በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በመዝሙር 61:8 ላይ ዳዊት የአምላክን ስም “ለዘላለም” እንደሚያወድስ ተናግሯል። ዳዊት ይህን ሲል ማጋነኑ ወይም ፈጽሞ እንደማይሞት መናገሩ ነበር?

አልነበረም። ዳዊት የጻፈው ሐሳብ ትክክለኛና እውነታውን ከግምት ያስገባ ነበር።

ዳዊት በዚህ ጥቅስም ሆነ በሌሎች ተመሳሳይ ጥቅሶች ላይ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “እኔም ስእለቴን በየቀኑ ስፈጽም፣ ለስምህ ለዘላለም የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ።” “ይሖዋ አምላኬ ሆይ፣ በሙሉ ልቤ አወድስሃለሁ፤ ስምህንም ለዘላለም ከፍ ከፍ አደርጋለሁ።” “ለዘላለም ስምህን አወድሳለሁ።”—መዝ. 61:8፤ 86:12፤ 145:1, 2

ዳዊት ይህን ሲል ማጋነኑ ወይም መቼም እንደማይሞት መግለጹ አልነበረም። ይሖዋ፣ ሰዎች ኃጢአተኛ በመሆናቸው እንደሚሞቱ መግለጹን ዳዊት ያውቅ ነበር። በተጨማሪም ዳዊት ኃጢአተኛ መሆኑን አምኖ ተቀብሏል። (ዘፍ. 3:3, 17-19፤ መዝ. 51:4, 5) እንደ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ያሉ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሰዎች እንኳ እንደሞቱ ያውቃል። እሱም ቢሆን እንደሚሞት ያውቅ ነበር። (መዝ. 37:25፤ 39:4) ሆኖም በመዝሙር 61:8 ላይ የተናገራቸው ቃላት፣ አምላክን ለዘላለም ይኸውም እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ለማወደስ ያለውን ፍላጎትና ቁርጠኝነት ያሳያሉ።—2 ሳሙ. 7:12

ዳዊት የጻፋቸው አንዳንድ ሐሳቦች በወቅቱ ከነበረው ሕይወት ጋር የተያያዙ ናቸው። በመዝሙር 18፣ 51 እና 52 አናት ላይ ያሉት መግለጫዎች ይህን ያሳያሉ። ዳዊት በመዝሙር 23 ላይ ይሖዋን አመራር፣ እረፍትና ጥበቃ እንደሚሰጥ እረኛ አድርጎ ገልጾታል። ዳዊት እንዲህ ያለ እረኛ ነበር። እንዲሁም ‘ዕድሜውን በሙሉ’ አምላክን ማገልገል ይፈልግ ነበር።—መዝ. 23:6

ከዚህም ሌላ፣ ዳዊት መዝሙሮቹን እንዲጽፍ በመንፈሱ የመራው ይሖዋ እንደሆነ አስታውስ። ከጻፋቸው ነገሮች መካከል ከረጅም ጊዜ በኋላ የሚፈጸሙ ትንቢቶች ይገኙበታል። ለምሳሌ በመዝሙር 110 ላይ ዳዊት፣ ጌታው በሰማይ በአምላክ ‘ቀኝ የሚቀመጥበት’ እና ታላቅ ሥልጣን የሚቀበልበት ጊዜ እንደሚመጣ ጽፏል። ሥልጣን የሚቀበለው ምን ለማድረግ ነው? የአምላክን ጠላቶች ድል ለማድረግና በምድር ባሉ ‘ብሔራት ላይ የፍርድ እርምጃ ለመውሰድ’ ነው። ዳዊት፣ ከሰማይ ሆኖ የሚገዛውና “ለዘላለም ካህን” የሚሆነው የዚህ መሲሕ ቅድመ አያት ነበር። (መዝ. 110:1-6) ኢየሱስ በመዝሙር 110 ላይ የሚገኘው ትንቢት ስለ እሱ የሚናገር እንደሆነና ፍጻሜውን የሚያገኘው ወደፊት እንደሆነ ገልጿል።—ማቴ. 22:41-45

ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ዳዊት በመንፈስ ተመርቶ፣ እሱ ስለኖረበት ዘመንም ሆነ ወደፊት ከሞት ተነስቶ ይሖዋን ለዘላለም ስለሚያወድስበት ዘመን ጽፏል። ከዚህ አንጻር መዝሙር 37:10, 11, 29 በጥንቷ እስራኤል ስለነበረው ሁኔታ እንዲሁም ወደፊት የአምላክ ተስፋዎች ሲፈጸሙ በመላው ዓለም ስለሚሰፍነው ሁኔታ የሚገልጽ እንደሆነ መረዳት እንችላለን።—በዚህ መጽሔት ላይ የሚገኘውን “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” የሚለውን ርዕስ አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት።

ስለዚህ መዝሙር 61:8 እና ሌሎች ተመሳሳይ ጥቅሶች፣ ዳዊት በጥንቷ እስራኤል እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ይሖዋን ማክበር ይፈልግ እንደነበር ያሳያሉ። በተጨማሪም ዳዊት ወደፊት ይሖዋ ከሞት ሲያስነሳው ማድረግ የሚችለውን ነገር በትክክል ይገልጻሉ።