በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 45

አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ፍቅር ማሳየታችሁን ቀጥሉ

አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ፍቅር ማሳየታችሁን ቀጥሉ

“አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ፍቅርና ምሕረት አሳዩ።”—ዘካ. 7:9

መዝሙር 107 መለኮታዊው የፍቅር መንገድ

ማስተዋወቂያ *

1-2. አንዳችን ለሌላው ታማኝ ፍቅር ለማሳየት የሚያነሳሱን ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

አንዳችን ለሌላው ታማኝ ፍቅር እንድናሳይ የሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች አሉ። አንዳንዶቹ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት የሚከተሉት ጥቅሶች ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጡናል። “ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት አይለዩህ። . . . ያን ጊዜ በአምላክና በሰው ፊት ሞገስ ታገኛለህ፤ እንዲሁም ጥሩ ማስተዋል እንዳለህ ታስመሠክራለህ።” “ታማኝ ፍቅር የሚያሳይ ሰው ራሱን ይጠቅማል።” “ጽድቅንና ታማኝ ፍቅርን የሚከታተል ሰው ሁሉ ሕይወትን . . . ያገኛል።”—ምሳሌ 3:3, 4፤ 11:17 ግርጌ፤ 21:21

2 እነዚህ ጥቅሶች ታማኝ ፍቅር ማሳየት አስፈላጊ የሆነባቸውን ሦስት ምክንያቶች ይጠቅሳሉ። አንደኛ፣ ታማኝ ፍቅር ማሳየት በአምላክ ዓይን ውድ እንድንሆን ያደርገናል። ሁለተኛ፣ ታማኝ ፍቅር ማሳየታችን ራሳችንን ይጠቅመናል። ለምሳሌ ከሌሎች ጋር ዘላቂ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችለናል። ሦስተኛ፣ ታማኝ ፍቅርን መከታተል የዘላለም ሕይወትን ጨምሮ ለወደፊቱ ጊዜ በረከቶች ያስገኛል። በእርግጥም ይሖዋ “አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ፍቅርና ምሕረት አሳዩ” በማለት የሰጠንን ማሳሰቢያ የምንከተልበት ብዙ ምክንያት አለን።—ዘካ. 7:9

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመልሳለን?

3 በዚህ ርዕስ ውስጥ አራት ጥያቄዎችን እንመልሳለን። ታማኝ ፍቅር ማሳየት የሚኖርብን ለእነማን ነው? ታማኝ ፍቅር ማሳየትን በተመለከተ ከሩት መጽሐፍ ምን ትምህርት እናገኛለን? በዛሬው ጊዜ ታማኝ ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ታማኝ ፍቅር የሚያሳዩ ሰዎች ምን ጥቅም ያገኛሉ?

ታማኝ ፍቅር ማሳየት የሚኖርብን ለእነማን ነው?

4. ታማኝ ፍቅር በማሳየት ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? (ማርቆስ 10:29, 30)

4 ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ ታማኝ ፍቅሩን ማለትም ጽኑ ፍቅሩን የሚያሳየው ለሚወዱትና ለሚያገለግሉት ሰዎች ብቻ ነው። (ዳን. 9:4) እኛም “የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ” የሚለውን ምክር መከተል እንፈልጋለን። (ኤፌ. 5:1) ስለዚህ ለመንፈሳዊ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ታማኝ ፍቅር ማሳየት ይኖርብናል።ማርቆስ 10:29, 30ን አንብብ።

5-6. “ታማኝነት” የሚለው ቃል በተለምዶ የሚሠራበት እንዴት ነው?

5 የታማኝ ፍቅርን ትርጉም ይበልጥ መረዳታችን ይህን ባሕርይ ለእምነት ባልንጀሮቻችን በተሻለ መንገድ ለማሳየት ያስችለናል። ስለ ታማኝ ፍቅር ያለንን ግንዛቤ ለማስፋት ይህን አገላለጽ፣ ታማኝነት የሚለው ቃል በተለምዶ ከሚሠራበት መንገድ ጋር እናወዳድረው። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።

 6 በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የሠራ ሰው ታማኝ ሠራተኛ ተብሎ ሲጠራ እንሰማለን። ሆኖም ግለሰቡ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ለብዙ ዓመታት ቢያገለግልም የመሥሪያ ቤቱን ባለቤቶች አግኝቷቸው አያውቅ ይሆናል። በድርጅቱ ፖሊሲዎችም የማይስማማበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ለድርጅቱ የተለየ ፍቅር የለውም፤ ግን ገቢ ስለሚያስገኝለት በሥራው ደስተኛ ነው። ጡረታ እስኪወጣ ወይም ሌላ የተሻለ ሥራ እስኪያገኝ ድረስ በዚያ ድርጅት ውስጥ ማገልገሉን ይቀጥላል።

7-8. (ሀ) አንድ ሰው ታማኝ ፍቅር እንዲያሳይ የሚያነሳሳው ምንድን ነው? (ለ) በሩት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ዘገባዎችን የምንመረምረው ለምንድን ነው?

