በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 46

መዝሙር 49 የይሖዋን ልብ ማስደሰት

ወንድሞች—የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን እየተጣጣራችሁ ነው?

ወንድሞች—የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን እየተጣጣራችሁ ነው?

“ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”ሥራ 20:35

ዓላማ

የተጠመቁ ወንድሞች የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን እንዲጣጣሩና ብቃቱን እንዲያሟሉ ማበረታታት።

1. ሐዋርያው ጳውሎስ ለጉባኤ አገልጋዮች ምን አመለካከት ነበረው?

 የጉባኤ አገልጋዮች በጉባኤ ውስጥ ወሳኝ ሥራ ያከናውናሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለእነዚህ ታማኝ ወንድሞች አድናቆት ነበረው። ለምሳሌ በፊልጵስዩስ ለነበሩት ክርስቲያኖች ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት ሽማግሌዎቹን ብቻ ሳይሆን የጉባኤ አገልጋዮቹንም ለይቶ በመጥቀስ ሰላምታ አቅርቦላቸዋል።—ፊልጵ. 1:1

2. ሉዊስ የተባለ ወንድም የጉባኤ አገልጋይ በመሆኑ ምን ይሰማዋል?

2 በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ በርካታ የተጠመቁ ወንድሞች የጉባኤ አገልጋዮች በመሆናቸው በጣም ደስተኞች ናቸው። ለምሳሌ ዴቨን የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ የተሾመው በ18 ዓመቱ ነው። ሉዊስ የተባለ ወንድም ደግሞ አገልጋይ የሆነው በ50ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እያለ ነው። ሉዊስ ስሜቱን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በተለይ ወንድሞችና እህቶች ስላሳዩኝ ጥልቅ ፍቅር ሳስብ የጉባኤ አገልጋይ ሆኜ እነሱን ማገልገል በመቻሌ ትልቅ ክብር ይሰማኛል።” ሌሎች በርካታ የጉባኤ አገልጋዮችም እንዲህ ይሰማቸዋል።

3. የትኞቹን ጥያቄዎች እንመልሳለን?

3 ገና የጉባኤ አገልጋይ ሆነህ ያልተሾምክ የተጠመቅክ ወንድም ከሆንክ ይህን ግብ ማውጣት ትችል ይሆን? እንዲህ ለማድረግ ምን ሊያነሳሳህ ይችላል? የትኞቹን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ማሟላትስ ይጠበቅብሃል? በዚህ ርዕስ ውስጥ እነዚህን ጥያቄዎች እንመልሳለን። በመጀመሪያ ግን፣ የጉባኤ አገልጋዮች በጉባኤ ውስጥ ያላቸው ሚና ምን እንደሆነ እንመልከት።

የጉባኤ አገልጋዮች ሚና ምንድን ነው?

4. የጉባኤ አገልጋዮች ሚና ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

4 የጉባኤ አገልጋይ የሚባለው በጉባኤ ውስጥ የተለያዩ ጠቃሚ ሥራዎችን በማከናወን ሽማግሌዎችን እንዲረዳ በመንፈስ ቅዱስ የተሾመ የተጠመቀ ወንድም ነው። የአንዳንድ የጉባኤ አገልጋዮች ሥራ አስፋፊዎች ለአገልግሎታቸው በቂ ክልልና ጽሑፍ እንዲያገኙ ማድረግ ነው። ሌሎች ደግሞ የስብሰባ አዳራሹን በማጽዳቱና በመጠገኑ ሥራ ይካፈላሉ። ከዚህም ሌላ የጉባኤ አገልጋዮች በጉባኤ ስብሰባዎች ወቅት አስተናጋጅ ሆነው ይመደባሉ፤ እንዲሁም በድምፅና በቪዲዮ መሣሪያዎች ላይ ይሠራሉ። የጉባኤ አገልጋዮች እንደዚህ የመሰሉ ሥራዎችን በመሥራት በጉባኤያቸው ውስጥ ተግባራዊ እገዛ ያበረክታሉ። ሆኖም የሚያከናውኑት ሥራ ምንም ይሁን ምን በዋነኝነት መንፈሳዊ ሰዎች መሆን ይጠበቅባቸዋል። ይሖዋን ይወዳሉ፤ በጽድቅ መሥፈርቶቹም ይመራሉ። እንዲሁም ለክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጥልቅ ፍቅር አላቸው። (ማቴ. 22:37-39) ታዲያ አንድ የተጠመቀ ወንድም የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን መጣጣር የሚችለው እንዴት ነው?

