በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 47

ጠንካራ እምነት ይዛችሁ ትገኙ ይሆን?

ጠንካራ እምነት ይዛችሁ ትገኙ ይሆን?

“ልባችሁ አይረበሽ። . . . እመኑ።”—ዮሐ. 14:1

መዝሙር 119 ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል

ማስተዋወቂያ *

1. ራሳችንን ምን ብለን እንጠይቅ ይሆናል?

ከፊታችን ስለሚጠብቁን ክንውኖች ማለትም በሐሰት ሃይማኖት ላይ ስለሚደርሰው ጥፋት፣ የማጎጉ ጎግ ስለሚሰነዝረው ጥቃት እንዲሁም ስለ አርማጌዶን ጦርነት ስታስቡ አልፎ አልፎ ፍርሃት ይሰማችኋል? ‘ያንን አስፈሪ ጊዜ ታማኝነቴን ጠብቄ በጽናት አልፈው ይሆን?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ? እንዲህ ዓይነት ስጋት አድሮባችሁ የሚያውቅ ከሆነ በጭብጡ ጥቅስ ላይ ስለሚገኙት የኢየሱስ ቃላት የምናደርገው ውይይት በእጅጉ ይጠቅማችኋል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ልባችሁ አይረበሽ። . . . እመኑ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 14:1) ጠንካራ እምነት ካለን ወደፊት የሚመጡትን ፈተናዎች በልበ ሙሉነት ማለፍ እንችላለን።

2. እምነታችንን ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

2 በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች እንዴት እንደምንወጣቸው ማጤናችን፣ ወደፊት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት ማለፍ እንድንችል እምነታችንን ለማጠናከር ይረዳናል። በአሁኑ ጊዜ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን የምንሰጠውን ምላሽ ስናጤን እምነታችንን በየትኞቹ አቅጣጫዎች ማጠናከር እንደሚያስፈልገን እናስተውላለን። እያንዳንዱን ፈተና በጽናት ስናልፍ እምነታችን ይጠናከራል። ይህ ደግሞ ወደፊት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት ለማለፍ ይረዳናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያጋጠሟቸውን አራት ሁኔታዎች እንመለከታለን፤ እነዚህ ሁኔታዎች ደቀ መዛሙርቱ እምነታቸውን ማጠናከር እንደሚያስፈልጋቸው አሳይተዋል። በተጨማሪም እኛም በዛሬው ጊዜ ምን ዓይነት ተመሳሳይ ፈተናዎች ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ እንዲሁም እነዚህ ፈተናዎች ለወደፊቱ ጊዜ የሚያዘጋጁን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

አምላክ ቁሳዊ ፍላጎታችንን እንደሚያሟላልን እምነት ማሳደር

የኢኮኖሚ ችግር ሊያጋጥመን ይችላል፤ ሆኖም እምነታችን በይሖዋ አገልግሎት ላይ እንድናተኩር ይረዳናል (ከአንቀጽ 3-6⁠ን ተመልከት)

3. በማቴዎስ 6:30, 33 ላይ ኢየሱስ ስለ እምነት ምን ብሏል?

3 አንድ የቤተሰብ ራስ ለሚስቱና ለልጆቹ በቂ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ማቅረብ እንደሚፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም። ይሁንና በምንኖርበት በዚህ አስቸጋሪ ዘመን ይህን ማድረግ ቀላል የማይሆንበት ጊዜ አለ። አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻችን ከሥራቸው ተፈናቅለዋል፤ እንዲሁም ሌላ ሥራ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። ሌሎች ደግሞ ያገኙት ሥራ ለክርስቲያኖች ተገቢ ባለመሆኑ ምክንያት በዚያ ሥራ ላለመቀጠር ወስነዋል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመን ይሖዋ ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ነገር በሆነ መንገድ እንደሚያሟላልን ጠንካራ እምነት ማሳደር ያስፈልገናል። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ይህን ሐሳብ ለደቀ መዛሙርቱ በግልጽ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:30, 33ን አንብብ።) ይሖዋ መቼም ቢሆን እንደማይተወን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ከሆንን ትኩረታችንን በይሖዋ አገልግሎት ላይ ማሳረፍ እንችላለን። አምላካችን የሚያስፈልገንን ቁሳዊ ነገር የሚያሟላልን እንዴት እንደሆነ ስንመለከት ይሖዋ ይበልጥ እውን ይሆንልናል፤ እምነታችንም ይጠናከራል።

4-5. የአንድ ቤተሰብ አባላት በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት በተጨነቁበት ወቅት የረዳቸው ምንድን ነው?

