በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 52

ወጣት እህቶች—ጎልማሳ ክርስቲያኖች ሁኑ

ወጣት እህቶች—ጎልማሳ ክርስቲያኖች ሁኑ

“ሴቶችም እንደዚሁ . . . በልማዶቻቸው ልከኞችና በሁሉም ነገር ታማኞች ሊሆኑ ይገባል።”—1 ጢሞ. 3:11

መዝሙር 133 በወጣትነታችሁ ይሖዋን አምልኩ

ማስተዋወቂያ a

1. ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ ለመድረስ ምን ያስፈልገናል?

 አንድ ልጅ አድጎ ትልቅ ሰው የሚሆንበት ፍጥነት በጣም ያስገርመናል። ይህ እድገት በራሱ የሚከናወን ይመስል ይሆናል። ይሁንና እድገት አድርጎ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ መድረስ በራሱ የሚመጣ ነገር አይደለም። b (1 ቆሮ. 13:11፤ ዕብ. 6:1) እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ሊኖረን ይገባል። በተጨማሪም አምላካዊ ባሕርያትን ለማዳበር፣ ጠቃሚ ክህሎቶችን ለመማር እንዲሁም ወደፊት ለምንቀበላቸው ኃላፊነቶች ለመዘጋጀት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ያስፈልገናል።—ምሳሌ 1:5

2. ከዘፍጥረት 1:27 ምን እንማራለን? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

2 ይሖዋ ሰዎችን የፈጠራቸው ወንድ እና ሴት አድርጎ ነው። (ዘፍጥረት 1:27ን አንብብ።) ወንዶችና ሴቶች አካላዊ ልዩነት እንዳላቸው ግልጽ ነው፤ ይሁንና በሌሎች መንገዶችም ይለያያሉ። ለምሳሌ ይሖዋ ወንዶችንና ሴቶችን የፈጠራቸው የየራሳቸው ሚና ሰጥቶ ነው። በመሆኑም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችሉ ባሕርያትና ክህሎቶች ያስፈልጓቸዋል። (ዘፍ. 2:18) በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ አንዲት ወጣት እህት የጎለመሰች ክርስቲያን ለመሆን ምን ማድረግ እንደሚያስፈልጋት እንመለከታለን። በቀጣዩ ርዕስ ላይ ደግሞ ወጣት ወንድሞች ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንመለከታለን።

አምላካዊ ባሕርያትን አዳብሩ

እንደ ርብቃ፣ አስቴርና አቢጋኤል ያሉ ታማኝ ሴቶች ያንጸባረቋቸውን ባሕርያት መኮረጃችሁ የጎለመሳችሁ ክርስቲያኖች እንድትሆኑ ይረዳችኋል (ከአንቀጽ 3-4⁠ን ተመልከት)

3-4. ወጣት እህቶች አርዓያ ሊሆኗቸው የሚችሉ ሴቶችን ከየት ማግኘት ይችላሉ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

3 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን ይወዱና ያገለግሉ የነበሩ በርካታ ሴቶችን ታሪክ ይዟል። (“በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ ሴቶች ምን እንማራለን?” የሚለውን ርዕስ ከ​jw.org ላይ ተመልከት።) እነዚህ ሴቶች የጭብጡ ጥቅሳችን እንደሚገልጸው “በልማዶቻቸው ልከኞችና በሁሉም ነገር ታማኞች” ነበሩ። በተጨማሪም እህቶች አርዓያ ሊሆኗቸው የሚችሉ ጎልማሳ ክርስቲያን ሴቶችን በጉባኤያቸው ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።

4 ወጣት እህቶች፣ ልትኮርጇቸው የምትችሏቸውን አንዳንድ የጎለመሱ እህቶች ለማሰብ ለምን አትሞክሩም? ያሏቸውን ማራኪ ባሕርያት አስተውሉ። ከዚያም እነዚህን ባሕርያት ማሳየት የምትችሉት እንዴት እንደሆነ አስቡ። በቀጣዮቹ አንቀጾች ላይ፣ የጎለመሱ እህቶች ሊያዳብሯቸው የሚገቡ ሦስት አስፈላጊ ባሕርያትን እንመለከታለን።

5. አንዲት የጎለመሰች እህት ትሕትና የሚያስፈልጋት ለምንድን ነው?

