የጥናት ርዕስ 45
ይሖዋ አገልግሎታችንን እንድንፈጽም የሚረዳን እንዴት ነው?
“በመካከላቸው ነቢይ እንደነበረ በእርግጥ ያውቃሉ።”—ሕዝ. 2:5
መዝሙር 67 “ቃሉን ስበክ”
ማስተዋወቂያ a
1. ምን እንደሚያጋጥመን ልንጠብቅ እንችላለን? ስለ ምን ነገርስ እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
የስብከቱን ሥራችንን ስናከናውን ተቃውሞ ሊያጋጥመን እንደሚችል እንጠብቃለን። እንዲህ ያለው ተቃውሞ ደግሞ ወደፊት እየጨመረ መሄዱ አይቀርም። (ዳን. 11:44፤ 2 ጢሞ. 3:12፤ ራእይ 16:21) ያም ቢሆን ይሖዋ የሚያስፈልገንን እርዳታ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ጥንትም ሆነ ዛሬ፣ ይሖዋ አገልጋዮቹ በጣም ከባድ የሆኑ ኃላፊነቶችን እንኳ እንዲወጡ ረድቷቸዋል። ለምሳሌ በባቢሎን ለነበሩት አይሁዳውያን ግዞተኞች ይሰብክ የነበረው ነቢዩ ሕዝቅኤል ያጋጠሙትን ነገሮች እንመልከት።
2. ይሖዋ፣ ሕዝቅኤል በሚሰብክበት ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች ምን ዓይነት እንደሆኑ ተናግሯል? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን? (ሕዝቅኤል 2:3-6)
2 ሕዝቅኤል በሚሰብክበት ክልል ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ምን ዓይነት ነበሩ? ይሖዋ እነዚህ ሰዎች “ግትር፣” “ልበ ደንዳና” እና “ዓመፀኛ” እንደሆኑ ተናግሯል። እንደ እሾህ ጎጂ እና እንደ ጊንጥ አደገኛ ነበሩ። ከዚህ አንጻር ይሖዋ ለሕዝቅኤል በተደጋጋሚ “አትፍራ” ያለው መሆኑ አያስገርምም። (ሕዝቅኤል 2:3-6ን አንብብ።) ያም ቢሆን ሕዝቅኤል የተሰጠውን የስብከት ተልእኮ መወጣት ችሏል። ምክንያቱም (1) የተላከው በይሖዋ ነበር፤ (2) የአምላክ መንፈስ ኃይል ሰጥቶታል፤ እንዲሁም (3) የአምላክ ቃል እንደ ምግብ ሆኖለታል። እነዚህ ሦስት ነገሮች ሕዝቅኤልን የረዱት እንዴት ነው? ዛሬስ እኛን የሚረዱን እንዴት ነው?
ሕዝቅኤልን የላከው ይሖዋ ነው
3. ሕዝቅኤልን የትኛው ቃል አበረታቶት መሆን አለበት? ይሖዋ እንደሚረዳው ማረጋገጫ ያገኘውስ እንዴት ነው?
3 ይሖዋ ሕዝቅኤልን “እልክሃለሁ” ብሎታል። (ሕዝ. 2:3, 4) ይህ ቃል ሕዝቅኤልን አበረታቶት መሆን አለበት። ለምን? ይሖዋ ለሙሴና ለኢሳይያስ የነቢይነት ተልእኮ ሲሰጣቸው ይህንኑ ቃል እንደተጠቀመ ሕዝቅኤል አስታውሶ መሆን አለበት። (ዘፀ. 3:10፤ ኢሳ. 6:8) በተጨማሪም ሕዝቅኤል፣ ይሖዋ እነዚህ ሁለት ነቢያት የተሰጣቸውን ከባድ ኃላፊነት እንዲወጡ እንደረዳቸው ያውቃል። በመሆኑም ይሖዋ ለሕዝቅኤል ሁለት ጊዜ “እልክሃለሁ” ሲለው ነቢዩ ይሖዋ እንደሚረዳው የሚተማመንበት በቂ ምክንያት ነበረው። ከዚህም ሌላ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ “የይሖዋ ቃል ወደ እኔ መጣ” የሚለውን አገላለጽ በተደጋጋሚ እናገኛለን። (ሕዝ. 3:16) “የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ” የሚለው አገላለጽም በመጽሐፉ ውስጥ ብዙ ጊዜ ይገኛል። (ሕዝ. 6:1) በእርግጥም ሕዝቅኤል፣ የላከው ይሖዋ እንደሆነ ምንም አልተጠራጠረም። በተጨማሪም ሕዝቅኤል የካህን ልጅ ስለነበር አባቱ፣ ይሖዋ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ነቢያቱን እንደሚደግፋቸው ዋስትና እንደሰጣቸው አስተምሮት መሆን አለበት። ይሖዋ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብና ለኤርምያስ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝ” ብሏቸዋል።—ዘፍ. 28:15፤ 26:24፤ ኤር. 1:8
4. ሕዝቅኤልን ያበረታቱት የትኞቹ አጽናኝ ሐሳቦች ናቸው?
