የጥናት ርዕስ 49
መዝሙር 147 የዘላለም ሕይወት ተስፋ ተሰጥቶናል
የዘላለም ሕይወት ማግኘት ትችላለህ—ግን እንዴት?
“ወልድን የሚያውቅና በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት [ይኖረዋል]።”—ዮሐ. 6:40
ዓላማ
ቅቡዓኑም ሆኑ ሌሎች በጎች ከክርስቶስ መሥዋዕት ጥቅም የሚያገኙት እንዴት ነው?
1. አንዳንዶች ዘላለም ስለመኖር ምን ሊሰማቸው ይችላል?
ብዙ ሰዎች ጤናቸውን ለመጠበቅና ረጅም ዕድሜ ለመኖር ስለሚፈልጉ በሚበሉት ነገር ረገድ ይጠነቀቃሉ፤ እንዲሁም አዘውትረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። ቢሆንም ግን ለዘላለም እንኖራለን ብለው አይጠብቁም። ምክንያቱም ለዘላለም መኖር የሚቻል ነገር እንደሆነ አይሰማቸውም፤ እንዲሁም ከእርጅና ጋር ተያይዘው ከሚመጡት ችግሮች አንጻር ለዘላለም ለመኖር ላይመኙ ይችላሉ። ኢየሱስ ግን በዮሐንስ 3:16 እና 5:24 ላይ “የዘላለም ሕይወት” ማግኘት የሚቻልና አስደሳች ነገር እንደሆነ ተናግሯል።
2. ዮሐንስ ምዕራፍ 6 ስለ ዘላለም ሕይወት ምን ይነግረናል? (ዮሐንስ 6:39, 40)
2 ኢየሱስ በአንድ ወቅት ተአምራዊ በሆነ መንገድ ዓሣና ዳቦ በማቅረብ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግቧል። a ይህ በጣም አስገራሚ ቢሆንም ኢየሱስ በማግስቱ የተናገረው ነገር ይበልጥ አስደናቂ ነው። በገሊላ ባሕር አቅራቢያ ወደምትገኘው ወደ ቅፍርናሆም ተከትሎት ለመጣው ሕዝብ፣ ሰዎች ከሞት መነሳት እንዲሁም ለዘላለም መኖር እንደሚችሉ ተናግሯል። (ዮሐንስ 6:39, 40ን አንብብ።) እስቲ በሞት ስላጣሃቸው ወዳጅ ዘመዶችህ ለማሰብ ሞክር። ኢየሱስ የተናገረው ነገር በሞት ያንቀላፉ ብዙዎች ከሞት እንደሚነሱ እንዲሁም አንተም ሆንክ ወዳጅ ዘመዶችህ አንድ ላይ ለዘላለም መኖር እንደምትችሉ ያሳያል። ነገር ግን ኢየሱስ በዮሐንስ ምዕራፍ 6 ላይ ቀጥሎ የተናገረው ነገር ለብዙዎች ለመረዳት ከባድ ሆኖባቸዋል። እስቲ ኢየሱስ የተናገረውን ነገር በጥልቀት እንመርምር።
3. በዮሐንስ 6:51 መሠረት ኢየሱስ ስለ ራሱ ምን ብሏል?
