በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 50

“ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ”

“ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ”

“እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ።”—ሉቃስ 23:43

መዝሙር 145 አምላክ የሰጠው የገነት ተስፋ

ማስተዋወቂያ a

1. ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ፣ አብሮት የተሰቀለውን ወንጀለኛ ምን አለው? (ሉቃስ 23:39-43)

 ኢየሱስና ከጎኑ የተሰቀሉት ሁለት ወንጀለኞች ሊሞቱ እያጣጣሩ በከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ ናቸው። (ሉቃስ 23:32, 33) ሁለቱም ወንጀለኞች በኢየሱስ ላይ ሲያሾፉበት ነበር፤ ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ እንዳልነበሩ ግልጽ ነው። (ማቴ. 27:44፤ ማር. 15:32) ሆኖም አንደኛው አመለካከቱን ቀየረ። እንዲህ አለ፦ “ኢየሱስ ሆይ፣ ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ።” ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት መለሰለት። (ሉቃስ 23:39-43ን አንብብ።) ይህ ወንጀለኛ ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት ያወጀውን ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች’ የሚለውን መልእክት ተቀብሎ እንደነበር የሚጠቁም ምንም ነገር የለም። ኢየሱስም ቢሆን ሰውየው ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደሚገባ አልተናገረም። (ማቴ. 4:17) ኢየሱስ እየተናገረ ያለው፣ ወደፊት በምድር ላይ ስለሚኖረው ገነት ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

ከኢየሱስ ጋር ስለተሰቀለው ወንጀለኛ ማንነት እንዲሁም ስለሚያውቀው ነገር ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? (ከአንቀጽ 2-3⁠ን ተመልከት)

2. ንስሐ የገባው ወንጀለኛ አይሁዳዊ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ የሚያደርገን ምንድን ነው?

2 ንስሐ የገባው ወንጀለኛ አይሁዳዊ ነው ብለን መደምደም እንችላለን። ምክንያቱም ይህ ሰው አብሮት የተሰቀለውን ወንጀለኛ “አንተ ራስህ ተመሳሳይ ፍርድ ተቀብለህ እያለ ትንሽ እንኳ አምላክን አትፈራም?” ብሎታል። (ሉቃስ 23:40) አይሁዳውያን የሚያመልኩት አንድ አምላክ ነበር፤ አሕዛብ ግን ብዙ አማልክትን ያመልኩ ነበር። (ዘፀ. 20:2, 3፤ 1 ቆሮ. 8:5, 6) ወንጀለኞቹ ከአሕዛብ ወገን ቢሆኑ ኖሮ፣ ሰውየው የሚጠይቀው “ትንሽ እንኳ አማልክትን አትፈራም?” ብሎ ነበር። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ የተላከው ለአሕዛብ ሳይሆን “ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች” ነው። (ማቴ. 15:24) አምላክ ሙታንን እንደሚያስነሳ ለእስራኤላውያን ነግሯቸው ነበር። ንስሐ የገባው ወንጀለኛ ይህን ሳያውቅ አይቀርም። ከተናገረው ነገር መረዳት እንደምንችለው፣ ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት አስነስቶ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደሚያደርገው አስቧል። ሰውየው አምላክ እሱንም ከሞት እንደሚያስነሳው ተስፋ አድርጎ መሆን አለበት።

3. ንስሐ የገባው ወንጀለኛ፣ ኢየሱስ ስለ ገነት ሲናገር ምን ወደ አእምሮው መጥቶ መሆን አለበት? አብራራ። (ዘፍጥረት 2:15)

3 ንስሐ የገባው ወንጀለኛ፣ አይሁዳዊ እንደመሆኑ መጠን ስለ አዳምና ሔዋን እንዲሁም ይሖዋ መኖሪያ አድርጎ ስለሰጣቸው ገነት ማወቁ አይቀርም። በመሆኑም ወንጀለኛው፣ ኢየሱስ የጠቀሰው ገነት ምድር ላይ ያለ ውብ የአትክልት ቦታ እንደሆነ ተገንዝቦ መሆን አለበት።—ዘፍጥረት 2:15ን አንብብ።

4. ኢየሱስ ለወንጀለኛው የተናገራቸው ቃላት ስለ ምን እንድናስብ ያነሳሱናል?

