በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘እውነትን ግዛ፤ ፈጽሞም አትሽጠው’

‘እውነትን ግዛ፤ ፈጽሞም አትሽጠው’

“እውነትንና ጥበብን፣ ተግሣጽንና ማስተዋልን ግዛ፤ ፈጽሞም አትሽጣቸው።”—ምሳሌ 23:23

መዝሙሮች፦ 94, 96

1, 2. (ሀ) በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የምንሰጠው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ከፍ አድርገን የምንመለከታቸው እውነቶች የትኞቹ ናቸው? ለምንስ? (በመግቢያው ላይ ያሉትን ሥዕሎች ተመልከት።)

በሕይወትህ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የምትሰጠው ነገር ምንድን ነው? ይህን ነገር አነስተኛ ዋጋ ባለው ሌላ ነገር ለመለወጥ ፈቃደኛ ትሆናለህ? ራሳቸውን ለወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ግልጽ ነው። በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የምንሰጠው ከይሖዋ ጋር ላለን ዝምድና ሲሆን ይህን በምንም ነገር መለወጥ አንፈልግም። በተጨማሪም በሰማይ ካለው አባታችን ጋር ዝምድና ለመመሥረት ያስቻለንን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከፍ አድርገን እንመለከታለን።—ቆላ. 1:9, 10

2 እስቲ ታላቁ አስተማሪያችን ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የሚያስተምረንን ውድ እውነቶች ለማሰብ እንሞክር! ትልቅ ትርጉም ስላለው ስሙ እንዲሁም ማራኪ ስለሆኑት ባሕርያቱ አስተምሮናል። በፍቅር ተነሳስቶ በልጁ በኢየሱስ በኩል ስላደረገልን አስደናቂ የሆነ የቤዛ ዝግጅት ገልጾልናል። በተጨማሪም ስለ መሲሐዊው መንግሥት ያሳወቀን ከመሆኑም ሌላ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ የመግዛት ተስፋ ‘ለሌሎች በጎች’ ደግሞ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር ተስፋ ሰጥቷል። (ዮሐ. 10:16) ከዚህም በላይ ምን ዓይነት ምግባር ማሳየት እንዳለብን አስተምሮናል። ወደ ፈጣሪያችን መቅረብ እንድንችል የሚረዱንን እነዚህን እውነቶች ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን። ምክንያቱም እነዚህ እውነቶች ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን አድርገዋል።

3. እውነትን መግዛት ሲባል ምን ማለት አይደለም?

3 ይሖዋ ለጋስ አምላክ ነው። እውነትን ለማግኘት የሚጣጣሩ ሰዎች ልፋታቸው መና እንዲቀር አያደርግም። ሌላው ቀርቶ ይሖዋ የውድ ልጁን ሕይወት በነፃ ሰጥቶናል። በመሆኑም አምላክ እውነትን ለመግዛት ስንል ገንዘብ እንድንከፍል እንደማይጠብቅብን ግልጽ ነው። እንዲያውም በአንድ ወቅት ስምዖን የተባለ ሰው ገንዘብ እንደሚከፍል ቃል በመግባት መንፈስ ቅዱስን ለሌሎች የመስጠት ሥልጣን እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር። ሆኖም ሐዋርያው ጴጥሮስ “የአምላክን ነፃ ስጦታ በገንዘብ ማግኘት እንደምትችል ስላሰብክ የብር ገንዘብህ ከአንተ ጋር ይጥፋ” በማለት ገሥጾታል። (ሥራ 8:18-20) ታዲያ ‘እውነትን ግዛ’ የሚለው በመንፈስ መሪነት የተሰጠ ትእዛዝ ትርጉም ምንድን ነው?

እውነትን ‘መግዛት’ ሲባል ምን ማለት ነው?

4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ከእውነት ጋር በተያያዘ ምን እንመለከታለን?