3 በቅፍርናሆም ተሰብስበው የነበሩት ሰዎች ኢየሱስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ሲመግባቸው በጥንት ዘመን ይሖዋ አባቶቻቸውን መና በመስጠት እንደመገባቸው አስታውሰው ሊሆን ይችላል። እንዲሁም ቅዱሳን መጻሕፍት መናን ‘ከሰማይ የወረደ ምግብ’ ብለው እንደሚጠሩት ያውቃሉ። (መዝ. 105:40፤ ዮሐ. 6:31) ኢየሱስ መናን ቀጥሎ ለሚያስተምረው ትምህርት እንደ መነሻ አድርጎ ተጠቅሞበታል። ምንም እንኳ መና የአምላክ ተአምራዊ ዝግጅት ቢሆንም የበሉት ሰዎች ውሎ አድሮ መሞታቸው አልቀረም። (ዮሐ. 6:49) ኢየሱስ ግን ራሱን ‘ከሰማይ የመጣ እውነተኛ ምግብ’፣ “አምላክ የሚሰጠው ምግብ” እና “ሕይወት የሚያስገኘው ምግብ” በማለት ጠርቷል። (ዮሐ. 6:32, 33, 35) ኢየሱስ በእሱና በመናው መካከል ያለውን ቁልፍ ልዩነት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ከሰማይ የወረደው ሕያው ምግብ እኔ ነኝ። ከዚህ ምግብ የሚበላ ሁሉ ለዘላለም ይኖራል።” (ዮሐንስ 6:51ን አንብብ።) ያዳምጡት የነበሩት አይሁዳውያን ይህን ሲሰሙ በጣም ግራ ተጋቡ። ኢየሱስ ራሱን አምላክ ለአባቶቻቸው በተአምር ከሰጠው መና የሚበልጥ ከሰማይ የወረደ “ምግብ” አድርጎ እንዴት ሊገልጽ ይችላል? ኢየሱስ “ምግቡ ደግሞ . . . የምሰጠው ሥጋዬ ነው” በማለት ትኩረት የሚስብ ፍንጭ ሰጥቷል። ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቃችን አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም መልሱ እኛም ሆንን ወዳጅ ዘመዶቻችን የዘላለም ሕይወት የምናገኝበትን መንገድ ይጠቁማል። እስቲ ኢየሱስ ምን ለማለት እንደፈለገ እንመልከት።
ኢየሱስ ስለ ሕያው ምግብና ስለ ሥጋው ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?
4. አንዳንዶች ኢየሱስ የተናገረው ነገር ያስደነገጣቸው ለምንድን ነው?
4 ኢየሱስን ያዳምጡት ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ‘ሥጋውን ለዓለም ሕይወት ሲል እንደሚሰጥ’ ሲናገር በጣም ደንግጠው ነበር። ኢየሱስ ቃል በቃል ሥጋውን እንዲበሉ እየነገራቸው እንደሆነ ተሰምቷቸው ይሆን? (ዮሐ. 6:52) ኢየሱስ ቀጥሎ የተናገረውን ሌላ አስደንጋጭ ነገርም ልብ በል፦ “የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁና ደሙን ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።”—ዮሐ. 6:53
5. ኢየሱስ ሰዎቹ ቃል በቃል ደሙን መጠጣት እንዳለባቸው እየተናገረ እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን?
5 በኖኅ ዘመን አምላክ፣ ሰዎች ደም እንዳይበሉ ከልክሎ ነበር። (ዘፍ. 9:3, 4) ይሖዋ ይህንኑ ትእዛዝ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ውስጥም አካቶታል። ሕጉ፣ ደም የሚበላ ማንኛውም ሰው “ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ” ይላል። (ዘሌ. 7:27) ኢየሱስም ይህን ሕግ ያከብራል። (ማቴ. 5:17-19) ስለዚህ ኢየሱስ፣ ሕዝቡ ቃል በቃል ሥጋውን እንዲበሉ ወይም ደሙን እንዲጠጡ ይነግራቸዋል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ያም ቢሆን ኢየሱስ ይህን እንግዳ ሐሳብ የተናገረው ሰዎቹ “የዘላለም ሕይወት” የሚያገኙት እንዴት እንደሆነ ሊያስተምራቸው ስለፈለገ ነው።—ዮሐ. 6:54
6. ኢየሱስ ሥጋውን ስለመብላትና ደሙን ስለመጠጣት የተናገረውን ሐሳብ እንዴት ልንረዳው ይገባል?
6 ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? ኢየሱስ በምሳሌያዊ ሁኔታ እየተናገረ እንደነበር ግልጽ ነው። ከዚያ ቀደምም ሳምራዊቷን ሴት ባነጋገረበት ወቅት ምሳሌያዊ አገላለጽ ተጠቅሟል። እንዲህ ብሏታል፦ “እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ፈጽሞ አይጠማም፤ ከዚህ ይልቅ እኔ የምሰጠው ውኃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ የውኃ ምንጭ ይሆናል።” (ዮሐ. 4:7, 14) b ኢየሱስ ሳምራዊቷ ሴት ከሆነ ምንጭ የፈለቀ ውኃ በመጠጣት ብቻ የዘላለም ሕይወት እንደምታገኝ መናገሩ እንዳልነበር ግልጽ ነው። በተመሳሳይም በቅፍርናሆም ያነጋገራቸው ሰዎች ቃል በቃል ሥጋውን ቢበሉና ደሙን ቢጠጡ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ መናገሩ አልነበረም።
በሁለቱ ሐሳቦች መካከል ያለው ልዩነት
7. አንዳንዶች በዮሐንስ 6:53 ላይ ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ምን እንደሚያመለክት ይሰማቸዋል?
