በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 51

ተስፋችን ለሐዘን አይዳርገንም

ተስፋችን ለሐዘን አይዳርገንም

“[ተስፋው] ሳይፈጸም ቀርቶ ለሐዘን አይዳርገንም።”—ሮም 5:5

መዝሙር 142 ተስፋችንን አጥብቀን እንያዝ

ማስተዋወቂያ a

1. አብርሃም ይሖዋ በሰጠው ተስፋ ማመኑ ተገቢ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

 ይሖዋ ለወዳጁ ለአብርሃም የምድር ብሔራት ሁሉ በዘሩ አማካኝነት እንደሚባረኩ ቃል ገብቶለት ነበር። (ዘፍ. 15:5፤ 22:18) አብርሃም በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ስለነበረው ይህ ቃል እንደሚፈጸም እርግጠኛ ነበር። ያም ቢሆን አብርሃም 100 ዓመት፣ ሣራ ደግሞ 90 ዓመት ሞልቷቸውም እንኳ እነዚህ ታማኝ ባልና ሚስት ልጅ አልነበራቸውም። (ዘፍ. 21:1-7) ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ “[አብርሃም] በተነገረው መሠረት የብዙ ብሔራት አባት እንደሚሆን በተሰጠው ተስፋ አምኗል” ይላል። (ሮም 4:18) የአብርሃም ተስፋ እንደተፈጸመ እናውቃለን። ለረጅም ጊዜ ሲጠብቅ እንደነበረው ይስሐቅን ወልዷል። አብርሃም፣ ይሖዋ በገባው ቃል ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖረው የረዳው ምንድን ነው?

2. አብርሃም ይሖዋ የሰጠው ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኛ የሆነው ለምንድን ነው?

2 አብርሃም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ስለነበረው “አምላክ የሰጠውን ተስፋ መፈጸም እንደሚችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር።” (ሮም 4:21) አብርሃም እምነት በማሳየቱ የተነሳ ይሖዋ ሞገሱን አሳይቶታል፤ እንደ ጻድቅ አድርጎም ቆጥሮታል። (ያዕ. 2:23) ሮም 4:18 እንደሚገልጸው አብርሃም እምነትም ተስፋም ነበረው። ከዚህ በመቀጠል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ምዕራፍ 5 ላይ ስለ ተስፋ ምን እንዳለ እንመለከታለን።

3. ጳውሎስ ስለ ተስፋ ምን ተናግሯል?

3 ጳውሎስ ‘ተስፋችን ሳይፈጸም ቀርቶ ለሐዘን እንደማይዳርገን’ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምን እንደሆነ አብራርቷል። (ሮም 5:5) በተጨማሪም ክርስቲያናዊ ተስፋችንን ማጠናከር የምንችለው እንዴት እንደሆነ ገልጾልናል። ጳውሎስ በሮም 5:1-5 ላይ የጠቀሰውን ሐሳብ ስንመረምር የራስህን ሁኔታ መለስ ብለህ ለማሰብ ሞክር። እንዲህ ስታደርግ ክርስቲያናዊ ተስፋህ በጊዜ ሂደት ይበልጥ እንደተጠናከረ ማስተዋልህ አይቀርም። ከዚህም ሌላ፣ የምናደርገው ውይይት ተስፋህን ከአሁኑ ይበልጥ ማጠናከር የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ይረዳሃል። መጀመሪያ ግን፣ ጳውሎስ ለሐዘን አይዳርገንም ያለው ክብራማ ተስፋ ምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ክብራማ ተስፋችን

4. ሮም 5:1, 2 የሚናገረው ስለ ምን ጉዳይ ነው?

4 ሮም 5:1, 2ን አንብብ። ጳውሎስ እዚህ ላይ ያለውን ሐሳብ የጻፈው በሮም ለነበረው ጉባኤ ነው። በዚያ የነበሩት ወንድሞችና እህቶች ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ተምረዋል፤ እምነት አዳብረዋል፤ እንዲሁም ክርስቲያኖች ሆነዋል። በመሆኑም አምላክ ‘በእምነት አማካኝነት ጻድቃን ናችሁ ብሏቸዋል’፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ቀብቷቸዋል። አዎ፣ አስተማማኝና አስደናቂ ተስፋ አግኝተዋል።

5. የቅቡዓን ክርስቲያኖች ተስፋ ምንድን ነው?

