በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 47

ምንም ነገር ከይሖዋ እንዲለያችሁ አትፍቀዱ

ምንም ነገር ከይሖዋ እንዲለያችሁ አትፍቀዱ

“ይሖዋ ሆይ፣ . . . በአንተ እታመናለሁ።”—መዝ. 31:14

መዝሙር 122 ጸንታችሁ ቁሙ፣ አትነቃነቁ!

ማስተዋወቂያ a

1. ይሖዋ ወደ እኛ መቅረብ እንደሚፈልግ በምን እናውቃለን?

 ይሖዋ ወደ እሱ እንድንቀርብ ጋብዞናል። (ያዕ. 4:8) አምላካችን፣ አባታችንና ወዳጃችን መሆን ይፈልጋል። ይሖዋ ጸሎታችንን ይመልስልናል፤ እንዲሁም ፈተና ሲያጋጥመን ይረዳናል። በተጨማሪም ድርጅቱን በመጠቀም ያስተምረናል እንዲሁም ይጠብቀናል። ይሁንና ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

2. ወደ ይሖዋ መቅረብ የምንችለው እንዴት ነው?

2 ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ወደ እሱ መጸለይ እንዲሁም ቃሉን ማንበብና ማሰላሰል ይኖርብናል። ይህን ስናደርግ ልባችን ለእሱ ባለን ፍቅርና አድናቆት ይሞላል። ለእሱ የሚገባውን ውዳሴ ልንሰጠውና ልንታዘዘው እንነሳሳለን። (ራእይ 4:11) ይሖዋን ይበልጥ ባወቅነው መጠን በእሱም ሆነ እኛን ለመርዳት ባቋቋመው ድርጅት ይበልጥ እንተማመናለን።

3. ዲያብሎስ ከይሖዋ ሊለየን የሚሞክረው እንዴት ነው? ሆኖም አምላካችንንና ድርጅቱን ፈጽሞ ላለመተው ምን ይረዳናል? (መዝሙር 31:13, 14)

3 ይሁንና ዲያብሎስ፣ በተለይ ፈተና ሲያጋጥመን ከይሖዋ ሊለየን ይሞክራል። እንዲህ ለማድረግ ምን ስልት ይጠቀማል? በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ያለንን እምነት ቀስ በቀስ ለመሸርሸር ይሞክራል። ሆኖም እሱ የሚሸርባቸውን ሴራዎች ማክሸፍ እንችላለን። በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ጠንካራና የማይናወጥ ከሆነ አምላካችንንና ድርጅቱን በፍጹም አንተውም።—መዝሙር 31:13, 14ን አንብብ።

4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

4 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ያለንን እምነት ሊሸረሽሩ የሚችሉ ከጉባኤው ውጭ የሚመጡ ሦስት ፈተናዎችን እንመለከታለን። እነዚህ ፈተናዎች ከይሖዋ ሊለዩን የሚችሉት እንዴት ነው? የሰይጣንን ሴራዎች ለማክሸፍስ ምን ማድረግ እንችላለን?

ችግር ሲደርስብን

5. ችግሮች በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ያለንን እምነት ሊሸረሽሩት የሚችሉት እንዴት ነው?

