አምላክ ለአልኮል መጠጥ ባለው አመለካከት ተመራ
ይሖዋ የሰጠንን የተለያዩ ስጦታዎች ከፍ አድርገህ እንደምትመለከት ጥያቄ የለውም፤ ስጦታዎቹን የምንጠቀምበትን መንገድ የመምረጥ ነፃነት ስለሰጠንም አመስጋኞች ነን። መጽሐፍ ቅዱስ የወይን ጠጅ የአምላክ ስጦታ እንደሆነ ይናገራል። እንዲያውም “ምግብ ለሳቅ ይዘጋጃል፤ የወይን ጠጅም ሕይወትን አስደሳች ያደርጋል” ይላል። (መክ. 10:19፤ መዝ. 104:15) ሆኖም አንዳንድ ሰዎች በአልኮል መጠጥ አጠቃቀም ረገድ ችግር እንዳለባቸው አስተውለህ ይሆናል። በተጨማሪም ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ በዓለም ዙሪያ የተለያዩ አመለካከቶችና መሥፈርቶች አሉ። ታዲያ ክርስቲያኖች በዚህ ረገድ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ምን ይረዳቸዋል?
የምንኖርበት አገር ወይም ያደግንበት ባሕል ምንም ይሁን ምን የአምላክ አመለካከት አስተሳሰባችንን እና ውሳኔያችንን እንዲመራው መፍቀዳችን ለአሁንም ሆነ ለወደፊት ጥቅም ያስገኝልናል።
ብዙ ሰዎች አዘውትረው እንደሚጠጡና ከመጠን በላይ እንደሚጠጡ አስተውለህ መሆን አለበት። አንዳንዶች አልኮል የሚጠጡት ዘና ስለሚያደርጋቸው ነው። ሌሎች የሚጠጡት ደግሞ ችግራቸውን ለመርሳት ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ብዙ መጠጣት እንደ ዘመናዊነት ወይም እንደ ወንድነት ይታያል።
ይሁንና ክርስቲያኖች አፍቃሪ ከሆነው ፈጣሪያቸው ጥበብ የሚንጸባረቅበት መመሪያ አግኝተዋል። ለምሳሌ ከልክ በላይ መጠጣት የሚያስከትለውን አስከፊ መዘዝ ገልጾልናል። ሰካራሞች ስለሚያጋጥማቸው መከራ በዝርዝር የሚገልጸውን በምሳሌ 23:29-35 ላይ የሚገኘውን ዘገባ አንብበህ ይሆናል። a አውሮፓ ውስጥ በጉባኤ ሽማግሌነት የሚያገለግለው ዳንኤል፣ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ስለነበረው ሕይወት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ከልክ በላይ በመጠጣቴ ብዙ መጥፎ ውሳኔዎችን አድርጌያለሁ፤ በዚህ የተነሳ የደረሱብኝ ችግሮች አሁንም ድረስ የስሜት ጠባሳ ትተውብኛል።”
ታዲያ ክርስቲያኖች የመምረጥ ነፃነታቸውን ተጠቅመው፣ ከልክ በላይ መጠጣት ከሚያስከትለው መዘዝ መራቅ የሚችሉት እንዴት ነው? ቁልፉ የአምላክ አመለካከት አስተሳሰባችንን እና ድርጊታችንን እንዲመራው መፍቀድ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አልኮል መጠጥ ምን እንደሚልና አንዳንዶች የሚጠጡት ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርት
የአምላክ ቃል አልኮልን በመጠኑ መጠጣትን አያወግዝም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የወይን ጠጅ መጠጣት አስደሳች ሊሆን እንደሚችል ይናገራል። “ምግብህን በደስታ ብላ፤ ልብህም ደስ ብሎት የወይን ጠጅህን ጠጣ” ይላል። (መክ. 9:7) ኢየሱስ አልፎ አልፎ የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር፤ ሌሎች ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችም እንዲሁ አድርገዋል።—ማቴ. 26:27-29፤ ሉቃስ 7:34፤ 1 ጢሞ. 5:23
