የጥናት ርዕስ 53
ወጣት ወንድሞች—ጎልማሳ ክርስቲያኖች ሁኑ
“በርታ፤ ወንድ ሁን።”—1 ነገ. 2:2
መዝሙር 135 የይሖዋ ፍቅራዊ ግብዣ፦ ‘ልጄ ሆይ፣ ጥበበኛ ሁን’
ማስተዋወቂያ a
1. ክርስቲያን ወንዶች እንዲሳካላቸው ከፈለጉ ምን ማድረግ አለባቸው?
ንጉሥ ዳዊት ሰለሞንን “በርታ፤ ወንድ ሁን” በማለት መክሮታል። (1 ነገ. 2:1-3) በዛሬው ጊዜ ያሉ ሁሉም ክርስቲያን ወንዶች ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ እንዲሳካላቸው ከፈለጉ በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፎች የአምላክን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል የሚችሉት እንዴት እንደሆነ መማር ይኖርባቸዋል። (ሉቃስ 2:52) ወጣት ወንድሞች እድገት አድርገው የጎለመሱ ክርስቲያኖች መሆናቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2-3. ወጣት ወንድሞች ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ መድረሳቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ክርስቲያን ወንዶች በቤተሰባቸውም ሆነ በጉባኤያቸው ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ወጣት ወንድሞች፣ ወደፊት ስለምትቀበሏቸው ኃላፊነቶች አስባችሁ እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ የመግባት፣ የጉባኤ አገልጋይ የመሆን፣ በኋላም በጉባኤ ሽማግሌነት የማገልገል ግብ ይኖራችሁ ይሆናል። ትዳር መመሥረትና ልጆች መውለድ ትፈልጉም ይሆናል። (ኤፌ. 6:4፤ 1 ጢሞ. 3:1) እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስና ስኬታማ ለመሆን ክርስቲያናዊ ጉልምስና ያስፈልጋችኋል። b
3 ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ ለመድረስ ምን ሊረዳችሁ ይችላል? ልታዳብሯቸው የሚገቡ አስፈላጊ ክህሎቶች አሉ። ታዲያ ወደፊት ለምትቀበሏቸው ኃላፊነቶች ለመዘጋጀትና እነዚህን ኃላፊነቶች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ከአሁኑ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ ለመድረስ የሚረዱ እርምጃዎች
4. ልትኮርጇቸው የምትችሏቸውን ጥሩ ምሳሌዎች ከየት ማግኘት ትችላላችሁ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
4 ጥሩ ምሳሌ የሚሆኗችሁን ሰዎች ምረጡ። መጽሐፍ ቅዱስ ወጣት ወንዶች ሊኮርጇቸው የሚችሏቸውን በርካታ ግሩም ምሳሌዎች ይዟል። በጥንት ዘመን የኖሩት እነዚህ ወንዶች አምላክን ይወዱ ነበር፤ በተጨማሪም የአምላክን ሕዝቦች ለመንከባከብ የተለያዩ ኃላፊነቶችን ተወጥተዋል። በቤተሰባችሁ ወይም በጉባኤያችሁ ውስጥ ካሉ ክርስቲያን ወንዶች መካከልም ግሩም ምሳሌዎችን ማግኘት ትችላላችሁ። (ዕብ. 13:7) ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወው ፍጹም ምሳሌ አለላችሁ። (1 ጴጥ. 2:21) እነዚህ ሰዎች የተዉትን ምሳሌ በጥንቃቄ ስታጠኑ ያንጸባረቋቸውን ግሩም ባሕርያት ለማስተዋል ሞክሩ። (ዕብ. 12:1, 2) ከዚያም እነሱን መኮረጅ የምትችሉባቸውን መንገዶች አስቡ።
5. የማመዛዘን ችሎታ ማዳበር የምትችሉት እንዴት ነው? ይህን ማድረጋችሁ አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው? (መዝሙር 119:9)
