በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስተሳሰባችሁን የሚቀርጸው ማን ነው?

አስተሳሰባችሁን የሚቀርጸው ማን ነው?

“ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ።”—ሮም 12:2

መዝሙሮች፦ 88, 45

1, 2. (ሀ) ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ‘በራስህ ላይ አትጨክን’ በማለት ለሰጠው ምክር ምን ምላሽ ሰጥቷል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ምላሽ የሰጠው ለምንድን ነው?

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጆሯቸውን ማመን አቅቷቸዋል። የእስራኤልን መንግሥት መልሶ ያቋቁማል ብለው ያሰቡት ኢየሱስ በቅርቡ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚገደል ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ቀድሞ ምላሽ የሰጠው ሐዋርያው ጴጥሮስ ነው። “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን” በማለት ተናገረ። አክሎም “በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” አለው። ኢየሱስም “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ ስለማታስብ እንቅፋት ሆነህብኛል” በማለት መለሰለት።—ማቴ. 16:21-23፤ ሥራ 1:6

2 ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሐሳብ በአምላክ አስተሳሰብና በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው ዓለም አስተሳሰብ መካከል ግልጽ ልዩነት እንዳለ ይጠቁማል። (1 ዮሐ. 5:19) ጴጥሮስ በዓለም ላይ የሚታየውን ለራስ የመሳሳት ዝንባሌ እያንጸባረቀ ነበር። ኢየሱስ ግን የአባቱ አስተሳሰብ ከዚህ የተለየ እንደሆነ ያውቃል። አምላክ ከእሱ የሚፈልገው ከፊቱ ለሚጠብቀው መከራና ሞት ራሱን እንዲያዘጋጅ እንደሆነ ተገንዝቧል። ለጴጥሮስ የሰጠው መልስ እንደሚያሳየው ኢየሱስ የዓለምን አስተሳሰብ በግልጽ በመቃወም በይሖዋ አስተሳሰብ ለመመራት መርጧል።

3. የዓለምን አስተሳሰብ ውድቅ አድርጎ የይሖዋን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ ተፈታታኝ የሆነው ለምንድን ነው?

3 ስለ እኛስ ምን ማለት ይቻላል? የምናንጸባርቀው የአምላክን አስተሳሰብ ነው ወይስ የዚህን ዓለም? እርግጥ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ምግባራችንን አምላክ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር እንዳስማማን ግልጽ ነው። ሆኖም አስተሳሰባችንስ እንዴት ነው? አስተሳሰባችንና አመለካከታችን ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር እንዲስማማ እያደረግን ነው? ይህ የታሰበበት ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። በሌላ በኩል ግን የዓለምን አስተሳሰብ መቀበል ያን ያህል ጥረት አይጠይቅም፤ እንዲያውም በጣም ቀላል ነው። ምክንያቱም ዙሪያችንን የከበበን የዓለም መንፈስ ነው። (ኤፌ. 2:2) ከዚህም በተጨማሪ የዓለም አስተሳሰብ በአብዛኛው ለራሳችን ፍላጎት ቅድሚያ እንድንሰጥ ስለሚያበረታታ በቀላሉ ሊማርከን ይችላል። አዎ፣ የይሖዋን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ ተፈታታኝ ቢሆንም የዓለምን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ ግን በጣም ቀላል ነው።

4. (ሀ) ዓለም አስተሳሰባችንን እንዲቀርጸው መፍቀዳችን ምን ውጤት ያስከትላል? (ለ) ይህ ርዕስ የሚረዳን እንዴት ነው?

4 ይሁንና ዓለም አስተሳሰባችንን እንዲቀርጸው የምንፈቅድ ከሆነ በራስ የመመራት ዝንባሌ ሊጠናወተንና ራስ ወዳዶች ልንሆን እንችላለን። (ማር. 7:21, 22) ስለዚህ “የሰውን” ሳይሆን “የአምላክን ሐሳብ” ለማዳበር ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። ይህ ርዕስ በዚህ ረገድ ይረዳናል። አስተሳሰባችንን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ማስማማት መፈናፈኛ የሚያሳጣ ሳይሆን ጠቃሚ ነው የምንልባቸውን ምክንያቶች ያብራራል። በተጨማሪም በዓለም አስተሳሰብ እንዳንቀረጽ መከላከል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይጠቁማል። ቀጣዩ ርዕስ ደግሞ ይሖዋ ስለተለያዩ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት ማወቅና የእሱ ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበር የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይገልጻል።

የይሖዋ አስተሳሰብ ጠቃሚና አስደሳች ነው

5. አንዳንድ ሰዎች ማንም እንዲቀርጻቸው የማይፈልጉት ለምንድን ነው?

