በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 44

የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?

የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?

‘የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።’—መዝ. 136:1

መዝሙር 108 የአምላክ ታማኝ ፍቅር

ማስተዋወቂያ *

1. ይሖዋ ምን እንድናደርግ አበረታቶናል?

ይሖዋ ታማኝ ፍቅር ያስደስተዋል። (ሆሴዕ 6:6) የሰው ልጆችም ይህን ባሕርይ ከፍ አድርገው እንዲመለከቱት ይፈልጋል። አምላካችን ‘ታማኝ ፍቅርን እንድንወድ’ በነቢዩ ሚክያስ አማካኝነት አበረታቶናል። (ሚክ. 6:8 ግርጌ) እንዲህ ማድረግ እንድንችል ግን ታማኝ ፍቅር ራሱ ምን እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል።

2. ታማኝ ፍቅር ምንድን ነው?

2 ታማኝ ፍቅር ምንድን ነው? “ታማኝ ፍቅር” የሚለው አገላለጽ በአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 230 ጊዜ ገደማ ይገኛል። ይሁንና ታማኝ ፍቅር ምንድን ነው? በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ የሚገኘው “የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፍቻ” እንደሚገልጸው ታማኝ ፍቅር “በከፍተኛ ቅንዓት፣ በጽኑ አቋም፣ በታማኝነትና ከልብ በመነጨ የመውደድ ስሜት ተነሳስቶ ፍቅር ማሳየትን ያመለክታል። ብዙውን ጊዜ አምላክ ለሰዎች ያለውን ፍቅር ለማመልከት የተሠራበት ቢሆንም በሰዎች መካከል ያለውንም ፍቅር ሊያመለክት ይችላል።” ይሖዋ ታማኝ ፍቅር በማሳየት ረገድ ወደር የሌለው ምሳሌ ነው። ይሖዋ ለሰዎች ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን። በቀጣዩ ርዕስ ላይ ደግሞ የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን አንዳችን ለሌላው ታማኝ ፍቅር በማሳየት ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

ይሖዋ “ታማኝ ፍቅሩ . . . እጅግ ብዙ” ነው

3. ይሖዋ ለሙሴ ራሱን የገለጠው እንዴት ነው?

3 እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ስሙንና ባሕርያቱን በማወጅ ራሱን ለሙሴ ገለጠለት። እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ፣ ይሖዋ፣ መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነ አምላክ፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ፣ ታማኝ ፍቅርን ለሺዎች የሚያሳይ፣ ስህተትን፣ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል።” (ዘፀ. 34:6, 7) በእነዚህ ማራኪ ቃላት አማካኝነት ይሖዋ ለሙሴ ስለ ታማኝ ፍቅሩ ልዩ ነገር ነግሮታል። ይህ ነገር ምን ይሆን?

4-5. (ሀ) ይሖዋ ራሱን የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመልሳለን?

4 ይሖዋ ስለ ራሱ ሲናገር ታማኝ ፍቅር እንዳለው ብቻ ሳይሆን “ታማኝ ፍቅሩ . . . እጅግ ብዙ” እንደሆነም ገልጿል። ይህ ዓይነቱ አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ቦታዎች ላይ ይገኛል። (ዘኁ. 14:18፤ ነህ. 9:17፤ መዝ. 86:15፤ 103:8፤ ኢዩ. 2:13፤ ዮናስ 4:2) በሁሉም ቦታዎች ላይ ይህ አገላለጽ የሚያመለክተው ይሖዋን ብቻ ነው፤ ሰዎችን ለማመልከት ተሠርቶበት አያውቅም። ይሖዋ ታማኝ ፍቅሩን በዚህ መንገድ ጎላ አድርጎ መግለጹ ትኩረት የሚስብ አይደለም? ይሖዋ ታማኝ ፍቅርን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ምንም ጥያቄ የለውም። * ከዚህ አንጻር ንጉሥ ዳዊት እንዲህ ብሎ መዘመሩ የሚያስገርም አይደለም፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ታማኝ ፍቅርህ እስከ ሰማያት፣ . . . ይደርሳል። አምላክ ሆይ፣ ታማኝ ፍቅርህ ምንኛ ክቡር ነው! የሰው ልጆች በክንፎችህ ጥላ ሥር ይሸሸጋሉ።” (መዝ. 36:5, 7) እኛስ እንደ ዳዊት የይሖዋን ታማኝ ፍቅር ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን?