5 አንዳንድ ጊዜ እንደ ቤተሰብ ተቃውሞ ወይም ሥራ ማጣት ያሉ ችግሮች ያጋጥሙናል። እነዚህ ችግሮች በይሖዋ ድርጅት ላይ ያለንን እምነት ሊሸረሽሩትና ከአምላካችን ሊለዩን የሚችሉት እንዴት ነው? ረዘም ላለ ጊዜ ችግሮች ሲያጋጥሙን ቅስማችን ሊሰበርና ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። ሰይጣን ደግሞ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ ይሖዋ የሚወደን መሆኑን እንድንጠራጠር ለማድረግ ይሞክራል። ዲያብሎስ ለሚደርስብን ችግር ተጠያቂው ይሖዋ ወይም ድርጅቱ እንደሆነ እንድናስብ ይፈልጋል። በግብፅ የነበሩት አንዳንድ እስራኤላውያንም እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። መጀመሪያ ላይ፣ ይሖዋ እነሱን ከባርነት ለማውጣት ሙሴንና አሮንን እንደሾመላቸው አምነው ነበር። (ዘፀ. 4:29-31) በኋላ ግን ፈርዖን ሕይወታቸውን ከባድ ሲያደርግባቸው፣ ላጋጠማቸው ችግር ሙሴንና አሮንን ተጠያቂ አደረጉ። ‘በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ፊት እንድንጠላ አደረጋችሁን፤ እንዲገድሉንም በእጃቸው ሰይፍ ሰጣችኋቸው’ ብለዋቸዋል። (ዘፀ. 5:19-21) የአምላክን ታማኝ አገልጋዮች ወቀሱ። እንዴት ያሳዝናል! እናንተስ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ችግር ከደረሰባችሁ በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ያላችሁ እምነት እንዳይዳከም ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

6. ችግሮችን መቋቋም ስለሚቻልበት መንገድ ከነቢዩ ዕንባቆም ምን እንማራለን? (ዕንባቆም 3:17-19)

6 በጸሎት ልባችሁን ለይሖዋ አፍስሱ፤ እንዲሁም እርዳታውን ፈልጉ። ነቢዩ ዕንባቆም ብዙ ችግሮች አጋጥመውታል። እንዲያውም በአንድ ወቅት ይሖዋ የሚያስብለት መሆኑን ተጠራጥሮ የነበረ ይመስላል። በመሆኑም በጸሎት ልቡን ለይሖዋ አፈሰሰ። እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ ሆይ፣ እርዳታ ለማግኘት ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? . . . ጭቆናንስ ለምን ዝም ብለህ ታያለህ?” (ዕን. 1:2, 3) ይሖዋ የታማኝ አገልጋዩን ልባዊ ጸሎት መልሶለታል። (ዕን. 2:2, 3) ዕንባቆም በይሖዋ የማዳን ሥራዎች ላይ ካሰላሰለ በኋላ ደስታው ተመለሰለት። ይሖዋ እንደሚያስብለትና የትኛውንም ፈተና ለመቋቋም እንደሚረዳው እርግጠኛ ሆነ። (ዕንባቆም 3:17-19ን አንብብ።) እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ችግሮች ሲያጋጥሟችሁ ወደ ይሖዋ በመጸለይ የሚሰማችሁን ንገሩት። ከዚያም የእሱን እርዳታ ፈልጉ። እንዲህ ካደረጋችሁ ይሖዋ ለመጽናት የሚያስችላችሁን ኃይል እንደሚሰጣችሁ መተማመን ትችላላችሁ። ይሖዋ እንደረዳችሁ ስታዩ ደግሞ በእሱ ላይ ያላችሁ እምነት ይጠናከራል።

7. አንድ የሸርሊ ዘመድ ምን ሊያሳምናት ሞከረ? በይሖዋ ላይ ያላትን እምነት እንዳታጣ የረዳትስ ምንድን ነው?