4 አብዛኞቹ እስራኤላውያን ለሕዝቅኤል ስብከት ምን ምላሽ ይሰጣሉ? ይሖዋ “የእስራኤል ቤት . . . ሊሰሙህ አይፈልጉም፤ እኔን መስማት አይፈልጉምና” ብሎታል። (ሕዝ. 3:7) ሕዝቡ ሕዝቅኤልን ባለመቀበል ይሖዋን እንደማይቀበሉ አሳይተዋል። ይሖዋ የተናገረው ሐሳብ፣ ሕዝቡ ሕዝቅኤልን አለመቀበላቸው ሕዝቅኤል የነቢይነት ተልእኮውን በአግባቡ እንዳልተወጣ የሚያሳይ እንዳልሆነ አረጋግጦለታል። ከዚህም ሌላ ሕዝቅኤል የተናገረው የፍርድ መልእክት ሲፈጸም ሕዝቡ “በመካከላቸው ነቢይ እንደነበረ በእርግጥ [እንደሚያውቁ]” ይሖዋ ለሕዝቅኤል ገልጾለታል። (ሕዝ. 2:5፤ 33:33) እነዚህ አጽናኝ ሐሳቦች፣ ሕዝቅኤል አገልግሎቱን ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ብርታት እንደሰጡት ምንም ጥርጥር የለውም።
የላከን ይሖዋ ነው
5. በኢሳይያስ 44:8 መሠረት ብርታት የሚሰጠን ምንድን ነው?
5 እኛም ይሖዋ እንደላከን ማወቃችን ብርታት ይሰጠናል። ይሖዋ “ምሥክሮቼ” ብሎ በመጥራት አክብሮናል። (ኢሳ. 43:10) ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ይሖዋ ሕዝቅኤልን “አትፍራ” እንዳለው ሁሉ እኛንም “ስጋት አይደርባችሁ” ብሎናል። ተቃዋሚዎቻችንን ልንፈራ የማይገባው ለምንድን ነው? እንደ ሕዝቅኤል ሁሉ እኛንም የላከን ይሖዋ ነው፤ ደግሞም እሱ ይደግፈናል።—ኢሳይያስ 44:8ን አንብብ።
6. (ሀ) ይሖዋ እንደሚደግፈን ቃል የገባልን እንዴት ነው? (ለ) የሚያጽናናንና የሚያበረታታን ምንድን ነው?
