በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 46

አዲስ ባለትዳሮች—ሕይወታችሁ ይሖዋን በማገልገል ላይ ያተኮረ ይሁን

አዲስ ባለትዳሮች—ሕይወታችሁ ይሖዋን በማገልገል ላይ ያተኮረ ይሁን

“ይሖዋ ብርታቴ . . . ነው፤ ልቤ በእሱ ይተማመናል።”—መዝ. 28:7

መዝሙር 131 “አምላክ ያጣመረውን”

ማስተዋወቂያ *

1-2. (ሀ) አዲስ ተጋቢዎች በይሖዋ መታመን ያለባቸው ለምንድን ነው? (መዝሙር 37:3, 4) (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

በቅርቡ ትዳር ለመመሥረት አቅዳችኋል? ወይም አዲስ ባለትዳር ናችሁ? ከሆነ በጣም ከምትወዱት ሰው ጋር አስደሳች ሕይወት ለመምራት እንደጓጓችሁ ጥያቄ የለውም። እርግጥ ነው፣ ትዳር የራሱ የሆኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉት፤ እንዲሁም ትላልቅ ውሳኔዎችን ማድረግ ይጠበቅባችኋል። በትዳር ሕይወታችሁ የምታገኙት ደስታ የተመካው እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በምትወጡበት መንገድ እንዲሁም በምታደርጓቸው ውሳኔዎች ላይ ነው። በይሖዋ የምትታመኑ ከሆነ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ታደርጋላችሁ፤ ትዳራችሁ የሰመረ ይሆናል፤ እንዲሁም ይበልጥ ደስተኛ ትሆናላችሁ። ሆኖም የአምላክን አመለካከት ግምት ውስጥ ካላስገባችሁ በትዳራችሁ ላይ ውጥረት የሚፈጥሩና ደስታችሁን እንድታጡ የሚያደርጉ ችግሮች ሊያጋጥሟችሁ ይችላሉ።መዝሙር 37:3, 4ን አንብብ።

2 ይህ ርዕስ በዋነኝነት የተዘጋጀው ለአዲስ ተጋቢዎች ቢሆንም ሁሉንም ባለትዳሮች ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያወሳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት እንደምናገኝ ያብራራል። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ትዳርን ጨምሮ በተለያዩ የሕይወታችን ዘርፎች ተግባራዊ ልናደርግ የምንችላቸውን ትምህርቶች ይዘውልናል። በተጨማሪም በዘመናችን ካሉ አንዳንድ ባለትዳሮች ተሞክሮ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመለከታለን።

አዲስ ተጋቢዎች የትኞቹ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ?

አዲስ ተጋቢዎች ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አገልግሎት ከማስፋት ሊያግዷቸው የሚችሉት የትኞቹ ውሳኔዎች ናቸው? (ከአንቀጽ 3-4⁠ን ተመልከት)

3-4. አዲስ ተጋቢዎች የትኞቹ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ?

3 አንዳንዶች አዲስ ተጋቢዎችን፣ የተለመደውን ዓይነት ሕይወት እንዲመሩ ይገፋፏቸው ይሆናል። ለምሳሌ ወላጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ‘ልጅ በልጅነት’ ይሏቸው ይሆናል። ወይም ደግሞ ጓደኞቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ቤት እንዲገዙና የቤት ዕቃ እንዲያሟሉ ይገፋፏቸው ይሆናል።

4 ባልና ሚስቱ ካልተጠነቀቁ ዕዳ ውስጥ እንዲዘፈቁ የሚያደርጋቸው ውሳኔ ሊወስኑ ይችላሉ። ከዚያም ዕዳቸውን ለመክፈል ሲሉ ሁለቱም ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸው ይሆናል። ሰብዓዊ ሥራቸው በግል ጥናት፣ በቤተሰብ አምልኮና በአገልግሎት የሚያሳልፉትን ጊዜ ሊሻማባቸው ይችላል። ምናልባትም ባልና ሚስቱ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ወይም ሥራቸውን ላለማጣት ሲሉ ትርፍ ሰዓት መሥራት ሊጀምሩ ይችላሉ። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ ከስብሰባዎች እንኳ ይቀሩ ይሆናል። በዚህም ምክንያት አገልግሎታቸውን ማስፋት የሚችሉባቸው አስደሳች አጋጣሚዎች ያመልጧቸዋል።

5. የክላውስ እና የማሪሳ ተሞክሮ ምን ያስተምረናል?

