በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 46

‘ትልቁን የእምነት ጋሻህን’ እያጠናከርከው ነው?

‘ትልቁን የእምነት ጋሻህን’ እያጠናከርከው ነው?

“ትልቅ የእምነት ጋሻ አንሱ።”—ኤፌ. 6:16

መዝሙር 119 ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል

ማስተዋወቂያ *

1-2. (ሀ) በኤፌሶን 6:16 መሠረት “ትልቅ የእምነት ጋሻ” የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (ለ) የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ እንመረምራለን?

“ትልቅ የእምነት ጋሻ” አለህ? (ኤፌሶን 6:16ን አንብብ።) እንዲህ ዓይነት ጋሻ እንዳለህ ምንም አያጠራጥርም። ትልቅ ጋሻ የአንድን ወታደር አብዛኛውን የሰውነት ክፍል ከጥቃት እንደሚከላከል ሁሉ፣ እምነትህም በሥነ ምግባር ብልግና እንዲሁም በዓመፅ የተሞላውና አምላክ የለሽ የሆነው ይህ ሥርዓት ከሚያሳድረው ተጽዕኖ ይጠብቅሃል።

2 ይሁንና የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” በመሆኑ እምነታችንን የሚፈትን ነገር ሁልጊዜ ያጋጥመናል። (2 ጢሞ. 3:1) ታዲያ የእምነት ጋሻህ ያለበትን ሁኔታ በመገምገም ጠንካራ መሆኑን ማረጋገጥ የምትችለው እንዴት ነው? ጋሻህን ምንጊዜም አጥብቀህ መያዝ የምትችለውስ እንዴት ነው? እስቲ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመልከት።

ጋሻህ ያለበትን ሁኔታ በጥንቃቄ ገምግም

ወታደሮች ከተዋጉ በኋላ ጋሻቸውን ይጠግናሉ (አንቀጽ 3⁠ን ተመልከት)

3. ወታደሮች ጋሻቸውን ምን ያደርጉ ነበር? ለምንስ?

3 በጥንት ዘመን ወታደሮች የሚይዙት ጋሻ ብዙውን ጊዜ በቆዳ ይለበጥ ነበር። ወታደሮቹ ቆዳው እንዳይበላሽና ከብረት የተሠሩት የጋሻው ክፍሎች እንዳይዝጉ ለማድረግ ጋሻቸውን ዘይት ይቀቡት ነበር። አንድ ወታደር ጋሻው ጉዳት እንደደረሰበት ካስተዋለ እንዲጠገን ያደርጋል፤ ይህም ለቀጣዩ ውጊያ ምንጊዜም ዝግጁ ለመሆን ያስችለዋል። ይህ ምሳሌ ከእምነታችን ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

4. የእምነት ጋሻህን መፈተሽ ያለብህ ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምትችለውስ እንዴት ነው?

4 በጥንት ዘመን እንደነበሩ ወታደሮች ሁሉ አንተም የእምነት ጋሻህን ዘወትር መፈተሽና መንከባከብ ያስፈልግሃል፤ ይህም ምንጊዜም ለውጊያ ዝግጁ እንድትሆን ያስችልሃል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በመንፈሳዊ ውጊያ ላይ ነን፤ ከጠላቶቻችን መካከል ደግሞ ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ይገኙበታል። (ኤፌ. 6:10-12) የእምነት ጋሻህ ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ የራስህ ኃላፊነት ነው። ታዲያ ፈተናዎችን ለመቋቋም ዝግጁ መሆን አለመሆንህን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ጸልይ። ከዚያም እምነትህ አምላክ በሚፈልገው ሁኔታ ላይ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ የአምላክን ቃል ተጠቅመህ ራስህን መርምር። (ዕብ. 4:12) መጽሐፍ ቅዱስ “በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ” ይላል። (ምሳሌ 3:5, 6) ይህን ነጥብ በአእምሮህ በመያዝ፣ በቅርብ ጊዜ ስላደረግካቸው ውሳኔዎች ለማሰብ ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ ከባድ የገንዘብ ችግር አጋጥሞህ ነበር? በዚህ ጊዜ በዕብራውያን 13:5 ላይ ይሖዋ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት የገባው ቃል ትዝ ብሎህ ነበር? ይህ ጥቅስ ይሖዋ እንደሚረዳህ እንድትተማመን ረድቶህ ነበር? ከሆነ የእምነት ጋሻህ ጠንካራ ነው ማለት ነው።

5. እምነትህን ስትመረምር ምን ልታስተውል ትችላለህ?