6 ይሖዋ እንደሚደግፈን ቃል ገብቶልናል። ለምሳሌ “እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ” ከማለቱ በፊት እንዲህ ብሏል፦ “በውኃዎች መካከል ስታልፍ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ በወንዞችም መካከል ስትሻገር አያሰምጡህም። በእሳት መካከል ስትሄድ አትቃጠልም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም።” (ኢሳ. 43:2) አገልግሎታችንን ስናከናውን አንዳንድ ጊዜ እንደ ወንዝ ያሉ እንቅፋቶችና እንደ እሳት ያሉ ፈተናዎች ያጋጥሙናል። ያም ቢሆን በይሖዋ እርዳታ መስበካችንን እንቀጥላለን። (ኢሳ. 41:13) እንደ ሕዝቅኤል ዘመን ሁሉ ዛሬም አብዛኞቹ ሰዎች መልእክታችንን አይቀበሉም። ሆኖም እነሱ መልእክቱን አለመቀበላቸው የስብከቱን ሥራ በአግባቡ እንዳላከናወንን የሚያሳይ እንዳልሆነ እንገነዘባለን። መልእክቱን በታማኝነት ማወጃችንን እስከቀጠልን ድረስ ይሖዋ እንደሚደሰት ማወቃችን ያጽናናናል እንዲሁም ያበረታታናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የራሱን ወሮታ ይቀበላል” ብሏል። (1 ቆሮ. 3:8፤ 4:1, 2) ለረጅም ጊዜ በአቅኚነት ያገለገለች አንዲት እህት “ይሖዋ ወሮታ የሚሰጠን ለጥረታችን መሆኑን ማወቄ ያስደስተኛል” ብላለች።
የአምላክ መንፈስ ለሕዝቅኤል ኃይል ሰጥቶታል
7. ሕዝቅኤል ያየውን ራእይ ባስታወሰ ቁጥር ምን ተሰምቶት መሆን አለበት? (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)
7 ሕዝቅኤል የአምላክ መንፈስ ምን ያህል ኃያል እንደሆነ ተመልክቷል። ሕዝቅኤል፣ መንፈስ ቅዱስ ኃያል በሆኑት መንፈሳዊ ፍጥረታት ላይ ሲሠራ እንዲሁም የሰማያዊውን ሠረገላ ግዙፍ መንኮራኩሮች ሲያንቀሳቅስ በራእይ አይቷል። (ሕዝ. 1:20, 21) ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን አደረገ? “እኔም ባየሁት ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ” ብሏል። ሕዝቅኤል በድንጋጤ ተውጦ መሬት ላይ ወደቀ። (ሕዝ. 1:28) ሕዝቅኤል ይህን አስደናቂ ራእይ ባስታወሰ ቁጥር፣ በአምላክ መንፈስ እርዳታ አገልግሎቱን ማከናወን እንደሚችል ያለው እምነት ይበልጥ እንደሚጠናከር ጥያቄ የለውም።
8-9. (ሀ) የይሖዋ ትእዛዝ ለሕዝቅኤል ምን ሰጠው? (ለ) ይሖዋ ሕዝቅኤልን ለተመደበበት አስቸጋሪ ክልል ለማዘጋጀት ሌላስ ምን አደረገ?
8 ይሖዋ ሕዝቅኤልን “የሰው ልጅ ሆይ፣ ተነስተህ በእግርህ ቁም፤ እኔም አናግርሃለሁ” በማለት አዘዘው። ይህ ትእዛዝ ከአምላክ መንፈስ ጋር ተደምሮ፣ ለሕዝቅኤል ከመሬት ለመነሳት የሚያስፈልገውን ጥንካሬ ሰጥቶታል። ሕዝቅኤል “መንፈስ ወደ ውስጤ ገባ፤ [በእግሬም] አቆመኝ” በማለት ጽፏል። (ሕዝ. 2:1, 2) ከጊዜ በኋላም ሕዝቅኤል አገልግሎቱን ባከናወነበት ዘመን ሁሉ የአምላክ “እጅ” ማለትም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ መርቶታል። (ሕዝ. 3:22፤ 8:1፤ 33:22፤ 37:1፤ 40:1) የአምላክ መንፈስ፣ ሕዝቅኤል ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማለትም በክልሉ ውስጥ ላሉ “ግትርና ልበ ደንዳና” ሰዎች እንዲሰብክ ኃይል ሰጥቶታል። (ሕዝ. 3:7) ይሖዋ ሕዝቅኤልን እንዲህ ብሎታል፦ “ፊትህን ልክ እንደ እነሱ ፊት ጠንካራ አድርጌዋለሁ፤ ግንባርህንም ልክ እንደ እነሱ ግንባር አጠንክሬዋለሁ። ግንባርህን እንደ አልማዝ፣ ከባልጩትም ይበልጥ ጠንካራ አድርጌዋለሁ። አትፍራቸው፤ ከፊታቸውም የተነሳ አትሸበር።” (ሕዝ. 3:8, 9) ይሖዋ ለሕዝቅኤል እንዲህ ያለው ያህል ነበር፦ ‘የሰዎቹ ልበ ደንዳናነት ተስፋ እንዲያስቆርጥህ አትፍቀድ። እኔ አበረታሃለሁ።’
9 ከዚያም የአምላክ መንፈስ ሕዝቅኤልን ወደሚሰብክበት ክልል ወሰደው። ሕዝቅኤል “[የይሖዋ] ብርቱ እጅ በእኔ ላይ አርፋ ነበር” በማለት ጽፏል። ሕዝቅኤል መልእክቱን እስኪያብላላውና የራሱ እስኪያደርገው ድረስ አንድ ሳምንት ፈጅቶበታል። (ሕዝ. 3:14, 15) ከዚያም ይሖዋ ወደ ሸለቋማው ሜዳ እንዲሄድ አዘዘው፤ በዚያም ‘መንፈስ ወደ ውስጡ ገባ።’ (ሕዝ. 3:23, 24) አሁን ሕዝቅኤል አገልግሎቱን ለመጀመር ዝግጁ ሆነ።
የአምላክ መንፈስ ኃይል ይሰጠናል
10. የስብከቱን ሥራችንን ለማከናወን ምን ዓይነት እርዳታ ያስፈልገናል? ለምንስ?
