በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 50

መዝሙር 135 የይሖዋ ፍቅራዊ ግብዣ፦ ‘ልጄ ሆይ፣ ጥበበኛ ሁን’

ወላጆች—ልጆቻችሁ እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ እርዷቸው

ወላጆች—ልጆቻችሁ እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ እርዷቸው

“ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ [አረጋግጡ]።”—ሮም 12:2

ዓላማ

ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት መመሥረት እንዲሁም ልጆቻቸው በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ መርዳት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

1-2. ወላጆች ልጆቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን እምነታችንን አስመልክቶ ጥያቄ ሲያነሱ ምን ምላሽ ሊሰጡ ይገባል?

 ወላጅ መሆን ብዙ ሥራ እንደሚጠይቅ ብዙዎች ይስማማሉ። ትናንሽ ልጆች ያሏችሁ ወላጆች ከሆናችሁ ልጆቻችሁ ጠንካራ እምነት እንዲያዳብሩ ለመርዳት በርትታችሁ ስለምትሠሩ እናመሰግናችኋለን። (ዘዳ. 6:6, 7) ልጆቻችሁ እያደጉ ሲሄዱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው እምነታችንና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጥያቄ ማንሳት ሊጀምሩ ይችላሉ።

2 መጀመሪያ ላይ ልጆቻችሁ ጥያቄ የተፈጠረባቸው መሆኑ ሊያሳስባችሁ ይችላል። እንዲያውም የልጆቻችሁ እምነት እንደተዳከመ ሊሰማችሁ ይችላል። ሆኖም ልጆች እያደጉ ሲሄዱ ጠንካራ እምነት እንዲያዳብሩ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮ. 13:11) ስለዚህ ይህ ሊያሳስባችሁ አይገባም። ልጆቻችሁ የምናምንባቸውን ነገሮች በተመለከተ ጥያቄ በሚያነሱበት ጊዜ አጋጣሚውን ተጠቅማችሁ የማሰብ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ልትረዷቸው ትችላላችሁ።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 በዚህ ርዕስ ውስጥ ወላጆች ልጆቻቸው (1) እምነታቸውን እንዲያሳድጉ፣ (2) ለመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አድናቆት እንዲያዳብሩ እንዲሁም (3) ለእምነታቸው ጥብቅና እንዲቆሙ መርዳት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። እግረ መንገዳችንን፣ ልጆች ጥያቄ ማንሳታቸው ጠቃሚ የሆነው ለምን እንደሆነ እንዲሁም ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ስለ ክርስቲያናዊ እምነታችን ለመነጋገር የትኞቹን አጋጣሚዎች መጠቀም እንደሚችሉ እንመለከታለን።

ልጆቻችሁ እምነታቸውን እንዲያሳድጉ እርዷቸው

4. ልጆች የትኞቹ ጥያቄዎች ሊፈጠሩባቸው ይችላሉ? ለምንስ?

4 ክርስቲያን ወላጆች በአምላክ ላይ የሚኖረን እምነት በዘር የሚወረስ ነገር እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። እናንተ በይሖዋ ላይ እምነት ኖሯችሁ እንዳልተወለዳችሁ የታወቀ ነው። የልጆቻችሁም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ልጆቻችሁ እያደጉ ሲሄዱ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ሊያሳስቧቸው ይችላሉ፦ ‘አምላክ እንዳለ እርግጠኛ መሆን የምችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው ነገር ላይ መተማመን እችላለሁ?’ መጽሐፍ ቅዱስም ‘የማሰብ ችሎታችንን’ እንድንጠቀምና ‘ሁሉንም ነገር እንድንመረምር’ ያበረታታናል። (ሮም 12:1፤ 1 ተሰ. 5:21) ታዲያ ልጆቻችሁ እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?

5. ወላጆች ልጆቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያሳድጉ ለመርዳት ምን ማድረግ ይችላሉ? (ሮም 12:2)