5 አንዳንድ ሰዎች ማንም አስተሳሰባቸውን እንዲቀርጸው ወይም በአስተሳሰባቸው ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድርባቸው አይፈልጉም። “በራሴ እንጂ በሌላ በማንም አስተሳሰብ መመራት አልፈልግም” ይላሉ። ምናልባትም እንዲህ የሚሉት የራሳቸውን ውሳኔ ራሳቸው ማድረግ ስለሚፈልጉና እንዲህ ማድረጋቸው ትክክል እንደሆነ ስለሚሰማቸው ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች በማንም ቁጥጥር ሥር መሆን ወይም ማንነታቸውን ማጣት አይፈልጉም። *

6. (ሀ) ይሖዋ ምን ነፃነት ሰጥቶናል? (ለ) ይሖዋ የሰጠን ነፃነት ምንም ገደብ የለውም?

6 ሆኖም አስተሳሰባችንን ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር ማስማማታችን በራሳችን የማሰብ ወይም ሐሳባችንን የመግለጽ ነፃነታችንን እንደማያሳጣን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ሁለተኛ ቆሮንቶስ 3:17 እንደሚናገረው “የይሖዋ መንፈስ ባለበት . . . ነፃነት አለ።” እያንዳንዳችን የየራሳችንን ስብዕና የማዳበርና የምንወደውን ነገር የመምረጥ ነፃነት አለን። ደግሞም ይሖዋ የፈጠረን በዚህ መንገድ ነው። ይሁንና ነፃነታችን ምንም ገደብ የለውም ማለት አይደለም። (1 ጴጥሮስ 2:16ን አንብብ።) ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ከመወሰን ጋር በተያያዘ ይሖዋ በእሱ አስተሳሰብ እንድንመራ ይፈልጋል፤ አስተሳሰቡን ደግሞ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል። ታዲያ የይሖዋ አስተሳሰብ የማያፈናፍን ነው? በእሱ አስተሳሰብ መመራታችንስ የሚያስገኝልን ጥቅም ይኖራል?

7, 8. ይሖዋ ለነገሮች ያለውን አመለካከት ማዳበር መፈናፈኛ የሚያሳጣ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

7 እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ወላጆች በልጆቻቸው ውስጥ መልካም እሴቶችን ለመቅረጽ ጥረት ያደርጋሉ። ልጆቻቸውን ሐቀኛ፣ ታታሪና ለሌሎች አሳቢ እንዲሆኑ ያስተምሯቸው ይሆናል። ይህ ልጆቹን መፈናፈኛ የሚያሳጣ አይደለም። ወላጆች ይህን የሚያደርጉት ልጆቻቸው ወደፊት ራሳቸውን ችለው መኖር ሲጀምሩ ስኬታማ ሕይወት እንዲመሩ ሊያሠለጥኗቸው ስለሚፈልጉ ነው። ልጆቹ አድገው ከቤት ሲወጡ የራሳቸውን ምርጫ የማድረግ ነፃነት ይኖራቸዋል። ወላጆቻቸው ባስተማሯቸው እሴቶች ለመመራት ከመረጡ በአብዛኛው የኋላ ኋላ የማይቆጩባቸውን ውሳኔዎች ያደርጋሉ። በመሆኑም በራሳቸው ላይ አላስፈላጊ ችግርና ጭንቀት ከማምጣት ይድናሉ።