5 እምነትህን በጥንቃቄ ስትመረምር ያልጠበቅከው ነገር ልታገኝ ትችላለህ። እስካሁን ያላስተዋልካቸው አንዳንድ ድክመቶች እንዳሉብህ ትገነዘብ ይሆናል። ለምሳሌ ከልክ ያለፈ ጭንቀት፣ የሐሰት ወሬ እንዲሁም ተስፋ መቁረጥ እምነትህን እንዳዳከሙት ታስተውል ይሆናል። ታዲያ እምነትህን ለማጠናከር ምን ማድረግ ትችላለህ?

ጭንቀት፣ የሐሰት ወሬ እና ተስፋ መቁረጥ ከሚያስከትሉት ጉዳት ራስህን ጠብቅ

6. ስለ የትኞቹ ጉዳዮች መጨነቃችን ተገቢ ነው?

6 ስለ አንዳንድ ጉዳዮች መጨነቅ ተገቢ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋን እና ኢየሱስን ስለ ማስደሰት ልንጨነቅ ይገባል። (1 ቆሮ. 7:32) ከባድ ኃጢአት ሠርተን ከሆነ ደግሞ ከአምላክ ጋር ያለንን ወዳጅነት የማደሱ ጉዳይ ሊያስጨንቀን ይገባል። (መዝ. 38:18) ከዚህም ሌላ የትዳር ጓደኛችንን ስለ ማስደሰት ወይም የቤተሰባችንን አባላትና የእምነት ባልንጀሮቻችንን ስለ መንከባከብ መጨነቃችን ተገቢ ነው።—1 ቆሮ. 7:33፤ 2 ቆሮ. 11:28

7. በምሳሌ 29:25 መሠረት ሰውን መፍራት የሌለብን ለምንድን ነው?

7 በሌላ በኩል ግን ከልክ ያለፈ ጭንቀት እምነታችንን ሊያዳክመው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በቂ ምግብና ልብስ የማግኘታችን ጉዳይ ነጋ ጠባ ያስጨንቀን ይሆናል። (ማቴ. 6:31, 32) እንዲህ ያለው ጭንቀት ደግሞ ቁሳዊ ነገሮችን በማካበት ላይ እንድናተኩር ሊያደርገን ይችላል። እንዲያውም የገንዘብ ፍቅር ሊያድርብን ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ በይሖዋ ላይ ያለን እምነት መዳከሙና መንፈሳዊነታችን መጎዳቱ አይቀርም። (ማር. 4:19፤ 1 ጢሞ. 6:10) ከልክ ባለፈ ጭንቀት ልንዋጥ የምንችልበት ሌላም አቅጣጫ አለ፤ ይህም በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ስለ ማግኘት መጨነቅ ነው። እንዲህ ያለው ጭንቀት ይሖዋን ከማሳዘን የበለጠ ከሰዎች የሚሰነዘርብንን ፌዝ ወይም ስደትን እንድንፈራ ሊያደርገን ይችላል። እንዲህ ባለው ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ፣ ፈተናውን ለመቋቋም የሚያስችል እምነትና ድፍረት እንዲሰጠን ይሖዋን መለመን ይኖርብናል።ምሳሌ 29:25ን አንብብ፤ ሉቃስ 17:5

(አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት) *

8. የሐሰት ወሬዎችን በተመለከተ ምን አቋም ሊኖረን ይገባል?

8 “የውሸት አባት” የሆነው ሰይጣን በእሱ ቁጥጥር ሥር ባሉት ሰዎች በመጠቀም ስለ ይሖዋ እንዲሁም ስለ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሐሰት ወሬ ያዛምታል። (ዮሐ. 8:44) ለምሳሌ ከሃዲዎች በኢንተርኔት፣ በቴሌቪዥንና በሌሎች መገናኛ ብዙኃን በመጠቀም ስለ ይሖዋ ድርጅት የሐሰት ወሬዎችንና የተዛቡ መረጃዎችን ያሰራጫሉ። እነዚህ ውሸቶች የሰይጣን ‘የሚንበለበሉ ፍላጻዎች’ ናቸው። (ኤፌ. 6:16) አንድ ሰው እንዲህ ያሉ የሐሰት ወሬዎችን ሊነግረን ቢሞክር ምን ማድረግ ይኖርብናል? ፈጽሞ ልንሰማው አይገባም! ለምን? ምክንያቱም በይሖዋ ላይ እምነት አለን፤ በወንድሞቻችንም እንተማመናለን። እንዲያውም ከከሃዲዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዲኖረን አንፈልግም። ምን እንደሚሉ ለማወቅ በመጓጓትም እንኳ ስለ ማንኛውም ጉዳይ ከእነሱ ጋር ለመከራከር ፈቃደኞች አንሆንም።

9. ተስፋ መቁረጥ ሊጎዳን የሚችለው እንዴት ነው?