5 ስለ ታማኝ ፍቅር ያለንን ግንዛቤ ለማስፋት ሁለት ጥያቄዎችን እንመልስ፦ ይሖዋ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው ለእነማን ነው? የይሖዋ ታማኝ ፍቅር የሚጠቅመንስ እንዴት ነው?

ይሖዋ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው ለእነማን ነው?

6. ይሖዋ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው ለእነማን ነው?

6 ይሖዋ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው ለእነማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለተለያዩ ነገሮች ፍቅር ሊኖረን እንደሚችል ይናገራል። ለምሳሌ ‘ግብርናን፣’ ‘የወይን ጠጅንና ዘይትን፣’ “ተግሣጽን፣” “እውቀትን፣” እንዲሁም “ጥበብን” ልንወድ እንደምንችል ይናገራል። (2 ዜና 26:10፤ ምሳሌ 12:1፤ 21:17፤ 29:3) ታማኝ ፍቅርን ግን ለግዑዝ ነገሮች ወይም ለጽንሰ ሐሳቦች ማሳየት አይቻልም። ይሖዋ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው ማሰብ ለሚችሉ ፍጥረታት ብቻ ነው። ሆኖም ይሖዋ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው ለሁሉም ሰው አይደለም። እንዲህ ዓይነት ፍቅር የሚያሳየው ከእሱ ጋር ልዩ የሆነ ዝምድና ላላቸው ሰዎች ነው። አምላካችን ለወዳጆቹ ታማኝ ነው። ለእነሱ አስደናቂ ዓላማ አለው፤ እንዲሁም መቼም ቢሆን እነሱን መውደዱን አያቆምም።

ይሖዋ እሱን የማያመልኩትን ጨምሮ ለሁሉም ሰዎች ብዙ መልካም ነገሮች ሰጥቷል (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት) *

7. ይሖዋ ለሁሉም ሰዎች ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?

7 ይሖዋ ለሰው ልጆች በሙሉ ፍቅር አሳይቷል። ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ እንዲህ ብሎታል፦ “አምላክ ዓለምን [ማለትም ሁሉንም ሰው] እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”—ዮሐ. 3:1, 16፤ ማቴ. 5:44, 45

ንጉሥ ዳዊትና ነቢዩ ዳንኤል የተናገሩት ሐሳብ እንደሚያሳየው ይሖዋ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው ለሚያውቁት፣ ለሚፈሩት፣ ለሚወዱትና ትእዛዛቱን ለሚያከብሩ ሰዎች ነው (ከአንቀጽ 8-9⁠ን ተመልከት)

8-9. (ሀ) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው ለምንድን ነው? (ለ) ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመለከታለን?

8 ቀደም ሲል እንደተገለጸው ይሖዋ ታማኝ ፍቅሩን የሚያሳየው ከእሱ ጋር የቅርብ ዝምድና ላላቸው ሰዎች ማለትም ለአገልጋዮቹ ብቻ ነው። ንጉሥ ዳዊትና ነቢዩ ዳንኤል የተናገሩት ሐሳብ ይህን ያሳያል። ለምሳሌ ዳዊት “ለሚያውቁህ ታማኝ ፍቅርህን . . . ዘወትር አሳያቸው” ብሏል። በተጨማሪም “ይሖዋ . . . እሱን ለሚፈሩት ታማኝ ፍቅሩን ከዘላለም እስከ ዘላለም ያሳያል” ብሏል። ዳንኤልም ቢሆን እንዲህ ብሏል፦ “እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ለሚወዱህ፣ ትእዛዛትህንም ለሚያከብሩ . . . ታማኝ ፍቅር የምታሳይ . . . አምላክ ነህ።” (መዝ. 36:10፤ 103:17፤ ዳን. 9:4) እነዚህ ጥቅሶች እንደሚያሳዩት ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው ስለሚያውቁት፣ ስለሚፈሩት፣ ስለሚወዱት እና ትእዛዛቱን ስለሚያከብሩ ነው። ይሖዋ ታማኝ ፍቅሩን የሚያሳየው ለሕዝቦቹ ማለትም ለእውነተኛ አገልጋዮቹ ብቻ ነው።