4 በቬኔዙዌላ የሚገኝ አንድ ቤተሰብ አባላት በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት በተጨነቁበት ወቅት የይሖዋን እርዳታ ያዩት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ወንድም ሚጌል ካስትሮ እና ቤተሰቡ ቀደም ሲል እርሻቸውን በማልማት በቂ ገቢ ያገኙ ነበር። ሆኖም መሣሪያ የታጠቁ ወንበዴዎች የእርሻ መሬታቸውን ወሰዱባቸው፤ እንዲሁም ከንብረታቸው አፈናቀሏቸው። አባትየው ሚጌል እንዲህ ብሏል፦ “አሁን በዋነኝነት ራሳችንን የምናስተዳድረው ከሌሎች በተበደርነው ትንሽ መሬት ላይ በምናለማው ሰብል ነው። በየቀኑ ጠዋት ላይ ይሖዋ ለዚያ ቀን የሚያስፈልገንን ነገር እንዲሰጠን እጠይቀዋለሁ።” ለዚህ ቤተሰብ ኑሮ ከባድ ነው። ሆኖም አፍቃሪው አባታቸው ዕለታዊ ፍላጎታቸውን እንደሚያሟላላቸው ሙሉ በሙሉ በመተማመን አዘውትረው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ፤ እንዲሁም በአገልግሎት ይካፈላሉ። በሕይወታቸው ውስጥ መንግሥቱን ያስቀድማሉ፤ ይሖዋም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ያሟላላቸዋል።

5 ሚጌልና ባለቤቱ ዩራይ እንዲህ ዓይነት መከራ ቢያጋጥማቸውም ይሖዋ በሚያደርግላቸው እንክብካቤ ላይ ያተኩራሉ። አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በማነሳሳት፣ ቁሳዊ እርዳታ እንዲሰጧቸው ወይም ሚጌል ተስማሚ የሆነ ሥራ እንዲያገኝ እንዲረዱት አድርጓል። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ይሖዋ ቅርንጫፍ ቢሮው በሚያደርገው የእርዳታ እንቅስቃሴ አማካኝነት የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ ነገር ሰጥቷቸዋል። ይሖዋ ፈጽሞ ትቷቸው አያውቅም። በመሆኑም የቤተሰባቸው እምነት ተጠናክሯል። ትልቋ ልጃቸው ሆሴሊን ይሖዋ በአንድ ወቅት የረዳቸው እንዴት እንደሆነ ከገለጸች በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋን እጅ እንዲህ በግልጽ ማየት ልብ ይነካል። ይሖዋን ምንጊዜም ልተማመንበት እንደምችለው ወዳጄ አድርጌ እመለከተዋለሁ።” አክላም እንዲህ ብላለች፦ “በቤተሰብ ያሳለፍነው ፈተና ወደፊት ለሚጠብቁን ይበልጥ ከባድ የሆኑ ፈተናዎች አዘጋጅቶናል።”

6. የኢኮኖሚ ችግር ሲያጋጥማችሁ እምነታችሁን ማጠናከር የምትችሉት እንዴት ነው?