5 ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ ለመድረስ ከሚያስፈልጉት ወሳኝ ባሕርያት አንዱ ትሕትና ነው። አንዲት ሴት ትሑት ከሆነች ከይሖዋም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ጥሩ ዝምድና ይኖራታል። (ያዕ. 4:6) ለምሳሌ ይሖዋን የምትወድ ሴት የሰማዩ አባቷ ያቋቋመውን የራስነት ሥርዓት በትሕትና ትደግፋለች። (1 ቆሮ. 11:3) የራስነት ሥርዓት በጉባኤም ሆነ በቤተሰብ ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ይሠራል። c

6. ወጣት እህቶች በትሕትና ረገድ ከርብቃ ምን ይማራሉ?

6 የርብቃን ምሳሌ እንመልከት። ርብቃ አስተዋይና ቆራጥ ሴት የነበረች ሲሆን በሕይወቷ ውስጥ በራሷ ተነሳሽነት ወሳኝ እርምጃዎችን የወሰደችባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ዘፍ. 24:58፤ 27:5-17) ያም ቢሆን ሰው አክባሪና ታዛዥ ነበረች። (ዘፍ. 24:17, 18, 65) እናንተም እንደ ርብቃ የይሖዋን ዝግጅቶች በትሕትና የምትደግፉ ከሆነ ለቤተሰባችሁም ሆነ ለጉባኤያችሁ ጥሩ ምሳሌ ትሆናላችሁ።

7. ወጣት እህቶች ልክን በማወቅ ረገድ የአስቴርን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

7 ሁሉም የጎለመሱ ክርስቲያኖች ሊያዳብሩት የሚገባው ሌላው ባሕርይ ልክን ማወቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” ይላል። (ምሳሌ 11:2) አስቴር ልኳን የምታውቅና ፈሪሃ አምላክ ያላት ሴት ነበረች። ልኳን የምታውቅ መሆኗ የትዕቢት እርምጃ ከመውሰድ ጠብቋታል። በዕድሜ ከእሷ የሚበልጠው ዘመዷ መርዶክዮስ የሰጣትን ምክር አዳምጣለች፤ እንዲሁም በሥራ ላይ አውላዋለች። (አስ. 2:10, 20, 22) እናንተም ምክር በመጠየቅና የተሰጣችሁን ጥሩ ምክር በሥራ ላይ በማዋል ልካችሁን እንደምታውቁ ማሳየት ትችላላችሁ።—ቲቶ 2:3-5

8. በ1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10 መሠረት አንዲት እህት ልኳን ማወቋ በአለባበስና በአጋጌጥ ረገድ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምርጫ እንድታደርግ የሚረዳት እንዴት ነው?

8 አስቴር ልኳን እንደምታውቅ በሌላም መንገድ አሳይታለች። አስቴር “ቁመናዋ ያማረ፣ መልኳም ቆንጆ ነበር”፤ ሆኖም ወደ ራሷ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት ለመሳብ አልሞከረችም። (አስ. 2:7, 15) ክርስቲያን ሴቶች የአስቴርን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? አንዱ መንገድ በ1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10 ላይ ተጠቅሷል። (ጥቅሱን አንብብ።) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያን ሴቶች በልከኝነትና በማስተዋል እንዲለብሱ መክሯቸዋል። እዚህ ላይ የተሠራባቸው የግሪክኛ ቃላት አንዲት ክርስቲያን የሚያስከብር እንዲሁም ለሌሎች ስሜት እንደምትጠነቀቅ የሚያሳይ አለባበስ ሊኖራት እንደሚገባ ይጠቁማሉ። የጎለመሱ እህቶቻችን ልከኛ የሆነ ልብስ ስለሚለብሱ በጣም እናደንቃቸዋለን!

9. ከአቢጋኤል ምሳሌ ምን እንማራለን?

