በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 52

ወንድሞቻችሁ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት እንዲቋቋሙ እርዷቸው

ወንድሞቻችሁ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት እንዲቋቋሙ እርዷቸው

“ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችል አቅም ካለህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አትበል።”—ምሳሌ 3:27

መዝሙር 103 እረኞች—ስጦታ የሆኑ ወንዶች

ማስተዋወቂያ a

1. ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡትን ጸሎት ብዙውን ጊዜ የሚመልሰው እንዴት ነው?

 ይሖዋ አገልጋዮቹ ያቀረቡትን ልባዊ ጸሎት ለመመለስ በአንተ ሊጠቀም እንደሚችል ታውቃለህ? የጉባኤ ሽማግሌም ሆንክ አገልጋይ፣ አቅኚም ሆንክ አስፋፊ ሊጠቀምብህ ይችላል። አረጋውያንም ሆኑ ወጣቶች፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ይሖዋ ሊጠቀምባቸው ይችላል። ይሖዋን የሚወድ አንድ ሰው እርዳታ ለማግኘት ወደ እሱ ሲጮኽ፣ አምላካችን ብዙውን ጊዜ ሽማግሌዎችና ሌሎች ታማኝ አገልጋዮቹ ለዚያ ሰው “የብርታት ምንጭ” እንዲሆኑለት ያደርጋል። (ቆላ. 4:11) ይሖዋንና ወንድሞቻችንን በዚህ መንገድ ማገልገል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ወረርሽኝ፣ አደጋ ወይም ስደት በሚያጋጥምበት ጊዜ ወንድሞቻችንን መርዳት እንችላለን።

በወረርሽኝ ወቅት ሌሎችን መርዳት

2. ወረርሽኝ ሲከሰት ሌሎችን መርዳት አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

2 ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ እርስ በርስ መረዳዳት ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ለምሳሌ ጓደኞቻችንን ሄደን መጠየቅ ብንፈልግም እንዲህ ማድረግ አደገኛ ሊሆን ይችላል። የኢኮኖሚ ችግር ያጋጠማቸውን ወንድሞቻችንን ምግብ መጋበዝ እንፈልግ ይሆናል፤ ሆኖም እንዲህ ማድረግ አይቻልም። ሌሎችን መርዳት ብንፈልግም የእኛም ቤተሰቦች ችግር ውስጥ ከሆኑ እንዲህ ማድረግ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ያም ቢሆን ወንድሞቻችንን መርዳት እንፈልጋለን፤ ይሖዋም እነሱን ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን ስናደርግ ይደሰታል። (ምሳሌ 3:27፤ 19:17) ታዲያ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?

3. በዴዚ ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ኤርምያስ 23:4)

3 ሽማግሌዎች ምን ማድረግ ይችላሉ? ሽማግሌ ከሆንክ መንጋውን በደንብ ለማወቅ ጥረት አድርግ። (ኤርምያስ 23:4ን አንብብ።) ቀደም ባለው የጥናት ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ዴዚ እንዲህ ብላለች፦ “በአገልግሎት ቡድናችን ውስጥ ያሉት ሽማግሌዎች ቀድሞውንም አብረውን ያገለግሉ እንዲሁም አብረውን ጊዜ ያሳልፉ ነበር።” b እነዚህ እረኞች እንዲህ ማድረጋቸው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከስቶ ዴዚ በቫይረሱ ምክንያት የቤተሰቧን አባላት ባጣችበት ወቅት እሷን መርዳት ቀላል እንዲሆንላቸው አድርጓል።

4. ሽማግሌዎች ዴዚን መርዳት የቻሉት ለምንድን ነው? ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት ይቻላል?

