በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 47

መዝሙር 103 እረኞች—ስጦታ የሆኑ ወንዶች

ወንድሞች—የጉባኤ ሽማግሌ ለመሆን እየተጣጣራችሁ ነው?

ወንድሞች—የጉባኤ ሽማግሌ ለመሆን እየተጣጣራችሁ ነው?

“የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣር ሰው መልካም ሥራን ይመኛል።”1 ጢሞ. 3:1

ዓላማ

አንድ ወንድም ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል የትኞቹን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ማሟላት ይጠበቅበታል?

1-2. ሽማግሌዎች የሚያከናውኑት “መልካም ሥራ” የትኞቹን ነገሮች ያካትታል?

 የጉባኤ አገልጋይ ሆነህ እያገለገልክ ከሆነ ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል የሚያስፈልጉትን ብቃቶች እያሟላህ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ይህን “መልካም ሥራ” ለመሥራት መጣጣር ትችል ይሆን?—1 ጢሞ. 3:1

2 የሽማግሌዎች ሥራ የትኞቹን ነገሮች ያካትታል? በስብከቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት ይካፈላሉ፤ ለማስተማርና እረኝነት ለማድረግ ተግተው ይሠራሉ፤ እንዲሁም በንግግራቸውና በመልካም ምሳሌነታቸው ጉባኤውን ያንጻሉ። በዚህም የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ በትጋት የሚሠሩትን ሽማግሌዎች “ስጦታ” በማለት ይጠራቸዋል።—ኤፌ. 4:8

3. አንድ ወንድም ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል ብቃቱን ማሟላት የሚችለው እንዴት ነው? (1 ጢሞቴዎስ 3:1-7፤ ቲቶ 1:5-9)

3 የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል ብቃቱን ማሟላት የምትችለው እንዴት ነው? ሽማግሌ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ማሟላት ሥራ ለመቀጠር የሚያስፈልገውን ብቃት ከማሟላት የተለየ ነው። ሥራ ለመቀጠር ካሰብክ ቀጣሪህ የሚፈልጋቸው ክህሎቶች እስካሉህ ድረስ ሥራውን ማግኘት ትችላለህ። በአንጻሩ ግን፣ ሽማግሌ ሆነህ ለመሾም ከፈለግክ የመስበክና የማስተማር ክህሎት ማዳበርህ ብቻውን በቂ አይደለም። በ1 ጢሞቴዎስ 3:1-7 እና በቲቶ 1:5-9 ላይ የተገለጹትን ከሽማግሌዎች የሚጠበቁ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ማሟላት ይኖርብሃል። (ጥቅሱን አንብብ።) ይህ ርዕስ ከሦስት ቁልፍ አቅጣጫዎች አንጻር ከሽማግሌዎች የሚጠበቁትን ብቃቶች ያብራራል፤ እነሱም በጉባኤ ውስጥም ሆነ ውጭ ባሉ ሰዎች ዘንድ መልካም ስም ማትረፍ፣ ጥሩ የቤተሰብ ራስ በመሆን ረገድ ምሳሌ መሆን እንዲሁም ጉባኤውን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆን ናቸው።

መልካም ስም ማትረፍ

4. “የማይነቀፍ” ሲባል ምን ማለት ነው?

4 ለሽምግልና ብቃቱን ለማሟላት ‘የማትነቀፍ’ መሆን ይኖርብሃል። ይህም ሲባል ማንም ሰው በመጥፎ ምግባር ስለማይከስህ በጉባኤ ውስጥ ጥሩ ስም ይኖርሃል ማለት ነው። ከዚህም ሌላ ‘በውጭ ባሉት ሰዎች ዘንድ በመልካም የተመሠከረልህ’ ልትሆን ይገባል። የማያምኑ ሰዎች ክርስቲያናዊ እምነትህን ሊተቹ ይችላሉ፤ ሆኖም በሐቀኝነትህ ወይም በምግባርህ ላይ ጥያቄ ለማንሳት የሚያበቃ መሠረት ሊኖራቸው አይገባም። (ዳን. 6:4, 5) ‘በጉባኤ ውስጥም ሆነ በውጭ ባሉ ሰዎች ዘንድ ጥሩ ስም አትርፌያለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