የጉባኤ አገልጋዮች ራሳቸውን ሳይቆጥቡ ሌሎችን በማገልገል የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላሉ (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)


5. የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን መጣጣር የምትችለው እንዴት ነው?

5 መጽሐፍ ቅዱስ የጉባኤ አገልጋይ ሆነው የሚሾሙ ወንድሞች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ብቃቶችን ይዘረዝራል። (1 ጢሞ. 3:8-10, 12, 13) ስለ እነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች በማጥናት ከዚያም ብቃቶቹን ለማሟላት ተግተህ በመሥራት ይህን መብት ለማግኘት መጣጣር ትችላለህ። በቅድሚያ ግን፣ የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የተነሳሳህበትን ምክንያት በጥንቃቄ ማጤን ይኖርብሃል።

ለመጣጣር የሚያነሳሳህ ምንድን ነው?

6. ወንድሞችህንና እህቶችህን ለመርዳት ስትል ማንኛውንም ሥራ እንድታከናውን የሚያነሳሳህ ምን ሊሆን ይገባል? (ማቴዎስ 20:28፤ ሥዕሉንም ተመልከት።)

6 ከሁሉ የላቀ ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው ለአባቱና ለሰዎች ባለው ፍቅር ተነሳስቶ ነበር። ይህ ፍቅር ሌሎችን ለመርዳት ሲል ተግቶ እንዲሠራና ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን እንዲያከናውን አነሳስቶታል። (ማቴዎስ 20:28ን አንብብ፤ ዮሐ. 13:5, 14, 15) አንተም የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የሚያነሳሳህ ፍቅር ከሆነ ይሖዋ ይባርክሃል፤ እንዲሁም ግብህ ላይ ለመድረስ ብቃቱን እንድታሟላ ይረዳሃል።—1 ቆሮ. 16:14፤ 1 ጴጥ. 5:5

ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱ የክብር ቦታ ለማግኘት ከመፈለግ ይልቅ ሌሎችን በትሕትና ማገልገል እንዳለባቸው ምሳሌ በመሆን አስተምሯቸዋል (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)


7. አንድ ወንድም ከሥልጣን ጥመኝነት መራቅ ያለበት ለምንድን ነው?

7 በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ራሳቸውን ከፍ የሚያደርጉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ይከበራሉ። በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ግን ሁኔታው ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። እንደ ኢየሱስ ፍቅር ያለው ወንድም ሥልጣን ወይም ከፍ ያለ ቦታ ለማግኘት አይመኝም። እንዲህ ያለው የሥልጣን ጥመኛ ሰው በጉባኤው ውስጥ ቢሾም የይሖዋን ውድ በጎች ለመንከባከብ የሚያስፈልጉ አንዳንድ ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን ለመሥራት ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል። እንዲህ ያሉት ሥራዎች እንደማይመጥኑት ይሰማው ይሆናል። (ዮሐ. 10:12) ይሖዋ በኩራት ወይም በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ መብት ለማግኘት የሚጣጣርን ሰው አይባርክም።—1 ቆሮ. 10:24, 33፤ 13:4, 5

8. ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ምን ምክር ሰጥቷቸዋል?