9 ተስፋ መቁረጥ እምነታችንን ሊያዳክመው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ችግሮች ሲያጋጥሙን ተስፋ እንቆርጥ ይሆናል። እርግጥ ስለ ችግሮቻችን ደንታ ቢስ መሆን የለብንም። ይሁን እንጂ ችግሮቻችን አስተሳሰባችንን እንዲቆጣጥሩት መፍቀድ አይኖርብንም። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ የሰጠን አስደናቂ ተስፋ ሊደበዝዝብን ይችላል። (ራእይ 21:3, 4) በዚህም የተነሳ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፤ ይህ ደግሞ ኃይላችንን ሊያሟጥጠውና ይሖዋን ማገልገላችንን እንድናቆም ሊያደርገን ይችላል። (ምሳሌ 24:10) ሆኖም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዳይደርስብን ማድረግ የምንችለው ነገር አለ።

10. አንዲት እህት ከጻፈችው ደብዳቤ ምን ትምህርት እናገኛለን?

10 በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር አንዲት እህት በጠና የታመመ ባለቤቷን ትንከባከባለች፤ ይህች እህት እምነቷ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ያደረገችው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ለዋናው መሥሪያ ቤታችን በጻፈችው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብላለች፦ “ያለንበት ሁኔታ አንዳንድ ጊዜ ውጥረት የሚፈጥርና ተስፋ አስቆራጭ ነው፤ ያም ቢሆን በተስፋችን ላይ ጠንካራ እምነት አለን። ከድርጅቱ ለምናገኛቸው እምነት የሚያጠናክሩና የሚያበረታቱ ትምህርቶች በጣም አመስጋኝ ነኝ። እንዲህ ያለውን ምክርና ማበረታቻ ማግኘታችን በጣም ጠቅሞናል። እንድንጸና እንዲሁም ሰይጣን የሚያመጣብንን ፈተናዎች እንድንቋቋም ይረዳናል።” ይህች እህት የሰጠችው ሐሳብ፣ የተስፋ መቁረጥ ስሜትን መቋቋም እንደምንችል ያስተምረናል። ይህን ስሜት መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? የሚያጋጥሙንን ችግሮች የሰይጣን ፈተና አድርገን እንመልከታቸው። ይሖዋ መጽናኛ እንደሚሰጠን አንዘንጋ። እንዲሁም ይሖዋ ለሚያዘጋጅልን መንፈሳዊ ምግብ አድናቆት ይኑረን።

‘ትልቁን የእምነት ጋሻህን’ እያጠናከርከው ነው? (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት) *

11. እምነታችን ጠንካራ መሆኑን ለመገምገም የትኞቹ ጥያቄዎች ይረዱናል?

11 የእምነት ጋሻህ ማጠናከሪያ የሚያስፈልገው አቅጣጫ እንዳለ ይሰማሃል? እስቲ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ስለነበረህ ሁኔታ አስብ፤ ከልክ በላይ ላለመጨነቅ ያደረግከው ጥረት ተሳክቶልሃል? የከሃዲዎችን የሐሰት ወሬ ለመስማት ወይም ከእነሱ ጋር ለመከራከር ብትፈተንም ፈተናውን መወጣት ችለሃል? የተስፋ መቁረጥ ስሜትን መቋቋም ችለሃል? ከሆነ እምነትህ ጠንካራ ነው ማለት ነው። ያም ቢሆን መዘናጋት የለብህም፤ ምክንያቱም ሰይጣን እኛን ለማጥቃት የሚጠቀምባቸው ሌሎች ዘዴዎችም አሉ። እስቲ ከእነዚህ አንዱን እንመልከት።

ከፍቅረ ንዋይ ራስህን ጠብቅ

12. ፍቅረ ንዋይ ምን ጉዳት ሊያስከትልብን ይችላል?

12 ፍቅረ ንዋይ ትኩረታችን እንዲከፋፈልና የእምነት ጋሻችንን ችላ እንድንል ሊያደርገን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ወታደር ሆኖ የሚያገለግል ማንኛውም ሰው ለውትድርና የመለመለውን ሰው ደስ ማሰኘት ስለሚፈልግ ራሱን በንግድ ሥራ አያጠላልፍም።” (2 ጢሞ. 2:4) እንዲያውም የሮም ወታደሮች በሌላ በማንኛውም ሥራ እንዲካፈሉ አይፈቀድላቸውም ነበር። አንድ ወታደር ይህን ደንብ ቢተላለፍ ምን ሊፈጠር ይችላል?

