በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 48

መዝሙር 97 የአምላክ ቃል ሕይወት ነው

ከዳቦው ተአምር ምን እንማራለን?

ከዳቦው ተአምር ምን እንማራለን?

“ሕይወት የሚያስገኘው ምግብ እኔ ነኝ። ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ፈጽሞ አይራብም።”ዮሐ. 6:35

ዓላማ

ኢየሱስ ዳቦውንና ዓሣውን በማብዛት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደመገበ የሚገልጸውን በዮሐንስ ምዕራፍ 6 ላይ የሚገኘውን ዘገባ በመመርመር ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመለከታለን።

1. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዳቦ ምን ያህል ጉልህ ቦታ ተሰጥቶታል?

 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ዳቦ ለብዙዎች ዋነኛ ምግብ ነበር። (ዘፍ. 18:6፤ ሉቃስ 9:3) እንዲያውም ዳቦ በጣም የተለመደ ምግብ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ “ዳቦ” የሚለውን ቃል ምግብን በአጠቃላይ ለማመልከት ይጠቀምበታል። (ሕዝ. 5:16 ግርጌ፤ ማቴ. 6:11 ግርጌ) ኢየሱስ በፈጸማቸው ሁለት ተአምራት ላይም ዳቦ ትልቅ ቦታ ነበረው። (ማቴ. 16:9, 10) ከእነዚህ ዘገባዎች አንደኛውን የምናገኘው በዮሐንስ ምዕራፍ 6 ላይ ነው። ይህን ዘገባ በመመርመር በዘመናችን ተግባራዊ ልናደርጋቸው የምንችላቸውን ትምህርቶች እንመለከታለን።

2. በቤተሳይዳ ምን ዓይነት ሁኔታ ተከሰተ?

2 የኢየሱስ ሐዋርያት ዕለቱን በስብከት ካሳለፉ በኋላ እረፍት አስፈልጓቸው ነበር፤ በዚህ ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ጀልባ ተሳፍረው የገሊላን ባሕር ተሻገሩ። (ማር. 6:7, 30-32፤ ሉቃስ 9:10) ቤተሳይዳ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ ገለል ያለ ስፍራ ሄዱ። ብዙም ሳይቆይ ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰብስበው ወደ እነሱ መጡ። ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች ፊት አልነሳቸውም። ጊዜ ወስዶ በደግነት ስለ መንግሥቱ አስተማራቸው፤ የታመሙትንም ፈወሰ። ቀኑ እየመሸ ሲሄድ ደቀ መዛሙርቱ እነዚያ ሁሉ ሰዎች የሚበሉት ምግብ የሚያገኙት ከየት እንደሆነ ያሳስባቸው ጀመር። ምናልባት አንዳንዶቹ ትንሽ ምግብ ይዘው ሊሆን ይችላል፤ አብዛኞቹ ግን ወደ መንደሮቹ ሄደው ምግብ መግዛት ነበረባቸው። (ማቴ. 14:15፤ ዮሐ. 6:4, 5) ታዲያ ኢየሱስ ምን ያደርግ ይሆን?

ዳቦ በተአምር አቀረበ

3. ኢየሱስ ሐዋርያቱን ምን እንዲያደርጉ ነገራቸው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

3 ኢየሱስ ሐዋርያቱን “መሄድ አያስፈልጋቸውም፤ እናንተ የሚበሉት ነገር ስጧቸው” አላቸው። (ማቴ. 14:16) እንዲህ ማድረግ ግን ቀላል አይደለም። ምክንያቱም በቦታው ሴቶችንና ልጆችን ሳይጨምር 5,000 ገደማ ወንዶች ነበሩ። ስለዚህ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 15,000 ሊደርስ ይችላል። (ማቴ. 14:21) በዚህ ጊዜ እንድርያስ እንዲህ አለ፦ “አምስት የገብስ ዳቦና ሁለት ትናንሽ ዓሣ የያዘ አንድ ትንሽ ልጅ እዚህ አለ። ይህ ግን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ እንዴት ይበቃል?” (ዮሐ. 6:9) በወቅቱ የገብስ ዳቦ ድሆችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች የሚመገቡት የተለመደ ምግብ ነበር፤ ትናንሾቹ ዓሣዎች ደግሞ በጨው ተቀምመው የደረቁ ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ቢሆን ልጁ የያዘው ምግብ ያንን ሁሉ ሰው ለመመገብ ሊበቃ አይችልም።

