በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

በጦርነትም ሆነ በሰላም ወቅት ይሖዋ ብርታት ሰጥቶናል

በጦርነትም ሆነ በሰላም ወቅት ይሖዋ ብርታት ሰጥቶናል

ፖል፦ በጣም ጓጉተን ነበር! ጊዜው ኅዳር 1985 ሲሆን የመጀመሪያ ሚስዮናዊ ምድባችን ወደሆነችው በምዕራብ አፍሪካ ወደምትገኘው ወደ ላይቤሪያ እየተጓዝን ነበር። አውሮፕላናችን ሴኔጋል ላይ አረፈ። አን “ከአንድ ሰዓት በኋላ እኮ ላይቤሪያ እንገባለን” አለች። ከዚያ ግን እንዲህ የሚል ማስታወቂያ ሰማን፦ “ወደ ላይቤሪያ የሚሄዱ ተጓዦች ከአውሮፕላኑ መውረድ አለባቸው። መፈንቅለ መንግሥት በመከሰቱ እዚያ ማረፍ አንችልም።” ለቀጣዮቹ አሥር ቀናት፣ ሴኔጋል ውስጥ ካሉ ሚስዮናውያን ጋር ቆየን። ላይቤሪያ ውስጥ ብዙ ሰዎች እንደተጨፈጨፉ እንዲሁም ሰዓት እላፊ እንደተጣለና እሱን የተላለፉ ሰዎች እንደሚገደሉ የሚገልጽ ዜና እንሰማ ነበር።

አን፦ በባሕርያችን አደገኛ ነገር መሞከር የሚያስደስተን ሰዎች አይደለንም። እንዲያውም ከልጅነቴ ጀምሮ የምታወቀው ጭንቀታም በመሆኔ ነው። መንገድ መሻገር እንኳ ያስፈራኛል! ሆኖም ወደ ምድባችን ለመድረስ ቆርጠን ነበር።

ፖል፦ እኔና አን የተወለድነው በምዕራባዊ እንግሊዝ ሲሆን በሰፈራችን መካከል ያለው ርቀት ስምንት ኪሎ ሜትር ብቻ ነበር። ወላጆቼና የአን እናት በእጅጉ ስላበረታቱን ሁለታችንም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታችንን እንዳጠናቀቅን አቅኚነት ጀመርን። በመላ ሕይወታችን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል የነበረንን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ደግፈውልናል። በ19 ዓመቴ ቤቴል የመግባት መብት አገኘሁ። በ1982 ከተጋባን በኋላ ደግሞ አንም በቤቴል አብራኝ ማገልገል ጀመረች።

የጊልያድ ምረቃ፣ መስከረም 8, 1985

አን፦ የቤቴል አገልግሎታችንን እንወደው ነበር። ሆኖም የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ የማገልገል ፍላጎት ነበረን። ቀደም ሲል ሚስዮናውያን ከነበሩ ክርስቲያኖች ጋር በቤቴል ማገልገላችን ደግሞ ይህን ፍላጎታችንን ይበልጥ አቀጣጠለው። ለሦስት ዓመት ያህል በየምሽቱ ይህን ጉዳይ ለይተን በመጥቀስ እንጸልይ ነበር። ስለዚህ በ1985 በጊልያድ ትምህርት ቤት 79ኛ ክፍል እንድንማር ስንጋበዝ በጣም ተደሰትን! በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው በላይቤሪያ እንድናገለግል ተመደብን።