5 “የማመዛዘን ችሎታን” አዳብሩ እንዲሁም ጠብቁ። (ምሳሌ 3:21) የማመዛዘን ችሎታ ያለው ሰው እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ያሉትን አማራጮች በጥንቃቄ ያጤናል። ስለዚህ ይህን ችሎታ ለማዳበርና ይዛችሁ ለመቀጠል ከፍተኛ ጥረት አድርጉ። ለምን? የምንኖርበት ዓለም በራሳቸው ሐሳብ ወይም በስሜት ተነድተው እርምጃ በሚወስዱ ወጣቶች የተሞላ ነው። (ምሳሌ 7:7፤ 29:11) በተጨማሪም የሚዲያው ዓለም ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድርባችሁ ይችላል። ታዲያ የማመዛዘን ችሎታን ማዳበር የምትችሉት እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በመማር እንዲሁም ያላቸውን ጥቅም በማሰብ ጀምሩ። ከዚያም እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተጠቅማችሁ ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን አድርጉ። (መዝሙር 119:9ን አንብብ።) ይህን አስፈላጊ ክህሎት ካዳበራችሁ ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና የሚያደርሰውን ወሳኝ እርምጃ ወስዳችኋል ሊባል ይችላል። (ምሳሌ 2:11, 12፤ ዕብ. 5:14) የማመዛዘን ችሎታ ማዳበራችሁ በሁለት ሁኔታዎች ውስጥ የሚጠቅማችሁ እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት፦ (1) ከእህቶች ጋር ባላችሁ ግንኙነት እንዲሁም (2) ከአለባበስና ከፀጉር አያያዝ ጋር በተያያዘ ውሳኔ ስታደርጉ።
6. አንድ ወጣት ወንድም የማመዛዘን ችሎታ ማዳበሩ እህቶችን በአክብሮት እንዲይዝ የሚረዳው እንዴት ነው?
6 የማመዛዘን ችሎታ ሴቶችን በአክብሮት እንድትይዙ ይረዳችኋል። አንድ ወጣት ወንድም ከአንዲት እህት ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር ማሰቡ ምንም ስህተት የለውም። ይሁንና የማመዛዘን ችሎታ ያለው ወጣት ወንድም አንዲትን እህት ለትዳር ካላሰባት በስተቀር ለእሷ የፍቅር ስሜት እንዳለው የሚጠቁም ነገር ሊናገር፣ ሊጽፍ ወይም ሊያደርግ አይገባም። (1 ጢሞ. 5:1, 2) ከአንዲት እህት ጋር እየተጠናና ከሆነ ደግሞ ማንም ሰው በሌለበት ቦታ ከእሷ ጋር ብቻውን ላለመሆን በመጠንቀቅ መልካም ስሟን ላለማጉደፍ ጥረት ያደርጋል።—1 ቆሮ. 6:18
7. አንድ ወጣት ወንድም በአለባበስና በፀጉር አያያዝ ረገድ ምርጫ ሲያደርግ የማመዛዘን ችሎታ የሚረዳው እንዴት ነው?
7 አንድ ወጣት ወንድም ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንዳለው የሚያሳይበት ሌላው መንገድ በአለባበስና በፀጉር አያያዝ ረገድ ጥሩ ምርጫ በማድረግ ነው። ብዙውን ጊዜ፣ የፋሽኑን ዓለም የሚያራምዱት ለይሖዋ አክብሮት የሌላቸው እንዲሁም ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር የሚከተሉ ሰዎች ናቸው። የሚመርጧቸው ሰውነት ላይ የሚጣበቁ ወይም ወንዶችን ሴት የሚያስመስሉ ልብሶች ሥነ ምግባር የጎደለውን አስተሳሰባቸውን ያንጸባርቃሉ። ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና መድረስ የሚፈልግ ወጣት ወንድም ልብስ ሲመርጥ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ያሉ መልካም ምሳሌዎችን ከግምት ያስገባል። ራሱን እንዲህ እያለ ይጠይቃል፦ ‘የማደርገው ምርጫ ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለኝና ለሌሎች ስሜት እንደምጠነቀቅ ያሳያል? አለባበሴ የአምላክ አገልጋይ መሆኔን ሌሎች በግልጽ እንዲያዩ ያስችላል?’ (1 ቆሮ. 10:31-33፤ ቲቶ 2:6) የማመዛዘን ችሎታ ያለው ወጣት በወንድሞቹና በእህቶቹ ብቻ ሳይሆን በሰማዩ አባቱ ዘንድም አክብሮት ያተርፋል።
8. አንድ ወጣት ወንድም እምነት የሚጣልበት ሰው መሆን የሚችለው እንዴት ነው?
