በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 45

መንፈስ ቅዱስ የሚረዳን እንዴት ነው?

መንፈስ ቅዱስ የሚረዳን እንዴት ነው?

“ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።”—ፊልጵ. 4:13

መዝሙር 104 የአምላክ ስጦታ የሆነው መንፈስ ቅዱስ

ማስተዋወቂያ *

1-2. (ሀ) በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ለመወጣት ምን ይረዳናል? አብራራ። (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

“በራሴ ቢሆን ኖሮ ያን ሁሉ ፈተና ልወጣው አልችልም ነበር” ያልክበት ጊዜ አለ? ብዙዎቻችን እንዲህ ተሰምቶን ያውቃል። ምናልባትም እንዲህ የተሰማህ፣ እንደ ከባድ ሕመም ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት እንደ ማጣት ያሉ ችግሮችን ከተቋቋምክ በኋላ ሊሆን ይችላል። የደረሰብህን መከራ መለስ ብለህ ስታስብ፣ እያንዳንዷን ቀን ማለፍ የቻልከው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” ስለሰጠህ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል።—2 ቆሮ. 4:7-9

2 ይህ ክፉ ዓለም የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቋቋምም የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልገናል። (1 ዮሐ. 5:19) ከዚህም በተጨማሪ “ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች” ጋር እንታገላለን። (ኤፌ. 6:12) መንፈስ ቅዱስ፣ ተጽዕኖ የሚያሳድሩብንን እነዚህን ነገሮች መቋቋም እንድንችል በየትኞቹ ሁለት መንገዶች እንደሚረዳን ቀጥለን እንመረምራለን። ከዚያም ከመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን እንመለከታለን።

መንፈስ ቅዱስ ኃይል ይሰጠናል

3. ይሖዋ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንድንወጣ የሚረዳበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

3 የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ፣ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እያሉም እንኳ ኃላፊነቶቻችንን ለመወጣት የሚያስፈልገንን ኃይል ወይም ጥንካሬ በመስጠት ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም በአገልግሎቱ መቀጠል የቻለው ‘በክርስቶስ ኃይል’ እንደሆነ ተሰምቶታል። (2 ቆሮ. 12:9) ጳውሎስ ሁለተኛውን ሚስዮናዊ ጉዞ ባደረገበት ወቅት በስብከቱ ሥራ በትጋት ከመካፈል በተጨማሪ የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች ለማሟላት መሥራት ነበረበት። ጳውሎስ፣ ቆሮንቶስ እያለ አቂላ እና ጵርስቅላ ቤት አርፎ ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት ድንኳን ሠሪዎች ነበሩ። ጳውሎስም የእነሱ ዓይነት ሙያ ስለነበረው ለተወሰነ ጊዜ አብሯቸው ይሠራ ነበር። (ሥራ 18:1-4) ጳውሎስ ሰብዓዊ ሥራ እየሠራም አገልግሎቱን ማከናወን እንዲችል መንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰጥቶታል።

4. በ2 ቆሮንቶስ 12:7ለ-9 ላይ እንደተገለጸው ጳውሎስ ምን ችግር አጋጥሞት ነበር?

4 ሁለተኛ ቆሮንቶስ 12:7ለ-9ን አንብብ። ጳውሎስ በዚህ ጥቅስ ላይ “ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? እሾህ ቢሰካብህ በጣም እንደሚያሠቃይህ የታወቀ ነው። ጳውሎስም በጣም የሚያሠቃይ አንድ ዓይነት ችግር እንዳጋጠመው መግለጹ ነበር። ጳውሎስ ይህን ችግር “ዘወትር የሚያሠቃየኝ [“የሚመታኝ፣” ግርጌ] የሰይጣን መልአክ” በማለት ጠርቶታል። ጳውሎስ ላይ እሾሁን የሰኩበት ይኸውም ላጋጠመው ችግር መንስኤ የሆኑት ሰይጣን ወይም አጋንንቱ ላይሆኑ ይችላሉ። ሆኖም እነዚህ ክፉ መናፍስት ጳውሎስ የገጠመውን ችግር ወይም “እሾህ” ሲመለከቱ እሾሁ ወደ ሰውነቱ ጠልቆ እንዲገባ ለማድረግ በሌላ አባባል ሥቃዩን ለማባባስ ሞክረው ሊሆን ይችላል። ታዲያ ጳውሎስ ምን አደረገ?

5. ይሖዋ የጳውሎስን ጸሎት የመለሰለት እንዴት ነው?