9 ይሖዋን ማገልገል ከመጀመራችን በፊት አምላክ ለሁሉም ሰዎች ከሚያሳየው ፍቅር ተጠቅመናል። (መዝ. 104:14) እሱን ማምለክ ከጀመርን በኋላ ደግሞ ታማኝ ፍቅሩንም አሳይቶናል። እንዲያውም ይሖዋ ለአገልጋዮቹ “ታማኝ ፍቅሬ [ከእናንተ] አይለይም” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ኢሳ. 54:10) በእርግጥም “ይሖዋ ለእሱ ታማኝ የሆነውን ሰው ልዩ በሆነ መንገድ” ይይዘዋል፤ ዳዊትም ይህንን በሕይወቱ እንደተመለከተ እናውቃለን። (መዝ. 4:3) ታዲያ ይሖዋ እኛን ልዩ በሆነ መንገድ የሚይዘን መሆኑ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል? መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል፦ “ጥበበኛ የሆነ ሁሉ እነዚህን ነገሮች ልብ ይላል፤ ደግሞም ይሖዋ በታማኝ ፍቅር ያከናወናቸውን ነገሮች በትኩረት ይመለከታል።” (መዝ. 107:43) ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በአእምሯችን ይዘን፣ የይሖዋ አገልጋዮች ከእሱ ታማኝ ፍቅር የሚያገኟቸውን ሦስት ጥቅሞች እስቲ እንመልከት።

ከይሖዋ ታማኝ ፍቅር ምን ጥቅም እናገኛለን?

ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ተጨማሪ በረከቶችን ይሰጣል (ከአንቀጽ 10-16⁠ን ተመልከት) *

10. የአምላክ ታማኝ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር ማወቃችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? (መዝሙር 31:7)

10 የአምላክ ታማኝ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ይህ ሐሳብ በመዝሙር 136 ውስጥ 26 ጊዜ ተጠቅሷል። የመጀመሪያው ቁጥር እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ ጥሩ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” (መዝ. 136:1) ከቁጥር 2 እስከ 26 ላይም “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” የሚለው አዝማች ይገኛል። ይህን መዝሙር ስናነብ ይሖዋ ታማኝ ፍቅሩን ያለማቋረጥ ያሳየባቸውን በርካታ መንገዶች እንመለከታለን። “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” የሚለው አዝማች አምላክ ለሕዝቦቹ የሚያሳየው ፍቅር ጊዜያዊ እንዳልሆነ ያረጋግጥልናል። ይሖዋ በአገልጋዮቹ ቶሎ ተስፋ እንደማይቆርጥ ማወቃችን ምንኛ የሚያበረታታ ነው! ከዚህ ይልቅ ከእነሱ ጋር ይጣበቃል፤ በተለይ አገልጋዮቹ መከራ ሲያጋጥማቸው በፍጹም ከጎናቸው አይለይም። የምናገኘው ጥቅም፦ ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሚጣበቅ ማወቃችን ደስታና ብርታት ይሰጠናል፤ ይህም የሚያጋጥመንን መከራ ለመቋቋምና በሕይወት ጎዳና ላይ መጓዛችንን ለመቀጠል ይረዳናል።መዝሙር 31:7ን አንብብ።

11. በመዝሙር 86:5 መሠረት ይሖዋ ይቅር እንዲል የሚያነሳሳው ምንድን ነው?