5 ቁሳዊ ነገሮችን በማካበት ላይ ያተኮረ ሕይወት መምራት እውነተኛ ደስታ እንደማያስገኝ የሚያሳዩ በርካታ ተሞክሮዎች አሉ። ክላውስ እና ማሪሳ የተባሉ ባልና ሚስት በዚህ ረገድ ምን ትምህርት እንዳገኙ እንመልከት። * ከተጋቡ በኋላ የተደላደለ ሕይወት ለመምራት ሲሉ ሁለቱም የሙሉ ቀን ሥራ ይሠሩ ነበር። ሆኖም ውስጣዊ እርካታ አልነበራቸውም። ክላውስ እንዲህ በማለት በሐቀኝነት ተናግሯል፦ “በቁሳዊ ረገድ ከሚያስፈልገን በላይ ነበረን፤ ሆኖም መንፈሳዊ ግብ አልነበረንም። እውነቱን ለመናገር ሕይወታችን የተወሳሰበና ውጥረት የሞላበት ነበር።” ምናልባት እናንተም ቁሳዊ ነገሮችን በማካበት ላይ ያተኮረ ሕይወት መምራታችሁ እርካታ እንዳላስገኘላችሁ አስተውላችሁ ይሆናል። ከሆነ አይዟችሁ! ሌሎች የተዉትን መልካም ምሳሌ መመርመራችሁ አስፈላጊውን ለውጥ እንድታደርጉ ይረዳችኋል። በመጀመሪያ፣ ባሎች ከንጉሥ ኢዮሳፍጥ ምሳሌ ምን ትምህርት እንደሚያገኙ እንመልከት።

እንደ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ በይሖዋ ታመኑ

6. በምሳሌ 3:5, 6 ላይ ከሚገኘው ምክር ጋር በሚስማማ መልኩ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ከባድ ችግር ሲያጋጥመው ምን አደረገ?

6 ባሎች፣ ያለባችሁ ኃላፊነት ከአቅማችሁ በላይ እንደሆነ የሚሰማችሁ ጊዜ አለ? ከሆነ የንጉሥ ኢዮሳፍጥን ምሳሌ መመርመራችሁ ይጠቅማችኋል። ኢዮሳፍጥ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን የመላውን ብሔር ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ነበረበት። ታዲያ ኢዮሳፍጥ ይህን ከባድ ኃላፊነት የተወጣው እንዴት ነው? ኢዮሳፍጥ ሕዝቡን ከጉዳት ለመጠበቅ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። በይሁዳ ከተሞች ምሽጎችን ገነባ፤ እንዲሁም ከ1,160,000 የሚበልጡ ወታደሮችን ያቀፈ ኃያል ሠራዊት አደራጀ። (2 ዜና 17:12-19) ከጊዜ በኋላ ኢዮሳፍጥ አንድ ከባድ ችግር አጋጠመው። አሞናውያን፣ ሞዓባውያንና በሴይር ተራራማ ክልል የሚኖሩ ሰዎች ግዙፍ ሠራዊት አስከትለው ሊወጉት በመጡበት ወቅት የእሱ፣ የቤተሰቡና የሕዝቡ ደህንነት አደጋ ላይ ወደቀ። (2 ዜና 20:1, 2) ታዲያ ኢዮሳፍጥ ምን አደረገ? እንዲረዳውና ብርታት እንዲሰጠው ይሖዋን ለመነ። ኢዮሳፍጥ የወሰደው እርምጃ በምሳሌ 3:5, 6 ላይ ከሚገኘው ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ጋር የሚስማማ ነው። (ጥቅሱን አንብብ።) በ2 ዜና መዋዕል 20:5-12 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ኢዮሳፍጥ ያቀረበው ትሕትና የሚንጸባረቅበት ጸሎት ይህ ንጉሥ አፍቃሪ በሆነው ሰማያዊ አባቱ ምን ያህል እንደሚታመን የሚያሳይ ነው። ታዲያ ይሖዋ የኢዮሳፍጥን ጸሎት የመለሰለት እንዴት ነው?