5 ልጆቻችሁ እውነትን በራሳቸው መርምረው እንዲያረጋግጡ አበረታቷቸው። (ሮም 12:2ን አንብብ።) ልጆቻችሁ ጥያቄ ሲያነሱ አጋጣሚውን ተጠቅማችሁ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) እና የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች የተባሉትን መሣሪያዎች ተጠቅመው መልስ ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አሳዩአቸው። የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች በተባለው መጽሐፍ ውስጥ “መጽሐፍ ቅዱስ” በሚለው ርዕስ ሥር ያለውን “በአምላክ መንፈስ መሪነት ተጽፏል” የሚለውን ክፍል እንዲመለከቱ ልትጠቁሟቸው ትችላላችሁ። በዚህ ክፍል ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁ በሰዎች የተጻፈ ጥሩ መጽሐፍ ሳይሆን “የአምላክ ቃል” መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ያገኛሉ። (1 ተሰ. 2:13) ለምሳሌ የአሦር ከተማ ስለነበረችው ስለ ጥንቷ ነነዌ ምርምር ሊያደርጉ ይችላሉ። ከተወሰነ ጊዜ በፊት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ነነዌ የምትባል ከተማ ኖራ እንደማታውቅ ይናገሩ ነበር። ሆኖም በ1850ዎቹ የከተማዋ ፍርስራሾች በቁፋሮ ተገኙ፤ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እውነት መሆኑን አረጋግጧል። (ሶፎ. 2:13-15) የነነዌ ጥፋት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም ያደረገው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ በኅዳር 2021 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ይህን ያውቁ ኖሯል?” የሚለውን ርዕስ መመልከት ይችላሉ። ልጆቻችሁ በጽሑፎቻችን ላይ የሚያገኙትን ትምህርት ከኢንሳይክሎፒዲያዎችና ተአማኒ ከሆኑ ሌሎች ምንጮች ጋር በማወዳደር መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው ነገር ላይ ያላቸውን እምነት የሚያጠናክር አሳማኝ ምክንያት ማግኘት ይችላሉ።

6. ወላጆች ልጆቻቸው የማሰብ ችሎታቸውን እንዲያሠሩ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ሥዕሉንም ተመልከት።)

6 ልጆቻችሁ የማሰብ ችሎታቸውን እንዲያሠሩ እርዷቸው። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በአምላክ ላይ እምነት ስለማሳደር አስደሳች ውይይት ማድረግ የሚችሉባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች አሉ። እንዲህ የመሰሉ አጋጣሚዎች የሚፈጠሩላችሁ ሙዚየሞችን፣ መናፈሻዎችን ወይም የይሖዋ ምሥክሮችን ቅርንጫፍ ቢሮዎች ስትጎበኙ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ሙዚየሞችን በአካል ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት ስትጎበኙ ልጆቻችሁ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ታሪካዊ ዘገባዎችን ወይም ቅርሶችን ልብ ብለው እንዲመለከቱ ልትጠቁሟቸው ትችሉ ይሆናል። ልጆቻችሁ “የሞዓባውያን ጽላት” ተብሎ በሚታወቅ 3,000 ዓመት ያስቆጠረ አንድ ጥንታዊ ድንጋይ ላይ የይሖዋ ስም እንደሚገኝ ያውቃሉ? ኦሪጅናሉ የሞዓባውያን ጽላት ፈረንሳይ ውስጥ በፓሪስ በሚገኝ አንድ ሙዚየም ውስጥ ለእይታ ቀርቧል። ከዚህም በተጨማሪ ዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ባለው “መጽሐፍ ቅዱስ እና መለኮታዊው ስም” በሚለው ሙዚየም ውስጥ ከኦሪጅናሉ ጋር ተመሳስሎ የተሠራ የሞዓባውያን ጽላት አለ። ይህ ጽላት የሞዓብ ንጉሥ ሜሻ በእስራኤል ላይ እንዳመፀ ይናገራል። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ነገር ጋር የሚስማማ ነው። (2 ነገ. 3:4, 5) ልጆቻችሁ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነትና ትክክለኛነት የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በገዛ ዓይናቸው ሲመለከቱ እምነታቸው ይጠናከራል።—ከ2 ዜና መዋዕል 9:6 ጋር አወዳድር።

በሙዚየም ውስጥ የሚገኙ ቅርሶችን በመጠቀም ልጆቻችሁ እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ ልትረዷቸው ትችላላችሁ (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)


7-8. (ሀ) በተፈጥሮ ላይ ከምናየው ውበትና ንድፍ ምን ትምህርት እናገኛለን? ምሳሌ ስጥ። (ሥዕሉንም ተመልከት።) (ለ) ልጆቻችሁ በፈጣሪ ላይ ያላቸው እምነት እንዲጠናከር የትኞቹን ጥያቄዎች ልታነሱላቸው ትችላላችሁ?