11 የአምላክ ታማኝ ፍቅር ይቅር ባይ እንዲሆን ያነሳሳዋል። ይሖዋ አንድ ኃጢአተኛ ከልቡ ንስሐ እንደገባና በኃጢአት ጎዳና ላይ መመላለሱን እንዳቆመ ሲመለከት ታማኝ ፍቅሩ ግለሰቡን ይቅር እንዲለው ያነሳሳዋል። መዝሙራዊው ዳዊት ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፤ ለበደላችን የሚገባውንም ብድራት አልከፈለንም።” (መዝ. 103:8-11) ዳዊት የሕሊና ወቀሳ ምን ያህል ከባድ ሸክም እንደሆነ ከራሱ ተሞክሮ ያውቃል። ሆኖም ዳዊት፣ ይሖዋ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ እንደሆነም ተመልክቷል። ይሖዋ ይቅር እንዲል የሚያነሳሳው ምንድን ነው? መልሱን መዝሙር 86:5 ላይ እናገኛለን። (ጥቅሱን አንብብ።) ዳዊት በጸሎቱ ላይ እንደገለጸው ይሖዋ ይቅር የሚለው እሱን ለሚጠሩ ሁሉ የሚያሳየው ታማኝ ፍቅር ወሰን ስለሌለው ነው።

12-13. ቀደም ሲል በፈጸምነው ኃጢአት የተነሳ የበደለኝነት ስሜት የሚያሠቃየን ከሆነ ምን ሊረዳን ይችላል?

12 ኃጢአት ስንፈጽም የጸጸት ስሜት ቢሰማን ተገቢ ነው፤ እንዲያውም ይህ ስሜት ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ንስሐ እንድንገባና ስህተታችንን ለማረም እርምጃ እንድንወስድ ያነሳሳናል። ይሁንና አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ቀደም ሲል በፈጸሙት ኃጢአት የተነሳ በበደለኝነት ስሜት ተውጠዋል። ልባቸው በእጅጉ ስለሚኮንናቸው ንስሐ ቢገቡም እንኳ ይሖዋ ጨርሶ ይቅር ሊላቸው እንደማይችል ይሰማቸዋል። አንተም እንዲህ ያለ ስሜት የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ታማኝ ፍቅር ለማሳየት ዝግጁ እንደሆነ ማወቅህ በእጅጉ ይጠቅምሃል።

13 የምናገኘው ጥቅም፦ ፍጹማን ባንሆንም እንኳ ንጹሕ ሕሊና ይዘን ይሖዋን በደስታ ማገልገል እንችላለን። ይህ ሊሆን የቻለው “የልጁ የኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ” ስለሚያነጻን ነው። (1 ዮሐ. 1:7) ባለብህ አለፍጽምና ምክንያት ተስፋ ከቆረጥክ ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆነ አልፎ ተርፎም ይህን ለማድረግ እንደሚጓጓ አስታውስ። ዳዊት በታማኝ ፍቅርና በይቅር ባይነት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት ብሎ እንደገለጸው ልብ በል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እሱ ለሚፈሩት የሚያሳየው ታማኝ ፍቅር ታላቅ ነውና። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ በደላችንን ከእኛ አራቀ።” (መዝ. 103:11, 12) በእርግጥም ይሖዋ “ይቅርታው ብዙ ነው።”—ኢሳ. 55:7

14. ዳዊት የአምላክ ታማኝ ፍቅር ስለሚያስገኘው ጥበቃ ምን ብሏል?