7. ይሖዋ የኢዮሳፍጥን ጸሎት የመለሰለት እንዴት ነው?

7 ይሖዋ ያሃዚኤል በተባለ ሌዋዊ አማካኝነት ኢዮሳፍጥን አነጋገረው። እንዲህ አለው፦ “ቦታ ቦታችሁን ይዛችሁ ዝም ብላችሁ ቁሙ፤ ይሖዋ ለእናንተ ሲል የሚወስደውን የማዳን እርምጃ ተመልከቱ።” (2 ዜና 20:13-17) ይህ ከተለመደው የውጊያ ስልት በጣም የተለየ ነው! ይሁንና ይህ መመሪያ የመጣው ከሰው ሳይሆን ከይሖዋ ነው። ኢዮሳፍጥ በአምላኩ ሙሉ በሙሉ በመታመን የታዘዘውን አደረገ። እሱና ሕዝቡ ጠላቶቻቸውን ለመግጠም ሲወጡ ከፊት ያሰለፈው ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ወታደሮች ሳይሆን ምንም መሣሪያ ያልታጠቁትን ዘማሪዎች ነው። ይሖዋ ኢዮሳፍጥን አላሳፈረውም፤ ጠላቶቹን ድል አድርጎለታል።—2 ዜና 20:18-23

አዲስ ተጋቢዎች በመጸለይ እና የአምላክን ቃል በማንበብ ሕይወታቸው በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረግ ይችላሉ (አንቀጽ 8, 10ን ተመልከት)

8. ባሎች ከኢዮሳፍጥ ምሳሌ ምን ትምህርት ያገኛሉ?

8 ባሎች ከኢዮሳፍጥ ምሳሌ መማር ትችላላችሁ። ቤተሰባችሁን የመንከባከብ ኃላፊነት ስላለባችሁ ቤተሰባችሁን ከጉዳት ለመጠበቅና ለማስተዳደር ተግታችሁ ትሠራላችሁ። ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟችሁ ችግሩን በራሳችሁ መፍታት እንደምትችሉ ይሰማችሁ ይሆናል። ሆኖም በራሳችሁ ብርታት አትመኩ። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንዲረዳችሁ በግላችሁ ጸልዩ። በተጨማሪም ከሚስታችሁ ጋር ሆናችሁ አጥብቃችሁ ጸልዩ። መጽሐፍ ቅዱስን እና ድርጅቱ ያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በማጥናት ከይሖዋ መመሪያ ለማግኘት ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም ያገኛችሁትን ምክር በሥራ ላይ አውሉ። እርግጥ ባደረጋችሁት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ሌሎች አይስማሙ ይሆናል። እንዲያውም የሞኝነት ውሳኔ እንደወሰናችሁ ሊነግሯችሁ ይችላሉ። የቤተሰባችሁን ደህንነት ማስጠበቅ የምትችሉት ገንዘብና ቁሳዊ ነገር ሲኖራችሁ እንደሆነ ይነግሯችሁ ይሆናል። ሆኖም የኢዮሳፍጥን ምሳሌ አስታውሱ። ኢዮሳፍጥ በይሖዋ ታምኗል፤ እምነቱንም በተግባር አሳይቷል። ይሖዋ ያንን ታማኝ ሰው አልተወውም፤ እናንተንም ቢሆን አይተዋችሁም። (መዝ. 37:28፤ ዕብ. 13:5) ባለትዳሮች እርካታ ያለው ሕይወት ለመምራት ሌላስ ምን ማድረግ ይችላሉ?

እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ እና እንደ ሚስቱ ሕይወታችሁ በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ እንዲሆን አድርጉ

9. ስለ ኢሳይያስ እና ስለ ሚስቱ ምን ማለት ይቻላል?

9 ነቢዩ ኢሳይያስ እና ሚስቱ ሕይወታቸው በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ እንዲሆን አድርገዋል። ኢሳይያስ ነቢይ ነበር። ሚስቱም ‘ነቢዪት’ ተብላለች፤ ስለዚህ እሷም የነቢይነት ሥራ ታከናውን የነበረ ይመስላል። (ኢሳ. 8:1-4) ኢሳይያስ እና ሚስቱ ሕይወታቸው ለይሖዋ በሚያቀርቡት አምልኮ ላይ ያተኮረ ነበር። በዛሬው ጊዜ ላሉ ባለትዳሮችም ግሩም ምሳሌ ትተዋል።

10. ባለትዳሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ማጥናታቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን በይሖዋ አገልግሎት እንዲካፈሉ የሚያነሳሳቸው እንዴት ነው?

10 በዛሬው ጊዜ ያሉ ባለትዳሮችም በይሖዋ አገልግሎት አቅማቸው በፈቀደ መጠን በመካፈል ሕይወታቸው ይሖዋን በማገልገል ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረግ ይችላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች አብረው በማጥናት እንዲሁም ትንቢቶቹ ምንጊዜም ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ በማስተዋል በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት ማጠናከር ይችላሉ። * (ቲቶ 1:2) ከአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ጋር በተያያዘ እነሱም የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ማሰላሰል ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ምሥራቹ በመላው ምድር እንደሚሰበክ የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ። (ማቴ. 24:14) ባልና ሚስቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እያገኙ እንዳለ እርግጠኛ መሆናቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን በይሖዋ አገልግሎት እንዲካፈሉ ይበልጥ ያነሳሳቸዋል።

እንደ ጵርስቅላ እና እንደ አቂላ መንግሥቱን አስቀድሙ

11. ጵርስቅላ እና አቂላ ምን አከናውነዋል? ለምንስ?

11 ወጣት ባለትዳሮች ከጵርስቅላ እና ከአቂላ መማር ይችላሉ። ጵርስቅላ እና አቂላ በሮም ከተማ ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን ባልና ሚስት ናቸው። ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች ከሰሙ በኋላ ክርስቲያኖች ሆኑ። በወቅቱ በሕይወታቸው ደስተኛ እንደነበሩ ምንም ጥያቄ የለውም። ሆኖም ንጉሠ ነገሥቱ ቀላውዴዎስ ሁሉም አይሁዳውያን ሮምን ለቀው እንዲወጡ ባዘዘበት ወቅት ሕይወታቸው በድንገት ተቀየረ። ይህ ለውጥ ምን ያካትታል? አቂላ እና ጵርስቅላ የለመዱትን አካባቢ ለቀው መሄድ፣ ቤት ማግኘት እንዲሁም የድንኳን ሥራቸውን በአዲስ አካባቢ መጀመር ነበረባቸው። ሕይወታቸው መቀየሩ በይሖዋ አገልግሎት የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንዲቀንሱ ያደርጋቸው ይሆን? የዚህን ጥያቄ መልስ እናውቀዋለን። አቂላ እና ጵርስቅላ በአዲሱ መኖሪያቸው በቆሮንቶስ የሚገኘውን ጉባኤ መርዳት ጀመሩ፤ እንዲሁም ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር ሆነው በዚያ ያሉትን ወንድሞች ለማበረታታት ጥረት ያደርጉ ነበር። ከጊዜ በኋላም ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው ሌሎች ከተሞች ሄደው አገልግለዋል። (ሥራ 18:18-21፤ ሮም 16:3-5) በእርግጥም በትዳር አብረው ያሳለፉት ሕይወት ትርጉም ያለውና አስደሳች ነበር!