6 የኢኮኖሚ ችግር አጋጥሟችኋል? ከሆነ ሁኔታው ከባድ እንደሚሆንባችሁ ምንም ጥያቄ የለውም። ያላችሁበት ሁኔታ ተፈታታኝ ቢሆንም አጋጣሚውን እምነታችሁን ለማጠናከር ተጠቀሙበት። ወደ ይሖዋ ጸልዩ፤ በማቴዎስ 6:25-34 ላይ የሚገኙትን የኢየሱስን ቃላት አንብቡ፤ እንዲሁም አሰላስሉባቸው። በተጨማሪም በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ለሚጠመዱ ሰዎች ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያሟላላቸው በሚያረጋግጡ በዘመናችን የተገኙ ተሞክሮዎች ላይ አሰላስሉ። (1 ቆሮ. 15:58) እንዲህ ማድረጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ከእናንተ ጋር ተመሳሳይ ችግር ያጋጠማቸውን ሰዎች እንደረዳቸው ሁሉ እናንተንም እንደሚረዳችሁ ይበልጥ እርግጠኛ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል። ይሖዋ ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል፤ የሚያስፈልጋችሁን ነገር እንዴት እንደሚያሟላላችሁም ያውቃል። በሕይወታችሁ ውስጥ የይሖዋን እርዳታ ስትመለከቱ እምነታችሁ ይጠናከራል፤ ይህም ወደፊት የሚያጋጥሟችሁን ይበልጥ ከባድ የሆኑ ፈተናዎች በጽናት እንድትቋቋሙ ይረዳችኋል።—ዕን. 3:17, 18

‘ኃይለኛ ማዕበልን’ በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል እምነት

ጠንካራ እምነት ቃል በቃልም ሆነ በምሳሌያዊ ሁኔታ የሚያጋጥመንን ኃይለኛ ማዕበል ለማለፍ ይረዳናል (ከአንቀጽ 7-11⁠ን ተመልከት)

7. በማቴዎስ 8:23-26 መሠረት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ‘በኃይለኛ ማዕበል’ እምነታቸው የተፈተነው እንዴት ነው?

7 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በባሕር ላይ እየተጓዙ ሳሉ ማዕበል አጋጥሟቸው ነበር። ኢየሱስ ይህን አጋጣሚ ደቀ መዛሙርቱ በየትኛው አቅጣጫ እምነታቸውን ማጠናከር እንደሚያስፈልጋቸው ለማስተማር ተጠቀመበት። (ማቴዎስ 8:23-26ን አንብብ።) በማዕበሉ ምክንያት ጀልባዋ በውኃ ተሞልታ ልትሰጥም ተቃርባ የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ለጥ ብሎ ተኝቶ ነበር። በፍርሃት የተዋጡት ደቀ መዛሙርቱ ቀስቅሰው እንዲያድናቸው ጠየቁት፤ በዚህ ጊዜ ጌታ “እናንተ እምነት የጎደላችሁ! ለምን ትሸበራላችሁ?” በማለት በደግነት ተግሣጽ ሰጣቸው። ደቀ መዛሙርቱ ይሖዋ ኢየሱስንም ሆነ ከእሱ ጋር ያሉትን ሰዎች ከጉዳት ለመጠበቅ ኃይሉ እንዳለው መተማመን ነበረባቸው። ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? ጠንካራ እምነት ካለን ቃል በቃልም ሆነ በምሳሌያዊ ሁኔታ የሚያጋጥመንን “ኃይለኛ ማዕበል” መቋቋም እንችላለን።

8-9. የአኔል እምነት የተፈተነው እንዴት ነው? የረዳትስ ምንድን ነው?

8 በፖርቶ ሪኮ የምትኖር አኔል የተባለች ያላገባች እህት ያጋጠማትን ከባድ ፈተና በጽናት መቋቋሟ እምነቷን ያጠናከረላት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። አኔል ቃል በቃል “ኃይለኛ ማዕበል” አጋጥሟት ነበር ሊባል ይችላል። በ2017 በአካባቢዋ የተከሰተው ዝናብ የቀላቀለ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ቤቷን አፈረሰው። መከራዋ ግን በዚህ አላበቃም፤ በአውሎ ነፋሱ ምክንያት ሥራዋን አጣች። አኔል እንዲህ ብላለች፦ “ይሄ ሁሉ መከራ ሲደርስብኝ ተጨንቄ ነበር። ሆኖም ወደ ይሖዋ በመጸለይ በእሱ እንደምታመን ማሳየት እንዳለብኝ ተማርኩ፤ እንዲሁም የሚሰማኝ ጭንቀት ማድረግ ያለብኝን ነገር ከማድረግ እንዲያግደኝ መፍቀድ እንደሌለብኝ ተገነዘብኩ።”