13. አንድ ወታደር በንግድ ሥራ መጠላለፍ የሌለበት ለምንድን ነው?

13 እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ ለማሰብ ሞክር። የተወሰኑ ወታደሮች በማለዳ ተነስተው ወታደራዊ ልምምድ እያደረጉ ነው፤ ሆኖም የቡድናቸው አባል የሆነ አንድ ወታደር በልምምዱ ላይ አልተገኘም። ይህ ወታደር ገበያ ላይ ምግብ ለመሸጥ ጉድ ጉድ እያለ ነው። አመሻሹ ላይ ወታደሮቹ የጦር ትጥቃቸውን ይፈትሻሉ እንዲሁም ሰይፋቸውን ይስላሉ። ምግብ የሚሸጠው ወታደር ግን በቀጣዩ ቀን የሚያቀርበውን ምግብ እያዘጋጀ ነው። በቀጣዩ ቀን ማለዳ ላይ የጠላት ሠራዊት ድንገተኛ ጥቃት ሰነዘረ። ታዲያ በዚህ ጊዜ ለውጊያው ዝግጁ የሚሆነውና አዛዡን ማስደሰት የሚችለው የትኛው ወታደር ነው? አንተ በውጊያው ላይ ብትሆን ከጎንህ እንዲሰለፍ የምትመርጠው ለውጊያ የተዘጋጀውን ወታደር ነው? ወይስ ትኩረቱ የተከፋፈለውን ወታደር?

14. የክርስቶስ ወታደሮች እንደመሆናችን መጠን አስበልጠን የምናየው ነገር ምንድን ነው?

14 ዝግጁ እንደሆኑት ወታደሮች ሁሉ እኛም ዋነኛው ግባችን አዛዦቻችንን ይኸውም ይሖዋንና ክርስቶስን ማስደሰት ነው፤ ትኩረታችን ተከፋፍሎ ይህን ከማድረግ ወደኋላ ማለት አንፈልግም። ይሖዋንና ኢየሱስን ማስደሰት፣ የሰይጣን ዓለም ከሚያቀርብልን ከማንኛውም ነገር እንደሚበልጥ ይሰማናል። በመሆኑም ይሖዋን ለማገልገል እንዲሁም የእምነት ጋሻችንንና ሌሎች መንፈሳዊ የጦር ትጥቆቻችንን ለማጠናከር የሚሆን ጊዜና ጉልበት ላለማጣት ጥረት እናደርጋለን።

15. ጳውሎስ ምን ማሳሰቢያ ሰጥቶናል? ለምንስ?

15 ምንጊዜም ቢሆን መዘናጋት የለብንም! ለምን? ሐዋርያው ጳውሎስ “ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ . . . ከእምነት ጎዳና ስተው ወጥተዋል” በማለት አሳስቧል። (1 ጢሞ. 6:9, 10) “ስተው ወጥተዋል” የሚለው አገላለጽ፣ አላስፈላጊ ቁሳዊ ነገሮችን ለማከማቸት መሞከር ትኩረታችን እንዲከፋፈል ሊያደርግ እንደሚችል ይጠቁማል። እንዲህ ያለው አካሄድ ደግሞ ‘ከንቱና ጎጂ የሆኑ ብዙ ምኞቶች’ በልባችን ውስጥ እንዲያቆጠቁጡ ሊያደርግ ይችላል። እንደነዚህ ያሉ ምኞቶች እንዲያድሩብን ከመፍቀድ ይልቅ ሰይጣን እኛን ለማጥቃት የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች መሆናቸውን ማስተዋል ይኖርብናል።

16. በማርቆስ 10:17-22 ላይ የሚገኘው ዘገባ የትኞቹን ጥያቄዎች እንድናስብባቸው ሊያነሳሳን ይገባል?

16 ብዙ ቁሳዊ ነገሮች ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ አለን እንበል። ታዲያ ያማሩንን ሆኖም የግድ የማያስፈልጉንን ነገሮች ብንገዛ ስህተት ነው? ስህተት ነው ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልናስብባቸው ይገባል፦ አንድን ዕቃ የመግዛት አቅም ቢኖረንም እንኳ ዕቃውን ለመጠቀምም ሆነ በአግባቡ ለመያዝ የሚያስፈልገው ጊዜና ጉልበት አለን? በተጨማሪም ለቁሳዊ ንብረታችን ከልክ ያለፈ ፍቅር እናዳብር ይሆን? ደግሞስ አምላክን ይበልጥ እንዲያገለግል ኢየሱስ ያቀረበለትን ግብዣ መቀበል እንደከበደው ወጣት ሁሉ እኛም ለቁሳዊ ነገሮች ያለን ፍቅር እንቅፋት ይሆንብን ይሆን? (ማርቆስ 10:17-22ን አንብብ።) ከዚህ በተቃራኒ አኗኗራችንን ቀላል በማድረግ፣ ውድ የሆነውን ጊዜያችንን እና ጉልበታችንን የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ብንጠቀምበት ምንኛ የተሻለ ይሆናል!

