በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 46

ይሖዋ በደስታ እንድንጸና የሚረዳን እንዴት ነው?

ይሖዋ በደስታ እንድንጸና የሚረዳን እንዴት ነው?

“ይሖዋ ሞገስ ሊያሳያችሁ በትዕግሥት ይጠባበቃል፤ ምሕረት ሊያሳያችሁም ይነሳል።”—ኢሳ. 30:18

መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን

ማስተዋወቂያ a

1-2. (ሀ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመልሳለን? (ለ) ይሖዋ እኛን ለመርዳት እንደሚጓጓ የሚያሳየው ምንድን ነው?

 ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንድንወጣና በቅዱስ አገልግሎታችን ደስታ እንድናገኝ ይረዳናል። ይሁንና የሚረዳን በየትኞቹ መንገዶች ነው? ይሖዋ ከሚሰጠን እርዳታ የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለውስ እንዴት ነው? በዚህ ርዕስ ውስጥ እነዚህን ጥያቄዎች እንመልሳለን። እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለሳችን በፊት ግን ተያያዥ የሆነ ሌላ ጥያቄ እናንሳ፦ ይሖዋ እኛን ለመርዳት በእርግጥ ፈቃደኛ ነው?

2 ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የተጠቀመበት ቃል መልሱን ለማግኘት ይረዳናል። ጳውሎስ “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” በማለት ጽፏል። (ዕብ. 13:6) የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሣከሪያ ጽሑፎች እንደሚገልጹት በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ‘ረዳት’ የሚለው ቃል እርዳታ ለማግኘት የሚጮኽን ግለሰብ ለመርዳት የሚሮጥን ሰው ያመለክታል። ይሖዋ አንድን የተጨነቀ ሰው ለመርዳት ሲቻኮል እስቲ ይታያችሁ። ይህ አገላለጽ ይሖዋ እኛን ለመርዳት ፈቃደኛ እንደሆነ አልፎ ተርፎም እንደሚጓጓ በግልጽ ያሳያል። ይሖዋ ከጎናችን ስለሆነ ፈተናዎች ቢያጋጥሙንም በደስታ መጽናት እንችላለን።

3. ይሖዋ ፈተና ሲያጋጥመን በደስታ እንድንጸና የሚረዳን በየትኞቹ ሦስት መንገዶች ነው?

3 ይሖዋ ፈተና ሲያጋጥመን በደስታ እንድንጸና የሚረዳን በየትኞቹ መንገዶች ነው? መልሱን ለማግኘት ወደ ኢሳይያስ መጽሐፍ እንሂድ። ምክንያቱም ኢሳይያስ በመንፈስ መሪነት የጻፋቸው ብዙዎቹ ትንቢቶች በዛሬው ጊዜ ላሉ የአምላክ አገልጋዮች ይሠራሉ። በተጨማሪም ኢሳይያስ ብዙ ጊዜ ቀላል አገላለጾችን በመጠቀም ስለ ይሖዋ ተናግሯል። ኢሳይያስ ምዕራፍ 30⁠ን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በዚህ ምዕራፍ ላይ ኢሳይያስ ግሩም ምሳሌዎችን በመጠቀም ይሖዋ ሕዝቡን የሚረዳው እንዴት እንደሆነ ተናግሯል፤ ይሖዋ (1) ጸሎታችንን በጥሞና በማዳመጥና በመመለስ፣ (2) መመሪያ በመስጠት እንዲሁም (3) አሁንም ሆነ ወደፊት እኛን በመባረክ ይረዳናል። ይሖዋ በእነዚህ ሦስት መንገዶች የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እስቲ በዝርዝር እንመልከት።

ይሖዋ ያዳምጠናል

4. (ሀ) ይሖዋ በኢሳይያስ ዘመን የነበሩትን አይሁዳውያን የገለጻቸው እንዴት ነው? በኋላስ ምን እንዲደርስባቸው ፈቀደ? (ለ) ይሖዋ ለታማኞቹ እስራኤላውያን ምን ተስፋ ሰጣቸው? (ኢሳይያስ 30:18, 19)