9 አኔል ፈተናውን ለመቋቋም የረዳት ሌላው ነገር ታዛዥነት እንደሆነ ገልጻለች። እንዲህ ብላለች፦ “ድርጅቱ የሚሰጠውን መመሪያ መከተሌ እንድረጋጋ ረድቶኛል። ያገኘሁት መንፈሳዊ ማበረታቻ እንዲሁም ከወንድሞቼ ያገኘሁት ቁሳዊ ድጋፍ የይሖዋን እጅ እንዳይ አድርጎኛል። ይሖዋ ካሰብኩት በላይ አትረፍርፎ ሰጥቶኛል፤ ከዚህ በላይ ምን ልጠይቅ እችላለሁ! እምነቴም በእጅጉ ተጠናክሯል።”

10. “ኃይለኛ ማዕበል” ካጋጠማችሁ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

10 እናንተስ በሕይወታችሁ ውስጥ “ኃይለኛ ማዕበል” አጋጥሟችኋል? በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት መከራ ደርሶባችሁ ይሆናል። ወይም ደግሞ ምሳሌያዊ ማዕበል አጋጥሟችሁ ይሆናል፤ ምናልባትም ባጋጠማችሁ ከባድ የጤና ችግር ምክንያት ተስፋ ቆርጣችሁና ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ግራ ገብቷችሁ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ በጭንቀት ትዋጡ ይሆናል፤ ያም ቢሆን የሚሰማችሁ ጭንቀት በይሖዋ ከመታመን እንቅፋት እንዲሆንባችሁ አትፍቀዱ። ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ይሖዋን አነጋግሩት። ይሖዋ ከዚህ ቀደም የረዳችሁ እንዴት እንደሆነ በማሰላሰል እምነታችሁን አጠናክሩ። (መዝ. 77:11, 12) ይሖዋ መቼም ቢሆን እንደማይተዋችሁ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ።

11. አመራር ለሚሰጡት ወንድሞች ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

11 ፈተናዎችን ለመቋቋም ሊረዳችሁ የሚችለው ሌላው ነገር ምንድን ነው? አኔል እንደጠቀሰችው ታዛዥነት ይረዳችኋል። ይሖዋ እና ኢየሱስ በሚተማመኑባቸው ሰዎች ተማመኑ። አመራር እንዲሰጡ የተሾሙት ወንድሞች አንዳንድ ጊዜ የሚሰጡት መመሪያ አይዋጥልን ይሆናል። ይሁንና ይሖዋ ታዛዦችን ይባርካል። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ ምሳሌዎችና በዘመናችን ያሉ ወንድሞችና እህቶች ያጋጠሟቸው ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ታዛዥነት ሕይወት ያድናል። (ዘፀ. 14:1-4፤ 2 ዜና 20:17) እንዲህ ባሉት ምሳሌዎች ላይ አሰላስሉ። እንዲህ ማድረጋችሁ አሁንም ሆነ ወደፊት ድርጅቱ ከሚያደርጋቸው ዝግጅቶች ጋር ተባብራችሁ ለመሥራት ያላችሁን ቁርጠኝነት ያጠናክረዋል። (ዕብ. 13:17) በቅርቡ የሚመጣውን እጅግ ኃይለኛ የሆነ ማዕበልም የምትፈሩበት ምክንያት አይኖርም።—ምሳሌ 3:25

የፍትሕ መጓደልን ለመቋቋም የሚያስችል እምነት

ሳናሰልስ መጸለያችን እምነታችንን ያጠናክርልናል (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)

12. በሉቃስ 18:1-8 መሠረት በእምነት እና የፍትሕ መጓደልን በመቋቋም መካከል ምን ግንኙነት አለ?