የወንድሞቻችንና የእህቶቻችን ፍቅር ብርታት ሰጥቶናል

ፖል፦ ወደ ላይቤሪያ በረራ እንደተጀመረ በመጀመሪያው አውሮፕላን ተሳፈርን። ሁኔታው ውጥረት የነገሠበት ነበር፤ ሰዓት እላፊውም ገና አልተነሳም። ሕዝቡ ከፍተኛ ድምፅ የሚያሰማ መኪና ሲሰሙ እንኳ እጅግ ይሸበሩ ነበር። አእምሯችንን ለማረጋጋት በየምሽቱ ከመዝሙር መጽሐፍ የተወሰነ ክፍል እናነብ ነበር። ሆኖም የአገልግሎት ምድባችንን በጣም ወደድነው። አን የመስክ ሚስዮናዊ ነበረች፤ እኔ ደግሞ ቤቴል ውስጥ ከወንድም ጆን ቻሩክ a ጋር አብሬ እሠራ ነበር። ወንድም ቻሩክ በዚያ ለረጅም ዓመታት ያገለገለ ከመሆኑም ሌላ የወንድሞችንና የእህቶችን ሁኔታ በጥልቅ ይረዳ ስለነበር ከእሱ ብዙ ትምህርት አግኝቻለሁ።

አን፦ ላይቤሪያን ወዲያውኑ በጣም የወደድናት ለምንድን ነው? በወንድሞቻችንና እህቶቻችን የተነሳ ነው። አፍቃሪ፣ በቀላሉ የሚቀረቡና ታማኞች ነበሩ። በጣም ተቀራረብን፤ አዲስ ቤተሰብ አገኘን። የሰጡን ምክር በመንፈሳዊ እንድንጠነክር ረድቶናል። አገልግሎቱ ደግሞ በጣም ደስ ይል ነበር። ሰዎቹ ለረጅም ሰዓት ሳናነጋግራቸው ከቤታቸው ከሄድን ይበሳጩብናል። በየመንገዱ ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች የሚያወሩ ሰዎች እናገኛለን። ከእኛ የሚጠበቀው ቀረብ ብለን ውይይታቸውን መቀላቀል ብቻ ነው። በጣም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ከማግኘታችን የተነሳ ሁሉንም ለማስጠናት ተቸግረን ነበር። ደስ የሚል ችግር ነው የገጠመን!

ፍርሃት ቢሰማንም ይሖዋ ብርታት ሰጥቶናል

በላይቤሪያ ቤቴል የተቀበልናቸው ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ክርስቲያኖች፣ 1990

ፖል፦ ለአራት ዓመት ያህል አንጻራዊ ሰላም ካገኘን በኋላ በ1989 አስደንጋጭ ለውጥ ተከሰተ፤ የለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ተነሳ። ሐምሌ 2, 1990 ዓማፅያኑ በቤቴል ዙሪያ ያለውን አካባቢ ተቆጣጠሩ። ለሦስት ወር ያህል ቤተሰቦቻችንንና ዋናውን መሥሪያ ቤት ጨምሮ ከውጩ ዓለም ጋር ሙሉ በሙሉ ተቆራርጠን ነበር። ሥርዓት አልበኝነት፣ የምግብ እጥረትና አስገድዶ መድፈር ተስፋፍቶ ነበር። ይህ መከራ ለ14 ዓመት ያህል የቀጠለ ሲሆን መላ አገሪቷ ታምሳ ነበር።

አን፦ የአንዳንድ ጎሳዎች አባላት ከሌሎች ጎሳዎች አባላት ጋር ይዋጉና ይገዳደሉ ነበር። እንግዳ ልብስ የለበሱና ብዙ መሣሪያ የታጠቁ ተዋጊዎች መንገድ ለመንገድ እየዞሩ እያንዳንዱን ሕንፃ ይዘርፋሉ። አንዳንዶቹ ሰው መግደልን ዶሮ እንደማረድ ነበር የሚቆጥሩት። በኬላዎች ላይ የተከመሩ አስከሬኖች ነበሩ። በቅርንጫፍ ቢሮው አቅራቢያም ጭምር እንዲህ ያለ ሁኔታ ነበር። ሁለት ውድ ሚስዮናውያንን ጨምሮ ታማኝ ወንድሞቻችን ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ወንድሞቻችን ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል፣ እየታደኑ ከሚገደሉት ጎሳዎች ወገን የሆኑትን ወንድሞቻቸውን ደብቀዋል። ሚስዮናውያንና ቤቴላውያንም ተመሳሳይ ነገር አድርገዋል። ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች በቤቴል ምድር ቤት ውስጥ ያድሩ ነበር። ሌሎቹ ደግሞ ፎቅ ላይ ባሉት መኝታ ክፍሎቻችን ውስጥ አብረውን ይኖሩ ነበር። ለምሳሌ በእኛ ክፍል ውስጥ ሌሎች ሰባት ሰዎች ይኖሩ ነበር።