5 መጀመሪያ ላይ ጳውሎስ ‘እሾሁ’ እንዲወገድለት ፈልጎ ነበር። “ይህ ነገር ከእኔ እንዲርቅ [ይሖዋን] ሦስት ጊዜ ለመንኩት” ብሏል። ጳውሎስ እንዲህ ያለ ጸሎት ቢያቀርብም ሥጋውን የሚወጋው እሾህ አልተወገደም። ታዲያ ይሖዋ የጳውሎስን ጸሎት አልመለሰለትም ማለት ነው? በፍጹም። ጸሎቱን መልሶለታል። ይሖዋ ችግሩን ከማስወገድ ይልቅ ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ለጳውሎስ ሰጥቶታል። ይሖዋ “ኃይሌ ፍጹም የሚሆነው በምትደክምበት ጊዜ ነው” ብሎታል። (2 ቆሮ. 12:8, 9) ደግሞም ጳውሎስ በአምላክ እርዳታ ደስታውንና ውስጣዊ ሰላሙን ጠብቆ መኖር ችሏል።—ፊልጵ. 4:4-7

6. (ሀ) ይሖዋ ለጸሎታችን ምላሽ የሚሰጠን እንዴት ሊሆን ይችላል? (ለ) በአንቀጹ ውስጥ ያሉት ጥቅሶች ብርታት የሚሰጥ ምን ማረጋገጫ ይዘዋል?

6 አንተስ እንደ ጳውሎስ ይሖዋን ከአንድ ችግር እንዲገላግልህ ለምነኸው ታውቃለህ? ስለ ችግሩ ደጋግመህ ብትጸልይም እንኳ ችግሩ አይወገድ እንዲያውም ይባባስ ይሆናል፤ ታዲያ በዚህ ጊዜ ‘ይሖዋ አዝኖብኝ ይሆን?’ ብለህ ትጨነቃለህ? ከሆነ ጳውሎስ ያጋጠመውን ሁኔታ አስታውስ። ይሖዋ የጳውሎስን ጸሎት እንደመለሰለት ሁሉ የአንተንም ጸሎት እንደሚመልስልህ አትጠራጠር! ይሖዋ ችግሩን አያስወግደው ይሆናል። ይሁንና ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ይሰጥሃል። (መዝ. 61:3, 4) ‘ብትወድቅም’ ይሖዋ አይተውህም።—2 ቆሮ. 4:8, 9 ግርጌ፤ ፊልጵ. 4:13

መንፈስ ቅዱስ ወደፊት እንድንገፋ ይረዳናል

7-8. (ሀ) መንፈስ ቅዱስ ከነፋስ ጋር የሚመሳሰለው በምን መንገድ ነው? (ለ) ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስ የሚሠራበትን መንገድ የገለጸው እንዴት ነው?

7 መንፈስ ቅዱስ እኛን የሚረዳበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው? በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ላይ የሚጓዝ መርከብ፣ ወደሚፈልገው አቅጣጫ የሚነፍስ ነፋስ ካጋጠመው በሰላም ወደ ወደብ መድረስ ይችላል፤ በተመሳሳይም መንፈስ ቅዱስ እንደ ማዕበል ያሉ ፈተናዎችን ተቋቁመን፣ አምላክ ቃል ወደገባልን አዲስ ዓለም እንድንገባ ይረዳናል።

8 ሐዋርያው ጴጥሮስ ዓሣ አጥማጅ እንደመሆኑ መጠን በባሕር ላይ ስለሚደረግ ጉዞ በሚገባ ያውቃል። በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ የሚሠራበትን መንገድ ሲገልጽ፣ ባሕር ላይ ከመጓዝ ጋር ተያያዥነት እንዳለው የሚገመት ቃል መጠቀሙ ትኩረት የሚስብ ነው። ጴጥሮስ “መቼም ቢሆን ትንቢት በሰው ፈቃድ አልመጣምና፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው ተናገሩ” ሲል ጽፏል። “ተገፋፍተው” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ፍቺው “ተነድተው” የሚል ነው።—2 ጴጥ. 1:21 ግርጌ

9. ጴጥሮስ “ተነድተው” የሚለውን ቃል የተጠቀመው የትኛውን ሁኔታ በአእምሯችን እንድንሥል ፈልጎ ነው?