የእምነት ጋሻህን አጥብቀህ ያዝ

17. ፈጽሞ ልንረሳው የማይገባው ነገር ምንድን ነው?

17 ጦርነት ላይ እንዳለንና በየዕለቱ ለውጊያ ዝግጁ መሆን እንዳለብን ፈጽሞ መርሳት አይኖርብንም። (ራእይ 12:17) የእምነት ጋሻችንን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ሊይዙልን አይችሉም። ጋሻችንን አጥብቀን መያዝ ያለብን እኛው ራሳችን ነን።

18. በጥንት ዘመን የነበሩ ወታደሮች ጋሻቸውን አጥብቀው የሚይዙት ለምን ነበር?

18 በጥንት ዘመን አንድ ወታደር በጦርነት ወቅት ላሳየው ድፍረት ክብር ይሰጠው ነበር። ይሁንና ይህ ወታደር ጋሻውን ሳይዝ ቢመለስ ውርደት ይሆንበታል። ሮማዊው የታሪክ ጸሐፊ ታሲተስ “ጋሻ ሳይዙ ከጦርነት መመለስ ከሁሉ የከፋ ውርደት ነበር” በማለት ጽፏል። ወታደሮች ጋሻቸውን አጥብቀው የሚይዙበት አንዱ ምክንያት ይህ ነበር።

አንዲት እህት የአምላክን ቃል ትኩረት ሰጥታ በማንበብ፣ አዘውትራ በስብሰባ ላይ በመገኘትና በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ በማድረግ ትልቁን የእምነት ጋሻዋን አጥብቃ ለመያዝ ስትጥር (አንቀጽ 19⁠ን ተመልከት)

19. የእምነት ጋሻችንን አጥብቀን ለመያዝ ምን ይረዳናል?

19 የእምነት ጋሻችንን አጥብቀን መያዝ እንድንችል፣ አዘውትረን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲሁም ስለ ይሖዋ ስምና ስለ መንግሥቱ ለሌሎች መናገር ይኖርብናል። (ዕብ. 10:23-25) በተጨማሪም የአምላክን ቃል በየቀኑ ትኩረት ሰጥተን ማንበብ እንዲሁም በውስጡ የሚገኘውን ምክርና መመሪያ በመላ ሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ አለብን። (2 ጢሞ. 3:16, 17) እንዲህ ካደረግን ሰይጣን የሚጠቀምበት የትኛውም መሣሪያ ዘላቂ ጉዳት ሊያደርስብን አይችልም። (ኢሳ. 54:17) ‘ትልቁ የእምነት ጋሻችን’ የሚሰነዘርብንን ጥቃት ይከላከልልናል። ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ጸንተን እንቆማለን። እንዲሁም በየቀኑ የምንገጥመውን ውጊያ ከማሸነፍም አልፈን ወደፊት ኢየሱስ ከሰይጣንና ከተከታዮቹ ጋር በሚያካሂደው ጦርነት ድል ሲነሳ ከእሱ ጎን የመሰለፍ መብት እናገኛለን።—ራእይ 17:14፤ 20:10

መዝሙር 118 “እምነት ጨምርልን”

^ አን.5 ወታደሮች ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል ጋሻ ይይዙ ነበር። እምነታችን ለእኛም እንደ ጋሻ ነው። ልክ እንደ ወታደሮች ሁሉ እኛም የእምነት ጋሻችንን ማጠናከር ያስፈልገናል። ይህ ርዕስ፣ ‘ትልቁ የእምነት ጋሻችን’ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ምን ማድረግ እንዳለብን ያብራራል።

^ አን.58 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ቴሌቪዥን እየተመለከተ ሳለ ከሃዲዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የሐሰት ወሬ ሲያቀርቡ አባትየው ቴሌቪዥኑን ወዲያውኑ አጠፋው።

^ አን.60 የሥዕሉ መግለጫ፦ በኋላ ላይ በቤተሰብ አምልኮ ወቅት አባትየው መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም የቤተሰቡን እምነት ሲያጠናክር ይታያል።