ፖል፦ በየቀኑ ዓማፅያኑ ሰዎችን ሸሽገን እንደሆነ ለማጣራት ወደ ቤቴል ለመግባት ይሞክሩ ነበር። ግቢውን ለመጠበቅ አራት ሰዎች ተቀናጅተው ይሠራሉ። ሁለቱ ዓማፅያኑን ለማነጋገር ወደ ውጨኛው በር ሲሄዱ ሁለቱ ደግሞ መስኮት ጋ ቆመው ይመለከታሉ። ወደ በሩ የሄዱት ሁለት ወንድሞች እጃቸውን ከፊታቸው ካደረጉ ምንም ችግር የለም ማለት ነው። እጃቸውን ከኋላቸው ካደረጉ ግን ዓማፅያኑ ጠበኛ ናቸው ማለት ነው። ስለዚህ መስኮቱ ጋ የቆሙት ቤቴላውያን ቶሎ በመግባት ወንድሞቻችንን ለመደበቅ ይሞክራሉ።

አን፦ ከበርካታ ሳምንታት በኋላ፣ አንድ ቀን በቁጣ የተሞሉ ዓማፅያን ወደ ቤቴል ገቡ። ከአንዲት እህት ጋር ወደ መታጠቢያ ቤት በመግባት በሩን ቆለፍኩት። መታጠቢያ ቤቱ ውስጥ ለመደበቅ የሚያስችል ጠባብ ቦታ ያለው መደርደሪያ ነበር። እህት ተጣጥፋ እዚያ ውስጥ ገባች። ዓማፅያኑ መሣሪያቸውን እንደታጠቁ እኔ ወዳለሁበት ፎቅ ወጡ። በቁጣ ተሞልተው በሩን ደበደቡት። ፖል “ባለቤቴ መታጠቢያ ቤት እየተጠቀመች ነው” በማለት እንዳይገቡ ለመናቸው። እህት የገባችበትን ቦታ መክደንና ዕቃዎቹን መልሶ ማስተካከል ድምፅ የፈጠረ ከመሆኑም ሌላ ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶብኝ ነበር። ይህም በዓማፅያኑ ላይ ጥርጣሬ ሊፈጥርባቸው እንደሚችል ስለተሰማኝ ከራስ ፀጉሬ እስከ እግር ጥፍሬ በኃይል መንቀጥቀጥ ጀመርኩ። እንዲህ እየተንቀጠቀጥኩ በሩን እንዴት ልከፍት ነው? በልቤ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ለመረጋጋት እንዲረዳኝ ለመንኩት። ከዚያም በሩን ከፈትኩና እንደ ምንም ተረጋግቼ ሰላም አልኳቸው። ከዓማፅያኑ አንዱ ገፍትሮኝ ገባና ሰተት ብሎ ወደ መደርደሪያው በመሄድ ከፈተው፤ ዕቃዎቹንም ማተረማመስ ጀመረ። ምንም ነገር ሳያገኝ ሲቀር ማመን ከበደው። ከዚያም እሱና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሌሎቹን ክፍሎችና ከጣሪያው ሥር ያለውን ቦታ ፈተሹ። ግን አሁንም ምንም ነገር አላገኙም።

እውነት ደምቆ ማብራቱን ቀጠለ

ፖል፦ ለተወሰኑ ወራት ያህል ከባድ የምግብ እጥረት አጋጥሞን ነበር። ሆኖም መንፈሳዊ ምግባችን ሕይወታችንን አቆይቶልናል። የቤቴል የማለዳ አምልኮ ብቸኛው “ቁርሳችን” ነበር። ሁላችንም ይህ ፕሮግራም ለሚሰጠን ውስጣዊ ጥንካሬ አድናቆት ነበረን።

