በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 48

ታማኝነታችሁ ሲፈተን የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ

ታማኝነታችሁ ሲፈተን የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ

“በሁሉም ነገር የማስተዋል ስሜትህን ጠብቅ።”—2 ጢሞ. 4:5

መዝሙር 123 ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት በታማኝነት መገዛት

ማስተዋወቂያ a

1. የማስተዋል ስሜታችንን መጠበቅ ሲባል ምን ማለት ነው? (2 ጢሞቴዎስ 4:5)

 ችግሮች ሲያጋጥሙን ለይሖዋና ለድርጅቱ ያለን ታማኝነት ሊፈተን ይችላል። እንዲህ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መወጣት የምንችለው እንዴት ነው? የማስተዋል ስሜታችንን መጠበቅ፣ ነቅተን መኖርና በእምነት ጸንተን መቆም ይኖርብናል። (2 ጢሞቴዎስ 4:5ን አንብብ።) በመረጋጋት፣ ቆም ብለን በማሰብ እንዲሁም ነገሮችን በይሖዋ ዓይን ለማየት በመሞከር የማስተዋል ስሜታችንን መጠበቅ እንችላለን። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ስሜታችን አስተሳሰባችንን አይቆጣጠረውም።

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

2 ባለፈው ርዕስ ላይ ከጉባኤው ውጭ የሚመጡ ሦስት ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ተመልክተናል። በዚህ ርዕስ ላይ ደግሞ ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት የሚፈትኑ በጉባኤ ውስጥ ሊያጋጥሙን የሚችሉ ሦስት ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንመለከታለን። (1) የእምነት ባልንጀራችን እንደበደለን ሲሰማን፣ (2) ተግሣጽ ሲሰጠን እንዲሁም (3) ድርጅታዊ ማስተካከያዎችን መቀበል ሲከብደን። እንዲህ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የማስተዋል ስሜታችንን መጠበቅ እንዲሁም ከይሖዋና ከድርጅቱ ጋር በታማኝነት መጣበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

የእምነት ባልንጀራችን እንደበደለን ሲሰማን

3. የእምነት ባልንጀራችን እንደበደለን ሲሰማን ምን ምላሽ ልንሰጥ እንችላለን?

3 አንድ የእምነት ባልንጀራህ እንደበደለህ ተሰምቶህ ያውቃል? ምናልባትም ግለሰቡ ኃላፊነት ያለው ወንድም ሊሆን ይችላል። መቼም ግለሰቡ የበደለህ ሊጎዳህ አስቦ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። (ሮም 3:23፤ ያዕ. 3:2) ያም ቢሆን ያደረገው ነገር በጣም አስከፍቶህ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም በጉዳዩ ላይ ስትብሰለሰል እንቅልፍ አጥተህ ይሆናል። እንዲያውም ‘አንድ ወንድም እንዲህ ካደረገኝ ይሄ ምኑን የይሖዋ ድርጅት ሆነ?’ የሚል ሐሳብ ወደ አእምሮህ መጥቶ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ብለን እንድናስብ የሚፈልገው ሰይጣን ነው። (2 ቆሮ. 2:11) እንዲህ ያለው አሉታዊ አስተሳሰብ ከይሖዋና ከድርጅቱ እንድንርቅ ሊያደርገን ይችላል። ታዲያ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት እንደበደሉን በሚሰማን ጊዜ የማስተዋል ስሜታችንን መጠበቅና ከአሉታዊ አስተሳሰብ መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

4. ዮሴፍ በደል ሲፈጸምበት የማስተዋል ስሜቱን የጠበቀው እንዴት ነው? ከእሱ ምሳሌስ ምን እንማራለን? (ዘፍጥረት 50:19-21)