4 ኢየሱስ ለወንጀለኛው የተናገራቸው ቃላት፣ በገነት ውስጥ ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል እንድናስብ ያነሳሱናል። ሰላም ከሰፈነበት የንጉሥ ሰለሞን ግዛት፣ ገነትን በተመለከተ አንዳንድ ትምህርቶች ማግኘት እንችላለን። በተጨማሪም ከሰለሞን የሚበልጠው ኢየሱስ ከተባባሪ ገዢዎቹ ጋር ሆኖ ምድርን ውብ ገነት እንደሚያደርጋት መጠበቅ እንችላለን። (ማቴ. 12:42) በእርግጥም “ሌሎች በጎች” በገነት ውስጥ ለመኖር ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል።—ዮሐ. 10:16

በገነት ውስጥ ሕይወት ምን ይመስላል?

5. በገነት ውስጥ ስለሚኖረን ሕይወት ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው?

5 በገነት ውስጥ ስለሚኖረን ሕይወት ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ምናልባትም እንደ ኤደን የአትክልት ስፍራ ያለ ውብ መናፈሻ ወደ አእምሮህ ይመጣ ይሆናል። (ዘፍ. 2:7-9) “እያንዳንዱም ከወይኑና ከበለስ ዛፉ ሥር ይቀመጣል” የሚለውን ሚክያስ ስለ አምላክ ሕዝቦች የተናገረውን ትንቢት ታስታውስ ይሆናል። (ሚክ. 4:3, 4) መጽሐፍ ቅዱስ፣ የተትረፈረፈ ምግብ እንደሚኖር የሚሰጠውን ተስፋም ታስታውስ ይሆናል። (መዝ. 72:16፤ ኢሳ. 65:21, 22) በመሆኑም ውብ መናፈሻ ውስጥ ብዙ ዓይነት ጣፋጭ ምግብ በቀረበበት ጠረጴዛ ፊት ተቀምጠህ ይታይህ ይሆናል። አየሩ በዕፀዋትና በአበቦች መዓዛ ተሞልቷል። ከሞት የተነሱትን ጨምሮ ወዳጅ ዘመዶችህ ተሰባስበው ሲሳሳቁ ይሰማል። ይህ ሕልም አይደለም። እንዲህ ያሉ ነገሮች በምድር ላይ እንደሚፈጸሙ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም በገነት ውስጥ የሚኖረው ሕይወት አርኪ የሆነ ሥራንም ይጨምራል።

ትንሣኤ ያገኙ ሰዎችን የማስተማር ወሳኝ ሥራ ይኖረናል (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)

6. በገነት ውስጥ ምን ሥራ ይኖረናል? (ሥዕሉን ተመልከት።)

6 ይሖዋ የፈጠረን በሥራችን ደስታ እንድናገኝ አድርጎ ነው። (መክ. 2:24) በተለይም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ብዙ ሥራ ይኖረናል። ታላቁን መከራ በሕይወት የሚያልፉ ሰዎች እንዲሁም ከሞት የሚነሱት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ልብስ፣ ምግብና መኖሪያ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህን ነገሮች ለማሟላት ብዙ ሥራ ይጠይቃል። ደግሞም ይህ ሥራ አስደሳች ነው። አዳምና ሔዋን መኖሪያቸው የሆነውን የአትክልት ስፍራ መንከባከብ እንደነበረባቸው ሁሉ እኛም ገነት የሆነችውን ምድር የመንከባከብ መብት እናገኛለን። በተጨማሪም ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ምንም እውቀት የሌላቸውን ከሞት የተነሱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ማስተማር ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን አስበው። ከኢየሱስ ዘመን በፊት የኖሩ ታማኝ ሰዎች እነሱ ከሞቱ በኋላ ስለተከናወነው ነገር እንዲማሩ መርዳትም ልዩ መብት ነው።

7. ስለ ምን ጉዳይ እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ለምንስ?