8 እምነት የሚጣልባችሁ ሁኑ። እምነት የሚጣልበት ወጣት ወንድም የተሰጡትን ኃላፊነቶች በሙሉ በትጋት ይወጣል። (ሉቃስ 16:10) ኢየሱስ የተወውን ፍጹም ምሳሌ ልብ በሉ። ኢየሱስ ግድ የለሽ ወይም ቸልተኛ ሆኖ አያውቅም። ከዚህ ይልቅ በአስቸጋሪ ጊዜያትም ጭምር ይሖዋ የሰጠውን ኃላፊነቶች በሙሉ ተወጥቷል። ለሰዎች በተለይም ለደቀ መዛሙርቱ ፍቅር ስለነበረው ለእነሱ ሲል ሕይወቱን በፈቃደኝነት አሳልፎ ሰጥቷል። (ዮሐ. 13:1) እናንተም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል የተሰጣችሁን ማንኛውንም ኃላፊነት በትጋት ተወጡ። ሥራውን እንዴት ማከናወን እንዳለባችሁ ግራ ከገባችሁ የጎለመሱ ወንድሞችን እርዳታ በትሕትና ጠይቁ። የግድ የሚጠበቅባችሁን ነገር ብቻ በማድረግ አትወሰኑ። (ሮም 12:11) ከዚህ ይልቅ “ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ እንደምታደርጉት በማሰብ” ኃላፊነታችሁን በአግባቡ ተወጡ። (ቆላ. 3:23) እርግጥ ፍጹም እንዳልሆናችሁ የታወቀ ነው፤ ስለዚህ ስህተት ስትሠሩ በትሕትና ስህተታችሁን አምናችሁ ተቀበሉ።—ምሳሌ 11:2
ጠቃሚ ክህሎቶችን አዳብሩ
9. ወጣት ወንድሞች ጠቃሚ ክህሎቶችን ማዳበር የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
9 ጎልማሳ ክርስቲያን መሆን ከፈለጋችሁ ጠቃሚ ክህሎቶችን ማዳበር ይኖርባችኋል። እንዲህ ማድረጋችሁ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ለመቀበል፣ ራሳችሁን ወይም ቤተሰባችሁን ለማስተዳደር የሚያስችል ሥራ ለመያዝ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት ይረዳችኋል። ከእነዚህ አስፈላጊ ክህሎቶች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።
10-11. አንድ ወንድም ጥሩ የማንበብና የመጻፍ ችሎታ ማዳበሩ ራሱንም ሆነ ጉባኤውን የሚጠቅመው እንዴት ነው? (መዝሙር 1:1-3) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
10 ጥሩ የማንበብና የመጻፍ ችሎታ አዳብሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ደስተኛና ስኬታማ የሆነ ሰው በየዕለቱ የአምላክን ቃል እንደሚያነብና እንደሚያሰላስልበት ይናገራል። (መዝሙር 1:1-3ን አንብብ።) አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበቡ የይሖዋን አስተሳሰብ ለመረዳት ያስችለዋል፤ ይህ ደግሞ አጥርቶ ለማሰብና በሚገባ ለማመዛዘን ይረዳዋል። (ምሳሌ 1:3, 4) በጉባኤ ውስጥ እንዲህ ያሉ ወንድሞች ያስፈልጋሉ። ለምን?
