በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ሕይወቴ ዓላማ እንዲኖረው ያደረግሁት ጥረት

ሕይወቴ ዓላማ እንዲኖረው ያደረግሁት ጥረት

በሜድትራንያን ባሕር መሃል ላይ ሳለሁ አሮጌዋ ጀልባዬ ቀዳዳ እንዳላትና ብዙ ውኃ እያስገባች እንደሆነ ተመለከትኩ፤ በዚህ ጊዜ በጣም ደነገጥኩ። ከዚያ ደግሞ ማዕበል ተነሳ። በጣም ስለፈራሁ ከረጅም ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጸለይኩ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ የገባሁት እንዴት ነው? እስቲ ከመጀመሪያው አንስቶ ታሪኬን ላጫውታችሁ።

የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ፣ እኔና ቤተሰቤ በብራዚል ስንኖር

የተወለድኩት በ1948 በኔዘርላንድስ ነው። በቀጣዩ ዓመት ወደ ሳኦ ፓውሎ፣ ብራዚል ሄድን። ወላጆቼ አዘውትረው ቤተ ክርስቲያን ይሄዱ ነበር፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከራት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን አብረን እናነብ ነበር። በ1959 ደግሞ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተዛወርን፤ እዚያም በማሳቹሴትስ ግዛት መኖር ጀመርን።

አባቴ ስምንት አባላት ያሉትን ቤተሰባችንን ለማስተዳደር ተግቶ ይሠራ ነበር። የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቷል፦ ተጓዥ የሽያጭ ሠራተኛ ነበር፤ በመንገድ ሥራ ድርጅት ውስጥ የሠራበት ጊዜ አለ፤ በዓለም አቀፍ አየር መንገድ ውስጥም የሽያጭ ሠራተኛ ነበር። አባቴ በአየር መንገድ ውስጥ መሥራት ሲጀምር ሁላችንም በጣም ተደስተን ነበር፤ ምክንያቱም ወደተለያዩ ቦታዎች መጓዝ ያስችለናል።

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለሁ ‘ሳድግ ምንድን ነው የምሆነው?’ የሚለው ጉዳይ ብዙ ጊዜ ያሳስበኝ ነበር። አንዳንዶቹ ጓደኞቼ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ወሰኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ ጦር ሠራዊቱን ተቀላቀሉ። እኔ ግን ውጊያ ቀርቶ ጭቅጭቅ እንኳ በጣም ያስጠላኝ ነበር፤ ስለዚህ ጦር ሠራዊቱ ውስጥ መግባት ጨርሶ የማላስበው ነገር ነበር። ጦር ሠራዊቱን ላለመቀላቀል ስል ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ወሰንኩ። ዋነኛው ፍላጎቴ ግን ሌሎችን መርዳት ነበር፤ ይህን ማድረጌ ለሕይወቴ ትርጉም እንደሚሰጠው ተሰምቶኝ ነበር።

የዩኒቨርሲቲ ሕይወቴ

ለበርካታ ዓመታት የሕይወትን ትርጉም ስፈልግ ኖሬያለሁ

ዩኒቨርሲቲ ሳለሁ አንትሮፖሎጂ (የሰው ዘር ጥናት) ትኩረቴን ሳበው፤ ምክንያቱም ስለ ሕይወት አመጣጥ ማወቅ እፈልግ ነበር። ስለ ዝግመተ ለውጥ የተማርን ሲሆን ይህ ጽንሰ ሐሳብ እውነት መሆኑን እንድንቀበል ይጠበቅብን ነበር። ሆኖም አንዳንዶቹ ማብራሪያዎች ምክንያታዊ ያልሆኑና በጭፍን ማመንን የሚጠይቁ እንደሆኑ ተሰማኝ፤ ይህ ደግሞ ከሳይንሳዊው ዘዴ ጋር ይጋጫል።

ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የግብረ ገብነት ትምህርት አልተሰጠንም። ከዚህ ይልቅ ስኬት ለማግኘት ስንል ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ እንዳንል እንበረታታ ነበር። ከጓደኞቼ ጋር ፓርቲ መሄድና ዕፅ መውሰድ የደስታ ስሜት እንዲሰማኝ አደረገ፤ ግን ይህ ደስታ ጊዜያዊ ነበር። ‘በእርግጥ ሕይወቴ ዓላማ አለው ሊባል ይችላል?’ ብዬ አሰብኩ።

በዚያ መሃል ወደ ቦስተን ከተማ ተዛውሬ እዚያ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መማር ጀመርኩ። የትምህርት ወጪዬን ለመሸፈን ትምህርት ቤት ሲዘጋ እሠራ ነበር፤ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘሁት ያኔ ነው። አንዱ የሥራ ባልደረባዬ በዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ የሚገኘውን ስለ “ሰባት ዘመናት” የሚገልጽ ትንቢት አብራራልኝ፤ እንዲሁም የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እንደሆነ ነገረኝ። (ዳን. 4:13-17) ከእሱ ጋር መወያየቴን ከቀጠልኩና በሚነግረኝ ነገር ካመንኩ አኗኗሬን መቀየር እንደሚያስፈልገኝ ወዲያውኑ ገባኝ። ስለዚህ ይህን የሥራ ባልደረባዬን እሸሸው ጀመር።

ዩኒቨርሲቲ ሳለሁ፣ ደቡብ አሜሪካ ሄጄ የበጎ ፈቃደኝነት ሥራ ለመሥራት የሚያዘጋጁ ኮርሶች ወስጃለሁ። ለሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ መስጠት ሕይወቴ ዓላማ ያለው እንዲሆን ያደርጋል ብዬ አስቤ ነበር። ግን ይህም ቢሆን ዓላማ ያለው ሕይወት ለመምራት እንደማያስችል ተገነዘብኩ። ግራ ስለተጋባሁ በሴሚስተሩ መጨረሻ ላይ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን አቋረጥኩ።

ወደተለያዩ አገሮች ስጓዝም የሕይወትን ዓላማ መፈለጌን ቀጠልኩ

ግንቦት 1970 ወደ አምስተርዳም፣ ኔዘርላንድስ ተዛውሬ አባቴ ይሠራ በነበረበት አየር መንገድ ውስጥ መሥራት ጀመርኩ። በዚህ ሥራ ምክንያት ወደተለያዩ አገሮች መጓዝ ችያለሁ፤ በአፍሪካ፣ በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ፣ በአውሮፓ እንዲሁም በሩቅ ምሥራቅ ወደሚገኙ የተለያዩ አገሮች ሄጃለሁ። የሄድኩባቸው አገሮች በሙሉ ትላልቅ ችግሮች እንዳሉባቸውና ችግሮቹን መፍታት የቻለ ማንም እንደሌለ አስተዋልኩ። በሕይወቴ ጠቃሚ ነገር ለማከናወን ያለኝ ፍላጎት እንደገና ስለተቀሰቀሰ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመልሼ ቦስተን በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትምህርቴን ለመቀጠል ወሰንኩ።

ወደ ዩኒቨርሲቲ ከተመለስኩ ብዙም ሳይቆይ ግን ሕይወትን በተመለከተ ያሉኝ ጥያቄዎች አሁንም እንዳልተመለሱልኝ ተገነዘብኩ። ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ስለገባኝ የአንትሮፖሎጂ ፕሮፌሰሬን ምክር ጠየቅሁት። እሱም የሚያስገርም ምክር ሰጠኝ፦ “ታዲያ ለምን ትቀጥላለህ? ለምን አሁኑኑ ትምህርትህን አታቋርጥም?” አለኝ። ይህን ሲለኝ ሁለቴ ማሰብ አላስፈለገኝም። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን እርግፍ አድርጌ ተውኩት።