7  በአንቀጽ 6 ላይ በተጠቀሰው ዓይነት ታማኝነት እና በታማኝ ፍቅር መካከል ያለው ልዩነት የግለሰቡ የልብ ዝንባሌ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት የአምላክ አገልጋዮች ታማኝ ፍቅር ለማሳየት ያነሳሳቸው ምንድን ነው? እነዚህ ሰዎች ታማኝ ፍቅር ያሳዩት ይህን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተሰምቷቸው ሳይሆን ልባቸው ስለገፋፋቸው ነው። የዳዊትን ምሳሌ እንመልከት። የዮናታን አባት ዳዊትን ለመግደል ይፈልግ የነበረ ቢሆንም ዳዊት ከልቡ ተነሳስቶ ለወዳጁ ለዮናታን ታማኝ ፍቅር አሳይቶታል። ዮናታን ከሞተ ከዓመታት በኋላ እንኳ ዳዊት ለዮናታን ልጅ ለሜፊቦስቴ ታማኝ ፍቅር ማሳየቱን ቀጥሎ ነበር።—1 ሳሙ. 20:9, 14, 15፤ 2 ሳሙ. 4:4፤ 8:15፤ 9:1, 6, 7

8 በሩት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ዘገባዎችን በመመርመር ስለ ታማኝ ፍቅር ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከተጠቀሱ ባለታሪኮች ስለ ታማኝ ፍቅር ምን ትምህርት እናገኛለን? የምናገኘውን ትምህርት በጉባኤ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው? *

ታማኝ ፍቅር ማሳየትን በተመለከተ ከሩት መጽሐፍ ምን ትምህርት እናገኛለን?

9. ናኦሚ ይሖዋ እየተቃወማት እንዳለ የተሰማት ለምንድን ነው?

9 በሩት መጽሐፍ ውስጥ ስለ ናኦሚ፣ ስለ ምራቷ ሩት እንዲሁም የናኦሚ ባል ዘመድ ስለሆነው ቦዔዝ የተባለ ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው እናነባለን። በእስራኤል ምድር ረሃብ በመከሰቱ ናኦሚ፣ ባሏና ሁለት ልጆቿ ወደ ሞዓብ ተሰደዱ። እዚያ እያሉ የናኦሚ ባል ሞተ። ሁለቱ ልጆቿ ትዳር መሥርተው ነበር፤ የሚያሳዝነው ግን እነሱም ሞቱ። (ሩት 1:3-5፤ 2:1) እነዚህ አስከፊ መከራዎች ናኦሚ በተስፋ መቁረጥ ስሜት እንድትዋጥ አደረጓት። በሐዘን ከመዋጧ የተነሳ ይሖዋ እየተቃወማት እንዳለ ተሰምቷት ነበር። ስሜቷን እንዴት ብላ እንደገለጸች ልብ በሉ፦ “የይሖዋ እጅ በእኔ ላይ [ተነስቷል]።” “ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሕይወቴን መራራ አድርጎታል።” በተጨማሪም እንዲህ ብላለች፦ ‘ይሖዋ ተቃውሞኛል፤ ሁሉን የሚችለው አምላክ መከራ አምጥቶብኛል።’—ሩት 1:13, 20, 21

10. ናኦሚ በምሬት ብትናገርም ይሖዋ ምን አደረገላት?