ነገር ግን የአምላክ ቃል በመጠኑ በመጠጣትና በመስከር መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ያስቀምጣል። “በወይን ጠጅ አትስከሩ” በማለት በቀጥታ ይናገራል። (ኤፌ. 5:18) ‘ሰካራሞች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱም’ ይገልጻል። (1 ቆሮ. 6:10) አዎ፣ ይሖዋ ከልክ በላይ መጠጣትንና ስካርን አጥብቆ ያወግዛል። በባሕላችን ላይ ተመሥርተን ውሳኔ ከማድረግ ይልቅ የይሖዋን አመለካከት ማወቃችን ተገቢ ነው።
አንዳንዶች ሳይሰክሩ ብዙ መጠጣት እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። ይህ ግን በጣም አደገኛ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለብዙ ወይን ጠጅ የሚገዙ’ ሰዎች ለሥነ ምግባራዊና ለመንፈሳዊ ውድቀት እንደሚዳረጉ በግልጽ ይናገራል። (ቲቶ 2:3፤ ምሳሌ 20:1) እንዲያውም ኢየሱስ ‘ከልክ በላይ መጠጣት’ ሰዎች ወደ አምላክ አዲስ ዓለም እንዳይገቡ ሊያግዳቸው እንደሚችል አስጠንቅቋል። (ሉቃስ 21:34-36) ታዲያ አንድ ክርስቲያን በአልኮል መጠጥ የተነሳ በሚመጡ ወጥመዶች ውስጥ እንዳይገባ ምን ሊረዳው ይችላል?
የምትጠጣበትን ምክንያትና የመጠጥ ልማድህን ገምግም
አንድ ሰው ያደገበት ባሕል ስለ መጠጥ ያለውን አመለካከት እንዲቀርጸው መፍቀዱ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ክርስቲያኖች እንደ ምግብና መጠጥ ካሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ይሖዋን የሚያስደስተውን ነገር ማድረጋቸው ጥበብ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ።” (1 ቆሮ. 10:31) የሚከተሉትን ጥያቄዎችና የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ልብ በል።
መጠጥ የምጠጣው ከሌሎች ጋር ለመመሳሰል ነው? ዘፀአት 23:2 ‘ብዙኃኑን አትከተል’ ይላል። እዚህ ላይ ይሖዋ፣ እስራኤላውያን እሱን የማያስደስቱ ሰዎችን እንዳይከተሉ እያስጠነቀቃቸው ነበር። ይህ ማሳሰቢያ በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖችም ይሠራል። ሰዎች ስለ መጠጥ ባለን አመለካከትና ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ ከፈቀድን ከይሖዋና ከመሥፈርቶቹ እየራቅን ልንሄድ እንችላለን።—ሮም 12:2
የምጠጣው ጥንካሬዬን ለማሳየት ነው? በአንዳንድ ባሕሎች፣ አዘውትሮ መጠጣትና ከልክ በላይ መጠጣት የተለመደና ተቀባይነት ያለው ነገር ነው። (1 ጴጥ. 4:3) ሆኖም 1 ቆሮንቶስ 16:13 ምን እንደሚል ልብ በል፦ “ነቅታችሁ ኑሩ፤ በእምነት ጸንታችሁ ቁሙ፤ ወንድ ሁኑ፤ ብርቱዎች ሁኑ።” የአልኮል መጠጥ አንድ ሰው ብርቱ እንዲሆን ሊረዳው ይችላል? በፍጹም። የአልኮል መጠጥ ስሜታችንን በቀላሉ ሊያደነዝዘው እንዲሁም አስተሳሰባችንንና ድርጊታችንን ሊያዛባው ይችላል። ስለዚህ ብዙ መጠጣት የጥንካሬ ሳይሆን የድክመት ምልክት ነው። ኢሳይያስ 28:7 አንድ ሰው በመጠጥ የተነሳ መንገድ እንደሚስት እንዲሁም እንደሚንገዳገድና እንደሚሳሳት ይገልጻል።