ይሁን እንጂ አሁንም ሕይወቴ ትርጉም እንዳለው አልተሰማኝም፤ ስለዚህ የሂፒዎች ዓይነት ሕይወት ለመምራት ወሰንኩ። ከአንዳንድ ጓደኞቼ ጋር ዩናይትድ ስቴትስን አቋርጠን ከተጓዝን በኋላ አካፑልኮ፣ ሜክሲኮ ደረስን። ከሂፒዎች ጋር በጋራ እንኖር ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ማኅበረሰቡ የሚከተላቸውን መሥፈርቶች የማይቀበሉ ሲሆን ሕይወታቸው ጭንቀት የሌለበት ይመስል ነበር። ሆኖም አብሬያቸው መኖር ከጀመርኩ ብዙም ሳይቆይ፣ የሚከተሉት የሕይወት ጎዳና ትርጉም እንደሌለውና ዘላቂ ደስታ እንደማያስገኝ ተገነዘብኩ። እንዲያውም በእነሱ መካከል ውሸትና ታማኝነት ማጉደል የተለመደ ነገር ነበር።

ፍለጋዬን በጀልባ ቀጠልኩ

እኔና ጓደኛዬ ውብ የሆነ ደሴት ስንፈልግ

በዚህ መሃል በልጅነቴ የነበረኝ ሕልም ተቀሰቀሰ። ባሕር ላይ የመጓዝ ምኞት ነበረኝ፤ ሆኖም የምፈልገው ተሳፋሪ ሳይሆን ካፒቴን ሆኜ መጓዝ ነበር። ይህን ማድረግ የምችልበት ብቸኛው መንገድ ደግሞ የራሴን ጀልባ መግዛት ነበር። ቶም የተባለው ጓደኛዬም ተመሳሳይ ፍላጎት ነበረው፤ ስለዚህ አብረን ዓለምን በጀልባ ለመዞር ወሰንን። በማኅበረሰቡ ደንቦች ሳልታሰር የምኖርበት ውብ የሆነ ደሴት ማግኘት ፈልጌ ነበር።

እኔና ቶም በባርሴሎና፣ ስፔን አቅራቢያ ወደምትገኘው ወደ አሬንስ ደ ማር ተጓዝን። በዚያም 9 ሜትር ርዝመት ያላት ሊግራ የተባለች ጀልባ ገዛን። ጀልባዋ ውቅያኖስ ላይ መጓዝ እንድትችል ጥገና አደረግንላት። ያሰብነው ቦታ ለመድረስ የሚያስቸኩለን ነገር ስለሌለ የጀልባዋን ሞተር አውጥተን ቦታውን ተጨማሪ የመጠጥ ውኃ ለማስቀመጥ ተጠቀምንበት። በጠባብ ወደቦች ላይ ጀልባዋን ማንቀሳቀስ እንዲመቸን ሁለት ባለ 5 ሜትር መቅዘፊያዎች ገዛን። በመጨረሻም በሕንድ ውቅያኖስ ላይ ወደሚገኘው ወደ ሲሸልስ መጓዝ ጀመርን። የአፍሪካን ምዕራባዊ ዳርቻ ይዘን ከተጓዝን በኋላ በኬፕ ኦቭ ጉድ ሆፕ፣ ደቡብ አፍሪካ በኩል ዞረን ወደ ሲሸልስ ለመሄድ አቅደን ነበር። ትክክለኛውን አቅጣጫ ይዘን ለመጓዝ ኮከቦችን፣ የኮከብ ካርታዎችን፣ መጻሕፍትን እና አንዳንድ አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያዎችን እንጠቀም ነበር። ያለንበትን ቦታ በትክክል ማወቅ የምንችል መሆኑ በጣም አስደነቀኝ።

ብዙም ሳይቆይ ግን አሮጌዋ የእንጨት ጀልባችን ውቅያኖስ አቋርጣ መጓዝ እንደማትችል ተገነዘብን። በሰዓት ከ20 ሊትር በላይ ውኃ ታስገባ ነበር! በመግቢያው ላይ እንደጠቀስኩት በአንድ ወቅት ማዕበል ሲያጋጥመን በጣም ስለፈራሁ ከብዙ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አምላክ ጸለይኩ። በሕይወት ከተረፍን እሱን ለማወቅ ጥረት እንደማደርግ ለአምላክ ቃል ገባሁለት። ቀስ በቀስ ባሕሩ ተረጋጋ፤ እኔም ቃሌን ጠበቅኩ።