8 የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆችም እንኳ ተገቢ ባልሆነ ምክንያት ተነሳስተው መብት ለማግኘት የሞከሩበት ጊዜ አለ። የኢየሱስ ሐዋርያት የሆኑት ያዕቆብና ዮሐንስ ምን እንዳደረጉ ልብ በል። በመንግሥቱ ውስጥ ለየት ያለ ቦታ እንዲሰጣቸው ኢየሱስን ጠይቀውት ነበር። ኢየሱስ ይህን በመመኘታቸው አላመሰገናቸውም። ከዚህ ይልቅ ለ12ቱም ሐዋርያት እንዲህ አላቸው፦ “ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋያችሁ ሊሆን ይገባል፤ እንዲሁም ከመካከላችሁ ፊተኛ መሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ሊሆን ይገባል።” (ማር. 10:35-37, 43, 44) በትክክለኛው የልብ ዝንባሌ ተነሳስተው፣ ማለትም ሌሎችን ለማገልገል ብለው መብት ለማግኘት የሚጣጣሩ ወንድሞች ለጉባኤው በረከት ይሆናሉ።—1 ተሰ. 2:8

ለመጣጣር ያለህን ፍላጎት ማሳደግ የምትችለው እንዴት ነው?

9. ለመጣጣር ያለህን ፍላጎት ማሳደግ የምትችለው እንዴት ነው?

9 ይሖዋን እንደምትወደውና ሌሎችን ማገልገል እንደምትፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም። ያም ቢሆን የጉባኤ አገልጋይ መሆን ተጨማሪ ሥራዎችን ማከናወን የሚጠይቅ ከመሆኑ አንጻር ይህን ለማድረግ ፍላጎት ላይኖርህ ይችላል። ታዲያ ሌሎችን ለማገልገል ያለህን ፍላጎት ማሳደግ የምትችለው እንዴት ነው? ወንድሞችህንና እህቶችህን ማገልገል ስለሚያስገኘው ደስታ ለማሰብ ሞክር። ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሏል። (ሥራ 20:35) እሱም ቢሆን በሕይወቱ ይህንኑ አድርጓል። ሌሎችን በማገልገል እውነተኛ ደስታ አግኝቷል፤ አንተም እንዲህ ያለውን ደስታ ማግኘት ትችላለህ።

10. ኢየሱስ ሌሎችን ማገልገል እንደሚያስደስተው ያሳየው እንዴት ነው? (ማርቆስ 6:31-34)

10 ኢየሱስ ሌሎችን ማገልገል ያስደስተው እንደነበር የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። (ማርቆስ 6:31-34ን አንብብ።) በአንድ ወቅት እሱና ሐዋርያቱ ስለደከማቸው አረፍ ለማለት ገለል ወዳለ ስፍራ እየሄዱ ነበር። ሆኖም ብዙ ሰዎች ኢየሱስ እንዲያስተምራቸው ስለፈለጉ ቀድመዋቸው ደረሱ። ኢየሱስ “አላስተምራችሁም” ማለት ይችል ነበር። ደግሞም እሱና ሐዋርያቱ “ምግብ ለመብላት እንኳ ፋታ አላገኙም” ነበር። ወይም ደግሞ ኢየሱስ አንድ ወይም ሁለት ነገር ብቻ ካስተማራቸው በኋላ ሊያሰናብታቸው ይችል ነበር። ሆኖም ፍቅር ስለነበረው ‘ብዙ ነገር ያስተምራቸው ጀመር።’ እንዲያውም ‘ሰዓቱ እስኪገፋ’ ድረስ እነሱን ማስተማሩን ቀጥሏል። (ማር. 6:35) ይህን ያደረገው ግዴታ ስለነበረበት ሳይሆን ‘በጣም ስላዘነላቸው’ ነው። ስለሚወዳቸው ሊያስተምራቸው ፈልጓል። ሌሎችን ማገልገል ለኢየሱስ ታላቅ ደስታ ሰጥቶታል።

11. ኢየሱስ ለአድማጮቹ ተግባራዊ እርዳታ የሰጣቸው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