4 ምሳሌ 23:23ን አንብብ። በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን እውነት ያለምንም ጥረት ማግኘት አንችልም። ይህን እውነት ለማግኘት አስፈላጊ የሆነውን መሥዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ፈቃደኞች መሆን አለብን። ጠቢብ የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ ጸሐፊ እንደተናገረው “እውነትን” አንዴ ‘ከገዛን’ ወይም ካገኘን በኋላ ‘እንዳንሸጠው’ ወይም እንዳናጣው መጠንቀቅ ይኖርብናል። እውነትን ‘መግዛት’ ሲባል ምን ማለት እንደሆነና እውነትን ለመግዛት ስንል ምን ዋጋ መክፈል እንዳለብን እስቲ እንመልከት። እንዲህ ማድረጋችን ለእውነት ያለንን አድናቆት ለማሳደግና እውነትን ፈጽሞ ‘ላለመሸጥ’ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ለማጠናከር ይረዳናል። ቀጥሎ እንደምንመለከተው እውነትን ለመግዛት ስንል የምንከፍለው ዋጋ መቼም ቢሆን አያስቆጭም።

5, 6. (ሀ) ምንም ገንዘብ ሳንከፍል እውነትን መግዛት የምንችለው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ለ) እውነት ምን ጥቅሞች ያስገኝልናል?

5 ነፃ የሆነን ነገር ለማግኘት እንኳ ዋጋ መክፈል ሊያስፈልገን ይችላል። በምሳሌ 23:23 ላይ ‘መግዛት’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ‘ማግኘት’ የሚል ትርጉምም ሊኖረው ይችላል። ሁለቱም ቃላት ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ወይም ውድ ዋጋ ያለውን ነገር የራስ ለማድረግ ሲባል በምትኩ ሌላ ነገር መስጠትን ያመለክታሉ። ‘እውነትን መግዛት’ የሚለውን ሐሳብ ግልጽ ለማድረግ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በአንድ የገበያ ቦታ “ሙዝ በነፃ ውሰዱ” የሚል ማስታወቂያ ተሰቅሏል እንበል። ይህ ሲባል ታዲያ ሙዙ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ወደ ቤታችሁ ይመጣል ማለት ነው? በፍጹም። ወደ ገበያ ቦታ ሄዳችሁ ሙዙን ይዛችሁ መምጣት ይኖርባችኋል። እርግጥ ሙዙን ያገኛችሁት በነፃ ነው። ሆኖም ወደ ገበያ ቦታው ለመሄድ ጊዜያችሁንና ጉልበታችሁን መሥዋዕት ማድረግ ያስፈልጋችኋል። በተመሳሳይም እውነትን ለመግዛት ገንዘብ መክፈል አይጠበቅብንም፤ ጥረት ማድረግ ግን ያስፈልገናል።

6 ኢሳይያስ 55:1-3ን አንብብ። ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል የተናገራቸው ቃላት እውነትን መግዛት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ ያደርጉልናል። በዚህ ጥቅስ ላይ ይሖዋ ቃሉን ከውኃ፣ ከወተትና ከወይን ጠጅ ጋር አመሳስሎታል። ኩልል እንዳለ ቀዝቃዛ ውኃ ሁሉ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት እውነቶችም መንፈሳችንን ያድሱልናል። በተጨማሪም ወተት ጥንካሬ እንደሚሰጥና ለልጆች እድገት እንደሚጠቅም ሁሉ ገንቢ የሆኑት የይሖዋ ሐሳቦችም ያጠነክሩናል እንዲሁም በመንፈሳዊ እንድናድግ ይረዱናል። ከዚህም ሌላ ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት ከወይን ጠጅ ጋር ተመሳስለዋል። በምን መንገድ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የወይን ጠጅ ከደስታ ጋር ተያይዞ ተገልጿል። (መዝ. 104:15) ይሖዋ ‘የወይን ጠጅ እንዲገዙ’ ለሕዝቡ የተናገረው ሕይወታችንን በእሱ መመሪያዎች መምራታችን ደስታ እንደሚያስገኝልን ስለሚያውቅ ነው። (መዝ. 19:8) በእርግጥም ይህ ንጽጽር በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች መማራችንና ተግባራዊ ማድረጋችን የሚያስገኘውን ጥቅም ግሩም አድርጎ ይገልጻል! እውነትን ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት እውነትን ለመግዛት እንደምንከፍለው ዋጋ አድርገን ልንቆጥረው እንችላለን። ከዚህ በመቀጠል እውነትን ለመግዛት ስንል ልንከፍላቸው የምንችላቸውን አምስት ነገሮች እንመለከታለን።

እውነትን ለመግዛት ስትሉ ምን ነገሮችን መሥዋዕት አድርጋችኋል?

7, 8. (ሀ) እውነትን ለመግዛት ጊዜያችንን መሥዋዕት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) አንዲት ወጣት ተማሪ እውነትን ለመግዛት ስትል ምን ያህል ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ ሆናለች? ምን ውጤትስ አግኝታለች?

