በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 51

መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን

ይሖዋ እንባህን ይመለከታል

ይሖዋ እንባህን ይመለከታል

“እንባዬን በአቁማዳህ አጠራቅም። ደግሞስ በመጽሐፍህ ውስጥ ሰፍሮ የለም?”መዝ. 56:8

ዓላማ

ይሖዋ የሚደርስብንን የስሜት ሥቃይ ሙሉ በሙሉ ይረዳል፤ እንዲሁም የሚያስፈልገንን ማጽናኛ ይሰጠናል።

1-2. እንድናነባ የሚያደርጉን የትኞቹ ሁኔታዎች ሊሆኑ ይችላሉ?

 ሁላችንም በተለያዩ ጊዜያት አንብተን እናውቃለን። በጣም የሚያስደስት ነገር ሲያጋጥመን የደስታ እንባ እናነባ ይሆናል። ልዩ ስሜት የሚያሳድር ሁኔታ ሲያጋጥምህ ለምሳሌ ልጅህ ሲወለድ፣ ያሳለፍከውን አስደሳች ጊዜ ስታስታውስ ወይም ለበርካታ ዓመታት ያላገኘኸውን ጓደኛህን ስታገኝ በደስታ አልቅሰህ ሊሆን ይችላል።

2 ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ የምናለቅሰው በሐዘን የተነሳ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ስሜታችንን በጥልቅ ሲጎዳው ልናለቅስ እንችላለን። ባደረብን ሕመም የተነሳ የማያባራ ሥቃይ ሲሰማን ወይም የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ ማልቀሳችን አይቀርም። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ነቢዩ ኤርምያስ ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን እጅ በወደቀችበት ጊዜ የተሰማው ዓይነት ስሜት ሊሰማን ይችላል። ኤርምያስ እንዲህ ብሏል፦ “ዓይኔ የእንባ ጎርፍ አፈሰሰ። ዓይኖቼ ያለማቋረጥና ያለእረፍት ያነባሉ።”—ሰቆ. 3:48, 49

3. ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚደርስባቸውን መከራ ሲመለከት ምን ይሰማዋል? (ኢሳይያስ 63:9)

3 ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ የሐዘን እንባ ያነባንበትን እያንዳንዱን ጊዜ ያውቃል። ይሖዋ አገልጋዮቹ ያጋጠማቸውን ማንኛውንም አስጨናቂ ሁኔታ በደንብ እንደሚያውቅ እንዲሁም እርዳታ ለማግኘት ወደ እሱ ሲጮኹ እንደሚሰማቸው መጽሐፍ ቅዱስ ዋስትና ይሰጠናል። (መዝ. 34:15) ሆኖም ይሖዋ እኛን በማየትና በመስማት ብቻ አይወሰንም። ልክ እንደ አፍቃሪ ወላጅ፣ ልጆቹ ሲያለቅሱ ሲመለከት ስሜቱ በጥልቅ ይነካል፤ ሊረዳንም ይፈልጋል።—ኢሳይያስ 63:9ን አንብብ።

4. የይሖዋን አስተሳሰብ በተመለከተ ከአንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ታሪክ ምን እንማራለን?

4 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ የአገልጋዮቹን እንባ ሲመለከት ምን እርምጃ እንደወሰደ ይነግረናል። የሐናን፣ የዳዊትንና የንጉሥ ሕዝቅያስን ታሪክ በመመርመር ይህን መረዳት እንችላለን። እነዚህ ሰዎች እንዲያለቅሱ ያደረጋቸው ምንድን ነው? እርዳታ ለማግኘት ወደ እሱ ሲጮኹ ይሖዋ የመለሰላቸው እንዴት ነው? እኛስ ባጋጠመን ሐዘን፣ ክህደት ወይም ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ የተነሳ ስናለቅስ የእነሱ ምሳሌ የሚያጽናናን እንዴት ነው?

ሐዘን ደርሶብን ስናነባ

5. ሐና ባጋጠማት ችግር የተነሳ ምን ተሰምቷት ነበር?

5 ሐና ባጋጠሟት የተለያዩ ችግሮች የተነሳ የሐዘን እንባ አንብታለች። ባሏ፣ ፍናና የተባለች ሌላ ሚስት የነበረው ሲሆን እሷም ሐናን ትጠላት ነበር። ይህ እንዳይበቃ ደግሞ ሐና ልጅ አልነበራትም፤ ፍናና ግን ብዙ ልጆች ነበሯት። (1 ሳሙ. 1:1, 2) ሐና መሃን በመሆኗ ፍናና ሁልጊዜ ትሳለቅባት ነበር። እኛ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ምን ይሰማን ነበር? ሐና “እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ” በሐዘን ተውጣና “በጣም ተማርራ ነበር።”—1 ሳሙ. 1:6, 7, 10

6. ሐና ማጽናኛ ለማግኘት ምን አደረገች?