8 ይሖዋም ልክ እንደ አንድ ጥሩ ወላጅ፣ ልጆቹ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ይፈልጋል። (ኢሳ. 48:17, 18) ስለዚህ ከሥነ ምግባርና ከሌሎች ጋር ካለን ግንኙነት ጋር በተያያዘ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሰጥቶናል። እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ረገድ የእሱን አመለካከት እንድናዳብርና በዚያ መሠረት እንድንኖር ግብዣ አቅርቦልናል። ይህ መፈናፈኛ የሚያሳጣ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የማሰብ ችሎታችን እንዲሰፋ፣ እንዲዳብርና የላቀ እንዲሆን ያደርጋል። (መዝ. 92:5፤ ምሳሌ 2:1-5፤ ኢሳ. 55:9) በግለሰብ ደረጃ ማንነታችንን ሳናጣ ደስተኛ ሕይወት ለመምራት የሚያስችሉ ምርጫዎችን እንድናደርግ ይረዳናል። (መዝ. 1:2, 3) በእርግጥም በይሖዋ አስተሳሰብ መመራት ጠቃሚና አስደሳች ነው!

የይሖዋ አስተሳሰብ የላቀ ነው

9, 10. የይሖዋ አስተሳሰብ ከዓለም አስተሳሰብ የላቀ እንደሆነ የታየው እንዴት ነው?

9 የይሖዋ አገልጋዮች አስተሳሰባቸውን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ለማስማማት የሚፈልጉበት ሌላው ምክንያት የይሖዋ አስተሳሰብ ከዓለም አስተሳሰብ እጅግ የላቀ መሆኑ ነው። ይህ ዓለም ከሥነ ምግባር፣ ከቤተሰብ ሕይወት፣ በሥራ እርካታ ከማግኘትና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ምክር ይሰጣል። ዓለም የሚሰጠው ምክር አብዛኛውን ጊዜ ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር ይጋጫል። ለምሳሌ ያህል፣ ዓለም አብዛኛውን ጊዜ ራስን ከፍ ከፍ ማድረግን ያበረታታል። እንዲሁም የፆታ ብልግና መፈጸምን የሚመለከተው ተቀባይነት እንዳለው ነገር አድርጎ ነው። በተጨማሪም ባለትዳሮች ተራ በሆኑ ነገሮች እንኳ መለያየታቸው ወይም መፋታታቸው ይበልጥ ደስተኛ ለመሆን እንደሚያስችላቸው የሚመክርበት ጊዜ አለ። እንዲህ ያሉ ምክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጋጫሉ። ይሁንና ከእነዚህ ምክሮች መካከል አንዳንዶቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይበልጥ ለዘመናችን ተስማሚ ናቸው ሊባል ይችላል?

10 ኢየሱስ “ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 11:19) ዓለም በቴክኖሎጂ ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሰ ቢሆንም እንደ ጦርነት፣ ዘረኝነትና ወንጀል ያሉ ደስታ የሚያሳጡ ከባድ ችግሮችን ማስወገድ አልቻለም። በሥነ ምግባር ረገድ ስላለው ልል አቋምስ ምን ማለት ይቻላል? በርካታ ሰዎች ዓለም የሚያራምደው አቋም ችግሮችን ከማስወገድ ይልቅ እንደ ቤተሰብ መፈራረስና በሽታ ያሉ ሌሎች ችግሮችን እያስከተለ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በሌላ በኩል ግን የአምላክን አስተሳሰብ ለማዳበር ጥረት የሚያደርጉ ክርስቲያኖች ከቤተሰባቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ተሻሽሏል፤ ልቅ በሆነ የሥነ ምግባር አቋም ምክንያት ከሚመጡ የጤና ችግሮች ተጠብቀዋል እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር በሰላም መኖር ችለዋል። (ኢሳ. 2:4፤ ሥራ 10:34, 35፤ 1 ቆሮ. 6:9-11) ታዲያ ይህ፣ የይሖዋ አስተሳሰብ ከዓለም አስተሳሰብ የላቀ መሆኑን የሚያሳይ አይደለም?

11. ሙሴ የሚመራው በማን አስተሳሰብ ነበር? ምን ውጤትስ አግኝቷል?