እዚያው ባሕሩ ላይ እያለን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀመርኩ። ሜድትራንያን ባሕር መሃል ላይ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ አስቡት። በዙሪያዬ ከሚዋኙት ዶልፊኖች እና የተለያየ ዝርያ ያላቸው ዓሦች እንዲሁም በርቀት ከሚታየው አድማስ በቀር ሌላ ምንም ነገር አልነበረም። ማታ ላይ በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ ስመለከት በጣም እደነቅ ነበር። ይህም ለሰው ልጆች የሚያስብ አምላክ እንዳለ ይበልጥ እርግጠኛ እንድሆን አደረገኝ።

ለተወሰኑ ሳምንታት ባሕር ላይ ከቆየን በኋላ በአሊካንቴ፣ ስፔን ወደሚገኘው ወደብ ደረስን። እዚያም የተሻለ ጀልባ ለመግዛት ስንል ጀልባችንን የሚገዛን ሰው መፈለግ ጀመርን። ጀልባችን አሮጌ፣ ሞተር የሌላትና ውኃ የምታስገባ ከመሆኗ አንጻር ገዢ ማግኘት ቀላል አልነበረም። በሌላ በኩል ግን በዚህ ወቅት መጽሐፍ ቅዱሴን ለማንበብ ሰፊ ጊዜ ማግኘት ቻልኩ።

መጽሐፍ ቅዱስን ባነበብኩ መጠን ለሕይወታችን የሚጠቅም መመሪያ የያዘ መጽሐፍ እንደሆነ ይበልጥ እርግጠኛ ሆንኩ። መጽሐፍ ቅዱስ ንጹሕ ሥነ ምግባር መከተልን በተመለከተ የያዘው መመሪያ በጣም ግልጽ ነው፤ ያም ሆኖ እኔን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ክርስቲያን ነን እያሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች ችላ የሚሉት ለምን እንደሆነ ሳስብ በጣም ተገረምኩ።

በሕይወቴ ላይ ትልቅ ለውጥ ለማድረግ ወሰንኩ፤ ስለዚህ ዕፅ መውሰድ አቆምኩ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚመሩ ሰዎች መኖር አለባቸው ብዬ አሰብኩ፤ እነዚህን ሰዎች ለማግኘትም ተነሳሳሁ። ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አምላክ በመጸለይ እነዚህን ሰዎች ለማግኘት እንዲረዳኝ ጠየቅኩት።

እውነተኛውን ሃይማኖት ለማግኘት ያደረግኩት ፍለጋ

እውነተኛውን ሃይማኖት እስካገኝ ድረስ እያንዳንዱን ሃይማኖት ለመመርመር ወሰንኩ። በአሊካንቴ ጎዳናዎች ላይ ስዘዋወር በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ተመለከትኩ። ሆኖም ብዙዎቹ ምስሎች ስለነበሯቸው እውነተኛው ሃይማኖት በዚያ እንደማይገኝ ለማወቅ አልከበደኝም።

አንድ እሁድ ቀን ከሰዓት በኋላ ላይ የባሕሩን ዳርቻ ማየት በምችልበት ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሆኜ ያዕቆብ 2:1-5⁠ን እያነበብኩ ነበር፤ ጥቅሱ ለሀብታሞች ማዳላት ተገቢ እንዳልሆነ ይናገራል። ወደ ጀልባችን እየተመለስኩ ሳለ የሃይማኖት ስብሰባ የሚደረግበት ቦታ የሚመስል ሕንፃ ተመለከትኩ። መግቢያው ላይ “የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ” የሚል ምልክት ተሰቅሏል።

