በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥናትን ቋሚ ለማድረግ የሚረዱ ሐሳቦች

ጥናትን ቋሚ ለማድረግ የሚረዱ ሐሳቦች

የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህን ቋሚ እና አስደሳች ማድረግ ያታግልሃል? ሁላችንም አልፎ አልፎ እንደዚያ ይሰማናል። ሆኖም በቋሚነት የምናደርጋቸውን ሌሎች ነገሮች ለማሰብ ሞክር፤ ለምሳሌ ገላችንን እንታጠባለን። መታጠብ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል፤ ሆኖም ከታጠብን በኋላ መንፈሳችን ይታደሳል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትም እንደዚሁ ነው፤ ‘በቃሉ አማካኝነት በውኃ መታጠብ’ መንፈስን ያድሳል። (ኤፌ. 5:26) በዚህ ረገድ ሊረዱን የሚችሉ አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮችን እንመልከት፦

  • ፕሮግራም አውጣ። የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አንድ ክርስቲያን ችላ ሊላቸው ከማይገቡ ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች’ መካከል አንዱ ነው። (ፊልጵ. 1:10) ፕሮግራምህን መከተል ቀላል እንዲሆንልህ በቀላሉ በሚታይበት ቦታ ምናልባትም በግድግዳህ ወይም በፍሪጅህ በር ላይ ለምን አትለጥፈውም? ወይም ደግሞ ለጥናት የመደብከው ሰዓት ሲቃረብ እንዲያስታውስህ በኤሌክትሮኒክ መሣሪያህ ላይ አላርም ልትሞላ ትችላለህ።

  • ሁኔታህን ከግምት አስገባ። ትኩረትህን ሰብስበህ ረዘም ያለ ሰዓት መቆየት ትችላለህ? ወይስ ሰዓቱን ከፋፍለህ አጠር አጠር ላሉ ጊዜያት ብታጠና ይቀልሃል? ያለህበትን ሁኔታ ከማንም በተሻለ የምታውቀው አንተ ነህ። የጥናት ፕሮግራምህን ከሁኔታህ ጋር ለማስማማት ሞክር። ለጥናት የመደብከው ሰዓት ሲደርስ ተነሳሽነት ካጣህ ለአሥር ደቂቃ ብቻ ለማጥናት ለምን አትሞክርም? ጥቂት ደቂቃም ቢሆን ማጥናት ምንም ካለማጥናት በእጅጉ የተሻለ ነው። ደግሞም አንዴ ከጀመርክ በኋላ ለመቀጠል ልትነሳሳ ትችላለህ።—ፊልጵ. 2:13

  • ርዕሰ ጉዳዩን አስቀድመህ ምረጥ። ለማጥናት ከተቀመጥክ በኋላ ‘ምን ላጥና?’ ብለህ የምታስብ ከሆነ ‘ጊዜህን በተሻለ መንገድ እየተጠቀምክበት’ ላይሆን ይችላል። (ኤፌ. 5:16) ለማጥናት የምትፈልጋቸውን ጽሑፎች ወይም ርዕሰ ጉዳዮች የያዘ ዝርዝር ለምን አታዘጋጅም? አንድ ጥያቄ በተፈጠረብህ ቁጥር ዝርዝሩ ላይ አስፍረው። በተጨማሪም በእያንዳንዱ የጥናት ፕሮግራምህ መጨረሻ ላይ በዝርዝሩ ውስጥ ልታካትታቸው የምትችላቸውን ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ልትጨምር ትችላለህ።

  • እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ አድርግ። በፕሮግራምህ ላይ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ ለማድረግ ዝግጁ ሁን፤ ለምሳሌ ለጥናት በመደብከው ጊዜ ርዝመት ወይም በምታጠናው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለውጥ ማድረግ ትችላለህ። ዋናው ነገር መቼ፣ ለምን ያህል ሰዓት ወይም ምን አጠናህ የሚለው ሳይሆን ጥናትህ ቋሚ መሆኑ ነው።

ቋሚ የጥናት ፕሮግራም ካለን በእጅጉ እንጠቀማለን። ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንቀርባለን፤ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎችን ማድረግ እንችላለን፤ እንዲሁም መንፈሳችን ይታደሳል።—ኢያሱ 1:8