5 ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ፣ በኤፌሶን ለነበሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለተጠሩበት ተስፋ ጽፎላቸዋል። ይህ ተስፋ ‘ለቅዱሳን የተዘጋጀውን ውርሻ’ መቀበልን ያካትታል። (ኤፌ. 1:18) በተጨማሪም ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ተስፋቸው የሚፈጸመው የት እንደሆነ ነግሯቸዋል። ‘በሰማይ የሚጠብቃችሁ ተስፋ’ በማለት ጠርቶታል። (ቆላ. 1:4, 5) በመሆኑም የቅቡዓን ክርስቲያኖች ተስፋ ከሞት ተነስተው በሰማይ የዘላለም ሕይወት ማግኘትና ከክርስቶስ ጋር መግዛት ነው።—1 ተሰ. 4:13-17፤ ራእይ 20:6

ወንድም ፍሬድሪክ ፍራንዝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በተስፋቸው ላይ ያላቸውን እምነት ግሩም አድርጎ ገልጾታል (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)

6. አንድ ቅቡዕ ወንድም ስለ ተስፋው ምን ብሏል?

6 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይህን ተስፋ ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። በመንፈስ የተቀባ ክርስቲያን የሆነው ወንድም ፍሬድሪክ ፍራንዝ ስለ ተስፋው ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ተስፋችን እርግጠኛ ነገር ነው። የትንሹ መንጋ አባላት ለሆኑት 144,000 ሰዎች በሙሉ ከምንገምተው በላይ በሆነ መጠን ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል።” ወንድም ፍራንዝ ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ሲያገለግል ከቆየ በኋላ በ1991 እንዲህ ብሏል፦ “ለዚህ ተስፋ ዋጋማነት ያለንን ከፍተኛ ግምት አላጣንም። . . . ተስፋችንን እየጠበቅን የምንቆይበት ጊዜ በረዘመ መጠን ለተስፋው ያለን አድናቆት ጨምሯል። ለሚሊዮን ዓመታት የሚያስጠብቅ ቢሆንም እንኳ ሊጠባበቁት የሚገባ ተስፋ ነው። ተስፋችንን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ።”

7-8. የአብዛኞቹ ክርስቲያኖች ተስፋ ምንድን ነው? (ሮም 8:20, 21)

7 በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች ተስፋቸው ከዚህ የተለየ ነው። እንደ አብርሃም በአምላክ መንግሥት ሥር በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ያደርጋሉ። (ዕብ. 11:8-10, 13) ጳውሎስ፣ ይህ ተስፋ ያላቸው ሰዎች የሚጠብቃቸውን አስደናቂ በረከት ገልጿል። (ሮም 8:20, 21ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚሰጠውን ተስፋ ለመጀመሪያ ጊዜ ስታውቅ በጣም የማረከህ ምን ነበር? ፍጹምና ከኃጢአት የጸዳህ እንደምትሆን የሚገልጸው ተስፋ ነው? ወይስ በሞት የተለዩህ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ እንደሚኖሩ የሚገልጸው ተስፋ? እነዚህ ተስፋዎች የሚፈጸሙበትን ጊዜ ለማየት ጓጉተህ መሆን አለበት።

8 ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የምናደርገው በሰማይም ይሁን በምድር አስደሳች የሆነ ክብራማ ተስፋ አለን። ደግሞም ተስፋችን እየተጠናከረ መሄድ ይችላል። ጳውሎስ ቀጥሎ የጻፈው ሐሳብ ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት እንደሆነ ይገልጻል። ጳውሎስ ስለ ተስፋችን ምን ብሎ እንደጻፈ እስቲ እንመልከት። እንዲህ ማድረጋችን ተስፋችን እውን እንደሚሆንና ለሐዘን እንደማይዳርገን ይበልጥ እንድንተማመን ያደርገናል።

ተስፋችን የሚጠናከረው እንዴት ነው?