7 ምንጊዜም ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይኑራችሁ። በፓፑዋ ኒው ጊኒ የምትኖር ሸርሊ የተባለች እህት ችግር ባጋጠማት ጊዜ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ መያዟ የጠቀማት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። b የሸርሊ ቤተሰቦች ድሃ ነበሩ፤ አንዳንዴም ምግብ ለማግኘት ይቸገሩ ነበር። አንድ ዘመዷ በይሖዋ ላይ ያላትን እምነት የሚሸረሽር ነገር ተናገራት። እንዲህ አላት፦ “የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እየረዳኝ ነው ትያለሽ። ታዲያ የት አለ የሚረዳሽ? ቤተሰብሽ አሁንም ድሃ ነው። ‘ስብከት ስብከት’ እያልሽ ጊዜሽን እያባከንሽ ነው።” ሸርሊ እንዲህ ብላለች፦ “‘በእርግጥ አምላክ ያስብልናል?’ የሚል ጥርጣሬ አደረብኝ። በመሆኑም ወዲያውኑ ወደ ይሖዋ በመጸለይ የሚሰማኝን ሁሉ ነገርኩት። መጽሐፍ ቅዱስንና ጽሑፎቻችንን ማንበቤን እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ መገኘቴንና ማገልገሌን ቀጠልኩ።” ብዙም ሳይቆይ ሸርሊ፣ ይሖዋ ቤተሰቧን እየተንከባከበላት እንዳለ ተረዳች። የሚበሉት ነገር አላጡም፤ እንዲሁም ደስተኞች ነበሩ። ሸርሊ “ይሖዋ ጸሎቴን እንደመለሰልኝ ተሰማኝ” ብላለች። (1 ጢሞ. 6:6-8) እናንተም ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይዛችሁ ከቀጠላችሁ ችግርም ሆነ ጥርጣሬ ከይሖዋ ሊለያችሁ አይችልም።

ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ስደት ሲደርስባቸው

8. በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያሉ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ምን ሊደርስባቸው ይችላል?

8 ጠላቶቻችን በመገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት፣ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያሉ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞችን በተመለከተ ውሸት ወይም የተዛባ መረጃ ያሰራጫሉ። (መዝ. 31:13) አንዳንድ ወንድሞች ታስረዋል፤ እንዲሁም የወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በሐሰት ተከሶ በታሰረበት ጊዜ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። ታዲያ ምን አደረጉ?

9. ሐዋርያው ጳውሎስ በታሰረበት ወቅት አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን አደረጉ?

9 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም በታሰረበት ወቅት እሱን መደገፋቸውን አቁመው ነበር። (2 ጢሞ. 1:8, 15) ለምን? ሕዝቡ ጳውሎስን እንደ ወንጀለኛ ስለሚቆጥረው አፍረውበት ይሆን? (2 ጢሞ. 2:8, 9) ወይስ እነሱም ስደት እንዳይደርስባቸው ፈርተው ይሆን? ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን፣ ጳውሎስ ምን ሊሰማው እንደሚችል ለማሰብ ሞክሩ። ጳውሎስ ለእነሱ ሲል ብዙ መከራ አሳልፏል፤ እንዲያውም ሕይወቱን ሳይቀር አደጋ ላይ ጥሏል። (ሥራ 20:18-21፤ 2 ቆሮ. 1:8) ጳውሎስን በችግሩ ጊዜ እንደተዉት ሰዎች ፈጽሞ መሆን አንፈልግም! ታዲያ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ስደት ሲደርስባቸው ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

10. ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ስደት ሲደርስባቸው ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

10 ስደት የሚደርስብን ለምን እንደሆነና የስደቱ ምንጭ ማን እንደሆነ አስታውሱ። ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:12 እንዲህ ይላል፦ “የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል።” ስለዚህ ሰይጣን በተለይ ኃላፊነት ያላቸውን ወንድሞች የጥቃቱ ዒላማ ቢያደርጋቸው ልንደነቅ አይገባም። ሰይጣን እንዲህ ያለ ጥቃት የሚያደርስባቸው ንጹሕ አቋማቸውን እንዲያጎድፉ ለማድረግና እኛን ለማስፈራራት ነው።—1 ጴጥ. 5:8

ጳውሎስ ታስሮ በነበረበት ወቅት ኦኔሲፎሮስ በድፍረት ደግፎታል። በዛሬው ጊዜም፣ በትወናው ላይ እንደሚታየው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የታሰሩ የእምነት አጋሮቻቸውን ይደግፋሉ (ከአንቀጽ 11-12⁠ን ተመልከት)

11. ከኦኔሲፎሮስ ምን ትምህርት እናገኛለን? (2 ጢሞቴዎስ 1:16-18)