4 አትመረር። ዮሴፍ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ ወንድሞቹ በደል አድርሰውበት ነበር። ይጠሉት ነበር፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ሊገድሉት ፈልገው ነበር። (ዘፍ. 37:4, 18-22) በስተ መጨረሻም ለባርነት ሸጡት። በዚህም የተነሳ ዮሴፍ ለ13 ዓመት ያህል ከባድ መከራ ደርሶበታል። ዮሴፍ ይሖዋ በእርግጥ የሚወደው መሆኑን ሊጠራጠር ይችል ነበር። በተጨማሪም እርዳታ በጣም በሚያስፈልገው ጊዜ ይሖዋ እንደተወው ሊሰማው ይችል ነበር። ሆኖም ዮሴፍ አልተመረረም። ከዚህ ይልቅ በመረጋጋት የማስተዋል ስሜቱን ጠብቋል። ወንድሞቹን ለመበቀል አጋጣሚ ባገኘ ጊዜ እንዲህ ከማድረግ ተቆጥቧል፤ ከዚህ ይልቅ ፍቅር አሳይቷቸዋል፤ እንዲሁም ይቅር ብሏቸዋል። (ዘፍ. 45:4, 5) ዮሴፍ እንዲህ ያደረገው ቆም ብሎ ማሰብ ስለቻለ ነው። በራሱ ችግሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ እይታውን በማስፋት በይሖዋ ዓላማ ላይ ትኩረት አድርጓል። (ዘፍጥረት 50:19-21ን አንብብ።) ታዲያ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? በደል ሲፈጸምብህ በይሖዋ አትመረር፤ ወይም ‘እሱ ትቶኛል’ ብለህ አታስብ። ከዚህ ይልቅ ፈተናውን እንድትወጣ እየረዳህ ያለው እንዴት እንደሆነ አሰላስል። በተጨማሪም ሌሎች ሲበድሉህ ድክመታቸውን በፍቅር ለመሸፈን ሞክር።—1 ጴጥ. 4:8

5. ሚክያስ በደል እንደተፈጸመበት በተሰማው ጊዜ የማስተዋል ስሜቱን የጠበቀው እንዴት ነው?

5 በደቡብ አሜሪካ የሚኖር ሚክያስ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ ያጋጠመውን እንመልከት። b በአንድ ወቅት ኃላፊነት ያላቸው አንዳንድ ወንድሞች አግባብ ያልሆነ ድርጊት እንደፈጸሙበት ተሰምቶት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ያለ አስጨናቂ ሁኔታ አጋጥሞኝ አያውቅም። በፍርሃት ተዋጥኩ፤ እንቅልፍ አልወስድ አለኝ፤ አቅመ ቢስ እንደሆንኩ ስለተሰማኝ አለቅስ ነበር።” ያም ቢሆን ሚክያስ የማስተዋል ስሜቱን ጠብቋል፤ ስሜቱንም ለመቆጣጠር ጥረት አድርጓል። ወደ ይሖዋ አዘውትሮ በመጸለይ ቅዱስ መንፈሱንና ለመጽናት የሚያስችለውን ኃይል እንዲሰጠው ይለምን ነበር። ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችን ከጽሑፎቻችን ላይ ለማግኘትም ጥረት አድርጓል። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት እንደበደሉህ ከተሰማህ ለመረጋጋትና በውስጥህ ያለውን ማንኛውንም አሉታዊ ስሜት ለመቆጣጠር ጥረት አድርግ። ግለሰቡ እንደዚያ እንዲናገር ወይም እንዲያደርግ ምክንያት የሆነው ምን እንደሆነ ላታውቅ ትችላለህ። በመሆኑም ወደ ይሖዋ በመጸለይ ራስህን በግለሰቡ ቦታ ለማስቀመጥ እንዲረዳህ ጠይቀው። እንዲህ ማድረግህ የእምነት ባልንጀራህ የበደለህ ሆን ብሎ ሊጎዳህ ፈልጎ እንዳልሆነ እንድታስብና በደሉን እንድትተወው ይረዳሃል። (ምሳሌ 19:11) ይሖዋ ያለህበትን ሁኔታ እንደሚረዳና ለመጽናት የሚያስፈልግህን ኃይል እንደሚሰጥህ አስታውስ።—2 ዜና 16:9፤ መክ. 5:8

ተግሣጽ ሲሰጠን

6. የይሖዋን ተግሣጽ የፍቅሩ መገለጫ አድርገን ማየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ዕብራውያን 12:5, 6, 11)

6 ተግሣጽ ስሜታችንን ሊጎዳው ይችላል። ሆኖም በሚሰማን ስሜት ላይ ብቻ ካተኮርን ተግሣጹ ለእኛ እንደማይሠራና ከመጠን ያለፈ እንደሆነ ልናስብ እንችላለን። ይህ ደግሞ አንድ ውድ ነገር ያሳጣናል፤ ተግሣጹ የይሖዋ ፍቅር መገለጫ እንደሆነ ማየት ይሳነናል። (ዕብራውያን 12:5, 6, 11ን አንብብ።) ስሜታችን እንዲቆጣጠረን ከፈቀድን ደግሞ ሰይጣን ጥቃት እንዲሰነዝርብን አጋጣሚ እንሰጠዋለን። ሰይጣን የሚፈልገው ተግሣጹን ችላ እንድንል ይባስ ብሎም ራሳችንን ከይሖዋና ከጉባኤው እንድናርቅ ነው። አንተስ ተግሣጽ ተሰጥቶህ ከሆነ የማስተዋል ስሜትህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