4 በኢሳይያስ ምዕራፍ 30 መክፈቻ ላይ ይሖዋ፣ አይሁዳውያን ‘በኃጢአት ላይ ኃጢአት የሚጨምሩ ግትር የሆኑ ልጆች’ እንደሆኑ ገልጿል። አክሎም “እነሱ ዓመፀኛ ሕዝብ፣ . . . የይሖዋን ሕግ ለመስማት እንቢተኛ የሆኑ ልጆች ናቸው” ብሏል። (ኢሳ. 30:1, 9) ሕዝቡ ለመስማት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ይሖዋ መከራ እንዲደርስባቸው እንደሚፈቅድ ኢሳይያስ ትንቢት ተናገረ። (ኢሳ. 30:5, 17፤ ኤር. 25:8-11) ደግሞም እንዳለው በባቢሎናውያን በግዞት ተወስደዋል። ይሁንና አንዳንድ ታማኝ አይሁዳውያን ነበሩ፤ ኢሳይያስም ለእነሱ የሚያውጀው የተስፋ መልእክት ነበረው። ኢሳይያስ፣ ይሖዋ አንድ ቀን መልሶ ሞገስ እንደሚያሳያቸው ነግሯቸዋል። (ኢሳይያስ 30:18, 19ን አንብብ።) የሆነውም ይኸው ነው። ይሖዋ የግዞት ዘመናቸው እንዲያበቃ አደረገ። ይሁንና መዳናቸው ወዲያውኑ አልመጣም። “ይሖዋ ሞገስ ሊያሳያችሁ በትዕግሥት ይጠባበቃል” የሚለው አገላለጽ፣ እነዚህ ታማኝ ሰዎች መዳን እስኪመጣላቸው ድረስ የተወሰነ ጊዜ እንደሚያልፍ የሚያሳይ ነው። እንዲያውም የተወሰኑ ቀሪዎች ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት፣ እስራኤላውያን ለ70 ዓመት በባቢሎን በግዞት ከቆዩ በኋላ ነው። (ኢሳ. 10:21፤ ኤር. 29:10) ሕዝቡ ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ፣ በግዞት ሳሉ ያነቡት የሐዘን እንባ በደስታ እንባ ተተካ።

5. ኢሳይያስ 30:19 ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?

5 ዛሬም “እርዳታ ለማግኘት በምትጮኹበት ጊዜ በእርግጥ ሞገስ ያሳያችኋል” ከሚለው ጥቅስ ማጽናኛ ማግኘት እንችላለን። (ኢሳ. 30:19) ኢሳይያስ፣ ይሖዋ ወደ እሱ ስንጮኽ በጥሞና እንደሚያዳምጠንና ለምናቀርበው ምልጃ በአፋጣኝ መልስ እንደሚሰጠን አረጋግጦልናል። አክሎም “ጩኸታችሁን እንደሰማም ይመልስላችኋል” ብሏል። እነዚህ የሚያበረታቱ ቃላት፣ አባታችን ወደ እሱ የሚጮኹትን ለመርዳት እንደሚፈልግ አልፎ ተርፎም እንደሚጓጓ ያስታውሱናል። ይህን ማወቃችን በደስታ ለመጽናት ይረዳናል።

6. ኢሳይያስ የተጠቀመባቸው ቃላት ይሖዋ የእያንዳንዱን አገልጋዩን ጸሎት እንደሚሰማ የሚጠቁሙት እንዴት ነው?

6 ይህ ጥቅስ ጸሎታችንን በተመለከተ ሌላስ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል? ይሖዋ ለእያንዳንዳችን ጸሎት ትኩረት ይሰጣል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በኢሳይያስ ምዕራፍ 30 የመጀመሪያ ክፍል ላይ ይሖዋ ሕዝቡን እያነጋገረ የነበረው በቡድን ደረጃ ስለሆነ ጥቅሱ ላይ ያለው ግስ የብዙ ቁጥር ነው። ይሁንና ቁጥር 19 ላይ በኩረ ጽሑፉ የነጠላ ቁጥር ግስ ይጠቀማል፤ ምክንያቱም መልእክቱ የተላለፈው ለግለሰቦች ነው። ጥቅሱ በበኩረ ጽሑፉ “ፈጽሞ አታለቅስም”፤ “በእርግጥ ሞገስ ያሳይሃል” እንዲሁም “ይመልስልሃል” ይላል። ይሖዋ አፍቃሪ አባት ስለሆነ ተስፋ የቆረጠ ልጁን “ለምን እንደ ወንድምህ ወይም እንደ እህትህ ጠንካራ አትሆንም?” አይለውም። ከዚህ ይልቅ በግለሰብ ደረጃ ያስብልናል፤ የእያንዳንዳችንን ጸሎትም በጥሞና ያዳምጣል።—መዝ. 116:1፤ ኢሳ. 57:15