10 ናኦሚ በምሬት ስትናገር ይሖዋ ምን አደረገ? ይሖዋ በጭንቀት የተዋጠችውን አገልጋዩን አልተቆጣትም። ከዚህ ይልቅ ስሜቷን ተረድቶላታል። ይሖዋ “ግፍ ጥበበኛውን ሊያሳብደው [እንደሚችል]” ያውቃል። (መክ. 7:7) ናኦሚ ይሖዋ እንዳልተለያት ለመገንዘብ እርዳታ አስፈልጓት ነበር። ታዲያ አምላክ የረዳት እንዴት ነው? (1 ሳሙ. 2:8) ለናኦሚ ታማኝ ፍቅር እንድታሳይ ሩትን በማነሳሳት ነው። ሩት፣ አማቷ ስሜታዊ እንዳትሆንና መንፈሳዊ ሚዛኗን እንድትጠብቅ በደግነትና በፈቃደኝነት ረድታታለች። ከሩት ምሳሌ ምን እንማራለን?

11. አሳቢ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች ተስፋ የቆረጡ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለመርዳት የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው?

11 ታማኝ ፍቅር ያዘኑ ወይም ተስፋ የቆረጡ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንድንረዳቸው ያነሳሳናል። ሩት ከናኦሚ አልተለየችም፤ በዛሬው ጊዜ ያሉ አሳቢ ወንድሞችና እህቶችም በጉባኤያቸው ካሉ ያዘኑ ወይም የተጨነቁ ክርስቲያኖች ጎን ይቆማሉ። ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን ይወዷቸዋል፤ ስለዚህ እነሱን ለመርዳት የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ ይጓጓሉ። (ምሳሌ 12:25 ግርጌ፤ 24:10) ሐዋርያው ጳውሎስም እንዲህ እንድናደርግ አሳስቦናል፦ “የተጨነቁትን አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ” ብሏል።—1 ተሰ. 5:14

ተስፋ የቆረጡ ወንድሞቻችንን በማዳመጥ ልንረዳቸው እንችላለን (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)

12. ብዙውን ጊዜ፣ ተስፋ የቆረጡ ወንድሞችን ወይም እህቶችን መርዳት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው?

12 ብዙውን ጊዜ፣ ተስፋ የቆረጡ ወንድሞችን ወይም እህቶችን መርዳት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ እነሱን ማዳመጥ እንዲሁም እንደምንወዳቸው መግለጽ ነው። ይሖዋ ውድ ለሆኑት በጎቹ የምታሳዩትን አሳቢነት በትኩረት ይመለከታል። (መዝ. 41:1) ምሳሌ 19:17 እንዲህ ይላል፦ “ለችግረኛ ሞገስ የሚያሳይ ለይሖዋ ያበድራል፤ ላደረገውም ነገር ብድራት ይከፍለዋል።”

ዖርፋ ወደ ሞዓብ ስትመለስ ሩት ግን ከአማቷ ከናኦሚ ላለመለየት የሙጥኝ አለች። ሩት ናኦሚን “ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ” አለቻት (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13. የሩት ውሳኔ ከዖርፋ የሚለየው እንዴት ነው? ውሳኔዋ ታማኝ ፍቅር የሚንጸባረቅበት ነው የምንለውስ ለምንድን ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

13 የናኦሚ ባልና ሁለት ልጆቿ ከሞቱ በኋላ የተከሰተውን ነገር ስናነብ ታማኝ ፍቅርን በተመለከተ ተጨማሪ ትምህርት እናገኛለን። ናኦሚ “ይሖዋ ለሕዝቡ እህል በመስጠት ፊቱን ወደ እነሱ እንደመለሰ” በሰማች ጊዜ ወደ አገሯ ለመመለስ ወሰነች። (ሩት 1:6) ሁለቱም ምራቶቿ አብረዋት መጓዝ ጀመሩ። ሆኖም መንገድ ላይ ሳሉ ናኦሚ ምራቶቿ ወደ ሞዓብ እንዲመለሱ ሦስት ጊዜ ጠይቃቸዋለች። ታዲያ ምን አደረጉ? ዘገባው “ዖርፋ አማቷን ስማ ተሰናበተቻት። ሩት ግን ከእሷ ላለመለየት የሙጥኝ አለች” ይላል። (ሩት 1:7-14) ዖርፋ የተመለሰችው ናኦሚ ያለቻትን በመስማት ነው፤ ያደረገችው የሚጠበቅባትን ነው። ሩት ግን ከሚጠበቅባት ያለፈ ነገር አድርጋለች። እሷም መመለስ ትችል ነበር፤ ሆኖም ለናኦሚ ታማኝ ፍቅር ስለነበራት ከእሷ ላለመለየት ወስናለች። (ሩት 1:16, 17) ሩት ከናኦሚ ላለመለየት የሙጥኝ ያለችው ስለሚጠበቅባት ሳይሆን ይህን ለማድረግ ስለፈለገች ነው። ሩት ይህን ውሳኔ እንድታደርግ ያነሳሳት ታማኝ ፍቅር ነው። ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?