ጴጥሮስ የተሰጠውን ምክርና ተግሣጽ በትሕትና ተቀብሏል፤ ይህም ለይሖዋ ይበልጥ ጠቃሚ እንዲሆን አድርጎታል (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)

7. (ሀ) ሥዕሉ ላይ እንደሚታየው ጴጥሮስ የተሰጠውን ተግሣጽ ከተቀበለ በኋላ ይሖዋ የተጠቀመበት እንዴት ነው? (ለ) ከጴጥሮስ ምሳሌ ምን እንማራለን?

7 ተግሣጽን ተቀበል፤ አስፈላጊውን ማስተካከያም አድርግ። ኢየሱስ ለጴጥሮስ በሌሎቹ ሐዋርያት ፊት በተደጋጋሚ እርማት ሰጥቶታል። (ማር. 8:33፤ ሉቃስ 22:31-34) በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ተሸማቅቆ መሆን አለበት! ያም ቢሆን ጴጥሮስ ለኢየሱስ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። ተግሣጹን በመቀበል ከስህተቱ ተምሯል። በዚህም የተነሳ ይሖዋ ጴጥሮስን ለታማኝነቱ ክሶታል፤ እንዲሁም በጉባኤው ውስጥ ትላልቅ ኃላፊነቶች ሰጥቶታል። (ዮሐ. 21:15-17፤ ሥራ 10:24-33፤ 1 ጴጥ. 1:1) ከጴጥሮስ ምሳሌ ምን እንማራለን? ተግሣጽ ከሚያሳድርብን የኀፍረት ስሜት አሻግረን ስናይ፣ እርማቱን ስንቀበል እንዲሁም አስፈላጊውን ማስተካከያ ስናደርግ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን እንጠቅማለን። እንዲህ ስናደርግ ለይሖዋና ለወንድሞቻችን ይበልጥ ጠቃሚ እንሆናለን።

8-9. በርናርዶ ተግሣጽ ሲሰጠው መጀመሪያ ላይ ምን ተሰምቶት ነበር? አስተሳሰቡን ለማስተካከል የረዳውስ ምንድን ነው?

8 በሞዛምቢክ የሚኖር በርናርዶ የተባለ ወንድም ያጋጠመውን እስቲ እንመልከት። በርናርዶ ከሽምግልና ወረደ። በርናርዶ መጀመሪያ ላይ ምን ተሰምቶት ነበር? “የተሰጠኝ ተግሣጽ ስላላስደሰተኝ ቅር ብሎኝ ነበር” ብሏል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ለእሱ የሚኖራቸው አመለካከት አሳስቦት ነበር። “ለጉዳዩ ተገቢውን አመለካከት ለመያዝና በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ያለኝን እምነት መልሼ ለመገንባት የተወሰኑ ወራት ወስዶብኛል” በማለት ተናግሯል። ታዲያ በርናርዶ ትክክለኛውን አመለካከት ለመያዝ የረዳው ምንድን ነው?

9 በርናርዶ አስተሳሰቡን አስተካከለ። እንዲህ ብሏል፦ “ሽማግሌ በነበርኩበት ጊዜ ሌሎች ለይሖዋ ተግሣጽ ተገቢው አመለካከት እንዲኖራቸው ለመርዳት ዕብራውያን 12:7⁠ን እጠቀም ነበር። አሁን ግን ‘ይሄን ጥቅስ ተግባራዊ ማድረግ ያለበት ማን ነው?’ ብዬ ራሴን ጠየቅኩ። እኔን ጨምሮ ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ናቸው።” ከዚያም በርናርዶ በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ያለውን እምነት መልሶ ለመገንባት ተጨማሪ እርምጃዎችን ወሰደ። መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብና በጥልቀት የማሰላሰል ልማዱን አጠናከረ። ወንድሞችና እህቶች ለእሱ ያላቸው አመለካከት ቢያሳስበውም አብሯቸው በአገልግሎትና በጉባኤ ስብሰባዎች ይካፈል ነበር። ውሎ አድሮ በርናርዶ በድጋሚ ሽማግሌ ሆኖ ተሾመ። አንተም እንደ በርናርዶ ተግሣጽ ተሰጥቶህ ከሆነ ከሚሰማህ የኀፍረት ስሜት አሻግረህ ለመመልከት ሞክር፤ ምክሩን ተቀበል፤ እንዲሁም አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርግ። c (ምሳሌ 8:33፤ 22:4) እንዲህ ካደረግክ ይሖዋ ከእሱና ከድርጅቱ ጋር በታማኝነት በመጣበቅህ አትረፍርፎ እንደሚባርክህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።