5. ‘ጥሩ የሆነውን ነገር እንደምትወድ’ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

5 ‘ጥሩ የሆነውን ነገር የምትወድ’ ከሆነ የሌሎችን ጥሩ ጎን ትመለከታለህ፤ እንዲሁም ላሏቸው መልካም ባሕርያት ታመሰግናቸዋለህ። ለሌሎች መልካም ማድረግም ያስደስትሃል፤ እንዲያውም ከሚጠበቅብህ አልፈህ ትሄዳለህ። (1 ተሰ. 2:8) ይህ ባሕርይ ለሽማግሌዎች በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሽማግሌዎች ለጉባኤው እረኝነት በማድረግና ሌሎች ኃላፊነቶቻቸውን በመወጣት ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ። (1 ጴጥ. 5:1-3) ያም ቢሆን ሌሎችን በማገልገል የምታገኘው ደስታ ከምትከፍለው ከማንኛውም መሥዋዕት በእጅጉ የላቀ ነው።—ሥራ 20:35

6. “እንግዳ ተቀባይ” መሆን የሚቻልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? (ዕብራውያን 13:2, 16፤ ሥዕሉንም ተመልከት።)

6 ለቅርብ ጓደኞችህ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መልካም ነገር የምታደርግ ከሆነ “እንግዳ ተቀባይ” መሆንህን ታሳያለህ። (1 ጴጥ. 4:9) አንድ ማመሣከሪያ እንግዳ ተቀባይ ስለሆነ ሰው ሲናገር “የቤቱም ሆነ የልቡ በር ለእንግዶች ክፍት መሆን አለበት” ይላል። ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘እንግዶችን በመቀበል ረገድ ምን ዓይነት ስም አትርፌያለሁ?’ (ዕብራውያን 13:2, 16ን አንብብ።) እንግዳ ተቀባይ የሆነ ሰው ያለውን ነገር ለሁሉም ዓይነት እንግዶች ያካፍላል፤ ይህም የተቸገሩ ሰዎችን እንዲሁም እንደ ወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የሕዝብ ተናጋሪዎች ያሉ ታታሪ የአምላክ አገልጋዮችን ያካትታል።—ዘፍ. 18:2-8፤ ምሳሌ 3:27፤ ሉቃስ 14:13, 14፤ ሥራ 16:15፤ ሮም 12:13

እንግዳ ተቀባይ የሆኑ ባልና ሚስት አንድን ተጓዥ የበላይ ተመልካችና ሚስቱን ቤታቸው ሲቀበሉ (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)


7. አንድ ሽማግሌ ‘ገንዘብ ወዳድ እንዳልሆነ’ ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው?

7 “ገንዘብ ወዳድ ያልሆነ።” ይህ ሲባል ትኩረትህ በቁሳዊ ነገሮች ላይ አይሆንም ማለት ነው። ሀብታምም ሆንክ ድሃ በሁሉም የሕይወትህ ዘርፎች ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ታስቀድማለህ። (ማቴ. 6:33) ጊዜህን፣ ጉልበትህንና ገንዘብህን የምታውለው ይሖዋን ለማምለክ፣ ቤተሰብህን ለመንከባከብ እንዲሁም ጉባኤውን ለማገልገል ነው። (ማቴ. 6:24፤ 1 ዮሐ. 2:15-17) ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ለገንዘብ ምን ዓይነት አመለካከት አለኝ? ባሉኝ መሠረታዊ ነገሮች እረካለሁ? ወይስ ትኩረቴ ያረፈው ገንዘብ በመሰብሰብና ንብረት በማካበት ላይ ነው?’—1 ጢሞ. 6:6, 17-19

8. ‘በልማዶችህ ልከኛ እንደሆንክ’ እና ‘ራስህን እንደምትገዛ’ ማሳየት የምትችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

8 ‘በልማዶችህ ልከኛ ከሆንክ’ እና ‘ራስህን የምትገዛ’ ከሆነ በሁሉም የሕይወትህ ዘርፎች ሚዛናዊ ትሆናለህ። ይህም ማለት ከምግብ፣ ከመጠጥ፣ ከአለባበስ፣ ከአጋጌጥ እንዲሁም ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ ልከኛ ትሆናለህ ማለት ነው። ለዓለም የአኗኗር ዘይቤ ባሪያ አይደለህም። (ሉቃስ 21:34፤ ያዕ. 4:4) የሚያበሳጭ ነገር በሚያጋጥምህ ጊዜም እንኳ ትረጋጋለህ። “ሰካራም” አትሆንም፤ ወይም ብዙ ይጠጣል የሚል ስም አታተርፍም። ‘አኗኗሬ በልማዶቼ ልከኛ እንደሆንኩና ራሴን እንደምገዛ ያሳያል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

9. “ጤናማ አስተሳሰብ ያለው” እና “ሥርዓታማ” ሲባል ምን ማለት ነው?

