በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

መርዶክዮስ በእውን የኖረ ሰው ነው?

መርዶክዮስ የተባለው አይሁዳዊ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በአስቴር መጽሐፍ ውስጥ ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶታል። መርዶክዮስ በፋርስ ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚሠራ አይሁዳዊ ግዞተኛ ነበር። ታሪኩ የተፈጸመው በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ‘በንጉሥ አሐሽዌሮስ ዘመን’ ነው። (ይህ ንጉሥ ቀዳማዊ ጠረክሲስ እንደሆነ ይታመናል።) መርዶክዮስ ንጉሡን ለመግደል የተሸረበውን ሴራ አከሸፈ። በመሆኑም ንጉሡ በአመስጋኝነት ተነሳስቶ መርዶክዮስ በሕዝብ ፊት ክብር እንዲሰጠው አደረገ። የመርዶክዮስና የሌሎቹ አይሁዳውያን ጠላት የነበረው ሃማ ከሞተ በኋላ ደግሞ ንጉሡ መርዶክዮስን ጠቅላይ ሚኒስቴር አድርጎ ሾመው። መርዶክዮስ ይህ ሥልጣን ስለተሰጠው በፋርስ ግዛት ውስጥ የነበሩትን አይሁዳውያን ከዘር ማጥፋት ዘመቻ ለማዳን የሚያስችል አዋጅ ማውጣት ችሏል።—አስ. 1:1፤ 2:5, 21-23፤ 8:1, 2፤ 9:16

በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የኖሩ አንዳንድ የታሪክ ምሁራን የአስቴር መጽሐፍ ልብ ወለድ እንደሆነና መርዶክዮስ የሚባል ሰው ኖሮ እንደማያውቅ ተናግረው ነበር። ሆኖም በ1941 የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ስለ መርዶክዮስ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የሚደግፍ ማስረጃ አገኙ። ለመሆኑ ይህ ማስረጃ ምንድን ነው?

ተመራማሪዎች ማርዱካ (በአማርኛ መርዶክዮስ) የተባለ ሰው ስም የተጻፈበት የፋርስ የኪዩኒፎርም ጽሑፍ አገኙ። ይህ ሰው በሹሻን የሚሠራ ባለሥልጣን ምናልባትም የሒሳብ ባለሙያ ነበር። የምሥራቃውያን ታሪክ ሊቅ የሆኑት አርተር ኡንግናድ በወቅቱ የነበረው “ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ መርዶክዮስን የሚጠቅሰው ማመሣከሪያ” ይህ ኪዩኒፎርም ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።

እኚህ ምሁር ሪፖርታቸውን ከጻፉ ወዲህ ምሁራን በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች የፋርስ ኪዩኒፎርሞችን ተርጉመዋል። ከእነዚህ መካከል የፐርሰፖሊስ ጽላቶች ይገኙበታል፤ እነዚህ ጽላቶች የተገኙት በፐርሰፖሊስ ቅጥሮች አቅራቢያ በሚገኘው ግምጃ ቤት ፍርስራሾች ውስጥ ነው። ጽላቶቹ የተቀረጹት በቀዳማዊ ጠረክሲስ የግዛት ዘመን እንደሆነ ተደርሶበታል። ጽላቶቹ የተጻፉት በኤላም ቋንቋ ሲሆን በአስቴር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ስሞችን ይዘዋል። a

መርዶክዮስ (ማርዱካ) የሚለው ስም በፋርስ የኪዩኒፎርም ጽሑፍ ውስጥ

በርካታ የፐርሰፖሊስ ጽላቶች በቀዳማዊ ጠረክሲስ የግዛት ዘመን በሹሻን የቤተ መንግሥት ጸሐፊ ሆኖ ይሠራ የነበረውን ማርዱካ የተባለውን ሰው ስም ይጠቅሳሉ። አንዱ ጽላት ማርዱካ ተርጓሚ እንደነበር ይናገራል። ይህ መረጃ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መርዶክዮስ ከሚሰጠው መግለጫ ጋር ይስማማል። መርዶክዮስ በንጉሥ አሐሽዌሮስ (ቀዳማዊ ጠረክሲስ) ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚሠራ ቢያንስ ሁለት ቋንቋዎችን የሚናገር ባለሥልጣን ነበር። መርዶክዮስ በሹሻን በሚገኘው ቤተ መንግሥት በንጉሡ በር አዘውትሮ ይቀመጥ ነበር። (አስ. 2:19, 21፤ 3:3) የንጉሡ በር የተባለው የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት የሚሠሩበት ትልቅ ሕንፃ ነው።

በጽላቶቹ ላይ በተጠቀሰው ማርዱካ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሰው መርዶክዮስ መካከል አስደናቂ ተመሳሳይነት አለ። የኖሩት በተመሳሳይ ዘመንና በተመሳሳይ ቦታ ሲሆን በተመሳሳይ የሥራ ቦታ ባለሥልጣን ሆነው አገልግለዋል። ይህ ሁሉ ተመሳሳይነት መኖሩ፣ ማርዱካ እና መርዶክዮስ አንድን ሰው ያመለክታል የሚል መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ሊያደርገን ይችላል።

a ፕሮፌሰር ኤድዊን ያማውቺ በ1992 ባሳተሙት ጽሑፍ ላይ፣ በፐርሰፖሊስ ጽላቶችም ሆነ በአስቴር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ አሥር ስሞችን ጠቅሰዋል።