9 ጴጥሮስ “ተነድተው” የሚለውን ቃል የተጠቀመው የትኛውን ሁኔታ በአእምሯችን እንድንሥል ፈልጎ ነው? የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን የጻፈው ሉቃስ ‘በነፋስ እየተነዳ’ ስለሚሄድ መርከብ ሲጽፍ ይህን የግሪክኛ ቃል በሌላ መልኩ ተጠቅሞበታል። (ሥራ 27:15) በመሆኑም ጴጥሮስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “ተነድተው” እንደጻፉ ሲናገር “ከባሕር ጉዞ ጋር የተያያዘ ትኩረት የሚስብ ዘይቤያዊ አገላለጽ” መጠቀሙ እንደሆነ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ገልጸዋል። ጴጥሮስ አንድ መርከብ በነፋስ እየተነዳ ጉዞውን እንደሚያጠናቅቅ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያትና ጸሐፊዎችም በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ሥራቸውን ዳር ማድረስ እንደቻሉ መግለጹ ነበር። “ነቢያቱ ነፋሱ እንዲነዳቸው ሸራቸውን የወጠሩ ያህል ነው” በማለት እኚሁ ምሁር ተናግረዋል። ይሖዋ የራሱን ድርሻ ተወጥቷል። “ነፋሱን” ይኸውም መንፈስ ቅዱስን ሰጥቷቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም የሚጠበቅባቸውን አድርገዋል። ይኸውም የመንፈስ ቅዱስን አመራር በመከተል ሥራቸውን አከናውነዋል።

የመጀመሪያው እርምጃ፦ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አዘውትረህ ተካፈል

ሁለተኛው እርምጃ፦ በእነዚህ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አቅምህ የፈቀደውን ያህል የተሟላ ተሳትፎ አድርግ (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት) *

10-11. ከአምላክ ቅዱስ መንፈስ አመራር ጥቅም ለማግኘት የትኞቹን ሁለት እርምጃዎች መውሰድ ይኖርብናል? በምሳሌ አስረዳ።

10 እርግጥ ነው፣ በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ በመንፈሱ ተጠቅሞ ሰዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዲጽፉ አያደርግም። ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜም የአምላክን ሕዝቦች እየመራ ነው። ይሖዋ አሁንም የራሱን ድርሻ እየተወጣ ነው። ታዲያ እኛስ ከአምላክ ቅዱስ መንፈስ አመራር ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል? የበኩላችንን ማድረግ አለብን። ይህን የምናደርገው እንዴት ነው?

11 እስቲ የሚከተለውን ንጽጽር እንመልከት። አንድ ባሕረኛ ነፋሱ እንዲረዳው ከፈለገ ሁለት ነገሮችን ማድረግ ይኖርበታል። በመጀመሪያ፣ መርከቡ ነፋሱ በሚነፍስበት አቅጣጫ እንዲጓዝ ማድረግ አለበት። ደግሞም መርከቡ ከነፋሱ አቅጣጫ ርቆ ወደብ ላይ ከቆመ ወደፊት መሄድ አይችልም። ሁለተኛ፣ መርከበኛው ሸራውን ሙሉ በሙሉ መዘርጋት ይኖርበታል። ነፋሱ ቢኖርም እንኳ መርከቡ ወደፊት መጓዝ የሚችለው ነፋሱ ሸራውን ካገኘው ብቻ እንደሆነ የታወቀ ነው። በተመሳሳይ እኛም በይሖዋ አገልግሎት መጽናት የምንችለው የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ካገኘን ብቻ ነው። ይህ መንፈስ እንዲረዳን ከፈለግን ሁለት እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርብናል። በመጀመሪያ የአምላክን መንፈስ ለማግኘት በሚያስችሉን እንቅስቃሴዎች መካፈል አለብን። ሁለተኛ፣ በእነዚህ እንቅስቃሴዎች አቅማችን የፈቀደውን ያህል የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ በሌላ አባባል ሸራችንን ሙሉ በሙሉ መዘርጋት ይኖርብናል። (መዝ. 119:32) እነዚህን እርምጃዎች የምንወስድ ከሆነ መንፈስ ቅዱስ እንደ ማዕበል ያሉ ተቃውሞዎችንና ፈተናዎችን ተቋቁመን ወደፊት እንድንገፋ ይኸውም ወደ አምላክ አዲስ ዓለም በሚወስደው ጎዳና ላይ በታማኝነት መጓዛችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።

12. ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመረምራለን?

12 የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ የምናገኝባቸውን ሁለት መንገዶች ተመልክተናል። መንፈስ ቅዱስ፣ ኃይል የሚሰጠን ከመሆኑም ሌላ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያሉም ታማኝ ሆነን እንድንቀጥል ይረዳናል። በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ ወደፊት እንድንገፋ ይኸውም የዘላለም ሕይወት በሚያስገኘው ጎዳና ላይ መጓዛችንን እንድንቀጥል ይረዳናል። ከዚህ ቀጥሎ፣ ከመንፈስ ቅዱስ የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ማድረግ ያለብንን አራት ነገሮች እንመረምራለን።

ከመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13. በ2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17 መሠረት ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ጥቅም ያስገኙልናል? ሆኖም ከእኛ ምን ይጠበቃል?

