በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብ ለማዳበር ጥረት እያደረጋችሁ ነው?

የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብ ለማዳበር ጥረት እያደረጋችሁ ነው?

“አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።”—ሮም 12:2

መዝሙሮች፦ 56, 123

1, 2. በመንፈሳዊ እያደግን ስንሄድ ምን ማድረግን እንማራለን? በምሳሌ አስረዳ።

አንድ ትንሽ ልጅ ስጦታ ተሰጠው። በዚህ ጊዜ ወላጆቹ “አመሰግናለሁ በል” ይሉታል። ልጁ ወላጆቹን ለመታዘዝ ሲል ብቻ “አመሰግናለሁ” ይላል። ከፍ እያለ ሲሄድ ግን የወላጆቹን አስተሳሰብ ይበልጥ መረዳትና ሌሎች ለሚያሳዩት ደግነት አመስጋኝ መሆን ያለበት ለምን እንደሆነ መገንዘብ ይጀምራል። በመሆኑም በራሱ ተነሳሽነት አመስጋኝነቱን ይገልጻል። ለምን? ምክንያቱም አስተሳሰቡ በዚያ መንገድ ስለተቀረጸ እንዲህ ማድረግ ቀላል ይሆንለታል።

2 እኛም በተመሳሳይ እውነትን ስንሰማ፣ ይሖዋ ያወጣቸውን መሠረታዊ ብቃቶች ማሟላት አስፈላጊ እንደሆነ ተምረናል። በመንፈሳዊ እያደግን ስንሄድ ግን የይሖዋን አስተሳሰብ ማለትም እሱ የሚወዳቸውንና የሚጠላቸውን ነገሮች እንዲሁም ስለተለያዩ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት ይበልጥ ማወቅ ችለናል። ይሖዋ ነገሮችን በሚያይበት መንገድ ለማየት ጥረት በማድረግ እንዲሁም የእሱ አስተሳሰብ በድርጊታችንና በግል ምርጫችን ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ በመፍቀድ የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብ እያዳበርን እንዳለ እናሳያለን።

3. የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበር ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

3 የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብ ለማዳበር ጥረት ማድረግ አስደሳች ቢሆንም ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ፣ ፍጽምና የጎደለው አእምሯችን የሚያመነጫቸው ሐሳቦች እንቅፋት ሊፈጥሩብን ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ከሥነ ምግባር ንጽሕና፣ ከፍቅረ ንዋይ፣ ከስብከቱ ሥራ፣ ከደም አጠቃቀም ወይም ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ያለውን አመለካከት መቀበል ሊከብደን ይችላል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ እንችላለን? አስተሳሰባችን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ይበልጥ የሚስማማ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ አሁንም ሆነ ወደፊት በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

የአምላክ ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበር

4. ጳውሎስ ‘አእምሯችሁ ይታደስ’ በማለት የሰጠው ምክር ምን ማድረግን ይጨምራል?

4 ሮም 12:2ን አንብብ። ሐዋርያው ጳውሎስ የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብ ለማዳበር ጥረት ማድረግ ምን እንደሚጨምር እዚህ ጥቅስ ላይ ገልጿል። ከዚህ በፊት ያለው የጥናት ርዕስ ‘ይህ ሥርዓት እንዳይቀርጸን’ ከፈለግን ዓለማዊ አስተሳሰቦችንና ዝንባሌዎችን ወደ አእምሯችን ከማስገባት መቆጠብ እንዳለብን አስገንዝቦናል። ሆኖም ጳውሎስ ‘አእምሯችንን ማደስ’ እንደሚያስፈልገንም ጠቅሷል። ይህም የአምላክን አስተሳሰብ መረዳትን ግብ አድርጎ ቃሉን ማጥናትን፣ ባጠናነው ነገር ላይ ማሰላሰልንና አስተሳሰባችንን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ለማስማማት ጥረት ማድረግን ይጨምራል።