11 ወንድሞቻችሁን መደገፋችሁን ቀጥሉ፤ እንዲሁም በታማኝነት ከእነሱ ጋር ተጣበቁ። (2 ጢሞቴዎስ 1:16-18ን አንብብ።) ኦኔሲፎሮስ የተባለ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ ክርስቲያን፣ ጳውሎስ በታሰረበት ወቅት ከሌሎች የተለየ ምላሽ ሰጥቷል። ጳውሎስ ‘በታሰረበት ሰንሰለት አላፈረም።’ ከዚህ ይልቅ ኦኔሲፎሮስ ጳውሎስን አፈላልጎ አገኘው፤ ከዚያም ተግባራዊ እርዳታ ሰጠው። ኦኔሲፎሮስ ይህን ያደረገው የራሱን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎ ነው። እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? የሰው ፍርሃት እንዲያሽመደምደን ወይም ስደት የሚደርስባቸውን ወንድሞች ከመደገፍ ወደኋላ እንድንል እንዲያደርገን መፍቀድ አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ ለእነሱ ጥብቅና ልንቆምና ልንረዳቸው ይገባል። (ምሳሌ 17:17) እነዚህ ወንድሞች ፍቅራችንና እርዳታችን ያስፈልጋቸዋል።

12. በሩሲያ ካሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምን እንማራለን?

12 በሩሲያ የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸው በሚታሰሩበት ጊዜ እንዴት እንደረዷቸው ለማሰብ ሞክሩ። አንዳንዶች ችሎት ፊት ሲቀርቡ ብዙ ወንድሞችና እህቶች እነሱን ለመደገፍ ወደ ፍርድ ቤት ይመጣሉ። ከእነሱ ምሳሌ ምን እንማራለን? ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ስማቸው ሲጠፋ፣ ሲታሰሩ ወይም ስደት ሲደርስባቸው አትሸበሩ። ጸልዩላቸው፤ ቤተሰቦቻቸውን ተንከባከቡላቸው፤ እንዲሁም በሌሎች ተግባራዊ መንገዶች እነሱን ለመርዳት ሞክሩ።—ሥራ 12:5፤ 2 ቆሮ. 1:10, 11

ሲፌዝብን

13. ፌዝ በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ያለንን እምነት ሊሸረሽረው የሚችለው እንዴት ነው?

13 የማያምኑ ዘመዶቻችን፣ የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም አብረውን የሚማሩ ልጆች ምሥራቹን በመስበካችን ወይም ላቅ ባሉት የይሖዋ መሥፈርቶች በመመራታችን ሊያፌዙብን ይችላሉ። (1 ጴጥ. 4:4) “አንተ ጥሩ ሰው ነህ። ሃይማኖትህ ግን በጣም ጥብቅና ጊዜ ያለፈበት ነው” ይሉን ይሆናል። ሌሎች ደግሞ የተወገዱ ሰዎችን በምንይዝበት መንገድ የተነሳ ይተቹን ይሆናል። “እንዲህ እያደረጋችሁ ፍቅር አለን ማለት ትችላላችሁ?” ይሉን ይሆናል። እንዲህ ያሉ ሐሳቦች በአእምሯችን ውስጥ ጥርጣሬ ሊዘሩብን ይችላሉ። ይሖዋ የሚጠብቅብን ነገር ከአቅማችን በላይ እንደሆነና ድርጅቱ በጣም ጥብቅ እንደሆነ ሊሰማን ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠማችሁ ከይሖዋና ከድርጅቱ ላለመራቅ ምን ይረዳችኋል?