9 ‘ጤናማ አስተሳሰብ ካለህ’ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ማመዛዘን ትችላለህ። በእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ስለምታሰላስል ጥልቅ ግንዛቤና ማስተዋል አለህ። መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አትቸኩልም። ከዚህ ይልቅ የተሟላ መረጃ ያለህ መሆኑን ታረጋግጣለህ። (ምሳሌ 18:13) በመሆኑም የይሖዋን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ሚዛናዊ ውሳኔ ታደርጋለህ። “ሥርዓታማ” ሲባል የተደራጀና ሰዓት አክባሪ የሆነ ሰው ማለት ነው። እምነት የሚጣልብህና መመሪያ የምትከተል ሰው በመሆንህ ትታወቃለህ። እነዚህ ባሕርያት መልካም ስም እንድታተርፍ ይረዱሃል። አሁን ደግሞ ጥሩ የቤተሰብ ራስ በመሆን ረገድ ምሳሌ እንድትሆን የሚረዱህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች እንመልከት።

ጥሩ የቤተሰብ ራስ በመሆን ረገድ ምሳሌ መተው

10. አንድ ወንድም ‘የራሱን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ ማስተዳደር’ የሚችለው እንዴት ነው?

10 ባለትዳር ከሆንክና ሽማግሌ ለመሆን ብቃቱን ማሟላት የምትፈልግ ከሆነ ቤተሰብህ ያተረፈው ስም ብቃትህን ይነካዋል። በመሆኑም ‘የራስህን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ ማስተዳደር’ ይኖርብሃል። አፍቃሪና ኃላፊነት የሚሰማው የቤተሰብ ራስ በመሆን ልትታወቅ ይገባል። ይህም በሁሉም የአምልኳችን ገጽታዎች ከቤተሰብህ ጋር መካፈልን ይጨምራል። እንዲህ ማድረግ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “አንድ ሰው የራሱን ቤተሰብ እንዴት እንደሚያስተዳድር ካላወቀ የአምላክን ጉባኤ እንዴት ሊንከባከብ ይችላል?” ብሏል።—1 ጢሞ. 3:5

11-12. የአንድ ወንድም የቤተሰብ አባላት ምግባር የወንድምን ብቃት የሚነካው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

11 አባት ከሆንክ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችህ ‘ታዛዥና ቁም ነገረኛ ሊሆኑ’ ይገባል። እነሱን በፍቅር ማስተማርና ማሠልጠን ይኖርብሃል። እርግጥ ነው፣ እንደ ማንኛውም ልጅ መሳቃቸውና መጫወታቸው አይቀርም። ሆኖም በደንብ አድርገህ ስላሠለጠንካቸው ታዛዥ፣ ሰው አክባሪና ጨዋ ይሆናሉ። ከዚህም ሌላ ልጆችህ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲመሩ እንዲሁም እድገት አድርገው እንዲጠመቁ ለመርዳት አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ አለብህ።

12 “በስድነት ወይም በዓመፀኝነት የማይከሰሱ አማኝ የሆኑ ልጆች ያሉት።” በቤቱ ውስጥ ካሉት አማኝ የሆኑ ልጆች መካከል አንዱ ከባድ ኃጢአት ቢፈጽም ይህ የአባትየውን ብቃት የሚነካው እንዴት ነው? አባትየው ሥልጠና እና ተግሣጽ በመስጠት ረገድ ቸልተኛ ከነበረ ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል ብቁ ላይሆን ይችላል።—የጥቅምት 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 21 አን. 6-7⁠ን ተመልከት።

የቤተሰብ ራሶች ልጆቻቸው በተለያዩ የቅዱስ አገልግሎት ገጽታዎች እንዲካፈሉ በማድረግ ያሠለጥኗቸዋል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)


ጉባኤውን ማገልገል

13. “ምክንያታዊ” መሆንህን እና ‘በራስህ ሐሳብ የምትመራ’ አለመሆንህን ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