5. ላይ ላዩን በማንበብና በማጥናት መካከል ያለውን ልዩነት ግለጽ።

5 ጥናት፣ ላይ ላዩን ከማንበብ ወይም በጥያቄዎች መልስ ላይ ከማስመር ያለፈ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። በምናጠናበት ወቅት ጽሑፉ ስለ ይሖዋ፣ ስለ መንገዶቹና ስለ አስተሳሰቡ ምን እንደሚያስተምረን ለመረዳት እንሞክራለን። አምላክ አንድን ነገር እንድናደርግ ያዘዘውም ሆነ እንዳናደርግ የከለከለው ለምን እንደሆነ ለማስተዋል ጥረት እናደርጋለን። በተጨማሪም በአኗኗራችንና በአስተሳሰባችን ላይ ምን ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልገን እናስባለን። እርግጥ በእያንዳንዱ የጥናት ፕሮግራማችን ላይ እነዚህን ሁሉ ነጥቦች እያነሳን አናሰላስል ይሆናል፤ ሆኖም ለጥናት ከመደብነው ጊዜ ላይ ምናልባት ግማሹን፣ ባነበብነው ነገር ላይ ለማሰላሰል ብንጠቀምበት ብዙ በረከት እናገኛለን።—መዝ. 119:97፤ 1 ጢሞ. 4:15

6. በይሖዋ አስተሳሰብ ላይ ማሰላሰላችን ምን ውጤት ይኖረዋል?

6 በአምላክ ቃል ላይ አዘውትረን ስናሰላስል በራሳችን ላይ አስደናቂ ለውጥ እናያለን። ይሖዋ ስለተለያዩ ነገሮች ያለው አስተሳሰብ ፍጹም መሆኑን ለራሳችን ‘እናረጋግጣለን።’ ነገሮችን እሱ በሚያይበት መንገድ ማየት እንጀምራለን፤ እንዲሁም የእሱ አመለካከት ትክክል መሆኑን አምነን እንቀበላለን። አእምሯችን ‘ስለሚታደስ’ አዲስ ዓይነት አስተሳሰብ እያዳበርን እንሄዳለን። ቀስ በቀስ የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብ ይኖረናል።

አስተሳሰባችን በድርጊታችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል

7, 8. (ሀ) ይሖዋ ለቁሳዊ ነገሮች ምን አመለካከት አለው? (በመግቢያው ላይ ያሉትን ሥዕሎች ተመልከት።) (ለ) የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ካለን ምንጊዜም ቅድሚያ የምንሰጠው ለየትኛው ነገር ነው?

7 ማሰብ ከአእምሮ ጋር ብቻ የተያያዘ ጉዳይ ነው ብለን መደምደም አይኖርብንም። የምናስበው ነገር በድርጊታችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። (ማር. 7:21-23፤ ያዕ. 2:17) ይህን ግልጽ የሚያደርጉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን እንመልከት። ለምሳሌ ያህል፣ የወንጌል ዘገባዎች ይሖዋ ለቁሳዊ ነገሮች ምን አመለካከት እንዳለው ያሳዩናል። አምላክ ልጁን እንዲያሳድጉ የመረጠው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ባልና ሚስት ነበር። (ዘሌ. 12:8፤ ሉቃስ 2:24) ማርያም ኢየሱስን ስትወልድ በእንግዶች ማረፊያ ቤት ውስጥ ቦታ ስላልተገኘ ‘ልጁን በግርግም ውስጥ ለማስተኛት’ ተገዳ ነበር። (ሉቃስ 2:7) ይሖዋ ቢፈልግ ኖሮ ልጁ በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ እንዲወለድ ማድረግ የሚችልባቸው ብዙ መንገዶች ነበሩ። ሆኖም የይሖዋ ዋነኛ ፍላጎት ልጁ መንፈሳዊ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ እንክብካቤ አግኝቶ እንዲያድግ ነበር።

8 ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ ስለነበረው ሁኔታ የሚናገረው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይሖዋ ለቁሳዊ ነገሮች ያለውን አመለካከት እንድንገነዘብ ይረዳናል። አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በቁሳዊ ነገሮች ረገድ የተሻለ ሕይወት ሊኖራቸው እንደሚገባ ያምናሉ፤ ለዚህ ሲባል የልጆቻቸው መንፈሳዊ ጤንነት አደጋ ላይ ቢወድቅ እንኳ ግድ አይሰጣቸውም። ይሖዋ ግን ከሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠው ለመንፈሳዊ ነገሮች እንደሆነ በግልጽ መረዳት እንችላለን። ታዲያ ስለዚህ ጉዳይ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት አላችሁ? ድርጊታችሁ ምን ያሳያል?—ዕብራውያን 13:5ን አንብብ።