6 ሐና መጽናናት የቻለችው እንዴት ነው? የረዳት አንዱ ነገር፣ የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል ወደሆነው ወደ ማደሪያ ድንኳኑ መሄዷ ነው። እዚያም በማደሪያ ድንኳኑ መግቢያ አካባቢ ቆማ ሳይሆን አይቀርም “ስቅስቅ [ብላ] እያለቀሰች ወደ ይሖዋ ትጸልይ ጀመር።” “አገልጋይህ እየደረሰባት ያለውን መከራ ተመልክተህ [አስበኝ]” በማለት ይሖዋን ለመነችው። (1 ሳሙ. 1:10, 11) ሐና የልቧን አውጥታ ለይሖዋ በጸሎት ነግራዋለች። ይሖዋ ይህች ውድ ልጁ ስታለቅስ ሲመለከት ምንኛ አዝኖ ይሆን!

7. ሐና የልቧን አውጥታ ወደ ይሖዋ ከጸለየች በኋላ ምን ተሰማት?

7 ሐና የልቧን አውጥታ ወደ ይሖዋ ከጸለየችና ሊቀ ካህናቱ ኤሊ፣ ይሖዋ ጸሎቷን እንደሚመልስላት ዋስትና ከሰጣት በኋላ ምን ተሰማት? ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ከዚያም ተነስታ ሄደች፤ ምግብም በላች፤ ዳግመኛም በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።” (1 ሳሙ. 1:17, 18) ያለችበት አስጨናቂ ሁኔታ ገና ባይቀየርም ሐና ተጽናንታለች። እንደ ሸክም የከበዳትን ጉዳይ በይሖዋ ላይ ጥላዋለች። ይሖዋም ጭንቀቷን ተመልክቷል፤ ለቅሶዋን አዳምጧል፤ በኋላም እንድትጸንስ በማድረግ ባርኳታል።—1 ሳሙ. 1:19, 20፤ 2:21

8-9. በዕብራውያን 10:24, 25 መሠረት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

8 የምናገኘው ትምህርት። ባጋጠመህ አሳዛኝ ሁኔታ የተነሳ እያለቀስክ ነው? የቤተሰብህን አባል ወይም ጓደኛህን በሞት በማጣትህ የተነሳ በሐዘን ተውጠህ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ብቻችንን ለመሆን መፈለጋችን የሚጠበቅ ነገር ነው። ሆኖም ሐና ወደ ማደሪያ ድንኳኑ በመሄድ ማጽናኛና ማበረታቻ እንዳገኘች ሁሉ አንተም ጥሩ ስሜት ባይሰማህም እንኳ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ማጽናኛ ማግኘት ትችላለህ። (ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።) ይሖዋ በስብሰባዎች ላይ በምንሰማቸው የሚያጽናኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አማካኝነት አፍራሽ ሐሳቦችን በአዎንታዊ ሐሳቦች ለመተካት ሊረዳን ይችላል። ይህም ያለንበት ሁኔታ ወዲያውኑ ባይሻሻልም እንኳ ስሜታችንን ለመቆጣጠር ይረዳናል።

9 ከዚህም ሌላ፣ በስብሰባዎቻችን ላይ ሩኅሩኅ ከሆኑ የእምነት አጋሮቻችን ጋር አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ እንችላለን። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንደሚወዱንና እንደሚያስቡልን ሲነግሩን እንጽናናለን። (1 ተሰ. 5:11, 14) ባለቤቱን በሞት ያጣ አንድ ልዩ አቅኚ ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “አሁንም አለቅሳለሁ። ብቻዬን ጥጌን ይዤ ተቀምጬ የማለቅስበት ጊዜ አለ። ሆኖም ስብሰባዎቻችን የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል። ወንድሞቼና እህቶቼ የሚናገሯቸው ማራኪ ቃላት በጣም ያጽናኑኛል። ስብሰባ ከመሄዴ በፊት ምንም ያህል በጭንቀት ብዋጥ እዚያ ከደረስኩ በኋላ ሁሌም እበረታታለሁ።” በስብሰባዎቻችን ላይ ስንገኝ ይሖዋ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ተጠቅሞ ይረዳናል።