9 ሁሉም የጎለመሱ እህቶች ሊያዳብሩት የሚገባው ሌላው ባሕርይ ማስተዋል ነው። ማስተዋል ምንድን ነው? የማመዛዘን ችሎታ ማለትም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር የመለየት ከዚያም ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ የማድረግ ችሎታ ነው። የአቢጋኤልን ምሳሌ እንመልከት። ባለቤቷ በመላው ቤተሰቡ ላይ አስከፊ መዘዝ የሚያስከትል መጥፎ ውሳኔ አድርጎ ነበር። በዚህ ጊዜ አቢጋኤል አፋጣኝ እርምጃ ወሰደች። የወሰደችው ማስተዋል የሚንጸባረቅበት እርምጃ የብዙ ሰዎችን ሕይወት አድኗል። (1 ሳሙ. 25:14-23, 32-35) ከዚህም ሌላ ማስተዋል መቼ መናገር፣ መቼ ደግሞ ዝም ማለት እንዳለብን ለማወቅ ይረዳናል። በተጨማሪም ለሌሎች አሳቢነት በምናሳይበት ወቅት በግል ሕይወታቸው ውስጥ ጣልቃ እንዳንገባ ይረዳናል።—1 ተሰ. 4:11

ጠቃሚ ክህሎቶችን አዳብሩ

ጥሩ የማንበብና የመጻፍ ችሎታ ማዳበራችሁ የጠቀማችሁ እንዴት ነው? (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

10-11. ጥሩ የማንበብና የመጻፍ ችሎታ ማዳበራችሁ እናንተንም ሆነ ሌሎችን የሚጠቅመው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

10 ክርስቲያን ሴቶች ጠቃሚ ክህሎቶችን ማዳበር ያስፈልጋቸዋል። አንዲት ሴት በልጅነቷ የምትማራቸው አንዳንድ ክህሎቶች በመላ ሕይወቷ ሊጠቅሟት ይችላሉ። አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

11 ጥሩ የማንበብና የመጻፍ ችሎታ አዳብሩ። በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ ማንበብና መጻፍ ለሴቶች አስፈላጊ እንደሆኑ ክህሎቶች ተደርገው አይታዩም። d ይሁንና ሁሉም ክርስቲያኖች እነዚህን ክህሎቶች ማዳበር ይኖርባቸዋል። (1 ጢሞ. 4:13) ስለዚህ ማንኛውም እንቅፋት ጥሩ አድርጋችሁ የማንበብና የመጻፍ ችሎታ ከማዳበር እንዲያግዳችሁ አትፍቀዱ። እንዲህ ማድረጋችሁ የሚጠቅማችሁ እንዴት ነው? እነዚህ ክህሎቶች ሥራ ለማግኘትና ራሳችሁን ለማስተዳደር ሊረዷችሁ ይችላሉ። ከዚህም ሌላ የአምላክን ቃል በመማርና በማስተማር ረገድ ይበልጥ ውጤታማ ትሆናላችሁ። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ የአምላክን ቃል ማንበባችሁና ማሰላሰላችሁ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርቡ ይረዳችኋል።—ኢያሱ 1:8፤ 1 ጢሞ. 4:15

12. ምሳሌ 31:26 የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ ለማዳበር የሚረዳን እንዴት ነው?

12 የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ አዳብሩ። ክርስቲያኖች ከሌሎች ጋር ውጤታማ በሆነ መንገድ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ በዚህ ረገድ ጥሩ ምክር ሰጥቶናል፤ ‘ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነና ለመናገር የዘገየ መሆን አለበት’ ብሏል። (ያዕ. 1:19) ሌሎች ሲናገሩ በጥሞና የምታዳምጡ ከሆነ ‘ስሜታቸውን እንደምትረዱላቸው’ ታሳያላችሁ። (1 ጴጥ. 3:8) ግለሰቡ የተናገረው ሐሳብ ወይም የተሰማው ስሜት በደንብ ካልገባችሁ ተገቢ ጥያቄዎችን ጠይቁ። ከዚያም ከመናገራችሁ በፊት ቆም ብላችሁ አስቡ። (ምሳሌ 15:28 ግርጌ) እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘ልናገር ያሰብኩት ነገር እውነተኛና የሚያንጽ ነው? አክብሮትና ደግነት የሚንጸባረቅበት ነው?’ የሐሳብ ልውውጥ በማድረግ ረገድ ጥሩ ችሎታ ካላቸው የጎለመሱ እህቶች ተማሩ። (ምሳሌ 31:26ን አንብብ።) የሚናገሩበትን መንገድ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። ይህን ክህሎት ባዳበራችሁ መጠን ከሌሎች ጋር ያላችሁ ዝምድና ይሻሻላል።

