በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ስለ ኢየሱስ የልጅነት ሕይወት የሚናገሩት የማቴዎስና የሉቃስ ዘገባዎች የሚለያዩት ለምንድን ነው?

ማቴዎስ ያሰፈረው ስለ ኢየሱስ ልደትና የልጅነት ሕይወት የሚናገረው ዘገባ፣ ስለዚሁ ጉዳይ ከሚናገረው የሉቃስ ዘገባ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የተለየ ነው፤ ይህ የሆነው ጸሐፊዎቹ ክንውኖቹን የዘገቡት ከተለያየ አቅጣጫ ስለሆነ ነው።

የማቴዎስ ዘገባ ትኩረት ያደረገው ከዮሴፍ ጋር በተያያዙ ክንውኖች ላይ ነው። ዘገባው ዮሴፍ የማርያምን መፀነስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያውቅ ምን እንደተሰማው፣ አንድ መልአክ በሕልም ተገልጦ ስለ ሁኔታው እንዳብራራለትና ዮሴፍ ከዚያ በኋላ ምን እርምጃ እንደወሰደ ይገልጻል። (ማቴ. 1:19-25) በተጨማሪም የማቴዎስ ዘገባ አንድ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ ወደ ግብፅ እንዲሄድ እንደነገረው፣ ዮሴፍ ቤተሰቡን ይዞ ወደዚያ እንደሄደ፣ በሕልሙ አንድ መልአክ ተገልጦለት ወደ እስራኤል እንዲመለስ እንደነገረው፣ በዚህም መሠረት ወደ እስራኤል እንደተመለሰና ቤተሰቡን ይዞ በናዝሬት መኖር እንደጀመረ ይናገራል። (ማቴ. 2:13, 14, 19-23) በማቴዎስ ወንጌል የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች ላይ የዮሴፍ ስም አሥር ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን የማርያም ስም ግን የተጠቀሰው አራት ጊዜ ብቻ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የሉቃስ ዘገባ ይበልጥ የሚያተኩረው በማርያም ላይ ነው። ዘገባው መልአኩ ገብርኤል ማርያምን እንዳነጋገራትና ማርያም ዘመዷን ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ እንደሄደች ይናገራል፤ እንዲሁም ማርያም ይሖዋን በማወደስ የተናገረችውን ሐሳብ ይዟል። (ሉቃስ 1:26-56) በተጨማሪም ሉቃስ፣ ኢየሱስ ወደፊት የሚቀበለውን መከራ በተመለከተ ስምዖን ለማርያም የተናገረውን ሐሳብ ዘግቧል። ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ቤተሰቡ ወደ ቤተ መቅደሱ ስላደረገው ጉዞ በሚናገረው ዘገባ ላይም እንኳ ሉቃስ የጠቀሰው የዮሴፍን ሳይሆን የማርያምን ንግግር ነው። አክሎም ሉቃስ እነዚህ ነገሮች በማርያም ላይ ምን ስሜት እንዳሳደሩ ገልጿል። (ሉቃስ 2:19, 34, 35, 48, 51) በሉቃስ ወንጌል የመጀመሪያዎቹ ሁለት ምዕራፎች ውስጥ የማርያም ስም 12 ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን የዮሴፍ ስም ግን የተጠቀሰው ሦስት ጊዜ ብቻ ነው። ከዚህ ማየት እንደሚቻለው፣ የማቴዎስ ዘገባ ዮሴፍን ባሳሰቡት ጉዳዮችና ባከናወናቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ሲያተኩር የሉቃስ ዘገባ ደግሞ ማርያምን ባጋጠሟት ሁኔታዎችና ባደረገቻቸው ነገሮች ላይ ያተኩራል።

ሁለቱ የወንጌል ጸሐፊዎች ያሰፈሯቸው የትውልድ ሐረግ ዘገባዎችም የተለያዩ ናቸው። ማቴዎስ የዘረዘረው የዮሴፍን የትውልድ ሐረግ መስመር ተከትሎ ሲሆን የዮሴፍ የማደጎ ልጅ የሆነው ኢየሱስ በሕጋዊ መንገድ የዳዊት ዙፋን ወራሽ እንደሆነ ያሳያል። እንዴት? ምክንያቱም ዮሴፍ በዳዊት ልጅ በሰለሞን በኩል የንጉሥ ዳዊት ዘር ነው። (ማቴ. 1:6, 16) ሉቃስ የዘረዘረው ደግሞ የማርያምን የትውልድ ሐረግ ሲሆን ኢየሱስ በውልደት ማለትም “በሥጋ” የዳዊት ዙፋን ወራሽ እንደሆነ ያሳያል። (ሮም 1:3) እንዴት? ምክንያቱም ማርያም በዳዊት ልጅ በናታን በኩል የንጉሥ ዳዊት ዘር ናት። (ሉቃስ 3:31) ይሁንና ማርያም የሄሊ ልጅ ሆና ሳለ ሉቃስ በትውልድ ሐረግ ዘገባው ላይ የሄሊ ልጅ እንደሆነች ያልጠቀሰው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በአብዛኛው የትውልድ ሐረግ መስመር የሚዘረዘረው በወንዱ በኩል ነው። በመሆኑም ሉቃስ፣ ዮሴፍን የሄሊ ልጅ እንደሆነ አድርጎ የገለጸው ዮሴፍ የሄሊ አማች በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ አንባቢዎቹ መረዳት አያዳግታቸውም።—ሉቃስ 3:23

ማቴዎስም ሆነ ሉቃስ ያሰፈሯቸው የትውልድ ሐረግ ዘገባዎች ኢየሱስ በትንቢት የተነገረለት መሲሕ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ያረጋግጣሉ። እንዲያውም የኢየሱስ የትውልድ ሐረግ ዝርዝር በሰፊው የሚታወቅ ከመሆኑ የተነሳ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም እንኳ በትክክለኛነቱ ላይ ጥያቄ ሊያነሱ አልቻሉም። ማቴዎስም ሆነ ሉቃስ ያሰፈሯቸው የትውልድ ሐረግ ዘገባዎች በዛሬው ጊዜ ለእምነታችን መሠረት ከሆኑት ነገሮች መካከል ከመሆናቸውም ሌላ አምላክ ቃል የገባቸው ነገሮች አስተማማኝ መሆናቸውን ያሳያሉ።