7 ልጆቻችሁ በፍጥረት ላይ እንዲያሰላስሉ አበረታቷቸው። በገጠራማ አካባቢ ስትጓዙ ወይም አትክልት ስትንከባከቡ ልጆቻችሁ በፍጥረት ላይ የሚታዩ ንድፎችን ልብ ብለው እንዲመለከቱ ጋብዟቸው። ለምን? እነዚህ ንድፎች ጥበበኛ የሆነ ንድፍ አውጪ እንዳለ ይመሠክራሉ። ለምሳሌ ሳይንቲስቶች በጥምዝምዝ ቅርጾች ላይ ለረጅም ዓመታት ጥናት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ኒኮላ ፋሜሊ የተባሉ አንድ ሳይንቲስት እንደተናገሩት በተፈጥሮ ላይ የሚገኙ ጥምዝምዝ ቅርጾችን ስንቆጥር ቁጥሮቹ አንድን ቀመር እንደሚከተሉ እናስተውላለን። ይህ ቀመር የፊቦናቺ ቀመር በመባል ይታወቃል። ጥምዝምዝ ቅርጾች በጋላክሲዎች፣ በዛጎሎች፣ በቅጠሎች፣ በሱፍ አበቦችና በሌሎች በርካታ ፍጥረታት ላይ ይታያሉ። a

8 ልጆቻችሁ በሳይንስ ትምህርታቸው ወቅት የብዙ ነገሮች ቅርጽ የተመሠረተው በተፈጥሮ ሕጎች ላይ እንደሆነ መረዳታቸው አይቀርም። ለምሳሌ ዛፎችን ብንመለከት ግንዱ ቅርንጫፎችን ያወጣል፤ እያንዳንዱ ቅርንጫፍ ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ያወጣል፤ እነዚህ ቅርንጫፎች ደግሞ ቀንበጦችን ያወጣሉ። እንዲህ ያለው ንድፍ በሌሎች ፍጥረታትም ላይ ይታያል። ታዲያ እነዚህን ውብ ንድፎች ያስገኘውን ሕግ የፈጠረው ማን ነው? ተፈጥሮ በዚህ መልኩ ሥርዓቱን እንዲጠብቅ ያስቻለው ማን ነው? ልጆቻችሁ በእነዚህ ነገሮች ላይ ይበልጥ ባሰላሰሉ መጠን ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው አምላክ ስለመሆኑ ያላቸው እምነት መጠናከሩ አይቀርም። (ዕብ. 3:4) ከዚያም እንዲህ ብላችሁ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ፦ “የፈጠረን አምላክ ከሆነ ደስተኛ እንድንሆን የሚረዱንን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ይሰጠናል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ አይሆንም?” በተጨማሪም እንዲህ ያለው ጠቃሚ መመሪያ የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሆነ ልትጠቁሟቸው ትችላላችሁ።

NASA, ESA, and the Hubble Heritage (STScl/AURA)-ESA/Hubble Collaboration

በተፈጥሮ ላይ ከሚታየው ውበትና ንድፍ በስተ ጀርባ ያለው ማን ነው? (አንቀጽ 7-8⁠ን ተመልከት)


ለመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አድናቆት እንዲያዳብሩ እርዷቸው

9. ልጆቻችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ላይ ጥያቄ እንዲያነሱ የሚያደርጋቸው ምን ሊሆን ይችላል?

9 ልጆቻችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጠቃሚ ስለመሆናቸው ጥያቄ ከተፈጠረባቸው ከጥያቄው በስተ ጀርባ ያለው ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችል ለማስተዋል ሞክሩ። በእርግጥ የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ትክክል እንዳልሆኑ ስለሚሰማቸው ነው? ወይስ እነዚህ መሥፈርቶች ያላቸውን ጥቅም ለሌሎች ማስረዳት ስለሚከብዳቸው ነው? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ከልጆቻችሁ ጋር ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ በማጥናት ለመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አድናቆት እንዲያዳብሩ ልትረዷቸው ትችላላችሁ። b

10. ልጆቻችሁ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት እንዲነሳሱ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?