11 ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መመሪያና ምክር ለማግኘት ብቃት ያላቸው ወንድሞች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። (ቲቶ 1:9) ጥሩ የማንበብና የመጻፍ ችሎታ ካላችሁ ግንዛቤ የሚያሰፉና እምነት የሚያጠናክሩ ንግግሮችንና ሐሳቦችን መዘጋጀት ትችላላችሁ። በተጨማሪም የግል ጥናት በምታደርጉበት እንዲሁም በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ ንግግሮችን በምታዳምጡበት ጊዜ ጥሩ ማስታወሻ መያዝ ትችላላችሁ። እንዲህ ያለ ማስታወሻ መያዛችሁ እምነታችሁን ለማጠናከር እንዲሁም ሌሎችን ለማበረታታት ይረዳችኋል።
12. የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ ለማዳበር ምን ይረዳችኋል?
12 የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ አዳብሩ። ክርስቲያን ወንዶች ከሌሎች ጋር የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ጥሩ ችሎታ ሊያዳብሩ ይገባል። የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ ያለው ወንድም ሌሎች ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን ሲገልጹ በሚገባ ያዳምጣል፤ ስሜታቸውንም ይረዳላቸዋል። (ምሳሌ 20:5) ሌሎች ሲናገሩ የድምፃቸውን ቃና፣ የፊታቸውን ገጽታ እንዲሁም አካላዊ መግለጫቸውን ማስተዋል ይችላል። ይህን ችሎታ ማዳበር የምትችሉት ከሌሎች ጋር ጊዜ የምታሳልፉ ከሆነ ብቻ ነው። የሐሳብ ልውውጥ የምታደርጉት እንደ ኢሜይል እና የጽሑፍ መልእክት ባሉት የኤሌክትሮኒክ መልእክት መላላኪያ ዘዴዎች ብቻ ከሆነ በአካል የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታችሁ እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል። ስለዚህ ከሌሎች ጋር በአካል ተገናኝታችሁ ማውራት የምትችሉባቸውን አጋጣሚዎች ለመፍጠር ሞክሩ።—2 ዮሐ. 12
13. ወጣት ወንዶች ሌላስ ምን መማር ይኖርባቸዋል? (1 ጢሞቴዎስ 5:8) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
13 ራሳችሁን ለማስተዳደር የሚረዷችሁን ክህሎቶች አዳብሩ። የጎለመሰ ክርስቲያን ወንድም ራሱንም ሆነ ቤተሰቡን የማስተዳደር ችሎታ ሊኖረው ይገባል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8ን አንብብ።) በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ወጣቶች ከአባታቸው ወይም ከሌላ ዘመዳቸው ጠቃሚ ሙያ ይማራሉ። በሌሎች አገሮች ደግሞ ወጣቶች በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያሉ አንዳንድ ሙያዎችንና ክህሎቶችን ሊማሩ ይችላሉ። ያም ሆነ ይህ፣ ሥራ ለማግኘት የሚረዳችሁን ክህሎት ማዳበራችሁ ጠቃሚ ነው። (ሥራ 18:2, 3፤ 20:34፤ ኤፌ. 4:28) በትጋት በመሥራት እንዲሁም የጀመራችሁትን ሥራ በመጨረስ ረገድ ጥሩ ስም ለማትረፍ ጥረት አድርጉ። እንዲህ ካደረጋችሁ ሥራ የማግኘታችሁና ሥራችሁን ይዛችሁ የመቀጠላችሁ አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል። እስካሁን የተመለከትናቸው ባሕርያትና ክህሎቶች ክርስቲያን ወንድሞች ወደፊት የሚቀበሏቸውን ኃላፊነቶች እንዲወጡም ይረዷቸዋል። ከእነዚህ ኃላፊነቶች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።
ወደፊት ለምትቀበሏቸው ኃላፊነቶች ተዘጋጁ
14. ወጣት ወንድሞች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር መዘጋጀት የሚችሉት እንዴት ነው?