9, 10. ሌሎችን ከማሰናከል ጋር በተያያዘ ይሖዋ ያለውን አመለካከት እንደምንጋራ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

9 ሌሎችን ከማሰናከል ጋር በተያያዘ አምላክ ምን አመለካከት እንዳለው የሚያሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ደግሞ እንመልከት። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል።” (ማር. 9:42) እነዚህ ቃላት ጠንካራ መልእክት ያስተላልፋሉ! ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል፤ ስለዚህ ይሖዋም ግድ የለሽ በሆነ ድርጊታቸው ምክንያት የኢየሱስን ተከታዮች የሚያሰናክሉ ሰዎችን አጥብቆ እንደሚቃወም እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዮሐ. 14:9

10 እኛስ በዚህ ረገድ የይሖዋና የኢየሱስ ዓይነት አመለካከት አለን? ድርጊታችን ምን ያሳያል? ለምሳሌ ያህል፣ እኛ የወደድነው አለባበስ ወይም አጋጌጥ በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎችን ቅር የሚያሰኝ ወይም የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅስ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ለእምነት ባልንጀሮቻችን ያለን ፍቅራዊ አሳቢነት የግል ምርጫችንን እንድንተው ያነሳሳናል?—1 ጢሞ. 2:9, 10

11, 12. ራሳችንን መግዛታችንና አምላክ ለክፋት ያለውን አመለካከት ማዳበራችን ከመጥፎ ድርጊቶች እንድንርቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

11 ሦስተኛው ምሳሌ ደግሞ ይሖዋ ክፋትን እንደሚጠላ የሚያሳይ ነው። (ኢሳ. 61:8) ይሖዋ በወረስነው አለፍጽምና ምክንያት ውስጣችን ወደ መጥፎ ነገር ያዘነበለ እንደሆነ ቢያውቅም ለክፋት የእሱ ዓይነት ጥላቻ እንድናዳብር መክሮናል። (መዝሙር 97:10ን አንብብ።) ይሖዋ ክፋትን የሚጠላው ለምን እንደሆነ ማሰላሰላችን የእሱ ዓይነት አመለካከት እንድናዳብር ይረዳናል፤ ይህም ከመጥፎ ድርጊቶች ለመራቅ የሚያስችል ተጨማሪ ጥንካሬ ይሰጠናል።

12 ከዚህም ሌላ ይሖዋ ለክፋት ያለውን አመለካከት ማዳበራችን፣ አንዳንድ ድርጊቶች በአምላክ ቃል ውስጥ በቀጥታ ባይወገዙም እንኳ ስህተት መሆናቸውን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ ላፕ ዳንሲንግ የሚባለው የዳንስ ዓይነት በዓለም ዙሪያ በብዙዎች ዘንድ እየተለመደ መጥቷል። ይህ የዳንስ ዓይነት ልቅ የሆነ ምግባር የሚንጸባረቅበት ቢሆንም አንዳንዶች ድርጊቱ የፆታ ግንኙነት እንደመፈጸም ስለማይቆጠር ምንም ችግር እንደሌለው ይሰማቸዋል። * ይሁንና ማንኛውንም ዓይነት ክፋት የሚጸየፈው አምላክ ለዚህ ድርጊት ያለው አመለካከት ፈጽሞ የተለየ ነው። እንግዲያው ራስን የመግዛት ባሕርይን በማዳበርና ይሖዋ የሚጸየፋቸውን ነገሮች በመጸየፍ ከክፋት ድርጊት እንራቅ።—ሮም 12:9

ወደፊት ለሚያጋጥሙን ነገሮች አስቀድመን መዘጋጀት

13. የይሖዋ አስተሳሰብ ወደፊት በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ማሰባችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

13 በምናጠናበት ወቅት፣ የይሖዋ አስተሳሰብ ወደፊት በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አስቀድመን ማሰባችን ጠቃሚ ነው። እንዲህ ማድረጋችን በአፋጣኝ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ግራ እንዳንጋባ ይረዳናል። (ምሳሌ 22:3) እስቲ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመልከት።

14. ዮሴፍ የጶጢፋር ሚስት ላቀረበችው ማባበያ ከሰጠው ምላሽ ምን ትምህርት እናገኛለን?