14. (ሀ) በዛሬው ጊዜ አፍቃሪ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች ምን ያደርጋሉ? (ለ) በዕብራውያን 13:16 መሠረት አምላክ የሚደሰተው በምን ዓይነት መሥዋዕቶች ነው?

14 ታማኝ ፍቅር ከሚጠበቅብን አልፈን እንድንሄድ ያነሳሳናል። እንደ ጥንት ጊዜው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ወንድሞችና እህቶችም በግለሰብ ደረጃ የማያውቋቸውን ጨምሮ ለሁሉም የእምነት ባልንጀሮቻቸው ታማኝ ፍቅር ያሳያሉ። ለምሳሌ በአንድ አካባቢ የተፈጥሮ አደጋ እንደደረሰ ሲሰሙ እርዳታ ማበርከት የሚችሉበትን መንገድ ወዲያውኑ ማሰብ ይጀምራሉ። በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ሰው የኢኮኖሚ ችግር ሲያጋጥመው ግለሰቡን ለመርዳት በፈቃደኝነት ራሳቸውን ያቀርባሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደኖሩት የመቄዶንያ ክርስቲያኖች ሁሉ እነሱም ከሚጠበቅባቸው በላይ ያደርጋሉ። የተቸገሩ ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ሲሉ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ያደርጋሉ፤ “እንዲያውም ከአቅማቸው በላይ” ይሰጣሉ። (2 ቆሮ. 8:3) እንዲህ ያለውን ፍቅር ሲመለከት ይሖዋ ምንኛ ይደሰት ይሆን!ዕብራውያን 13:16ን አንብብ።

በዛሬው ጊዜ ታማኝ ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

15-16. ደጋግሞ በመሞከር ረገድ ሩት ምን ምሳሌ ትታለች?

15 ስለ ሩትና ስለ ናኦሚ የሚገልጸውን ዘገባ በመመርመር በርካታ ግሩም ትምህርቶች እናገኛለን። እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

16 ደጋግማችሁ ሞክሩ። ሩት ከናኦሚ ጋር ወደ ይሁዳ ለመሄድ ራሷን ስታቀርብ መጀመሪያ ላይ ናኦሚ ከልክላት ነበር፤ ሆኖም ሩት ተስፋ አልቆረጠችም። ታዲያ ይህ ምን ውጤት አስገኘ? “ናኦሚ፣ ሩት ከእሷ ጋር ለመሄድ እንደቆረጠች ስታውቅ መወትወቷን አቆመች።”—ሩት 1:15-18

17. ወንድሞቻችንን ለመርዳት መሞከራችንን እንዳናቆም የሚረዳን ምንድን ነው?

17 የምናገኘው ትምህርት፦ የተጨነቁ ወንድሞቻችንን መርዳት ትዕግሥት ይጠይቃል፤ ሆኖም እነሱን ለመርዳት መሞከራችንን ማቆም የለብንም። እገዛ የሚያስፈልጋት አንዲት እህት መጀመሪያ ላይ እርዳታችንን ለመቀበል ፈቃደኛ ላትሆን ትችላለች። * ያም ቢሆን ታማኝ ፍቅር፣ እሷን ለመርዳት ጥረት ማድረጋችንን እንድንቀጥል ያነሳሳናል። (ገላ. 6:2) ውሎ አድሮ የእርዳታ እጃችንን እንደምትቀበልና እንድናጽናናት እንደምትፈቅድልን ተስፋ እናደርጋለን።

18. ሩት ስሜቷን ሊጎዳ የሚችል ምን ነገር አጋጥሟታል?

18 ቅር አትሰኙ። ናኦሚና ሩት ቤተልሔም ሲደርሱ ናኦሚ የቀድሞ ጎረቤቶቿን አገኘቻቸው። እንዲህ አለቻቸው፦ “ከዚህ ስወጣ ሙሉ ነበርኩ፤ ይሖዋ ግን ባዶ እጄን እንድመለስ አደረገኝ።” (ሩት 1:21) ናኦሚ ይህን ስትናገር ሩት ምን ተሰምቷት ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስቡት! ሩት ናኦሚን ለመርዳት ስትል ብዙ መሥዋዕት ከፍላለች። አብራት አልቅሳለች፣ አጽናንታታለች እንዲሁም ለበርካታ ቀናት አብራት ተጉዛለች። ሩት ይህን ሁሉ ብታደርግላትም ናኦሚ “ይሖዋ . . . ባዶ እጄን እንድመለስ አደረገኝ” ብላለች። የናኦሚ ንግግር አጠገቧ የቆመችው ሩት ያደረገችላትን ድጋፍ ከቁብ ያልቆጠረችው ያስመስልባታል። ሩት ይህን ስትሰማ ስሜቷ ምንኛ ተጎድቶ ይሆን! ያም ቢሆን ከናኦሚ ላለመለየት የሙጥኝ ብላለች።