ኢዮብ ጓደኛ ተብዬዎቹ የሰነዘሩበትን ፌዝና ውሸት ለማመን ፈቃደኛ አልሆነም። ከዚህ ይልቅ ለይሖዋ ያለውን ንጹሕ አቋም ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)

14. በይሖዋ መሥፈርቶች በመመራታችን ሌሎች ፌዝ ሲሰነዝሩብን ምን ልናደርግ ይገባል? (መዝሙር 119:50-52)

14 በይሖዋ መሥፈርቶች ለመመራት ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። ኢዮብ ፌዝ ቢሰነዘርበትም በይሖዋ መሥፈርቶች የሚመራ ሰው ነበር። እንዲያውም ከኢዮብ ጓደኛ ተብዬዎች አንዱ፣ ኢዮብ በአምላክ መሥፈርቶች መመራቱ በአምላክ ዘንድ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ሊያሳምነው ሞክሮ ነበር። (ኢዮብ 4:17, 18፤ 22:3) ኢዮብ ግን እንዲህ ያለውን ውሸት ለማመን ፈቃደኛ አልሆነም። ይሖዋ ትክክልና ስህተት ስለሆኑ ነገሮች ያወጣቸው መሥፈርቶች እንከን የለሽ እንደሆኑ ያውቅ ነበር። በእነዚህ መሥፈርቶች ለመመራትም ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። በሌሎች ተጽዕኖ ንጹሕ አቋሙን አላጎደፈም። (ኢዮብ 27:5, 6) ታዲያ ከዚህ ምን እንማራለን? ፌዝ በይሖዋ መሥፈርቶች ላይ ጥርጣሬ እንዲዘራባችሁ አትፍቀዱ። በራሳችሁ ሕይወት ያጋጠሟችሁን ነገሮች መለስ ብላችሁ አስቡ። የይሖዋ መሥፈርቶች ትክክልና ጠቃሚ እንደሆኑ በተደጋጋሚ አልተመለከታችሁም? በእነዚህ መሥፈርቶች የሚመራውን ድርጅት ለመደገፍ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። እንዲህ ካደረጋችሁ ከየትኛውም ምንጭ የሚሰነዘርባችሁ ፌዝ ከይሖዋ ፈጽሞ ሊለያችሁ አይችልም።—መዝሙር 119:50-52ን አንብብ።

15. ብሪጅት የተፌዘባት ለምንድን ነው?

15 በሕንድ የምትኖር ብሪጅት የተባለች እህት ያጋጠማትን ነገር እስቲ እንመልከት። በእምነቷ የተነሳ ቤተሰቦቿ ያፌዙባት ነበር። በ1997 ከተጠመቀች ብዙም ሳይቆይ፣ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ባለቤቷ ከሥራ ተባረረ። በመሆኑም እሱ፣ ብሪጅትና ልጆቻቸው ወደ ሌላ ከተማ ተዛውረው የእሱ ወላጆች ጋር ለመኖር ተገደዱ። የብሪጅት መከራ በዚህ አላበቃም። ባለቤቷ ሥራ ስለሌለው ቤተሰቧን ለማስተዳደር የሙሉ ቀን ሥራ መሥራት ይጠበቅባት ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ ጉባኤ ያለው እሷ ካለችበት ቦታ 350 ኪሎ ሜትር ርቆ ነው። የሚያሳዝነው የባለቤቷ ቤተሰቦች በእምነቷ ምክንያት ይቃወሟት ነበር። ተቃውሞው ከአቅሟ በላይ ስለሆነባት እሷና ቤተሰቧ በድጋሚ ወደ ሌላ አካባቢ ተዛወሩ። ከዚያም ባለቤቷ በድንገት ሞተባት። በኋላ ላይ ደግሞ የ12 ዓመት ልጇ በካንሰር ሞተች። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ የብሪጅት ዘመዶች ‘ይህ ሁሉ መከራ የደረሰብሽ በራስሽ ጥፋት ነው’ ይሏት ጀመር። የይሖዋ ምሥክር ባትሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ችግር እንደማይደርስባት ተናገሩ። ያም ቢሆን ብሪጅት በይሖዋ መታመኗንና ከድርጅቱ ጋር መተባበሯን ቀጥላለች።

16. ብሪጅት ይሖዋንና ድርጅቱን የሙጥኝ በማለቷ የተባረከችው እንዴት ነው?