ሁሉም ክርስቲያኖች በሆነ መልኩ መከራ እንደሚደርስባቸው ሊጠብቁ ይገባል (ከአንቀጽ 9-10⁠ን ተመልከት)

9-10. የጳውሎስ ምሳሌ እንደሚያሳየው ክርስቲያኖች ምን እንደሚደርስባቸው ሊጠብቁ ይገባል? (ሮም 5:3) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

9 ሮም 5:3ን አንብብ። ጳውሎስ መከራ ተስፋችንን ሊያጠናክረው እንደሚችል ገልጿል። ይህ ሐሳብ ሊያስገርመን ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሁሉም የክርስቶስ ተከታዮች መከራ እንደሚደርስባቸው ሊጠብቁ ይገባል። የጳውሎስን ምሳሌ እንመልከት። በተሰሎንቄ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አብረናችሁ በነበርንበት ጊዜ መከራ መቀበላችን እንደማይቀር አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ ደግሞም እንደምታውቁት ይኸው ነገር ደርሷል።” (1 ተሰ. 3:4) በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ደግሞ “ወንድሞች . . . ስለደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንፈልጋለን። . . . በሕይወት የመትረፍ ተስፋችን እንኳ ተሟጦ ነበር” ብሏቸዋል።—2 ቆሮ. 1:8፤ 11:23-27

10 በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም በሆነ መልኩ መከራ እንደሚደርስባቸው ሊጠብቁ ይገባል። (2 ጢሞ. 3:12) አንተስ በኢየሱስ በማመንህና እሱን በመከተልህ የተነሳ መከራ ደርሶብሃል? ምናልባትም ጓደኞችህና ዘመዶችህ አፊዘውብህ ይሆናል። ይባስ ብሎም ስደት አድርሰውብህ ሊሆን ይችላል። በሁሉም ነገር ሐቀኛ ለመሆን ያደረግከው ውሳኔ በሥራ ቦታህ ችግር አስከትሎብሃል? (ዕብ. 13:18) ተስፋህን ለሌሎች በማካፈልህ የተነሳ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተቃውመውሃል? ይሁንና የሚደርስብን መከራ ምንም ይሁን ምን ጳውሎስ ልንደሰት እንደሚገባ ገልጿል። ለምን?

11. ማንኛውንም ፈተና በጽናት ለመቋቋም ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

11 መከራ ሲደርስብን የምንደሰተው የሚያስገኝልንን ጥቅም ስለምናውቅ ነው። ሮም 5:3 እንደሚለው ‘መከራ ጽናትን ያስገኛል።’ ሁሉም ክርስቲያኖች መከራ ስለሚደርስባቸው ሁሉም ክርስቲያኖች መጽናት ያስፈልጋቸዋል። የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና በጽናት ለመቋቋም ቁርጥ ውሳኔ ልናደርግ ይገባል። ተስፋችን ሲፈጸም ማየት የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። ኢየሱስ በድንጋያማ መሬት ላይ ስለተዘራው ዘር በሚገልጸው ምሳሌ ላይ የጠቀሳቸውን ዓይነት ሰዎች መሆን አንፈልግም። እንዲህ ያሉት ሰዎች ቃሉን ሲሰሙ በደስታ ቢቀበሉም ‘መከራ ወይም ስደት ሲደርስባቸው’ ይሰናከላሉ። (ማቴ. 13:5, 6, 20, 21) ተቃውሞና መከራ አስደሳች ወይም ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ሆኖም መከራን በጽናት መቋቋማችን ጥቅም ያስገኝልናል። እንዴት?

12. ፈተናን በጽናት ስንቋቋም ምን ጥቅም እናገኛለን?

