ታስታውሳለህ?
በዚህ ዓመት የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በደንብ አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦
‘አእምሯችንን ማደስ’ ምን ይጠይቃል? (ሮም 12:2)
‘አእምሯችንን ማደስ’ ማለት ጥቂት መልካም ነገሮችን በመሥራት ሕይወታችንን ማስጌጥ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ውስጣዊ ማንነታችንን በጥልቀት መመርመር እንዲሁም የይሖዋን መሥፈርቶች በተቻለ መጠን በጥብቅ ለመከተል አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይጠይቃል።—w23.01 ገጽ 8-9
የዓለምን ክስተቶች ስንከታተል ሚዛናዊ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ላይ እየተከናወኑ ያሉት ነገሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን። ይሁንና ክፍፍል እንዲፈጠር ሊያደርጉ የሚችሉ ግምታዊ ሐሳቦችን ከመሰንዘር ይልቅ ከሌሎች ጋር የምናደርገው ውይይት የይሖዋ ድርጅት ባቀረበው መረጃ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 1:10)—w23.02 ገጽ 16
በኢየሱስ ጥምቀትና በተከታዮቹ ጥምቀት መካከል ምን ልዩነት አለ?
ኢየሱስ የተወለደው ራሱን ለይሖዋ በወሰነ ብሔር ውስጥ ስለሆነ እንደ እኛ ራሱን ለይሖዋ መወሰን አላስፈለገውም። ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበት ፍጹም ሰው ስለነበር ለኃጢአቱ ንስሐ መግባት አላስፈለገውም።—w23.03 ገጽ 5
በስብሰባዎች ላይ ሌሎች እንዲሳተፉ አጋጣሚ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
አጭር መልስ በመመለስ ብዙ ሰዎችን ለማሳተፍ የሚያስችል ጊዜ እንዲገኝ ማድረግ እንችላለን። በተጨማሪም ብዙ ነጥቦችን ከመጥቀስ መቆጠብ ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን ሌሎች ተጨማሪ ሐሳብ መስጠት ይችላሉ።—w23.04 ገጽ 23
በኢሳይያስ 35:8 ላይ የተጠቀሰው “የቅድስና ጎዳና” ምን ያመለክታል?
ይህ ምሳሌያዊ አውራ ጎዳና በመጀመሪያ የሚያመለክተው አይሁዳውያን ከባቢሎን ወደ ትውልድ አገራቸው ሲመለሱ የተጓዙበትን መንገድ ነበር። ባለፉት ጥቂት መቶ ዘመናትስ? ከ1919 በፊት በነበሩት መቶ ዘመናት አውራ ጎዳናውን የማዘጋጀቱ ሥራ ሲከናወን ቆይቷል፤ ይህም መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎምና ማተምን ይጨምራል። የአምላክ ሕዝቦች ‘በቅድስና ጎዳና’ ላይ ሲጓዙ ቆይተዋል፤ ይህ ጎዳና ወደ መንፈሳዊው ገነት እንዲገቡና መንግሥቱ ወደፊት የሚያመጣቸውን በረከቶች እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።—w23.05 ገጽ 15-19
ምሳሌ ምዕራፍ 9 በየትኞቹ ሁለት ምሳሌያዊ ሴቶች ላይ የተመሠረተ ምክር ይሰጠናል?
የምሳሌ መጽሐፍ ‘ማስተዋል ስለጎደላት ሴት’ ይናገራል፤ ይህች ሴት የምታቀርበው ግብዣ ወደ “መቃብር” ይመራል። በተጨማሪም በሴት ስለተመሰለችው “እውነተኛ ጥበብ” ይናገራል፤ እሷ የምታቀርበው ግብዣ ደግሞ ወደ “ማስተዋል መንገድ” እና ወደ ሕይወት ይመራል። (ምሳሌ 9:1, 6, 13, 18)—w23.06 ገጽ 22-24
አምላክ ሎጥን የያዘበት መንገድ ትሑትና ምክንያታዊ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?
ይሖዋ፣ ሎጥ ከሰዶም ወጥቶ ወደ ተራራማው አካባቢ እንዲሸሽ መመሪያ ሰጠው። ሎጥ ወደ ዞአር ለመሸሽ እንዲፈቀድለት ልመና ሲያቀርብ አምላክ ልመናውን ሰማው።—w23.07 አን 21
አንዲት ሚስት የትዳር አጋሯ ፖርኖግራፊ የሚመለከት ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለች?
ባለቤቷ ፖርኖግራፊ ማየቱ የእሷ ጥፋት እንዳልሆነ ልታስታውስ ይገባል። ከአምላክ ጋር ባላት ዝምድና ላይ ማተኮር እንዲሁም በጭንቀት በተዋጡበት ጊዜ ከይሖዋ ማጽናኛ ስላገኙ ሴቶች በሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ላይ ማሰላሰል ይኖርባታል። በተጨማሪም ባለቤቷ ፖርኖግራፊ የማየት ፍላጎቱ እንዲቀሰቀስበት ከሚያደርጉ ሁኔታዎች እንዲርቅ ልትረዳው ትችላለች።—w23.08 ገጽ 14-17
አንድ ሰው እምነታችንን በተመለከተ በጥያቄ ቢያፋጥጠን ጥልቅ ማስተዋል ገርነት እንድናሳይ የሚረዳን እንዴት ነው?
ጥያቄውን የግለሰቡን አመለካከት ወይም ፍላጎት ለማወቅ እንደሚያስችለን መንገድ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን በገርነት መልስ ለመስጠት ይረዳናል።—w23.09 ገጽ 17
ጥንካሬ ማግኘት የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ ከማርያም ምን እንማራለን?
ማርያም የመሲሑ እናት እንደምትሆን ስታውቅ ከሌሎች ጥንካሬ አግኝታለች። ገብርኤልና ኤልሳቤጥ ለማርያም ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻ ሰጥተዋታል። እኛም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጥንካሬ ማግኘት እንችላለን።—w23.10 ገጽ 15
ይሖዋ ጸሎታችንን የሚመልስልን እንዴት ሊሆን ይችላል?
ይሖዋ ዓላማውን ከግምት ባስገባ መልኩ ጸሎታችንን እንደሚሰማ ቃል ገብቶልናል። (ኤር. 29:12) ለተመሳሳይ ጥያቄዎች የተለያየ መልስ ሊሰጥ ይችላል፤ ሆኖም ምንጊዜም ይደግፈናል።—w23.11 ገጽ 21-22
ሮም 5:2 ስለ “ተስፋ” ይናገራል፤ ታዲያ ቁጥር 4 ላይ ተስፋ ድጋሚ የተጠቀሰው ለምንድን ነው?
አንድ ሰው ምሥራቹን ሲሰማ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖር ተስፋ ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም መከራ ሲያጋጥመው፣ ሲጸና እንዲሁም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ሲያገኝ ተስፋው ይበልጥ መጠናከሩ አይቀርም።—w23.12 ገጽ 12-13