10 የስብከቱን ሥራችንን ለማከናወን ምን ዓይነት እርዳታ ያስፈልገናል? ይህን ጥያቄ ለመመለስ ሕዝቅኤል ያጋጠመውን ነገር በድጋሚ እንመልከት። የስብከት ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የአምላክ መንፈስ የሚያስፈልገውን ጥንካሬ ሰጥቶታል። እንደ ሕዝቅኤል ሁሉ እኛም የስብከቱን ሥራ ማከናወን የቻልነው የአምላክ መንፈስ ስለረዳን ብቻ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሰይጣን የስብከት ሥራችንን ለማስቆም ጦርነት አውጆብናል። (ራእይ 12:17) በሰብዓዊ አመለካከት ሲታይ ሰይጣንን ፈጽሞ ልናሸንፈው የምንችል አይመስልም። ሆኖም በስብከቱ ሥራችን አማካኝነት ድል እያደረግነው ነው! (ራእይ 12:9-11) እንዴት? በአገልግሎት ስንካፈል የሰይጣንን ዛቻ እንደማንፈራ እናሳያለን። በስብከቱ ሥራ በተካፈልን ቁጥር ሰይጣን ድል ይደረጋል። ከዚህ አንጻር፣ ተቃውሞ ቢኖርም የስብከቱን ሥራ ማከናወን መቻላችን ምን ያሳያል? መንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደሰጠንና የይሖዋ ሞገስ እንዳለን ያሳያል።—ማቴ. 5:10-12፤ 1 ጴጥ. 4:14
11. የአምላክ መንፈስ ምን ሊያደርግልን ይችላል? መንፈሱን በቀጣይነት ለማግኘትስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
11 ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ የሕዝቅኤልን ፊትና ግንባር ማጠንከሩን ማወቃችን ሌላስ ምን ዋስትና ይሰጠናል? የአምላክ መንፈስ በአገልግሎት ላይ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና እንድንወጣ ሊረዳን ይችላል። (2 ቆሮ. 4:7-9) ታዲያ የአምላክን መንፈስ በቀጣይነት ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን? ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማ በመተማመን መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን አዘውትረን ልንለምነው ይገባል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ . . . ሳታሰልሱ ፈልጉ፣ . . . ደጋግማችሁ አንኳኩ” በማለት አስተምሯቸዋል። በምላሹም ይሖዋ “ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን” ይሰጣቸዋል።—ሉቃስ 11:9, 13፤ ሥራ 1:14፤ 2:4
የአምላክ ቃል ለሕዝቅኤል እንደ ምግብ ሆኖለታል
12. ጥቅልሉ የመጣው ከየት ነው? በውስጡስ ምን ይዟል? (ሕዝቅኤል 2:9 እስከ 3:3)
12 ሕዝቅኤል የአምላክ መንፈስ ኃይል ሰጥቶታል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን የአምላክ ቃል እንደ ምግብ ሆኖለታል። ሕዝቅኤል ጥቅልል የያዘ እጅ በራእይ ተመልክቷል። (ሕዝቅኤል 2:9 እስከ 3:3ን አንብብ።) ጥቅልሉ የመጣው ከየት ነው? በውስጡ ምን ይዟል? ለሕዝቅኤል እንደ ምግብ የሆነለትስ እንዴት ነው? እስቲ መልሶቹን እንመልከት። ጥቅልሉ የመጣው ከአምላክ ዙፋን ነው። ይሖዋ ጥቅልሉን ለሕዝቅኤል ለመስጠት የተጠቀመው፣ ሕዝቅኤል ቀደም ሲል ካያቸው አራት መላእክት አንዱን ሳይሆን አይቀርም። (ሕዝ. 1:8፤ 10:7, 20) ጥቅልሉ የያዘው የአምላክን ቃል ይኸውም ሕዝቅኤል ለዓመፀኞቹ ግዞተኞች የሚያስተላልፈውን ረጅም የፍርድ መልእክት ነበር። (ሕዝ. 2:7) መልእክቱ በጥቅልሉ ላይ የተጻፈው ከፊትና ከኋላ ነበር።
13. ይሖዋ ለሕዝቅኤል ጥቅልሉን ምን እንዲያደርገው ነገረው? የጣፈጠውስ ለምንድን ነው?