10 ልጆቻችሁ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት እንዲነሳሱ እርዷቸው። ከልጆቻችሁ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠኑ ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ላይ ያሉትን የአመለካከት ጥያቄዎችና ምሳሌዎች ተጠቅማችሁ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ አበረታቷቸው። (ምሳሌ 20:5) ለምሳሌ ምዕራፍ 8 ላይ ይሖዋ የሚጠቅሙንንና ከአደጋ የሚጠብቁንን ምክሮች ከሚሰጠን አሳቢ ጓደኛ ጋር ተመሳስሏል። በ1 ዮሐንስ 5:3 ላይ ከተወያያችሁ በኋላ “ይሖዋ እንዲህ የመሰለ ጥሩ ጓደኛ መሆኑን ከተረዳን የሚሰጠንን መመሪያዎች እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?” ብላችሁ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። ይህ ቀላል ጥያቄ ሊመስል ይችላል። ሆኖም እንዲህ ያለ ጥያቄ መጠየቃችሁ ልጆቻችሁ ይሖዋ ሕጎችን የሚሰጠን በፍቅር ተነሳስቶ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል።—ኢሳ. 48:17, 18

11. ልጆቻችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያላቸውን ጥቅም እንዲገነዘቡ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? (ምሳሌ 2:10, 11)

11 የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል የሚጠቅመን እንዴት እንደሆነ ከልጆቻችሁ ጋር ተወያዩ። አንድ ላይ ሆናችሁ መጽሐፍ ቅዱስን ወይም የዕለቱን ጥቅስ በምታነቡበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ቤተሰባችሁን የጠቀሙት እንዴት እንደሆነ ተወያዩ። ለምሳሌ ልጆቻችሁ ታታሪና ሐቀኛ መሆን ያለውን ጥቅም ተረድተዋል? (ዕብ. 13:18) በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጉዳት ከሚያደርሱ ነገሮች ሊጠብቀን የሚችለው እንዴት እንደሆነ ልታጎሉ ትችላላችሁ። (ምሳሌ 14:29, 30) ስለ እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መወያየታችሁ ልጆቻችሁ ለመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይበልጥ አድናቆት እንዲኖራቸው ሊረዳቸው ይችላል።—ምሳሌ 2:10, 11ን አንብብ።

12. አንድ አባት ልጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች የሚያስገኙትን ጥቅም እንዲገነዘብ የሚረዳው እንዴት ነው?

12 በፈረንሳይ የሚኖረው ስቲቭ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ኤታን የተባለ ልጅ አለው። እሱና ባለቤቱ የይሖዋ ሕጎች ፍቅሩን የሚያሳዩት እንዴት እንደሆነ ለልጃቸው ለማስረዳት ምን እንዳደረጉ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን እንጠይቀዋለን፦ ‘ይሖዋ ይህን መመሪያ እንድናከብር የሚጠብቅብን ለምንድን ነው? ይህ መመሪያ ይሖዋ እንደሚወደን የሚያሳየው እንዴት ነው? ይህን መመሪያ ባትከተል ምን ሊያጋጥምህ ይችላል?’” እንዲህ ያሉት ውይይቶች፣ ኤታን ይሖዋ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ከልቡ እንዲያምንባቸው ረድተውታል። ስቲቭ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “ዓላማችን ኤታን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ከሰብዓዊ ጥበብ እጅግ የላቁ እንደሆኑ እንዲገነዘብ መርዳት ነው።”

13. ወላጆች ልጆቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ እንዲያውሉ ማሠልጠን የሚችሉት እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

13 ልጆቻችሁ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ እንዲያውሉ አሠልጥኗቸው። ልጆቻችሁ አንድ መጽሐፍ እንዲያነቡ የቤት ሥራ ሲሰጣቸው ይህን ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ ልታገኙ ትችላላችሁ። መጽሐፉ ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት የሚፈጽሙ ወይም ቁጣቸውን የማይቆጣጠሩ ገጸ ባሕርያትን ጥሩ አስመስሎ ሊያቀርብ ይችላል። ልጆቻችሁ ገጸ ባሕርያቱ የሚያደርጉትን ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንጻር እንዲመለከቱት ልታበረታቷቸው ትችላላችሁ። (ምሳሌ 22:24, 25፤ 1 ቆሮ. 15:33፤ ፊልጵ. 4:8) እንዲህ ማድረጋችሁ የቤት ሥራውን በተመለከተ የክፍል ውይይት በሚደረግበት ጊዜ ልጆቻችሁ ለአስተማሪዎቻቸውና አብረዋቸው ለሚማሩት ልጆች ለመመሥከር ዝግጁ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።

ልጆቻችሁ ለእምነታቸው ጥብቅና እንዲቆሙ አዘጋጇቸው

14. ወጣት ክርስቲያኖች የትኛውን ርዕስ በተመለከተ እምነታቸውን በግልጽ መናገር ሊከብዳቸው ይችላል? ለምንስ?