14 የሙሉ ጊዜ አገልጋይ። በርካታ የጎለመሱ ክርስቲያን ወንዶች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የጀመሩት በወጣትነታቸው ነው። ወጣት ወንድሞች በአቅኚነት ማገልገላቸው ከተለያዩ ዓይነት ሰዎች ጋር ተባብሮ መሥራት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለመማር ይረዳቸዋል። በተጨማሪም ምክንያታዊ የሆነ በጀት ማውጣትና በበጀታቸው መመራት የሚችሉበትን መንገድ ያስተምራቸዋል። (ፊልጵ. 4:11-13) በረዳት አቅኚነት ማገልገላችሁ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ይረዳችኋል። ብዙዎች ለተወሰነ ጊዜ ያህል ረዳት አቅኚ ሆነው ማገልገላቸው የዘወትር አቅኚነት ለመጀመር ዝግጁ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። አቅኚነት ወደ ሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች ለመግባት መንገድ ሊከፍትላችሁ ይችላል፤ ይህም የግንባታ አገልጋይ ወይም ቤቴላዊ መሆንን ይጨምራል።
15-16. አንድ ወጣት ወንድም በጉባኤ ውስጥ ለማገልገል ብቃቱን ማሟላት የሚችለው እንዴት ነው?
15 የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ። ክርስቲያን ወንዶች የጉባኤ ሽማግሌዎች ሆነው ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን የማገልገል ግብ ሊኖራቸው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ የሚጣጣሩ ወንድሞች ‘መልካም ሥራን እንደሚመኙ’ ይናገራል። (1 ጢሞ. 3:1) አንድ ወንድም የጉባኤ ሽማግሌ ከመሆኑ በፊት ብቃቱን አሟልቶ የጉባኤ አገልጋይ መሆን አለበት። የጉባኤ አገልጋዮች በተለያዩ መንገዶች የጉባኤ ሽማግሌዎችን ይረዳሉ። ሽማግሌዎችም ሆኑ የጉባኤ አገልጋዮች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን በትሕትና ያገለግላሉ፤ እንዲሁም በአገልግሎት በቅንዓት ይካፈላሉ። ወጣት ወንድሞች በአሥራዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ እያሉም የጉባኤ አገልጋይ ሆነው ለመሾም የሚያስፈልገውን ብቃት ሊያሟሉ ይችላሉ። በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ጥሩ ብቃት ያለው የጉባኤ አገልጋይ ደግሞ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ሊሾም ይችላል።
16 እነዚህን ኃላፊነቶች ለመቀበል ብቃቱን ማሟላት የምትችሉት እንዴት ነው? የተለየ ቀመር የለውም። የሚያስፈልጉት ብቃቶች በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ እንዲሁም ለይሖዋ፣ ለቤተሰባችሁና ለጉባኤያችሁ ካላችሁ ፍቅር ጋር የተያያዙ ናቸው። (1 ጢሞ. 3:1-13፤ ቲቶ 1:6-9፤ 1 ጴጥ. 5:2, 3) እያንዳንዱን ብቃት ለመረዳት ጥረት አድርጉ። ይሖዋ እነዚህን ብቃቶች ለማሟላት እንዲረዳችሁ ጸልዩ። c
17. አንድ ወጣት ወንድም ባልና የቤተሰብ ራስ ለመሆን መዘጋጀት የሚችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
17 ባል እና የቤተሰብ ራስ። ኢየሱስ እንደተናገረው አንዳንድ የጎለመሱ ክርስቲያን ወንዶች ሳያገቡ ሊኖሩ ይችላሉ። (ማቴ. 19:12) ይሁንና ትዳር ለመመሥረት ከወሰናችሁ ባልና የቤተሰብ ራስ የመሆን ተጨማሪ ኃላፊነት ትቀበላላችሁ። (1 ቆሮ. 11:3) ይሖዋ፣ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዲወዱ እንዲሁም አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉላቸው ይጠብቅባቸዋል። (ኤፌ. 5:28, 29) የማመዛዘን ችሎታ ማዳበርን፣ ሴቶችን በአክብሮት መያዝን እንዲሁም እምነት የሚጣልባችሁ መሆንን ጨምሮ ቀደም ሲል የተመለከትናቸውን ባሕርያትና ክህሎቶች ማዳበራችሁ ትዳር ስትመሠርቱ ይረዳችኋል። ባልና የቤተሰብ ራስ የመሆን ኃላፊነታችሁን ለመወጣት ዝግጁ ትሆናላችሁ።
18. አንድ ወጣት ወንድም አባት ለመሆን መዘጋጀት የሚችለው እንዴት ነው?