12 ኢየሱስ በፍትሕ መጓደል ምክንያት የደቀ መዛሙርቱ እምነት እንደሚፈተን ያውቅ ነበር። እንዲህ ያለውን ሁኔታ እንዲቋቋሙ ለመርዳት ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው። ይህ ምሳሌ በሉቃስ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። ኢየሱስ የነገራቸው ምሳሌ፣ ፍትሕ እንዲፈጸምላት አንድን ዓመፀኛ ዳኛ በተደጋጋሚ ትለምን ስለነበረች አንዲት መበለት የሚገልጽ ነው። ይህች ሴት ሳታቋርጥ ከለመነች መፍትሔ እንደምታገኝ እርግጠኛ ነበረች። ከጊዜ በኋላ ዳኛው ልመናዋን ሰማት። ነጥቡ ምንድን ነው? ይሖዋ ዓመፀኛ አይደለም። ከዚህ አንጻር ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ታዲያ አምላክ . . . ቀን ከሌት ወደ እሱ የሚጮኹት ምርጦቹ ፍትሕ እንዲያገኙ አያደርግም?” (ሉቃስ 18:1-8ን አንብብ።) አክሎም ኢየሱስ “የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ በእርግጥ እንዲህ ያለ እምነት ያገኝ ይሆን?” አለ። (ሉቃስ 18:8 ግርጌ) የፍትሕ መጓደል ሲፈጸምብን በመታገሥና በመጽናት እንደ መበለቷ ያለ ጠንካራ እምነት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። እንዲህ ያለ እምነት ካለን፣ ይዋል ይደር እንጂ ይሖዋ እንደሚረዳን እርግጠኞች እንሆናለን። ጸሎት ኃይል እንዳለውም ማመን ይኖርብናል። አንዳንድ ጊዜ ጸሎታችን ያልተጠበቀ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል።

13. አንድ ቤተሰብ የፍትሕ መጓደል በደረሰባቸው ወቅት ጸሎት የረዳቸው እንዴት ነው?

13 በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የምትኖር ቬሮ የተባለች እህት ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት። ታጣቂዎች በምትኖርበት መንደር ላይ ጥቃት በሰነዘሩበት ወቅት እሷ፣ የማያምነው ባሏ እንዲሁም የ15 ዓመት ልጃቸው መንደሩን ለቀው ተሰደዱ። እየተጓዙ ሳሉ አንድ ኬላ ላይ ደረሱ፤ በዚያም ታጣቂዎቹ በቁጥጥር ሥር አዋሏቸው፤ እንደሚገድሏቸውም ዛቱባቸው። ቬሮ ስታለቅስ ልጇ ጮክ ብላ በመጸለይ ልታረጋጋት ሞከረች፤ በጸሎቷ ላይ የይሖዋን ስም ደጋግማ ትጠቅስ ነበር። ጸልያ ከጨረሰች በኋላ የታጣቂዎቹ አዛዥ “አንቺ ልጅ፣ ጸሎት ያስተማረሽ ማን ነው?” ብሎ ጠየቃት። እሷም “እናቴ ነች፤ በማቴዎስ 6:9-13 ላይ ያለውን ናሙና ተጠቅማ ነው ያስተማረችኝ” አለችው። አዛዡም “ከወላጆችሽ ጋር በሰላም ሂጂ፤ አምላካችሁ ይሖዋ ይጠብቃችሁ!” አላት።

14. እምነታችን እንዴት ሊፈተን ይችላል? ፈተናውን በጽናት ለመቋቋም የሚረዳንስ ምንድን ነው?

14 እንዲህ ያሉት ተሞክሮዎች የጸሎትን ኃይል ፈጽሞ አቅልለን እንዳንመለከተው ያስተምሩናል። ይሁንና ያቀረባችሁት ጸሎት በአፋጣኝ ወይም አስደናቂ በሆነ መንገድ መልስ ባያገኝስ? በዚህ ጊዜ እምነታችሁ ሊፈተን ይችላል። ታዲያ ይህን ሁኔታ በጽናት ለመቋቋም የሚረዳችሁ ምንድን ነው? በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰችው መበለት መጸለያችሁን ቀጥሉ። አምላካችን እንደማይተዋችሁ እንዲሁም በትክክለኛው ጊዜ፣ በሆነ መንገድ ጸሎታችሁን እንደሚመልስላችሁ ተማመኑ። ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጣችሁ ሳታቋርጡ ለምኑት። (ፊልጵ. 4:13) በቅርቡ ይሖዋ አትረፍርፎ ስለሚባርካችሁ ቀደም ሲል ያጋጠሟችሁ መከራዎች ጨርሶ ትዝ እንኳ እንደማይሏችሁ አትዘንጉ። አሁን የሚያጋጥሟችሁን ፈተናዎች በይሖዋ እርዳታ በጽናት ስትቋቋሙ ወደፊት ለሚያጋጥሟችሁ ፈተናዎች ዝግጁ ትሆናላችሁ።—1 ጴጥ. 1:6, 7

እንቅፋቶችን ለመወጣት የሚያስችል እምነት

15. በማቴዎስ 17:19, 20 ላይ እንደተገለጸው የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን ፈተና አጋጥሟቸው ነበር?

