በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት “በጎ አድራጊዎች” በማለት የገለጻቸው ሰዎች እነማን ነበሩ? ይህ የማዕረግ ስም የተሰጣቸውስ ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ሐዋርያቱን በእምነት ባልንጀሮቻቸው መካከል የክብር ቦታ ለማግኘት መጣጣር እንደሌለባቸው መክሯቸዋል። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “የአሕዛብ ነገሥታት በእነሱ ላይ ሥልጣናቸውን ያሳያሉ፤ እንዲሁም በሕዝባቸው ላይ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች በጎ አድራጊዎች ተብለው ይጠራሉ። እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ።”—ሉቃስ 22:25, 26

ኢየሱስ በጎ አድራጊዎች በማለት የገለጻቸው ሰዎች እነማን ናቸው? በድንጋይ ላይ የተቀረጹ ጽሑፎች፣ ሳንቲሞችና በእጅ የተጻፉ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት በግሪካውያንና በሮማውያን ማኅበረሰቦች ዘንድ ዝነኛ ሰዎችንና ገዢዎችን ለማክበር ዩዌርጊቲስ ወይም በጎ አድራጊ የሚል የማዕረግ ስም መስጠት የተለመደ ነገር ነበር። እነዚህ ሰዎች ይህ የማዕረግ ስም የሚሰጣቸው ሕዝቡን የሚጠቅሙ አንዳንድ ተግባሮችን ስላከናወኑ ነው።

በርካታ ነገሥታት በጎ አድራጊ የሚል ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል። ከእነዚህ መካከል ሣልሳዊ ቶሌሚ (ከ247-222 ዓ.ዓ. ገደማ) እና ቶሌሚ ስምንተኛ (ከ147-117 ዓ.ዓ. ገደማ) የተባሉት የግብፅ ገዢዎች ይገኙበታል። በተጨማሪም ሮማዊ ገዢዎች የሆኑት ጁሊየስ ቄሳር (48-44 ዓ.ዓ.) እና አውግስጦስ (31 ዓ.ዓ.–14 ዓ.ም.) እንዲሁም የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ታላቁ ሄሮድስ በዚህ የማዕረግ ስም ተጠርተዋል። ሄሮድስ ይህን የማዕረግ ስም ያገኘው ረሃብ በተከሰተበት ወቅት ሕዝቡን ለመታደግ ስንዴ ከውጭ አገር ስላስመጣና ለችግረኞች ልብስ ስለሰጠ ሳይሆን አይቀርም።

ጀርመናዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር አዶልፍ ዲስማን እንደገለጹት በጎ አድራጊ የሚለው የማዕረግ ስም በስፋት ይሠራበት ነበር። እንዲህ ብለዋል፦ “በድንጋይ ላይ ከተቀረጹ ጽሑፎች መካከል ብንፈልግ [ይህ የማዕረግ ስም የተጠቀሰባቸውን] ከመቶ የሚበልጡ ቦታዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ማግኘት እንችላለን።”

ታዲያ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ” ሲላቸው ምን ማለቱ ነበር? ለማኅበረሰቡ ችግር ደንታ ቢሶች እንዲሆኑ ማለትም በዙሪያቸው ስላለው ሕዝብ ደህንነት እንዳያስቡ እየነገራቸው ነበር? በጭራሽ። ኢየሱስን ያሳሰበው የልግስና ድርጊት ለመፈጸም የሚነሳሱበት ዓላማ መሆን አለበት።

በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ባለጸጋ ሰዎች በስፖርት ውድድር ቦታዎች ለሚቀርቡ ትርኢቶችና ጨዋታዎች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ መናፈሻዎችንና ቤተ መቅደሶችን በመገንባት እንዲሁም እንዲህ ያሉ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ ጥሩ ስም ለማትረፍ ይሞክሩ ነበር። ሆኖም ዓላማቸው አድናቆትና ተወዳጅነት ማትረፍ ወይም በምርጫ ወቅት ብዙ ሰው እንዲመርጣቸው ማድረግ ነበር። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ “ከእነዚህ ሰዎች መካከል ከልባቸው ተነሳስተው ልግስና የሚያሳዩ ሰዎች ቢኖሩም የአብዛኞቹ ዓላማ ግን ፖለቲካዊ ጥቅም ማግኘት ነበር” በማለት ይገልጻል። ኢየሱስ ተከታዮቹን ያሳሰባቸው እንዲህ ያለውን ከፍ ያለ ቦታ ላይ የመድረስ ፍላጎትና የግል ጥቅምን የማራመድ ዝንባሌ እንዲያስወግዱ ነበር።

ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ለመስጠት የምንነሳሳበትን ትክክለኛ ዓላማ አስመልክቶ ሲጽፍ ይህን አስፈላጊ እውነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። በቆሮንቶስ ለነበሩ የእምነት ባልንጀሮቹ “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ” በማለት ጽፎላቸዋል።—2 ቆሮ. 9:7