ኢየሱስ የሰዎቹን መንፈሳዊም ሆነ አካላዊ ፍላጎት አሟልቶላቸዋል (አንቀጽ 3⁠ን ተመልከት)


4. ከዮሐንስ 6:11-13 ምን እንማራለን? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

4 ኢየሱስ ለሕዝቡ ደግነት ማድረግ ስለፈለገ በቡድን በቡድን ሆነው ሣሩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ። (ማር. 6:39, 40፤ ዮሐንስ 6:11-13ን አንብብ።) ኢየሱስ ለዳቦውና ለዓሣው አባቱን እንዳመሰገነ ዘገባው ይናገራል። ደግሞም እንዲህ ማድረጉ ተገቢ ነበር፤ ምክንያቱም የምግቡ ምንጭ አምላክ ነው። እኛም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ከመመገባችን በፊት መጸለይ ይኖርብናል። ሌሎች ሰዎች ኖሩም አልኖሩ እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። ከዚያም ኢየሱስ ምግቡን አከፋፈለ፤ ሰዎቹም በልተው ጠገቡ። እንዲያውም ምግቡ ተረፈ። ኢየሱስ የተረፈው ምግብም እንዲባክን አልፈለገም። በመሆኑም የተረፈው ቁርስራሽ እንዲሰበሰብ አዘዘ፤ ይህን ያደረገው ሌላ ጊዜ ጥቅም ላይ እንዲውል አስቦ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ያሉንን ነገሮች በጥበብ በመጠቀም ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ወላጅ ከሆናችሁ ስለ ጸሎት፣ ስለ እንግዳ ተቀባይነትና ስለ ልግስና ልጆቻችሁን ለማስተማር ይህን ዘገባ ለምን አትጠቀሙበትም?

‘ከመመገቤ በፊት በመጸለይ የኢየሱስን ምሳሌ እከተላለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)


5. ሕዝቡ ኢየሱስ ያደረገውን ካዩ በኋላ ምን አደረጉ? እሱስ ምን ምላሽ ሰጠ?

5 ሰዎቹ በኢየሱስ የማስተማር ጥበብና በፈጸማቸው ተአምራት በእጅጉ ተደነቁ። ሙሴ፣ አምላክ ታላቅ ነቢይ እንደሚያስነሳላቸው ትንቢት ተናግሮ እንደነበር ስለሚያውቁ ‘ኢየሱስ ያ ነቢይ ይሆን እንዴ?’ ብለው አስበው ሊሆን ይችላል። (ዘዳ. 18:15-18) ከሆነ፣ ኢየሱስ ለመላው ብሔር የሚያስፈልገውን ምግብ ማቅረብ የሚችል ኃያል ንጉሥ እንደሚሆን ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። በዚህም የተነሳ ሕዝቡ ኢየሱስን ‘ሊይዙትና ሊያነግሡት አሰቡ።’ (ዮሐ. 6:14, 15) ኢየሱስ እንዲያነግሡት ከፈቀደላቸው በሮም አገዛዝ ሥር በነበሩት አይሁዳውያን ፖለቲካ ውስጥ እጁን ማስገባት ይሆንበታል። ታዲያ እንዲህ አድርጓል? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ ወዲያውኑ ‘ወደ ተራራ ገለል እንዳለ’ ዘገባው ይናገራል። ስለዚህ ኢየሱስ ሌሎች ጫና ቢያሳድሩበትም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ አልሆነም። እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!

6. ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

6 መቼም ሰዎች በተአምር እንድንመግባቸው፣ የታመሙትን እንድንፈውስ አሊያም ደግሞ ንጉሥ ወይም የአገር መሪ እንድንሆን ይጠይቁናል ብለን አናስብም። ሆኖም ነገሮችን ያሻሽላል ብለው የሚያስቡትን ሰው በመደገፍ ወይም ለእሱ ድምፅ በመስጠት በፖለቲካዊ ጉዳዮች እጃችንን እንድናስገባ ይገፋፉን ይሆናል። ነገር ግን ኢየሱስ የተወው ምሳሌ የሚያሻማ አይደለም። በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ አልሆነም። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም” ብሏል። (ዮሐ. 17:14፤ 18:36) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም የኢየሱስን አስተሳሰብና ምግባር መኮረጃቸው ተገቢ ነው። መንግሥቱን እንደግፋለን፤ ስለ መንግሥቱ እንሰብካለን፤ እንዲሁም መንግሥቱ እንዲመጣ እንጸልያለን። (ማቴ. 6:10) ኢየሱስ በተአምር ሕዝቡን እንደመገበ ወደሚገልጸው ዘገባ ተመልሰን ሌላ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት።

ኢየሱስ በአይሁዳውያንም ሆነ በሮማውያን ፖለቲካ ውስጥ እጁን ባለማስገባት ለተከታዮቹ ምሳሌ ትቷል (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)


የዳቦው ተአምር ትርጉም

7. ኢየሱስ ምን አደረገ? ሐዋርያቱስ ምን ምላሽ ሰጡ? (ዮሐንስ 6:16-20)

7 ኢየሱስ ሕዝቡን ከመገበ በኋላ ሐዋርያቱ ጀልባ ተሳፍረው ወደ ቅፍርናሆም እንዲመለሱ አደረገ። እሱ ግን ሊያነግሡት የሞከሩትን ሰዎች ትቶ በመሄድ ወደ ተራራ ወጣ። (ዮሐንስ 6:16-20ን አንብብ።) ሐዋርያቱ በጀልባ ላይ ሳሉ ኃይለኛ ነፋስና ማዕበል ተነሳ። ከዚያም ኢየሱስ በውኃው ላይ እየተራመደ ወደ እነሱ መጣ። ሐዋርያው ጴጥሮስንም በውኃው ላይ እየተራመደ እንዲመጣ ነገረው። (ማቴ. 14:22-31) ኢየሱስ ጀልባው ላይ ሲወጣ አውሎ ነፋሱ ጸጥ አለ። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ተደንቀው “አንተ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነህ” አሉት። a (ማቴ. 14:33) ያም ቢሆን፣ በዚህኛው ተአምርና ኢየሱስ ቀደም ሲል ሕዝቡን በመመገብ በፈጸመው ተአምር መካከል ያለውን ተያያዥነት አላስተዋሉም ነበር። በማርቆስ ዘገባ ውስጥ የሚከተለውን ተጨማሪ መረጃ እናገኛለን፦ “በዚህ ጊዜ በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት ተዋጡ፤ ይህም የሆነው የዳቦውን ተአምር ትርጉም ባለማስተዋላቸው ነው፤ ልባቸው አሁንም መረዳት ተስኖት ነበር።” (ማር. 6:50-52) ሐዋርያቱ፣ ይሖዋ ለኢየሱስ የሰጠው ተአምር የመፈጸም ኃይል ሕዝቡን በመመገብ ብቻ የሚወሰን እንዳልሆነ አላስተዋሉም ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ኢየሱስ ራሱ የዳቦውን ተአምር በመጥቀስ ምን ትምህርት እንደምናገኝ ገልጿል።

8-9. ሕዝቡ ኢየሱስን ለመፈለግ የሞከሩት ለምንድን ነው? (ዮሐንስ 6:26, 27)

