የአንባቢያን ጥያቄዎች
በ1 ጢሞቴዎስ 5:21 ላይ የተጠቀሱት ‘የተመረጡ መላእክት’ እነማን ናቸው?
ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ እሱ በሽምግልና ለሚያገለግለው ለጢሞቴዎስ እንዲህ ሲል ጽፎለታል፦ “እነዚህን መመሪያዎች መሠረተ ቢስ ከሆነ ጥላቻና ከአድልዎ በራቀ መንገድ እንድትጠብቅ በአምላክ፣ በክርስቶስ ኢየሱስና በተመረጡት መላእክት ፊት በጥብቅ አዝሃለሁ።”—1 ጢሞ. 5:21
በመጀመሪያ እነዚህ መላእክት እነማንን ሊያመለክቱ እንደማይችሉ እንመልከት። እነዚህ መላእክት 144,000ዎቹን እንደማያመለክቱ ግልጽ ነው። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈበት ወቅት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚያገኙት ሰማያዊ ትንሣኤ አልጀመረም ነበር። ሐዋርያቱም ሆኑ የቀሩት ቅቡዓን ገና መንፈሳዊ ፍጥረታት አልሆኑም፤ ስለዚህ ‘የተመረጡት መላእክት’ እነሱን ሊያመለክቱ አይችሉም።—1 ቆሮ. 15:50-54፤ 1 ተሰ. 4:13-17፤ 1 ዮሐ. 3:2
በተጨማሪም ‘የተመረጡት መላእክት’ በጥፋት ውኃው ወቅት በአምላክ ላይ ያመፁትን መላእክት ሊያመለክቱ አይችሉም። እነዚያ መላእክት ከሰይጣን ጋር በማበር አጋንንት ሆነዋል፤ ኢየሱስም ተቃውሟቸዋል። (ዘፍ. 6:2፤ ሉቃስ 8:30, 31፤ 2 ጴጥ. 2:4) ወደፊት ደግሞ ለ1,000 ዓመታት በጥልቁ ውስጥ ይታሰራሉ፤ ከዚያም ከዲያብሎስ ጋር አብረው ይጠፋሉ።—ይሁዳ 6፤ ራእይ 20:1-3, 10
ጳውሎስ የጠቀሳቸው ‘የተመረጡ መላእክት’ ‘አምላክንና ክርስቶስ ኢየሱስን’ የሚደግፉ በሰማይ ያሉ መላእክት መሆን አለባቸው።
በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ታማኝ መላእክት አሉ። (ዕብ. 12:22, 23) ሁሉም በተመሳሳይ ጊዜ ተመሳሳይ ሥራ ይሰጣቸዋል ብለን ልናስብ አይገባም። (ራእይ 14:17, 18) ለምሳሌ በአንድ ወቅት አንድ መልአክ 185,000 አሦራውያን ወታደሮችን እንዲያጠፋ ታዝዞ ነበር። (2 ነገ. 19:35) በተጨማሪም “እንቅፋት የሚፈጥሩትን ነገሮች ሁሉና ዓመፅ የሚፈጽሙትን ሰዎች [ከኢየሱስ መንግሥት እንዲለቅሙ]” የተመደቡ የተወሰኑ መላእክት ሳይኖሩ አይቀሩም። (ማቴ. 13:39-41) ሌሎች ደግሞ የተመደቡት “ለእሱ የተመረጡትን” ወደ ሰማይ እንዲሰበስቡ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 24:31) ‘በመንገዳችን ሁሉ እንዲጠብቁን’ የታዘዙም አሉ።—መዝ. 91:11፤ ማቴ. 18:10፤ ከማቴዎስ 4:11፤ ሉቃስ 22:43 ጋር አወዳድር።
በ1 ጢሞቴዎስ 5:21 ላይ የተጠቀሱት ‘የተመረጡ መላእክት’ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር በተያያዘ ልዩ ኃላፊነት የተሰጣቸው መላእክት ሳይሆኑ አይቀሩም። በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ስንመለከት፣ ጳውሎስ ሽማግሌዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ምክር ሰጥቷል፤ እንዲሁም ጉባኤው ሊያከብራቸው እንደሚገባ ተናግሯል። ሽማግሌዎች ኃላፊነታቸውን “መሠረተ ቢስ ከሆነ ጥላቻና ከአድልዎ በራቀ መንገድ” መወጣት እንዲሁም በችኮላ ውሳኔ ከማድረግ ወይም ከመፍረድ መቆጠብ አለባቸው። ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የሰጣቸውን ምክር በሥራ ላይ እንዲያውሉ የሚያነሳሳቸው አንዱ ወሳኝ ምክንያት ሥራቸውን የሚያከናውኑት “በአምላክ፣ በክርስቶስ ኢየሱስና በተመረጡት መላእክት ፊት” መሆኑን ማወቃቸው ነው። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው፣ አንዳንድ መላእክት ከጉባኤው ጋር የተያያዘ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፤ ይህም ጉባኤውን መጠበቅን፣ የስብከቱን ሥራ መምራትን እንዲሁም የተመለከቱትን ነገር ለይሖዋ ሪፖርት ማድረግን ይጨምራል።—ማቴ. 18:10፤ ራእይ 14:6