12 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ፈተናን በጽናት መቋቋም የሚያስገኘውን ጥቅም ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “በሁሉም ረገድ ምንም የማይጎድላችሁ ፍጹማንና እንከን የለሽ እንድትሆኑ ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም።” (ያዕ. 1:2-4) ያዕቆብ፣ ጽናት የሚያከናውነው ሥራ እንዳለ ተናግሯል። ለመሆኑ ይህ ሥራ ምንድን ነው? እንደ ትዕግሥትና እምነት ያሉትን ባሕርያት በተሻለ ሁኔታ እንድናዳብር እንዲሁም በአምላክ ይበልጥ እንድንታመን ሊረዳን ይችላል። ሆኖም መጽናታችን ሌላም ወሳኝ ጥቅም ያስገኝልናል።

13-14. ጽናት ምን ያስገኛል? ይህስ ከተስፋ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? (ሮም 5:4)

13 ሮም 5:4ን አንብብ። ጳውሎስ “[ጽናት] በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንድናገኝ ያስችለናል” ብሏል። ከጸናህ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ታገኛለህ። ይህ ሲባል ግን ይሖዋ ፈተና ወይም ችግር ስላጋጠመህ ይደሰታል ማለት አይደለም። ይሖዋ የሚደሰተው በአንተ ነው። መጽናታችን የይሖዋን ልብ እንደሚያስደስተው ማወቃችን በጣም የሚያበረታታ ነው።—መዝ. 5:12

14 አብርሃም ፈተናን በጽናት በመቋቋሙ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘ አስታውስ። ይሖዋ እንደ ወዳጁ አድርጎ ተመልክቶታል፤ ጻድቅ አድርጎም ቆጥሮታል። (ዘፍ. 15:6፤ ሮም 4:13, 22) እኛም እንዲሁ ሊባልልን ይችላል። አምላክ ሞገሱን የሚያሳየን በእሱ አገልግሎት ያከናወንነውን ሥራ ወይም ያለንን መብት መሠረት አድርጎ አይደለም። ሞገስ የሚያሳየን በታማኝነት በመጽናታችን ነው። ደግሞም ዕድሜያችን፣ ያለንበት ሁኔታ ወይም ችሎታችን ምንም ይሁን ምን ሁላችንም መጽናት እንችላለን። በአሁኑ ጊዜ እየደረሰብህ ያለውን መከራ በጽናት እየተቋቋምክ ነው? ከሆነ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘህ ማወቅህ ሊያጽናናህ ይችላል። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘን ማወቃችን ተስፋችንን ሊያጠናክርልን ይችላል።

ጠንካራ ተስፋ

15. ጳውሎስ በመቀጠል ምን አለ? ይህስ አንዳንዶችን ግራ ሊያጋባ የሚችለው ለምንድን ነው?

15 ጳውሎስ እንደገለጸው ፈተናዎችን በጽናት ስንቋቋም በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እናገኛለን። ጳውሎስ ማብራሪያውን ሲቀጥል እንዲህ ብሏል፦ “ተቀባይነት ማግኘት ደግሞ ተስፋን ያጎናጽፋል፤ ተስፋውም ሳይፈጸም ቀርቶ ለሐዘን አይዳርገንም።” (ሮም 5:4, 5) ይህ ሐሳብ አንዳንዶችን ግራ ያጋባ ይሆናል። ለምን? ምክንያቱም ቀደም ሲል ጳውሎስ በሮም 5:2 ላይ በሮም ያሉ ክርስቲያኖች ተስፋ እንዳላቸው ጽፏል፤ ‘የአምላክን ክብር ለማግኘት ተስፋ’ እንደሚያደርጉ ገልጿል። ከዚህ አንጻር ‘እነዚህ ክርስቲያኖች ቀድሞውንም ተስፋ ካላቸው ጳውሎስ ተስፋን በድጋሚ የጠቀሰው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።

እውነትን ስትሰማ የማረከህ ተስፋ አሁን ይበልጥ ጠንካራና አስተማማኝ ሆኗል (ከአንቀጽ 16-17⁠ን ተመልከት)

16. ተስፋ በአንድ ሰው ውስጥ እያደገ የሚሄደው እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

16 ተስፋ የሚያድግ ነገር እንደሆነ ከተገነዘብን ጳውሎስ የተናገረውን ሐሳብ መረዳት አይከብደንም። ለምሳሌ ያህል፣ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን አስደናቂ ተስፋ መጀመሪያ የሰማህበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? በወቅቱ፣ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር የሕልም እንጀራ እንደሆነ ተሰምቶህ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይሖዋንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰጣቸውን ተስፋዎች ይበልጥ እያወቅክ ስትሄድ ይህ ተስፋ እውን እንደሚሆን እምነት ማዳበር ቻልክ።

17. ራስህን ወስነህ ከተጠመቅክ በኋላ ተስፋህ እያደገ የሚሄደው እንዴት ነው?