8 ኢየሱስ የመገባቸው ሰዎች ትኩረታቸው ያረፈው ሰብዓዊ ፍላጎታቸውን በማርካት ላይ ብቻ ነበር። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በማግስቱ ሲመጡ ኢየሱስና ሐዋርያቱ እንደሄዱ አስተዋሉ። ስለዚህ ከጥብርያዶስ በመጡ ጀልባዎች ላይ ተሳፍረው ኢየሱስን ፍለጋ ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ። (ዮሐ. 6:22-24) ይህን ያደረጉበት ዋነኛ ዓላማ ስለ መንግሥቱ መስማት ስለፈለጉ ነው? አይደለም። በዋነኝነት ያሳሰባቸው የምግብ ፍላጎታቸውን ማርካታቸው ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን?

9 ሕዝቡ ኢየሱስን ቅፍርናሆም አቅራቢያ ባገኙት ጊዜ ምን እንደተከሰተ ልብ በል። ኢየሱስ በዋነኝነት ያሳሰባቸው የምግብ ጉዳይ እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። ‘ዳቦ በልተው ቢጠግቡም’ ያ ምግብ ‘የሚጠፋ ምግብ’ እንደሆነ ነግሯቸዋል። ‘ዘላቂ ለሆነውና የዘላለም ሕይወት ለሚያስገኘው ምግብ እንዲሠሩም’ መክሯቸዋል። (ዮሐንስ 6:26, 27ን አንብብ።) ኢየሱስ አባቱ እንዲህ ያለውን ምግብ እንደሚሰጣቸው ተናግሯል። ሕዝቡ ‘የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ ምግብ አለ’ የሚለው ሐሳብ እንግዳ ሆኖባቸው መሆን አለበት። የዘላለም ሕይወት መስጠት የሚችለው ምን ዓይነት ምግብ ነው? የኢየሱስ አድማጮች ይህን ምግብ ማግኘት የሚችሉትስ እንዴት ነው?

10. ሕዝቡ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ ነበረባቸው?

10 እነዚያ አይሁዳውያን ይህን ምግብ ለማግኘት የሆነ ዓይነት ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ተሰምቷቸው የነበረ ይመስላል። ምናልባትም በሙሴ ሕግ ውስጥ የተጠቀሱትን ‘ሥራዎች’ በአእምሯቸው ይዘው ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ግን “አምላክ የሚቀበለው ሥራማ እሱ በላከው ሰው ማመን ነው” አላቸው። (ዮሐ. 6:28, 29) ‘የዘላለም ሕይወት ለማግኘት’ በአምላክ ወኪል ማመን አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ ከዚያ በፊትም ስለዚህ ጉዳይ ተናግሯል። (ዮሐ. 3:16-18, 36) ከጊዜ በኋላም የዘላለም ሕይወት ማግኘት ስለሚቻልበት መንገድ ተጨማሪ ነገሮችን ተናግሯል።—ዮሐ. 17:3

11. አይሁዳውያኑ ያሳሰባቸው የምግብ ፍላጎታቸው ብቻ እንደነበር ያሳዩት እንዴት ነው? (መዝሙር 78:24, 25)

11 እነዚያ አይሁዳውያን ኢየሱስ ‘አምላክ ስለሚቀበለው’ አዲስ “ሥራ” የሰጠውን ትምህርት አልተቀበሉም። “ታዲያ አይተን እንድናምንብህ ምን ተአምራዊ ምልክት ትፈጽማለህ?” ብለው ጠየቁት። (ዮሐ. 6:30) አባቶቻቸው በሙሴ ዘመን መና እንደወረደላቸው ተናገሩ። (ነህ. 9:15፤ መዝሙር 78:24, 25ን አንብብ።) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አእምሯቸው አሁንም ያተኮረው የምግብ ፍላጎታቸውን በማርካት ላይ ብቻ ነበር። ኢየሱስ ሕይወት ሰጪ የሆነውን በመና የተመሰለውን ‘ከሰማይ የወረደ እውነተኛ ምግብ’ አስመልክቶ ሲናገር እንኳ ማብራሪያ አልጠየቁትም። (ዮሐ. 6:32) ያተኮሩት በምግብ ፍላጎታቸው ላይ ብቻ ስለነበር ኢየሱስ ሊያካፍላቸው እየሞከረ የነበረውን መንፈሳዊ እውነት መረዳት አልቻሉም። ከዚህ ዘገባ ምን እንማራለን?