13 ግሩም ክርስቲያናዊ ባሕርያትን የሚያንጸባርቁ ወንድሞች ለጉባኤው ውድ ሀብት ናቸው። “ምክንያታዊ” የሆነ ሰው ሰላም ያሰፍናል። ምክንያታዊ በመሆንህ መታወቅ የምትፈልግ ከሆነ ሌሎች ሲናገሩ አዳምጥ፤ እንዲሁም አመለካከታቸውን ለማስተናገድ ፈቃደኛ ሁን። ለምሳሌ በሽማግሌዎች ስብሰባ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ወይም መሠረታዊ ሥርዓት እስካልተጣሰ ድረስ የብዙሃኑን ውሳኔ ለመደገፍ ፈቃደኛ ትሆናለህ? ‘በራስህ ሐሳብ የምትመራ’ ልትሆን አይገባም ሲባል ‘እኔ ያልኩት ካልሆነ’ ብለህ ድርቅ አትልም ማለት ነው። ብዙ አማካሪዎች መኖራቸው ያለውን ጥቅም ትገነዘባለህ። (ዘፍ. 13:8, 9፤ ምሳሌ 15:22) አትጣላም’  ወይም “ግልፍተኛ” አትሆንም። ሻካራ ወይም ብስጩ ከመሆን ይልቅ ገርና ዘዴኛ ትሆናለህ። ሰላማዊ ሰው ስለሆንክ ውጥረት በሚፈጥሩ ሁኔታዎች ውስጥም ሰላም ለመፍጠር ቅድሚያውን ትወስዳለህ። (ያዕ. 3:17, 18) ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ቃላት መጠቀምህ የተቃዋሚዎችን ልብ ሳይቀር ሊያለሰልስ ይችላል።—መሳ. 8:1-3፤ ምሳሌ 20:3፤ 25:15፤ ማቴ. 5:23, 24

14. “አዲስ ክርስቲያን አይሁን” ሲባል ምን ማለት ነው? “ታማኝ” ሲባልስ?

14 የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚሾም ወንድም ‘አዲስ ክርስቲያን ሊሆን’ አይገባም። ከተጠመቅክ ብዙ ዓመት መቆጠር ባያስፈልገውም የጎለመስክ ክርስቲያን እንድትሆን የተወሰነ ጊዜ ሊያልፍ ይገባል። ሽማግሌ ሆነህ ከመሾምህ በፊት ልክ እንደ ኢየሱስ ትሑት እንደሆንክና ይሖዋ ኃላፊነት እስኪሰጥህ ድረስ በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ እንደሆንክ ማሳየት አለብህ። (ማቴ. 20:23፤ ፊልጵ. 2:5-8) ይሖዋን የሙጥኝ በማለትና የጽድቅ መሥፈርቶቹን በጥብቅ በመከተል እንዲሁም በድርጅቱ በኩል የምታገኘውን መመሪያ በመታዘዝ “ታማኝ” መሆንህን ታሳያለህ።—1 ጢሞ. 4:15

15. አንድ ሽማግሌ ከመድረክ ሲያስተምር አንደበተ ርቱዕ መሆን ይጠበቅበታል? አብራራ።

15 ቅዱሳን መጻሕፍት የበላይ ተመልካች የሚሆን ሰው “የማስተማር ብቃት ያለው” ሊሆን እንደሚገባ በግልጽ ይናገራሉ። ታዲያ ይህ ሲባል ከመድረክ ስታስተምር አንደበተ ርቱዕ መሆን አለብህ ማለት ነው? አይደለም። ብቃት ያላቸው በርካታ ሽማግሌዎች ከመድረክ ሲያስተምሩ አንደበተ ርቱዕ ባይሆኑም እንኳ በአገልግሎትና በእረኝነት ጉብኝት ወቅት ውጤታማ በሆነ መንገድ ያስተምራሉ። (ከ1 ቆሮንቶስ 12:28, 29 እና ኤፌሶን 4:11 ጋር አወዳድር።) ያም ቢሆን የማስተማር ክህሎትህን ለማሻሻል ምንጊዜም ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። በዚህ ረገድ ይበልጥ ውጤታማ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

