባ የሚረዳህ እንዴት ነው?

6 ወረርሽኝ መከሰቱ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችህ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጥያቄ የለውም። ሆኖም የግል ጥናት ከማድረግ ወይም በስብሰባ ላይ ከመገኘት እንዲያግድህ ልትፈቅድ አይገባም። በጽሑፎቻችንና በቪዲዮዎቻችን ላይ የሚወጡት ተሞክሮዎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተመሳሳይ ፈተና ቢያጋጥማቸውም በታማኝነት ይሖዋን እያገለገሉ እንደሆነ ያሳዩናል። (1 ጴጥ. 5:9) በስብሰባዎች ላይ መገኘትህ አእምሮህን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ አዎንታዊ ሐሳቦች ለመሙላት ይረዳሃል። በተጨማሪም ሌሎችን ለማበረታታትና ከሌሎች ማበረታቻ ለማግኘት የሚያስችል አጋጣሚ ይሰጥሃል። (ሮም 1:11, 12) ይሖዋ አገልጋዮቹ በታመሙበት፣ በፈሩበት ወይም ብቸኝነት በተሰማቸው ጊዜ የደገፋቸው እንዴት እንደሆነ ማሰላሰልህ አንተንም እንደሚደግፍህ ያለህን እምነት ያጠናክርልሃል።

7. ከሐዋርያው ዮሐንስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

7 ወንድሞችህንና እህቶችህን ለማግኘት ጥረት አድርግ። ወረርሽኝ ሲከሰት ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በምንሆንበት ጊዜም ጭምር አካላዊ ርቀት መጠበቅ ሊኖርብን ይችላል። በዚህ ጊዜ እንደ ሐዋርያው ዮሐንስ ዓይነት ስሜት ይሰማህ ይሆናል። ዮሐንስ ወዳጁን ጋይዮስን በአካል ማግኘት ይፈልግ ነበር። (3 ዮሐ. 13, 14) ሆኖም ዮሐንስ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ጋይዮስን ሊያገኘው እንደማይችል ተገንዝቧል። በመሆኑም ዮሐንስ ማድረግ የሚችለውን ነገር አደረገ፤ ለጋይዮስ ደብዳቤ ጻፈለት። አንተም ወንድሞችህንና እህቶችህን በአካል ማግኘት ካልቻልክ በስልክ፣ በቪዲዮ ጥሪ ወይም በጽሑፍ መልእክት አማካኝነት እነሱን ለማነጋገር ጥረት አድርግ። ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር አዘውትረህ መገናኘትህ የሰላምና የደህንነት ስሜት እንዲሰማህ ያደርጋል። ከባድ ጭንቀት ከተሰማህ ሽማግሌዎችን ለማነጋገር ጥረት አድርግ፤ የሚሰጡህን ፍቅራዊ ማበረታቻም ተቀበል።—ኢሳ. 32:1, 2

በአደጋ ወቅት ሰላም ማግኘት

8. አደጋ ሲደርስ ሰላማችን ሊረበሽ የሚችለው እንዴት ነው?

8 በምትኖርበት አካባቢ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የምድር ነውጥ ወይም የእሳት አደጋ ደርሶ የሚያውቅ ከሆነ አደጋው ከደረሰ ከረጅም ጊዜ በኋላም ከባድ ጭንቀት ሊሰማህ ይችላል። በአደጋው ምክንያት ወዳጅ ዘመዶችህን በሞት አጥተህ ወይም ንብረትህ ወድሞ ከሆነ ደግሞ ሐዘን፣ ተስፋ መቁረጥ አልፎ ተርፎም ብስጭት ሊሰማህ ይችላል። ይህ መሆኑ ለቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ ቦታ እንደምትሰጥ ወይም እምነት እንደጎደለህ የሚያሳይ አይደለም። ከባድ ፈተና ስላጋጠመህ አፍራሽ ስሜት ቢያድርብህ አያስገርምም። (ኢዮብ 1:11) ሆኖም አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ብትሆንም እንኳ ሰላም ማግኘት ትችላለህ። እንዴት?