እውነተኛ ብርታት የሚገኘው ከይሖዋ ነው፤ እንዲሁም ‘ነቅቶ መኖርና በእምነት ጸንቶ መቆም’ ይጠይቃል። (መዝ. 18:32) አንድ ክርስቲያን አደገኛ ሁኔታዎችን በንቃት በመከታተልና በመንፈሳዊ ሊጎዱት ከሚችሉ ነገሮች ራሱን ለመጠበቅ ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ ይህን ማድረግ ይችላል። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ እንዲህ ያለ ጥንካሬ አሳይቷል፤ ደግሞም ባሳየው ቆራጥነትና ድፍረት የብዙዎችን አክብሮት አትርፏል።
የምጠጣው ከችግሬ ለመሸሽ ነው? አንድ መዝሙራዊ “[ይሖዋ ሆይ] በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ” በማለት በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (መዝ. 94:19) ችግሮች ሲደራረቡብህ እፎይታ ለማግኘት ወደ መጠጥ ሳይሆን ወደ ይሖዋ ዞር በል። ይህን ማድረግ የምትችልበት አንዱ ወሳኝ መንገድ ወደ ይሖዋ አዘውትረህ መጸለይ ነው። በተጨማሪም ብዙዎች በጉባኤ ውስጥ ካለ የጎለመሰ ክርስቲያን ምክር መጠየቃቸው ጠቅሟቸዋል። አንድ ሰው ችግሩን ለመርሳት ሲል መጠጥ መጠጣቱ የሥነ ምግባር አቋሙን ሊያላላው እንዲሁም ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ሊያዳክመው ይችላል። (ሆሴዕ 4:11) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዳንኤል እንዲህ ሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል፦ “በጭንቀትና በበደለኝነት ስሜት እዋጥ ነበር። የምጠጣው ችግሬን ለመርሳት ቢሆንም ችግሮቹ ጭራሽ ተባባሱ። እንዲሁም ጓደኞቼንና ለራሴ ያለኝን አክብሮት አጣሁ።” ታዲያ ዳንኤልን የረዳው ምንድን ነው? “ከጎኔ ማድረግ ያለብኝ ይሖዋን እንጂ አልኮልን እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። በስተ መጨረሻ ችግሮቼን መቋቋምና ማሸነፍ ቻልኩ” ብሏል። ያለንበት ሁኔታ ተስፋ ያለው ባይመስልም እንኳ ይሖዋ ምንጊዜም ሊረዳን ዝግጁ ነው።—ፊልጵ. 4:6, 7፤ 1 ጴጥ. 5:7
አልፎ አልፎ የምትጠጣ ከሆነ የመጠጥ ልማድህን ከሚከተሉት ጥያቄዎች አንጻር ለመገምገም ሞክር፦ ‘አንድ የቤተሰቤ አባል ወይም የቅርብ ጓደኛዬ የመጠጥ አወሳሰዴ እንደሚያሳስበው ገልጾልኛል?’ ሁኔታው እንዲህ ከሆነ፣ አንተ ባታስተውለውም ሱስ እየያዘህ ሊሆን ይችላል። ‘ከቀድሞው ይበልጥ ብዙ እየጠጣሁ ነው?’ ይህ ሁኔታ የአልኮል ሱስ ባይኖርብህም እንኳ ወደዚያ እያመራህ እንደሆነ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ‘አልኮል ሳልጠጣ ከተወሰኑ ቀናት በላይ መቆየት ይከብደኛል?’ ከሆነ፣ የመጠጥ ሱስ ተጠናውቶህ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ችግሩን ለማሸነፍ የባለሙያዎች እርዳታ ሊያስፈልግህ ይችላል።