13 አንደኛ፣ የአምላክን ቃል አጥና። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17ን አንብብ።) “በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “አምላክ የተነፈሰበት” የሚል ፍቺ አለው። አምላክ ሐሳቡን ለመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “ለመተንፈስ” ማለትም ሐሳቡን ለማስተላለፍ በቅዱስ መንፈሱ ተጠቅሟል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብና ባነበብነው ነገር ላይ ስናሰላስል የአምላክ ትምህርቶች ወደ አእምሯችንና ልባችን ጠልቀው ይገባሉ። በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉት እነዚህ ትምህርቶች ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወታችንን ለመምራት ያነሳሱናል። (ዕብ. 4:12) ከመንፈስ ቅዱስ የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ግን መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን የምናነብበትና ባነበብነው ነገር ላይ የምናሰላስልበት ጊዜ መመደብ ያስፈልገናል። የአምላክ ቃል በአነጋገራችንና በድርጊታችን ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችለው እንዲህ ስናደርግ ነው።

14. (ሀ) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ የመንፈስ ቅዱስ ነፋስ ይነፍሳል የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ሸራችንን ሙሉ በሙሉ የዘረጋን ያህል ከስብሰባዎች ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

14 ሁለተኛ፣ ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር ሆነህ ይሖዋን አምልክ። (መዝ. 22:22) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ የመንፈስ ቅዱስ ነፋስ ይነፍሳል ሊባል ይችላል። በስብሰባዎች ላይ የይሖዋ መንፈስ ይኖራል። (ራእይ 2:29) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ለአምልኮ ስንሰበሰብ፣ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት እንጸልያለን፤ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረቱትን የመንግሥቱን መዝሙሮች እንዘምራለን እንዲሁም በአምላክ ቅዱስ መንፈስ የተሾሙ ወንድሞች የሚያቀርቧቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች እናዳምጣለን። እህቶችም ክፍሎቻቸውን ተዘጋጅተው እንዲያቀርቡ የሚረዳቸው መንፈስ ቅዱስ ነው። ሆኖም ከመንፈስ ቅዱስ የተሟላ ጥቅም ማግኘት ከፈለግን በስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅተን መምጣት ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን ሸራችንን ሙሉ በሙሉ የዘረጋን ያህል ከስብሰባዎች መጠቀም እንችላለን።

15. መንፈስ ቅዱስ በአገልግሎታችን ላይ እንዲረዳን መፍቀድ የምንችለው እንዴት ነው?

15 ሦስተኛ፣ በስብከቱ ሥራ ተካፈል። ስንሰብክና ስናስተምር መጽሐፍ ቅዱስን የምንጠቀም ከሆነ መንፈስ ቅዱስ በአገልግሎታችን ላይ እንዲረዳን እየፈቀድን ነው። (ሮም 15:18, 19) ከአምላክ መንፈስ ሙሉ ጥቅም ማግኘት ከፈለግን ግን በስብከቱ ሥራ አዘውትረን መካፈልና ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን መጥቀስ ይኖርብናል። በአገልግሎትህ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ማድረግ የምትችለው አንዱ ነገር፣ በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ ላይ የሚገኙትን የውይይት ናሙናዎች መጠቀም ነው።

16. መንፈስ ቅዱስን ማግኘት የምንችልበት ቀጥተኛ መንገድ ምንድን ነው?

16 አራተኛ፣ ወደ ይሖዋ ጸልይ። (ማቴ. 7:7-11፤ ሉቃስ 11:13) መንፈስ ቅዱስን ማግኘት የምንችልበት ቀጥተኛ መንገድ ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን መጸለይ ነው። ጸሎታችን ወደ ይሖዋ እንዳይደርስ ሊያግድ ወይም የአምላክ መልካም ስጦታ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን እንዳናገኝ እንቅፋት ሊሆን የሚችል ምንም ነገር የለም፤ እስራትም ሆነ ራሱ ሰይጣንም እንኳ ይህን ማድረግ አይችሉም። (ያዕ. 1:17) ታዲያ ከመንፈስ ቅዱስ የተሟላ ጥቅም ለማግኘት እንዴት መጸለይ አለብን? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በሉቃስ ወንጌል ላይ ብቻ የተዘገበን አንድ ምሳሌ እስቲ እንመርምር። *

ሳታሰልሱ ጸልዩ

17. ኢየሱስ በሉቃስ 11:5-9, 13 ላይ ከተናገረው ምሳሌ ስለ ጸሎት ምን እንማራለን?