ትኩረታችን በዋነኝነት ሊያርፍ የሚገባው በምን ላይ ነው?

12. ኢየሱስ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?

12 ከዮሐንስ ምዕራፍ 6 የሚከተለውን ወሳኝ ትምህርት እናገኛለን፦ ትኩረታችን በዋነኝነት ሊያርፍ የሚገባው በመንፈሳዊ ፍላጎታችን ላይ ነው። ኢየሱስ ለሰይጣን ፈተና ምላሽ በሰጠበት ወቅት ይህን ነጥብ ጎላ አድርጎ እንደገለጸ አስታውስ። (ማቴ. 4:3, 4) በተራራ ስብከቱም ላይ ቢሆን ለመንፈሳዊ ፍላጎታችን ንቁ መሆን እንዳለብን ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ማቴ. 5:3 ግርጌ) ከዚህ አንጻር ራሳችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፦ ‘ትኩረቴ በዋነኝነት ያረፈው በመንፈሳዊ ፍላጎቴ ላይ ነው ወይስ በሥጋዊ ፍላጎቴ? ሕይወቴን የምመራበት መንገድ ምን ያሳያል?’

13. (ሀ) በምግብ መደሰት ስህተት ያልሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የትኛውን ማስጠንቀቂያ ልብ ልንል ይገባል? (1 ቆሮንቶስ 10:6, 7, 11)

13 ስለ አካላዊ ፍላጎታችን መጸለያችንና ይህን ፍላጎታችንን በማርካት መደሰታችን ተገቢ ነው። (ሉቃስ 11:3) ‘መብላትና መጠጣት’ እንዲሁም ተግቶ በመሥራት የሚገኝ እርካታ “ከእውነተኛው አምላክ እጅ የተገኘ” ስጦታ ነው። (መክ. 2:24፤ 8:15፤ ያዕ. 1:17) ያም ቢሆን ለቁሳዊ ነገሮች ከተገቢው ያለፈ ትኩረት ልንሰጥ አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስ በአይሁድ ሥርዓት መደምደሚያ ላይ ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች በጻፈበት ወቅት ይህን ሐሳብ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ጳውሎስ እስራኤላውያን በጥንት ዘመን ያጋጠሟቸውን ነገሮች ጠቅሷል፤ ከእነዚህም መካከል በሲና ተራራ አቅራቢያ ያደረጉት ነገር ይገኝበታል። “[እስራኤላውያን] ጎጂ የሆኑ ነገሮችን እንደተመኙ እኛም እንዳንመኝ” በማለት ለክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 10:6, 7, 11ን አንብብ።) እስራኤላውያን የምግብ ፍላጎታቸው ይሖዋ በተአምር ያደረገላቸው ዝግጅትም እንኳ ‘ጎጂ ነገር’ እንዲሆንባቸው አድርጓል። (ዘኁ. 11:4-6, 31-34) የወርቅ ጥጃ በሠሩበት ጊዜ ደግሞ በልተዋል፣ ጠጥተዋል እንዲሁም ጨፍረዋል። (ዘፀ. 32:4-6) ጳውሎስ የጥንቶቹ እስራኤላውያን ያጋጠማቸውን ነገር በ70 ዓ.ም. የአይሁድ ሥርዓት መጨረሻ ከመምጣቱ በፊት ለኖሩት ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ አድርጎ ጠቅሶታል። እኛም የምንኖረው የዚህ ሥርዓት መጨረሻ በተቃረበበት ዘመን ስለሆነ የጳውሎስን ምክር በቁም ነገር ልንመለከተው ይገባል።

14. በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖረው የምግብ አቅርቦት ምን ይመስላል?