ምግብና ውኃ በማለቁ የተነሳ እኛም ሆንን ሌሎቹ ቅርንጫፍ ቢሮውን ለቀን ለመውጣት ከተገደድን እዚያ የተሸሸጉት ወንድሞች ሊገደሉ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ተአምራዊ በሚመስል ሁኔታ የሚያስፈልገንን ነገር አሟልቶልናል። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ከመስጠት በተጨማሪ ፍርሃታችንን እንድንቋቋም ረድቶናል።

ዓለም ይበልጥ በጨለማ በተዋጠ መጠን እውነት ይበልጥ ደምቆ ያበራ ነበር። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሕይወታቸውን ለማትረፍ በተደጋጋሚ መሸሽ አስፈልጓቸዋል። ሆኖም እምነታቸውና ድፍረታቸው አልተናጋም። አንዳንዶቹ በዚህ ጦርነት ማለፋቸው “ለታላቁ መከራ ልምምድ” እንደሚሆንላቸው ይናገሩ ነበር። ደፋር የጉባኤ ሽማግሌዎችና ወጣት ወንድሞች ቅድሚያውን ወስደው የእምነት አጋሮቻቸውን ለመርዳት ይንቀሳቀሱ ነበር። ወንድሞችና እህቶች ከመኖሪያቸው በሚፈናቀሉበት ወቅት እርስ በርስ ይረዳዱ፣ አዳዲስ የስብከት ክልሎችን ይከፍቱ እንዲሁም ጫካ ውስጥ ባዘጋጇቸው ጊዜያዊ የመሰብሰቢያ ቦታዎች ስብሰባ ያደርጉ ነበር። ተነዋዋጭ በሆነው በዚያ ሁኔታ ውስጥ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አንድ ላይ መሰብሰባቸውና መስበካቸው አበረታቷቸዋል፤ እንዲሁም እንዲጸኑ ረድቷቸዋል። የእርዳታ ቁሳቁሶችን በምናከፋፍልበት ወቅት ወንድሞች ከልብስ ይልቅ በዋነኝነት የሚጠይቁት የአገልግሎት ቦርሳ እንዲሰጣቸው ነበር፤ ይህን ማየታችን ልባችንን በጥልቅ ነክቶታል። በሐዘንና በፍርሃት የተዋጡ ሰዎች ምሥራቹን ያዳምጣሉ። የይሖዋ ምሥክሮች የነበራቸው ደስታና አዎንታዊ አመለካከት በጣም ያስገርማቸው ነበር። በእርግጥም ወንድሞቻችን በዚያ ጨለማ ውስጥ እንደ ብርሃን አብርተዋል! (ማቴ. 5:14-16) የወንድሞቻችን ቅንዓት ጨካኝ የነበሩ አንዳንድ ዓማፅያን እንኳ እውነትን እንዲቀበሉ አነሳስቷቸዋል።

ከወንድሞቻችን ለመለየት ብንገደድም ብርታት አግኝተናል

ፖል፦ አገሪቱን ለቀን ለመውጣት የተገደድንባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ሦስቴ ለአጭር ጊዜ ያህል፣ ሁለቴ ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ከአገሪቱ ወጥተን ለመቆየት ተገድደናል። አንዲት ሚስዮናዊት እንዲህ በማለት ስሜታችንን ጥሩ አድርጋ ገልጻዋለች፦ “ጊልያድ ሳለን ሙሉ ልባችንን ለአገልግሎት ምድባችን እንድንሰጥ ተምረናል፤ እኛም ያደረግነው ይህንኑ ነው። ስለዚህ እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ወንድሞቻችንን ትተን ስንሄድ ልባችንን የተወጋን ያህል ይሰማናል።” ደስ የሚለው፣ በአቅራቢያ ባሉ አገሮች ውስጥ ሆነን በላይቤሪያ ያሉ ወንድሞቻችንን መርዳታችንን ቀጥለናል።