4 ዴዚ እንዲህ ብላለች፦ “ቀድሞውንም ከሽማግሌዎቹ ጋር እቀራረብ ስለነበር የሚሰማኝን ስሜት እንዲሁም የሚያስጨንቀኝን ነገር ለእነሱ መናገር ቀላል ሆኖልኛል።” ሽማግሌዎች፣ ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላላችሁ? ችግር ከመከሰቱ በፊት መንጋውን ተንከባከቡ። ጓደኛ ሁኑላቸው። የተከሰተው ወረርሽኝ በአካል ሄዳችሁ እንዳትጠይቋቸው ቢያግዳችሁ እንኳ በሌሎች መንገዶች እነሱን ለማግኘት ጥረት አድርጉ። ዴዚ እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ፣ በአንድ ቀን ውስጥ የተለያዩ ሽማግሌዎች ይደውሉልኝ ወይም የጽሑፍ መልእክት ይልኩልኝ ነበር። የጋበዙኝን ጥቅሶች ከዚህ በፊት በደንብ ባውቃቸውም ድጋሚ ሳነባቸው ልቤ በጥልቅ ተነክቷል።”

5. ሽማግሌዎች፣ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ምን እንደሚያስፈልጋቸው ማወቅና እነሱን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

5 ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ምን እንደሚያስፈልጋቸው ማወቅ የምትችሉበት አንዱ መንገድ በዘዴ ጥያቄዎችን መጠየቅ ነው። (ምሳሌ 20:5) በቂ ምግብ፣ መድኃኒት ወይም ሌሎች ቁሳቁሶች አሏቸው? ከሥራቸው የመፈናቀል አደጋ ተደቅኖባቸዋል? ወይም የቤት ኪራይ መክፈል ተቸግረዋል? መንግሥት የሚሰጠውን ድጎማ ለማግኘት በማመልከት ረገድ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል? ዴዚ ከእምነት ባልንጀሮቿ ቁሳዊ እርዳታ አግኝታለች። ሆኖም የደረሰባትን መከራ ለመቋቋም የረዳት ዋነኛው ነገር ከሽማግሌዎች ያገኘችው ስሜታዊና መንፈሳዊ ድጋፍ ነው። እንዲህ ብላለች፦ “ሽማግሌዎቹ አብረውኝ ይጸልዩ ነበር። ምን ብለው እንደጸለዩ በትክክል ባላስታውስም ያኔ የተሰማኝን ስሜት አልረሳውም። ይሖዋ በእነሱ ተጠቅሞ ‘ብቻሽን አይደለሽም’ እንዳለኝ ተሰምቶኛል።”—ኢሳ. 41:10, 13

ክፍል የሚያቀርበው ወንድም፣ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት የሚሳተፈው የታመመ ወንድም እንዲሁም በስብሰባ ላይ የተገኙት ብዙ ወንድሞች ሐሳብ ሲሰጡ በመስማቱ ተደስቷል (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)

6. የጉባኤው ወንድሞችና እህቶች ሌሎችን ለመርዳት ምን ማድረግ ይችላሉ?

6 ሌሎች ምን ማድረግ ይችላሉ? ሌሎችን በመርዳት ረገድ ሽማግሌዎች ቅድሚያውን እንደሚወስዱ እንጠብቃለን። ሆኖም ይሖዋ ሁላችንም ሌሎችን እንድናበረታታና እንድንረዳ ጋብዞናል። (ገላ. 6:10) ቀላል በሚመስል መንገድ እንኳ ፍቅራችንን መግለጻችን የታመሙ ወንድሞቻችንን በእጅጉ ሊያበረታታቸው ይችላል። ለምሳሌ አንድ ትንሽ ልጅ አንድን ወንድም ለማበረታታት ፖስት ካርድ ወይም ሥዕል ሊልክ ይችላል። አንድ ወጣት ለአንዲት እህት ሊላላክላት ወይም ዕቃ ሊገዛላት ይችል ይሆናል። ወይም ደግሞ ምግብ አዘጋጅተን ለታመመ ወንድማችን ልናደርስለት እንችል ይሆናል። እርግጥ በሽታው በከፍተኛ መጠን ከተስፋፋ የጉባኤው ወንድሞችና እህቶች በሙሉ ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ምናልባት በአካልም ሆነ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ስብሰባ ስናደርግ ከስብሰባው በኋላ ጥቂት ቆይተን ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንችል ይሆናል። ሽማግሌዎችም ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ሽማግሌዎች በወረርሽኝ ወቅት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሥራ ይበዛባቸዋል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ሽማግሌዎችን ለማመስገን ደብዳቤ ጽፈውላቸዋል። ‘እርስ በርስ ለመበረታታት እንዲሁም እርስ በርስ ለመተናነጽ’ የበኩላችንን ድርሻ መወጣታችን ምንኛ ጠቃሚ ነው!—1 ተሰ. 5:11

በአደጋ ወቅት ሌሎችን መርዳት

7. አደጋ ምን ችግር ሊያስከትል ይችላል?