7 በገነት ውስጥ ሰላምና ብልጽግና እንደሚሰፍን እንዲሁም በሚገባ የተደራጀ ሕይወት እንደሚኖረን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ በልጁ አገዛዝ ሥር ሕይወት ምን እንደሚመስል ፍንጭ ሰጥቶናል። ስለ ንጉሥ ሰለሞን የግዛት ዘመን የሚገልጸው ዘገባ ይህን ያሳያል።

የንጉሥ ሰለሞን ግዛት—የገነት ቅምሻ

8. በመዝሙር 37:10, 11, 29 ላይ የሚገኙት ቃላት ዳዊት ከጻፋቸው በኋላ የተፈጸሙት እንዴት ነው? (በዚህ መጽሔት ላይ የሚገኘውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።)

8 ንጉሥ ዳዊት፣ ጥበበኛና ታማኝ የሆነ ንጉሥ ወደፊት ዙፋን ላይ ሲቀመጥ ሕይወት ምን እንደሚመስል በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (መዝሙር 37:10, 11, 29ን አንብብ።) ወደፊት ስለሚመጣው ገነት ከሰዎች ጋር ስንወያይ ብዙ ጊዜ መዝሙር 37:11⁠ን እናነባለን። እንዲህ ማድረጋችን ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ይህን ጥቅስ በተራራው ስብከት ላይ ጠቅሶታል፤ ይህም ጥቅሱ ወደፊት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ይጠቁማል። (ማቴ. 5:5) ይሁንና ዳዊት የተናገራቸው ቃላት፣ በንጉሥ ሰለሞን ዘመን ሕይወት ምን እንደሚመስልም ይጠቁማሉ። በሰለሞን የግዛት ዘመን የአምላክ ሕዝቦች ‘ወተትና ማር በምታፈሰው’ ምድር ላይ ለየት ያለ ሰላምና ብልጽግና አግኝተዋል። አምላክ ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ባወጣኋቸው ደንቦች መሠረት ብትሄዱ . . . በምድሪቱ ሰላም አሰፍናለሁ፤ እናንተም ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ።” (ዘሌ. 20:24፤ 26:3, 6) በሰለሞን የግዛት ዘመን ይህ ቃል ተፈጽሟል። (1 ዜና 22:9፤ 29:26-28) በተጨማሪም ክፉዎች ‘እንደማይኖሩ’ ትንቢቱ ይገልጻል። (መዝ. 37:10) በመሆኑም በመዝሙር 37:10, 11, 29 ላይ የሚገኙት ቃላት በጥንት ዘመን ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል፤ ወደፊትም ፍጻሜ ያገኛሉ።

9. የሳባ ንግሥት ስለ ንጉሥ ሰለሞን ግዛት ምን ብላለች?

9 እስራኤላውያን በሰለሞን ግዛት ሥር ስላገኙት ሰላምና ብልጽግና የሚገልጸው ወሬ ወደ ሳባ ንግሥት ጆሮ ደረሰ። በሩቅ አገር የምትኖረው ይህች ንግሥት ሁኔታውን በዓይኗ ማየት ስለፈለገች ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች። (1 ነገ. 10:1) የሰለሞንን መንግሥት ከቃኘች በኋላ እንዲህ አለች፦ “ግማሹ እንኳ አልተነገረኝም! . . . አብረውህ ያሉ ሰዎች ደስተኞች ናቸው፤ ዘወትር በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙት አገልጋዮችህም እጅግ ደስተኞች ናቸው!” (1 ነገ. 10:6-8) ሆኖም በሰለሞን የግዛት ዘመን የነበረው ሁኔታ ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ ግዛት ሥር ለሰው ልጆች ከሚያደርገው ነገር ጋር ሲወዳደር የቅምሻ ያህል ብቻ ነው።