ወደ ላይቤሪያ በደስታ ስንመለስ፣ 1997

አን፦ ግንቦት 1996 አራት ሆነን አስፈላጊ የቅርንጫፍ ቢሮ ሰነዶች በተጫኑበት የቤቴል መኪና ላይ ተሳፍረን ጉዞ ጀመርን። አሥራ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ የተሻለ ደህንነት ያለበት አካባቢ መሄድ ፈልገን ነበር። በዚያ ሰዓት፣ በነበርንበት አካባቢ ጥቃት ተሰነዘረ። በቁጣ የተሞሉ ዓማፅያን ወደ ላይ እየተኮሱ አስቆሙን፤ ሦስታችንን ጎትተው አወጡን፤ ከዚያም ፖል እዚያው መኪና ውስጥ እንዳለ እየነዱ ሄዱ። በድንጋጤ እዚያው ቆመን ቀረን። በድንገት ፖል ግንባሩ ደም በደም ሆኖ በሕዝቡ መካከል ሲመጣ አየን። ግራ ተጋብተን ስለነበር በጥይት የተመታ መስሎን ነበር። በኋላ ግን፣ በጥይት ተመቶ ቢሆን ኖሮ እየተራመደ አይመጣም ነበር ብለን አሰብን። ለካስ ከዓማፅያኑ አንዱ ከመኪናው ገፍትሮ ሲያስወጣው ጭንቅላቱን መቶት ነው። ደግነቱ ከባድ ጉዳት አልደረሰበትም።

በፍርሃት በተዋጡ ሰዎች የተሞላ የመከላከያ ሠራዊት መኪና በአቅራቢያችን ነበር። መኪናው ጥቅጥቅ ብሎ ሞልቶ ስለነበር በውጭ በኩል ተንጠላጠልን። ሹፌሩ በፍጥነት መንዳት ሲጀምር ልንወድቅ ተቃርበን ነበር። መኪናውን እንዲያቆም ለመንነው። እሱ ግን በጣም ፈርቶ ስለነበር ሊሰማን አልቻለም። እንደ ምንም ብለን ሳንወድቅ ደረስን። ሆኖም ከመዛላችንና ከመፍራታችን የተነሳ መላ ሰውነታችን እየተንቀጠቀጠ ነበር።

ፖል፦ ከለበስነው የቆሸሸና የተቀዳደደ ልብስ ውጭ ምንም ነገር አልነበረንም። ሆኖም እርስ በርስ ተያየንና በሕይወት በመትረፋችን ተገረምን። በጥይት ከተበሳሳ አሮጌ ሄሊኮፕተር አጠገብ ሜዳ ላይ አደርን። ሄሊኮፕተሩ በማግስቱ ወደ ሴራ ሊዮን ወሰደን። በሕይወት በመትረፋችን አመስጋኝ ብንሆንም የክርስቲያን ወንድሞቻችን ጉዳይ በጣም አስጨንቆን ነበር።

ያጋጠመንን ያልተጠበቀ ተፈታታኝ ሁኔታ ለመቋቋም ብርታት አግኝተናል

አን፦ በፍሪታውን፣ ሴራ ሊዮን ወደሚገኘው ቤቴል በሰላም ደረስን፤ እዚያም ወንድሞች በጣም ተንከባከቡን። ሆኖም በላይቤሪያ ያሳለፍነው ሁኔታ ፊቴ ላይ ድቅን እያለ ያስቸግረኝ ጀመር። ቀን ላይ፣ ሁልጊዜ ከፍተኛ ስጋት ይሰማኝ ነበር፤ በተጨማሪም አካባቢዬ ብዥ ይልብኛል፤ ሕልም ውስጥ ያለሁ ይመስለኛል። ሌሊት ላይ ደግሞ በላብ ተጠምቄ በፍርሃት እየተንቀጠቀጥኩ ብንን ብዬ እነቃለሁ። መተንፈስ ያቅተኛል። በዚህ ጊዜ ፖል እቅፍ አድርጎ ይጸልይልኛል። መንቀጥቀጤን እስካቆም ድረስ የመንግሥቱን መዝሙሮች እንዘምራለን። አእምሮዬን ልስት እንደተቃረብኩና በሚስዮናዊነት ማገልገሌን መቀጠል እንደማልችል ተሰምቶኝ ነበር።