14 አንዳንድ ጊዜ ወጣት ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ጥብቅና ለመቆም ሊፈሩ ይችላሉ። ክፍል ውስጥ የዝግመተ ለውጥ ርዕሰ ጉዳይ ሲነሳ ሊጨንቃቸው ይችላል። ለምን? እንዲህ የሚሰማቸው አስተማሪዎቻቸው ዝግመተ ለውጥ የተረጋገጠ ሐቅ እንደሆነ ስለሚናገሩ ሊሆን ይችላል። ወላጆች ከሆናችሁ፣ ልጆቻችሁ ለእምነታቸው ጥብቅና ለመቆም የሚያስችል ድፍረት እንዲኖራቸው ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?

15. ወጣት ክርስቲያኖች በእምነታቸው እንዳያፍሩ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

15 ልጆቻችሁ በሚያምኑበት ነገር እንዳያፍሩ እርዷቸው። ልጆቻችሁ ፍጥረትን በተመለከተ እውነቱን በማወቃቸው ሊያፍሩ አይገባም። (2 ጢሞ. 1:8) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ብዙ ሳይንቲስቶችም እንኳ ሕይወት እንዲሁ በአጋጣሚ ወይም በራሱ እንዳልተገኘ ያምናሉ። በፍጥረት ላይ ከሚታየው ውስብስብነት አንጻር ጥበበኛ የሆነ ንድፍ አውጪ እንዳለ ይረዳሉ። በመሆኑም በዓለም ዙሪያ በየትምህርት ቤቶቹ እየተሰጠ ያለውን የዝግመተ ለውጥ ትምህርት አይቀበሉም። ልጆቻችሁ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ሕይወት በፍጥረት እንደተገኘ እንዲያምኑ ያደረጓቸውን ምክንያቶች በመመርመር የራሳቸውን እምነት ማጠናከር ይችላሉ። c

16. ወላጆች ልጆቻቸው በፈጣሪ የሚያምኑበትን ምክንያት እንዲያብራሩ ሊያዘጋጇቸው የሚችሉት እንዴት ነው? (1 ጴጥሮስ 3:15) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

16 ልጆቻችሁ በፈጣሪ የሚያምኑበትን ምክንያት እንዲያብራሩ አዘጋጇቸው። (1 ጴጥሮስ 3:15ን አንብብ።) ከልጆቻችሁ ጋር በ​jw.org ላይ የሚገኙትን “የወጣቶች ጥያቄ—ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?” የሚሉትን ተከታታይ ርዕሶች አብራችሁ መከለሳችሁ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ከዚያም ልጆቻችሁ ፈጣሪን በተመለከተ ለሌሎች እውነቱን ለማስረዳት ይበልጥ አሳማኝ እንደሆነ የሚሰማቸውን ነጥብ ተወያዩ። አብረዋቸው ከሚማሩት ልጆች ጋር ክርክር ውስጥ መግባት እንደማያስፈልጋቸው አስታውሷቸው። ጥሩ ውይይት ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ካገኙ ቀላል የሆነ ማብራሪያ ተጠቅመው እንዲያወያዩት አበረታቷቸው። ለምሳሌ አንድ ልጅ “የማምነው የማየውን ነገር ብቻ ነው፤ አምላክን ደግሞ አይቼው አላውቅም” ይላቸው ይሆናል። አንድ ክርስቲያን ወጣት እንዲህ ብሎ ሊመልስ ይችላል፦ “ሰዎች ከሚኖሩበት አካባቢ በጣም ርቆ በሚገኝ ጫካ ውስጥ በድንጋይ የተገነባ የውኃ ጉድጓድ አገኘህ እንበል። ምን መደምደሚያ ላይ ትደርሳለህ? አንድ የውኃ ጉድጓድ መኖሩ የሠራው ሰው እንዳለ የሚያረጋግጥ ከሆነ የጽንፈ ዓለሙ መኖር ፈጣሪ እንዳለ የሚያረጋግጥ አይደለም?”