11 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች የይሖዋ አስተሳሰብ የላቀ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። ለምሳሌ ሙሴ “የግብፃውያንን ጥበብ ሁሉ” የተማረ ቢሆንም “ጥበበኛ ልብ” ለማግኘት የአምላክን እርዳታ ጠይቋል። (ሥራ 7:22፤ መዝ. 90:12) በተጨማሪም “መንገድህን አሳውቀኝ” በማለት ለይሖዋ ልመና አቅርቧል። (ዘፀ. 33:13) በይሖዋ አስተሳሰብ መመራቱ በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲጫወት የረዳው ከመሆኑም ሌላ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ግሩም የእምነት ምሳሌ ሆኖ እንዲጠቀስ አስችሎታል።—ዕብ. 11:24-27

12. ሐዋርያው ጳውሎስ ለመመራት የመረጠው በምንድን ነው?

12 ሐዋርያው ጳውሎስ ብሩሕ አእምሮ ያለው፣ የተማረና ቢያንስ ሁለት ቋንቋዎችን መናገር የሚችል ሰው ነበር። (ሥራ 5:34፤ 21:37, 39፤ 22:2, 3) ሆኖም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መወሰን ሲያስፈልገው በዓለማዊ ጥበብ ከመመራት ይልቅ በቅዱሳን መጻሕፍት ለመመራት መርጧል። (የሐዋርያት ሥራ 17:2ን እና 1 ቆሮንቶስ 2:6, 7, 13ን አንብብ።) በመሆኑም በአገልግሎቱ ስኬታማ ሊሆንና ዘላለማዊ ሽልማት እንደሚያገኝ ተስፋ ሊያደርግ ችሏል።—2 ጢሞ. 4:8

13. እያንዳንዱ ክርስቲያን ምን ኃላፊነት አለበት?

13 በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የአምላክ አስተሳሰብ ከዓለም አስተሳሰብ የላቀ ነው። በአምላክ አስተሳሰብ መመራት እውነተኛ ደስታና ስኬት ያስገኝልናል። ሆኖም ይሖዋ የእሱን አስተሳሰብ እንድንቀበል አያስገድደንም። ‘ታማኝና ልባም ባሪያም’ ሆነ ሽማግሌዎች የሌሎችን አስተሳሰብ ለመቆጣጠር አይሞክሩም። (ማቴ. 24:45፤ 2 ቆሮ. 1:24) ከዚህ ይልቅ እያንዳንዳችን አስተሳሰባችንን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የማስማማት ኃላፊነት አለብን። ታዲያ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

በዚህ ሥርዓት እንዳትቀረጹ ተጠንቀቁ

14, 15. (ሀ) የይሖዋን አስተሳሰብ ለማዳበር በምን ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል? (ለ) በሮም 12:2 መሠረት ዓለማዊ ሐሳቦችን ወደ አእምሯችን እንዳናስገባ መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

14 ሮም 12:2 የሚከተለውን ምክር ይሰጠናል፦ “ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ፤ ከዚህ ይልቅ ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።” በመንፈስ መሪነት የተሰጠው ይህ ምክር፣ ቀደም ሲል አስተሳሰባችን ተቀርጾ የነበረው በየትኛውም መንገድ ቢሆን እውነትን ከሰማን በኋላ አስተሳሰባችንን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር እያስማማን መሄድ እንደምንችል ያሳያል። እርግጥ ነው፣ በዘር የወረስናቸው ነገሮችና ከዚህ በፊት ያሳለፍነው ሕይወት በአስተሳሰባችን ላይ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ግልጽ ነው። ሆኖም አእምሯችን በተፈለገው መንገድ የመቀረጽና የመለዋወጥ ችሎታ አለው። ይህ ለውጥ በአብዛኛው የተመካው ወደ አእምሯችን በምናስገባውና በምናውጠነጥነው ነገር ላይ ነው። የይሖዋን አስተሳሰብ ማውጠንጠናችን ወይም በእሱ አስተሳሰብ ላይ ማሰላሰላችን የእሱ አመለካከት ትክክል መሆኑን አምነን እንድንቀበል ያደርገናል። ይህም አስተሳሰባችንን ከእሱ አስተሳሰብ ጋር የማስማማት ውስጣዊ ፍላጎት እንዲያድርብን ይረዳናል።