14 ዮሴፍ የጶጢፋር ሚስት ያቀረበቻቸውን ማባበያዎች ወዲያውኑ ውድቅ አድርጓል፤ ይህም ይሖዋ ለትዳር ጓደኛ ታማኝ ስለመሆን ያለውን አመለካከት አስቀድሞ እንዳሰበበት የሚያሳይ ነው። (ዘፍጥረት 39:8, 9ን አንብብ።) በተጨማሪም ለጶጢፋር ሚስት “እንዲህ ያለውን እጅግ መጥፎ ድርጊት በመፈጸም በአምላክ ላይ እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?” የሚል ምላሽ መስጠቱ የአምላክ ዓይነት አመለካከት እንዳዳበረ የሚጠቁም ነው። እናንተስ በዚህ ረገድ እንዴት ናችሁ? ለምሳሌ የሥራ ባልደረባችሁ ሊያሽኮረምማችሁ ቢሞክር አሊያም አንድ ሰው የብልግና ጽሑፍ ወይም ምስል ወደ ሞባይል ስልካችሁ ቢልክ ምን ታደርጋላችሁ? * ይሖዋ እንዲህ ስላሉ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት ለማወቅ አስቀድመን ጥረት ካደረግንና ምን እርምጃ እንደምንወስድ ከወሰንን ሁኔታው ሲከሰት ቆራጥ አቋም መያዝ ቀላል ይሆንልናል።

15. ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት እንድናጓድል የሚደርስብንን ጫና ልክ እንደ ሦስቱ ዕብራውያን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

15 አሁን ደግሞ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የተባሉ ሦስት ዕብራውያን ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንመልከት። እነዚህ ዕብራውያን፣ ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው የወርቅ ምስል ለመስገድ ፈጽሞ ፈቃደኞች አለመሆናቸውና ይህን አቋማቸውን በተመለከተ ለንጉሡ ቀጥተኛ ምላሽ መስጠታቸው ለይሖዋ ታማኝ መሆን ሲባል ምን ነገሮችን እንደሚጨምር አስቀድመው እንዳሰቡበት የሚያሳይ ነው። (ዘፀ. 20:4, 5፤ ዳን. 3:4-6, 12, 16-18) እናንተስ ተመሳሳይ ነገር ሊያጋጥማችሁ ይችላል? አሠሪያችሁ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ንክኪ ላለው በቅርቡ የሚከበር አንድ በዓል የገንዘብ መዋጮ እንድታደርጉ ጠየቃችሁ እንበል። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጋላችሁ? እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች እስኪያጋጥሟችሁ ድረስ ከመጠበቅ ይልቅ ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ለምን ከወዲሁ ጥረት አታደርጉም? ይህም ተመሳሳይ ሁኔታ በሚያጋጥማችሁ ጊዜ ልክ እንደ ሦስቱ ዕብራውያን ትክክለኛውን ነገር ማድረግም ሆነ መናገር ቀላል እንዲሆንላችሁ ይረዳችኋል።

ምርምር በማድረግ፣ ሕጋዊ የሕክምና ሰነድ በመሙላትና ከሐኪምህ ጋር በመነጋገር አስቀድመህ ዝግጅት አድርገሃል? (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)

16. የይሖዋን አስተሳሰብ ከወዲሁ መገንዘባችን ድንገተኛ ሕክምና የሚጠይቅ ሁኔታ ቢያጋጥመን የሚረዳን እንዴት ነው?