12. ባለትዳሮች መንፈሳዊ ግብ ማውጣት ያለባቸው ለምንድን ነው?

12 በዛሬው ጊዜ ያሉ ባለትዳሮችም መንግሥቱን በማስቀደም የጵርስቅላን እና የአቂላን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። ጥንዶቹ ስለ ግቦቻቸው መነጋገር የሚችሉበት ከሁሉ የተሻለው ጊዜ እየተጠናኑ ያሉበት ወቅት ነው። ባለትዳሮች አብረው መንፈሳዊ ግብ የሚያወጡና ግቦቻቸው ላይ ለመድረስ ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ የይሖዋን መንፈስ በሕይወታቸው ውስጥ ማየት የሚችሉበት ተጨማሪ አጋጣሚ ይኖራቸዋል። (መክ. 4:9, 12) የራስልን እና የኤሊዛቤትን ተሞክሮ እንመልከት። ራስል “እንጠናና በነበረበት ወቅት ስለ መንፈሳዊ ግቦቻችን በግልጽ ተነጋግረናል” ብሏል። ኤሊዛቤት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ይህን ውይይት ያደረግነው ወደፊት ውሳኔ የሚጠይቁ የተለያዩ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን፣ ግባችን ላይ ለመድረስ እንቅፋት የማይሆንብን ውሳኔ ማድረግ እንድንችል ነው።” ራስልና ኤሊዛቤት ሁኔታቸው ስለፈቀደላቸው ወደ ማይክሮኔዥያ ተዛውረው የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል ጀምረዋል።

አዲስ ተጋቢዎች መንፈሳዊ ግቦችን በማውጣት ሕይወታቸው በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረግ ይችላሉ (አንቀጽ 13ን ተመልከት)

13. በመዝሙር 28:7 መሠረት በይሖዋ የምንታመን ከሆነ ውጤቱ ምን ይሆናል?

13 እንደ ራስል እና እንደ ኤሊዛቤት ሁሉ በርካታ ባለትዳሮች፣ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላለመጠላለፍ ጥረት በማድረግ በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ አቅማቸው በፈቀደ መጠን የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ ወስነዋል። አንድ ባልና ሚስት መንፈሳዊ ግቦችን የሚያወጡና ግቦቻቸው ላይ ለመድረስ ተባብረው የሚሠሩ ከሆነ ግሩም ውጤቶችን ያገኛሉ። የይሖዋን እጅ ያያሉ፤ በእሱ ላይ ያላቸው እምነት ያድጋል፤ እንዲሁም እውነተኛ ደስታ ያገኛሉ።መዝሙር 28:7ን አንብብ።

እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ እና እንደ ሚስቱ ይሖዋ በገባው ቃል ተማመኑ

14. ሐዋርያው ጴጥሮስና ሚስቱ በማቴዎስ 6:25, 31-34 ላይ ይሖዋ በገባው ቃል እንደሚተማመኑ ያሳዩት እንዴት ነው?