15 ይሁንና አእምሯችንን በማደስ የይሖዋን አስተሳሰብ ለመቀበል “ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የሚጋጩ ሐሳቦችን ወይም አመለካከቶችን ወደ አእምሯችን ማስገባታችንን ማቆም አለብን። ይህን የመጀመሪያ እርምጃ መውሰድ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ሰው ጤንነቱን ለማሻሻል ገንቢ ምግቦችን መመገብ ጀመረ እንበል። ሆኖም ይህ ሰው ጎን ለጎን የተበላሸ ምግብም የሚመገብ ከሆነ ገንቢ ምግብ መመገቡ ምን ጥቅም ይኖረዋል? በተመሳሳይም የተበላሹ ዓለማዊ ሐሳቦችን ወደ አእምሯችን የምናስገባ ከሆነ አእምሯችንን በይሖዋ አስተሳሰብ ለመሙላት መሞከራችን እምብዛም ጥቅም አይኖረውም።

16. ራሳችንን ከምን መጠበቅ ይኖርብናል?

16 ከዓለም አስተሳሰብ ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖረን ማድረግ ይቻላል? አይቻልም፤ ቃል በቃል ከዓለም መውጣት የማይቻል ነገር ነው። በተወሰነ መጠንም ቢሆን ለዓለም አስተሳሰብ መጋለጣችን አይቀርም። (1 ቆሮ. 5:9, 10) ሌላው ቀርቶ በስብከቱ ሥራችን ስንካፈል እንኳ አንዳንድ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን እንሰማለን። ሆኖም ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ከሚጋጩ ሐሳቦች መራቅ በማንችልባቸው ሁኔታዎች ሥር ስንሆን እነዚህን ሐሳቦች ላለማውጠንጠን ወይም ላለመቀበል እንጠነቀቃለን። የሰይጣንን ዓላማ የሚያራምዱ አስተሳሰቦችን ውድቅ ለማድረግ ልክ እንደ ኢየሱስ ፈጣኖች እንሆናለን። በተጨማሪም ሳያስፈልግ ለዓለም አስተሳሰብ እንዳንጋለጥ በመጠንቀቅ ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን።—ምሳሌ 4:23ን አንብብ።

17. ራሳችንን ሳያስፈልግ ለዓለም አስተሳሰብ ከማጋለጥ መቆጠብ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

17 ለምሳሌ ያህል፣ የቅርብ ወዳጆቻችንን ስንመርጥ ጠንቃቆች መሆን አለብን። ይሖዋን ከማያመልኩ ሰዎች ጋር የምንቀራረብ ከሆነ አስተሳሰባቸው እንደሚጋባብን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮ. 15:12, 32, 33) ከምንዝናናባቸው ነገሮች ጋር በተያያዘም መራጮች መሆን ይኖርብናል። የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ ከሚያራምዱ አሊያም ዓመፅ ወይም የፆታ ብልግና ከሚታይባቸው መዝናኛዎች በመራቅ አስተሳሰባችን “ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት [በሚጻረሩ]” ሐሳቦች እንዳይመረዝ መከላከል እንችላለን።—2 ቆሮ. 10:5

ልጆቻችንን ጎጂ ከሆኑ መዝናኛዎች እንዲርቁ እየረዳናቸው ነው? (አንቀጽ 18, 19⁠ን ተመልከት)

18, 19. (ሀ) ስውር በሆነ መንገድ የሚቀርቡ ዓለማዊ ሐሳቦችን መከላከል ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል? ለምንስ?

18 በተጨማሪም እምብዛም ግልጽ ባልሆነ መንገድ የሚመጡ ዓለማዊ አስተሳሰቦችን ማወቃችንና ከእነሱ መራቃችን አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ የዜና ሪፖርቶች አንድን ፖለቲካዊ አመለካከት በሚደግፍ መልኩ ሊቀርቡ ይችላሉ። በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚቀርቡ ዘገባዎች፣ ዓለም ግብን ወይም ስኬትን አስመልክቶ ያለውን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ፊልሞችና መጻሕፍት “ከራስ በላይ ነፋስ” አሊያም “ቅድሚያ ለቤተሰብ” የሚሉትን ፍልስፍናዎች የሚያበረታቱ ሲሆን እነዚህን አስተሳሰቦች ምክንያታዊ፣ ማራኪ አልፎ ተርፎም ትክክል የሆኑ አስመስለው ያቀርባሉ። እንዲህ ያሉት አስተሳሰቦች እኛም ሆንን ቤተሰባችን እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምንችለው ይሖዋን ከማንም በላይ ስንወድ እንደሆነ ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር የሚቃረኑ ናቸው። (ማቴ. 22:36-39) ከዚህም በተጨማሪ ለልጆች ተብለው የሚዘጋጁ አንዳንድ መዝናኛዎች በራሳቸው ምንም ችግር ባይኖራቸውም ልጆቻችን ቀስ በቀስ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ድርጊቶችን እንዲቀበሉ ሊያደርጉ ይችላሉ።