10. ኢየሱስ ከሰለሞን የሚበልጠው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

10 ኢየሱስ በሁሉም መንገድ ከሰለሞን ይበልጣል። ሰለሞን ፍጹም ያልሆነ ሰው ነበር፤ ከባድ ስህተቶችንም ሠርቷል። በእነዚህ ስህተቶች ምክንያት በአምላክ ሕዝቦች ላይ መከራ አምጥቷል። ኢየሱስ ግን ፈጽሞ ስህተት የማይሠራ ፍጹም ንጉሥ ነው። (ሉቃስ 1:32፤ ዕብ. 4:14, 15) ኢየሱስ፣ ሰይጣን ያመጣበትን እጅግ ከባድ ፈተናዎች አልፏል። ክርስቶስ መቼም ቢሆን ኃጢአት እንደማይሠራ እንዲሁም ታማኝ ተገዢዎቹን የሚጎዳ ምንም ነገር እንደማያደርግ አስመሥክሯል። በእርግጥም ኢየሱስ ንጉሣችን በመሆኑ ልዩ ክብር ይሰማናል።

11. ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙት እነማን ናቸው?

11 ኢየሱስ የሰው ልጆችን ለማስተዳደርና ይሖዋ ለምድር ያለውን ዓላማ ለመፈጸም አብረውት የሚሠሩ 144,000 ተባባሪ ገዢዎች ይኖሩታል። (ራእይ 14:1-3) እነዚህ ቅቡዓን በምድር ላይ በነበሩበት ወቅት ብዙ ፈተናዎችንና መከራዎችን አሳልፈዋል። በመሆኑም ለሌሎች አዘኔታ የሚያሳዩ ገዢዎች ይሆናሉ። እነዚህ ተባባሪ ገዢዎች ምን ሚና ይጫወታሉ?

ቅቡዓኑ ምን ሚና ይጫወታሉ?

12. ይሖዋ ለ144,000ዎቹ ምን ሥራ ይሰጣቸዋል?

12 ለኢየሱስና ለተባባሪ ገዢዎቹ የተሰጣቸው ሥራ ለሰለሞን ከተሰጠው ሥራ እጅግ የላቀ ነው። የንጉሥ ሰለሞን ኃላፊነት፣ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ማስተዳደር ነበር። በአምላክ መንግሥት ውስጥ ሥልጣን የሚኖራቸው ገዢዎች ግን በመላው ዓለም የሚኖሩ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያስተዳድራሉ። በእርግጥም ይሖዋ ለ144,000ዎቹ የሚሰጣቸው መብት እጅግ ታላቅ ነው!

13. የኢየሱስ ተባባሪ ገዢዎች ምን ልዩ ሚና ይኖራቸዋል?

13 እንደ ኢየሱስ ሁሉ 144,000ዎቹም ነገሥታትና ካህናት ሆነው ያገለግላሉ። (ራእይ 5:10) በሙሴ ሕግ ሥር የካህናቱ ዋነኛ ኃላፊነት የሕዝቡን አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ጤንነት ማስጠበቅ ነበር። ሕጉ “ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ” ነው፤ በመሆኑም የኢየሱስ ተባባሪ ገዢዎች የአምላክ ሕዝቦች ያሏቸውን ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች በማሟላት ረገድ ልዩ ሚና ይኖራቸዋል ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው። (ዕብ. 10:1) እነዚህ ነገሥታትና ካህናት፣ በምድር ላይ ካሉት የመንግሥቱ ተገዢዎች ጋር የሐሳብ ግንኙነት የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ ወደፊት የምናየው ይሆናል። ይሖዋ የሚያደርገው ዝግጅት ምንም ይሁን ምን፣ ወደፊት በሚመጣው ገነት ውስጥ በምድር ላይ ያሉ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን መመሪያ እንደሚያገኙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ራእይ 21:3, 4

“ሌሎች በጎች” በገነት ውስጥ ለመኖር ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?

14. ‘በሌሎች በጎች’ እና ‘በትንሹ መንጋ’ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው?