7 አደጋዎች የአንድን ሰው ሕይወት በቅጽበት ሊያተረማምሱት ይችላሉ። የአደጋው ሰለባዎች ንብረታቸውን፣ ቤታቸውን አልፎ ተርፎም ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ሊያጡ ይችላሉ። ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም እንዲህ ያለው መከራ ሊደርስባቸው ይችላል። ታዲያ እነሱን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

8. አደጋ ከመከሰቱ በፊት ሽማግሌዎችና የቤተሰብ ራሶች ምን ማድረግ ይችላሉ?

8 ሽማግሌዎች ምን ማድረግ ይችላሉ? ሽማግሌዎች፣ ወንድሞቻችሁ አደጋ ከመከሰቱ በፊት እንዲዘጋጁ እርዷቸው። ሁሉም የጉባኤው ወንድሞችና እህቶች ራሳቸውን ከጉዳት ለመጠበቅ እንዲሁም ሽማግሌዎችን ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲያውቁ አድርጉ። ባለፈው የጥናት ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ማርጋሬት እንዲህ ብላለች፦ “ሽማግሌዎቻችን ‘ለጉባኤው እንደሚያስፈልግ’ በሚለው ክፍል ላይ፣ ሰደድ እሳት የሚከሰትበት ወቅት ገና እንዳላበቃ አስጠንቅቀውን ነበር። ባለሥልጣናቱ ቤታችንን ለቅቀን እንድንወጣ ካዘዙን ወይም ደህንነታችን አደጋ ላይ ከወደቀ ወዲያውኑ አካባቢውን መልቀቅ እንዳለብን ነገሩን።” ይህ ወቅታዊ መመሪያ ነበር፤ ምክንያቱም ከአምስት ሳምንት በኋላ ኃይለኛ ሰደድ እሳት ተከሰተ። ምናልባትም የቤተሰብ ራሶች በቤተሰብ አምልኮ ወቅት፣ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አደጋ ሲከሰት ምን ማድረግ እንዳለበት ሊከልሱ ይችላሉ። እናንተም ሆናችሁ ልጆቻችሁ በደንብ ከተዘጋጃችሁ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ መረጋጋት አይከብዳችሁም።

9. ሽማግሌዎች አደጋ ከመከሰቱ በፊትና በኋላ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

9 የቡድን የበላይ ተመልካች ከሆንክ፣ አደጋ ከመከሰቱ በፊት በመስክ አገልግሎት ቡድንህ ውስጥ ያሉት የሁሉም ወንድሞችና እህቶች ትክክለኛ አድራሻ እንዲኖርህ አድርግ። የአስፋፊዎችን አድራሻ የያዘ ዝርዝር አዘጋጅ። እንዲሁም በዝርዝሩ ውስጥ ያለው መረጃ ትክክል መሆኑን በየጊዜው አረጋግጥ። እንዲህ ካደረግክ፣ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት እያንዳንዱን አስፋፊ ማግኘትና ምን እንደሚያስፈልገው ማወቅ ትችላለህ። ከዚያም ከአስፋፊዎቹ ያገኘኸውን መረጃ ወዲያውኑ ለሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ስጠው፤ እሱም ሁኔታውን ለወረዳ የበላይ ተመልካቹ ያሳውቃል። የምታደርጉት የተቀናጀ ጥረት ትልቅ ለውጥ ያመጣል። የእነማርጋሬት የወረዳ የበላይ ተመልካች ሰደድ እሳቱ ከተከሰተ በኋላ ለ36 ሰዓታት ያህል አልተኛም ነበር፤ ምክንያቱም ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ 450 ገደማ ወንድሞችና እህቶች የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲያገኙ ለማድረግ ሽማግሌዎችን ሲያስተባብር ነበር። (2 ቆሮ. 11:27) በመሆኑም ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት በሙሉ ማረፊያ ማግኘት ችለዋል።

10. ሽማግሌዎች ለእረኝነት ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለምንድን ነው? (ዮሐንስ 21:15)