11 ኢየሱስ ሕዝቡን በማስተማር ብቻ አልተወሰነም። አካላዊ ፍላጎታቸውንም አሟልቶላቸዋል። በተአምራዊ መንገድ ምግቡን ካበዛ በኋላ ለሕዝቡ እንዲያከፋፍሉ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። (ማር. 6:41) በዚህ መንገድ ደቀ መዛሙርቱን ሌሎችን ማገልገል የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አስተምሯቸዋል። በተጨማሪም የጉባኤ አገልጋዮች እንደሚያከናውኗቸው ያሉ ተግባራዊ አገልግሎቶችም አስፈላጊ እንደሆኑ አሳይቷቸዋል። ሐዋርያቱ ‘ሁሉም በልተው እስኪጠግቡ’ ድረስ ከኢየሱስ ጋር በዚህ ምግብ የማከፋፈል ሥራ በመካፈላቸው ምን ያህል ተደስተው ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። (ማር. 6:42) ደግሞም ኢየሱስ ከራሱ ፍላጎት ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት ያስቀደመው በዚህ ወቅት ብቻ አይደለም። በምድራዊ ሕይወቱ በሙሉ ሰዎችን ያገለግል ነበር። (ማቴ. 4:23፤ 8:16) ኢየሱስ ሌሎችን በማስተማር እንዲሁም እነሱን ለመንከባከብ ሲል በትሕትና በመሥራት ደስታ አግኝቷል። አንተም ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንፈስ ተነሳስተህ የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን ስትጣጣር ታላቅ ደስታ እንደምታገኝ ምንም ጥያቄ የለውም።

ለይሖዋ ያላችሁ ፍቅር እንዲሁም ሌሎችን ለማገልገል ያላችሁ ፍላጎት ጉባኤውን በቻላችሁት መንገድ ሁሉ ለማገልገል ያነሳሳችኋል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት) a


12. ማናችንም ብንሆን በጉባኤ ውስጥ ማበርከት የምንችለው አስተዋጽኦ እንደሌለ ሊሰማን የማይገባው ለምንድን ነው?

12 ለየት ያለ ችሎታ እንደሌለህ የሚሰማህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ጉባኤውን የሚጠቅሙ ባሕርያትና ችሎታዎች እንዳሉህ ምንም ጥያቄ የለውም። ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 12:12-30 ላይ የሰጠውን ማብራሪያ በጸሎት ታግዘህ ብታስብበት ሊጠቅምህ ይችላል። ጳውሎስ የተናገራቸው ቃላት አንተን ጨምሮ ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች በጉባኤው ውስጥ አስፈላጊና ጠቃሚ ሚና እንዳላቸው በግልጽ ያሳያሉ። የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት በአሁኑ ጊዜ የማታሟላ ከሆነ በሐዘን ልትዋጥ አይገባም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋንና ወንድሞችህን ለማገልገል የምትችለውን ሁሉ ለማድረግ ጥረት አድርግ። ሽማግሌዎች ማንኛውንም ኃላፊነት የሚሰጡህ ችሎታህን ከግምት አስገብተው እንደሆነ እርግጠኛ ሁን።—ሮም 12:4-8

13. ከተሾሙ ወንዶች ከሚጠበቁት ከአብዛኞቹ ብቃቶች ጋር በተያያዘ እውነታው ምንድን ነው?

13 የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን እንድትጣጣር የሚያነሳሳ ሌላም ምክንያት አለ፦ አብዛኞቹ ብቃቶች ከሁሉም ክርስቲያኖች የሚጠበቁ ናቸው። ሁሉም ክርስቲያኖች ወደ ይሖዋ መቅረብ፣ በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ማጣጣም እንዲሁም በክርስቲያናዊ አኗኗር ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ይሁንና አንድ ወንድም የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የትኞቹን ነገሮች ማድረግ ይችላል?

መጣጣር የምትችለው እንዴት ነው?