ቀጥሎ የተከሰተውን ነገር መቼም ቢሆን አልረሳውም። በዚያው ሳምንት ሁለት መጽሔቶች ደረሱን። አንዱ የሰኔ 8, 1996 ንቁ! መጽሔት ነበር። መጽሔቱ “ድንገተኛ የሆነ የመሸበር ስሜትን መቋቋም” የሚል ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። መጽሔቱን ሳነብ ችግሬ ምን እንደሆነ ገባኝ። ሁለተኛው መጽሔት ደግሞ የግንቦት 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ሲሆን “ኃይል የሚያገኙት ከየት ነው?” የሚል ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። መጠበቂያ ግንቡ ላይ ክንፏ የተጎዳን ቢራቢሮ የሚያሳይ ሥዕል አለ። መጽሔቱ፣ ቢራቢሮዎች ክንፋቸው በጣም ተጎድቶም እንኳ መመገባቸውንና መብረራቸውን መቀጠል እንደሚችሉ ሁሉ እኛም ስሜታችን ቢጎዳም እንኳ በይሖዋ መንፈስ እገዛ ሌሎችን መርዳታችንን መቀጠል እንደምንችል ይናገራል። ይሖዋ በትክክለኛው ጊዜ የሰጠኝ ይህ መንፈሳዊ ምግብ ብርታት ሰጥቶኛል። (ማቴ. 24:45) ስለዚህ ጉዳይ የሚናገሩ ሌሎች ርዕሶችን መፈለጌና ሰብስቤ ማስቀመጤ በጣም ረድቶኛል። በመጥፎ ትዝታዎች ምክንያት የሚያድርብኝ የጭንቀት ስሜት ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጣ።

አዲሱን ምድባችንን ለመልመድ ብርታት አግኝተናል

ፖል፦ ሁኔታው ፈቅዶ ላይቤሪያ ወዳለው ቤታችን በተመለስን ቁጥር በጣም እንደሰት ነበር። በዚህ የአገልግሎት ምድብ እስከ 2004 መገባደጃ ድረስ ለ20 ዓመታት ገደማ ቆይተናል። በወቅቱ ጦርነቱ አብቅቶ ነበር። በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ ግንባታ ለማካሄድም ዕቅድ ተይዞ ነበር። ሆኖም በድንገት አዲስ ምድብ እንድንቀበል ተጠየቅን።

ይህ ለእኛ ትልቅ ፈተና ነበር። በጣም ከምንቀርባቸው መንፈሳዊ ቤተሰቦቻችን ተለይተን እንዴት ልንሆን ነው? ቤተሰቦቻችንን ትተን ወደ ጊልያድ በሄድንበት ወቅት ይሖዋ በፈለገው መንገድ እንዲጠቀምብን መፍቀድ ብዙ በረከቶችን እንደሚያስገኝ ተመልክተን ስለነበር አዲሱን ምድብ ተቀበልን። ከላይቤሪያ አቅራቢያ በምትገኘው በጋና እንድናገለግል ተመደብን።

አን፦ ላይቤሪያን ለቀን የወጣነው በጣም እያለቀስን ነው። ፍራንክ የተባለ ጥበበኛ የሆነ አረጋዊ ወንድም “እኛን ልትረሱን ይገባል” ሲለን በጣም ተገረምን። ከዚያም ምን ማለቱ እንደሆነ ሲያብራራ እንዲህ አለ፦ “መቼም ቢሆን እንደማትረሱን እናውቃለን። ግን ለአዲሱ ምድባችሁ ሙሉ ልባችሁን መስጠት ይኖርባችኋል። ምድቡን የሰጣችሁ ይሖዋ ነው፤ ስለዚህ እዚያ ባሉት ወንድሞችና እህቶች ላይ አተኩሩ።” ይህ ወንድም የሰጠን ምክር፣ ምንም በማንታወቅበት አዲስ አካባቢ ሕይወትን “ሀ” ብለን ለመጀመር ብርታት ሰጥቶናል።