ድርጅታዊ ማስተካከያዎችን መቀበል ሲከብደን

10. የአንዳንድ እስራኤላውያንን ታማኝነት የፈተነው የትኛው ድርጅታዊ ማስተካከያ ሊሆን ይችላል?

10 ድርጅታዊ ማስተካከያዎች ታማኝነታችንን ሊፈትኑት ይችላሉ። እንዲያውም ካልተጠነቀቅን ከይሖዋ እንዲለዩን ልንፈቅድላቸው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ የሙሴ ሕግ ሲመጣ የተደረገ አንድ ድርጅታዊ ማስተካከያ አንዳንድ እስራኤላውያንን የነካቸው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ሕጉ ከመሰጠቱ በፊት የክህነት ሥራዎችን የሚያከናውኑት የቤተሰብ ራሶች ነበሩ። መሠዊያ በመሥራት ቤተሰቦቻቸውን ወክለው ለይሖዋ መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። (ዘፍ. 8:20, 21፤ 12:7፤ 26:25፤ 35:1, 6, 7፤ ኢዮብ 1:5) ሕጉ ሲቋቋም ግን የቤተሰብ ራሶች ይህን መብት አጡ። ይሖዋ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ የአሮን ዘር የሆኑ ካህናትን ሾመ። ይህ ድርጅታዊ ማስተካከያ ከተደረገ በኋላ የአሮን ዘር ያልሆነ አንድ የቤተሰብ ራስ የካህናትን ሥራ ካከናወነ ሊገደል ይችላል። d (ዘሌ. 17:3-6, 8, 9) ቆሬ፣ ዳታን፣ አቤሮንና 250ዎቹ አለቆች በሙሴና በአሮን ሥልጣን ላይ እንዲያምፁ ያደረጋቸው አንዱ ምክንያት ይህ ማስተካከያ ይሆን? (ዘኁ. 16:1-3) ይህን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ቆሬና ግብረ አበሮቹ ለይሖዋ ታማኝ ሳይሆኑ ቀርተዋል። አንተስ አንድ ድርጅታዊ ማስተካከያ ታማኝነትህን ከፈተነው ምን ማድረግ ትችላለህ?

ቀአታውያን የአገልግሎት ምድብ ለውጥ ሲያጋጥማቸው ዘማሪ፣ በር ጠባቂና የግምጃ ቤት ኃላፊ ሆነው ለማገልገል ፈቃደኞች ነበሩ (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

11. ከቀአታውያን ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

11 ድርጅታዊ ማስተካከያዎችን ሙሉ በሙሉ ደግፍ። እስራኤላውያን በምድረ በዳ በሚጓዙበት ወቅት ቀአታውያን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ኃላፊነት ነበራቸው። እስራኤላውያን ጉዞ በጀመሩ ቁጥር አንዳንድ ቀአታውያን በሕዝቡ ሁሉ ፊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ይሸከማሉ። (ዘኁ. 3:29, 31፤ 10:33፤ ኢያሱ 3:2-4) ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ሆኖም እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ ሁኔታው ተቀየረ። አሁን ታቦቱ ከቦታ ቦታ መጓጓዝ አያስፈልገውም። በመሆኑም በሰለሞን የንግሥና ዘመን አንዳንድ ቀአታውያን ዘማሪዎች፣ አንዳንዶቹ የበር ጠባቂዎች ሌሎቹ ደግሞ የግምጃ ቤት ኃላፊ ሆነው እንዲያገለግሉ ተመድበው ነበር። (1 ዜና 6:31-33፤ 26:1, 24) ቀአታውያን ቅሬታ እንዳሰሙ ወይም ደግሞ ቀደም ሲል ከነበራቸው ልዩ መብት አንጻር ትልቅ ቦታ ያለው ሥራ እንዲሰጣቸው እንደጠየቁ የሚገልጽ አንድም ዘገባ አናገኝም። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? የአንተን የአገልግሎት ምድብ በቀጥታ የሚነካ ቢሆንም እንኳ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የሚደረጉትን ማስተካከያዎች በሙሉ በታማኝነት ደግፍ። ከሚሰጥህ ከየትኛውም የአገልግሎት ምድብ ደስታ ለማግኘት ሞክር። ዋጋማነትህ የሚለካው በአገልግሎት ምድብህ እንዳልሆነ አትዘንጋ። ይሖዋ ከየትኛውም የአገልግሎት ምድብ በላይ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ታዛዥነትህን ነው።—1 ሳሙ. 15:22

12. ዛይና ከቤቴል ወጥታ ሌላ የአገልግሎት ምድብ ሲሰጣት ምን ተሰማት?