14. ‘ቁም ነገረኛ’ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? (1 ጢሞቴዎስ 3:8-10, 12)

14 ከዚህ በመቀጠል በ1 ጢሞቴዎስ 3:8-10, 12 ላይ ከሚገኙት ብቃቶች መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት። (ጥቅሱን አንብብ።) የጉባኤ አገልጋዮች “ቁም ነገረኞች” ሊሆኑ ይገባል። “ቁም ነገረኛ” የሚለው አገላለጽ “አክብሮት የሚገባው፣” “ሥርዓታማ” ወይም “የተከበረ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ይህ ሲባል ግን ፈጽሞ መሳቅ ወይም መቀለድ የለብህም ማለት አይደለም። (መክ. 3:1, 4) ሆኖም የተሰጡህን ኃላፊነቶች በሙሉ በቁም ነገር ልትይዝ ይገባል። እምነት የሚጣልብህ በመሆን ረገድ መልካም ስም ካለህ የጉባኤውን አክብሮት ታተርፋለህ።

15. “በሁለት ምላስ የማይናገሩ” እና “አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የማይስገበገቡ” የሚሉት አገላለጾች ምን ያመለክታሉ?

15 “በሁለት ምላስ የማይናገሩ” የሚለው አገላለጽ ሐቀኛና ተአማኒ መሆን እንዳለብህ ያመለክታል። ቃልህን ትጠብቃለህ፤ እንዲሁም ሌሎችን አታታልልም። (ምሳሌ 3:32) “አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የማይስገበገቡ” የሚለው አገላለጽ በንግድና በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ረገድ ሐቀኛ መሆን እንዳለብህ ያመለክታል። ከእምነት አጋሮችህ ጋር ያለህን መልካም ግንኙነት ገንዘብ ለማግኘት አላግባብ አትጠቀምበትም።

16. (ሀ) “ብዙ የወይን ጠጅ የማይጠጡ” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል? (ለ) “ንጹሕ ሕሊና” ያለው ሲባል ምን ማለት ነው?

16 “ብዙ የወይን ጠጅ የማይጠጡ” የሚለው አገላለጽ ከመጠን በላይ መጠጣት ወይም ጠጪ የሚል ስም ማትረፍ እንደሌለብህ ያመለክታል። “ንጹሕ ሕሊና” ያለው ሲባል ደግሞ በይሖዋ መሥፈርቶች መመራት እንዳለብህ ያመለክታል። ፍጹም ባትሆንም እንኳ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና በመመሥረት የሚገኘው ሰላም አለህ።

17. ወንድሞች ‘ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚፈተኑት’ እንዴት ነው? (1 ጢሞቴዎስ 3:10፤ ሥዕሉንም ተመልከት።)

17 “ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ . . . ይፈተኑ” የሚለው አገላለጽ ኃላፊነት ለመሸከም ብቁ መሆንህን አስቀድመህ ማስመሥከር እንዳለብህ ያሳያል። በመሆኑም ሽማግሌዎች አንድ ሥራ ሲሰጡህ የእነሱንም ሆነ የድርጅቱን መመሪያ በጥንቃቄ ተከትለህ ሥራውን አከናውን። ሥራው ምን እንደሚጠይቅ እንዲሁም እስከ መቼ ማለቅ እንዳለበት በትክክል ለማወቅ ጥረት አድርግ። እያንዳንዱን ኃላፊነትህን በትጋት የምትወጣ ከሆነ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖችም ጥሩ እድገት እያደረግክ መሆኑን አስተውለው ማድነቃቸው አይቀርም። ሽማግሌዎች፣ የተጠመቁ ወንድሞችን ለማሠልጠን ንቁ ሁኑ። (1 ጢሞቴዎስ 3:10ን አንብብ።) በጉባኤያችሁ ውስጥ በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኙ የተጠመቁ ወንድሞች አሉ? ምሳሌ የሚሆን የግል ጥናት ልማድ አላቸው? በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው ሐሳብ ይሰጣሉ? በአገልግሎትስ አዘውትረው ይካፈላሉ? ከሆነ ዕድሜያቸውንና ሁኔታቸውን የሚመጥን ኃላፊነት ስጧቸው። በዚህ መንገድ እነዚህ ወጣት ወንድሞች ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ መፈተን ትችላላችሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ አካባቢ ሲደርሱ የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን ብቃቱን ማሟላታቸው አይቀርም።