16 ብሪጅት የምትኖረው ከጉባኤው በጣም ርቃ ስለነበረ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች በአካባቢዋ እንድትሰብክና በቤቷ የጉባኤ ስብሰባዎችን እንድታደርግ አበረታታት። መጀመሪያ ላይ እንዲህ ማድረግ በጣም ከባድ እንደሚሆንባት ተሰምቷት ነበር። ሆኖም የተሰጣትን መመሪያ ተከተለች። ምሥራቹን ለሌሎች ለመስበክ፣ በቤቷ ስብሰባዎችን ለማካሄድ እንዲሁም ከልጆቿ ጋር የቤተሰብ አምልኮ ለማድረግ ጥረት አደረገች። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ብሪጅት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር ቻለች። ከጥናቶቿ ብዙዎቹም እድገት አድርገው ተጠመቁ። በ2005 የዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። በይሖዋ ላይ ያላት እምነትና ለድርጅቱ ያላት ታማኝነት ወሮታ አስገኝቶላታል። ልጆቿ ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ነው። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ በዚያ አካባቢ ሁለት ጉባኤዎች አሉ። ብሪጅት ያጋጠሟትን ችግሮችና ከቤተሰቧ የሚሰነዘርባትን ፌዝ ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል የሰጣት ይሖዋ እንደሆነ እርግጠኛ ነች።

ለይሖዋና ለድርጅቱ ምንጊዜም ታማኝ ሁኑ

17. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?

17 ሰይጣን፣ ችግሮች ሲደርሱብን ይሖዋ እንደሚተወን እንዲሁም የይሖዋን ድርጅት መደገፍ ሕይወታችንን ይበልጥ ከባድ እንደሚያደርግብን እንዲሰማን ይፈልጋል። በተጨማሪም ሰይጣን፣ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ስማቸው ሲጠፋ፣ ስደት ሲደርስባቸው ወይም ሲታሰሩ እንድንሸበር ይፈልጋል። ከዚህም ሌላ፣ የሚሰነዘርብን ፌዝ በይሖዋ መሥፈርቶችና በድርጅቱ ላይ ያለንን እምነት እንዲሸረሽረው ይፈልጋል። እኛ ግን ሰይጣን የሚሸርበውን ሴራ ስለምናውቅ በፍጹም አንታለልም። (2 ቆሮ. 2:11) የሰይጣንን ውሸቶች ለመቃወምና ምንጊዜም ለይሖዋና ለድርጅቱ ታማኝ ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። ይሖዋ መቼም ቢሆን እንደማይተዋችሁ አትዘንጉ። (መዝ. 28:7) እንግዲያው ማንኛውም ነገር ከይሖዋ እንዲለያችሁ አትፍቀዱ።—ሮም 8:35-39

18. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

18 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ከጉባኤው ውጭ የሚመጡ ፈተናዎችን ተመልክተናል። ሆኖም በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ያለን እምነት ጉባኤ ውስጥ በሚያጋጥሙ ችግሮችም ሊፈተን ይችላል። እንዲህ ያሉ ፈተናዎችን መወጣት የምንችለው እንዴት ነው? ይህ ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።

መዝሙር 118 “እምነት ጨምርልን”

a በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በታማኝነት ለመጽናት ከፈለግን በይሖዋና በድርጅቱ መታመናችንን መቀጠል ይኖርብናል። ዲያብሎስ ይህን እምነታችንን ለማዳከም የተለያዩ ፈተናዎችን ይጠቀማል። ይህ ርዕስ፣ ዲያብሎስ የሚጠቀምባቸው ሦስት ፈተናዎች የትኞቹ እንደሆኑ እንዲሁም የእሱን ሴራ ለማክሸፍ ምን ማድረግ እንደምንችል ያብራራል።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።