15 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ፣ እምነት እንቅፋቶችን ለመወጣት እንደሚረዳቸው አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 17:19, 20ን አንብብ።) ደቀ መዛሙርቱ በተለያዩ ጊዜያት አጋንንት ማስወጣት ችለው የነበረ ቢሆንም በአንድ ወቅት አንድን ጋኔን ማስወጣት አቅቷቸው ነበር። ይህን ማድረግ ያልቻሉት ለምንድን ነው? ኢየሱስ እምነታቸው ስላነሰ እንደሆነ ነግሯቸዋል። ጠንካራ እምነት ካላቸው፣ እንደ ተራራ ያሉ እንቅፋቶችን እንኳ መወጣት እንደሚችሉ ነገራቸው። እኛም በዛሬው ጊዜ ፈጽሞ ልንወጣው የማንችለው የሚመስል ፈተና ሊያጋጥመን ይችላል።

ከባድ ሐዘን ሊያጋጥመን ይችላል፤ ሆኖም እምነታችን በይሖዋ አገልግሎት እንድንጠመድ ይረዳናል (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)

16. ጌዲ የደረሰባትን መሪር ሐዘን ለመቋቋም እምነቷ የረዳት እንዴት ነው?

16 በጓቴማላ የምትኖር ጌዲ የተባለች እህት ያጋጠማትን ሁኔታ እንመለከት። ከጉባኤ ስብሰባ ወደ ቤት እየተመለሱ ሳሉ ባለቤቷ ኤዲ በወንጀለኞች ተገደለ። ጌዲ የደረሰባትን መሪር ሐዘን ለመቋቋም እምነቷ የረዳት እንዴት ነው? እንዲህ ብላለች፦ “መጸለዬ ሸክሜን በይሖዋ ላይ እንድጥል ረድቶኛል፤ ይህም ውስጣዊ ሰላም ይሰጠኛል። በቤተሰቦቼና በጉባኤ ውስጥ ባሉ ጓደኞቼ አማካኝነት ይሖዋ እንደሚረዳኝ ይሰማኛል። በይሖዋ አገልግሎት መጠመዴ ሥቃዬ ቀለል እንዲለኝ አድርጓል፤ በተጨማሪም ስለ ነገ ከልክ በላይ ሳልጨነቅ እያንዳንዱን ቀን ማለፍ እንድችል ይረዳኛል። ያሳለፍኩት ነገር፣ ወደፊት ምንም ዓይነት ፈተና ቢመጣ በይሖዋ፣ በኢየሱስና በድርጅቱ እርዳታ ልወጣው እንደምችል እርግጠኛ እንድሆን አድርጎኛል።”

17. እንደ ተራራ ያለ እንቅፋት ሲያጋጥመን ምን ማድረግ እንችላለን?