ሽማግሌዎች ለተጠመቁ ወንድሞች ሥራ በመስጠት ‘ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ መፈተን’ ይችላሉ (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)


18. “ከክስ ነፃ” መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

18 “ከክስ ነፃ” መሆን ሲባል ከባድ ኃጢአት ፈጽሟል የሚል መሠረት ያለው ክስ ሊነሳብህ አይገባም ማለት ነው። እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች የሐሰት ክስ ሊሰነዘርባቸው ይችላል። ኢየሱስም በሐሰት ተከሶ ነበር፤ ተከታዮቹም ተመሳሳይ ነገር እንደሚያጋጥማቸው ትንቢት ተናግሯል። (ዮሐ. 15:20) ይሁን እንጂ እንደ ኢየሱስ ንጹሕ ምግባር ካለህ በጉባኤው ዘንድ ጥሩ ስም ታተርፋለህ።—ማቴ. 11:19

19. “የአንዲት ሚስት ባል” መሆን ምን ያካትታል?

19 “የአንዲት ሚስት ባል።” ባለትዳር ከሆንክ ይሖዋ ለትዳር ያወጣውን የመጀመሪያ መሥፈርት ማክበር ይኖርብሃል፤ ይሖዋ በትዳር ያጣመረው አንድን ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ነው። (ማቴ. 19:3-9) አንድ ክርስቲያን የፆታ ብልግና ሊፈጽም እንደማይገባ የታወቀ ነው። (ዕብ. 13:4) ግን የሚጠበቅበት ይህ ብቻ አይደለም። ለሌሎች ሴቶች ተገቢ ያልሆነ ትኩረት ፈጽሞ ባለመስጠት ለሚስትህ ታማኝ ልትሆን ይገባል።—ኢዮብ 31:1

20. አንድ ወንድም ቤተሰቡን ‘በተገቢው ሁኔታ ማስተዳደር’ የሚችለው እንዴት ነው?

20 “ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳድሩ።” የቤተሰብ ራስ ከሆንክ ኃላፊነትህን በቁም ነገር ልትመለከተው ይገባል። አዘውትረህ የቤተሰብ አምልኮ አድርግ። ከእያንዳንዱ የቤተሰብህ አባል ጋር የምትችለውን ያህል አዘውትረህ በአገልግሎት ተካፈል። ልጆችህ ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና እንዲመሠርቱ እርዳቸው። (ኤፌ. 6:4) ቤተሰቡን የሚንከባከብ ወንድ ጉባኤውንም መንከባከብ እንደሚችል ያሳያል።—ከ1 ጢሞቴዎስ 3:5 ጋር አወዳድር።

21. በአሁኑ ወቅት የጉባኤ አገልጋይ ካልሆናችሁ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

21 ወንድሞች፣ በአሁኑ ወቅት የጉባኤ አገልጋይ ሆናችሁ እያገለገላችሁ ካልሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚገኙትን ሐሳቦች በጸሎት ታግዛችሁ አስቡባቸው። ከጉባኤ አገልጋዮች ስለሚጠበቁት ብቃቶች አጥኑ፤ እነዚህን ብቃቶች ለማሟላትም ተግታችሁ ሥሩ። ይሖዋን እንዲሁም ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን ምን ያህል እንደምትወዷቸው አስቡ። እነሱን ለማገልገል ያላችሁን ፍላጎትም አጠናክሩ። (1 ጴጥ. 4:8, 10) መንፈሳዊ ቤተሰባችሁን በማገልገል የሚገኘውን ደስታ አጣጥሙ። የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ አትረፍርፎ እንዲባርክላችሁ እንመኛለን!—ፊልጵ. 2:13

መዝሙር 17 “እፈልጋለሁ”

a የሥዕሉ መግለጫ፦ በስተ ግራ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በትሕትና እያገለገለ ነው፤ በስተ ቀኝ፣ አንድ የጉባኤ አገልጋይ በጉባኤ ውስጥ ያለን አንድ አረጋዊ ወንድም እየረዳ ነው።