7 ጊዜ። እውነትን መግዛት የሚፈልግ ሁሉ ጊዜውን መሥዋዕት ማድረግ አለበት። የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት፣ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማንበብ፣ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ጥሩ ዝግጅት አድርጎ ለመገኘት ጊዜ ያስፈልጋል። ለእነዚህ ነገሮች የሚሆን ጊዜ ለማግኘት እምብዛም አስፈላጊ ካልሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ ‘ጊዜ መግዛት’ ወይም መውሰድ ይኖርብናል። (ኤፌሶን 5:15, 16ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ።) መሠረታዊ ስለሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ትክክለኛውን እውቀት ለመቅሰም ምን ያህል ጊዜ ያስፈልገናል? ይህ እንደ ግለሰቡ ሁኔታ ይለያያል። ይሖዋ ስላለው ጥበብ፣ ስለ መንገዶቹና ስለ ሥራዎቹ መቼም ቢሆን ተምረን መጨረስ አንችልም። (ሮም 11:33) የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ እትም እውነትን ከአንድ “ትንሽ አበባ” ጋር ያመሳሰለው ሲሆን የሚከተለውን ሐሳብ ይዟል፦ “አንድ የእውነት አበባ ስላገኘህ ብቻ አትርካ። አንድ ብቻ በቂ ቢሆን ኖሮ ተጨማሪ አበቦች ባልኖሩ ነበር። መሰብሰብህን አታቋርጥ፤ ፍለጋህን ቀጥል።” እንግዲያው ‘የያዝኩት የአበባ እቅፍ ምን ያህል ትልቅ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው። ለዘላለም ብንኖር እንኳ ሁልጊዜ ስለ ይሖዋ የምንማረው አዲስ ነገር ይኖራል። በዛሬው ጊዜ ግን ጊዜያችንን በጥበብ በመጠቀም ሁኔታችን የሚፈቅደውን ያህል ብዙ እውነት መግዛታችን አስፈላጊ ነው። እስቲ እውነትን ለማግኘት ከፍተኛ ጉጉት የነበራትን አንዲት ሴት ተሞክሮ እንመልከት።

8 ማሪኮ * የተባለች አንዲት ጃፓናዊት ወጣት ትምህርት ለመከታተል ወደ ኒው ዮርክ ሲቲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሄደች። በወቅቱ፣ ጃፓን ውስጥ የተመሠረተ አንድ ሃይማኖታዊ ቡድን አባል ነበረች። አንዲት አቅኚ ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ማሪኮን አገኘቻት። ማሪኮ በተማረችው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በጣም ስለተደሰተች በሳምንት ሁለት ቀን እንድታስጠናት እህትን ጠየቀቻት። ማሪኮ በምትከታተለው ትምህርትና በምትሠራው ሥራ ምክንያት ጊዜዋ የተጣበበ ቢሆንም ወዲያውኑ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረች። በተጨማሪም እውነትን የምትማርበት ጊዜ ለመግዛት ስትል በአንዳንድ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል አቆመች። እንዲህ ያሉ መሥዋዕቶችን መክፈሏ ፈጣን መንፈሳዊ እድገት እንድታደርግ ረድቷታል። በአንድ ዓመት ውስጥ ተጠመቀች። ከስድስት ወር በኋላ ማለትም በ2006 ደግሞ አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። ማሪኮ አሁንም ድረስ በአቅኚነት እያገለገለች ነው።

9, 10. (ሀ) እውነትን መግዛታችን ለቁሳዊ ነገሮች ባለን አመለካከት ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? (ለ) አንዲት ወጣት ምን ነገሮችን መሥዋዕት አድርጋለች? ይህን በማድረጓስ ምን ተሰምቷታል?

9 ቁሳዊ ነገሮች። እውነትን ለመግዛት ስንል ጥሩ ገቢ የሚያስገኝልንን ሥራ ወይም ሙያ መተው ሊያስፈልገን ይችላል። ኢየሱስ ዓሣ አጥማጆች ለነበሩት ለጴጥሮስና ለእንድርያስ “ሰው አጥማጆች” እንዲሆኑ ግብዣ ሲያቀርብላቸው ሁለቱም “መረቦቻቸውን ትተው” ተከትለውታል። (ማቴ. 4:18-20) እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ እውነትን የሚሰሙ በርካታ ሰዎች ሥራቸውን እርግፍ አድርገው መተው አይችሉም። ምክንያቱም ሊወጧቸው የሚገቡ ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶች አሉባቸው። (1 ጢሞ. 5:8) ሆኖም እውነትን የሚሰሙ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ለቁሳዊ ነገሮች ያላቸውን አመለካከት መለወጥና ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ነገሮች ማስተካከል ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ “በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። ከዚህ ይልቅ . . . በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ” በማለት እንዲህ የማድረግን አስፈላጊነት በግልጽ አሳይቷል። (ማቴ. 6:19, 20) እስቲ አንዲት ወጣት ያደረገችውን እንደ ምሳሌ እንመልከት።