7 አንዳንድ ሃይማኖተኛ ሰዎች ኢየሱስ በዮሐንስ 6:53 ላይ ሥጋውን ስለመብላትና ደሙን ስለመጠጣት የተናገረው ሐሳብ በጌታ ራት ወቅት መከናወን ያለበትን ነገር እንደሚያመለክት ይናገራሉ። ይህን የሚሉት፣ ኢየሱስ በጌታ ራት ላይ ተቀራራቢ አገላለጽ ስለተጠቀመ ነው። (ማቴ. 26:26-28) በዚህም የተነሳ በጌታ ራት ላይ የሚገኙት ሰዎች በሙሉ በተሰብሳቢዎቹ ፊት ከሚዞረው ቂጣና የወይን ጠጅ መካፈል እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። ይህ ሐሳብ ትክክል ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ ያስፈልገናል። ምክንያቱም በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አብረውን በጌታ ራት ላይ ይገኛሉ። በዮሐንስ 6:53 ላይ በሚገኘው ሐሳብና ኢየሱስ በጌታ ራት ላይ በተናገረው ሐሳብ መካከል ያሉትን ልዩነቶች እስቲ እንመልከት።
8. በሁለቱ ወቅቶች መካከል ያሉት አንዳንድ ልዩነቶች የትኞቹ ናቸው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
8 በሁለቱ ወቅቶች መካከል ያሉትን ሁለት ልዩነቶች እንመልከት። በመጀመሪያ ኢየሱስ በዮሐንስ 6: ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የተናገረው መቼና የት ነው? ይህን ያደረገው በ32 ዓ.ም. በገሊላ ለተሰበሰቡ አይሁዳውያን ነው። ይህ የሆነው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም የጌታ ራት በዓልን ከማቋቋሙ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ነው። ሁለተኛ ኢየሱስ እነዚህን ሐሳቦች የተናገረው ለእነማን ነው? በገሊላ ካነጋገራቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በዋነኝነት ያሳሰባቸው ከመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ይልቅ ሥጋዊ ፍላጎታቸውን የማርካታቸው ጉዳይ ነበር። ( 53-56ዮሐ. 6:26) እንዲያውም ኢየሱስ የተናገረውን ነገር መረዳት በከበዳቸው ጊዜ ወዲያውኑ በእሱ ላይ ያላቸውን እምነት አጥተዋል። ከደቀ መዛሙርቱ መካከል እንኳ አንዳንዶቹ እሱን መከተላቸውን አቁመዋል። (ዮሐ. 6:14, 36, 42, 60, 64, 66) ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ማለትም በ33 ዓ.ም. ኢየሱስ የጌታ ራትን ባቋቋመበት ወቅት የነበሩት ሰዎች ግን ከእነዚህ ፈጽሞ የተለዩ ነበሩ። በዚያ ወቅት አብረውት የነበሩት 11 ታማኝ ሐዋርያቱ ናቸው። እነሱም ኢየሱስ ያስተማረው ነገር ሁሉ ገብቷቸዋል ማለት አይደለም። ያም ቢሆን በገሊላ ከነበሩት ከአብዛኞቹ ሰዎች በተለየ መልኩ ታማኝ ሐዋርያቱ ኢየሱስ ከሰማይ የወረደው የአምላክ ልጅ እንደሆነ እርግጠኞች ነበሩ። (ማቴ. 16:16) ኢየሱስም “እናንተ በፈተናዎቼ ከጎኔ ሳትለዩ ቆይታችኋል” በማለት አመስግኗቸዋል። (ሉቃስ 22:28) እነዚህ ሁለት ልዩነቶች ብቻ እንኳ ኢየሱስ በዮሐንስ 6:53 ላይ የተናገረው ሐሳብ በጌታ ራት ወቅት መከናወን ያለበትን ነገር የሚያመለክት እንዳልሆነ ያሳያሉ። ሆኖም ሌሎች ማስረጃዎችም አሉ።
ጉዳዩ አንተንም ይመለከታል
9. ኢየሱስ በጌታ ራት ላይ የተናገረው ሐሳብ የሚመለከተው የትኛውን ቡድን ነው?