14 ኢየሱስ አብረውት የሚገዙትን ሰዎች “ትንሽ መንጋ” በማለት ጠርቷቸዋል። (ሉቃስ 12:32) ኢየሱስ ስለ ሌላ ቡድን ማለትም ስለ ‘ሌሎች በጎችም’ ተናግሯል። እነዚህ ሁለት ቡድኖች አንድ መንጋ ናቸው። (ዮሐ. 10:16) ሁለቱ ቡድኖች አሁንም አብረው እየሠሩ ነው፤ ምድር ገነት በምትሆንበት ጊዜም ይህ ሁኔታ ይቀጥላል። እርግጥ በዚያ ወቅት ‘የትንሹ መንጋ’ አባላት በሰማይ ላይ ይሆናሉ፤ “ሌሎች በጎች” ደግሞ በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ የመኖር ተስፋ ይኖራቸዋል። ይሁንና “ሌሎች በጎች” በገነት ውስጥ ለመኖር የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ከአሁኑ ማድረግ ያለባቸው ነገር አለ።

በገነት ውስጥ ለመኖር እየተዘጋጀን እንዳለን ከአሁኑ ማሳየት እንችላለን (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት) b

15. (ሀ) “ሌሎች በጎች” የክርስቶስን ወንድሞች የሚደግፉት በምን መንገድ ነው? (ለ) መድኃኒት መደብር ውስጥ ያለውን ወንድም ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉን ተመልከት።)

15 ንስሐ የገባው ወንጀለኛ የሞተው፣ ለክርስቶስ ያለውን አድናቆት በተሟላ ሁኔታ ማሳየት የሚችልበት አጋጣሚ ሳያገኝ ነው። እኛ ‘የሌሎች በጎች’ አባላት ግን ለኢየሱስ ያለንን አድናቆት ለማሳየት የሚያስችል ብዙ አጋጣሚ አለን። ለምሳሌ በመንፈስ የተቀቡ ወንድሞቹን በምንይዝበት መንገድ ለእሱ ያለንን ፍቅር ማሳየት እንችላለን። ኢየሱስ ለበጎቹ የሚፈርድላቸው ይህን መሠረት አድርጎ እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴ. 25:31-40) በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት በመካፈል የክርስቶስን ወንድሞች መደገፍ እንችላለን። (ማቴ. 28:18-20) ለዚህም ሲባል፣ የተዘጋጁልንን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስተማሪያ መሣሪያዎች ጥሩ አድርገን እንጠቀምባቸዋለን፤ ከእነዚህ መሣሪያዎች መካከል ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው መጽሐፍ ይገኝበታል። እስካሁን ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን የምታስጠናው ሰው ካላገኘህ የቻልከውን ያህል ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ለመጋበዝ ለምን ግብ አታወጣም?

16. የአምላክ መንግሥት ዜጎች ለመሆን ከአሁኑ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?

16 ይሖዋ በገነት ውስጥ እንዲኖሩ የሚፈልጋቸው ዓይነት ሰዎች ለመሆን እዚያ እስክንገባ መጠበቅ አያስፈልገንም። ከአሁኑ በንግግራችንና በድርጊታችን ሐቀኛ ለመሆን እንዲሁም በልማዳችን ልከኛ ለመሆን ጥረት ማድረግ እንችላለን። ከዚህም ሌላ ለይሖዋ፣ ለትዳር ጓደኛችን እንዲሁም ለእምነት ባልንጀሮቻችን ታማኞች መሆን እንችላለን። በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ እየኖርን የአምላክን መሥፈርቶች በጥብቅ በተከተልን መጠን በገነት ውስጥ በአምላክ መሥፈርቶች መመራት ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል። በተጨማሪም በገነት ውስጥ ለመኖር እየተዘጋጀን እንዳለን ለማሳየት አንዳንድ ክህሎቶችንና ባሕርያትን ማዳበር እንችላለን። በዚህ መጽሔት ላይ የሚገኘውን “‘ምድርን ለመውረስ’ ዝግጁ ነህ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