10 ማሪያ ገና ትምህርት ቤት ሳትገባ ጀምሮ ጎልፍ መጫወት ትወድ ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለች የጎልፍ ችሎታዋን ይበልጥ ያዳበረች ሲሆን ከጊዜ በኋላ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነፃ የትምህርት ዕድል አገኘች። በሕይወቷ ውስጥ ከምንም በላይ ቅድሚያ የምትሰጠው ለዚህ ስፖርት ነበር። የወደፊት ግቧም በዚህ መስክ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ነበር። በኋላ ግን ማሪያ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረች ሲሆን የምትማረውን እውነት በጣም ወደደችው። እውነትን ስትማር ባደረገቻቸው ለውጦችም በጣም ደስተኛ ሆነች። እንዲህ ብላለች፦ “አመለካከቴንና አኗኗሬን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር ይበልጥ እያስማማሁ በሄድኩ ቁጥር ይበልጥ ደስተኛ ሆንኩ።” ማሪያ ቁሳዊ ሀብት እያሳደደች መንፈሳዊ ሀብት ማካበት እንደማትችል ተገነዘበች። (ማቴ. 6:24) በመሆኑም ከልጅነቷ ጀምሮ ትመኘው የነበረውን የጎልፍ ተጫዋች የመሆን ግብ እንዲሁም ከዚያ ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችለውን ሀብትና ዝና መሥዋዕት አደረገች። እነዚህን ነገሮች መሥዋዕት አድርጋ እውነትን መግዛቷ በአሁኑ ጊዜ በአቅኚነት ለማገልገል አስችሏታል። ማሪያ ይህን ሕይወት “እጅግ አስደሳችና ከሁሉ በላይ ትርጉም ያለው ሕይወት” በማለት ገልጻዋለች።

11. እውነትን መግዛታችን ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?

11 ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት። ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር መወሰናችን ከወዳጆቻችንና ከዘመዶቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ለምን? ኢየሱስ ተከታዮቹን አስመልክቶ “በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው” በማለት ጸልዮአል። (ዮሐ. 17:17 ግርጌ) “ቀድሳቸው” የሚለው ቃል “ለያቸው” የሚል ትርጉም ሊያስተላልፍም ይችላል። እውነትን ስንቀበል ከዓለም እንለያለን፤ ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ዓለም በፈለገው መንገድ ሊቀርጸን አይችልም። ዓለም ከሚመራበት የተለየ መሥፈርት መከተል ስለምንጀምር ሰዎች ለእኛ ያላቸው አመለካከት ይቀየራል። ሕይወታችንን የምንመራው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባለው እውነት ይሆናል። ከሌሎች ጋር ጥሩ ዝምድና ይዘን መቀጠል ብንፈልግም አንዳንድ ወዳጆቻችንና የቤተሰባችን አባላት ራሳቸውን ከእኛ ሊያርቁ አልፎ ተርፎም የምናምንበትን ነገር ሊቃወሙ ይችላሉ። ይህ ሊያስደንቀን አይገባም። ምክንያቱም ኢየሱስ “በእርግጥም የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 10:36) በተጨማሪም እውነትን በመግዛታችን የምናገኘው በረከት እውነትን ለመግዛት ስንል ከምንከፍለው ከማንኛውም መሥዋዕት በእጅጉ እንደሚበልጥ ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—ማርቆስ 10:28-30ን አንብብ።

12. አንድ አይሁዳዊ እውነትን ለመግዛት ሲል ምን ዋጋ ከፍሏል?