9 በጌታ ራት ወቅት ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ቂጣ ከሰጣቸው በኋላ ሥጋውን እንደሚያመለክት ነገራቸው። ከዚያም የወይን ጠጁን ሰጣቸውና ‘የቃል ኪዳን ደሙን’ እንደሚያመለክት ተናገረ። (ማር. 14:22-25፤ ሉቃስ 22:20፤ 1 ቆሮ. 11:24) ይህ ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ነው። አዲሱ ቃል ኪዳን የተገባው ከሁሉም የሰው ልጆች ጋር ሳይሆን በአምላክ መንግሥት ውስጥ ቦታ ከሚኖራቸው “[ከመንፈሳዊ] እስራኤል ቤት ጋር” ነው። (ዕብ. 8:6, 10፤ 9:15) ሐዋርያቱ በወቅቱ ባይገነዘቡትም ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተው የአዲሱ ቃል ኪዳን ክፍል ይሆናሉ፤ እንዲሁም ከኢየሱስ ጋር በሰማይ ቦታ ይኖራቸዋል።—ዮሐ. 14:2, 3
10. በቅፍርናሆም በነበረው ሁኔታና በጌታ ራት ወቅት በነበረው ሁኔታ መካከል ያለው ሌላው ልዩነት ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
10 ኢየሱስ በጌታ ራት ላይ ትኩረት ያደረገው ‘በትንሹ መንጋ’ ላይ እንደሆነ ልብ በል። የዚህ አነስተኛ ቡድን የመጀመሪያ አባላት እዚያ ክፍል ውስጥ ከኢየሱስ ጋር አብረው የነበሩት ታማኝ ሐዋርያቱ ናቸው። (ሉቃስ 12:32) እነሱም ሆኑ ወደፊት በዚያ ቡድን ውስጥ የሚካተቱ ሰዎች ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈል ይኖርባቸዋል። ከኢየሱስ ጋር አብረው እንዲሆኑ በሰማይ ቦታ የሚያገኙት እነሱ ናቸው። በገሊላ ከነበረው ሁኔታ በተለየ መልኩ ኢየሱስ በዚህ ወቅት የተናገረው ሐሳብ የሚመለከተው ጥቂት ሰዎችን ብቻ ነው። በገሊላ የተናገረው ሐሳብ ግን ብዙ ሰዎችን ይመለከታል።
11. ኢየሱስ በገሊላ የተናገረው ሐሳብ የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ የሚመለከት እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን?
11 ኢየሱስ በ32 ዓ.ም. በገሊላ ያነጋገራቸው አብዛኞቹ ሰዎች በዋነኝነት የፈለጉት ምግብ ማግኘት ነበር። ይሁንና ምግብ ከመብላት የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ይኸውም የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ ዝግጅት እንዳለ ነገራቸው። በተጨማሪም ኢየሱስ የሞቱ ሰዎች በመጨረሻው ቀን እንደሚነሱና ለዘላለም እንደሚኖሩ ተናግሯል። በጌታ ራት ላይ ካደረገው በተለየ መልኩ ኢየሱስ በዚህ ወቅት የተናገረው ስለተመረጡ ጥቂት ሰዎች ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ያተኮረው ሁሉም ሰዎች ማግኘት በሚችሉት በረከት ላይ ነው። እንዲያውም እንዲህ ብሏል፦ “ከዚህ ምግብ የሚበላ ሁሉ ለዘላለም ይኖራል፤ ምግቡ ደግሞ ለዓለም ሕይወት ስል የምሰጠው ሥጋዬ ነው።”—ዮሐ. 6:51
12. ኢየሱስ የተናገረውን በረከት ለማግኘት ምን ያስፈልጋል?
12 ኢየሱስ በገሊላ ከተሰበሰቡት አይሁዳውያን ጋር በተነጋገረበት ወቅት ይህን በረከት የሚያገኘው በምድር ላይ የኖረ ሰው ሁሉ እንደሆነ አልተናገረም። ይህን በረከት የሚያገኙት ‘ከዚህ ምግብ የሚበሉ’ ማለትም በእሱ የሚያምኑ ሰዎች ብቻ ናቸው። ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች ለመዳን የሚጠበቅባቸው በኢየሱስ “ማመን” እንዲሁም እሱን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው መቀበል ብቻ እንደሆነ ይሰማቸዋል። (ዮሐ. 6:29) ይሁንና በገሊላ ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ መጀመሪያ በኢየሱስ ቢያምኑም እንኳ በኋላ ትተውት ሄደዋል። ለምን?
13. የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዝሙር ለመሆን ምን ያስፈልጋል?