ከእምነት አጋሮቻችን ማጽናኛ ማግኘት እንችላለን (አንቀጽ 8-9⁠ን ተመልከት)


10. በሐዘን በምንዋጥበት ጊዜ የሐናን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

10 ሐና የልቧን አውጥታ ወደ ይሖዋ መጸለይዋም አጽናንቷታል። አንተም ይሖዋ እንደሚሰማህ በመተማመን ‘የሚያስጨንቅህን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ መጣል’ ትችላለህ። (1 ጴጥ. 5:7) ባለቤቷ በዘራፊዎች የተገደለባት አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ልቤ በጣም ከመሰበሩ የተነሳ መቼም የማገግም አልመሰለኝም ነበር። ሆኖም ወደሚወደኝ አባቴ ወደ ይሖዋ መጸለዬ አጽናንቶኛል። ምን ብዬ መጸለይ እንዳለብኝ ግራ በምጋባበት ጊዜም ጭምር እሱ ስሜቴን ተረድቶልኛል። በከባድ ሐዘን በምዋጥበት ጊዜ ሰላም እንዲሰጠኝ እጸልይ ነበር። በዚህ ጊዜ ልቤና አእምሮዬ ሲረጋጋ ይሰማኛል፤ ወደፊት ለመግፋት የሚያስችል ብርታትም አገኛለሁ።” እንባህን እያፈሰስክ የልብህን አውጥተህ ለይሖዋ ስትነግረው ስሜቱ በጥልቅ ይነካል፤ የልብህን ሥቃይም ይረዳልሃል። የጭንቀትህ መንስኤ ባይወገድም እንኳ ይሖዋ የተጨነቀውን ልብህን ሊያረጋጋልህና በተወሰነ መጠን ሰላም እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል። (መዝ. 94:19፤ ፊልጵ. 4:6, 7) በታማኝነት በመጽናትህም ይባርክሃል።—ዕብ. 11:6

ክህደት ተፈጽሞብን ስናነባ

11. ዳዊት ባጋጠሙት መከራዎች የተነሳ ምን ተሰምቶታል?

11 ዳዊት በሕይወት ዘመኑ ውስጥ እንዲያለቅስ የሚያደርጉ ብዙ መከራዎች አጋጥመውታል። የሚጠሉት ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ያምናቸው የነበሩ አንዳንድ ሰዎችም እንኳ ከድተውታል። (1 ሳሙ. 19:10, 11፤ 2 ሳሙ. 15:10-14, 30) በአንድ ወቅት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከመቃተቴ የተነሳ ዝያለሁ፤ ሌሊቱን ሙሉ መኝታዬን በእንባ አርሳለሁ፤ በለቅሶ አልጋዬን አጥለቀልቃለሁ።” ዳዊት እንዲህ የተሰማው ለምንድን ነው? ምክንያቱን ሲገልጽ “ከሚያጠቁኝ ሰዎች ሁሉ የተነሳ” ብሏል። (መዝ. 6:6, 7) ዳዊት ሌሎች የፈጸሙበት በደል በጣም ስላሳዘነው እንባውን መቆጣጠር ተስኖት ነበር።

12. መዝሙር 56:8 እንደሚገልጸው ዳዊት ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር?

12 ዳዊት ብዙ ችግሮች ቢያጋጥሙትም ይሖዋ እንደሚወደው እርግጠኛ ነበር። “ይሖዋ የለቅሶዬን ድምፅ ይሰማል” ሲል ጽፏል። (መዝ. 6:8) በሌላ ወቅት ደግሞ ዳዊት በመዝሙር 56:8 ላይ የሚገኘውን ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ጽፏል። (ጥቅሱን አንብብ።) እነዚህ ቃላት የይሖዋን ርኅራኄ ግሩም አድርገው ይገልጻሉ። ዳዊት፣ ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ እንባውን በአቁማዳ እንደሚያጠራቅም ወይም በመጽሐፍ ላይ እንደሚያሰፍረው ተሰምቶት ነበር። ዳዊት፣ ይሖዋ ሥቃዩን ልብ እንደሚልና እንደሚያስታውስ እርግጠኛ ነበር። ዳዊት የሚወደው አባቱ፣ ያሳለፈውን መከራ ብቻ ሳይሆን መከራው ያሳደረበትን ስሜትም ጭምር እንደሚያውቅ ተማምኗል።

13. ሰዎች ስሜታችንን ሲጎዱት ምን ማስታወሳችን ሊያጽናናን ይችላል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