አልኮል መጠጣት ከሚያስከትላቸው አደጋዎች አንጻር አንዳንድ ክርስቲያኖች ጨርሶ ላለመጠጣት ወስነዋል። ሌሎች ደግሞ ጣዕሙን ስለማይወዱት መጠጣት አይፈልጉም። አንድ ጓደኛህ እንዲህ ያለ ምርጫ ካደረገ እሱን ከመተቸት ይልቅ ውሳኔውን በማክበር ደግነት ልታሳየው ትችላለህ።
ወይም ደግሞ ለራስህ አንዳንድ ገደቦች ማበጀቱን ጠቃሚ ሆኖ አግኝተኸው ሊሆን ይችላል። አንድ ክርስቲያን በሚጠጣው መጠን ላይ ገደብ ሊያበጅ ይችላል። ወይም ደግሞ መቼ መቼ ልጠጣ በሚለው ላይ ገደብ ሊያስቀምጥ ይችላል፤ ምናልባት በሳምንት አንዴ ወይም ከምግብ ጋር በልኩ ለመጠጣት ሊወስን ይችላል። ሌሎች ደግሞ በሚጠጡት የአልኮል መጠጥ ዓይነት ላይ ገደብ አበጅተዋል። ለምሳሌ የወይን ጠጅ ወይም ቢራ
በልኩ ቢጠጡም ከባድ መጠጦችን በርዘውም እንኳ ላለመጠጣት ሊወስኑ ይችላሉ። አንድ ሰው ግልጽ ገደበ ካስቀመጠ ያወጣውን ገደብ መከተል ቀላል ይሆንለታል። አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ውሳኔ በማድረጉና ውሳኔውን አጥብቆ በመከተሉ ሊያፍር አይገባም።ሊታሰብበት የሚገባው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የሌሎች አመለካከት ነው። ሮም 14:21 “ወንድምህ የሚሰናከልበት ከሆነ ሥጋ አለመብላት፣ የወይን ጠጅ አለመጠጣት ወይም ማንኛውንም የሚያሰናክል ነገር አለማድረግ የተሻለ ነው” ይላል። ይህን ምክር በሥራ ላይ ማዋል የምትችለው እንዴት ነው? ወንድማዊ ፍቅር አሳይ። አልኮል መጠጣትህ አንድን ሰው ቅር ሊያሰኘው እንደሚችል ከተሰማህ ለወንድምህ ያለህ ፍቅር መብትህ የሆነውን ነገር እንድትተው ሊያነሳሳህ አይገባም? እንዲህ በማድረግ ለሌሎች እንደምታስብና ስሜታቸውን እንደምታከብር እንዲሁም የራስህን ሳይሆን የእነሱን ጥቅም እንደምትፈልግ ታሳያለህ።—1 ቆሮ. 10:24
ከዚህም ሌላ አንድ ክርስቲያን ከመጠጥ ጋር በተያያዘ ውሳኔ ሲያደርግ የመንግሥትን ሕግ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል። ለምሳሌ መንግሥት አልኮል ለመጠጣት የዕድሜ ገደብ ሊደነግግ ወይም ጠጥቶ ማሽከርከርንና ሌሎች ማሽኖችን ማንቀሳቀስን ሊከለክል ይችላል።—ሮም 13:1-5
ይሖዋ ብዙ ግሩም ስጦታዎችን ሰጥቶናል፤ እነዚህን ስጦታዎች የምንጠቀምበትን መንገድ የመምረጥ መብት በመስጠትም አክብሮናል። ይህም የምንበላውንና የምንጠጣውን ነገር የመምረጥ ነፃነትን ይጨምራል። በዚህ ነፃነት ተጠቅመን የሰማዩን አባታችንን በማስደሰት የሰጠንን ስጦታ ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው እናሳይ።
a የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል እንደገለጸው ከልክ በላይ የአልኮል መጠጥ መጠጣት ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች መካከል የሰው ነፍስ ማጥፋት፣ ራስን መግደል፣ የፆታ ጥቃት፣ በትዳር አጋር ላይ የሚፈጸም ጥቃት፣ አደገኛ ፆታዊ ምግባር እንዲሁም የፅንስ መቋረጥ ይገኙበታል።