ኢሳይያስ “[ለይሖዋ] ምንም እረፍት አትስጡት” ሲል ምን ማለቱ ነበር? (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)

7. ኢሳይያስና ኢየሱስ በተደጋጋሚ የመጸለይን አስፈላጊነት ያጎሉት እንዴት ነው?

7 የሚያሳስበንን ጉዳይ አስመልክቶ ወደ ይሖዋ ስንጸልይ እሱ የሚያደርግልን የመጀመሪያው ነገር ፈተናውን ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል መስጠት ሊሆን ይችላል። የደረሰብን መከራ በጠበቅነው ጊዜ ካላበቃ ደግሞ ይሖዋ ለመጽናት የሚያስችል ኃይል እንዲሰጠን በተደጋጋሚ መጸለይ ሊያስፈልገን ይችላል። ደግሞም እንዲህ እንድናደርግ ይሖዋ ጋብዞናል። ኢሳይያስ “[ለይሖዋ] ምንም እረፍት አትስጡት” ማለቱ ይህን ያሳያል። (ኢሳ. 62:7) ይህ ሐሳብ ምን ትርጉም አለው? ይሖዋን እረፍት እንደነሳነው እስኪቆጠር ድረስ በተደጋጋሚ ልንለምነው ይገባል ማለት ነው። ኢሳይያስ የተጠቀመበት አገላለጽ፣ ኢየሱስ በሉቃስ 11:8-10, 13 ላይ ጸሎትን አስመልክቶ የተናገራቸውን ምሳሌዎች ያስታውሰናል። እዚህ ላይ ኢየሱስ፣ ይሖዋን ‘እንድንወተውተው’ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠን ‘ደጋግመን እንድንለምነው’ አበረታቶናል። በተጨማሪም ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳ አመራር እንዲሰጠን ይሖዋን ልንለምነው እንችላለን።

ይሖዋ ይመራናል

8. በኢሳይያስ 30:20, 21 ላይ የሚገኘው ትንቢት በጥንት ዘመን የተፈጸመው እንዴት ነው?

8 ኢሳይያስ 30:20, 21ን አንብብ። የባቢሎን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ለአንድ ዓመት ተኩል ከብቦ በቆየበት ጊዜ ሕዝቡ ጭንቀት የምግብና የውኃ ያህል የዕለት ተዕለት ጉዳይ ሆኖባቸው ነበር። ሆኖም በቁጥር 20 እና 21 ላይ ይሖዋ፣ አይሁዳውያኑ ንስሐ ከገቡና አካሄዳቸውን ካስተካከሉ እንደሚያድናቸው ቃል ገብቶላቸዋል። ኢሳይያስ ‘ታላቅ አስተማሪ’ የሆነው ይሖዋ፣ ሕዝቡ እሱን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለክ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንደሚያስተምራቸው ነግሯቸዋል። አይሁዳውያን ከግዞት ነፃ ሲወጡ ይህ ትንቢት ተፈጽሟል። ይሖዋ ታላቅ አስተማሪ ሆኖላቸዋል፤ በእሱ አመራር ሥር ሕዝቡ ንጹሕ አምልኮን መልሰው ማቋቋም ችለዋል። በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ታላቅ አስተማሪ ስለሆነልን አመስጋኞች ነን።

9. በዛሬው ጊዜ የይሖዋን መመሪያ የምናገኝበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