19 ይህ ሲባል ግን ጤናማ በሆኑ መዝናኛዎች መካፈል ስህተት ነው ማለት አይደለም። ያም ቢሆን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘ስውር በሆነ መንገድ የሚመጡ ዓለማዊ ትምህርቶችን አስተውላለሁ? አንዳንድ ፕሮግራሞችን ላለመመልከት ወይም ጽሑፎችን ላለማንበብ በእኔም ሆነ በልጆቼ ላይ ገደብ አበጃለሁ? ልጆቼ ዓለማዊ ሐሳቦች በሚያሳድሩት ተጽዕኖ እንዳይሸነፉ የአምላክን አስተሳሰብ እንዲያዳብሩ እረዳቸዋለሁ?’ በአምላክ አስተሳሰብና በዓለም አስተሳሰብ መካከል ያለውን ልዩነት በመገንዘብ “ይህ ሥርዓት [እንዳይቀርጸን]” መከላከል እንችላለን።

እየቀረጻችሁ ያለው ማን ነው?

20. አስተሳሰባችንን የሚቀርጸው ማን እንደሆነ የሚወስነው ምንድን ነው?

20 መረጃ የምናገኝባቸው ምንጮች ሁለት ብቻ እንደሆኑ አስታውሱ፤ እነሱም ይሖዋና በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም ናቸው። ታዲያ እኛን እየቀረጸን ያለው ማን ነው? መልሱ ‘መረጃ እየቀሰምን ያለነው ከየትኛው ምንጭ ነው?’ በሚለው ላይ የተመካ ነው። የዓለምን አስተሳሰብ ወደ አእምሯችን የምናስገባ ከሆነ አስተሳሰባችን የሚቀረጸው በዓለም አስተሳሰብ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ሥጋዊ አመለካከትና ባሕርይ እንድናንጸባርቅ ያደርገናል። በመሆኑም አእምሯችን እንዲያውጠነጥን የምንፈቅድለትን ነገሮች በጥንቃቄ መምረጣችን አስፈላጊ ነው።

21. በቀጣዩ ርዕስ ላይ የትኛው አስፈላጊ ነገር ይብራራል?

21 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የይሖዋን አስተሳሰብ ማዳበር አእምሯችንን ጎጂ ከሆኑ ተጽዕኖዎች ነፃ ከማድረግ ያለፈ እርምጃ መውሰድን ይጠይቃል። አስተሳሰባችንን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የማስማማት ግብ ይዘን የእሱን አስተሳሰብ ወደ አእምሯችን ማስገባት ይኖርብናል። ቀጣዩ ርዕስ እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በሰፊው ያብራራል።

^ አን.5 እንደ እውነቱ ከሆነ በአስተሳሰቡ ላይ ማንም ተጽዕኖ እንዳላሳደረበት የሚያስብ ሰውም እንኳ በሆነ አካል ተጽዕኖ ሥር መሆኑ አይቀርም። ሰዎች እንደ ሕይወት አመጣጥ ባሉ የተወሳሰቡ ጉዳዮችም ሆነ የሚለብሱትን ልብስ እንደመምረጥ ባሉ ቀላል ጉዳዮች ረገድ በተወሰነ መጠንም ቢሆን የሌሎች አስተሳሰብ ተጽዕኖ ያደርግባቸዋል። ሆኖም እያንዳንዳችን ተጽዕኖ እንዲያደርግብን የምንፈቅደው ማን እንደሆነ መምረጥ እንችላለን።