19. ከተጨነቀ የእምነት ባልንጀራችን ጋር የሙጥኝ ለማለት ምን ይረዳናል?

19 የምናገኘው ትምህርት፦ በዛሬው ጊዜ አንዲትን የተጨነቀች እህት ለማጽናናት ብዙ ጥረት ብናደርግም መጀመሪያ ላይ እህታችን የሚያስከፋ ነገር ትናገረን ይሆናል። ሆኖም በተናገረችው ነገር ቅር ላለመሰኘት ጥረት እናደርጋለን። እርዳታ ከሚያስፈልጋት እህታችን ጋር የሙጥኝ እንላለን፤ እንዲሁም ይሖዋ እሷን ለማጽናናት የሚያስችል መንገድ እንዲጠቁመን በጸሎት እንጠይቀዋለን።—ምሳሌ 17:17

በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ቦዔዝን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 20-21⁠ን ተመልከት)

20. ሩት ተስፋ እንዳትቆርጥ ብርታት የሰጣት ምንድን ነው?

20 በተገቢው ጊዜ ማበረታቻ ስጡ። ሩት ለናኦሚ ታማኝ ፍቅር አሳይታታለች፤ ሆኖም ሩትም ማበረታቻ ያስፈለጋት ጊዜ ነበር። ይሖዋ እሷን ለማበረታታት በቦዔዝ ተጠቅሟል። ቦዔዝ ሩትን እንዲህ አላት፦ “ላደረግሽው ሁሉ ይሖዋ ብድራትሽን ይመልስልሽ፤ በክንፎቹ ሥር ለመጠለል ብለሽ ወደ እሱ የመጣሽበት የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሙሉ ዋጋሽን ይክፈልሽ።” እነዚህ ቃላት ሩትን በእጅጉ አበረታተዋት መሆን አለበት። እሷም መልሳ ‘አጽናንተኸኛል፤ እኔን አገልጋይህን በሚያበረታታ መንገድ አነጋግረኸኛል’ አለችው። (ሩት 2:12, 13) ቦዔዝ ለሩት በተገቢው ጊዜ የሰጣት ማበረታቻ ተስፋ እንዳትቆርጥ ብርታት ሰጥቷታል።

21. ኢሳይያስ 32:1, 2 እንደሚገልጸው አሳቢ ሽማግሌዎች ምን ያደርጋሉ?

21 የምናገኘው ትምህርት፦ ለሌሎች ታማኝ ፍቅር የሚያሳዩ ክርስቲያኖችም ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸው ጊዜ አለ። ቦዔዝ፣ ሩት ለናኦሚ ደግነት በማሳየቷ አመስግኗታል። በዛሬው ጊዜ ያሉ አስተዋይ ሽማግሌዎችም፣ በጉባኤያቸው ውስጥ ያሉ ሌሎችን በደግነት የሚረዱ ወንድሞችንና እህቶችን ያመሰግኗቸዋል። እንዲህ ያለው በተገቢው ጊዜ የተሰጠ ልባዊ ምስጋና ወንድሞችና እህቶች መልካም ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ያበረታታቸዋል።ኢሳይያስ 32:1, 2ን አንብብ።

ታማኝ ፍቅር የሚያሳዩ ሰዎች ምን ጥቅም ያገኛሉ?

22-23. የናኦሚ አመለካከት የተቀየረው እንዴት ነው? እንዲቀየር ያደረገውስ ምንድን ነው? (መዝሙር 136:23, 26)

22 ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቦዔዝ ለሩትና ለናኦሚ በርከት ያለ እህል ሰጣቸው። (ሩት 2:14-18) በዚህ ጊዜ ናኦሚ ምን ተሰማት? “ለሕያዋንም ሆነ ለሙታን ታማኝ ፍቅሩን ከማሳየት ወደኋላ የማይለው ይሖዋ ይባርከው” አለች። (ሩት 2:20ሀ) በእርግጥም ናኦሚ አመለካከቷ ተቀይሯል! ቀደም ሲል እያለቀሰች ‘ይሖዋ ተቃውሞኛል’ ስትል የነበረችው ሴት ‘ይሖዋ ታማኝ ፍቅሩን ከማሳየት ወደኋላ አይልም’ ብላ በደስታ ተናግራለች። ናኦሚ አመለካከቷን እንድታስተካክል የረዳት ምን ሊሆን ይችላል?