9 ኢሳይያስ እኛ እንደ ተማሪዎች እንደሆንንና ይሖዋ በሁለት መንገዶች እንደሚያስተምረን ገልጿል። መጀመሪያ ላይ ኢሳይያስ “በገዛ ዓይኖችህም ታላቁን አስተማሪህን ታያለህ” ብሏል። በዚህ አገላለጽ መሠረት አስተማሪው ከተማሪዎቹ ፊት ቆሟል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የሚያስተምረን በመሆኑ በእጅጉ ተባርከናል። ለመሆኑ ይሖዋ የሚያስተምረን እንዴት ነው? በድርጅቱ አማካኝነት ነው። ከይሖዋ ድርጅት ለምናገኘው ግልጽ መመሪያ ምንኛ አመስጋኞች ነን! በጉባኤና በክልል ስብሰባዎች እንዲሁም በጽሑፎቻችን፣ በብሮድካስቶችና በሌሎች መንገዶች የምናገኘው ትምህርት አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን በደስታ ለመጽናት ይረዳናል።

10. ‘ከኋላችን ድምፅ’ የምንሰማው እንዴት ነው?

10 ኢሳይያስ፣ ይሖዋ እኛን ለማስተማር የሚጠቀምበትን ሁለተኛ መንገድ ሲገልጽ “ጆሮህ ከኋላህ . . . ድምፅ ይሰማል” ብሏል። ኢሳይያስ እዚህ ላይ ይሖዋን ከተማሪዎቹ ኋላ ኋላ እየሄደ አቅጣጫ እንደሚጠቁም ንቁ አስተማሪ አድርጎ ገልጾታል። በዛሬው ጊዜ የአምላክን ድምፅ ከኋላችን እንሰማለን። እንዴት? አምላክ በመንፈስ መሪነት መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው ከረጅም ጊዜ በፊት ነው፤ ከኋላችን ሊባል ይችላል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ የአምላክን ድምፅ ከኋላችን የምንሰማ ያህል ነው።—ኢሳ. 51:4

11. በደስታ ለመጽናት የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ይኖርብናል? ለምንስ?

11 ይሖዋ በድርጅቱና በቃሉ አማካኝነት ከሚሰጠው አመራር የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ኢሳይያስ ሁለት ነገሮችን እንደጠቀሰ ልብ በሉ። አንደኛ፣ “መንገዱ ይህ ነው።” ሁለተኛ፣ “በእሱ ሂድ።” (ኢሳ. 30:21) ስለዚህ ‘መንገዱን’ ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም። ‘በእሱ ልንሄድም’ ይገባል። በይሖዋ ቃልና ድርጅቱ በሚሰጠው ማብራሪያ አማካኝነት ይሖዋ ምን እንደሚጠብቅብን እንማራለን። የተማርነውን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችልም እንማራለን። ለይሖዋ በምናቀርበው አገልግሎት በደስታ ለመጽናት ከፈለግን ሁለቱንም እርምጃዎች መውሰድ ይጠበቅብናል። ይሖዋ እንደሚባርከን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ይህን ካደረግን ብቻ ነው።

ይሖዋ ይባርከናል

12. በኢሳይያስ 30:23-26 መሠረት ይሖዋ ሕዝቡን የሚባርካቸው እንዴት ነው?

12 ኢሳይያስ 30:23-26ን አንብብ። ይህ ትንቢት፣ ከባቢሎን ግዞት በኋላ ወደ እስራኤል ምድር ከተመለሱት አይሁዳውያን ጋር በተያያዘ የተፈጸመው እንዴት ነው? አይሁዳውያኑ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ የተትረፈረፈ በረከት አግኝተዋል። ይሖዋ ለሕዝቡ በቂ ሥጋዊ ምግብ በመስጠት ባርኳቸዋል። በዋነኝነት ደግሞ፣ ንጹሕ አምልኮ ቀስ በቀስ መልሶ ሲቋቋም የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ በመስጠት ሞገሱን አሳይቷቸዋል። በዚያ ወቅት የአምላክ ሕዝብ ያገኙት መንፈሳዊ በረከት ከዚያ በፊት ካገኙት በረከት ሁሉ በእጅጉ የሚበልጥ ነበር። ቁጥር 26 እንደሚገልጸው ይሖዋ መንፈሳዊ ብርሃን በእጅጉ ደምቆ እንዲበራ አድርጓል። (ኢሳ. 60:2) የይሖዋ በረከት፣ አገልጋዮቹ “ከልባቸው ደስታ የተነሳ” በርትተውና ሐሴት አድርገው እንዲያገለግሉት ረድቷቸዋል።—ኢሳ. 65:14

13. ስለ መልሶ መቋቋም የሚገልጸው ትንቢት በዘመናችን የተፈጸመው እንዴት ነው?