9. ኢየሱስ ለአደጋዎች ያዘጋጀን እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት አስታውስ። በዓለም ላይ ያሉ አንዳንድ ሰዎች የተፈጥሮ አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አይሰማቸውም፤ እኛ ግን አደጋ እየጨመረ እንደሚሄድ እንዲሁም እኛንም ሊነካን እንደሚችል እንገነዘባለን። ኢየሱስ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት “ታላላቅ የምድር ነውጦች” እና ሌሎች አደጋዎች እንደሚከሰቱ ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 21:11) በተጨማሪም “ሕገ ወጥነት እየበዛ” እንደሚሄድ ተናግሯል፤ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው ወንጀል፣ ዓመፅና የሽብርተኝነት ጥቃት ይህን ያሳያል። (ማቴ. 24:12 ግርጌ) ኢየሱስ እነዚህ አደጋዎች የሚደርሱት የይሖዋን ሞገስ ያጡ ሰዎች ላይ ብቻ እንደሆነ አልተናገረም። እንዲያውም በርካታ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች አደጋ ደርሶባቸዋል። (ኢሳ. 57:1፤ 2 ቆሮ. 11:25) ይሖዋ በተአምራዊ መንገድ ከሁሉም አደጋዎች ባይታደገንም ለመረጋጋትና ሰላም ለማግኘት የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ይሰጠናል።

10. ለአደጋ ከአሁኑ መዘጋጀታችን እምነት እንዳለን ያሳያል የምንለው ለምንድን ነው? (ምሳሌ 22:3)

10 አደጋ ሲደርስ ምን እንደምናደርግ አስቀድመን ካቀድን፣ ሁኔታው ሲያጋጥም መረጋጋት ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል። ይሁንና አስቀድመን መዘጋጀታችን በይሖዋ ላይ እምነት እንደሌለን የሚያሳይ ነው? በጭራሽ። እንዲያውም ለአደጋ መዘጋጀታችን ይሖዋ እኛን ለመንከባከብ ችሎታው እንዳለው እንደምናምን ያሳያል። እንዴት? የአምላክ ቃል፣ ሊያጋጥሙ ለሚችሉ አደጋዎች እንድንዘጋጅ ይመክረናል። (ምሳሌ 22:3ን አንብብ።) በተጨማሪም የአምላክ ድርጅት በመጽሔቶች፣ በጉባኤ ስብሰባዎች እንዲሁም ወቅታዊ በሆኑ ማስታወቂያዎች አማካኝነት ለአደጋ እንድንዘጋጅ በተደጋጋሚ ያበረታታናል። c ታዲያ በይሖዋ እንተማመናለን? ከሆነ፣ አደጋ ከመድረሱ በፊት ከአሁኑ ይህን ምክር እንከተላለን።

አስቀድመህ መዘጋጀትህ በአደጋ ወቅት ሕይወትህን ለማትረፍ ሊረዳህ ይችላል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት) d

11. ከማርጋሬት ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

11 ማርጋሬት የተባለች እህት ያጋጠማትን ነገር እስቲ እንመልከት። በአካባቢዋ ሰደድ እሳት በመነሳቱ ቤቷን ለቃ እንድትሄድ ተነገራት። በአንድ ጊዜ ብዙ ሰዎች አካባቢውን ለቀው ለመሄድ እየሞከሩ ስለነበር መንገዱ ተዘጋጋ፤ መኪኖቹም መንቀሳቀስ አልቻሉም። አየሩ በጥቁር ጭስ ተሞላ። ማርጋሬትም ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከመኪናዋ መውጣት አልቻለችም። ሆኖም አስቀድማ በመዘጋጀቷ ሕይወቷን አትርፋለች። ከአካባቢው መውጣት የሚያስችል መንገድ ለማግኘት የምታመሣክረው ካርታ ቦርሳዋ ውስጥ ይዛ ነበር። እንዲያውም አደጋ ሲያጋጥም መንገዱን በቀላሉ ማግኘት እንድትችል ያንን መንገድ አስቀድማ ሞክራዋለች። ማርጋሬት አስቀድማ በመዘጋጀቷ ከአደጋው መትረፍ ችላለች።

12. ከጥንቃቄ እርምጃዎች ጋር የተያያዙ መመሪያዎችን የምንከተለው ለምንድን ነው?