12 በመካከለኛው ምሥራቅ የምትኖር ዛይና የተባለች እህት ያጋጠማትን እንመልከት፤ ዛይና የአገልግሎት ምድቧ በመለወጡ የምትወደውን የአገልግሎት መብት አጣች። በቤቴል ከ23 ዓመት በላይ ካገለገለች በኋላ መስኩ ላይ እንድታገለግል ተመደበች። እንዲህ ብላለች፦ “የአገልግሎት ምድቤ ሲቀየር በጣም ደነገጥኩ። ምንም እንደማልጠቅም ሆኖ ተሰማኝ። ‘ምን አጥፍቼ ነው?’ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር።” የሚያሳዝነው በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች “በሥራሽ ጎበዝ ብትሆኚ ኖሮ በቤቴል ትቀጥዪ ነበር” በማለት ስሜቷን ይበልጥ ጎዷት። ለተወሰነ ጊዜ ያህል ዛይና ተስፋ ከመቁረጧ የተነሳ በየዕለቱ ማታ ማታ ታለቅስ ነበር። ሆኖም ዛይና እንዲህ ብላለች፦ “በድርጅቱም ሆነ ይሖዋ ለእኔ ባለው ፍቅር ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርብኝ ፈጽሞ አልፈቀድኩም።” ዛይና የማስተዋል ስሜቷን መጠበቅ የቻለችው እንዴት ነው?

13. ዛይና ከደረሰባት የስሜት ጉዳት ለማገገም ምን አደረገች?

13 ዛይና ከደረሰባት የስሜት ጉዳት ማገገም ችላለች። እንዴት? እሷ ያጋጠማትን ሁኔታ የሚመለከቱ ጽሑፎችን አነበበች። በየካቲት 1, 2001 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው “የተስፋ መቁረጥን ስሜት መቋቋም ትችላለህ!” የሚለው ርዕስ በእጅጉ ረድቷታል። ርዕሱ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ማርቆስ የአገልግሎት ምድብ ለውጥ ሲያጋጥመው ከእሷ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ስሜት ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል ይገልጻል። ዛይና “የማርቆስ ተሞክሮ የተስፋ መቁረጥን ስሜት ለማሸነፍ የሚረዳ ፍቱን መድኃኒት ሆኖልኛል” ብላለች። በተጨማሪም ዛይና ከጓደኞቿ አልራቀችም። ራሷን አላገለለችም፤ እንዲሁም በሐዘን አልቆዘመችም። የይሖዋ መንፈስ በድርጅቱ ላይ እንደሚሠራ እንዲሁም ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች በጣም እንደሚያስቡላት ተገነዘበች። በሌላ በኩል ደግሞ የአምላክ ድርጅት የይሖዋን ሥራ ለማራመድ ከሁሉ የተሻለውን ውሳኔ ማድረግ እንዳለበት ተረዳች።

14. ቭላዶ የትኛውን ድርጅታዊ ማስተካከያ መቀበል ከብዶት ነበር? የረዳውስ ምንድን ነው?