ፖል፦ ይሁንና በጋና ያሉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ወዲያውኑ ቤተሰባችን ሆኑ። እዚያ በጣም ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። አዳዲሶቹ ጓደኞቻችን ከነበራቸው ጥንካሬና መንፈሳዊነት ብዙ ትምህርት አግኝተናል። ከዚያም ለ13 ዓመት ያህል በጋና ካገለገልን በኋላ ያልተጠበቀ የምድብ ለውጥ አጋጠመን። በኬንያ በሚገኘው የምሥራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ እንድናገለግል ተጠየቅን። ባለፉት ምድቦቻችን የነበሩት ጓደኞቻችን በጣም ቢናፍቁንም በኬንያ ካሉት ታማኝ ወንድሞች ጋር ወዲያውኑ ተቀራረብን። አሁንም ሰባኪዎች በጣም በሚያስፈልጉበት በዚህ ሰፊ ክልል ውስጥ እያገለገልን እንገኛለን።

በምሥራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ ካፈራናቸው አዳዲስ ጓደኞቻችን ጋር፣ 2023

ሕይወታችንን መለስ ብለን ስንቃኝ

አን፦ ባለፉት ዓመታት የሚያንቀጠቅጡና በፍርሃት የሚያርዱ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመውኛል። አደገኛና ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች በአካላችንም ሆነ በስሜታችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። እንዲህ ካለው ሁኔታ ተአምራዊ ጥበቃ አናገኝም። የተኩስ ድምፅ ስሰማ ሆዴን ይቆርጠኛል፤ እጄም ይደነዝዛል። ሆኖም ይሖዋ እኛን ለማበርታት ሲል ባደረጋቸው ዝግጅቶች በሙሉ መጠቀም እንዳለብኝ ተምሬያለሁ፤ ይህም የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን ድጋፍ ይጨምራል። በተጨማሪም ቋሚ መንፈሳዊ ልማድ ይዘን እስከቀጠልን ድረስ ይሖዋ በምድባችን እንድንቀጥል እንደሚረዳን ተመልክቻለሁ።

ፖል፦ አንዳንዶች “ምድባችሁን ትወዱታላችሁ?” ብለው ይጠይቁናል። ውብ የሆኑ አገሮችም እንኳ ሰላም ሊያጡና አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ከአገሩ ይበልጥ የምንወደው ምኑን ነው? ውድ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን፣ ቤተሰባችንን ነው። አስተዳደጋችንና ባሕላችን የተለያየ ቢሆንም እንኳ አስተሳሰባችን አንድ ዓይነት ነው። የተላክነው እነሱን ለማበረታታት እንደሆነ ተሰምቶን ነበር፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ያበረታቱን እነሱ ናቸው።

ወደ አዲስ አካባቢ በተዛወርን ቁጥር ተአምር የሆነውን የወንድማማች ማኅበራችንን እናያለን። የአንድ ጉባኤ ክፍል እስከሆንን ድረስ ቤተሰብ አለን፤ እንደ ቤታችን ይሰማናል። በይሖዋ መታመናችንን ከቀጠልን እሱ የሚያስፈልገንን ብርታት እንደሚሰጠን እርግጠኞች ነን።—ፊልጵ. 4:13

a በመጋቢት 15, 1973 መጠበቂያ ግንብ ላይ “አምላክንና ክርስቶስን አመሰግናለሁ” በሚል ርዕስ የወጣውን የጆን ቻሩክን የሕይወት ታሪክ ተመልከት።