12 አሮን የተባለ አይሁዳዊ ነጋዴ ከልጅነቱ ጀምሮ የአምላክን ስም መጥራት ተገቢ እንዳልሆነ ተምሮ ነበር። ሆኖም አሮን እውነትን የማወቅ ጉጉት ነበረው። አንድ የይሖዋ ምሥክር የአምላክ ስም በሚጻፍባቸው አራት የዕብራይስጥ ተነባቢ ፊደላት ላይ አናባቢዎችን በመጨመር የአምላክን ስም “ይሖዋ” ብሎ ማንበብ እንደሚቻል ሲያሳየው በጣም ተደሰተ። ከዚያም የተማረውን አስደሳች እውነት ለረቢዎቹ ለማሳየት ወደ ምኩራብ ሄደ። ያገኘው ምላሽ ግን ከጠበቀው ፈጽሞ የተለየ ነበር። ረቢዎቹ ስለ አምላክ ስም እውነቱን በመማሩ አብረውት ከመደሰት ይልቅ ላዩ ላይ ተፉበት፤ እንዲሁም ከማኅበረሰቡ አገለሉት። ከቤተሰቡ ጋር ያለው ግንኙነትም ተበላሸ። ሆኖም አሮን በዚህ ሳይበገር እውነትን መግዛቱን የቀጠለ ሲሆን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ደፋር የይሖዋ ምሥክር ሆኖ አገልግሏል። እኛም ልክ እንደ አሮን፣ በእውነት ውስጥ ለመጓዝ ስንል በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለንን ቦታ ወይም ከቤተሰባችን ጋር ያለንን ግንኙነት መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች መሆን አለብን።

13, 14. እውነትን ለመግዛት ከፈለግን በአስተሳሰባችንና በአኗኗራችን ላይ ምን ለውጥ ማድረግ አለብን? ምሳሌ ስጥ።

13 አምላክ የማይደሰትበት አስተሳሰብና ምግባር። እውነትን መቀበልና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባሉት የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መመራት ከፈለግን በአስተሳሰባችንና በምግባራችን ላይ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኞች መሆን አለብን። ጴጥሮስ እንዲህ ያለውን ለውጥ አስመልክቶ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ታዛዥ ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ እውቀት ባልነበራችሁ ጊዜ ትከተሉት በነበረው ምኞት መሠረት መቀረጻችሁን አቁሙ፤ ከዚህ ይልቅ . . . በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።” (1 ጴጥ. 1:14, 15) በሥነ ምግባር ባዘቀጠችው በቆሮንቶስ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች እውነትን ለመግዛት ሲሉ በአኗኗራቸው ላይ ትልቅ ለውጥ ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር። (1 ቆሮ. 6:9-11) በዛሬው ጊዜም ቢሆን በርካታ ሰዎች እውነትን ለመግዛት ሲሉ አምላክን የማያስደስቱ ምግባሮችን መተው አስፈልጓቸዋል። ጴጥሮስ በዘመኑ ለነበሩ ክርስቲያኖች የሚከተለውን ማሳሰቢያም ሰጥቷቸዋል፦ “ዓይን ባወጣ ምግባር፣ ልቅ በሆነ የሥጋ ፍላጎት፣ ከልክ በላይ በመጠጣት፣ መረን በለቀቀ ድግስ፣ በመጠጥ ግብዣዎችና በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ በመካፈል የአሕዛብን ፈቃድ የፈጸማችሁበት ያለፈው ጊዜ ይበቃል።”—1 ጴጥ. 4:3

14 ዴቪን እና ጃዝሚን ለበርካታ ዓመታት የአልኮል ሱሰኞች ነበሩ። ዴቪን ጎበዝ የሒሳብ ባለሙያ ቢሆንም የአልኮል ሱሰኝነቱ አንድ ቦታ ላይ በቋሚነት መሥራት እንዳይችል እንቅፋት ሆኖበት ነበር። ጃዝሚን ደግሞ ቁጡና ጠበኛ በመሆኗ ትታወቅ ነበር። አንድ ቀን ሰክራ መንገድ ላይ ስትሄድ ከሁለት ሚስዮናውያን ጋር ተገናኘች። ሚስዮናውያኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊያስጀምሯት ቀጠሮ ያዙ። በቀጣዩ ሳምንት እሷና ዴቪን ወደሚኖሩበት ቤት ሲሄዱ ሁለቱንም ሰክረው አገኟቸው። ዴቪንና ጃዝሚን ሚስዮናውያኑ እነሱን ከቁም ነገር ቆጥረው ቤታቸው ድረስ እንደሚመጡ አልጠበቁም ነበር። ሚስዮናውያኑ በቀጣዩ ጊዜ ሲሄዱ ያዩት ነገር ግን ፈጽሞ የተለየ ነበር። ጃዝሚንና ዴቪን ጥናት ከጀመሩበት ቀን አንስቶ መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት መማርና የተማሩትን በሥራ ላይ ማዋል ጀመሩ። በሦስት ወር ውስጥ የአልኮል መጠጥ መጠጣታቸውን ለማቆም ወሰኑ፤ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ትዳራቸውን ሕጋዊ አደረጉ። ያደረጉት ለውጥ በግልጽ የሚታይ ስለነበር በርካታ የመንደራቸው ነዋሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተነሳስተዋል።

15. አንድ ሰው ለእውነት ሲል ከሚከፍላቸው በጣም ከባድ የሆኑ መሥዋዕቶች መካከል አንዱ ምን ሊሆን ይችላል? ለምንስ?