12 ባለሥልጣናት እኛን ከጉዳት ለመጠበቅ ወይም ሥርዓት ለማስከበር ሲሉ ሰዓት እላፊ ሊጥሉ፣ አካባቢውን ለቅቀን እንድንሄድ ሊጠይቁን ወይም ሌሎች እርምጃዎችን እንድንወስድ ሊያዙን ይችላሉ። አንዳንድ ሰዎች ንብረቶቻቸውን ጥለው መሄድ ስለማይፈልጉ ለመታዘዝ ይዘገያሉ ወይም ያመነታሉ። ክርስቲያኖችስ ምን ምላሽ ይሰጣሉ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ለጌታ ብላችሁ ለሰብዓዊ ሥልጣን ሁሉ ተገዙ፦ የበላይ ስለሆነ ለንጉሥ ተገዙ፤ ደግሞም . . . በእሱ የተላኩ ስለሆኑ ለገዢዎች ተገዙ።” (1 ጴጥ. 2:13, 14) የአምላክ ድርጅትም ጉዳት እንዳያገኘን የሚረዳ መመሪያ ይሰጠናል። ሽማግሌዎች አደጋ በሚደርስበት ጊዜ እንዲያገኙን ወቅታዊ አድራሻችንን እንድንሰጣቸው በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ይሰጠናል። አንተስ እንደዚህ አድርገሃል? ከዚህም ሌላ ቤታችን ከመቆየት፣ አካባቢውን ለቆ ከመሄድ እንዲሁም የእርዳታ ቁሳቁሶችን ከማግኘት ጋር የተያያዘ መመሪያ ሊሰጠን ይችላል። ሌሎችን መርዳት የምንችለው እንዴትና መቼ እንደሆነም ይነገረናል። መመሪያውን ሳንታዘዝ ከቀረን የእኛንም ሆነ የሽማግሌዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ልንጥል እንችላለን። እነዚህ ታማኝ ወንድሞች ‘ተግተው እንደሚጠብቁን’ አስታውስ። (ዕብ. 13:17) ማርጋሬት እንዲህ ብላለች፦ “ሕይወቴን ያተረፈልኝ የሽማግሌዎችንና የድርጅቱን መመሪያ መከተሌ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ።”

13. ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ በርካታ ክርስቲያኖች ሰላምና ደስታ የሰጣቸው ምንድን ነው?

13 በተፈጥሮ አደጋ፣ በጦርነት ወይም በሕዝባዊ ዓመፅ ምክንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ከአዲሱ ሁኔታቸው ጋር ለመላመድ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ በተጨማሪም ወዲያውኑ በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች መካፈላቸውን ቀጥለዋል። በደረሰባቸው ስደት ምክንያት ወደተለያየ አካባቢ እንደተበተኑት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሁሉ እነሱም ‘የአምላክን ቃል ምሥራች መስበካቸውን’ ቀጥለዋል። (ሥራ 8:4) እንዲህ ማድረጋቸው፣ ባሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ሳይሆን በመንግሥቱ ላይ እንዲያተኩሩ ረድቷቸዋል። በዚህም የተነሳ ደስታቸውንና ሰላማቸውን መጠበቅ ችለዋል።

በስደት ወቅት ሰላም ማግኘት

14. ስደት ሰላማችንን ሊያደፈርሰው የሚችለው እንዴት ነው?

14 ስደት ሰላም የሚያስገኙልንን የተለያዩ ነገሮች ሊያሳጣን ይችላል። በነፃነት ስንሰበሰብና ስንሰብክ እንዲሁም ‘እንታሰራለን’ የሚል ስጋት ሳያድርብን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችንን ስናከናውን ደስታና እርካታ ይሰማናል። እንዲህ ያሉ ነፃነቶችን ስንነጠቅ ‘ነገ ምን ይደርስብን ይሆን’ ብለን በመስጋት ልንጨነቅ እንችላለን። እንዲህ ቢሰማን አያስገርምም። ያም ቢሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ኢየሱስ፣ ስደት ተከታዮቹን ሊያሰናክላቸው እንደሚችል ተናግሯል። (ዮሐ. 16:1, 2) ታዲያ ስደት ሲደርስብን ሰላማችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

15. ስደትን መፍራት የሌለብን ለምንድን ነው? (ዮሐንስ 15:20፤ 16:33)

15 የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል።” (2 ጢሞ. 3:12) አንድሬ የተባለ ወንድም፣ በሚኖርበት አገር ውስጥ ሥራችን በታገደበት ወቅት ሁኔታውን መቀበል ከብዶት ነበር። እንዲህ በማለት አሰበ፦ ‘እዚህ በጣም ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። ባለሥልጣናቱ እንዴት ሁላችንንም ሊያስሩን ይችላሉ?’ ሆኖም እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ሰላም ከመስጠት ይልቅ በጭንቀት እንዲዋጥ አደረገው። ሌሎች ወንድሞች ግን እነሱ ሊታሰሩ እንደማይችሉ ከማሰብ ይልቅ ሁኔታውን በይሖዋ እጅ ትተውት ነበር። እነዚህ ወንድሞች፣ ሊታሰሩ እንደሚችሉ አምነው ተቀብለው ነበር፤ ሆኖም የአንድሬን ያህል በጭንቀት አልተዋጡም። በመሆኑም አንድሬ የእነሱን ዓይነት አመለካከት በማዳበር ሁኔታውን በይሖዋ እጅ ለመተው ወሰነ። ብዙም ሳይቆይ ሰላሙ ተመለሰለት። አሁን፣ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ደስተኛ ነው። እኛም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንችላለን። ኢየሱስ ስደት እንደሚደርስብን ቢናገርም ታማኝነታችንን መጠበቅ እንደምንችልም ዋስትና ሰጥቶናል።—ዮሐንስ 15:20፤ 16:33ን አንብብ።

16. በስደት ወቅት ምን ዓይነት መመሪያዎችን መታዘዝ ይኖርብናል?