የቤት ውስጥ ሙያዎችን የተማረች ሴት ቤተሰቧንም ሆነ ጉባኤዋን በእጅጉ ትጠቅማለች (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13. የቤት ውስጥ ሙያዎችን መማር የምትችሉት እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

13 የቤት ውስጥ ሙያዎችን ተማሩ። በብዙዎቹ አካባቢዎች አብዛኛውን የቤት ውስጥ ሥራ የሚያከናውኑት ሴቶች ናቸው። እናታችሁ ወይም ሌላ ባለሙያ እህት አስፈላጊዎቹን ሙያዎች እንድታዳብሩ ልትረዳችሁ ትችላለች። ሲንዲ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ ከሰጠችኝ ውድ ስጦታዎች አንዱ ተግቶ መሥራት የሚያስገኘውን ደስታ ያስተማረችኝ መሆኑ ነው። እንደ ምግብ ማብሰል፣ ቤት ማጽዳት፣ ልብስ መስፋት እና ገንዘብ አብቃቅቶ ዕቃ መሸመት ያሉትን ክህሎቶች ያስተማረችኝ መሆኑ ሕይወቴን አቅልሎልኛል፤ እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት ተጨማሪ ነገር ማከናወን እንድችል መንገድ ከፍቶልኛል። እናቴ እንግዳ ተቀባይ መሆን የምችለው እንዴት እንደሆነም አስተምራኛለች። ይህም አርዓያ ሊሆኑኝ የሚችሉ በርካታ ግሩም ወንድሞችና እህቶችን እንድተዋወቅ አስችሎኛል።” (ምሳሌ 31:15, 21, 22) የቤት ውስጥ ሙያዎችን የተማረች ታታሪና እንግዳ ተቀባይ ሴት ለቤተሰቧም ሆነ ለጉባኤዋ በረከት ነች።—ምሳሌ 31:13, 17, 27፤ ሥራ 16:15

14. ከክሪስታል ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝታችኋል? ትኩረታችሁ ሊያርፍ የሚገባውስ በምን ላይ ነው?

14 ራሳችሁን ለመቻል የሚረዷችሁን ክህሎቶች ተማሩ። ሁሉም የጎለመሱ ክርስቲያኖች ራሳቸውን የመቻል ግብ ማውጣታቸው አስፈላጊ ነው። (ፊልጵ. 4:11) ክሪስታል የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ጠቃሚ ክህሎቶችን ማዳበር እንድችል በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የምወስዳቸውን ኮርሶች እንድመርጥ ረድተውኛል። አባቴ የሒሳብ አያያዝ ኮርስ እንድወስድ አበረታታኝ፤ ይህም በጣም ጠቅሞኛል።” ሥራ ለማግኘት የሚረዷችሁን ክህሎቶች ከመማር በተጨማሪ በጀት ማውጣትና በበጀታችሁ መሠረት መኖር የምትችሉበትን መንገድ ለመማር ጥረት አድርጉ። (ምሳሌ 31:16, 18) አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ ላለመግባት በመጠንቀቅ እንዲሁም እንደ አቅማችሁ በመኖር ትኩረታችሁ በመንፈሳዊ ግቦች ላይ እንዲያርፍ አድርጉ።—1 ጢሞ. 6:8

ወደፊት ለምትቀበሏቸው ኃላፊነቶች ተዘጋጁ

15-16. ያላገቡ እህቶች ሌሎችን የሚጠቅሙት እንዴት ነው? (ማርቆስ 10:29, 30)

15 መንፈሳዊ ባሕርያትን ስታዳብሩና ጠቃሚ ክህሎቶችን ስትማሩ ወደፊት ለምትቀበሏቸው ኃላፊነቶች ዝግጁ ትሆናላችሁ። የትኞቹን ነገሮች ማድረግ እንደምትችሉ እስቲ እንመልከት።