14 ቭላዶ የተባለ በስሎቬንያ የሚኖር የ73 ዓመት የጉባኤ ሽማግሌ፣ የነበረበት ጉባኤ ከሌላ ጉባኤ ጋር በተዋሃደበትና የሚጠቀሙበት የስብሰባ አዳራሽ በተዘጋበት ጊዜ ለውጡን መቀበል ከብዶት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ያለ የሚያምር የስብሰባ አዳራሽ የተዘጋበት ምክንያት ሊገባኝ አልቻለም። አዳራሹን በቅርቡ አድሰነው ስለነበር ሁኔታው ይበልጥ ከባድ ሆነብኝ። አናጺ ስለሆንኩ ከአዳዲሶቹ ቁሳቁሶች የተወሰኑትን የሠራሁት እኔ ነበርኩ። ደግሞም የጉባኤዎቹ መዋሃድ በርካታ ማስተካከያዎችን እንድናደርግ አስገድዶናል፤ እነዚህ ማስተካከያዎች ደግሞ እንደ እኔ ላሉ አረጋውያን ቀላል አይደሉም።” ታዲያ ቭላዶ ይህን ውሳኔ እንዲደግፍ የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የሚደረጉ ማስተካከያዎችን ለመቀበል ጥረት ማድረግ ምንጊዜም በረከት ያስገኛል። እነዚህ ማስተካከያዎች ወደፊት ለሚያጋጥሙን ትላልቅ ለውጦች ያዘጋጁናል።” ከጉባኤዎች ውህደት ወይም ከአገልግሎት ምድብ ለውጥ ጋር በተያያዘ የተደረጉ ማስተካከያዎችን መቀበል ተፈታታኝ ሆኖብሃል? ከሆነ አይዞህ፣ ይሖዋ ስሜትህን ይረዳልሃል። እንዲህ ያሉ ማስተካከያዎችን ከደገፍክ እንዲሁም ከይሖዋና እሱ ከሚጠቀምበት ድርጅት ጋር በታማኝነት ከተጣበቅክ የተትረፈረፈ በረከት ታገኛለህ።—መዝ. 18:25

በሁሉም ነገር የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ

15. በጉባኤ ውስጥ ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን የማስተዋል ስሜታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

15 ወደዚህ ሥርዓት መጨረሻ እየተቃረብን በሄድን መጠን በጉባኤ ውስጥ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙን እንጠብቃለን። እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ሊፈትኑት ይችላሉ። በመሆኑም የማስተዋል ስሜታችንን መጠበቅ ይኖርብናል። አንድ የእምነት ባልንጀራህ እንደበደለህ ከተሰማህ፣ በሁኔታው አትመረር። ተግሣጽ ከተሰጠህ፣ ከሚሰማህ የኀፍረት ስሜት አሻግረህ ተመልከት፤ የተሰጠህን ምክር ተቀበል፤ እንዲሁም አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርግ። በተጨማሪም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የተደረጉ ማስተካከያዎች በግለሰብ ደረጃ ከነኩህ፣ ማስተካከያዎቹን በሙሉ ልብ ተቀብለህ መመሪያውን ታዘዝ።

16. በይሖዋና በድርጅቱ ላይ መተማመንህን መቀጠል የምትችለው እንዴት ነው?

16 ታማኝነትህ ሲፈተን በይሖዋና በድርጅቱ መተማመንህን መቀጠል ትችላለህ። ሆኖም ይህን ለማድረግ የማስተዋል ስሜትህን መጠበቅ በሌላ አባባል መረጋጋት፣ ቆም ብለህ ማሰብና ነገሮችን በይሖዋ ዓይን ማየት ይኖርብሃል። አንተ ያጋጠመህ ዓይነት ችግር አጋጥሟቸው ሁኔታውን በተሳካ መንገድ የተወጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮችን ምሳሌ አጥና፤ እንዲሁም አሰላስል። ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ። እንዲሁም ራስህን ፈጽሞ ከጉባኤው አታግልል። እንዲህ ካደረግክ፣ ምንም ይምጣ ምን ሰይጣን ከይሖዋም ሆነ ከድርጅቱ ሊለይህ አይችልም።—ያዕ. 4:7

መዝሙር 126 ነቅተህ ኑር፣ ጸንተህ ቁም፣ በርታ

a በተለይ በጉባኤ ውስጥ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ለይሖዋና ለድርጅቱ ያለን ታማኝነት ሊፈተን ይችላል። ከእነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች መካከል ሦስቱን በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን። በተጨማሪም ለይሖዋና ለድርጅቱ ምንጊዜም ታማኝ ለመሆን ምን ማድረግ እንደምንችል እናያለን።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

c ተጨማሪ ጠቃሚ ምክሮች ለማግኘት በነሐሴ 15, 2009 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 30 ላይ የወጣውን “ከዚህ ቀደም ታገለግል ነበር? አሁንስ ማገልገል ትችላለህ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

d የቤተሰብ ራሶች አንድን የቤት እንስሳ ለምግብነት ማረድ ከፈለጉ ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲወስዱት ሕጉ ያዝዝ ነበር። ከቤተ መቅደሱ በጣም ርቀው የሚኖሩ የቤተሰብ ራሶች ግን እንደዚያ ማድረግ አይጠበቅባቸውም።—ዘዳ. 12:21