13 ይሖዋ ለሕዝቅኤል ጥቅልሉን እንዲበላና ‘ሆዱን እንዲሞላ’ ነገረው። ሕዝቅኤልም የተባለውን በመታዘዝ ሙሉውን ጥቅልል በላው። ይህ ራእይ ምን ትርጉም አለው? ሕዝቅኤል የሚያውጀው መልእክት ሙሉ በሙሉ ሊዋሃደው ይገባል። ለመስበክ እንዲነሳሳ በመልእክቱ ላይ ሙሉ እምነት ሊኖረው ይገባ ነበር። ከዚያም አንድ አስደናቂ ነገር ተፈጠረ። ሕዝቅኤል ጥቅልሉ ‘እንደ ማር ጣፈጠው።’ (ሕዝ. 3:3) ለምን? ለሕዝቅኤል ይሖዋን የመወከል መብት ጣፋጭ ወይም አስደሳች ነገር ነበር። (መዝ. 19:8-11) ይሖዋ ነቢይ አድርጎ ስለሾመው አመስጋኝ ነበር።
14. ሕዝቅኤል የተሰጠውን ተልእኮ ለመጀመር ዝግጁ እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው?
14 በኋላ ላይ ይሖዋ ለሕዝቅኤል “የምነግርህን ቃል ሁሉ በልብህ ያዝ፤ ደግሞም አዳምጥ” አለው። (ሕዝ. 3:10) ይሖዋ ይህን መመሪያ የሰጠው ሕዝቅኤል በጥቅልሉ ውስጥ የተጻፈውን ሐሳብ እንዲያስታውስና እንዲያሰላስልበት ነው። ሕዝቅኤል እንዲህ ማድረጉ እንደ ምግብ ብርታት ሰጥቶታል። በተጨማሪም ለሕዝቡ የሚያውጀው ወሳኝ መልእክት በጥቅልሉ ውስጥ አግኝቷል። (ሕዝ. 3:11) የአምላክ መልእክት በልቡና በአንደበቱ ላይ ስለነበር ሕዝቅኤል የተሰጠውን ተልእኮ ለመጀመርና ለመፈጸም ዝግጁ ሆነ።—ከመዝሙር 19:14 ጋር አወዳድር።
የአምላክ ቃል እንደ ምግብ ይሆንልናል
15. መጽናት ከፈለግን ምን ነገር ‘በልባችን ልንይዝ’ ይገባል?
15 እኛም በአገልግሎታችን ለመጽናት የአምላክን ቃል አዘውትረን መመገብ ይኖርብናል። ይሖዋ የሚነግረንን ነገር ሁሉ ‘በልባችን ልንይዝ’ ይገባል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የሚያነጋግረን በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። ይሁንና የአምላክ ቃል በአስተሳሰባችን፣ በስሜታችንና በልባችን ዝንባሌ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን እንዲቀጥል ምን ማድረግ ይኖርብናል?