23 በስተ መጨረሻ ናኦሚ፣ ይሖዋ ፈጽሞ እንዳልተዋት ተገነዘበች። ይሖዋ ሩትን በመጠቀም ወደ ይሁዳ በምታደርገው ጉዞ ላይ ደግፏታል። (ሩት 1:16) ናኦሚ፣ ‘ከሚቤዧቸው ሰዎች አንዱ’ የሆነው ቦዔዝ በፍቅር ተነሳስቶ የሚያስፈልጋቸውን እህል በሰጣቸው ጊዜም የይሖዋን እጅ ተመልክታለች። * (ሩት 2:19, 20ለ) ናኦሚ እንዲህ ብላ አስባ መሆን አለበት፦ ‘አሁን ነው የገባኝ፤ ለካስ ይሖዋ ፈጽሞ አልተለየኝም! እስካሁን ከአጠገቤ ነበር!’ (መዝሙር 136:23, 26ን አንብብ።) ሩትና ቦዔዝ እሷን መደገፋቸውን ባለማቆማቸው ናኦሚ በአመስጋኝነት ስሜት ተሞልታ መሆን አለበት! ናኦሚ በመጽናናቷ ሦስቱም ተደስተው እንደሚሆን ጥያቄ የለውም።

24. ለእምነት ባልንጀሮቻችን ታማኝ ፍቅር ማሳየታችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?

24 ታማኝ ፍቅርን አስመልክቶ ከሩት መጽሐፍ ምን ትምህርት አግኝተናል? ታማኝ ፍቅር በጭንቀት የተዋጡ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ለመርዳት መሞከራችንን እንዳናቆም ያነሳሳናል። እነሱን ለመርዳት ስንል ከሚጠበቅብን አልፈን እንድንሄድም ይገፋፋናል። ሽማግሌዎች ለሌሎች ታማኝ ፍቅር የሚያሳዩ ክርስቲያኖችን በተገቢው ጊዜ ሊያበረታቷቸው ይገባል። ማጽናኛ የሚያስፈልጋቸው ወንድሞችና እህቶች ሲበረታቱ ስናይ እኛም በእጅጉ እንደሰታለን። (ሥራ 20:35) ይሁንና ታማኝ ፍቅር ማሳየታችንን እንድንቀጥል የሚያነሳሳን ከሁሉ የላቀው ምክንያት ምንድን ነው? “ታማኝ ፍቅሩ . . . እጅግ ብዙ” የሆነውን አምላካችንን ይሖዋን መምሰልና እሱን ማስደሰት ስለምንፈልግ ነው።—ዘፀ. 34:6፤ መዝ. 33:22

መዝሙር 130 ይቅር ባይ ሁኑ

^ አን.5 ይሖዋ በጉባኤ ውስጥ ላሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ታማኝ ፍቅር እንድናሳይ ይፈልጋል። በጥንት ዘመን የኖሩ አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ታማኝ ፍቅር ያሳዩት እንዴት እንደሆነ ማጥናታችን ስለዚህ ባሕርይ ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል። ከሩት፣ ከናኦሚና ከቦዔዝ ታሪክ ምን ትምህርት እንደምናገኝ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።

^ አን.8 ከዚህ ርዕስ የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ሩት ምዕራፍ 1⁠ን እና ምዕራፍ 2⁠ን በግላችሁ እንድታነቡ እናበረታታችኋለን።

^ አን.17 እርዳታ ስለሚያስፈልጋቸው እህቶች የጠቀስነው የናኦሚን ምሳሌ እየመረመርን ስለሆነ ነው። ሆኖም በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ከወንድሞች ጋር በተያያዘም ይሠራሉ።

^ አን.23 ቦዔዝ እንዴት እንደተቤዣቸው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በጥቅምት 1, 2012 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 20 ላይ የሚገኘውን “በእምነታቸው ምሰሏቸው—‘ምግባረ መልካም ሴት’” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።