16 በሥራችን ላይ እገዳ ወይም ከፍተኛ ገደብ በሚጣልበት ወቅት ከቅርንጫፍ ቢሮው ወይም ከሽማግሌዎች መመሪያ ሊሰጠን ይችላል። የእነዚህ መመሪያዎች ዓላማ እኛን ከጉዳት መጠበቅ፣ መንፈሳዊ ምግብ ማግኘታችንን እንድንቀጥል ማድረግ እንዲሁም ሁኔታው በሚፈቅደው መጠን መስበካችንን እንድንቀጥል መርዳት ነው። መመሪያው የተሰጠበት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ባይገባህም እንኳ የተሰጠህን መመሪያ ለመታዘዝ አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ አድርግ። (ያዕ. 3:17) በተጨማሪም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ወይም ከጉባኤው እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ማወቅ ለማይገባቸው ሰዎች እንዳትናገር ተጠንቀቅ።—መክ. 3:7

አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብትሆንም ሰላም ለማግኘት የሚረዳህ ምንድን ነው? (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት) e

17. በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ሐዋርያት ምን ለማድረግ ቆርጠናል?

17 ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጦርነት ካወጀባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ‘ስለ ኢየሱስ የመመሥከር ሥራ ስለተሰጣቸው’ ነው። (ራእይ 12:17) ሰይጣንና የእሱ ዓለም በፍርሃት እንዲያሽመደምድህ አትፍቀድ። ተቃውሞ ቢኖርም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ መካፈላችን ደስታና ሰላም ያስገኝልናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁድ ባለሥልጣናት ሐዋርያቱ መስበካቸውን እንዲያቆሙ ባዘዟቸው ወቅት እነዚህ ታማኝ ሰዎች አምላክን ለመታዘዝ መርጠዋል። መስበካቸውን ቀጥለዋል፤ ይህ ሥራም ደስታ አስገኝቶላቸዋል። (ሥራ 5:27-29, 41, 42) እርግጥ በሥራችን ላይ ገደብ ከተጣለ፣ በምንሰብክበት ወቅት ጠንቃቃ መሆን ይኖርብናል። (ማቴ. 10:16) ሆኖም አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ካደረግን ይሖዋን ከማስደሰት እንዲሁም ሕይወት አድን መልእክት ከመናገር የሚገኘውን ሰላም እናጣጥማለን።

‘የሰላም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል’

18. እውነተኛ ሰላም ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?

18 በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም እንኳ ሰላም ማግኘት እንደምንችል እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን፣ የሚያስፈልገን የሰላም ዓይነት የአምላክ ሰላም ማለትም ይሖዋ ብቻ ሊሰጠው የሚችለው ሰላም እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ወረርሽኝ፣ አደጋ ወይም ስደት ሲያጋጥምህ በይሖዋ ታመን። ድርጅቱን የሙጥኝ በል። የተዘረጋልህን ግሩም የወደፊት ተስፋ አሻግረህ ተመልከት። እንዲህ ካደረግክ ‘የሰላም አምላክ ከአንተ ጋር ይሆናል።’ (ፊልጵ. 4:9) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ፣ መከራ ያጋጠማቸው የእምነት ባልንጀሮቻችን የአምላክን ሰላም እንዲያገኙ መርዳት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል

a ይሖዋ ለሚወዱት ሰዎች ሰላም እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል። አምላክ የሚሰጠው ሰላም ምንድን ነው? ይህን ሰላም ማግኘት የምንችለውስ እንዴት ነው? ወረርሽኝ፣ አደጋ ወይም ስደት ሲያጋጥመን የአምላክን ሰላም ማግኘታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? ይህ ርዕስ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ያብራራል።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

c በቁጥር 5 2017 ንቁ! ላይ የወጣውን “አደጋ ሲደርስ ሕይወት ለማዳን የሚያስችሉ እርምጃዎች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

d የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት አደጋ ሲደርስ ቤቷን ለቅቃ ለመሄድ አስቀድማ ተዘጋጅታለች።

e የሥዕሉ መግለጫ፦ በስብከቱ ሥራችን ላይ ገደብ በተጣለበት አገር ውስጥ የሚኖር አንድ ወንድም በጥበብ ሲመሠክር።