10 ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከሚያከናውኑት ሥራ መካከል መንፈሳዊና ስሜታዊ ድጋፍ መስጠት ይገኝበታል። (1 ጴጥ. 5:2) አደጋ በሚከሰትበት ወቅት፣ ሽማግሌዎች በመጀመሪያ እያንዳንዱ አስፋፊ ደህና መሆኑን እንዲሁም ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ማግኘቱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ሆኖም አደጋው የደረሰባቸው ክርስቲያኖች፣ አደጋው ከተከሰተ በኋላ ባሉት በርካታ ወራት ስሜታዊና መንፈሳዊ ድጋፍ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። (ዮሐንስ 21:15ን አንብብ።) በቅርንጫፍ ኮሚቴ አባልነት የሚያገለግለውና በአደጋ ከተጎዱ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ጋር የተገናኘው ሃሮልድ እንዲህ ብሏል፦ “ከአደጋው ለማገገም ጊዜ ይወስዳል። ሕይወታቸው ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞው እየተመለሰ ቢመጣም እንኳ በሞት ያጡትን ወዳጅ ዘመዳቸውን፣ በጣም የሚወዱትን ዕቃ ወይም ከአደጋው ለጥቂት ያመለጡበትን ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ሊያስታውሱ ይችላሉ። እነዚህ ትዝታዎች ደግሞ እንደ አዲስ ሐዘናቸውን ሊቀሰቅሱባቸው ይችላሉ። እንዲህ ያለው ስሜት እምነት እንደጎደላቸው የሚያሳይ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ማንኛውም ሰው ሊሰማው የሚችለው ተፈጥሯዊ ስሜት ነው።”

11. ቤተሰቦች በቀጣይነት ምን ዓይነት እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል?

11 ሽማግሌዎች “ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ያደርጋሉ። (ሮም 12:15) አደጋ የደረሰባቸው ክርስቲያኖች የይሖዋንም ሆነ የወንድሞቻቸውን ፍቅር እንዳላጡ ማረጋገጫ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ሽማግሌዎች፣ ቤተሰቦች በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አዘውትረው መካፈላቸውን እንዲቀጥሉ ሊያበረታቷቸው ይገባል፤ ከእነዚህ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካከል ጸሎት፣ ጥናት፣ በስብሰባ ላይ መገኘት እንዲሁም በስብከቱ ሥራ መካፈል ይገኙበታል። በተጨማሪም ወላጆች ልጆቻቸውን በየትኛውም አደጋ ሊጠፉ በማይችሉ ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ ሊረዷቸው ይገባል፤ ወላጆች እንዲህ እንዲያደርጉ ሽማግሌዎች ሊያበረታቷቸው ይችላሉ። ወላጆች፣ ልጆቻችሁን ይሖዋ ምንጊዜም ወዳጃቸው እንደሚሆን እንዲሁም ሁሌም እንደሚደርስላቸው አስታውሷቸው። በተጨማሪም ምንጊዜም እነሱን ለመርዳት ዝግጁ የሆኑ ወንድሞችንና እህቶችን የያዘ ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ እንዳላቸው ግለጹላቸው።—1 ጴጥ. 2:17

በምትኖርበት አካባቢ አደጋ ከተከሰተ እርዳታ ማበርከት ትችላለህ? (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት) e

12. ሌሎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ ለማበርከት ምን ማድረግ ይችላሉ? (ሥዕሉን ተመልከት።)

12 ሌሎች ምን ማድረግ ይችላሉ? ከምትኖርበት አካባቢ ብዙም ሳይርቅ አደጋ ከተከሰተ እርዳታ ማበርከት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ሽማግሌዎችን ጠይቃቸው። ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ አስፋፊዎችን ወይም የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞችን በቤትህ ማሳረፍ ትችል ይሆናል። እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው አስፋፊዎች ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን ማድረስም ትችላለህ። አደጋ የተከሰተው ከምትኖርበት አካባቢ ርቆ ቢሆንም እንኳ እርዳታ ማበርከት ትችላለህ። እንዴት? በአደጋው ለተጎዱ ሰዎች በመጸለይ ነው። (2 ቆሮ. 1:8-11) ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ በማድረግ የእርዳታ ሥራውን በገንዘብ መደገፍም ትችል ይሆናል። (2 ቆሮ. 8:2-5) አደጋ ወደደረሰበት አካባቢ ተጉዘህ እርዳታ ማበርከት የምትችል ከሆነ በሥራው ለመካፈል ራስህን ማቅረብ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ሽማግሌዎችን አማክራቸው። በዚህ ሥራ እንድትካፈል ከተጋበዝክ ሥልጠና ሊሰጥህ ይችላል፤ ከዚያም በምትፈለግበት ጊዜና ቦታ እርዳታ ማበርከት ትችላለህ።

ወንድሞቻችን ስደትን እንዲቋቋሙ መርዳት

13. ሥራችን በታገደበት አገር ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞቻችን ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል?