16. ይበልጥ ውጤታማ የሆነ አስተማሪ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

16 “የታመነውን ቃል በጥብቅ የሚከተል።” የማስተማር ችሎታህን ለማሻሻል ከፈለግክ ከመድረክ የምታስተምረው ትምህርትም ሆነ በግል የምትሰጠው ምክር በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስን እንዲሁም ጽሑፎቻችንን በትጋት አጥና። (ምሳሌ 15:28፤ 16:23) የአምላክን ቃል ስታጠና የጥቅሱን ትክክለኛ ማብራሪያ እንዲሁም ጥቅሱን እንዴት ልትጠቀምበት እንደምትችል ለማስተዋል ሞክር። እንዲሁም በምታስተምርበት ጊዜ የአድማጮችህን ልብ ለመንካት ጥረት አድርግ። ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎች ምክር እንዲሰጡህ በመጠየቅና ምክሩን ተግባራዊ በማድረግ የማስተማር ችሎታህን ማሻሻል ትችላለህ። (1 ጢሞ. 5:17) ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን “ማበረታታት” መቻል ይኖርባቸዋል፤ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ መምከር አልፎ ተርፎም “መውቀስ” ይጠበቅባቸዋል። ያም ሆነ ይህ፣ ምንጊዜም ደግ ሊሆኑ ይገባል። ገርና አፍቃሪ ከሆንክ እንዲሁም ትምህርትህ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ከሆነ ውጤታማ ትሆናለህ፤ ምክንያቱም ታላቅ አስተማሪ የሆነውን የኢየሱስን ምሳሌ ትከተላለህ።—ማቴ. 11:28-30፤ 2 ጢሞ. 2:24

አንድ የጉባኤ አገልጋይ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅሞ ማስተማር ስለሚቻልበት መንገድ ተሞክሮ ካለው ሽማግሌ ይማራል። በተጨማሪም የጉባኤ አገልጋዩ ለጉባኤው የሚያቀርበውን ንግግር መስተዋት ፊት ቆሞ ይለማመዳል (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)


መጣጣርህን ቀጥል

17. (ሀ) የጉባኤ አገልጋዮች መጣጣራቸውን እንዲቀጥሉ ምን ሊረዳቸው ይችላል? (ለ) ሽማግሌዎች ወንድሞችን ለመሾም በማሰብ ብቃታቸውን በሚገመግሙበት ጊዜ ምን ማስታወስ ይኖርባቸዋል? (“ ሌሎችን ስትገመግሙ ልካችሁን እወቁ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

17 አንዳንድ የጉባኤ አገልጋዮች ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል የቀረቡትን ብቃቶች ከተመለከቱ በኋላ ፈጽሞ ብቃቱን ማሟላት እንደማይችሉ ይሰማቸው ይሆናል። ሆኖም ይሖዋም ሆነ ድርጅቱ እነዚህን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ እንድታንጸባርቅ እንደማይጠብቁብህ አስታውስ። (1 ጴጥ. 2:21) ደግሞም እነዚህን ብቃቶች እንድታሟላ የሚረዳህ ኃያል የሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ነው። (ፊልጵ. 2:13) ማሻሻል የምትፈልገው አንድ ባሕርይ አለ? ከሆነ፣ ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ ጸልይ። ምርምር አድርግ፤ እንዲሁም አንድን ሽማግሌ እንዴት ማሻሻል እንደምትችል ምክር እንዲሰጥህ ጠይቀው።

18. ሁሉም የጉባኤ አገልጋዮች ምን እንዲያደርጉ ይበረታታሉ?

18 በአሁኑ ጊዜ ሽማግሌ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙትን ወንድሞች ጨምሮ ሁላችንም በዚህ ርዕስ ላይ የተብራሩትን ባሕርያት ለማዳበር ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥል። (ፊልጵ. 3:16) በአሁኑ ወቅት የጉባኤ አገልጋይ ነህ? ከሆነ እድገት ማድረግህን ቀጥል! ይሖዋ እሱንም ሆነ ጉባኤውን ይበልጥ ማገልገል እንድትችል እንዲያሠለጥንህና እንዲቀርጽህ በጸሎት ጠይቀው። (ኢሳ. 64:8) ይሖዋ በሽምግልና ለማገልገል የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ለማሟላት የምታደርገውን ጥረት አብዝቶ እንዲባርክልህ እንመኛለን።

መዝሙር 101 በአንድነት አብሮ መሥራት