16 ለይሖዋ ታማኝ የመሆንን አስፈላጊነት አስቀድመን ማሰባችን ድንገተኛ ሕክምና በሚያስፈልገን ጊዜም ይረዳናል። ሙሉውን ደም ወይም ከአራቱ ዋና ዋና የደም ክፍልፋዮች አንዱን ፈጽሞ እንደማንወስድ የታወቀ ነው፤ ሆኖም የደም ንዑስ ክፍልፋዮችን መውሰድ ከሚጠይቁ ሕክምናዎች ጋር በተያያዘ እያንዳንዱ ክርስቲያን የይሖዋን አስተሳሰብ በሚያንጸባርቁ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርቶ የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። (ሥራ 15:28, 29) እንዲህ ስላሉ ጉዳዮች ማሰብ ያለብን ሆስፒታል ውስጥ በሕመም ላይ ሳለን ወይም በአፋጣኝ እንድንወስን ጫና በሚደረግብን ጊዜ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ምርምር የምናደርግበት፣ የምንቀበለውን የሕክምና ዓይነት የሚገልጽ ሕጋዊ ሰነድ የምንሞላበትና ከሐኪማችን ጋር የምንነጋገርበት ከሁሉ የተሻለ ጊዜ አሁን ነው። *

17-19. ይሖዋ ስለተለያዩ ነገሮች ያለውን አመለካከት አስቀድመን ለማወቅ መሞከራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አስቀድሞ መዘጋጀት አስፈላጊ የሚሆንባቸውን አንዳንድ ሁኔታዎች ጥቀስ።

17 በመጨረሻም ኢየሱስ “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን” በማለት ጴጥሮስ ለሰነዘረው የተሳሳተ ሐሳብ የሰጠውን ፈጣን ምላሽ እንመልከት። ኢየሱስ ከእሱ ጋር በተያያዘ የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስቀድሞ እንዳሰበበት ግልጽ ነው፤ ምድር ላይ ስለሚመራው ሕይወትና ስለ አሟሟቱ በሚናገሩ ጥቅሶች ላይም ቢሆን ከረጅም ጊዜ አንስቶ ያሰላስል እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ይህም ታማኝነቱን ጠብቆ ለመኖርና የራስን ጥቅም መሠዋት የሚጠይቅ ሕይወት ለመምራት ያደረገውን ውሳኔ በእጅጉ አጠናክሮለታል።—ማቴዎስ 16:21-23ን አንብብ።

18 በዛሬው ጊዜ አምላክ ለሕዝቡ ያለው ፈቃድ፣ ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠርቱና እሱ በሰጣቸው ሥራ የቻሉትን ያህል ሙሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ነው። (ማቴ. 6:33፤ 28:19, 20፤ ያዕ. 4:8) አንዳንድ ሰዎች ልክ እንደ ጴጥሮስ በቅን ልቦና ተነሳስተው ከዚህ የተለየ አካሄድ እንድንከተል ይገፋፉን ይሆናል። ለምሳሌ አሠሪህ ጠቀም ያለ የደሞዝ ጭማሪ የሚያስገኝ እድገት እንደሚሰጥህ ቢነግርህ፣ ሆኖም ይህ ሥራ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችህ ላይ እንቅፋት የሚፈጥርብህ ቢሆን ምን ታደርጋለህ? አሊያም ደግሞ ተማሪ ብትሆንና ከቤተሰቦችህ እንድትርቅ የሚያስገድድ ተጨማሪ የትምህርት ዕድል ብታገኝ ምን ትወስናለህ? በጉዳዩ ላይ ለመጸለይ፣ ምርምር ለማድረግ፣ ከቤተሰቦችህ ጋር ለመወያየት፣ ምናልባትም ሽማግሌዎችን ለማማከር የግድ ሁኔታው እስኪያጋጥምህ ድረስ መጠበቅ የለብህም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንዲህ ስላሉ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት ለማወቅና የእሱ ዓይነት አስተሳሰብ ለማዳበር አስቀድመህ ጥረት ማድረግህ አስፈላጊ ነው። እንዲህ ካደረግክ፣ የቀረበልህ ግብዣ ያን ያህል ፈታኝ አይሆንብህም። ምክንያቱም ከወዲሁ መንፈሳዊ ግብ ስላወጣህና እዚያ ላይ ለመድረስ ቁርጥ አቋም ስላለህ የሚቀርህ አስቀድመህ ያደረግከውን ውሳኔ ሥራ ላይ ማዋል ብቻ ይሆናል።