17 ሉቃስ 11:5-9, 13ን አንብብ። ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት እንዴት መጸለይ እንዳለብን ያሳያል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሰው የፈለገውን ነገር ማግኘት የቻለው ወዳጁን ‘በመወትወቱ’ ነው። ወደ ወዳጁ የሄደው በጣም ከመሸ በኋላ ቢሆንም እንኳ የእሱን እርዳታ መጠየቅ አላሳፈረውም። * ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ከጸሎት ጋር ያያያዘው እንዴት ነው? “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታሰልሱ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል” ብሏል። ታዲያ ከዚህ ምን እንማራለን? የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ማግኘት ከፈለግን ሳናሰልስ መጸለይ ይኖርብናል።

18. ኢየሱስ ከተናገረው ምሳሌ አንጻር ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጠን መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

18 ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ፣ ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን የሚሰጠን ለምን እንደሆነም ይጠቁመናል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ግለሰብ እንግዳውን ጥሩ አድርጎ ማስተናገድ ፈልጎ ነበር። ከመሸ በኋላ ለመጣው እንግዳው ምግብ ማቅረብ ቢፈልግም የሚያቀርብለት ምንም ነገር አልነበረውም። ኢየሱስ እንደገለጸው ጎረቤትየው የተጠየቀውን ዳቦ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነው ሰውየው ስለወተወተው ነው። ታዲያ ኢየሱስ ማስተማር የፈለገው ነገር ምንድን ነው? ፍጹም ያልሆነ ሰው፣ ጎረቤቱ ስለወተወተው ሊረዳው ፈቃደኛ ከሆነ ደግ የሆነው የሰማዩ አባታችንማ ሳያሰልሱ ለሚለምኑት አገልጋዮቹ መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጣቸው አያጠራጥርም! እንግዲያው ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን የምናቀርበውን ልመና እንደሚመልስልን በመተማመን መጸለይ እንችላለን።—መዝ. 10:17፤ 66:19

19. ድል እንደምናደርግ እርግጠኞች የምንሆነው ለምንድን ነው?

19 ሰይጣን እኛን ለመጣል ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርግም ድል አድራጊዎች እንደምንሆን እርግጠኞች ነን። ለምን? መንፈስ ቅዱስ በሁለት መንገዶች ስለሚረዳን ነው። በመጀመሪያ፣ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል። ሁለተኛ፣ አንድን መርከብ ወደ ወደብ እንደሚገፋ ነፋስ ሁሉ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ወዳዘጋጀው አዲስ ዓለም እስክንገባ ድረስ ይሖዋን ማገልገላችንን እንድንቀጥል ይረዳናል። እንግዲያው መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጠን እርዳታ የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ!

መዝሙር 41 እባክህ ጸሎቴን ስማ

^ አን.5 ይህ ርዕስ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ለመጽናት የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ያብራራል። በተጨማሪም ከመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን ይገልጻል።

^ አን.16 ጸሎት በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ እንደነበረው ከየትኛውም የወንጌል ጸሐፊ በላይ የዘገበው ሉቃስ ነው።—ሉቃስ 3:21፤ 5:16፤ 6:12፤ 9:18, 28, 29፤ 18:1፤ 22:41, 44

^ አን.17 በሐምሌ 2018 የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች ላይ የወጣውን ለሉቃስ 11:5-9 የተዘጋጀ ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት።

^ አን.60 የሥዕሉ መግለጫ፦ የመጀመሪያው እርምጃ፦ አንድ ወንድምና አንዲት እህት ወደ ስብሰባ አዳራሹ ሲገቡ። ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር መሰብሰባቸው የይሖዋ መንፈስ በሚኖርበት ፕሮግራም ላይ ለመገኘት ያስችላቸዋል። ሁለተኛው እርምጃ፦ ተዘጋጅተው በመምጣት በስብሰባ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ ነው። እነዚህ ሁለት እርምጃዎች በዚህ ርዕስ ላይ ከተጠቀሱት ሌሎች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ይኸውም የአምላክን ቃል ከማጥናት፣ በስብከቱ ሥራ ከመካፈል እንዲሁም ወደ ይሖዋ ከመጸለይ ጋር በተያያዘም ይሠራሉ።