‘እስቲ እነዚህን ሰዎች ልፈትናቸው፤ እንዴት እንደሚቀበሉኝ አያለሁ’ ብዬ በማሰብ ወደ አዳራሹ ገባሁ። ባዶ እግሬን ነበርኩ፣ ጢሜ አድጎ ነበር፤ እንዲሁም የለበስኩት የተቀዳደደ ጅንስ ነው። አስተናጋጁ ከአንዲት አረጋዊት ሴት ጎን አስቀመጠኝ፤ እሳቸውም ተናጋሪው የሚጠቅሳቸውን ጥቅሶች አውጥቼ እንድከታተል ረዱኝ። ስብሰባው ካለቀ በኋላ ሁሉም ሰዎች መጥተው በደግነት ሰላም ሲሉኝ በጣም ተደነቅሁ። አንደኛው ሰው ቤቱ ሄጄ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንድንወያይ ሐሳብ አቀረበልኝ፤ እኔ ግን ገና መጽሐፍ ቅዱስን አንብቤ ስላልጨረስኩ “ዝግጁ ስሆን እነግርሃለሁ” አልኩት። እስከዚያው ግን በሁሉም ስብሰባዎች ላይ እገኝ ነበር።

ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ወደ ሰውየው ቤት ሄድኩ፤ እሱም ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎቼ መልስ ሰጠኝ። ከአንድ ሳምንት በኋላ ደግሞ በርከት ያሉ ቆንጆ ቆንጆ ልብሶች ሰጠኝ። ከዚያም የልብሶቹ ባለቤት፣ መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርስ እንድንዋደድና ጦርነት እንዳንማር የሚሰጠውን መመሪያ በመታዘዙ ምክንያት እስር ቤት እንዳለ ነገረኝ። (ኢሳ. 2:4፤ ዮሐ. 13:34, 35) በዚህ ጊዜ፣ ስፈልግ የነበረውን ነገር ይኸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ግልጽ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚከተሉ ሰዎችን እንዳገኘሁ እርግጠኛ ሆንኩ! አሁን ግቤ ውብ የሆነ ደሴት ማግኘት መሆኑ ቀርቶ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ማጥናት ሆነ። ስለዚህ ወደ ኔዘርላንድስ ተመለስኩ።

ሥራ ፍለጋ

እኔ ወደምፈልገው ቦታ የሚሄዱ መኪኖችን እንዲያሳፍሩኝ እየጠየቅኩ ለአራት ቀናት ከተጓዝኩ በኋላ በኔዘርላንድስ ወደምትገኘው ግሮኒንገን ከተማ ደረስኩ። ራሴን ለማስተዳደር ሥራ ማግኘት ነበረብኝ። በአንድ የእንጨት ሥራ ድርጅት ውስጥ ለመቀጠር ሳመለክት ማመልከቻው ላይ ሃይማኖት የሚል ጥያቄ ነበር። እኔም “የይሖዋ ምሥክር” ብዬ ጻፍኩ። ባለቤቱ ይህን ሲያይ ፊቱ ተለዋወጠ። “ደውዬ እጠራሃለሁ” አለኝ፤ ግን አልደወለልኝም።

ከዚያም ወደ ሌላ የእንጨት ሥራ ድርጅት ሄጄ ባለቤቱን ሠራተኛ ይፈልግ እንደሆነ ጠየቅኩት። እሱም የትምህርት ማስረጃ እና የሥራ ልምድ እንዳቀርብ ጠየቀኝ። እኔም የእንጨት ጀልባዬን እጠግን እንደነበር ነገርኩት። እሱም እንዲህ አለኝ፦ “ዛሬ ከሰዓት ሥራ መጀመር ትችላለህ፤ ግን ከአንተ የሚጠበቅ አንድ ነገር አለ። እኔ የይሖዋ ምሥክር ነኝ፤ የምመራውም በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ነው። ስለዚህ በሱቄ ውስጥ ምንም ዓይነት ችግር እንድትፈጥር አልፈልግም።” እኔም በጣም ተገርሜ “እኔም እኮ የይሖዋ ምሥክር ነኝ!” አልኩት። እሱ ግን ረጅሙን ፀጉሬንና ጢሜን ስላየ የይሖዋ ምሥክር እንዳልሆንኩ አውቆ ነበር። “ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን አስጠናሃለሁ!” አለኝ። እኔም ግብዣውን በደስታ ተቀበልኩ። ቀደም ሲል ያመለከትኩበት ሰውዬ ለምን እንዳልጠራኝ አሁን ገባኝ፤ ይሖዋ የልቤን መሻት ሊሰጠኝ ፈልጎ ነበር። (መዝ. 37:4) በዚያ ወንድም ድርጅት ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል ሠራሁ፤ በዚያ ጊዜ ውስጥ ከእሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጠናሁ፤ ከዚያም ጥር 1974 ተጠመቅኩ።

በመጨረሻም ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት ቻልኩ!

ከአንድ ወር በኋላ አቅኚነት ጀመርኩ። አቅኚነት ጥልቅ እርካታ ያለው ሕይወት እንድመራ አስችሎኛል። በቀጣዩ ወር በአምስተርዳም አዲስ በተቋቋመው የስፓንኛ ቡድን ውስጥ ለማገልገል ስል ወደዚያ ተዛወርኩ። በስፓንኛና በፖርቱጋልኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት በመቻሌ በጣም ተደሰትኩ! ግንቦት 1975 ልዩ አቅኚ ሆኜ የማገልገል መብት አገኘሁ።

አንድ ቀን፣ ኢኔኬ የተባለች ልዩ አቅኚ ከቦሊቪያ የመጣችውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷን ልታስተዋውቀን ወደ ስፓንኛ ቡድናችን መጣች። እኔና ኢኔኬ ደብዳቤ እየተጻጻፍን ይበልጥ ለመተዋወቅ ወሰንን፤ ብዙም ሳይቆይ ተመሳሳይ ግብ እንዳለን ተገነዘብን። በ1976 ተጋብተን በልዩ አቅኚነት ማገልገላችንን ቀጠልን፤ በ1982 ደግሞ በጊልያድ ትምህርት ቤት 73ኛው ክፍል እንድንማር ተጋበዝን። በምሥራቅ አፍሪካ እንድናገለግል ስንመደብ በጣም ተገርመንና ተደስተን ነበር! በሞምባሳ፣ ኬንያ ለአምስት ዓመታት አገልግለናል። በ1987 በታንዛንያ እንድናገለግል ተመደብን፤ በወቅቱ በታንዛንያ በሥራችን ላይ የተጣለው እገዳ ተነስቶ ነበር። ለ26 ዓመታት በዚያ ካገለገልን በኋላ ወደ ኬንያ ተመለስን።

እኔና ባለቤቴ በምሥራቅ አፍሪካ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች የማስተማር መብት በማግኘታችን በጣም ተደስተናል

ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማስተማር ሕይወታችን እውነተኛ ትርጉም ያለው እንዲሆን አድርጓል። ለምሳሌ በሞምባሳ የነበረኝ የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መንገድ ላይ ሳገለግል ያገኘሁት ሰው ነበር። ሁለት መጽሔቶችን ሳበረክትለት “እነዚህን አንብቤ ከጨረስኩ በኋላስ ምን ላድርግ?” አለኝ። በቀጣዩ ሳምንት፣ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅመን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርን፤ በወቅቱ ይህ መጽሐፍ በስዋሂሊ ቋንቋ ገና መውጣቱ ነበር። ሰውየው ከአንድ ዓመት በኋላ ተጠመቀ፤ ከዚያም የዘወትር አቅኚ ሆነ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ እሱና ባለቤቱ 100 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ራሳቸውን ወሰነው እንዲጠመቁ ረድተዋል።

እኔና ኢኔኬ፣ ይሖዋ ትርጉም ያለው ሕይወት በመስጠት ሕዝቦቹን እንደሚባርካቸው በዓይናችን አይተናል

የሕይወትን ዓላማ ለመጀመሪያ ጊዜ በተረዳሁበት ወቅት ውድ የሆነ ዕንቁ እንዳገኘውና ዕንቁውን ወዲያውኑ እንደገዛው ተጓዥ ነጋዴ እንደሆንኩ ተሰምቶኝ ነበር። (ማቴ. 13:45, 46) ቀሪውን ሕይወቴን ሌሎችም የሕይወትን ዓላማ እንዲያውቁ በመርዳት ማሳለፍ ፈልጌ ነበር። እኔና ውዷ ባለቤቴ፣ ይሖዋ ትርጉም ያለው ሕይወት በመስጠት ሕዝቦቹን እንደሚባርካቸው በዓይናችን አይተናል።