13 ኢየሱስ ከመገባቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ፣ የሚፈልጉትን ነገር እስከሰጣቸው ድረስ እሱን በደስታ ለመከተል ዝግጁ ነበሩ። የሚፈልጉት ተአምራዊ ፈውስ ማግኘት፣ በነፃ ምግብ መብላት እንዲሁም የሚጥማቸውን ትምህርት መስማት ነበር። ይሁንና ኢየሱስ የእሱ እውነተኛ ደቀ መዝሙር መሆን ከዚህ ያለፈ ነገር እንደሚጠይቅ ተናግሯል። ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ዋነኛ ምክንያት የሰዎችን አካላዊ ፍላጎት ለማሟላት አልነበረም። ሰዎች እሱ ያስተማረውን ነገር በሙሉ በመቀበልና በመታዘዝ ‘ወደ እሱ መምጣት’ ይጠበቅባቸዋል።—ዮሐ. 5:40፤ 6:44
14. ከኢየሱስ ሥጋና ደም ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ ያስፈልገናል?
14 ኢየሱስ ሕዝቡ እምነት ማሳደር እንደሚያስፈልጋቸው ጎላ አድርጎ ገልጿል። ይሁንና እምነት ማሳደር ያለባቸው በምን ላይ ነው? ከጊዜ በኋላ መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው ሥጋው እና ደሙ ባለው የመዋጀት ኃይል ላይ ነው። እነዚያ አይሁዳውያን በዚህ ላይ እምነት ማሳደር ያስፈልጋቸው ነበር፤ እኛም እንዲህ ያለው እምነት በጣም ያስፈልገናል። (ዮሐ. 6:40) አዎ፣ በዮሐንስ 6:53 ላይ እንደተገለጸው ከኢየሱስ ሥጋና ደም ጥቅም ማግኘት ከፈለግን በቤዛው ማመን ያስፈልገናል። ይህ በረከት የተዘረጋው ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ሰዎች ነው።—ኤፌ. 1:7
15-16. ከዮሐንስ ምዕራፍ 6 የትኞቹን ትምህርቶች አግኝተናል?
15 በዮሐንስ ምዕራፍ 6 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ለእኛም ሆነ ለወዳጅ ዘመዶቻችን ትልቅ ትርጉም አለው። ይህ ዘገባ ኢየሱስ ለሰዎች ያለውን አሳቢነት በግልጽ ያሳያል። በገሊላ በነበረበት ወቅት የታመሙትን ፈውሷል፤ ስለ መንግሥቱ አስተምሯል፤ እንዲሁም ለሰዎቹ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ሰጥቷቸዋል። (ሉቃስ 9:11፤ ዮሐ. 6:2, 11, 12) በዋነኝነት ደግሞ “ሕይወት የሚያስገኘው ምግብ” እሱ እንደሆነ አስተምሯቸዋል።—ዮሐ. 6:35, 48
16 “ሌሎች በጎች” በማለት የጠራቸው ሰዎች በዓመታዊው የጌታ ራት ወቅት ከቂጣውና ከወይን ጠጁ አይካፈሉም፤ መካፈልም የለባቸውም። (ዮሐ. 10:16) ያም ቢሆን ከኢየሱስ ሥጋና ደም ጥቅም ያገኛሉ። ይህን የሚያደርጉት እሱ ያቀረበው መሥዋዕት ባለው የመዋጀት ኃይል ላይ እምነት በማሳደር ነው። (ዮሐ. 6:53) በአንጻሩ ግን፣ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈሉት ሰዎች የአዲሱ ቃል ኪዳን ክፍል እንደሆኑና የሰማያዊው መንግሥት ወራሾች ለመሆን እንደተመረጡ ያሳያሉ። ከዚህ እንደምንረዳው፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆንን የሌሎች በጎች ክፍል በዮሐንስ ምዕራፍ 6 ላይ የሚገኘው ዘገባ ለሁላችንም ትልቅ ትርጉም አለው። እምነት ማሳየት ያለውን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ያሳየናል። ምክንያቱም የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን የተመካው በዚህ ላይ ነው።
መዝሙር 150 ትድኑ ዘንድ አምላክን ፈልጉ
a በዮሐንስ 6:5-35 ላይ ያለው ሐሳብ ባለፈው ርዕስ ላይ ተብራርቷል።
b ኢየሱስ የጠቀሰው ውኃ፣ ይሖዋ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ሲል ያደረጋቸውን ዝግጅቶች ያመለክታል።