16 ለተወሰነ ጊዜ ያህል ሳታገቡ ልትኖሩ ትችላላችሁ። አንዳንድ ሴቶች፣ ሳያገቡ መኖር በባሕላቸው ውስጥ እንግዳ ነገር ቢሆንም እንኳ ኢየሱስ እንዳለው ሳያገቡ ለመኖር ሊመርጡ ይችላሉ። (ማቴ. 19:10-12) ሌሎች ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ሳያገቡ ሊኖሩ ይችላሉ። ይሖዋና ኢየሱስ ያላገቡ ክርስቲያኖችን ዝቅ አድርገው እንደማይመለከቷቸው እርግጠኛ ሁኑ። በዓለም ዙሪያ ያሉ ያላገቡ እህቶች በጉባኤያቸው ውስጥ ጠቃሚ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። እነዚህ ክርስቲያን ሴቶች ለሌሎች ያላቸው ፍቅርና አሳቢነት ለብዙዎች መንፈሳዊ እህቶችና እናቶች እንዲሆኑ ያነሳሳቸዋል።—ማርቆስ 10:29, 30ን አንብብ፤ 1 ጢሞ. 5:2  

17. አንዲት ወጣት እህት ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት ከአሁኑ መዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው?

17 የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ልትሆኑ ትችላላችሁ። ክርስቲያን ሴቶች በዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ ይህ ነው የማይባል አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። (መዝ. 68:11) ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት ከአሁኑ ዕቅድ ማውጣት ትችሉ ይሆን? አቅኚ፣ የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኛ ወይም ቤቴላዊ ሆናችሁ ልታገለግሉ ትችሉ ይሆናል። ግባችሁን በተመለከተ ጸልዩ። እንዲህ ያለ ግብ ላይ መድረስ የቻሉ ክርስቲያኖችን አነጋግሩ፤ እንዲሁም ብቃቱን ለማሟላት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልጋችሁ ለማወቅ ሞክሩ። ከዚያም ምክንያታዊ የሆነ ዕቅድ አውጡ። ግባችሁ ላይ መድረሳችሁ በይሖዋ አገልግሎት በርካታ ግሩም አጋጣሚዎችን ይከፍትላችኋል።

ትዳር ለመመሥረት እያሰባችሁ ከሆነ የትዳር አጋራችሁን በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርባችኋል (አንቀጽ 18⁠ን ተመልከት)

18. አንዲት እህት የትዳር አጋሯን በጥንቃቄ መምረጥ ያለባት ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

18 ትዳር ለመመሥረት ትወስኑ ይሆናል። እስካሁን የተመለከትናቸው ባሕርያትና ክህሎቶች ጥሩ ሚስት እንድትሆኑ ይረዷችኋል። እርግጥ ነው፣ ለማግባት የምታስቡ ከሆነ የትዳር አጋራችሁን በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርባችኋል። በሕይወታችሁ ከምታደርጓቸው በጣም አስፈላጊ ውሳኔዎች አንዱ ይህ ነው። ለምታገቡት ሰው የራስነት ሥልጣን መገዛት እንደሚኖርባችሁ አስታውሱ። (ሮም 7:2፤ ኤፌ. 5:23, 33) ስለዚህ እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘የጎለመሰ ክርስቲያን ነው? በሕይወቱ ውስጥ መንፈሳዊ ነገሮችን ያስቀድማል? ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ያደርጋል? ስህተቱን አምኖ ይቀበላል? ለሴቶች አክብሮት አለው? እኔን በመንፈሳዊ፣ በቁሳዊና በስሜታዊ ለመንከባከብ የሚያስፈልጉት ክህሎቶች አሉት? የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ይወጣል? ለምሳሌ በጉባኤ ውስጥ የትኞቹ ኃላፊነቶች አሉት? እነዚህን ኃላፊነቶቹን የሚወጣውስ እንዴት ነው?’ (ሉቃስ 16:10፤ 1 ጢሞ. 5:8) እርግጥ ነው፣ ጥሩ ባል ማግኘት ከፈለጋችሁ ከጥሩ ሚስት የሚጠበቁትን ብቃቶች ማሟላት ይኖርባችኋል።

19. “ረዳት” የሚለው አገላለጽ ክብር የተላበሰ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