13 ሥራችን በታገደባቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞቻችን የሚደርስባቸው ስደት ሕይወታቸውን ይበልጥ ከባድ ያደርግባቸዋል። እነዚህ ወንድሞች እንደ ማንኛውም ሰው የኢኮኖሚ ችግር ያጋጥማቸዋል፤ ይታመማሉ፤ እንዲሁም የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ያጣሉ። ሆኖም በእገዳው ምክንያት ሽማግሌዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ወይም ማበረታቻ ከሚያስፈልጋቸው ክርስቲያኖች ጋር በነፃነት መነጋገር አይችሉ ይሆናል። ቀደም ባለው የጥናት ርዕስ ላይ የተጠቀሰው አንድሬ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞታል። በአገልግሎት ቡድኑ ውስጥ ያለች አንዲት እህት የኢኮኖሚ ችግር አጋጥሟት ነበር። ከዚያም የመኪና አደጋ ደረሰባት። በተደጋጋሚ ቀዶ ሕክምና ስለተደረገላት ሥራ መሥራት አልቻለችም። እገዳውና ወረርሽኙ ቢኖርም እንኳ ወንድሞች እሷን ለመርዳት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ አደረጉ። ይሖዋም ጥረታቸውን ተመልክቷል።

14. ሽማግሌዎች በይሖዋ በመታመን ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?

14 ሽማግሌዎች ምን ማድረግ ይችላሉ? አንድሬ ወደ ይሖዋ ጸለየ፤ እንዲሁም ማድረግ የሚችለውን ነገር አደረገ። ታዲያ ይሖዋ ጸሎቱን የመለሰለት እንዴት ነው? ከእሱ ይበልጥ በነፃነት መንቀሳቀስ የሚችሉ ወንድሞችን ተጠቀመ። አንዳንዶቹ፣ እህት ወደ ሆስፒታል በምትሄድበት ጊዜ በመኪናቸው ይወስዷት ነበር። ሌሎች ደግሞ የገንዘብ እርዳታ አበረከቱላት። ይሖዋ አቅማቸው የፈቀደውን እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል፤ በተጨማሪም በኅብረትና በድፍረት ያደረጉትን ጥረት ባርኮላቸዋል። (ዕብ. 13:16) ሽማግሌዎች፣ በሥራችን ላይ ገደብ በሚጣልበት ጊዜ የሌሎችን እርዳታ ጠይቁ። (ኤር. 36:5, 6) ከሁሉ በላይ ደግሞ በይሖዋ ታመኑ። ይሖዋ ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን እንድታግዙ ይረዳችኋል።

15. በስደት ወቅት ክርስቲያናዊ አንድነታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

15 ሌሎች ምን ማድረግ ይችላሉ? በእገዳ ሥር ስንሆን የምንሰበሰበው በትናንሽ ቡድኖች ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መመሥረት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ ይሆናል። እርስ በርስ ከመጣላት ይልቅ ከሰይጣን ጋር ተዋጉ። ወንድሞቻችሁ የሚሠሯቸውን ስህተቶች ችላ ብላችሁ ለማለፍ ሞክሩ። አለመግባባት ከተፈጠረ ደግሞ ችግሩን ቶሎ ለመፍታት ጥረት አድርጉ። (ምሳሌ 19:11፤ ኤፌ. 4:26) እርስ በርስ ለመረዳዳት ቅድሚያውን ውሰዱ። (ቲቶ 3:14) ወንድሞችና እህቶች ለእህት እርዳታ በማበርከታቸው መላው የአገልግሎት ቡድን ተጠቅሟል። እንደ ቤተሰብ እርስ በርስ ተቀራርበዋል።—መዝ. 133:1

16. በቆላስይስ 4:3, 18 መሠረት ስደት የሚደርስባቸውን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