15 ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ባሕሎችና ልማዶች። አንድ ሰው ለእውነት ሲል ከሚከፍላቸው በጣም ከባድ የሆኑ መሥዋዕቶች መካከል አንዱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ባሕሎችንና ልማዶችን መተው ነው። አንዳንዶች እንዲህ ያሉትን ልማዶች እንዲተዉ የሚያነሳሷቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች መቀበል አይከብዳቸው ይሆናል፤ ሌሎች ግን ከቤተሰባቸው አባላት፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸውና ከቅርብ ጓደኞቻቸው በሚደርስባቸው ተጽዕኖ ምክንያት እነዚህን ልማዶች መተው ከባድ ይሆንባቸዋል። በተለይም የሞቱ ዘመዶችን ለማክበር ተብለው የሚደረጉ ሥርዓቶች ከስሜት ጋር የተያያዙ ስለሆኑ እነዚህን ልማዶች መተው ቀላል አይደለም። (ዘዳ. 14:1) ሌሎች በዚህ ረገድ የተዉትን የድፍረት ምሳሌ መመልከታችን አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ ይረዳናል። እስቲ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ የኤፌሶን ነዋሪዎች የወሰዱትን የድፍረት እርምጃ እንመልከት።

16. በኤፌሶን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እውነትን ለመግዛት ሲሉ ምን አድርገዋል?

16 ኤፌሶን በአስማት ድርጊቶቿ የምትታወቅ ከተማ ነበረች። ቀደም ሲል የአስማት ድርጊት ይፈጽሙ የነበሩ በቅርቡ ወደ ክርስትና የተለወጡ ሰዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ድርጊቶችን ለማስወገድና እውነትን ለመግዛት ሲሉ ምን እርምጃ ወሰዱ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አስማት ይሠሩ ከነበሩት መካከል ብዙዎች መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉ። የመጽሐፎቹንም ዋጋ ሲያሰሉ 50,000 የብር ሳንቲሞች ሆኖ አገኙት። በዚህ መንገድ የይሖዋ ቃል በኃይል እየተስፋፋና እያሸነፈ ሄደ።” (ሥራ 19:19, 20) እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ውድ ዋጋ የከፈሉ ሲሆን በውጤቱም በዋጋ ሊተመን የማይችል በረከት አግኝተዋል።

17. (ሀ) እውነትን ለመግዛት ከምንከፍለው ዋጋ ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉት ነገሮች የትኞቹ ናቸው? (ለ) በቀጣዩ ርዕስ ላይ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመለከታለን?

17 ለእውነት ስትሉ ምን ዋጋ ከፍላችኋል? ሁላችንም የእውነትን አበቦች ለመሰብሰብ ጊዜያችንን መሥዋዕት አድርገናል። አንዳንዶች ደግሞ እውነትን ለመግዛት ሲሉ ቁሳዊ ነገሮችን እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት መሥዋዕት አድርገዋል። ብዙዎች አስተሳሰባቸውንና ምግባራቸውን መለወጥ ያስፈለጋቸው ከመሆኑም ሌላ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ባሕሎችንና ልማዶችን ትተዋል። የከፈልነው ዋጋ ምንም ይሁን ምን ካገኘነው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ እርግጠኞች ነን። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀ ቦታ የምንሰጠውን ነገር ለማግኘት ማለትም ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና ለመመሥረት አስችሎናል። እውነትን ማወቃችን ባስገኘልን በረከቶች ላይ ስናሰላስል እውነትን መሸጥ የሚባለውን ነገር ማሰብ እንኳ ይከብደናል። ለመሆኑ አንድን ሰው እውነትን እንዲሸጥ የሚያደርገው ምንድን ነው? እኛስ እንዲህ ዓይነት ከባድ ስህተት ከመሥራት መራቅ የምንችለው እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

^ አን.8 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።