14 ኢየሱስ “የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን” ብለን እንድንጸልይ ባስተማረበት ወቅት የአምላክ ፈቃድ “በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም” ብለን እንድንጸልይ ነግሮናል። (ማቴ. 6:9-11) በዚያ ጊዜ ዓለማችን ምን ትመስል ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ሲፈጸም ጥሩ ምግብ እንደምናገኝ ይነግረናል። በኢሳይያስ 25:6-8 መሠረት በይሖዋ መንግሥት አገዛዝ ሥር የተትረፈረፈ ምርጥ ምግብ ይኖራል። መዝሙር 72:16 “በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል፤ በተራሮችም አናት ላይ በብዛት ይኖራል” ይላል። በዚያ ጊዜ የሚኖረውን እህል ተጠቅመህ የምትወደውን ዓይነት ዳቦ ስትጋግር ወይም ሌላ ዓይነት ምግብ ስትሠራ ይታይሃል? ወይን ተክለህ ከዚያ የሚገኘውን የወይን ጠጅ ማጣጣምም ትችላለህ። (ኢሳ. 65:21, 22) ደግሞም በምድር ላይ የሚኖር ሰው ሁሉ በእነዚህ ነገሮች ይደሰታል።

15. በትንሣኤ ወቅት ምን ዓይነት የትምህርት መርሐ ግብር ይዘረጋል? (ዮሐንስ 6:35)

15 ዮሐንስ 6:35ን አንብብ። ኢየሱስ በተአምር ያቀረበውን ዳቦና ዓሣ የበሉት ሰዎች ወደፊት ምን ይጠብቃቸዋል? በትንሣኤ ወቅት አንዳንዶቹን ታገኛቸው ይሆናል። ያኔ በኢየሱስ ያላመኑ ቢሆንም እንኳ ትንሣኤ ሊያገኙ ይችላሉ። (ዮሐ. 5:28, 29) እንዲህ ያሉ ሰዎች ኢየሱስ የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት ያላቸውን ትርጉም መማር ይኖርባቸዋል፦ “ሕይወት የሚያስገኘው ምግብ እኔ ነኝ። ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ፈጽሞ አይራብም።” በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ማዳበር ማለትም ለእነሱ ሲል ሕይወቱን እንደሰጠ ማመን ይኖርባቸዋል። በዚያ ወቅት፣ ከሞት ለተነሱ ሰዎችና በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለሚወለዱ ልጆች የመንፈሳዊ ትምህርት መርሐ ግብር ይዘረጋል። በዚህ የትምህርት ዘመቻ ላይ መካፈል ምንኛ የሚያስደስት ይሆን! ይህ ሥራ የሚያስገኘው ደስታ ዳቦ ከመብላት ጋር አይወዳደርም። በእርግጥም ሕይወታችን የሚያጠነጥነው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ይሆናል።

16. በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

16 እስካሁን የተመለከትነው በዮሐንስ ምዕራፍ 6 ላይ ያለውን ዘገባ የተወሰነ ክፍል ነው። ሆኖም ኢየሱስ ስለ ዘላለም ሕይወት ተጨማሪ ትምህርት ሰጥቷል። በወቅቱ የነበሩት አይሁዳውያን ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ልብ ሊሉ ይገባ ነበር፤ እኛም ብንሆን ትኩረት ልንሰጠው ይገባል። በቀጣዩ ርዕስ ላይ ዮሐንስ ምዕራፍ 6⁠ን መመርመራችንን እንቀጥላለን።

መዝሙር 20 ውድ ልጅህን ሰጠኸን

a ከዚህ አስደናቂ ዘገባ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 131 እንዲሁም በእምነታቸው ምሰሏቸው የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 185 ተመልከት።