16. የአምላክን ቃል ምን ልናደርገው ይገባል? ከልባችን ጋር እንዲዋሃድስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
16 ምግብ በልተን ሲዋሃደን ሰውነታችን እንደሚጠነክር ሁሉ የአምላክን ቃል አጥንተን ስናሰላስልበት መንፈሳዊነታችን ይጠናከራል። ስለ ጥቅልሉ ከሚገልጸው ራእይ ያገኘነውን ትምህርት አንዘንጋ። ይሖዋ በቃሉ ‘ሆዳችንን እንድንሞላ’ ማለትም መልእክቱን እንድንረዳው ይፈልጋል። ይህን ለማድረግ መጸለይ፣ ማንበብና ማሰላሰል ይኖርብናል። በመጀመሪያ የአምላክን ሐሳብ እንዲቀበል ልባችንን ለማዘጋጀት እንጸልያለን። ቀጥሎ መጽሐፍ ቅዱስን እናነባለን። ከዚያም ቆም ብለን በማሰላሰል ስላነበብነው ነገር በጥልቀት እናስባለን። እንዲህ ስናደርግ ውጤቱ ምን ይሆናል? ይበልጥ ባሰላሰልን ቁጥር የአምላክ ቃል ከምሳሌያዊ ልባችን ጋር ይበልጥ ይዋሃዳል።
17. መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰላችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
17 መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችንና ማሰላሰላችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን በአሁኑ ጊዜ የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ እንዲሁም በቅርቡ ልናውጅ የምንችለውን ኃይለኛ የፍርድ መልእክት ለመናገር ውስጣዊ ጥንካሬ ይሰጠናል። ከዚህም ሌላ፣ ማራኪ በሆኑት የይሖዋ ባሕርያት ላይ ስናሰላስል ከእሱ ጋር ያለን ዝምድና ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል። በውጤቱም እጅግ ጣፋጭ የሆነውን ውስጣዊ ሰላምና እርካታ እናጣጥማለን።—መዝ. 119:103
ለመጽናት ተነሳስተናል
18. በክልላችን ውስጥ ያሉት ሰዎች ምን ነገር ለመቀበል ይገደዳሉ? ለምንስ?
18 ከሕዝቅኤል በተለየ፣ እኛ በመንፈስ መሪነት የመተንበይ ተልእኮ አልተሰጠንም። ይሁንና የስብከቱ ሥራ ይሖዋ በሚፈልገው መጠን እስኪጠናቀቅ ድረስ፣ በመንፈስ መሪነት ባስጻፈው ቃሉ ውስጥ ያለውን መልእክት ማወጃችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። የፍርድ ጊዜ ሲመጣ በክልላችን ውስጥ ያሉት ሰዎች ማስጠንቀቂያ እንዳልተሰጣቸው ወይም አምላክ ችላ እንዳላቸው ለመናገር የሚያበቃ ምንም ምክንያት አይኖራቸውም። (ሕዝ. 3:19፤ 18:23) ከዚህ ይልቅ፣ መልእክታችን የመነጨው ከአምላክ እንደሆነ ለመቀበል ይገደዳሉ።
19. አገልግሎታችንን ለመፈጸም የሚያስችል ብርታት የሚሰጠን ምንድን ነው?
19 አገልግሎታችንን ለመፈጸም የሚያስችል ብርታት የሚሰጠን ምንድን ነው? ለሕዝቅኤል ብርታት የሰጡት ሦስት ነገሮች ለእኛም ብርታት ይሰጡናል። የላከን ይሖዋ እንደሆነ ስለምናውቅ፣ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ኃይል ስለሚሰጠን እንዲሁም የአምላክ ቃል እንደ ምግብ ስለሚሆንልን መስበካችንን እንቀጥላለን። በይሖዋ እርዳታ አገልግሎታችንን ለመፈጸምና “እስከ መጨረሻው” ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።—ማቴ. 24:13
መዝሙር 65 ወደፊት ግፋ!
a በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ነቢዩ ሕዝቅኤል የተሰጠውን የስብከት ተልእኮ ለመወጣት የረዱትን ሦስት ነገሮች እንመለከታለን። ይሖዋ ይህን ነቢይ የረዳው እንዴት እንደሆነ መመልከታችን እኛም አገልግሎታችንን ስናከናውን ይሖዋ እንደሚረዳን እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል።