የሕይወት ታሪክ
“ይሖዋን ማገልገል እፈልግ ነበር”
በሱሪናም ባለው ጥቅጥቅ ያለ ደን ውስጥ በሚገኘው የግራንቦሪ መንደር አቅራቢያ የሚኖሩትን ጥቂት ሰዎች ከጎበኘን በኋላ እጃችንን እያውለበለብን ተሰናበትናቸው። ከዚያም በአንዲት የእንጨት ጀልባ ተሳፍረን በታፓናሆኒ ወንዝ ላይ መጓዝ ጀመርን። በኋላም በፍጥነት በሚወርደው የወንዙ ክፍል በኩል ስናልፍ የጀልባው ሞተር ከድንጋይ ጋር ተጋጨ። ወዲያውኑ የጀልባው አፍንጫ ወንዙ ውስጥ ገባ፤ እኛም ውኃው ውስጥ ጠለቅን። ልቤ በፍጥነት ይመታ ጀመር። የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ሳገለግል ለበርካታ ዓመታት ወንዝ ላይ በጀልባ የተጓዝኩ ቢሆንም ዋና አልችልም ነበር!
ቀጥሎ የሆነውን ነገር ከመተረኬ በፊት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የጀመርኩት እንዴት እንደሆነ ልንገራችሁ።
ውብ የካሪቢያን ደሴት በሆነችው በኩራሳው በ1942 ተወለድኩ። አባቴ የሱሪናም ተወላጅ ቢሆንም ሥራ ፈልጎ ወደ ኩራሳው ተዛወረ። ከመወለዴ ከጥቂት ዓመታት በፊት አባቴ በኩራሳው ከተጠመቁት የመጀመሪያዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ሆነ። a እኔን እንዲሁም ወንድሜንና እህቶቼን በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናን ነበር፤ እርግጥ አንዳንድ ጊዜ እናስቸግረዋለን። አሥራ አራት ዓመት ሲሆነኝ አባቴ አረጋዊት እናቱን ለመንከባከብ ሲል ቤተሰባችንን ይዞ ወደ ሱሪናም ተዛወረ።
ጥሩ ጓደኞች ማፍራቴ ጠቅሞኛል
በሱሪናም ስንኖር ይሖዋን በቅንዓት ከሚያገለግሉ በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ ወጣቶች ጋር ጓደኝነት መሠረትኩ። እነዚህ ወጣቶች ትንሽ በዕድሜ ይበልጡኝ የነበረ ሲሆን የዘወትር አቅኚዎች ነበሩ። በአገልግሎት ስላገኟቸው ተሞክሮዎች ሲያወሩ ፊታቸው በደስታ ይፈካል። በተጨማሪም ከጉባኤ ስብሰባዎች በኋላ እኔና ጓደኞቼ ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች እናወራ ነበር። አንዳንዴም የምናወራው ደጅ ቁጭ ብለን በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ እያየን ነው። እነዚህ ጓደኞቼ ሕይወቴን እንዴት ልጠቀምበት እንደምፈልግ እንዳስተውል ረዱኝ፤ ይሖዋን ማገልገል እፈልግ ነበር። ስለዚህ በ16 ዓመቴ ተጠመቅኩ። በኋላም በ18 ዓመቴ የዘወትር አቅኚ ሆንኩ።
ጠቃሚ ትምህርቶች አገኘሁ
በአቅኚነት ሳገለግል በርካታ ትምህርቶችን አግኝቻለሁ። እነዚህ ትምህርቶች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ባሳለፍኩት ሕይወት በጣም ጠቅመውኛል። ለምሳሌ ካገኘኋቸው የመጀመሪያ ትምህርቶች አንዱ ሌሎችን ማሠልጠን ያለውን አስፈላጊነት ነው። አቅኚነት በጀመርኩበት ወቅት ቫይለም ቫን ሴይል የተባለ ሚስዮናዊ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አሠለጠነኝ። b ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችን መወጣት ስለምችልበት መንገድ ብዙ አስተምሮኛል። እንዲህ ያለው ሥልጠና ምን ያህል እንደሚያስፈልገኝ በወቅቱ አልተገነዘብኩም ነበር። በቀጣዩ ዓመት ልዩ አቅኚ ሆኜ ተሾምኩ። ከዚያም በሱሪናም ባለው ጥቅጥቅ ያለ ደን ውስጥ የሚገኙ ገለልተኛ ቡድኖችን መርዳት ጀመርኩ። ወንድሞች ልክ በሚያስፈልገኝ ጊዜ ሥልጠና ስለሰጡኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ከዚያ ወዲህ እኔም ጊዜ መድቤ ሌሎችን በማሠልጠን የእነሱን ምሳሌ ለመከተል ጥረት አድርጌያለሁ።
ያገኘሁት ሁለተኛ ትምህርት፣ ቀላል ሆኖም የተደራጀ ሕይወት መምራት ያለውን አስፈላጊነት ነው። በእያንዳንዱ ወር መጀመሪያ ላይ እኔና በልዩ አቅኚነት አብሮኝ የሚያገለግለው ወንድም ለቀጣዮቹ ሳምንታት ምን ያህል አስቤዛ እንደሚያስፈልገን እናስባለን። ከዚያም አንዳችን ረጅሙን ጉዞ ተጉዘን ወደ ዋናው ከተማ በመሄድ የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንገዛለን። ወርሃዊ ወጪ መሸፈኛችንን በቁጠባ መጠቀም እንዲሁም የገዛነው አስቤዛ ለወሩ እንዲያቆየን በጥንቃቄ ማቀድ ነበረብን። ጥቅጥቅ ያለው ደን ውስጥ ሆነን አስቤዛ ካለቀብን ማን ሊረዳን ይችላል? ቀላል ሆኖም የተደራጀ ሕይወት መምራት የምችለው እንዴት እንደሆነ በወጣትነቴ መማሬ ሕይወቴን በሙሉ በይሖዋ አገልግሎት ላይ ማተኮር እንድችል እንደረዳኝ ይሰማኛል።
ያገኘሁት ሦስተኛ ትምህርት፣ ሰዎችን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማስተማር ያለውን ጥቅም ነው። ከልጅነቴ አንስቶ ደች፣ እንግሊዝኛ፣ ፓፒያሜንቶ እንዲሁም በሱሪናም በስፋት የሚነገረውን ስራናንቶንጎን (ስራናን ተብሎም ይጠራል) መናገር እችላለሁ። ሆኖም በደኑ ውስጥ ያሉት ሰዎች ምሥራቹን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲሰሙ ጥሩ ምላሽ እንደሚሰጡ አስተዋልኩ። እርግጥ አንዳንዶቹን ቋንቋዎች መናገር ከብዶኝ ነበር። ለምሳሌ ሳራማካን በተባለው ቋንቋ ላይ የድምፁ ውፍረትና ቅጥነት መልእክቱን ይቀይረዋል። ይሁንና ጥረት በማድረጌ አልተቆጨሁም። እዚያ ባገለገልኩባቸው ዓመታት የሰዎቹን የአፍ መፍቻ ቋንቋ መናገር በመቻሌ እውነትን ለብዙ ሰዎች ማስተማር ችያለሁ።
እርግጥ አንዳንድ የሚያሸማቅቁ ሁኔታዎች አጋጥመውኛል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት፣ መጽሐፍ ቅዱስን የምታጠና አንዲት የሳራማካን ቋንቋ ተናጋሪ ሆዷን አሟት ስለነበር ‘ተሻለሽ ወይ’ ልላት ፈልጌ ነበር። ግን ለካ የጠየቅኳት “ነፍሰ ጡር ነሽ ወይ” ብዬ ነው። እንደሚጠበቀው በጥያቄዬ አልተደሰተችም። እንዲህ ያሉ ስህተቶችን ብሠራም በክልሌ ውስጥ ያሉትን ሰዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ ለመናገር ሁልጊዜ ከፍተኛ ጥረት አደርግ ነበር።
ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ተቀበልኩ
በ1970 የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። በዚያ ዓመት “የይሖዋ ምሥክሮችን ዋና መሥሪያ ቤት መጎብኘት” የሚለውን ስላይድ በደኑ ውስጥ ላሉት በርካታ ገለልተኛ ቡድኖች አሳይ ነበር። ወደ እነዚህ ቡድኖች ለመሄድ ከአንዳንድ ወንድሞች ጋር ሆነን በረጅም፣ ቀጭን የእንጨት ጀልባ ወንዞችን እናቋርጥ ነበር። ጀልባው ላይ ጀነሬተር፣ ነዳጅ የያዘ ጄሪካን፣ በነዳጅ የሚሠሩ መብራቶች እንዲሁም የስላይድ ማሳያ መሣሪያዎች እንይዝ ነበር። ወደምንጎበኘው ቦታ ስንደርስ የያዝናቸውን ነገሮች በሙሉ ተሸክመን ስላይዱን ወደምናሳይበት ቦታ እንሄዳለን። ከእነዚህ ጉዞዎች በጣም የማስታውሰው ነገር በእነዚያ ገለልተኛ አካባቢዎች ያሉ ሰዎች ፕሮግራሙን ምን ያህል ይወዱት እንደነበረ ነው። ሌሎች ስለ ይሖዋና ስለ ድርጅቱ ምድራዊ ክፍል እንዲማሩ መርዳት በጣም ያስደስተኝ ነበር። ይሖዋን
ሳገለግል የከፈልኩት ማንኛውም መሥዋዕት ካገኘሁት መንፈሳዊ በረከት ጋር የሚወዳደር አይደለም።በሦስት የተገመደ ገመድ
ነጠላ መሆኔ በዚያ የአገልግሎት ምድብ ማገልገል ቀላል እንዲሆንልኝ እንዳደረገ ብገነዘብም የሕይወት አጋር ማግኘት እፈልግ ነበር። ስለዚህ በዚህ አስቸጋሪ የአገልግሎት ምድብ በደስታ አብራኝ የምትካፈል ሚስት ለማግኘት መጸለይ ጀመርኩ። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ከኢቴል ጋር መጠናናት ጀመርን። ኢቴል የራሷን ጥቅም መሥዋዕት የምታደርግ ልዩ አቅኚ ነበረች። ኢቴል ከልጅነቷ አንስቶ ለሐዋርያው ጳውሎስ ከፍተኛ አድናቆት ነበራት፤ እንደ እሱ በክርስቲያናዊ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ መጠመድ ትፈልግ ነበር። መስከረም 1971 ተጋባን፤ ከዚያም አብረን ሆነን በወረዳ ሥራ መካፈል ጀመርን።
ኢቴል ያደገችው በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ስላልሆነ ጥቅጥቅ ባለው ደን ውስጥ የምናከናውነውን የወረዳ ሥራ ለመልመድ ብዙም አልተቸገረችም። ለምሳሌ ደኑ ውስጥ ርቀው የሚገኙ ጉባኤዎችን ለመጎብኘት ስንዘጋጅ ጓዝ አናበዛም ነበር። ልብሳችንን የምናጥበውም ሆነ ገላችንን የምንታጠበው በወንዞች ውስጥ ነው። በተጨማሪም ወንድሞች የሚያቀርቡልንን ነገር ሁሉ እንበላ ነበር፤ ወንድሞች ተሳቢ እንስሳትንና እንግዳ የሆኑ ዓሣዎችን ጨምሮ ደን ውስጥ ያደኑትንም ሆነ ወንዝ ውስጥ ያጠመዱትን ማንኛውንም ነገር ያቀርቡልን ነበር። ሳህን ከሌለ በኮባ እንበላለን። ሹካና ማንኪያ ከሌለ ደግሞ በእጃችን እንበላለን። እኔና ኢቴል በይሖዋ አገልግሎት አብረን መሥዋዕቶችን መክፈላችን በሦስት እንደተገመደ ገመድ ጥምረታችንን እንዳጠናከረልን ይሰማናል። (መክ. 4:12) እነዚህን ተሞክሮዎች በምንም አንለውጣቸውም!
በመግቢያው ላይ የጠቀስኩት ሁኔታ ያጋጠመን በደኑ ውስጥ ከሚገኝ አንድ ገለልተኛ ቦታ እየተመለስን ሳለ ነበር። በፍጥነት በሚወርደው የወንዙ ክፍል በኩል ስናልፍ ጀልባው ውኃ ውስጥ ገብቶ የነበረ ቢሆንም ቶሎ ወጣ። ደስ የሚለው፣ መንሳፈፊያ ጃኬት ለብሰን ነበር፤ ደግሞም ከጀልባው አልወደቅንም። ሆኖም ጀልባችን በውኃ ተሞላች።
በድስት የያዝነውን ምግብ ወደ ወንዙ ከደፋነው በኋላ ጀልባው ውስጥ የገባውን ውኃ በድስቱ እየቀዳን አፈሰስነው።ምግባችንን ስለደፋነው በወንዙ ላይ ጉዟችንን ስንቀጥል ዓሣ ለማጥመድ መሞከር ጀመርን። ግን ምንም ዓሣ መያዝ አልቻልንም። ስለዚህ ለዕለቱ የሚያስፈልገንን ምግብ እንዲሰጠን ይሖዋን ጠየቅነው። ልክ ጸልየን እንደጨረስን አንደኛው ወንድም ዓሣ ማጥመጃውን ወደ ወንዙ ጣለ። በዚህ ጊዜ አምስታችንንም ራት አብልቶ የሚያጠግብ ትልቅ ዓሣ ያዘ።
ባል፣ አባትና የወረዳ የበላይ ተመልካች
እኔና ኢቴል ለአምስት ዓመታት በወረዳ ሥራ ከተካፈልን በኋላ ያልተጠበቀ በረከት ይኸውም ወላጅ የመሆን መብት አገኘን። ይህን ዜና ስሰማ ብደሰትም ‘ከዚህ በኋላ ሕይወታችን ምን ይመስል ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ አሳስቦኝ ነበር። እኔና ኢቴል በተቻለ መጠን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ መቆየት እንፈልግ ነበር። በ1976 ልጃችን ኤትኒኤል ተወለደ። ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ ደግሞ ሁለተኛው ልጃችን ጆቫኒ ተወለደ።
በወቅቱ በሱሪናም ከነበረው ሁኔታ አንጻር ቅርንጫፍ ቢሮው ልጆቻችንን እያሳደግን በወረዳ ሥራ እንድቀጥል ዝግጅት አደረገ። ልጆቻችን ትናንሽ በነበሩበት ወቅት ጥቂት ጉባኤዎች ያሏቸውን ወረዳዎች እንድጎበኝ ተመደብኩ። በወቅቱ በወር የተወሰኑ ሳምንታት በወረዳ ሥራ እካፈላለሁ። የቀሩትን ሳምንታት ደግሞ በተመደብንበት ጉባኤ ውስጥ በአቅኚነት አገለግላለሁ። ከቤታችን አቅራቢያ ያሉ ጉባኤዎችን በምጎበኝበት ወቅት ኢቴልና ልጆቻችን አብረውኝ ይሄዱ ነበር። ጥቅጥቅ ባለው ደን ውስጥ ያሉ ጉባኤዎችን በምጎበኝበትና በዚያ የወረዳ ስብሰባዎችን በማደርግበት ወቅት ግን ብቻዬን እጓዛለሁ።
ሁሉንም ኃላፊነቶቼን በአግባቡ መወጣት እንድችል የተደራጀሁ ሰው መሆን ነበረብኝ። በየሳምንቱ የቤተሰብ ጥናት እናደርግ ነበር። በደኑ ውስጥ ያሉ ጉባኤዎችን ለመጎብኘት በምጓዝበት ወቅት ኢቴል ከልጆቻችን ጋር የቤተሰብ ጥናት ታደርጋለች። ሆኖም በተቻለ መጠን ሁላችንም አንድ ላይ ሆነን በተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንካፈል ነበር። በተጨማሪም እኔና ኢቴል አዘውትረን ከልጆቻችን ጋር እንዝናናለን፤ አብረን እንጫወታለን ወይም በቤታችን አቅራቢያ ሽርሽር እንሄዳለን። ብዙውን ጊዜ ለቲኦክራሲያዊ ሥራዎች ለመዘጋጀት እስከ ሌሊት አመሽ ነበር። ኢቴልም በምሳሌ 31:15 ላይ እንደተጠቀሰችው ባለሙያ ሚስት በማለዳ ተነስታ ቁርስ ታዘጋጃለች፤ ስለዚህ ልጆቻችን ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት አንድ ላይ ቁርስ በልተን የዕለቱን ጥቅስ እናነባለን። ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶቼን እንድወጣ የምትረዳኝ የራሷን ጥቅም መሥዋዕት የምታደርግ እንዲህ ያለች ሚስት በማግኘቴ ምንኛ አመስጋኝ ነኝ!
ወላጆች እንደመሆናችን መጠን ልጆቻችን ይሖዋንና አገልግሎትን እንዲወዱ ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት አድርገናል። ልጆቻችን እኛን ለማስደሰት ብለው ሳይሆን በገዛ ምርጫቸው ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲገቡ እንፈልግ ነበር። የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚያስገኘውን ደስታ ሁልጊዜ እንነግራቸው ነበር። እንዲህ ያለው ሕይወት የራሱ ተፈታታኝ ነገሮች እንዳሉት ባንክድም ይሖዋ በቤተሰብ ደረጃ የረዳንና የባረከን እንዴት እንደሆነ ጎላ አድርገን እንገልጽላቸዋለን። ከዚህም ሌላ ልጆቻችን በሕይወታቸው ውስጥ ይሖዋን ከሚያስቀድሙ የእምነት አጋሮቻቸው ጋር ጊዜ እንዲያሳልፉ እናደርግ ነበር።
ልጆቻችንን ስናሳድግ ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር በሙሉ አሟልቶልናል። እርግጥ እኔም የበኩሌን ድርሻ ለመወጣት አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርግ ነበር። ትዳር ከመመሥረቴ በፊት ጥቅጥቅ ባለው ደን ውስጥ በልዩ አቅኚነት ሳገለግል ያገኘሁት ተሞክሮ ከቁሳዊ ነገሮች ጋር በተያያዘ አስቀድሞ የማቀድን አስፈላጊነት አስተምሮኛል። አንዳንድ ጊዜ ግን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ብናደርግም እንኳ የሚያስፈልገንን ነገር በሙሉ ማግኘት ያስቸግረን ነበር። በእነዚያ ወቅቶች ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ እንደረዳን ይሰማኛል። ለምሳሌ በ1980ዎቹ መገባደጃና በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በሱሪናም ሕዝባዊ ዓመፅ ተነስቶ ነበር። በእነዚያ ዓመታት መሠረታዊ ነገሮችን ማግኘት እንኳ አስቸጋሪ ነበር። ያም ቢሆን ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር አሟልቶልናል።—ማቴ. 6:32
መለስ ብዬ ሳስብ
በመላው ሕይወታችን ይሖዋ ተንከባክቦናል፤ እንዲሁም ጥልቅ ደስታና እርካታ ሰጥቶናል። ልጆቻችንም ትልቅ በረከት ሆነውልናል። እነሱን የይሖዋ አገልጋዮች አድርገን ማሳደግ መቻላችንን እንደ ልዩ መብት አድርገን እንቆጥረዋለን። እነሱም የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን የሕይወት መንገዳቸው አድርገው በመምረጣቸው በጣም ደስተኞች ነን። ሁለቱም ልጆቻችን ከቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች ተመርቀዋል፤ በአሁኑ ወቅት ከሚስቶቻቸው ጋር በሱሪናም በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ያገለግላሉ።
እኔና ኢቴል አሁን አርጅተናል። ሆኖም አሁንም በልዩ አቅኚነት ይሖዋን በቅንዓት እያገለገልን ነው። እንዲያውም በሥራ ከመጠመዳችን የተነሳ እስካሁን ዋና ለመማር የሚያስችል ጊዜ አላገኘሁም። ሆኖም ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም። ያሳለፍኩትን ሕይወት መለስ ብዬ ሳስብ፣ በልጅነቴ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን የሕይወት መንገዴ አድርጌ መምረጤ ከሁሉ የተሻለ ውሳኔ እንደሆነ ይሰማኛል።
a የ2002 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 70ን (እንግሊዝኛ) ተመልከት።
b የቫይለም ቫን ሴይል የሕይወት ታሪክ በጥቅምት 1999 ንቁ! ላይ “ከጠበቅሁት በላይ የሆኑ ነገሮች” በሚል ርዕስ ወጥቷል።