13 የምናገኘው ትምህርት። አንድ ሰው እንደጠበቅከው ሆኖ ስላልተገኘ ወይም የምታምነው ሰው ስለከዳህ ስሜትህ ተጎድቷል? በትዳር አጋርህ ወይም በፍቅር ጓደኛህ በመከዳትህ አሊያም ደግሞ አንድ የምትወደው ሰው ይሖዋን ማገልገሉን በማቆሙ ልብህ ተሰብሮ ሊሆን ይችላል። አንድ ወንድም፣ ሚስቱ ምንዝር ፈጽማ ትታው በሄደችበት ወቅት ምን እንደተሰማው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በጣም ደነገጥኩ፤ ሁኔታውን ማመን አቃተኝ። ምንም እንደማልረባ ተሰማኝ፤ በሐዘንና በብስጭት ተዋጥኩ።” አንተም አንድ ሰው ቢከዳህ ወይም እንደጠበቅከው ሆኖ ባይገኝ ይሖዋ መቼም ቢሆን እንደማይተውህ አትዘንጋ። ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች ታማኝነት ሊያጓድሉ ቢችሉም ይሖዋ ዓለታችን እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ከጎናችን አይለይም። ታማኝ አገልጋዮቹን አይተዋቸውም።” (መዝ. 37:28) ከዚህም ሌላ የይሖዋ ፍቅር ከየትኛውም ሰው ፍቅር እንደሚበልጥ አስታውስ። ክህደት ከባድ የስሜት ሥቃይ ሊያስከትል ቢችልም ይሖዋ ለአንተ ያለውን አመለካከት አይቀይረውም። (ሮም 8:38, 39) ይህን ምንጊዜም አስታውስ፦ ሰዎች ምንም ቢያደርጉ የሰማዩ አባትህ ይወድሃል።

የመዝሙር መጽሐፍ ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ሰዎች ቅርብ እንደሆነ ዋስትና ይሰጠናል (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)


14. መዝሙር 34:18 ምን ዋስትና ይሰጠናል?

14 ክህደት ሲፈጸምብን ዳዊት በመዝሙር 34:18 ላይ የተናገራቸውን የሚያበረታቱ ቃላት ማስታወሳችንም ሊያጽናናን ይችላል። (ጥቅሱን አንብብ።) አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው “መንፈሳቸው የተደቆሰባቸው” የሚለው አገላለጽ “የወደፊቱ ጊዜ የጨለመባቸው” የሚል መልእክት ሊያስተላልፍ ይችላል። ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ስሜት የሚሰማቸውን ሰዎች የሚረዳቸው እንዴት ነው? በጭንቀት የተዋጠ ልጁን አቅፎ እንደሚያባብል ወላጅ፣ ይሖዋም ለእኛ “ቅርብ ነው።” እጅግ ይራራልናል፤ እንዲሁም በተፈጸመብን ክህደት የተነሳ መንፈሳችን ሲደቆስ ሊረዳን ምንጊዜም ዝግጁ ነው። የተሰበረውን ልባችንንና የተደቆሰውን መንፈሳችንን ለመጠገን ይጓጓል። በተጨማሪም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ግሩም ተስፋዎችን ሰጥቶናል፤ እነዚህ ተስፋዎች በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ለመቋቋም ይረዱናል።—ኢሳ. 65:17

ተስፋ ቆርጠን ስናነባ

15. ሕዝቅያስ እንዲያለቅስ ያደረገው የትኛው ሁኔታ ነው?

15 የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ የ39 ዓመት ጎልማሳ ሳለ የማይድን በሽታ እንዳለበት አወቀ። ይሖዋ፣ ሕዝቅያስ በሕመሙ የተነሳ እንደሚሞት በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት ነገረው። (2 ነገ. 20:1) ሕዝቅያስ ምንም ተስፋ ያለው አይመስልም ነበር። ይህን ዜና ሲሰማ ቅስሙ በጣም ስለተሰበረ ምርር ብሎ አለቀሰ። ወደ ይሖዋም አጥብቆ ጸለየ።—2 ነገ. 20:2, 3

16. ይሖዋ፣ ሕዝቅያስ በእንባ ላቀረበው ልመና ምን ምላሽ ሰጠ?