19 ድንገት ሳይታሰቡ የሚከሰቱ ሌሎች ሁኔታዎችም ወደ አእምሮህ ሊመጡ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ ሊያጋጥመን ለሚችለው ለእያንዳንዱ ነገር አስቀድመን መዘጋጀት አንችልም። ሆኖም የግል ጥናት ስናደርግ የይሖዋን አስተሳሰብ የማወቅ ግብ ይዘን የምናሰላስል ከሆነ ላጋጠመን ሁኔታ ተስማሚ የሆኑ ነጥቦችን ማስታወስና ተግባራዊ ማድረግ ቀላል ይሆንልናል። እንግዲያው ይሖዋ ስለተለያዩ ነገሮች ያለውን አመለካከት ማወቃችንና የእሱ ዓይነት አመለካከት ማዳበራችን በጣም አስፈላጊ ነው፤ እንዲሁም አስተሳሰባችንን ከእሱ አስተሳሰብ ጋር ማስማማታችን አሁንም ሆነ ወደፊት በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ማጤናችን ጠቃሚ ነው።

የይሖዋ አስተሳሰብና የወደፊቱ ጊዜ

20, 21. (ሀ) በአዲሱ ዓለም ውስጥ ምን ዓይነት ነፃነት ይኖረናል? (ለ) በዚያ ጊዜ የሚኖረንን ደስታ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ማጣጣም የምንችለው እንዴት ነው?

20 አዲሱ ዓለም የሚመጣበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። አብዛኞቻችን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር እንናፍቃለን። በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የሰው ዘር አሁን ባለንበት ሥርዓት ላይ ተስፋፍቶ ከሚታየው አሳዛኝ ሁኔታ ነፃ ይወጣል። እንዲሁም በዚያን ጊዜም ቢሆን እያንዳንዱ ሰው በፍላጎቱ ላይ ተመሥርቶ የግል ምርጫ የማድረግ ነፃነት ይኖረዋል።

21 እርግጥ ይህ ነፃነት ገደብ የለሽ አይደለም። የዋህ የሆኑ ሰዎች ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመወሰን በይሖዋ ሕግጋትና አስተሳሰብ መመራት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። ይህም ታላቅ ደስታና ብዙ ሰላም ያስገኝላቸዋል። (መዝ. 37:11) እስከዚያው ድረስ ግን የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብ ለማዳበር ጥረት በማድረግ ወደፊት የምናገኘውን ደስታ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ማጣጣም እንችላለን።

^ አን.12 ላፕ ዳንሲንግ “ከፊል እርቃኗን የሆነች አንዲት ዳንሰኛ በደንበኛዋ ጭን ላይ ተቀምጣ የፆታ ስሜትን በሚያነሳሳ መንገድ እየተንቀሳቀሰች የምትደንሰው የዳንስ ዓይነት ነው።” የተፈጸመውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ድርጊት እንደ ፆታ ብልግና ተቆጥሮ የፍርድ እርምጃ መውሰድ ሊያስፈልግ ይችላል። እንዲህ ባለ ድርጊት የተካፈለ ክርስቲያን የሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቅ ይኖርበታል።—ያዕ. 5:14, 15

^ አን.14 እርቃንን የሚያሳዩ ወይም ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ፎቶግራፎችን፣ ቪዲዮዎችን እንዲሁም የጽሑፍ መልእክቶችን በሞባይል አማካኝነት መላክ ሴክስቲንግ ይባላል። የተፈጸመውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የፍርድ እርምጃ መውሰድ ሊያስፈልግ ይችላል። እንዲህ ዓይነት መልእክት የሚልኩ ለአካለ መጠን ያልደረሱ አንዳንድ ልጆች ሌሎችን በፆታ በማስነወር ወንጀል ተከስሰዋል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በjw.org/am ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ—ስለ ሴክስቲንግ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት። (የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > ወጣቶች በሚለው ሥር ይገኛል።) ወይም በኅዳር 2013 ንቁ! መጽሔት ከገጽ 4-5 ላይ የወጣውን “ስለ ሴክስቲንግ ከልጃችሁ ጋር መነጋገር የምትችሉት እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.16 ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በጽሑፎቻችን ውስጥ ተብራርተዋል። ለምሳሌ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 246-249 መመልከት ትችላለህ።