13 ንጹሕ አምልኮ መልሶ ስለመቋቋሙ የሚገልጸው ትንቢት ከእኛ ጋር በተያያዘ ይሠራል? ምን ጥያቄ አለው! እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ከ1919 ዓ.ም. ወዲህ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን ግዞት ማለትም በዓለም ላይ ካሉ የሐሰት ሃይማኖቶች ባርነት ነፃ ወጥተዋል። እነዚህ ሰዎች እስራኤላውያን ይኖሩባት ከነበረችው ተስፋይቱ ምድር እጅግ ወደተሻለ ቦታ ማለትም ወደ መንፈሳዊው ገነት ገብተዋል። (ኢሳ. 51:3፤ 66:8) ይሁንና ይህ መንፈሳዊ ገነት ምንድን ነው?

14. መንፈሳዊው ገነት ምንድን ነው? በአሁኑ ጊዜ በዚያ የሚኖሩትስ እነማን ናቸው? (“ተጨማሪ ማብራሪያ” የሚለውን ተመልከት።)

14 ከ1919 ዓ.ም. ወዲህ ቅቡዓኑ በመንፈሳዊው ገነት b ውስጥ በደስታ እየኖሩ ነው። ውሎ አድሮ ደግሞ፣ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው “ሌሎች በጎች” በዚህ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ መኖር ጀመሩ፤ እነሱም የይሖዋን የተትረፈረፉ በረከቶች እያጨዱ ነው።—ዮሐ. 10:16፤ ኢሳ. 25:6፤ 65:13

15. መንፈሳዊው ገነት የሚገኘው የት ነው?

15 በዛሬው ጊዜ መንፈሳዊው ገነት የሚገኘው የት ነው? የይሖዋ አገልጋዮች የሚገኙት በሁሉም የዓለም ክፍሎች ነው። በመሆኑም እነሱ የሚኖሩበት መንፈሳዊ ገነት የሚገኘው በመላው ዓለም ነው። ስለዚህ በዛሬው ጊዜ የምንኖረው የትም ይሁን የት፣ ንጹሑን አምልኮ በንቃት እስከደገፍን ድረስ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ መኖር እንችላለን።

እያንዳንዳችን የመንፈሳዊው ገነት ውበት እንዲጨምር የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 16-17⁠ን ተመልከት)

16. መንፈሳዊው ገነት ያለውን ውበት ማየታችንን ለመቀጠል ምን ይረዳናል?

16 በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ መኖራችንን ለመቀጠል ማድረግ ካለብን ነገሮች አንዱ በዓለም ዙሪያ ለሚገኘው የክርስቲያን ጉባኤ ጥልቅ አድናቆት ማዳበር ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን አለፍጽምና ላይ ሳይሆን በውበታቸው ላይ በማተኮር ነው። (ዮሐ. 17:20, 21) እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ ምሳሌ እንመልከት። ውብ በሆነ መናፈሻ ውስጥ የተለያዩ ዓይነት ዛፎች እንደሚኖሩ እንጠብቃለን። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኘው መንፈሳዊ ገነት የተለያዩ ዓይነት ሰዎችን ይዟል። (ኢሳ. 44:4፤ 61:3) ትኩረት ማድረግ ያለብን “በደኑ” ውበት ላይ እንጂ አጠገባችን ያሉት “ዛፎች” ባላቸው እንከን ላይ አይደለም። የራሳችንም ሆነ የሌሎች ክርስቲያኖች አለፍጽምና፣ አንድነት ያለው ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ያለውን ውበት እንዳናይ እንቅፋት ሊሆንብን አይገባም።

17. እያንዳንዳችን የጉባኤውን አንድነት ለመጠበቅ ምን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን?