16 ይሖዋ፣ ሕዝቅያስ በእንባ ያቀረበውን ልመና ሲሰማ በጣም ስላዘነለት እንዲህ አለው፦ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ። እንባህንም አይቻለሁ። ስለሆነም እፈውስሃለሁ።” ይሖዋ የሕዝቅያስን ዕድሜ እንደሚያረዝምለት እንዲሁም ኢየሩሳሌምን ከአሦራውያን እጅ እንደሚታደጋት በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት ቃል በመግባት ምሕረት አሳየው።—2 ነገ. 20:4-6

17. ከባድ የጤና እክል ሲያጋጥመን ይሖዋ እንድንጸና የሚረዳን እንዴት ነው? (መዝሙር 41:3) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

17 የምናገኘው ትምህርት። ምንም መፍትሔ የሌለው የሚመስል የጤና ችግር አጋጥሞሃል? በእንባ ጭምር ወደ ይሖዋ ጸልይ። መጽሐፍ ቅዱስ “የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው” ይሖዋ በሚደርስብን መከራ ሁሉ እንደሚያጽናናን ዋስትና ይሰጠናል። (2 ቆሮ. 1:3, 4) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በሙሉ ያስወግድልናል ብለን ልንጠብቅ አንችልም። ሆኖም ለመጽናት እንደሚረዳን መተማመን እንችላለን። (መዝሙር 41:3ን አንብብ።) በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ሁኔታውን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ፣ ጥበብና ውስጣዊ ሰላም ይሰጠናል። (ምሳሌ 18:14፤ ፊልጵ. 4:13) በተጨማሪም ሁሉም በሽታዎች እንደሚወገዱ በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ አማካኝነት ያጽናናናል።—ኢሳ. 33:24

ይሖዋ ጥንካሬ፣ ጥበብና ውስጣዊ ሰላም በመስጠት ጸሎታችንን ይመልስልናል (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)


18. በጣም ከባድ ፈተና ሲያጋጥምህ የትኛው ጥቅስ ያጽናናሃል? (“ እንባችንን የሚያብሱልን አጽናኝ ጥቅሶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

18 ሕዝቅያስ ይሖዋ ከተናገረው ቃል ማጽናኛ አግኝቷል። እኛም ከአምላክ ቃል ማጽናኛ ማግኘት እንችላለን። ይሖዋ አስጨናቂ ሁኔታ ሲያጋጥመን የሚያጽናኑን ማራኪ ሐሳቦች በቃሉ ውስጥ እንዲቀመጡልን አድርጓል። (ሮም 15:4) በምዕራባዊ አፍሪካ የምትኖር አንዲት እህት በካንሰር በተያዘችበት ወቅት ብዙ ጊዜ ታለቅስ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “በጣም የሚያጽናናኝ ጥቅስ ኢሳይያስ 26:3 ነው። የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባንችልም ይህ ጥቅስ ይሖዋ ለፈተናዎቹ የምንሰጠውን ምላሽ ለመቆጣጠር የሚያስችል ውስጣዊ ሰላም እንደሚሰጠኝ ያረጋግጥልኛል።” አንተስ በጣም ከባድ ምናልባትም ተስፋ የሌለው የሚመስል ፈተና ሲያጋጥምህ የሚያጽናናህ ጥቅስ አለ?

19. ወደፊት ምን ተስፋ ይጠብቀናል?

19 የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት መጨረሻ ላይ እንደመሆኑ መጠን የሚያስለቅሱ ነገሮች እየጨመሩ እንደሚሄዱ እንጠብቃለን። ሆኖም ከሐና፣ ከዳዊትና ከንጉሥ ሕዝቅያስ ታሪክ እንደተማርነው ይሖዋ እንባችንን ያያል፤ እንዲሁም ስናለቅስ ሲመለከት ስሜቱ በጥልቅ ይነካል። እንባችንን ፈጽሞ በቸልታ አያልፍም። ስለዚህ አስጨናቂ ሁኔታ ሲያጋጥመን የልባችንን አውጥተን ወደ ይሖዋ መጸለይ ይኖርብናል። በጉባኤ ውስጥ ካሉት አፍቃሪ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ራሳችንን አናግልል። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት የሚያበረታቱ ሐሳቦች ማጽናኛ ማግኘታችንን እንቀጥል። በታማኝነት ከጸናን ይሖዋ እንደሚባርከን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይህም ሐዘን ደርሶብን፣ ክህደት ተፈጽሞብን ወይም ተስፋ ቆርጠን ያነባነውን እንባ በሙሉ የሚያብስበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚገልጸውን ተስፋ ይጨምራል። (ራእይ 21:4) ከዚያ በኋላ የምናነባው የደስታ እንባ ብቻ ይሆናል።

መዝሙር 4 “ይሖዋ እረኛዬ ነው”