14 የአምላክ ታማኝ ፍቅር መንፈሳዊ ጥበቃ ያስገኝልናል። ዳዊት ወደ ይሖዋ ሲጸልይ እንዲህ ብሏል፦ “አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፤ ከጭንቀት ትሰውረኛለህ። በድል እልልታ ትከበኛለህ። . . . በይሖዋ የሚታመን ሰው . . . ታማኝ ፍቅሩ ይከበዋል።” (መዝ. 32:7, 10) ጥንታዊ ከተሞች በቅጥር መከበባቸው ለነዋሪዎቹ ጥበቃ ያስገኝ ነበር። በተመሳሳይም የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ዙሪያችንን በመክበብ፣ ታማኝነታችንን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ነገሮች መንፈሳዊ ጥበቃ ያስገኝልናል። በተጨማሪም የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ወደ ራሱ እንዲስበን ያነሳሳዋል።—ኤር. 31:3

15. የይሖዋ ታማኝ ፍቅር እንደ መጠጊያና እንደ ምሽግ የሆነው እንዴት ነው?

15 ዳዊት የአምላክ ሕዝቦች የሚያገኙትን ጥበቃ ለመግለጽ ሌላም ምሳሌ ተጠቅሟል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ታማኝ ፍቅር የሚያሳየኝ አምላክ አስተማማኝ መጠጊያዬ ነው።” በተጨማሪም ዳዊት ስለ ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “እሱ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየኝ አምላኬና ምሽጌ፣ አስተማማኝ መጠጊያዬና ታዳጊዬ፣ ጋሻዬና መጠለያዬ . . . ነው።” (መዝ. 59:17፤ 144:2) ዳዊት የይሖዋን ታማኝ ፍቅር ከመጠጊያ እና ከምሽግ ጋር ያመሳሰለው ለምንድን ነው? የምንኖረው የትም ይሁን የት ይሖዋ የእሱ አገልጋዮች እስከሆንን ድረስ ከእሱ ጋር ያለንን ውድ ዝምድና ይዘን መቀጠል እንድንችል የሚያስፈልገንን ጥበቃ ሁሉ ያደርግልናል። በመዝሙር 91 ላይም ተመሳሳይ ማረጋገጫ እናገኛለን። ጥቅሱ “ይሖዋን ‘አንተ መጠጊያዬና ምሽጌ . . . ነህ’ እለዋለሁ” ይላል። (መዝ. 91:1-3, 9, 14) ሙሴም ተመሳሳይ አገላለጽ በመጠቀም ይሖዋ መጠጊያችን እንደሆነ ተናግሯል። (መዝ. 90:1 ግርጌ) በተጨማሪም ሙሴ በሕይወቱ መገባደጃ አካባቢ ሌላ የሚያጽናና አገላለጽ ተጠቅሟል፤ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አምላክ ከጥንት ጀምሮ መሸሸጊያ ነው፤ ዘላለማዊ ክንዶቹ ከበታችህ ናቸው።” (ዘዳ. 33:27) “ዘላለማዊ ክንዶቹ ከበታችህ ናቸው” የሚለው አገላለጽ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

16. የትኞቹን ሁለት በረከቶች ማግኘት እንችላለን? (መዝሙር 136:23)

16 ይሖዋ መጠጊያችን ከሆነ የደህንነት ስሜት ይሰማናል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ስሜታችን ከመደቆሱ የተነሳ ቀና ማለት ሊከብደን ይችላል። እንዲህ በሚሰማን ጊዜ ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው? (መዝሙር 136:23ን አንብብ።) ክንዶቹን ከሥራችን አድርጎ ደግፎ ያነሳናል፤ እንዲሁም በእግራችን እንድንቆም ይረዳናል። (መዝ. 28:9፤ 94:18) የምናገኘው ጥቅም፦ ይሖዋ ምንጊዜም እንደሚደግፈን እናውቃለን፤ ይህም በሁለት መንገዶች እንደሚባርከን እንድናስታውስ ያደርገናል። አንደኛ፣ የምንኖረው የትም ይሁን የት አስተማማኝ መጠጊያ አለን። ሁለተኛ፣ አፍቃሪ የሆነው የሰማዩ አባታችን በጥልቅ ያስብልናል።

የአምላክ ታማኝ ፍቅር የመተማመን ስሜት እንዲያድርብን ያደርጋል

17. የአምላክ ታማኝ ፍቅር የመተማመን ስሜት እንዲያድርብን የሚያደርገው እንዴት ነው? (መዝሙር 33:18-22)