18 አባት። ትዳር ከመሠረታችሁ በኋላ ልጆች ትወልዱ ይሆናል። ጥሩ አባት መሆን የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ከይሖዋ ምን ትማራላችሁ? ብዙ ትምህርቶችን ማግኘት ትችላላችሁ። (ኤፌ. 6:4) ይሖዋ ልጁን ኢየሱስን እንደሚወደውና እንደሚደሰትበት በይፋ ነግሮታል። (ማቴ. 3:17) ልጆች ከወለዳችሁ፣ ለልጆቻችሁ አዘውትራችሁ ፍቅራችሁን ግለጹላቸው። ላከናወኗቸው መልካም ነገሮች አመስግኗቸው። የይሖዋን ምሳሌ የሚከተሉ አባቶች ልጆቻቸው እድገት አድርገው የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ ይረዷቸዋል። የቤተሰባችሁን አባላትና የጉባኤያችሁን ወንድሞችና እህቶች በፍቅር በመንከባከብ እንዲሁም ለእነሱ ያላችሁን ፍቅርና አድናቆት የመግለጽ ልማድ በማዳበር ለዚህ ኃላፊነት ከአሁኑ መዘጋጀት ትችላላችሁ። (ዮሐ. 15:9) እንዲህ ማድረጋችሁ ወደፊት ለምትቀበሉት የባልነትና የአባትነት ኃላፊነት ያዘጋጃችኋል። እስከዚያው ድረስ ደግሞ ለይሖዋ፣ ለቤተሰባችሁና ለጉባኤያችሁ ውድ ሀብት ትሆናላችሁ።
ምን ለማድረግ አስባችኋል?
19-20. ወጣት ወንድሞች የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ የሚረዳቸው ምንድን ነው? (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)
19 ወጣት ወንድሞች፣ ያለምንም ጥረት የጎለመሳችሁ ክርስቲያኖች መሆን አትችሉም። ጥሩ ምሳሌ የሚሆኗችሁን ሰዎች መምረጥ፣ የማመዛዘን ችሎታን ማዳበር፣ እምነት የሚጣልባችሁ መሆን፣ ጠቃሚ ክህሎቶችን ማዳበር እንዲሁም ወደፊት ለምትቀበሏቸው ኃላፊነቶች መዘጋጀት ያስፈልጋችኋል።
20 ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ መድረስ የሚጠይቀውን ጥረት ስታስቡ ከአቅማችሁ በላይ እንደሆነ ይሰማችሁ ይሆናል። ሆኖም ሊሳካላችሁ ይችላል። ይሖዋ ሊረዳችሁ እንደሚፈልግ አስታውሱ። (ኢሳ. 41:10, 13) በጉባኤያችሁ ያሉ ወንድሞችና እህቶችም ይረዷችኋል። እድገት አድርጋችሁ የጎለመሳችሁ ክርስቲያኖች ስትሆኑ ሕይወታችሁ አስደሳችና እርካታ ያለው ይሆንላችኋል። ወጣት ወንድሞች፣ እንወዳችኋለን! የጎለመሳችሁ ክርስቲያኖች ለመሆን ከአሁኑ ጥረት ስታደርጉ ይሖዋ አትረፍርፎ እንዲባርካችሁ እንመኛለን።—ምሳሌ 22:4
መዝሙር 65 ወደፊት ግፋ!
a በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ጎልማሳ ወንድሞች ያስፈልጋሉ። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ወጣት ወንድሞች የጎለመሱ ክርስቲያኖች መሆን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
b ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ያለውን “ተጨማሪ ማብራሪያ” ተመልከት።
c የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ የተባለውን መጽሐፍ ምዕ. 5-6 ተመልከት።