በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በዚህ ዓመት የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በደንብ አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

ይሖዋ ለሴቶች ምን ዓይነት አመለካከት አለው?

ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ ይይዛቸዋል፤ ለወንዶች አያዳላም። አምላክ ሴቶችን ይሰማቸዋል፤ ስሜታቸውና ጭንቀታቸው ያሳስበዋል። እንዲሁም የሰጣቸውን ሥራ እንደሚያከናውኑ ይተማመንባቸዋል።—w24.01 ገጽ 15-16

በኤፌሶን 5:7 ላይ የሚገኘውን “ከእነዚህ ሰዎች ጋር አትተባበሩ” የሚለውን መመሪያ በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ የይሖዋን መሥፈርቶች መጠበቅ ከባድ እንዲሆንብን ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር እንዳንወዳጅ አስጠንቅቆናል። እንዲህ ያለው መጥፎ ወዳጅነት በአካል ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ሚዲያ የምናገኛቸውን ሰዎችም ያካትታል።—w24.03 ገጽ 22-23

ከምን ዓይነት የሐሰት ወሬዎች መጠንቀቅ ይኖርብናል?

ወንድሞችና እህቶች በቅን ልቦና ተነሳስተው ከሚነግሩን ያልተረጋገጡ ተሞክሮዎች፣ ከማናውቃቸው ሰዎች ከሚደርሱን ኢሜይሎች እንዲሁም ለእውነት ፍላጎት ያላቸው መስለው ከሚቀርቡ ከሃዲዎች መጠንቀቅ ይኖርብናል።—w24.04 ገጽ 12

ይሖዋ በንጉሥ ሰለሞን እንዲሁም በሰዶምና ገሞራ እና በጥፋት ውኃው በጠፉት ሰዎች ላይ የሚያስተላልፈውን ፍርድ በተመለከተ ምን እናውቃለን? ምንስ አናውቅም?

ይሖዋ በእነዚህ ሰዎች ላይ ዘላለማዊ ጥፋት የፈረደ መሆን አለመሆኑን በእርግጠኝነት አናውቅም። ሆኖም ይሖዋ የተሟላ መረጃ እንዳለውና ምሕረቱ ታላቅ እንደሆነ እናውቃለን።—w24.05 ገጽ 3-4

አምላክ “ዓለት” መሆኑን ማወቃችን ምን ዋስትና ይሰጠናል? (ዘዳ. 32:4)

ይሖዋ መጠጊያ ይሆንልናል። እምነት የሚጣልበት አምላክ ነው፤ ምንጊዜም ቃሉን ይጠብቃል። በተጨማሪም ባሕርዩም ሆነ ዓላማው አይቀየርም።w24.06 ገጽ 26-28

ከአዲስ ጉባኤ ጋር ለመላመድ ምን ይረዳሃል?

በይሖዋ ታመን፤ ይሖዋ በጥንት ዘመን የነበሩ አገልጋዮቹን እንደረዳቸው ሁሉ አንተንም ይረዳሃል። አዲሱን ጉባኤ ከቀድሞው ጉባኤህ ጋር ከማወዳደር ተቆጠብ። በአዲሱ ጉባኤ እንቅስቃሴዎች ተካፈል፤ አዳዲስ ጓደኞች ለማፍራትም ጥረት አድርግ።—w24.07 ገጽ 26-28

በማቴዎስ ምዕራፍ 25 ላይ የሚገኙት ሦስት ምሳሌዎች ምን ትምህርት ይዘዋል?

የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ ታማኝ እንድንሆን ያበረታታናል። የልባሞቹና የሞኞቹ ደናግል ምሳሌ ዝግጁና ንቁ የመሆንን አስፈላጊነት ያጎላል። የታላንቱ ምሳሌ ደግሞ ታታሪና ትጉ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል።—w24.09 ገጽ 20-24

የሰለሞን ቤተ መቅደስ በረንዳ ከፍታው ምን ያህል ነበር?

በእጅ የተገለበጡ አንዳንድ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች 2 ዜና መዋዕል 3:4 ላይ “120 ክንድ” ይላሉ፤ ይህም ማለት በረንዳው 53 ሜትር ከፍታ ነበረው ማለት ነው። ተአማኒነት ያላቸው ሌሎች ቅጂዎች ግን “20 ክንድ” ይላሉ፤ በዚህ መሠረት ደግሞ በረንዳው ዘጠኝ ሜትር ከፍታ ነበረው። ከቤተ መቅደሱ ግድግዳ ውፍረት አንጻር ሁለተኛው አማራጭ ይበልጥ ያስኬዳል።—w24.10 ገጽ 31

አንድ የጉባኤ አገልጋይ “የአንዲት ሚስት ባል” መሆን አለበት ሲባል ምን ማለት ነው? (1 ጢሞ. 3:12)

ይህ ሲባል አንዲት ሚስት ብቻ ማግባት እንዲሁም የፆታ ብልግና ከመፈጸም መቆጠብ አለበት ማለት ነው። በተጨማሪም ለሌሎች ሴቶች ተገቢ ያልሆነ ትኩረት ሊሰጥ አይገባም።—w24.11 ገጽ 19

ዮሐንስ 6:53 የሚናገረው በጌታ ራት ላይ መከናወን ስላለበት ነገር አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

ዮሐንስ 6:53 የኢየሱስን ሥጋ መብላትና ደሙን መጠጣት አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራል። ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የተናገረው በ32 ዓ.ም. ገሊላ ውስጥ ሲሆን አድማጮቹም በእሱ ላይ ገና እምነት ማሳደር የሚያስፈልጋቸው አይሁዳውያን ነበሩ። ይሁንና የጌታ ራት የተቋቋመው ከአንድ ዓመት በኋላ ኢየሩሳሌም ውስጥ ነው። ኢየሱስ በዚያ ወቅት ያነጋገረው አብረውት በሰማይ ላይ የሚገዙትን ሰዎች ነው።—w24.12 ገጽ 10-11