17 የምትወዱትን ሰው በሞት በማጣታችሁ ምክንያት በሐዘን ተውጣችኋል? ከሞት ስለተነሱ ሰዎች የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን በማንበብ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያላችሁን እምነት አጠናክሩ። የቤተሰባችሁ አባል ከጉባኤ በመወገዱ ምክንያት ልባችሁ በሐዘን ተሰብሯል? አምላክ የሚሰጠው ተግሣጽ ምንጊዜም ጠቃሚ እንደሆነ ያላችሁን እምነት ለማጠናከር የግል ጥናት አድርጉ። ያጋጠማችሁ ችግር ምንም ይሁን ምን አጋጣሚውን እምነታችሁን ለመገንባት ተጠቀሙበት። ልባችሁን በይሖዋ ፊት አፍስሱ። ራሳችሁን አታግልሉ፤ ከዚህ ይልቅ ከወንድሞቻችሁና ከእህቶቻችሁ ጋር ተቀራረቡ። (ምሳሌ 18:1) ለመጽናት በሚረዷችሁ እንቅስቃሴዎች ተካፈሉ፤ በእነዚህ እንቅስቃሴዎች የምትካፈሉት እያለቀሳችሁ ቢሆንም እንኳ እንዲህ ማድረጋችሁን አታቁሙ። (መዝ. 126:5, 6) አዘውትራችሁ በስብሰባዎች ላይ ተገኙ፤ በአገልግሎት ተካፈሉ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን አንብቡ። በተጨማሪም ይሖዋ ባዘጋጀላችሁ በረከቶች ላይ ምንጊዜም ትኩረት አድርጉ። ይሖዋ የሚረዳችሁ እንዴት እንደሆነ ስታስተውሉ በእሱ ላይ ያላችሁ እምነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይጠናከራል።

“እምነት ጨምርልን”

18. እምነታችሁ በሆነ አቅጣጫ እንደደከመ ካስተዋላችሁ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

18 ከዚህ በፊት ያጋጠሟችሁም ሆነ በአሁኑ ጊዜ እያጋጠሟችሁ ያሉት ፈተናዎች እምነታችሁ በሆነ አቅጣጫ እንደደከመ ካሳዩአችሁ ተስፋ አትቁረጡ። ሁኔታውን እምነታችሁን ለማጠናከር እንደሚያስችል አጋጣሚ አድርጋችሁ ተመልከቱት። እንደ ኢየሱስ ሐዋርያት “እምነት ጨምርልን” ብላችሁ ጠይቁ። (ሉቃስ 17:5) በተጨማሪም በዚህ ርዕስ ውስጥ በተመለከትናቸው ምሳሌዎች ላይ አሰላስሉ። እንደ ሚጌል እና እንደ ዩራይ፣ ይሖዋ የረዳችሁን ጊዜያት አስታውሱ። እንደ ቬሮ ልጅ እና እንደ አኔል፣ በተለይም ከባድ ችግር ሲያጋጥማችሁ ወደ ይሖዋ አጥብቃችሁ ጸልዩ። እንዲሁም እንደ ጌዲ፣ ይሖዋ በቤተሰቦቻችሁ ወይም በጓደኞቻችሁ አማካኝነት የሚያስፈልጋችሁን እርዳታ ሊሰጣችሁ እንደሚችል አስተውሉ። ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሟችሁን ፈተናዎች በጽናት ለማለፍ እንዲረዳችሁ ከፈቀዳችሁ ወደፊትም ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥማችሁ ለመጽናት እንደሚረዳችሁ ይበልጥ እርግጠኛ ትሆናላችሁ።

19. ኢየሱስ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር? እናንተስ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ?

19 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በየትኞቹ አቅጣጫዎች እምነት እንደጎደላቸው ጠቁሟቸዋል። ሆኖም ወደፊት የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በይሖዋ እርዳታ በጽናት ማለፍ እንደሚችሉ አልተጠራጠረም። (ዮሐ. 14:1፤ 16:33) ከፊታችን ከሚመጣው ታላቅ መከራ ጠንካራ እምነት ይዘው የሚያልፉ እጅግ ብዙ ሕዝብ እንደሚኖሩም እርግጠኛ ነበር። (ራእይ 7:9, 14) እናንተስ ከእነሱ መካከል ትገኙ ይሆን? በአሁኑ ወቅት ያገኛችሁትን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅማችሁ እምነታችሁን የምታጠናክሩ ከሆነ በይሖዋ ጸጋ ከእነሱ መካከል መገኘት ትችላላችሁ።—ዕብ. 10:39

መዝሙር 118 “እምነት ጨምርልን”

^ አን.5 ይህ ሥርዓት የሚያበቃበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። ይሁንና ‘ያን ጊዜ በጽናት ለማለፍ የሚያስችል ጠንካራ እምነት ይኖረኝ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ አንዳንዴ ያሳስበን ይሆናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ እምነታችንን ለማጠናከር የሚረዱንን ተሞክሮዎችና ጠቃሚ ትምህርቶች እንመለከታለን።