17. ቀደም ሲል በፈጸምናቸው ኃጢአቶች የተነሳ በጥፋተኝነት ስሜት ልንዋጥ ይገባል? አብራራ።

17 ቀደም ሲል በፈጸምናቸው ከባድ ኃጢአቶች ምክንያት የሚሰማንን የጥፋተኝነት ስሜት ለማስወገድም ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እርግጥ የኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት ‘ሆን ብለን በኃጢአት ጎዳና ለመመላለስ’ ሰበብ ልናደርገው እንደማይገባ ግልጽ ነው። (ዕብ. 10:26-31) ሆኖም ለፈጸምነው ከባድ ኃጢአት ከልባችን ንስሐ ከገባን፣ ይሖዋ የሚሰጠውን እርዳታ ለማግኘት ጥረት ካደረግን እንዲሁም ምግባራችንን ካስተካከልን ይቅርታው ብዙ የሆነው አምላካችን ይቅር እንዳለን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ኢሳ. 55:7፤ ሥራ 3:19) ኢየሱስ ለፈሪሳውያን ምን እንዳላቸው አስታውስ፤ “እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ልጠራ ነው” ብሏቸዋል። (ማቴ. 9:13) የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ኃጢአታችንን በሙሉ ለመሸፈን የሚያስችል ኃይል አለው።

በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር ትችላለህ

18. ከኢየሱስ ጋር ከተሰቀለው ወንጀለኛ ጋር ስለ ምን ጉዳይ መነጋገር ትፈልጋለህ?

18 ከኢየሱስ ጋር የተሰቀለውን ወንጀለኛ በገነት ውስጥ ስታነጋግረው በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ሁለታችሁም ለኢየሱስ መሥዋዕት ያላችሁን አድናቆት እንደምትገልጹ ምንም ጥያቄ የለውም። ምናልባትም ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበሩት ጥቂት ሰዓታት ምን እንደተፈጸመ በዝርዝር እንዲተርክልህ እንዲሁም ኢየሱስ ጥያቄውን ስለመለሰለት ምን እንደተሰማው እንዲነግርህ ልትጠይቀው ትችላለህ። እሱ ደግሞ በሰይጣን ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር ሊጠይቅህ ይችላል። እንደዚህ ሰውዬ ካሉ ሰዎች ጋር የአምላክን ቃል ማጥናት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!—ኤፌ. 4:22-24

አንድ ወንድም ሊያሻሽለው ይጓጓ የነበረውን ክህሎት በሺህ ዓመቱ ወቅት በማዳበር ሲደሰት (አንቀጽ 19⁠ን ተመልከት)

19. በገነት ውስጥ ሕይወት አሰልቺ የማይሆነው ለምንድን ነው? (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)

19 በገነት ውስጥ ሕይወት በፍጹም አሰልቺ አይሆንም። ሁልጊዜ ደስ ከሚሉ ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንዲሁም ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት እንችላለን። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ በየቀኑ የሰማዩን አባታችንን ይበልጥ ማወቅ እንዲሁም እሱ ባደረገልን ዝግጅቶች መደሰት እንችላለን። ስለ እሱ የምንማረው ነገር አያልቅም። ስለ ፍጥረታቱም ብዙ የምንማረው ነገር ይኖራል። ዕድሜያችን በጨመረ መጠን ለአምላክ ያለን ፍቅር እያደገ ይሄዳል። ይሖዋና ኢየሱስ በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ስለሰጡን ምንኛ አመስጋኞች ነን!

መዝሙር 22 በሰማይ የተቋቋመው መንግሥት ይምጣልን!

a በገነት ውስጥ ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል ብዙ ጊዜ ታስባለህ? እንዲህ ማድረጋችን ያበረታታናል። ይሖዋ ስላዘጋጀልን ተስፋ አዘውትረን ባሰብን መጠን ስለ አዲሱ ዓለም ለሌሎች ስንናገር ይበልጥ ቅንዓት ይኖረናል። ይህ ርዕስ፣ ኢየሱስ ወደፊት ስለሚመጣው ገነት በገባው ቃል ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።

b የሥዕሉ መግለጫ፦ ትንሣኤ ያገኙትን ሰዎች ለማስተማር ተስፋ የሚያደርግ አንድ ወንድም በአሁኑ ወቅት ሌሎችን ሲያስተምር።