16 መንግሥታት እገዳ በጣሉባቸው አገሮች ውስጥ ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች አሉ። አንዳንዶቹ በእምነታቸው ምክንያት ታስረዋል። ለእነዚህ ወንድሞች፣ ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም የራሳቸውን ነፃነት አደጋ ላይ ጥለው ለእነሱ መንፈሳዊ፣ ሥጋዊና ሕግ ነክ ድጋፍ ለሚሰጡ ወንድሞች መጸለይ እንችላለን። c (ቆላስይስ 4:3, 18ን አንብብ።) የምታቀርበው ጸሎት ያለውን ኃይል ፈጽሞ አቅልለህ አትመልከት!—2 ተሰ. 3:1, 2፤ 1 ጢሞ. 2:1, 2

ቤተሰብህን ከአሁኑ ለስደት ማዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)

17. ለስደት ከአሁኑ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?

17 እናንተም ሆናችሁ ቤተሰቦቻችሁ ለስደት ከአሁኑ መዘጋጀት ትችላላችሁ። (ሥራ 14:22) ሊያጋጥሟችሁ የሚችሉትን መጥፎ ነገሮች እያሰባችሁ አትብሰልሰሉ። ከዚህ ይልቅ ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት አጠናክሩ፤ ልጆቻችሁም እንደዚያው እንዲያደርጉ እርዷቸው። አልፎ አልፎ ጭንቀት የሚሰማችሁ ከሆነ ልባችሁን በይሖዋ ፊት አፍስሱ። (መዝ. 62:7, 8) በይሖዋ ለመተማመን የሚያነሳሷችሁን ምክንያቶች በቤተሰብ ሆናችሁ ተወያዩ። d ለአደጋ አስቀድሞ መዘጋጀት ልጆቻችሁን እንደሚጠቅማቸው ተመልክተናል። ከስደት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አስቀድማችሁ መዘጋጀታችሁና በይሖዋ መታመናችሁ በስደት ወቅት ልጆቻችሁ ድፍረትና ሰላም እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል።

18. ወደፊት ምን ይጠብቀናል?

18 የአምላክ ሰላም የደህንነት ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል። (ፊልጵ. 4:6, 7) በአሁኑ ጊዜ በሽታ፣ አደጋ ወይም ስደት ሊደርስብን ቢችልም ይሖዋ በዚህ ሰላም አማካኝነት ልባችንን ያረጋጋልናል። ትጉ የሆኑ ሽማግሌዎችን ተጠቅሞ ይንከባከበናል። በተጨማሪም ለሁላችንም እርስ በርስ የመረዳዳት መብት ሰጥቶናል። በአሁኑ ጊዜ የምናገኘው ሰላም ‘ታላቁን መከራ’ ጨምሮ ወደፊት የሚያጋጥሙንን ከባድ ፈተናዎች ለመጋፈጥ ያዘጋጀናል። (ማቴ. 24:21) በታላቁ መከራ ወቅት ሰላማችንን መጠበቅ እንዲሁም ሌሎችም ሰላማቸውን እንዲጠብቁ መርዳት ይኖርብናል። ከዚያ ጊዜ በኋላ ግን የሚያስጨንቁ ችግሮች አያጋጥሙንም። በስተ መጨረሻ፣ ይሖዋ ከመጀመሪያው አንስቶ ያሰበልንን ፍጹምና ዘላቂ ሰላም እናጣጥማለን።—ኢሳ. 26:3, 4

መዝሙር 109 አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ

a ይሖዋ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ሕዝቦቹን ለመርዳት ብዙውን ጊዜ ታማኝ አገልጋዮቹን ይጠቀማል። ለወንድሞችህና ለእህቶችህ የብርታት ምንጭ እንድትሆን አንተንም ሊጠቀምብህ ይችላል። ወንድሞቻችን ችግር ሲያጋጥማቸው ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

c በእስር ላሉ ወንድሞችና እህቶች የሚላኩ ደብዳቤዎችን በቅርንጫፍ ቢሮው ወይም በዋናው መሥሪያ ቤት በኩል መላክ አይቻልም።

d በሐምሌ 2019 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ከአሁኑ ለስደት ተዘጋጁ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

e የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ባልና ሚስት አደጋ ከደረሰ በኋላ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ለሚገኝ አንድ ቤተሰብ ምግብ ሲያደርሱ።