14 ባለትዳሮች ሐዋርያው ጴጥሮስ እና ሚስቱ ከተዉት ምሳሌም መማር ይችላሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገናኘ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ አንድ አስፈላጊ ውሳኔ ማድረግ ነበረበት። ጴጥሮስ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ዓሣ በማጥመድ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ሥራውን ትቶ እንዲከተለው ሲጠይቀው ጴጥሮስ የቤተሰቡን ሁኔታ ከግምት ማስገባት ነበረበት። (ሉቃስ 5:1-11) ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር አብሮ እየተጓዘ ለመስበክ ወሰነ። በእርግጥም ውሳኔው ጥበብ የሚንጸባረቅበት ነበር! ደግሞም የጴጥሮስ ሚስት ውሳኔውን እንደደገፈችለት መተማመን እንችላለን። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ የጴጥሮስ ሚስት ቢያንስ አልፎ አልፎ ከጴጥሮስ ጋር ትጓዝ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል። (1 ቆሮ. 9:5) በተጨማሪም ግሩም ክርስቲያን ሚስት መሆኗ ጴጥሮስ ለክርስቲያን ባሎችና ሚስቶች ምክር ሲሰጥ የመናገር ነፃነት እንዲኖረው እንደረዳው ጥያቄ የለውም። (1 ጴጥ. 3:1-7) ጴጥሮስም ሆነ ሚስቱ፣ ይሖዋ በሕይወታቸው ውስጥ መንግሥቱን ካስቀደሙ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያሟላላቸው በገባው ቃል ላይ እምነት እንደነበራቸው በግልጽ መመልከት ይቻላል።ማቴዎስ 6:25, 31-34ን አንብብ።

15. ከቲያጎ እና ከኤስተር ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን?

15 ከተጋባችሁ የተወሰኑ ዓመታት ያለፏችሁ ባለትዳሮችስ? አገልግሎታችሁን ለማስፋት ያላችሁን ፍላጎት ማሳደግ የምትችሉት እንዴት ነው? አንዱ መንገድ የሌሎች ባለትዳሮችን ተሞክሮ መመርመር ነው። ለምሳሌ “ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል” የሚለውን ዓምድ ማንበብ ትችላላችሁ። በብራዚል የሚኖሩት ቲያጎ እና ኤስተር የተባሉ ባልና ሚስት፣ እንዲህ ያሉትን ተሞክሮዎች ማንበባቸው ሰባኪዎች ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረው ለማገልገል ከፍተኛ ጉጉት እንዲያድርባቸው አድርጓል። ቲያጎ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ በዘመናችን ያሉ አገልጋዮቹን የረዳቸው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ተሞክሮዎችን ስናነብ እኛም የይሖዋን አመራርና እንክብካቤ በሕይወታችን ለማየት ፈለግን።” እነዚህ ባልና ሚስት ከጊዜ በኋላ ወደ ፓራጓይ ተዛወሩ፤ ከ2014 አንስቶ በፖርቱጋልኛ መስክ እያገለገሉ ይገኛሉ። ኤስተር እንዲህ ብላለች፦ “ሁለታችንም ኤፌሶን 3:20⁠ን በጣም እንወደዋለን። በይሖዋ አገልግሎት ባሳለፍነው ሕይወት ይህ ጥቅስ ሲፈጸም በተደጋጋሚ ተመልክተናል።” ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው በዚያ ደብዳቤ ላይ ይሖዋ ከምንጠይቀው እጅግ አብልጦ እንደሚሰጠን ገልጿል። ይሖዋም ይህን እንደሚያደርግ ብዙ ጊዜ አሳይቷል!

አዲስ ተጋቢዎች ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ምክር በመጠየቅ ሕይወታቸው በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረግ ይችላሉ (አንቀጽ 16ን ተመልከት)

16. ወጣት ባለትዳሮች ግባቸውን በሚገመግሙበት ወቅት ከማን ምክር መጠየቅ ይችላሉ?