17 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ የሚያስፈልገንን ድጋፍ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (2 ቆሮ. 4:7-9) ነቢዩ ኤርምያስ “ከይሖዋ ታማኝ ፍቅር የተነሳ ሙሉ በሙሉ አልጠፋንም፤ ምሕረቱ ፈጽሞ አያልቅምና” ብሏል። (ሰቆ. 3:22) የይሖዋ ታማኝ ፍቅር እንደማይለየን እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ምክንያቱም መዝሙራዊው “የይሖዋ ዓይን የሚፈሩትን፣ ደግሞም ታማኝ ፍቅሩን የሚጠባበቁትን በትኩረት ይመለከታል” ብሏል።መዝሙር 33:18-22ን አንብብ።

18-19. (ሀ) ከዚህ ጥናት ምን ትምህርት አግኝተናል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

18 ከዚህ ጥናት ምን ትምህርት አግኝተናል? ይሖዋን ማገልገል ከመጀመራችን በፊት አምላክ ለሁሉም ሰዎች ከሚያሳየው ፍቅር እንጠቀም ነበር። እሱን ማምለክ ከጀመርን ወዲህ ግን ታማኝ ፍቅሩንም አሳይቶናል። ይህ ፍቅር ይሖዋ በክንዶቹ እቅፍ አድርጎ ጥበቃ እንዲያደርግልን ያነሳሳዋል። ይሖዋ ምንጊዜም ከጎናችን አይለይም፤ እንዲሁም የሰጠንን አስደናቂ ተስፋዎች ይፈጽምልናል። ይሖዋ ለዘላለም የእሱ ወዳጆች እንድንሆን ይፈልጋል! (መዝ. 46:1, 2, 7) በመሆኑም ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ይሖዋ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ የሚያስፈልገንን ብርታት ይሰጠናል።

19 ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ ተመልክተናል። እኛም አንዳችን ለሌላው ታማኝ ፍቅር እንድናሳይ ይጠብቅብናል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህንን አስፈላጊ ጉዳይ ያብራራል።

መዝሙር 136 ከይሖዋ የምናገኘው “ሙሉ ወሮታ”

^ አን.5 ታማኝ ፍቅር ምንድን ነው? ይሖዋ ታማኝ ፍቅሩን የሚያሳየው ለእነማን ነው? ታማኝ ፍቅር የሚያሳያቸው ሰዎችስ ምን ጥቅም ያገኛሉ? በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን። ቀጣዩ የጥናት ርዕስም የሚናገረው ስለዚህ ግሩም ባሕርይ ነው።

^ አን.4 የአምላክ ታማኝ ፍቅር ብዙ እንደሆነ የሚገልጹ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችም አሉ።—ነህምያ 13:22⁠ን፤ መዝሙር 69:13⁠ን፤ 106:7⁠ን እና ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:32⁠ን ተመልከት።

^ አን.54 የሥዕሉ መግለጫ፦ ይሖዋ አገልጋዮቹን ጨምሮ ለሁሉም ሰዎች ፍቅር ያሳያል። ከሰዎቹ በላይ ያሉት ሥዕሎች አምላክ ፍቅሩን ያሳየባቸውን አንዳንድ መንገዶች ይጠቁማሉ። ከእነዚህ መካከል ዋነኛው የቤዛው ዝግጅት ነው።

^ አን.62 የሥዕሉ መግለጫ፦ ይሖዋ የእሱ አገልጋዮች ለመሆንና በቤዛው ለማመን የመረጡ ሰዎችን ልዩ በሆነ መንገድ ይይዛቸዋል። የይሖዋ አገልጋዮች አምላክ ለሁሉም ሰዎች ከሚያሳየው ፍቅር በተጨማሪ የእሱን ታማኝ ፍቅር ማጣጣም ይችላሉ። ከይሖዋ ታማኝ ፍቅር መግለጫዎች አንዳንዶቹ ሥዕሉ ላይ ይታያሉ።