አብረውህ ከሚማሩት ልጆች ጋር ስትወያይ ቀላልና ምክንያታዊ የሆኑ ማብራሪያዎችን ተጠቀም (አንቀጽ 16-17⁠ን ተመልከት) d


17. ወላጆች ልጆቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ለማካፈል የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን እንዲፈልጉ ሊያበረታቷቸው የሚችሉት እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

17 ልጆቻችሁ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ለማካፈል የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን እንዲፈልጉ አበረታቷቸው። (ሮም 10:10) ስለ እምነታቸው ለመናገር የሚያደርጉት ጥረት አንድን የሙዚቃ መሣሪያ ለመጫወት ከሚደረገው ጥረት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አንድ ሰው በመጀመሪያ ቀላል የሆኑ ዜማዎችን መጫወት ይለማመዳል። በጊዜ ሂደት ሙዚቃ መጫወት እየቀለለው ይመጣል። በተመሳሳይም ወጣት ክርስቲያኖች መጀመሪያ ላይ ቀላል አቀራረቦችን በመጠቀም ስለ እምነታቸው ለሌሎች መናገር ይችላሉ። ለምሳሌ አብሯቸው የሚማርን አንድ ልጅ እንዲህ ብለው ሊጠይቁት ይችላሉ፦ “ብዙ ጊዜ መሐንዲሶች በተፈጥሮ ላይ የሚታዩ ንድፎችን እንደሚኮርጁ ታውቃለህ? አንድ የሚያስገርም ቪዲዮ ላሳይህ።” ከዚያም ንድፍ አውጪ አለው? በሚለው ክፍል ሥር ካሉት ቪዲዮዎች መካከል አንዱን ካሳዩት በኋላ እንዲህ ሊሉት ይችላሉ፦ “አንድ ሳይንቲስት በተፈጥሮ ላይ ያየውን ንድፍ ኮርጆ ለሠራው ነገር እውቅና የሚሰጠው ከሆነ ለዋናው ንድፍ እውቅና ሊሰጠው የሚገባው ማን ነው?” እንዲህ ያለው ቀላል አቀራረብ ትኩረቱን ሊስበውና ይበልጥ ለማወቅ እንዲነሳሳ ሊያደርገው ይችላል።

ልጆቻችሁ እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ መርዳታችሁን ቀጥሉ

18. ወላጆች ልጆቻቸው በአምላክ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ መርዳታቸውን መቀጠል የሚችሉት እንዴት ነው?

18 የምንኖርበት ዓለም በይሖዋ ላይ እምነት በሌላቸው ሰዎች የተሞላ ነው። (2 ጴጥ. 3:3) እንግዲያው ወላጆች፣ ከልጆቻችሁ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠኑ ልጆቻችሁ ለአምላክ ቃልና ለሥነ ምግባር መሥፈርቶቹ አክብሮት እንዲያዳብሩ በሚረዷቸው ርዕሶች ላይ ምርምር እንዲያደርጉ አበረታቷቸው። ልጆቻችሁ የማሰብ ችሎታቸውን እንዲያሠሩ ለማበረታታት የይሖዋን ድንቅ የፍጥረት ሥራዎች ተጠቀሙ። ፍጻሜያቸውን ስላገኙ አስደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ግንዛቤያቸውን እንዲያሳድጉ እርዷቸው። ከሁሉም በላይ ግን ለልጆቻችሁ ጸልዩላቸው፤ እንዲሁም አብራችኋቸው ጸልዩ። እንዲህ ካደረጋችሁ ልጆቻችሁ እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ ለመርዳት የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ እንደሚባርከው እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ።—2 ዜና 15:7

መዝሙር 133 በወጣትነታችሁ ይሖዋን አምልኩ

a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች የአምላክን ክብር ይገልጣሉ (እንግሊዝኛ) የተባለውን ቪዲዮ jw.org ላይ ተመልከቱ።

b ልጆቻችሁ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ አጥንተው ጨርሰው ከሆነ በክፍል 3 እና 4 ውስጥ የሚገኙትን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚናገሩ አንዳንድ ምዕራፎች አብራችሁ ልትከልሱ ትችላላችሁ።

c በመስከረም 2006 ንቁ! ላይ የወጣውን “በፈጣሪ የምናምንበት ምክንያት” የሚለውን ርዕስ እንዲሁም የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የተባለውን ብሮሹር ተመልከቱ። ተጨማሪ ምሳሌዎችን ለማግኘት jw.org ላይ ስለ ሕይወት አመጣጥ የተሰጡ አስተያየቶች በሚል ርዕስ የሚወጡትን ተከታታይ ቪዲዮዎች ተመልከቱ።

d የሥዕሉ መግለጫ፦ የይሖዋ ምሥክር የሆነ ልጅ አብሮት ለሚማር ልጅ ንድፍ አውጪ አለው? በሚለው ክፍል ሥር የሚገኝ አንድ ቪዲዮ ሲያሳይ።