17 ራስህን ወስነህ ከተጠመቅክ በኋላም ይበልጥ እየተማርክና በመንፈሳዊ እየጎለመስክ ስትሄድ ተስፋህ ማደጉን ቀጥሏል። (ዕብ. 5:13–6:1) በሮም 5:2-4 ላይ ያለውን ሐሳብ እውነተኝነት በገዛ ሕይወትህ ተመልክተህ መሆን አለበት። የተለያዩ መከራዎች ቢያጋጥሙህም እነሱን በጽናት በመቋቋምህ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተሃል። አምላክ ሞገሱን እንዳሳየህ ስለምታውቅ እሱ ቃል የገባቸውን ነገሮች እንደምታገኝ ከበፊቱ ይበልጥ እርግጠኛ ነህ። ተስፋህ ከመጀመሪያው ይበልጥ ተጠናክሯል። ይበልጥ እውን ሆኖልሃል። በግለሰብ ደረጃ ይነካሃል። በሁሉም የሕይወትህ ዘርፎች ማለትም ቤተሰብህን በምትይዝበት መንገድ፣ ውሳኔ በምታደርግበት መንገድ አልፎ ተርፎም ጊዜህን በምትጠቀምበት መንገድ ላይ ለውጥ ያመጣል።

18. ይሖዋ ምን ዋስትና ሰጥቶናል?

18 ጳውሎስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ካገኘን በኋላ ስለምንጎናጸፈው ተስፋ ሌላ ወሳኝ ሐሳብ ተናግሯል። ተስፋችን እንደሚፈጸም ማረጋገጫ ሰጥቶናል። ይህን እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? ጳውሎስ ለክርስቲያኖች የሚከተለውን ዋስትና በመንፈስ መሪነት ሰጥቷል፦ “ተስፋውም ሳይፈጸም ቀርቶ ለሐዘን አይዳርገንም፤ ምክንያቱም የአምላክ ፍቅር፣ በተሰጠን መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በልባችን ውስጥ ፈሷል።” (ሮም 5:5) በእርግጥም ተስፋህ እንደሚፈጸም ለመተማመን የሚያበቃ አጥጋቢ ምክንያት አለህ።

19. ከተስፋህ ጋር በተያያዘ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን ትችላለህ?

19 ይሖዋ ለአብርሃም ምን ቃል እንደገባለት እንዲሁም ሞገሱን ያሳየውና ወዳጁ አድርጎ የቆጠረው እንዴት እንደሆነ አሰላስል። የአብርሃም ተስፋ ከንቱ ሆኖ አልቀረም። መጽሐፍ ቅዱስ “አብርሃም በትዕግሥት ከጠበቀ በኋላ ይህን የተስፋ ቃል አገኘ” ይላል። (ዕብ. 6:15፤ 11:9, 18፤ ሮም 4:20-22) ተስፋው ሳይፈጸም ቀርቶ ለሐዘን አልዳረገውም። አንተም ታማኝነትህን ከጠበቅክ ተስፋህ እንደሚፈጸም መተማመን ትችላለህ። ተስፋህ አስተማማኝ ነው፤ ደስታ ያስገኝልሃል እንጂ ለሐዘን አይዳርግህም! (ሮም 12:12) ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በእሱ በመታመናችሁ የተነሳ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተስፋ እንዲትረፈረፍላችሁ ተስፋ የሚሰጠው አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ።”—ሮም 15:13

መዝሙር 139 በአዲሱ ዓለም ስትኖር ይታይህ

a ክርስቲያናዊ ተስፋችን ምን እንደሚያካትትና ተስፋችን እንደሚፈጸም እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምን እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን። ሮም ምዕራፍ 5 አሁን ያለን ተስፋ እውነትን በሰማንበት ወቅት ከነበረን ተስፋ የሚለየው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ይረዳናል።