19 መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንዲት ጥሩ ሚስት ለባሏ “ረዳት” እና “ማሟያ” እንደሆነች ይናገራል። (ዘፍ. 2:18) ይህ አገላለጽ ሚስቶችን የሚያቃልል ነው? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ ክብር የተላበሰ ኃላፊነት ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ይሖዋን ‘ረዳት’ ብሎ ይጠራዋል። (መዝ. 54:4፤ ዕብ. 13:6) አንዲት ሚስት ለባሏ እውነተኛ ረዳት የምትሆነው እሱን የምትደግፈው እንዲሁም ቤተሰቡን የሚመለከቱ ውሳኔዎች ሲያደርግ ውሳኔዎቹ ለስኬት እንዲበቁ ለማድረግ የምትጥር ከሆነ ነው። ከዚህም ሌላ ይሖዋን ስለምትወደው ባለቤቷ በሌሎች ዘንድ አክብሮት እንዲያተርፍ ለመርዳት ጥረት ታደርጋለች። (ምሳሌ 31:11, 12፤ 1 ጢሞ. 3:11) ለዚህ ኃላፊነት መዘጋጀት የምትችሉት ለይሖዋ ያላችሁን ፍቅር በማጠናከር እንዲሁም በቤታችሁም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ሌሎችን ለመርዳት ጥረት በማድረግ ነው።

20. አንዲት እናት በቤተሰቧ ውስጥ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ልታሳድር ትችላለች?

20 እናት ልትሆኑ ትችላላችሁ። ትዳር ከመሠረታችሁ በኋላ ልጆች ትወልዱ ይሆናል። (መዝ. 127:3) በመሆኑም ለዚህ ኃላፊነት አስቀድሞ መዘጋጀት ጠቃሚ ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ የተመለከትናቸው ባሕርያትና ክህሎቶች ሚስትና እናት ስትሆኑ ይረዷችኋል። ፍቅር፣ ደግነትና ትዕግሥት ማሳየታችሁ ደስተኛ ቤተሰብ እንዲኖራችሁ እንዲሁም ልጆቻችሁ የወላጆቻቸውን ፍቅር አግኝተው ያለምንም ስጋት እንዲያድጉ ያስችላል።—ምሳሌ 24:3

ከቅዱሳን መጻሕፍት የተማሩና የተማሩትን ነገር በሥራ ላይ ያዋሉ በርካታ ወጣት ሴቶች የጎለመሱ ክርስቲያኖች መሆን ችለዋል (አንቀጽ 21⁠ን ተመልከት)

21. ስለ እህቶቻችን ምን ይሰማናል? ለምንስ? (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)

21 ውድ እህቶች፣ ይሖዋን ለማገልገልና ሕዝቦቹን ለመርዳት አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ ስለምታደርጉ በጣም እንወዳችኋለን። (ዕብ. 6:10) መንፈሳዊ ባሕርያትን ለማዳበር፣ ራሳችሁንም ሆነ ሌሎችን የሚጠቅሙ ክህሎቶችን ለመማር እንዲሁም ወደፊት ለምትቀበሏቸው ኃላፊነቶች ለመዘጋጀት ከፍተኛ ጥረት ታደርጋላችሁ። በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ትልቅ ቦታ አላችሁ!

መዝሙር 137 ታማኝ ሴቶች፣ ክርስቲያን እህቶች

a ውድ ወጣት እህቶች፣ በጉባኤው ውስጥ ትልቅ ቦታ አላችሁ። አምላካዊ ባሕርያትን በማዳበር፣ ጠቃሚ ክህሎቶችን በመማር እንዲሁም ወደፊት ለምትቀበሏቸው ኃላፊነቶች በመዘጋጀት ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ መድረስ ትችላላችሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ በይሖዋ አገልግሎት ብዙ በረከቶችን ታገኛላችሁ።

b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ የደረሰ ሰው በዓለማዊ ጥበብ ሳይሆን በአምላክ መንፈስ ይመራል። የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላል፤ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ጥረት ያደርጋል፤ እንዲሁም ለሌሎች ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳያል።

d የንባብን አስፈላጊነት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ንባብ ለልጆች አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?—ክፍል 1፦ ማንበብ ወይስ ማየት?” የሚለውን ርዕስ ከ​jw.org ላይ ተመልከት።