16 በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣት ባለትዳሮች፣ በይሖዋ እንደሚተማመኑ ካሳዩ ክርስቲያኖች ተሞክሮ ብዙ መማር ይችላሉ። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ይሖዋን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያገለገሉ አንዳንድ ባለትዳሮች አሉ። ግባችሁን መገምገም እንዳለባችሁ የሚሰማችሁ ከሆነ ለምን ምክር አትጠይቋቸውም? በይሖዋ እንደምትታመኑ የምታሳዩበት ሌላው መንገድ ይህ ነው። (ምሳሌ 22:17, 19) ሽማግሌዎችም ወጣት ባለትዳሮች መንፈሳዊ ግቦችን እንዲያወጡና ግባቸው ላይ እንዲደርሱ ሊረዷቸው ይችላሉ።

17. ክላውስ እና ማሪሳ ምን አጋጥሟቸዋል? ከእነሱ ተሞክሮስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

17 ይሁንና አንዳንድ ጊዜ፣ አገልግሎታችንን ለማስፋት ያደረግነው ውሳኔ ያልጠበቅነው ቦታ ሊወስደን ይችላል። በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሱትን የክላውስን እና የማሪሳን ምሳሌ እንመልከት። ለሦስት ዓመታት ያህል በትዳር ከቆዩ በኋላ መኖሪያቸውን ለቀው በመሄድ በፊንላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ በግንባታ ሥራ ለመካፈል ራሳቸውን አቀረቡ። ሆኖም በዚያ ከስድስት ወር በላይ መቆየት እንደማይፈቀድላቸው ተነገራቸው። ይህን ሲሰሙ መጀመሪያ ላይ አዝነው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን አረብኛ እንዲማሩ ተጋበዙ፤ በአሁኑ ወቅት በሌላ አገር ውስጥ በአረብኛ ቋንቋ መስክ በደስታ እያገለገሉ ነው። ማሪሳ ያለፈውን ጊዜ መለስ ብላ ስታስብ እንዲህ ብላለች፦ “አዲስ ነገር መሞከር በጣም ያስፈራል፤ እንዲሁም በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመን ይጠይቃል። ሆኖም ይሖዋ ባልጠበቅናቸው መንገዶች ምንጊዜም እንደሚረዳን ተመልክቻለሁ። ይህን ማየቴ በይሖዋ ይበልጥ እንድተማመን አድርጎኛል።” ይህ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ከተማመናችሁ እሱ ምንጊዜም ወሮታችሁን እንደሚከፍላችሁ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ።

18. ባለትዳሮች በይሖዋ መታመናቸውን ለመቀጠል ምን ማድረግ ይችላሉ?

18 ትዳር የይሖዋ ስጦታ ነው። (ማቴ. 19:5, 6) ይሖዋ ባለትዳሮች በዚህ ስጦታ እንዲደሰቱ ይፈልጋል። (ምሳሌ 5:18) ወጣት ባለትዳሮች፣ ሕይወታችሁን ስለምትመሩበት መንገድ ለምን ቆም ብላችሁ አታስቡም? ይሖዋ ለሰጣችሁ ስጦታዎች ሁሉ ያላችሁን አድናቆት ለማሳየት አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ እያደረጋችሁ ነው? ይሖዋን በጸሎት አነጋግሩት። በተጨማሪም ካላችሁበት ሁኔታ ጋር የሚስማሙ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማግኘት ቃሉን መርምሩ። ከዚያም ይሖዋ የሚሰጣችሁን ምክር በሥራ ላይ አውሉ። ሕይወታችሁ በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ እንዲሆን ካደረጋችሁ አስደሳችና አርኪ ሕይወት እንደምትመሩ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ!

መዝሙር 132 አንድ ሆነናል

^ አን.5 የምናደርጋቸው አንዳንድ ውሳኔዎች ይሖዋን ለማገልገል ልናውል በምንችለው ጊዜና ጉልበት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። በተለይም አዲስ ባለትዳሮች የሚያደርጓቸው ውሳኔዎች በቀሪው ሕይወታቸው ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ ናቸው። ይህ ርዕስ ደስተኛና ትርጉም ያለው ሕይወት እንዲመሩ የሚረዷቸውን ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ለማድረግ ይረዳቸዋል።

^ አን.5 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።