17 እያንዳንዳችን ለዚህ አንድነት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው? ሰላም ፈጣሪዎች በመሆን ነው። (ማቴ. 5:9፤ ሮም 12:18) በጉባኤ ውስጥ ካሉ ክርስቲያኖች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት ባደረግን ቁጥር የመንፈሳዊው ገነት ውበት እንዲደምቅ እናደርጋለን። በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ የሚኖረውን እያንዳንዱን ሰው ወደ ንጹሕ አምልኮ የሳበው ይሖዋ እንደሆነ አንዘነጋም። (ዮሐ. 6:44) ይሖዋ እንደ ውድ አድርጎ በሚመለከታቸው አገልጋዮቹ መካከል ያለውን ሰላምና አንድነት ለማጠናከር ተግተን ስንሠራ ሲመለከት ምን ያህል እንደሚደሰት እስቲ አስቡት!—ኢሳ. 26:3፤ ሐጌ 2:7

18. አዘውትረን በምን ጉዳይ ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል? ለምንስ?

18 አምላክ ለአገልጋዮቹ ከሚሰጠው በረከት የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? በአምላክ ቃልና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን ውስጥ የምናጠናውን ነገር ልናሰላስልበት ይገባል። በዚህ መልኩ ማጥናታችንና ማሰላሰላችን የተለያዩ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንድናዳብር ይረዳናል፤ እነዚህ ባሕርያት በጉባኤ ውስጥ ‘በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችን ከልብ ለመዋደድ’ ያነሳሱናል። (ሮም 12:10) አሁን ባሉን በረከቶች ላይ ስናሰላስል ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ይጠናከራል። ይሖዋ ወደፊት ባዘጋጀልን በረከቶች ላይ ማሰላሰላችን ደግሞ እሱን ለዘላለም ለማገልገል ያለን ተስፋ እውን ሆኖ እንዲታየን ያደርጋል። እነዚህ ነገሮች በሙሉ በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን በማገልገል ደስታ እንድናገኝ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል

19. (ሀ) በኢሳይያስ 30:18 መሠረት ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን? (ለ) በደስታ ለመጽናት ምን ይረዳናል?

19 ይሖዋ ይህን ክፉ ዓለም በማጥፋት ለእኛ ሲል “ይነሳል።” (ኢሳ. 30:18) “የፍትሕ አምላክ” የሆነው ይሖዋ፣ የሰይጣን ዓለም የእሱ የፍትሕ መሥፈርት ከሚጠይቀው በላይ ለአንድ ቀን እንኳ እንዲቆይ እንደማይፈቅድ እርግጠኞች ነን። (ኢሳ. 25:9) ይህ የመዳን ቀን እስኪመጣ ከይሖዋ ጋር በትዕግሥት እንጠብቃለን። እስከዚያው ግን የጸሎት መብታችንን ከፍ አድርገን ለመመልከት፣ የአምላክን ቃል ለማጥናትና በሥራ ላይ ለማዋል እንዲሁም ባሉን በረከቶች ላይ ለማሰላሰል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። እንዲህ ስናደርግ ይሖዋ እሱን እያመለክን በደስታ እንድንጸና ይረዳናል።

መዝሙር 142 ተስፋችንን አጥብቀን እንያዝ

a ይሖዋ አገልጋዮቹ በሕይወታቸው ውስጥ የተለያየ መከራ ቢያጋጥማቸውም በደስታ መጽናት እንዲችሉ የሚረዳቸው በየትኞቹ ሦስት መንገዶች እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። እነዚህን መንገዶች ለማየት ኢሳይያስ ምዕራፍ 30⁠ን እንመረምራለን። ይህን ምዕራፍ ስንመረምር ወደ ይሖዋ መጸለይ፣ ቃሉን ማጥናት እንዲሁም አሁንም ሆነ ወደፊት ስለምናገኛቸው በረከቶች ማሰላሰል ያለውን ጠቀሜታ እናያለን።

b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ “መንፈሳዊ ገነት” ይሖዋን በአንድነት የምናመልክበትን ደህንነቱ የተጠበቀ ሁኔታ ያመለክታል። በዚህ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ከሃይማኖታዊ ውሸቶች የጸዳ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እናገኛለን። እንዲሁም የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበክ አርኪ ሥራ አለን። ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና አለን። እንዲሁም አፍቃሪ ከሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በሰላም እንኖራለን፤ እነሱም በሕይወታችን ውስጥ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን በደስታ ለመጽናት ይረዱናል። ወደዚህ መንፈሳዊ ገነት የምንገባው ይሖዋን በትክክለኛው መንገድ ማምለክ ስንጀምርና እሱን ለመምሰል የቻልነውን ሁሉ ጥረት ስናደርግ ነው።